የሻምበል ሲስተር አስቴር አያና አጭር የሕይወት ታሪክ ከልጃቸው ከያፌት አስራት – ነሐሴ ፲፪, ፳፻፲፭ (August 18, 2023)

 

በማስቀደም ከብዙ የህይወት ፈተናዎች በኋላ ተርፌ ይህቺን የህይወት ታሪክ ለማበርከት በመብቃቴ እግዚአብሄርን አመሰግነዋለሁ፡፡ የወላጅ እናቴ የህይወት ታሪክ በመሆኑም በዘመኔ ውስጥ አከናወንኳቸው ከምላቸው ነገሮቸ መካከል ከፍተኛውን ስፍራ ሰጥቼዋለሁ፡፡

ሻመበሏ ይኽንን እና ያንን አከናውነዋል ማለት ከመጀመሬ በማስቀደም በዓለማችን እንዲሁም በራሴው ሕይወት በከፊሉ ብርሃን ፤ በከፊሉ ደግሞ ጨለማ የነበሩ ዓመታትን ለማጤን ሞከርኩ፡፡

በዚሁም የሚያበረታቱ በዛውም ልክ የሚዘገንኑ ነገሮችን መመልከት ችያለሁ፡፡ ዛሬ ጊዜ በርካታ ተአምራዊ  ክንዋኔዎች መኖራችውን ብረዳም ይህቺ አጭር መጣጥፌ የሻምበል ሲስተር አስቴር አያና የሕይወት ታሪክ “ይድረስ” ወደአልኩት አንባቢ ልብ በአርአያነት ትቀመጣለች በሚል ተስፋ ነው፡፡

ሕይወትን ወደኋላ መለስ ብዬ ስቃኘው ዓይኔ ይፈዛል፡፡ አንዱ የኑሮን ጣጣ ለመሸፋፈን ሌላኛው ደግሞ ኑሮን ራሱን ለመሆን በየፈርጁ ይወጣል ፤ ይገባል፡፡ ታሪክ ጎበዛዝትን ይፍጠር ወይንስ ጎበዛዝት ታሪክን ይፍጠሩ አሻሚ ሁኖብኛል፡፡ለእኔ ሻመበል የሁለቱም ውጤት ናቸው ብል ይበቃኛል፡፡

የሚታወቁት ግን በትንሹ ስለሆነብኝ የሚወሳ ተግባሮችን ፈጽመው ሳለ ተረስተው እንዳይቀሩ በመሻት ለአንባቢ የሕይወት ታሪካቸውን በመጠኑ አቅርቤአለሁ፡፡

ይህ በተለይ ለእኔ አበረታች ሆኖልኛል፡፡ በሕይወት ጎዳና ከገጠሙኝ መሰናክሎች ተላቅቄ ቅጽበት በቀራት ዘመኔ ውስጥ ፋታ በማግኘት የማበረክተው ኖሮኝ መነሳሳቴ አስደስቶኛል፡፡

በወንድሜ በአማኑኤል ኃይሉ ከመጥፋት በተረፉ መረማመጃ ከሆኑኝ ሠነዶች በቀር በእጄ ምንም አልነበረም፡፡ በዚህ ጉዞ ውስጥ የተረጋገጠልኝ ሀቅ ቢኖር ነገሮች በተለያየ እንከን ስኬት የማይኖራቸው ሊመስሉ ቢችሉም በዓላማ ላይ መጽናት ውጤታማነትን እንደሚስያገኝ ነው፡፡

በመጨረሻም ወደፊት በፈጣሪ ፈቃድ መጽሐፍ የማዘጋጀት እቅድ ስለአለኝ ለውጤቱ መሳካት ስለ ሻምበል ሲስተር አስቴር አያና እና አብሯቸው ስለዘመቱት የሚታወቅ ነገር ካለ፤ እንዲሁም እርማቶች ካሉ አንባቢዬን በመጋበዝ ወደ መተረኩ እገባለሁ፡፡

የሕይወት ታሪክ (1927-1987 ዓ.ም.)

 

ሻምበል ሲስተር አስቴር አያና ከአባታቸው ከግራዝማች  አያና ሊካሣ እና ከእናታቸው በትውልድ ከፊል  ኤርትራዊ በከፊሉ ደግሞ ኦሮሞ ከሆኑት ከተኽዓ ዳንኤል  በ1927 ዓ.ም.  በወለጋ ክፍለ ሃገር ይወለዳሉ፡፡  

አባታቸው ግራዝማች አያና ሊካሣ  በወለጋ በተለያዩ የአስተዳደር ዘርፎች ተሰማረተው ከመስራታቸው በላይ በከፍተኛው ፍርድ ቤት በዳኝነት አገልግለዋል፡፡በደቡብ ወለጋ የራስ እምሩን ኃይል በመቀላቀልም ፋሽሰት ኢጣልያን ተዋግተዋል፡፡ (1)

ቁመናቸው እጅግ ዘለግ ያለ ሲሆን ባሕሪያቸው በብዙዎች የሚደነቅ ነበር፡፡

የሲስተር አያት የወንጌል አገልጋይ ዳንኤል ገመዳ ሉሉ ደግሞ በስዊድን ሚሲዮናውያን አማካይነት ወደ ክርስትና እምነት ከመፍለሳቸው በፊት ደበላ ገመዳ በሚል መጠርያ የሚታወቁ ሰው ነበሩ፡፡ እኝህ ታላቅ ሰው ባለቤታቸውን ያገቡት ከኤርትራ ምድር ነው፡፡ የሲስተር እናት ተኽዓ የተወለዱት ወንጌላዊው አባታቸው ዳናኤል ገመዳ (2) ከታላቁ “የመጫፈ ቁልቁሉ”  ተርጓሚ ከሆኑት ከኦነሲሞስ ነሲብ ጋር በረዳትነት የወንጌላዊነት ስራቸውን ለመተግበር ወደ ወለጋ ባቀኑበት በጎጃም መስመር ላይ ነበር፡፡

ሲስተር አስቴር አያና በትምህርት ዘመናቸው፤

ሲስተር አስቴር የተወለዱት ቲንፋ በምትባል ከነቅምቴ  ወጣ ብላ በምትገኘዋ አነስተኛ ከተማ ነው፡፡ እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በነቀምቴ ከተማ መካነ ኢየሱስ መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለው ሲያበቁ አዲስ አበባ በመምጣት ለሚቀጥለው ጉዟቸው ያዘጋጃቸውን ጉዞ ጀመሩ፡፡ የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ብርሃንህ ዛሬ ነው ኢኒስቲትዩት 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ሲስተር የነርስነት ትምህርታቸውን ከኢትዮጵያ የቀይ መስቀል ማህበር በከፍተኛ ማዕረግ አጠናቀዋል፡፤

 

ስለ ትምህርት አስፈላጊነት አጥብቅው ይናገራሉ፡፡ በእድሜ ከገፉም በኋላ ከ1991 እስከ 1995 [እንደ/ኤሮፓ/አቆጣጠር] በተለያዩ ግዜያት  ወደ አሜሪካ በዘለቁበት ወቅት ብቃታቸውን ለሃገሪቱ  የነርስነት ምዝገባ ደረጃ ለማብቃት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ የአእምሮ ጤንነትን በሚመለከት የሚሰጡትን የተግባራዊ ልምምዶችን  መስፈርት ለማሟላት የተጠየቁትን ለማቅረብ ያደረጉት ጉዞ ለእኔ የማይታሰብ ነው፡፡ ወጣት በማይባለው እድሜያቸው አሁን ሳሰላስለው ወደ 58 አካባቢ ይሆናል፤ በሕዝብ ማመላለሻ ቁር ፣ ወበቅ ሳይሉ ያደረጉት ጥረት በተለይ በወጣትነት ላሉ አርዓያ ሊሆን ይችላል፡፡ራሳቸውን በትምህርት ለማነጽ ባደረጉት  ጉዞ የሚከተሉትን ዲፕሎማዎችን እና ሰርቲፊኬቶችን ተቀዳጅተዋል፤

የካቲት 21 1945ዓ.ም. – የክብር ያስታማሚነት ችሎታ ዲፕሎማ

መጋቢት 1945ዓ.ም. – በአዲስ አበባ በነርስንት ስለ መመዝገብ የምስክር ወርቀት –

1958 ዓ.ም.- በአዲስ አበባ ብርሃንህ ዛሬ ነው አኒስቲትዩት 2ኛ ደረጃ የመልቀቂያ ሰርቲፊኬት

1984- WORLD HEALTH ORGANIZATION PROGRAMME FOR CONTROL OF DIARRHEAL DISEASES (training course for managers of National Programs) አዲስ አበባ

1992  እ /ኤ/አ -ፕሪንስ ጆርጅ ኮሚኒቲ ኮሌጅ ጀሪአትሪክ ረዳት ኮርስ -በአሜሪካ፡፡

1993  እ /ኤ/አ – ዪኒቨርሲቲ ኦፍ ዲስትሪክት ኦፍ ኮሎምቢያ ኢኒስቲትዩት  ጄሮንቶሎጂ የጤና ረዳት-በአሜሪካ

1995  እ /ኤ/አ  – በሜሪላንድ የአእምሮ ጤና ሰርቲፊኬት  -STATE OF MARYLAND DEPARTMENT OF MENTAL HEALTH AND HYGIENE–GERIATRIC NURSING ASSISTANT ;በአሜሪካ፡፡

ሲስተር አስቴር በሥራ ዓለም እና በኑሮ፤

በሥራ መስክ ሲስተር ያገለገሉባቸው ሥፍራዎች እነሆ፤

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሆስፒታል፤ በነርስነት

በኮርያ 3ኛው ሻለቃ ጦር ፤በነርስነት

በክብር ዘበኛ ሆስፒታል ቀዶ ጥገና ክፍል፤ በነርስነት

በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ፤በነርስነት

በኮንጎ የዘማች ጦር ፤በነርስነት

በቅዱስ ጴጥሮስ ሳንባ ነቀርሳ ሆስፒታል፤ በሜትሮንነት

በፈንጣጣ እና ተላላፊ በሽታዎች መከላከያ ድርጅት ፤ በሜትሮንነት

በመላ አፍሪካ የሥጋ ደዌ መከላከያ ድርጅት ፤ በሜትሮንነት

በሕጻናት እና እናቶች ጤና ጣቢያ ፤ በሜትሮንነት

ብዙዎች የሚጠሯቸው “ሲስተር ሻመበል” በሚል ነበር፡፡ በቤተሰብ መካከል ደግሞ “አሹ” (በትርጉሙ “አክስት” ማለት በሆነው  መጠርያ ይታወቃሉ) ሲስተር አስቴር  ሦስት እህቶች እና አንድ ወንድም ነበሯችው፡፡ ሮዛ አያና፤ ማርታ አያና ፤ ሣራ አያና እና ወንድማቸው ብርሃኑ  ያዕቆብ::

 ሲስተር አስቴር በሥነ ምግባር ከፍተኛ ስፍራን የያዙ፤ በፈጣሪ ላይ ያላቸውን ዕምነት ደግሞ በቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ በሽማግሌነት ከማገልገል በተጨማሪ ከቅጥር ግቢዋ ተለየተው አያውቁም፡፡

በወዳጆቻቸው ዘንድ የተወደዱ እና የተከበሩም ነበሩ። ዘመድ አዝማድን በተመለከተ ለብዙዎች የልግስና እጃቸውን ዘርገተዋል፡፡ ይህንንም ያደረጉት የተትረፈረፈ ገቢ ኖሯቸው ሳይሆን ውሱን ከነበረው አቅማቸው ተነስተው ነው፡፡ ሲስተር ማጎብደድን የማይቀበሉ ግልጽ እና ቀጥተኛ ሴት ነበሩ፡፡ ወዳጆቻቸው በሕይወት መስፈርት ላይ ከከፍተኛው ደረጃ ውስጥ የሚካተቱ ሆነው ሳለ ከከፍተኞቹ ማደጎን ጠይቀው አያውቁም ፤ ሆኖም ግን በሰፈርተኞች ዘንድ መወደድን እና ጥሩ ስምን አትርፈዋል፡፡ ሰፈርተኞች “እጅሽ መድኅኒት ነው” ይሏቸው ነበር፡፡

 ለራሳችው የጎላ ድጎማ ሲያደርጉ አላየሁም፡፡ በስነ ልቦና አገነዛዘብ በጎ ይሁን አይሁን ማለት ባልችልም ፡”አይመቼ” ሆኖብኝ እንደነበር ከመግልጽ መቆጠብ ግን አልፈልግም፡፡ የልጅነት ጓደኛቸው ሃና ስፒሮ  “ለምን ብለሽ  ነው ራስሽን የማትጠብቂው” በሚል ያገባኛልነት ሲቆጥዋችው ተመልክቻልሁ፡፡ ከራሳቸው ቆጥበው እኔን የግል ት/ቤት መላካቸው ነፍስ ማወቅ ከጀመርኩበት ግዜ ጀምሮ  ሲረብሸኝ ኖርዋል፡፡ 

በሕይወት ውስጥ በርካታ ገጠመኞት ይፈጠራሉ፡፡ አንዳንዶቹ ሁካታ ሳይፈጥሩ ያልፋሉ፤ አንዳዶቹ ደግሞ ጥላሸትን በኑሮ ላይ ይቀስታሉ፡፡ የኝህ ሴት የመጀመርያ ትዳር መፋለስ በሕይወታቸው ላይ ጥቁር ነጥብን አስፍሯል፡፡ ከትዳር መፍረስ ጋር ቀብረው ሊያስቀሩ የሚችሉ መሰናከሎች በብዙዎች ኑሮ ውስጥ ታየተዋል፡፡ ሻምበል ግን በዚህ አጉል ገጠመኝ ስይስናከሉ ኑሮዋቸውን መርተዋል፡፡

በግል የባንክን ትብብር በመጠቀም የተዋበ ቪላ ሰሩ፡፡ እዳም ወቅቱን ጠብቆ ቀስ በቀስ ተከፈለ፡፡ እስከማውቀው ድረስ ቀላል አልነበረም፡፡

ስለ ሲስተር ድንቅ ብልህነት መናገር ካስፈለገ የሚከተለውን ብቻ ላውሳ፡፡ታላቅ እህታችው ሲስተር ቤቱን ከመጀመራቸው በፊት ትዳር እንዲመሰርቱ ሲጎተጉቷችው ቢቆዩም የግላቸውን ንብረት ለመትከል ‘በይደር’ አቋማቸው ጸኑ፡፡ ሲስትር በታታሪነታቸውም በብዙዎች አድናቆትን አትርፈዋል፡፡ አሁን መለስ ብዬ ሕየወታችውን ስመረምር ብዙ ነገሮችን ላመሳክር ችያልሁ፡፡ የመጀመርያ ትዳራቸው ፤ ከሻምበል አሥራት ደፈረሱ ጋር የፈጸሙት  የፈረሰው ኮንጎ ከመዝመታቸው ጥቂት ጊዜያት ብቻ ቀደም ያለ ቢሆንም በቁርጠኝነታችው ላይ ተጽእኖ አላደረገም፡፡ ለዚሁም የኮንጎው ስምሪታችው ምስክር ነው፡፡

በሃገራችን በንጉሡ ዘመን በነበረው የህዝብ ምክር ቤት  እንደራሴ የነበሩት ወ/ሮ ማሕሌት አካሉ “በወታደርና ጊዜው” ጋዜጣ ላይ ባወጡት ግጥም  ስለቁርጠኝነታቸወ እንዲህ ጽፈዋል፤

“ከተለያየንበት ከዚያች ማታ ወዲህ፤ ተልከሽ ከሄድሽ

ላንዱ ልጅሽ እንኳን ለምሳው ሳትሳሺ

በሰሜን፤ በደቡብ፤ በምስራቅ፤ በምእራብ ተሰማ ወሬሽ

የሌቃዋ እመቤት አስቴር እንዴት ነሽ፡፡

ልማደኛይቱ የኮርያ ገበሬ

እስከ ባሕር ማዶ ዘልቋል ስምሽ ዛሬ፡፡” (3)

በእኔ ግምት ትዳር ፈርሶ፤ሕጻንን ለአሳዳጊ ትቶ፤ ከዘመድ አዝማድ ተለይቶ በሙሉ ልብ ግዳጅ ላይ መዋል ቀላል አይመስለኝም፡፡

ሲስተር ሻምበል አስቴር አያና በሥራ ገበታቸው ላይ ባሳዩት ታታሪነት የፍሎረንስ ናይቲንጌል ሜዳሊያ ተሽላሚ ሆነዋል፡፡ የሄንሪ ዱናንት ሽልማትንም ተጎናጽፈዋል፡፡ ሄንሪ ዱናንት ሜዳልያ ምንጩ ምን እንደነበር እና መመዘኛዎቹን ለማጤን ያደረኩት ፍለጋ  የሲስተርን አግልግሎት ብቻ ሳይሆን ከባቢ ሁኔታዎችንም እንድመለከት ገፋፋኝ፡፡ ለመሆኑ በሃገር ውስጥ አገልግሎታችው ጊዜ ኑሮዋቸው ምን ይመስል ነበር? እንደሚታወቀው በሥራ ስምሪት ላይ አጥጋቢ ድርሻን ለማበርከት ቅድመ ዝግጅቶች ያስፈልጋሉ፡፡

ከቦታው መገኘት፤ የሥራ መንፈስን ማዳበር፤ ፈቃደኝነት ፤ችሎታ ወዘተ…እነዚህ በቦታቸው ከሌሉ እንኳንስ አየደለም ሽልማት ምሰጋና አይገኝም፡፡

ሲስተር በተደጋጋሚ ከአንድ የስራ ቦታ ወደ ሌላ የስራ ቦታ ሲዘዋወሩ ነው የኖሩት፡፡ በሥራቸው መጓደል  ምክንያት ነው እንዳይባል  በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ ዝውውርን ጠይቀው ነው እንዳልል በተዛወሩ ቁጥር ለሥራ ቦታው ቅርበት እና ለትምህርት ቤቴ ቅርበት አማካይነት ያለው ቤት ሲከራዩ መኖራቸውን ነው የማውቀው፡፡

በኑሮ ደረጃቸው ዝቅተኛ ከሚባለው እመድባቸዋለሁ፡፡ ከሻምበል አስራት ጋር የነበረው ትዳራቸው በ1951 ዓ.ም.  ከፈረሰ በኋላ ለረጅም ጊዜ ያለአጋር አሳልፈዋል፡፡

የተጎናጸፏቸው ሽልማቶቸ፤

የንግስተ ሳባ ኒሻን

የኮሪያ ጦር ሜዳ ኒሻን

የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ ኒሻን

የኮሪያ መታሰቢያ ኒሻን

የኮሪያ ዘማቾች መታሰቢያ ሜዳይ

የኮሪያ መንግስት ዩኒት ሳይቴሽን

የፍሎረንስ ናይቲንጌል ሜዳይ

የሄንሪ ዱናንት ሜዳይ

 

በተጨማሪም ሻመበል ሲስተር አስቴር ስለፈጸሙት ፈጣን፤ ወሳኝ እና ቆራጥ እርምጃ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ ዳግ ሃመርሾልድ ለንጉሡ የላኩት ቴሌግራምም  አለ፡፡የሚለውም ፤

 “ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ አዲስ አበባ፡፡ ነሓሴ 21ቀን 1952 ዓ.ም. ።ቅዳሜ በስታንቪል ስለተፈጸመው አሳዛኝና አሰቃቂ ድርጊት በመጥቀስ ለግርማዊነትዎና ለሌሎችም የአፍሪካ መንግሥታት መሪዎች የቴሌግራም መልእክት ከላክሁ ወዲህ በተባበሩት መንግሥታት አገልግሎት ሥር ያሉ ሰዎች ምን ያህል ግፍ እንደተፈጸመባቸው ኮንጎ ያለው ወኪል ገልጦልኛል፡፡ ከደረሰኝም ሪፖርት እጅግ አስደናቂ የሆነውን አንዱን ለግርማዊነትዎ እንድጠቅስ ይፈቀድልኝ፡፡

ስሟን ገና ያላወቅነው አንዲት ኢትዮጵያዊት ነርስ አንድ አሜሪካዊ መኮንን በአንድ ጂፕ መኪና ውስጥ ተይዞ ሲደበደብ ብቻዋንና ባዶ እጅዋን ልታድነው በሙሉ ልበኝነት ሞክራ ሳይሆንላት ቢቀር ኮንጎዎቹ አሜሪካኑን ይዘዉት ሲሄዱ ሰፈራቸው ድርስ ተከትላ ሔደች፡፡ እዚያም በጥይት ሊገድሏት ቢያስፈራሯትም ተመልሳ ወሬውን ለኢትዮጵያውያኑ ነግራ ሶስቱን አሜሪካውያን አድነዋቸዋል፡፡”  ንጉሡ በመልሳችው ለሲስተር የላኩት መልእክት ” ሥራሽ  ላይ ሆነሽ በፈጸምሸው መልካም ተግባር በጣም ተደስተናል፡፡ ስለ መልካም ሥራሽና ስለ መልካም አደራጎትሽ በጣም እናመሰግንሻለን” ብለው ነበር፡፡ ሲስተርም  በትህትና ሲመልሱ  “ላደርገው የሚገባኝን አገልግሎት በመፈጸሜ የግርማዊነትዎ የምስጋና ቴሌግራም ስለ ደረሰኝ ፤ አነስተኛ አገልጋይዎን በምስጋና ላሰበኝ ግርማዊነትዎ እድሜ በመለመን መሬት እስማለሁ” በማለት ነበር ፡፡(4)

                                   ከኮንጎ መልስ ሲስተር አስቴር አያና ከንጉሠ ነገሥቱ ሽልማት ሲቀበሉ፡፡

(Daily Independent Journal; August 30, 1960) እትሙ የአሜሪካን ስቴት ዲፓርትመንት ቃል አቀባይ የተባበሩት መንግሥታትን ረዳት ጸሃፊ ራልፍ ቦንችን ( Ralph Bunche) ጠቅሶ ሲያብራራ “አንዲት ኢትዮጵያዊት ነርስ ሦስት የአሜሪካ አየር ኃይል ባልደረቦችን አዳነች ” ይልና፤ “አሜሪካኖቹን ወደ እስር ቤት ሊወስድ በነበረው ጂፕ ላይ  ከተንጠላጠለች በኋላ ቢወረውሯትም በመኪና ተከታትላ በመሄድ ሁኔታውን ለባልደረቦችዋ በማሳወቅ ኢትዮጵያውያኑ ሊያደኗቸው ችለዋል” ሲል ያትታል፡፡(5)

የዚህን ትርክት ሙሉ ይዘት በበለጠ ለመረዳት የዲፓርትመንት ኦፍ አርካይቭስ ሂስትሪ ኸብ  (Dept. of Archives –History Hub ድረ-ገጽ ገብቼ ሳፈላልግ  ሻምበል ሲስትር አስቴር Legion of Merit  የተሸለሙት በአሜሪካኖቹ ላይ የደረሰው ድብደባ ከተፈጸመ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ መሆኑን የገለጸልኝ አሌክስ ዳቨርድ(Alex Daverde)  ሰለሜዳልያው ሲያብራራልኝ እንዲህ ብሏል፤

 “ሚዳልያው የተመሰረተው በኮንግሬስ ሲሆን የሚሰጠው በፕሬዚደንቱ ነው፡፡ የሚተላለፈውም በጦር ኃይሉ አዛዦች አማካይነት ነው፡፡ አራት ደረጃዎች አሉት ፡፡ ለዋና አዛዥ፤ ለአዛዥ ፤ ለባለማዕረግ መኮንን፡ እና ሊጅኔር (ወታደራዊ ባልደረባ)፡፡  ይህ ሽልማት ለውጭ ዜጎች ይሰጣል፡፡ ለእናትህ የተሰጠውን ሜዳሊያ ጉልህ የሚያደርገው የተሰጠበት ፍጥነት ነው ሲል ለሽልማቱ ከፍተኛ  ስፍራን ይሰጣል፡፡ (https://historyhub.history.gov) ፡፡ (6)

ስለ አስተዋጽኦዋቸው  በራሳቸው አንደበት  16/11/79 ዓ.ም.
                   

                                                  በምክትል መቶ እልቅና ማዕረግ ወደ ኮሪያ ሲዘምቱ የተነሱት ፎቶ

“ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የአስታማሚነት ት/ቤት 1945 ዓ.ም የካቲት 21 ተመረቅሁኝ። በተባበሩት መንግሥታት ለኢትዮጵያ ጥሪ በቀረበው መሰረት ከኢትዮጵያ 3ኛ ሻለቃ ጦር ጋር ሩቅ ምስራቅ ኮሪያ ዘመቻ ሄድኩኝ፡፡ በባቡር ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ፤ በመርከብ ከጂቡቲ ፑሳን  በ21 ቀን ገባን፡፡

የባሕሩ መንጣለል ፤የመርከቡ ጥሩንባ በንጋት ላይ ሆድ ይረብሽ ነበር፡፡  ሆኖም የሃገር ጥሪ ፤ ለወገን ያለኝ ፍቅር የተነሳሳውን ወኔዬን አላዳከመም፡፡ ተጓዝኩኝ፡፡ በቆራጥነት እኔ ሴትዋ፣ የማጀትዋ በልበ ሙሉነት የተጎዳውን ወገኔን ለመርዳት ወሰንኩ፡፡ የኮሪያ የአየሩ ጠባይ ራሱ ታላቅ ጦርነት ነበር፡፡ በበርሀ ጊዜ ያለው ብርድ ሃገሬ ማሪኝ ያሰኛል፡፡ የጦር ሠራዊቱ ተመቶ በውጊያ ላይ የሞተው ነው እንጂ ጦር ሜዳ ውስጥ ቆስሎ ለእርዳታ ከተወሰደ፣ በሕክምና መራቀቅ እያንዳንዱ የሰው አካላት ቦምብና አዳፍኔ ገነጣጥሎ የተበጣጠሰው አካላት እንዳለ ታክሞ ይድንና እንደገና ጤናው ሲመለስ ጦር ሜዳ ይገባ ነበር፡፡ የሕክምና ሳይንስ መራቀቅና እርዳታ አሰጣጥ ጉዳይ በጣም አስደናቂ ነበር፡፡ ጥሩ ትምህርትና ልምድ አግኝቼበታሁ፡፡ ጦርነት በአለም ላይ ለሰው ልጆች አስከፊና አሰቃቂ መሆኑን እያንዳንዱ ሰው ይረዳል፡፡ ጦርነት አካላዊ፣ መንፈሳዊ ፣ አስከፊ የድህነት፣ የድንቁርና ፣የበሽታ ፣ የርሃብ ፣በአካል መጉደል የሃገር ሽክም መሆን ፤የሰጋትና የጭንቀት ዓርማ የያዘ ነው፡፡ ስለዚህ ጦርነት ተፈላጊ አይደለም፡፡ሰላም ለሰው ልጆች አስፈላጊ ነው፡፡  ምርታማነት፣ አርሶ፣ነግዶ ፣ ተምሮ ፣ ወልዶ ማሳደግ ፣ ዳር ደንበር ፣ ቀን ካለጭንቀት፣ ሌት በእንቅልፍ ማሳልፍ የሚቻለው ጦርነት ቀርቶ ሰላም ሲኖር ነው፡፡ የአስታማሚነት ሙያዬን አስመልከቶ በግል ፍላጎቴ መሀይምነትንና ድንቁርናን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት በተዘረጋው ፕሮግራም በአካባቢዬ የሚገኙትን እናቶች መሠረተ ትምህርት  በሚማሩበት ጊዜ፣ በጀርባቸው አዝለው ወይም አቅፈው መማር ችግር ስላለው “ትንሣኤ ብርሃን ት/ቤት” ከ10 ሰዓት እስክ ምሽቱ 2 ሰዓት፣ ብዙ ሕጻናት በተሰበሰቡበትሥፍራ  ሞግዚት ሆኜ  አነስተኛ አገልገሎት ሰጥቻልሁ፡፡የሶማሌ ጦርነት በሃገራችን ላይ በተከፈተ ጊዜ በጤና ኮሚቴ በኩል ቤት ንብረታቸው ለጠፋባቸው መልሶ ለማቋቋም ከነዋሪ ሕዝብ ልብስና ቁሳቁስ በየቤቱ በመዞር ሰብሳቢ ነበርኩ፡፡

ስለ ኮንጎው ዘመቻቸው ደግሞ ይቺን አስፍረዋል፤ “በአፍሪካ ጸጥታን ለማስከበር በተባበሩት መንግሥታት ጥሪ ደርሶን በሻምበልነት ማዕረግ ከብዙ ሓኪሞችና ነርሶች ጋር ወደ ኮንጎ ዘምተናል፡፡ ኮንጎ በጣም ውብ የሆነች ሃገር ናት፡፡ፓትሪስ ሉሙምባ እስታንቪልን ይጎበኛል ተብሎ በሰልፍ ስንጠባበቅ በኮንጎ ወታደሮችና በተባበሩት መንግስታት ወታደሮች መካከል፤ ማለት በነጭና ጥቁር መካካል ረብሻ ተፈጥሮ ነበር፡፡ከአውሮፕላን የወረዱት ነጮች ቤልጅጎች መስለዋቸው በነበረው ረብሻ ክፉኛ ቆስለው በጭካኔ ስለተደበደቡ እስረኞች ሆነው እንዳሉ ሕክምና ማግኝት እንደሚገባቸው ድርድር አድርገን ቁስለኞቹ ስለተረዱ ላደረኩት ተጋድሎ ሊጅን ኦፍ ሜሪት ከአሜሪካ መንግስት ተልኮልኛል “(7) ሲሉ ስለተጋድሏቸው  ያለማጋነን ይገልጻሉ፡፡

ኮሪያና ሲስተር አስቴር አያና

በማስቀደም የዚች አነስተኛ ጽሑፍ ዓላማ ስለኮሪያው እና ስለኮንጎው ጦርነቶች ማብራራት አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ሲስተር በነርስነት ሙያቸው ስለተሳተፉባቸው ጦርነቶች አንዳንድ ነግሮችን አወሳለሁ፡፡

ኮርያ   ከ1910 እስከ 1945 2ኛው ዓለም ጦርነት መደምደሚያ ድረስ የኢምፔርያል ጃፓን ቅኝ ሆና ቆይታለች። ጃፓን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ስትሸነፍ እጇን ሰጠች፤ ይህም የሆነው ከአሜሪካው የአቶሚክ ቦምብ ጥቃት በኋላ ነበር፡፡ የኮርያ ምድር በአሜሪካ እና  በሶሺያሊስት ሶቭየት ህብረት በተደረገ ስምምነት  38ኛው ፓራልል ተበሎ በተጠራው የድንበር አከላለል ለሁለት ተከፈለች፡፡ ደቡቡ በምእራባውያን ርዕዮት የሚመራ ሲሆን ሰሜኑ ከሶሺያሊስት ወገን ሆነ፡፡ ደቡቡ በኢኮኖሚ በእጅጉ  እያደገ መምጣቱን በ2018 ኛው የኦሊምፒክ አዘጋጅነት ሲያስመሰክር ሰሜኑ ደግሞ የሚታወቀው በዘር ሐረግ በተመሰረተ የመንግስት አመራር በሚያስተዳድራት መሪዋ አሻፈረኝነት ነው፡፡ ከእርሱ በኩል ሊቀሰቀስ በሚችል የኑክሌር ጦስ ዓለማችን በስጋት ላይ ወድቃለች፡፡ ሰሜን ኮሪያ በሮቿን ለውጭው ዓለም  ከደቡቡ እጅግ በተለየ መልኩ የዘጋች ስትሆን ሕዝቦችዋ ሥቃይ ውስጥ እንደሚገኙ ይነገራል፡፡

ጦርነት አስክፊ ነው፤ ሲስተር አስቴር እንደገለጹት ሁሉ፡፡ የራሳችን ልምድም ይህንኑ አሳይቶናል፡፡ የተለያዩ ክፍለ ዓለማት እና ሕዝቦችም የዚሁ አስከፊ ተግባር ሰለባ ሆነዋል፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ ስፍራዎች የጦርነት ነጋሪት አሁንም ይጎሰማል፡፡ ዓለማችን ካለፈው የተማረች አይመስለኝም፡፡

ከ1910 እስከ 1945 የጃፓን ግዛት ሆና በቆየችበት ጊዜያት ዜጎችዋ ጥልቅ የሆነ የኢኮኖሚ በደል ሲፈጸምባቸው በማንነታቸው ላይ ደግሞ እንዲሁ እጅጉን ተገፍተዋል፡፡ መጠሪያ ስማቸውን ሳይቀር ደልዘው በጃፓንኛ መጠሪያ እንዲተኩ ይገደዱ ነበር፡፡

የቃኘው ጦር 6,007 ወታደሮችን ያካተተ ሲሆን የተመራው በጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ እና በኮሎኔል ጌታቸው ገብሬ ነበር፡፡ በጦርነቱ  121 ወታደሮች ሲሞቱ 536 ያህል ደግሞ ቆስለው በጀግንነት ስሙን በማስጠራት የተሰለፈበትን ግዴታ ተወጥቷል፡፡ በዛን ወቅት ኢትዮጵያ ሶስት ዲቪዚዮን የጦር ሰራዊት፤ እጅግ የተደራጀ የክብር ዘበኛ እና  በማበብ ላይ ያለ የአየር ኃይል ነበሯት፡፡ በነገራችን ላይ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ወደ ተከሰተው የኮንጎ ውዝግብ ኢትዮጵያ ኃይሏን የላከችው በገዛ አውሮፕላኖቿ ነበር፡፡ 

 የኮሪያው ዘመቻ አምስት  ዙሮች ተተግብሮበታል፡፡ ሰለዚህ ጦር አደረጃጀት እና ታሪክ በሰፊው  ከ”Emperor’s Own” በተሰኘ  የዳግማዊ  አበበ መጽሐፍ ውስጥ ማግኘት ይቻላል፡፡ ዳግማዊ አበበ ስለ ቃኘው በዋቢነት ያስቀመጠውን ጥቅስ ካነሳሁ በመለስ ለአንባቢው በስተግርጌ በግሌ መጠቆም የምፈልገው በአሜሪካ የጦር ተቋም በቀለም ልዩነት ሲራመድ የቆየውን ማግለል (segregation) ያገደው (desegregation  act)  ገና ጨቅላ ወቅቱ ላይ እንደነበር እና በቃኘው ብቃት ላይ ጥራጣሬ እንደነበረም ነው፡፡ ከጅምሩ ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ በአርቆ አስተዋይነታቸው ሠራዊታቸው “ጠላትን እንጂ ወዳጅን የማይወጋ ሠራዊት እንደመሆኑ ማንኛውም ዓይነት በዘረኝነት ላየ የተመሰረተ ችግር   እንደማይገጥመው ተስፋቸው ጽኑ እንደሆነ ” (8) ጠቆም አድርገው ነበር፡፡ በተጨማሪም ሠራዊቱ በአሜሪካ ዘርን በሚጠይቀው ሰነድ ላይ (Negro) የሚለውን መለያ እንዳልተቀበለ ዳግማዊ በገለጸው (9) አመላካች ለይ ማስመር አስፈላጊ ነው እላልሁ፡፡

በሠራዊቱ ብቃት ላይ በአንዳንድ የአሜሪካ ወታደሮች ጥርጣሬ የነበረ ቢሆንም  በማርሻል መጽሐፍ [Pork Chop Hill by S.L.A Marshal] ላይ “ አይነተኛና አዳጋች ሁኔታዎችን በመወጣት ድልን ይጎናጸፉ ነበር”(10) የሚለው የመጽሐፉ አገላለጽ ስለቃኘው ብቃት አስረግጦ ይናገራል፡፡ አልመተማመኑ ሊወገድ የቻለው በመጽሐፉ ላይ የሰፈሩ ዓይነተኛ ገድሎች በመፈጸማቸው ነው፡፡ በዚህ አገላለጼ ማንንም ለማጣጣል አቅጄ ሳይሆን በሁሉ ዘመናት ውስጥ ክብርን ለመመለስ የበቃነው ዋጋን በመክፈል ነው ለማለት ያክል ነው፡፡

 

የቃኘው ጦር የተውጣጣው ከክብር ዘበኛ ውስጥ ነበር፡፡ ንጉሡ በክብር ዘበኛ አካዳሚ 04/11/1951 እ /ኤ/አ ተገኝተው የምረቃ ሥነ ስርዐት ከተከናወነ በኋላ በማግስቱ በጃንሆይ ሜዳ አርማውን ተረከበ፡፡ የዚህ  ጦር አዛዥ ጄኔራል ደስታ ገመዳ ነበሩ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ወንድሜን እና ራሴን በመወከል ምስጋና ላቀርብላቸው እፈልጋለሁ፡፡ በአቃቂ የሚገኘው የእናት ባንክ ቅርንጫፍ በእናታችን ስም የተሰየመው እሳችውና ባለቤታቸው ምክትል መቶ አለቃ ሲስተር ብርቅነሽ ከበደ የተረሱትን እናታችንን በማስታወሳቸው ነው፡፡

ምክትል መቶ አለቃ ሲስተር ብርቅነሽ ከበደ ባንኩ በስማቸው ቅርንጫፍ መሰየም እንዳቀደ እና ለዚህ ፈቃደኝነታቸውን ሲጠይቃቸው ይልቁንስ በሻምበል ሲስተር አስቴር አያና ስም እንዲሰየም መረጡ፡፡

 

ሻምበል አስቴር የተሳተፉት በ1953 እ /ኤ/አ ከዘመተው 3ኛው ሻለቃ ጦር ጋር ነበር፡፡ 3ኛው ሻለቃ ወደዛች ሩቅ ምስራቅ ሰላጤም የተጓዘው በተሟላ አቋሙ በባቡር እስከ ጂቡቲ ከዚያም ለ21 ቀናት በመርከብ በመጓዝ ነበር፡፡

2ኛውን ሻለቃ ለመተካት በ04/21/1953 እ /ኤ/አ ፑሳን ወደብ ሲገባ አቋሙ ከመኮንኑ እስከ ተራው  በቁጥር 1266 ነበር፡፡  የተሰማራውም ከአሜሪካ 32ኛው እግረኛ ጦር 7ኛ ክፍለ ጦር ዲቪዚዮን ጋር ነበር፡፡ግዴታውን የፈጸመው ለ4ተኛው ቃኘው ሻለቃ በ06 /16 /1954  እ /ኤ/አ   በማስረከብ ነበር፡፡

ሁለቱ የምክትል መቶ አለቃ ነርሶች አገልግሎቶቻቸውን ያበረከቱት በቶክዮ በሚገኘው በአሁኑ ሰዓት ጣቢያ 128 ተብሎ በሚታወቀው የአሜሪካን ሆስፒታል ውስጥ ነበር፡፡

በጦር ሜዳ የተጎዳ እና የቆሰለ የቃኘው ሻለቃ አባል በቶክዮ አርሚ ሆስፒታል ምንም ወደኋላ ሳይሉ በቋንቋ የሚፈጠሩ ገደቦችን በመስበር ጉዳተኞቹ እርዳታ እንዲያገኙ ማስቻላቸውን እና ለዚህም ተግባራቸው “መወደስ  እንደሚገባችው” ኪሞን ስኮርዲለስ “ቃኘው” በተሰኘው መጽሐፉ  ውስጥ ላይ አመልክቷል፤(11)

እንዲሁም “ጠቅልና ሠራዊቱ” የተሰኘው መጽሐፍ ደግሞ እነዚህ “በሕዝብ ጤና ጥበቃ የተመሰከረላቸው” ስለሚላቸው  “ሴት መኮንኖች” ሲያብራራ፤ “….የ3ኛው ሻለቃ ጦር ወደ ኮሪያ ግንባር ሲታዘዝ በጠላት ጦር የተጠቁትን ወገኖቻቸውን በአስታማሚነት ረገድ ለመርዳት ፈቃደኞች ሆነው የምክትል መቶ አለቃ አስቴር አያና እና የምክትል መቶ አለቃ ብርቅነሽ ከበደ የተባሉት ልጃገረዶች በፈቃደኝነት ተጓዙ” ብሏል፡፡(12)

ጦሩ ብላችፎርድ በመትባል መርከብ ፑሳን ወደብ እንደደረሰ ቀደም ሲል ገብተው በነበሩት በጄኔራል ወልደዮሐንስ ሽታ አቀባበል እንደተደረገላችው ዳግማዊ አበበ ያትታል፡፡ ሠራዊቱ በካምፕ ሲሰፍር ነርሶቹ ማለትም አስቴር እና ብርቅነሽ በመኪና ወደ ማረፊያቸው እንደተውሰዱም ገልጿል፡፡ ስታር ኤንድ ስትራይፕስ(Star and Stripes) 04/18/2023 ባወጣው እትሙ በዚህ በኮሪያው ጦርነት ውስጥ በቀጥተኛ ውጊያ የሞቱ እንደሌሉ ቢገልጽም በአውሮፕላን አደጋ የሞቱ ነርሶች እንዳሉ ይናገራል፡፡

ባጠቃላዩ ከ7,000 በላይ ነርሶች እንደተሳተፉ ነው የሚገልጸው፡

 

ኮንጎና ሲስተር አስቴር አያና

የኮንጎው ግጭት ሌላኛው በዓለም አቀፍ ደረጃ ሃገራችንን ያሳተፈ ነው። ይህ ጦር  የጠቅል ብርጌድ አካል  ነው፡፡ ምንጩም ልክ እንደ ቃኘው ከክብር ዘበኛ ነበር፡፡ አዛዦቹም ኮሎኔል ከበደ ገብሬ እና ኮሎኔል ዮሐንስ ሽታ ነበሩ፡፡

የዚች በደቡብ ምዕራብ አፍሪካ የምትገኝ  “ በንጥረ ነገሮች እና በመዓድናት ” የተሞላች ሃገር ውስብስብ ታሪክ ከበርሊኑ ኮንፈረንሰ (1884-1885 እ /ኤ/አ ) ይጀምራል፡፡ ንጉሥ ሊዎፖልድ 2ኛ ከእንግሊዝዋ ንግሥት ቪክቶሪያ ጋር በነበረው ፉክክር በዛም በዚህም ብሎ የግል ንብረቱ እንድትሆን በኮንፈረንሱ ካጸደቀ በኋላ ሃግሪቱን ይህ ነው በማይባል ጭካኔ እና ምዝበራ ያስትዳድራት ገባ፡፡ 1908  እ /ኤ/አ በተፈጠረበት ተጽእኖ ኮንጎ ከአገዛዙ ተላቋ ” ቤልጅም ኮንጎ ፡” በመባል የቤልጅግ ቅኝ ሆና ተመሰረተች፡፡ በጁን 30, 1960  እ /ኤ/አ   ነጻነቷን ስትቀዳጅ የኮንጎው ሰራዊት የቀድሞውን የቤልጂግ ጦር “አፍሪካናይዝ” የማድረግ ሙከራው  በቤልጂጉ ጄኔራል ኤሚል ጃንሠንስ አሻፈረኝነት ውድቅ ሲሆን ” የአልገዛ ባይነት”  አመጽ ተቀሰቀሰ፡፡

የሠራዊቱ አባላት በነጮች ቁጥጥር ስር መሆንን አልውደዱም፡፡ “ራስ ገዝነትን፡” መረጡ፡፡ ይቺ ሃገር ከስረ መሰረቱ ሥር በሰደደ የቀለም ልዩነት ፤ በዘረኝነት እና የኢኮኖሚ/ማህበራዊ ጦስ ውስጥ የነበረች ናት፡፡በማከልም ነጻነቷን ተከትሎ ጁላይ 11, 1960  እ /ኤ/አ ሞይስ ሾምቤ  የካታንጋን ( ግዛት ) መገንጠላችው ነግሩን ሁሉ እጅግ አባባስው፡፡ የስልጣን ሽኩቻውም ከማይታሰብ  ደረጃ ደርሶ ነበር፡፡

የሰላም አስከባሪው” ሕግ እና ሥርዓትን ማስከበር”፤ “የሌሎች መንግስታተን ጣልቃ ገብነት ማገድ” ፤ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ መገንባት ፡ እና” መረጋጋትን መፍጥር “በሚል መርሕ ጥረቱን ቢያካሂድም ስለዚህ ጉዳይ ” ከሠላም አስከባሪነት  ወደ ተዋጊንት ” በተባበሩት መንግስታት ሠላም አስከባሪ ኃይል የተደረገው ሽግግር በርካታ ትችቶች ቀርበውበታል፡፡ አስከሬናቸው በአሲድ ውስጥ ተዘፍቆ እንዲቀልጥ የተደረጉት የሉሙምባ አሟሟትም በዙ ጥያቄዎችን አስከትሎ ነበር፡፡ ሉሙምባ ውዝግቡን ለማብረድ የተባበሩት መንግስታትን ዕርዳታ  ቢጠይቅም ዳግ ሃምርክስሆልድ ” የጣልቃ ገብነትን ” ምክንያቶች በመዘርዘር የጦር እርዳታ ሊያደርጉለት እንድማይችሉ ባስታውቁበት ቅጽበት ሉሙምባ ፊቱን ወደ ሩሲያ አዞረ፡፡ ወዲያውም ሩሲያ 1,000 የጦር አማካሪዎቿን ላከች፡፡

የተባበሩት መንግስታት ገላጋይነትን  በያዘ መርሆ ተልእኮውን ቢጀምርም  እያደር ሁኔታዎች ስለተቀያየሩ ማለትም “የቤልጅግ ወረራ “፣” የቅጥረኛ ወታደሮች በኮንጎ መሰማራት  “፤ “የካታንጋ መገንጠል ” እና ሌሎች ስር የሰደዱ ማሕበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ነበር በውጊያው ውስጥ በቀጥታ መሳተፍ የጀመረው፡፡ ከ100,000 ሰዎች በላይ የሞቱበት ይህ ውዝግብ የቀዝቃዛው ጦርነት (1954- 1991) “አቦል” ነበር ማለት ይቻላል።

በዚህ የሰላም ማስከበር ጥሪ ላይ በቀዳሚነት የተሳተፉት የአፍሪካና እስያ ሃገሮች ነበሩ፡፡ ወደ መገባደጃው ላይ ኖርዌና ስዊድን ተሳትፈዋል፡፡ እንግዲህ ሲስተር አስቴርም ልክ በኮሪያው ዘመቻ አሁን ግን ላቅ ባለ ደረጃ ፤ በሻምበልነት ማዕረግ ፤ ከመጀመሪያው ዘማች ቡደን ጋር ከተቱ፡፡ በኮሪያው ተልዕኳቸው ካገኙት ልምድ እና የጦርነትን ገጽታዎችን ከመለማመድ የመነጨ ይመስለኛል በስታንቪል፤ ኮንጎ ነሐሴ 21, 1952 ዓም በተነሳው ግጭት የአሜሪካን አየር ኃይል ባልደረቦች በኮንጎ ወታደሮች የደረሰባቸውን አሰቃቂ ድብደባ በመቃወም እና የግብረ አበር ባልደረቦቻቸውን እርዳታ በማስተባበር ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ድንቅ ሥራን አስመዝግበዋል፡፡

የሕክምና ባለሙያ ናችው፡፡ነገር ግን በጦር ሜዳ ላይ የዋሉ ወገኖቻቸውን በሕክምና ለመርዳት በኮርያው ዘመቻ በፈቃደኝነት በኮንጎው ደግሞ በኮሪያው ባካበቱት ልምዳቸው በመመረጥ ግዳጅ ላይ ተሰማሩ፡፡

ሻመበል ምንም እንኳን መደበኛ ወታደራዊ ስልጠና ባይኖራቸውም ከአንድ ወታደራዊና የሕክምና በለሟል የሚጠበቀውን ተግባር በኮንጎ አከናውነዋል፡፡ ለዚሁም አኩሪ ተግባራቸው ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ  የ575  ካሬ ሜትር ቦታ በካዛንቺስ በሽልማት መልክ ተሰጥቷቸዋል፡፡

መደምደሚያ

የቃኘው ሻለቃ እና የጠቅል ሠራዊት በኮሪያ እና በኮንጎ ያደረጉት ተሳትፎ እንዲሁም የፈጸሟቸው ጀብዶች በሻምበል ሲስተር አስቴር አያና ተግባሮች ብቻ ተገልጾ የሚያበቃ አይደለም፡፡ እጅግ ሰፊ ነው፡፡ ሃገራችንንም በዓለም አቀፉ መድረክ ጉልህ ስፍራን አጎናጽፏት ነበር፡፡ ጉዳዩ “በድሮ በሬ ያረሰ የለም” ቢሆንም፡፡ በዚህ ተልእኮ የሕይወት መስዕዋትነት ያደረጉ ይገኙባቸዋል፡፡ ልክ እንደ ሲስተር አስቴርም ቤት ንብረታቸውን ትተው ተልእኮውን ከግቡ ያደረሱ በርካቶች ናቸው፡፡

 የዛኔው የካሣ ተሰማ ፤ኮርያ ዘማች፤ “እልም አለ ባቡሩ፡ ወጣት ይዞ በሙሉ፡” ዜማ ዜጎችን ለዓላማ እንዳስተባበረ ሁሉ በአሁኑ ወቅት ዘር፤ ብሔር ሳንል ሃገራችንን ለመታደግ በአንድ ባቡር ላይ መሳፈር ይጠበቅብናል፡፡

መልካም ተግባር ይዋል ይደር  እንጂ መወሳቱ አይቀሬ ነው፡፡ የእናት ባንክ ቅርንጫፉን በሲስተር ስም ለመሰየም በተነሳበት ወቅት  ፎቶግራፋቸውን እንኳን ለማግኘት ተቸግሮ እንደነበር ገልጾልናል፡፡ አሁን ግን በአጭር መልኩ ታሪካቸውን ለአንባቢያን ማቅረብ ተችሏል፡፡

                      ዘመን ያልፋል ፣ ይተካል፤ መልካም ተግባር ግን በታሪክ መዝገብ ውስጥ በድንቅነቱ ይታወሳል፡፡

የግርጌ ማስታወሻዎች፤

1. “Profiles of Aster Ayanna and Berqnash Kabadda;” Ahmad Hassan Omar; Annales d’Ethiopie; V.30 ; pp 335-336.

2.Evangelical Pioneers in Ethiopia-Origins of The Evangelical Church Mekane Yesus by Gustav Aren; pp 212-213; p 294; p 388; pp 392-393; p 410; p 412

 3.”ወታደርና ጊዜው” 9ኛ ዓመት፣ ቁጥር 283/12 ዕትም፡፡  

4.ወታደርና ጊዜው 9ኛ ዓመት ቁጥር 283/12 ዕትም፡፡

5.“Daily Independent Journal;” August 30, 1960/ትርጉም ከእኔ

6. ድረ-ገጹ በDepartment of Archives የሚደገፍ የዜጎች መረብ ነው

ከአሌክስ ጋር የተገናኘነው በመጻጻፍ ነው፤ትርጉም ከእኔ

7. ለቃለ መጠይቅ ሲዘጋጁ የነደፉት ማስታወሻ ፤1979 ዓ.ም

8.  Emperor’s own ; Dagmawi Abebe p. 16

9. Emperor’s Own ; Dagmawi Abebe p. 73

10. Pork Chop Hill; Marshal S.L.A p. 164

11.  Kagnew: The Story of the Ethiopian Fighters in Korea; Kimon Scordiles PP. 155

12. ጠቅልና ሠራዊቱ ፤ በዳምጤ አሰማኸኝ፤ ገጽ 282

Leave a Reply

Scroll to Top

Discover more from ሰምና ወርቅ

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading