ፕሮፌሰር ሰይፉ በላይ (1951 – 2019)

ፕሮፌሰር ሰይፉ በላይና እኔ የተዋወቅነው እኔ የሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪና  የቤተ መጻሕፍቱ ሠራተኛ እያለሁ ነበር። እርሱ በዚያ ጊዜ የሳይንስ ፋክልቲ ተማሪ ነበር። ከተዋወቅን በጥቂት ጊዜ ውስጥ ቀደም ሲል  አውቀው ከነበረው አቶ ሙሉጌታ ከበደ  ጋር  ተቀናጅተን  አንድ  መጽሔት  እንድናቋቁም  ባቀረብኩላቸው ሃሳብ ላይ በመስማማታቸው በውይይት ሰምና ወርቅ ሁለገብ የጥናትና የምርምር መጽሔት በሚል ርእስ መጽሔት የማቋቋሙንና  በተግባር የመግለጹን እርምጃ   ተያያዝነው። እኔ የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ እንድሆን፣  ፕሮፌሰር ሰይፉና አቶ ሙሉጌታ ደግሞ የአዘጋጅው ቦርድ አባላት በመሆን አብረውኝ ሊሰሩ ተስማማን። የመጀመሪያውን እትም በምናዘጋጅበት ጊዜ እንደስምምነታችን በሁሉም የእውቀት ዘርፍ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ያሉበትን ደረጃ በመገምገም እንድንጀምር የሚል ሃሳብ ስለነበረ ፕሮፌሰር ሰይፉ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ያለውን ድርሻ በሚገባ ሰርቶ አቅርቦልናል። ከዚህም የመንደርደሪያ ጥራዝ በኋላ ፕሮፌሰር ሰይፉ በላይ በቀጣዩ ጥራዝ ላይ ማለትም ጥር 1979 ዓ.ም በታተመው እትም ላይ “የፕላስቲክ ኪነ ጥበብ” በሚል ርእስ ላይ ሰርቷል፤  ሰኔ 1979 ዓ.ም በታተመው ላይ ደግሞ “ጥንታዊ የብረት ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ” በሚል ርእስ አንድ መልካም ጽሑፍ ለአንባቢያን አቅርቧል። በመጨረሻም “የኢትዮጵያውያን የሳይንስ ሙያተኞች ድርጅት” በሚል አንድ ተጨማሪ ጽሑፍ ጥር 1981 ዓ.ም በወጣው እትም ላይ አቅርቧል። ፕሮፌሰር ሰይፉ በላይ ከሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ በባዮቴክኖሎጂ ከፍተኛ ድግሪ ከተቀበለ በኋላ፥   በአሜሪካ መንግስት መሥሪያ ቤቶች (በዋልተር ሪድስና ኤን አይ ኤች – Walter…