መጽሐፈ ምሳሌ ዘጨዋ ተረት  

ይህ መጽሐፍ ያልታተመና በዩናይትድ ስቴትስ የኮንግሬስ ቤተመጻሕፍት ውስጥ በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ዋና ክፍልየኢትዮጵያና የኤርትራ ሃገራት የመጻሕፍት ክምችት ክፍል ውስጥከሌሎች ካልታተሙ የግእዝ፣ የአማርኛና የትግርኛ መጻሕፍት ጋርይገኛል። የተጻፈው በ1911 ዓ.ም ሲሆን ተረቶቹን በጽሑፍያሰፈረው የንጉሥ ወልደጊዮርጊስ አሽከር ነኝ የሚለው ነጋዴው አቶአበሩ የተባለ  የማጂ ከተማ ነዋሪ ሰው ነው። ይህን ያጠናቀረውንየጥንት ተረት መድብል ለወዳጁ  ለእንግሊዝ መንግሥት መኮንንለሜጀር አጥሒል [Major Athil] ሲያበረክት በመጽሐፉ ላይ ተጽፎእንደተገኘው፣ “ ይህን እያዩ እንዲያስታውሱኝ” ከሚል ማሳሰቢያ ጋርነበር። በዚህ መድብል ውስጥ በወረቀት ላይ ተጽፈው የተገኙተረቶች አስራ ሁለት ያህል ናቸው።

የዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ የሕይወታቸው መጨረሻ ሰዓት እና የመቅደላ ዝርፊያ

ይህ ታሪክ፣ በ1874 [1866 ዓ.ም]  ሄንሪ ኤም. እስታንሊ የተባለው የኒውዮርክ  ሄራልድ ጋዜጣ ተቀጣሪ  እንደ አውሮፖ አቆጣጠር በ1868 በጄኔራል ሮበርት ናፕዬር የተመራው የእንግሊዝ ጦር ጋር ወደ ኢትዮጵያ  በመጓዝ ያከናወነውን “ኮማሲ እና መቅደላ” በተሰኘው የሚመስጥ መጽሐፉ የመዘገበው ነው። ይህ አጭር ጽሑፍም የተጻፈው የንጉሡን ሕይወት ማለፍ ተከትሎ እስታንሊ በገጽ  449-464 ያሰፈረውን ሀተታ ማስረጃ  መሰረት በማድረግ ነው። በተጨማሪም በእውን ያያቸውን ከመቅደላ የተዘረፉትን ቅርሶች ገጽ 454-462 በዝርዝር ያስቀምጣል። የእንግሊዝ ጦር ወደ ኢትዮጵያ የዘመተበት ምክንያት ንጉሡ ለንግሥት ቪክቶሪያ የሁለቱ ሃገራት ወዳጅነት መመስረት እና መጠናከር በተመለከተ ለጻፉላቸው ደብዳቤ መልስ ስለተነፈጋቸው፣ በአጸፋው ያሰሯቸውን የእንግሊዝ መልክተኞች ከእስር ለማስፈታት መሆኑ ሊታወስ ይገባል።