የሻምበል ሲስተር አስቴር አያና አጭር የሕይወት ታሪክ ከልጃቸው ከያፌት አስራት – ነሐሴ ፲፪, ፳፻፲፭ (August 18, 2023)

የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ ዳግ ሃመርሾልድ ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የላኩት ቴሌግራም:- “ስሟን ገና ያላወቅነው አንዲት ኢትዮጵያዊት ነርስ አንድ አሜሪካዊ መኮንን በአንድ ጂፕ መኪና ውስጥ ተይዞ ሲደበደብ ብቻዋንና ባዶ እጅዋን ልታድነው በሙሉ ልበኝነት ሞክራ ሳይሆንላት ቢቀር ኮንጎዎቹ አሜሪካኑን ይዘዉት ሲሄዱ ሰፈራቸው ድርስ ተከትላ ሔደች፡፡ እዚያም በጥይት ሊገድሏት ቢያስፈራሯትም ተመልሳ ወሬውን ለኢትዮጵያውያኑ ነግራ ሶስቱን አሜሪካውያን አድነዋቸዋል፡፡”  ንጉሡ በመልሳችው ለሲስተር የላኩት መልእክት ” ሥራሽ  ላይ ሆነሽ በፈጸምሸው መልካም ተግባር በጣም ተደስተናል፡፡ ስለ መልካም ሥራሽና ስለ መልካም አደራጎትሽ በጣም እናመሰግንሻለን” ብለው ነበር፡፡ ሲስተርም  በትህትና ሲመልሱ  “ላደርገው የሚገባኝን አገልግሎት በመፈጸሜ የግርማዊነትዎ የምስጋና ቴሌግራም ስለ ደረሰኝ ፤ አነስተኛ አገልጋይዎን በምስጋና ላሰበኝ ግርማዊነትዎ እድሜ በመለመን መሬት እስማለሁ” በማለት ነበር ፡፡