ሌስላውን ዘረፋ – አጭር የምርምር ማስታወሻ

ሌስላውን ዘረፋ – አጭር የምርምር ማስታወሻ

ዳንኤል አበራ

(ኤድሞንተን – ካናዳ)

ሰኔ ፳፲፯ . (June 2025)

ሌስላው በ1961 የዛሬ ስድሳ ዐምስት ዐመት የዐማርኛ የገደል ማሚቶ ጥምር ቃላት የተሰኘ መጣጥፍ አበርክቶልናል። ይህን ቀጣይ መጣጥፍ “ዘረፋ” ያልኩበት ምክንያት ዘረፈ – ቀጠለ፤ ዘርፍ “ቅጣይ” በሚለው ፍቺ መልኩ ሲኾን ዘረፈ፣ ነጠቀም ይኾናል። ለመንጠቁ ግን ሌስላው በሕይወት ቢኖር ነበር።

ነፍሰ-ሔር ፕሮፌሰር ዎልፍ ሌስላው (Professor Wolf Leslau) የሴማዊ  ቋንቋዎች ጥናት አባት ሊሰኝ የሚገባው፣ በዘር አይሁዳዊ በዜግነት ግን አሜሪካዊ ምሁር ነው። ዘር ከልጓም ይስባል እንዲሉ ኾኖ፣ ሌስላው ሲያልፍ ጥናቶቹን ያወረሰው ለተማረበት ፈረንሳይ፣ ላጠናበት ኢትዮጵያ፣ ለሠራበት አሜሪካ ሳይኾን ለእስራኤል ነው??። ሌስላው የቀ.ኃ.ሥ ሽልማት አሸናፊ ኾኖ በዘመኑ 8 ሺ የኢትዮጵያ ብር እና ሰርተፊኬት ከንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እጅ ተቀብሏል።

በ2023 (፳፲፮ ዓ.ም) በታተመ አንድ ጥናት የዐማርኛ ነጠላ ቃላት ስድስት ሚሊዮን ደርሷል። የዐማርኛ ቋት ስድስት ሚሊዮን ቃላት የኖረው እኛ ተናጋሪዎቹ በተለምዶ ቁብ የማንላቸው እነ “እንጃ”፣ “ኧረ”፣ “ጎሽ”፣ “እንቶ ፈንቶ” ተደማምረው ነው።

አንዳንድ የዐማርኛ ቃላት የፊደል መጠናቸው አነስተኛ ቢኾንም አንድምታ ትርጉም ላይ ያሳደሩት ጫና ግን ኹለቴ እንድናስብ መንገድ አመልካች ኾነው አግኝቻቸዋለሁ።

እንደ አስረጅም የ “ና” እና “ወይም” ለውጥን እንይ፤ ፕሮፌሰር ማዕምረሰናይ (1) ስለሰምና ወርቅ ሲያስረዱ ሰምና ወርቅ sem ena werq ፣ ሰም ወይም ወርቅ sem weyim werq ልዩነታቸው በዐይን አንሶ የሚታየው የ “ና” እና “ወይም” ጥልቅ ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ አመላካቾች ናቸው፤ ሰምና ወርቅ በ “ና” አብሮ መቆጠርና አንድ አካል አንድ አምሳል መኾንና ሰም ወይም ወርቅ በ”ወይም” መጣመር እንደ ኹለት ተፃራሪ ኹነት መታየቱን አመልክተዋል።

የፖላንዷ ተመራማሪ ዶ/ር ማግዳሊናም (2)  የ”ብዬ” እና “እንደ” መስተዋድድነት መተካካት በ”ይመጣል ብዬ አስባለሁ” እና “እንደሚመጣ አስባለሁ” የአንድን ኹነት የመምጣትን እርግጠኘነት objectivity እና የግል ፍላጎት subjectivity አመላካቾች ኾነው ተገኝተዋል።

ፍሬ ነገሩ በዐማርኛ ምርምር ቃላት መጠናቸው ቢያንስም ግልጋሎታቸው እንቶ ፈንቶ ቢኾንም ግልጋሎታቸውን ማጥናት ይበል ማሰኘቱን ለማሳየት ነው።

የዛሬውን መጣጥፍ የቋንቋው ተናጋሪዎች በአሉታዊ ትርጉማቸው የተነሣ ከጉዳይ የማይጣፉ ቃላትን መዘከር ነው። ሌስላው echo words የገደል ማሚቶ ቃላት ብሏቸዋል።

ሌስላው አብዛኞቹን የገደል ማሚቶ ጥምር ቃላት ከመዝገበ ቃላት የተወሰኑትን ደግሞ ከሰው ጠይቆ 80 ያህል የሰበሰበ ሲኾን፤ ከነዚህ ሰማንያው 25ቱ (መከረ ዘከረ። ሰጥ ለጥ አለ። ሰለሄ መለሄ። ሰላላ መላላ። በግድም በውድም። ብቅ ጥልቅ አለ። ወዘተርፈ።) አኹንም በሥራ ላይ ያሉ፣ ሠርክ የምንጠቀማቸው ኾነው አግኝቻቸዋለሁ።

አፌ ላይ የመጡትን 11 (ሰለሀ መለሄ። እልም ጭልም አለ። ቁራጭ ፍላጭ። ቆራጭ ፈላጭ። ፈላጭ ቆራጭ። በውድም በግድም። ብቅ እንቅ። ቢጣ ቢሎ። አገም ጠቀም። እጥር ምጥን። እፍን ሽፍን አደረገ። ውጥንቅጥ(?)። የባጥ የቆጡን።) ያክል የገደል ማሚቶ ጥምር ቃላት አክዬበት ከሰማንያ ቢያንስ 35ቱን አኹንም የምንጠቀምባቸው ኾነው አግኝቻቸዋለሁ። 55 ያኽሉ ታሪክ ኾነው ቀርተዋል ማለት ነው።

ሌላው አስደናቂው ነገር የገደል ማሚቶው ጥምር ቃላት በአንድ አንድ ፊደል ብቻ መለያየታቸው እና አንዱ ቃል ኹለተኛውን ቃል ወይንም ኹለተኛው ቃል የመጀመሪያውን ቃል ትርጉም አጎላማሽ ኾነው መገኘታቸው ነው።

ሌስላው እነዚህ ጥምር ቃላት “ቧልተኝነትን፤ አሉታዊነትን፤ ፅልመትን፤ ራሮትን፤ ርባና ቢስነትን” አመልካች እንደኾኑና፣ ያ ግን ሁሉም የገደል ማሚቶ ጥምር ቃላት አሉታዊነትን አመልካች እንዳልኾኑ (ሰለሄ መለሄ) ዘግቧል። ለምሳሌ የባህሩ ዘርጋው የዐማርኛ መዝገበ ቃላት ሰለሄ መለሄን የተጠቀመበትን አውድ ብናይ “ገንፎ በቅቤ ሰለሄ መለሄ” ብሎታል።

የገደል ማሚቶው ጥምር ቃላት በቋንቋው እርባታ ሰዋስው በኹለት ረዳት ግሶች “አለ” እና “አደረገ” አማካይነት ወደ እርባታ እና ሐረግ ምሥረታ የመግባት ጠባያቸው ዐማርኛን በገለፃ እና በአጎላማሽነት ውበት እንዲላበስ አድርገውታል።

የእነዚህን ጥምር ቃላት ቁጥር እና የተገኙበት አውድ ከመዝገበ ቃላት ለማየት እንዲኹም ቁጥራቸውን ለመጨመር በቴክኖሎጂ የታገዘን ፍለጋ አስቸጋሪ ያደረገው የቃላቱ ጥምር መኾን ለቀላል ፍለጋ እንዳይመቹ አድርጓቸዋል።

  የሌስላው ስብስብ አሁን በማገልገል ያሉ እና የዳንኤል ስብስብ
1 ለውዝ ገውዝ
2 ለጥ ሰጥ አለ ለጥ ሰጥ አለ
3 ሊል ዘሊል
4 ላጢ መላጢ
5 ልቅም ጥርቅም አደረገ
6 መለስ ቀለስ አደረገ መለስ ቀለስ አደረገ
7 መከረ ዘከረ መከረ ዘከረ
8 ሙጥር ጉጥር አለ
9 ሰለል መለል አለ
10 ሰለል ሸለል አለ
11 ሰለም ዘለም አለ
12 ሰሊጥ ፈሊጥ
13 ሰላሄ መላሄ ሰለሄ መለሄ
14 ሰላላ መላላ ሰላላ መላላ
15 ሳብ ረገብ አለ ሳብ ረገብ አለ
16 ስልም ጭልም አለ እልም ጭልም አለ
17 ቀውላላ ገውላላ
18 ቁርጥ ፍርጥ አደረገ
19 ቈራጭ ፈላጭ ቁራጭ ፍላጭ፣ ቆራጭ ፈላጭ፣ ፈላጭ ቆራጭ
20 ቈራጭ ፈራጅ
21 ቅልጥጥ ብልጥጥ አደረገ
22 ቅምዝምዝ ጥምዝምዝ
23 ቅንጥ ምንጥ አለ
24 ቅጥን ምጥን አለ
25 ቅጭጭ ብጭጭ አለ
26 በግድም በውድም በውድም በግድም
27 ብርቅ ድንቅ ቢጣ ቢሎ
28 ብቅ ጥልቅ አለ ብቅ እንቅ
29 ብጥስ ቅንጥስ አለ ብቅ ጥልቅ አለ
30 ተለል መለል አለ ብጥስ ቅንጥስ አለ
31 ተላላ ዘላላ
32 ተላሌ ዘላሌ
33 ተለሌ ዘለሌ
34 ትልክስ ምልክስ አለ
35  ትርኪ ምርኪ ትርኪ ምርኪ
36 አለል ዘለል አለ
37 አለቀ ደቀቀ አለቀ ደቀቀ
38 እልም ድርግም አለ እልም ድርግም አለ
39 አሰሱን ገሰሱን አሰሱን ገሰሱን
40 አራራ መራራ አራራ መራራ
41 አርቲ ቡርቲ አርቲ ቡርቲ
42 አሻር ባሸር አሸር ባሸር
43 አባጣ ጐርባጣ አባጣ ጐርባጣ
44 አባጣ ጐባጣ
45 አንጃ ግራንጃ አንጃ ግራንጃ
46 አከል መሰል
47 አዝሃ መዝሃ አገም ጠቀም
48 አጀብ ወጀብ
49 አጣ ነጣ አጣ ነጣ
50 እልም ስልም አለ እልም ስልም አለ
51 እርር ምርር አለ
52 እርር ክርር አለ
53 እርግፍ ዝርግፍ አለ
54 እርጥ ዝርጥ አለ
55 እቅ እንቅ አደረገ
56 እንቶ ፈንቶ
57 እጥብ ግጥብ አደረገ
58 እጥን ምጥን እጥር ምጥን
59 እፍን ጭፍን አደረገ እፍን ሽፍን አደረገ
60 ኩሪ ሙሪ
61 ወለም ዘለም አለ ወለም ዘለም አለ
62 ወራሽ ቈራሽ ዋዛ ፈዛዛ
63 ዋዛ ፈዛዛ ውጥንቅጥ?
64 ዘል መንዘል አለ
65 ዘርጋፋ መንጋፋ
66 ዘጥ ረጥ አለ
67 የቆጡን የባጡን አለ የባጥ የቆጡን አለ
68 የኰራ የደራ የኰራ የደራ
69 ደቀቀ ረቀቀ
70 ገውዝ ለውዝ
71 ጋረ ጣረ
72 ግዛ ምዛ
73 ግጥጥ ምጥጥ አደረገ
74 ጣረ ጋረ ጣረ ጋረ
75 ጣጣ ፈንጣጣ
76 ጭልጥ ቅልጥ አለ
77 ጨባጣ ጐባጣ
78 ፍንድስ ግንድስ አለ
79 ፍንጥር ምንጥር አለ ፍዝዝ ቅዝዝ አለ
80 ፍዝዝ ቅዝዝ አለ የፈናጅራ የፈናጅርቱ

 

Source: Leslau, Wolf. 1961. Echowords in Ethiosemitic. Annals D’Ethiopie. 4: 205-238

(1) Mennasemay, Maimire. 2021. Qiné Hermeneutics and Ethiopian Critical Theory)

(2) Krzyżnowska, Magdalina. 2024. Epistemic Modality in Amharic. Köln: Rüdiger Köppe Verlag)

ማሳሰቢያ፦ 

የዚህ ጽሑፍ ተከታይ ዳብሮና የጥምር ቃላቶቹ አገባብና ትርጉም ተካቶበት በክፍል ሁለት እንደሚቀርብ ለአንባብያን እንገልጻለን።

Summary

This short note revisited and celebrated Wolf Leslau’s 1961 study on Amharic echo words. In the study, Leslau identified 80 composites, pair echo words that described and exaggerated the events, arti burtiinto fento “nothing fancy nothing serious nothing important”. Currently, 25 of those 80 echo words words are in use and I added my 11 collection of echo words. It would be interesting how these echo words fit into the 6 million words of Amharic.

የረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል አበራ አጭር የስራ ተሞክሮ፤

አቶ ዳንኤል አበራ (ከአልበርታ ዩኒቨርሲቲ MSc እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቋንቋ ሳይንስ የMA ዲግሪ ያላቸው) በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቋንቋ ትምህርት ክፍል የቀድሞ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ኮሌጆች ያስተማሩ ናቸው። በተጨማሪም በካናዳ ፣ ኤድሞንተን በሚገኘው የአልበርታ ዩኒቨርሲቲ፣ በረዳት ክፍለ ጊዜ አስተማሪነት ሰርተዋል።

አቶ ዳንኤል በአባይ-ሰሃራዊ፣ በኦሞቲክና ሴማዊ ቋንቋዎች (Nilo-Saharan, Omotic and Semitic languages) በኢትዮጵያና በሱዳን የመስክ ተሞክሮ ያላቸው ሲሆን ለምሁራዊ አስተዋፅኦዋቸው ልዩ ልዩ ሽልማቶችን እና የገንዘብ ድጎማዎችን አግኝተዋል። በአሁኑ ጊዜ አቶ ዳንኤል የሚኖሩት በኤድሞንተን ፣ ካናዳ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ የሚያውሉት ምርምር በማድረግና የምርምር ውጤቶቻቸውን ለሌሎች በማካፈል ላይ ነው ። አቶ ዳንኤል ተመራማሪና ጸሐፊ እንደመሆናቸው እስከ አሁን ድረስ ከ20 በላይ የመጽሐፍ ምዕራፎችንና ጥናታዊ መጣጥፎችን እንዲሁም አስር መጻሕፍትን አሳትመዋል፤ ከአንደኛው በስተቀር ሁሉም መጽሐፎቻቸው በአማዞን የማከፋፈያ ድርጅት በኩል ማግኘት ይቻላል። ምሳሌዎችን እና እንቆቅልሾችን በተመለከተ በአማርኛ የተሰሩ ሁለት መጽሃፎቻቸው በ Aethiopica መጽሔት (2015 ዓ ም) በተመራማሪዎች ተቃኝተዋል። በቅርቡ የታተመው  “A Frequency Dictionary of Written Amharic” የተሰኘው መፅሐፋቸው በኢትዮጵያና በተቀረው የዓለም ክፍል ከፍተኛ ተቀባይነትን አግኝቷል።

Leave a Reply

Scroll to Top

Discover more from ሰምና ወርቅ

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading