ኢትዮጵያ፤ የአባይ ወንዝ ባለቤትነትና ተጠቃሚነት ጥያቄ ፤ ኪዳኔ ዓለማየሁ ፤ መስከረም 2012

በጥንቱ ዘመን፤ የአባይ ወንዝ ዋናዋ ምንጭ ኢትዮጵያ መሆኗና ባለቤትነቱዋ ታውቆ፤ የግብጽ መሪዎች በየዓመቱ ለሚጎርፍላቸው ውሀ ይከፍሉ ነበር። በቅርቡ በየድረ-ገጹ በስፋት ከሚቀርቡት ሐተታዎች፣ ትችቶችና አስተያየቶች ውስጥ ሰፊ ስፍራ ይዞ የሚገኘው አንደኛው አርእስት ኢትዮጵያ ውስጥ በመገንባት ስላለው ታላቅ የአባይ ግድብ ነው። ስለ ግድቡ የተንጸባረቁት የተለያዩ አስተያየቶች እንዳሉ ሆነው የአባይ ወንዝ ባለቤትነት የማን እንደ ሆነና በጋራ ተጠቃሚነት ዙርያ ውሱን በሆነ መንገድ ተነካ እንጂ በጥልቀት በተከናወነ ምርመራና በዓለም-አቀፍ ሕግ በተመሠረተ አስተማማኝ ማስረጃ የተደገፈ ጽሑፍ አልቀረበም። የዚች ጦማር ዓላማም ኢትዮጵያ ከሱዳንና ከግብጽ ጋር እንዲሁም ከሌሎች የአባይ ተፋሰስ ሀገሮች ጋር  በምታከናውናቸው ውሎች ያሁኑንና የመጪውን ትውልድ እንዲሁም የሌሎች ሀገሮችን መብት በሚጠብቅ ሥልት መጠቀሟን እንድታረጋግጥ ተገቢውን ቅድመ-ዝግጅትና ጥንቃቄ እንድታደርግ ለማሳሰብ ነው።