ቀኛዝማች አባ ናዳ፤ (ቀኛዝማች ድልነሣሁ ጠንፉ) የኢትዮጵያ ጀግናና ዲፕሎማት ከኪዳኔ ዓለማየሁ
አባ ናዳ ከቅርብ ዘመዳቸው ከልዑል ራስ መኰንን ወልደሚካኤል ጋር በመዝመት ሐረርጌ በቅኝ ገዥዎች እንዳትያዝ ካደረጉት ጀግኖች አንዱ ናቸው። ዓረቦች፣ እንግሊዞች ፣ ፈረንሳዮችና ኢጣልያኖች ሐረርጌን ለመያዝ አሰፍስፈው በነበረበት ጊዜ በአጼ ምኒልክ ብልሕና ፈጣን እርምጃና አመራር በነራስ መኰንንና አባ ናዳ ቆራጥነት ሐረርጌን ለማዳን ችለዋል። አባ ናዳ መኖሪያቸውን ጃርሶ ጎሮ አድርገው በልዑል ራስ መኰንን መሪነት ሐረርጌ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍለ-ግዛት ጋር የነበራት ትስስር እንዲጠናከር አድርገዋል። አባ ናዳን አስደናቂ የሚያደርጋቸው ሌላው ከፍ ያለ ቁምነገር በ1889 ዓ/ም ከራስ መኰንን ጋር ኢጣልያ ተጉዘው ከልዑካኑ ጋር በመሆን በጊዜው ከነበሩት ከንጉሥ ኡምቤርቶና ከኢጣልያ መንግሥት ጋር በመደራደር የውጫሌው ውል እንዲጸድቅ መደረጉ ብቻ ሳይሆን ከኢጣልያኖቹ በተገኘው ብድር ብዙ የጦር መሣሪያዎች ለኢትዮጵያ ያስገኙ መሆኑ ነው። ተፈሪ መኰንን (በኋላ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) የተወለዱትና እድሜያቸው ሶስት ዓመት እስኪሆን ድረስ የነበሩት በአባ ናዳ የበላይ ጠባቂነትና አሳዳጊነት በጃርሶ ጎሮ ነበር።