የኢትዮጵያ ጊዜያዊ ሁኔታና የመንፈሳዊ ፖለቲካ ራዕይ ከፈንታሁን ጥሩነህ (ዋሺንግተን ዲ.ሲ)

ሰኔ ወር 2010 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ምድር የሚካሄደው የለውጥ ነፋስ አዲስና አስገራሚ ነው። በእግዚአብሔር ማመን ተስፋ አስቆርጧቸው የነበሩ ሁሉ ተገርመው የዶክተር አቢይ አህመድ አሊ በፖለቲካው መስክ መነሳት ላይ “የእግዚአብሔር እጅ አለበት” እስኪሉ ድረስ ሁኔታው ማራኪ ሆኖ ይገኛል። በምዕራቡና በምሥራቁ ዓለም የፖለቲካ ንድፈ-ሃሳቦችና ጽንሰ-ሃሳቦች የተራቀቁ ኢትዮጵያውያን ምሁራን በሁኔታው በመደመም የሚሉት አጥተው ዝምታን የመረጡበት ጊዜ ነው። አንዳንድ ዜጎች ደግሞ ይህ ክስተት ጊዜያዊ ቅዠት እንጂ እውን አይደለም በማለት ያላቸውን ግራሞት ይገልጻሉ። እኔ በበኩሌ በዶክተር አህመድ አሊ የሚመራው አዲሱ ፖለቲካ ሲጠበቅ የነበረው የእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት ያስከተለው መሆኑን አምናለሁ። ይህ እምነቴ ደግሞ ይህን መጣጥፍ እንድጽፍ ምክንያት ሆኖኛል።