ወይዘሮ ሲልቪያ ፓንከርስት እንግሊዛዊቷ የኢትዮጵያ ጀግና፤ ኪዳኔ ዓለማየሁ ፤ ሰኔ 18 ቀን 2011 ዓ/ም

ይህ አጭር ጽሑፍ (1) የሚያተኩረው፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን፤ ወለተ ክርስቶስ ተብላ በተሰየመችው፤ የዓለም ስሟ ሲልቪያ ፓንከርስት በሆነው፤ ኢትዮጵያ በፋሺሽቶች በተወረረችበት ጊዜ፤ ከዚያም በሁዋላ ሌሎች ቅኝ ገዢዎች ሊቀራመቷት በቋመጡበት ዘመን በሚያስደንቅ ጀግንነት 20 ዓመት ሙሉ በታገለችው፤ በተከበረች፤ ወይዘሮ የሕይወት ታሪክ ላይ ነው።

ሲልቪያ ፓንከርስት፤ እ.ኤ.አ በ1882 እንግሊዝ ሐገር ተወልዳ፤ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው፤ እ.ኤ.አ መስከረም 27 ቀን 1960 አዲስ አበባ ነበር። አስከሬኗ የተቀበረውም፤ ወለተ ክርስቶስ ተሰኝታ፤ እንደ ሌሎች ታላላቅ አርበኞች፤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፤ ልዑል አልጋ ወራሽ አስፋ ወሰንና ሌሎች ክቡራን በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ነበር። የ50ኛው ዓመት መታሰቢያዋ መስከረም 17 ቀን 2003 ዓ/ም በቅድስት ሥላሴ ቤ/ክ ተከብሯል።