ኢትዮጵያ የብዝሀ ብሄረሰቦችና ማህበረሰቦች ሀገር ናት፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦችና ማህበረሰቦች አንደየአካባቢያቸው የተፈጥሮና የአየር ንብረት አንዲሁም በአንድ በኩል በተናጠል በሌላ በኩል ደግሞ እርስ በርስ ባደረጓቸው መስተጋብሮች የፈጠሯቸው ብዝሀ ባህላዊ እሴቶች አሏቸው፡፡ እነዚህ ብዝሀ ባህላዊ እሴቶች ለፈጠሯቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እየሰጡት ካሉ ፖለቲካዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታዎች በዘለለ በአገር አቀፍ ደረጃ አንድ የፖለቲካ እንዲሁም ተደጋጋፊ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ በመፍጠሩና ጠንካራ ሀገረ መንግስት በመገንባቱ ረገድ የበኩላቸውን የማይታለፍ ድርሻ እንደሚወጡ ይታመናል፡፡ በዚህ የባህል አምድ ስር ስለ ባህል በአጠቃላይ፤ የባህል ምንነት ጠቀሜታና አተገባበር ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ብሄረሰቦችና ማህበረሰቦች እንዲሁም አለም አቀፍ ተሞክሮ አንጻር ሃሳቦችን እየሰደርን የምናቀርብ ይሆናል፡፡ ጽሁፉ ተከታታይነት ባለው መልክ የሚቀርብና ሁሎቹንም የባህል ዘውጎችና ዘርፎች የሚዳስስ ሲሆን፤ ለዛሬ የባህልን ትርጓሜ፤ አለም አቀፍና አገር አቀፍ አተያይ በማሳያነት በማቅረብ አሃዱ ብለናል።