ተረት፣ ተረት፤
ባንድ ከተማ ሽፍታ መጥቶ ሰው ሁሉ ነፍሱን ለማዳን ሸሸ።
ሁለት ሰዎች ቀሩ ይላሉ።
እነርሱም እውርና አንካሳ ናቸው።
እውሩም የሚመራው ፣ አንካሳውም የሚሸከመው አጥተው ተጨነቁ።
ስለዚህ ተማከሩ።
እውሩ አንካሳውን ተሸከመው፤ በእውሩ እግር በመፃጉዑ *1 ዓይን እንደ አንድ ሰው ሆነው ሀገር ወዳለበት ደረሱና ነፍሳቸውን ከሞት አዳኑ።
የዚህ ምሣሌ ትርጓሜው እንዲህ ነው፤
ከተማ የተባለ ይህ ዓለም ነው።
በከተማው ያሉ ሰዎች በዚህ ዓለም የሚኖሩ ሰዎች ናቸው።
ሽፍታ የተባሉት ሰይጣናትና የዚህ ዓለም ክፋት ናቸው።
ከሽፍታውም የሸሹ ሰዎች ከዚህ ዓለም ተንኮልና ከኃጢአት ሸሽተው የነፍሳቸውን መንገድ የያዙ ናቸው።
እውሩ የሕዝብ ወይም የምዕመናን አምሳል ነው።
መፃጉዕ የመምሕራን አምሳል ነው።
መፃጉዑ የዕውሩ ዓይን እንደሆነ፣ እንዲሁም መምሕራን የሕዝብ ዓይኖች ናቸው።
ድንቁርናንና አለማወቅን ጭለማን አስወግደው፣ ብልሃቱንና እውቀቱን ብርሃን ለሕዝቡ የሚያሳዩ ስለሆኑ።
እውሩ ለመፃጉዑ እግርና ኃይል እንደሆነ፤ እንዲሁም ሕዝቡ የመምሕራን የሥጋ ኃይልና መጋቦች*2 ናቸው።
መፃጉዑ ለዕውሩ በዓይኑ ማየት ኮርቶ ፣ እኔ ላንተ መሪ ልሆን አልወድም ቢል በተቀመጠበት ረኅብ በገደለው፣ ወይም አውሬ በበላው ነበር።
እንዲሁም ዕውሩ በጉልበቱ ኮርቶ መፃጉዑን እኔ አንተን አልሸከምም ቢል፣ ገደል ገብቶ ወይም ወድቆ በሞተ ነበር።
በምክር በመስማማታቸው በመፃጉዑ ዓይን እያዩ በዕውሩ እግር እየሄዱ ከሀገር ደረሱና ሰውነታቸውን ከጥፋት አዳኑ።
ሰው ሁሉ እንዲሁ በምክር ቢተባበር ደኅንነት ይሆንለታል።
የተረቱ ምንጭ ካልታተመውና መጽሐፈ ምሳሌ ዘጨዋ ተረት ከተሰኘ የተረቶች ጥራዝ የተገኘ ነው። ይህ ጽሑፍ በዩናይትድ ስቴትስ የኮንግሬስ ቤተመጻሕፍት ውስጥ በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ዋና ክፍል የኢትዮጵያና የኤርትራ ሃገራት የመጻሕፍት ክምችት ክፍል ከሌሎች ካልታተሙ የግእዝ፣ የአማርኛና የትግርኛ መጻሕፍት ጋር ይገኛል። የተጻፈው በ1911 ዓ.ም ሲሆን ተረቶቹን በጽሑፍ ያሰፈረው የንጉሥ ወልደጊዮርጊስ አሽከር ነኝ የሚለው ነጋዴው አቶ አበሩ የተባለ የማጂ ከተማ ነዋሪ ሰው ነው። በዚህ መድብል ውስጥ በወረቀት ላይ ተጽፈው የተገኙ ተረቶች አስራ ሁለት ያህል ናቸው።
እነዚህን ጥንታዊ ተረቶች አንድ ባንድ አከታትለን የምናወጣበት ምክንያት የምንወርሳቸውንና የማንወርሳቸውን ለይተን ለማወቅ እንዲረዳን ነው። በተረቶች ውስጥ ታምቀው የሚገኙት አስተሳሰቦች ተረቶቹ በተፈጠሩበት ዘመን የነበረውን ደማቅ አስተሳሰብ ለመሰለቅ ሆን ብለው የተፈጠሩ ናቸው። በተረት መልክ ሲቀርቡም ለዛ እንዲኖራቸውና ለወጣት ልጆችም አስተሳሰቡን ለማስተላለፍ ቀላል እንዲሆን በማሰብ ነው። እነዚህ በተለያዩ ተረቶች አማካኝነት የቀረቡልን አስተሳሰቦች ላሁኑ ዘመን የሚጠቅሙ መሆን አለመሆናቸውን ለይቶ ማወቅ የኛ ፋንታ ነው።ይጠቅማል አይጠቅምም የሚል የተለያየ የአመለካከት ዘርፍ ሊኖር ይችላልና ተረቶቹ ቀርበው መነበባቸው ጥቅም- አልባ አይደለም ብለን እናምናለን። ያም ሆነ ይህ፣ ትርክቶች ለብዙ ዓይነት ጥናትና ምርምር ጠቃሚ ስለሆኑ ይህን አምድ ከፍተን ዘመናዊ እና ጥንታዊ ተረቶችን እንደተገኙ እያተምን እናስነብባለን።
የሰምና ወርቅ መጽሔት አዘጋጆች
*1መፃጉዕ፤ ጎባጣ፣ በጀርባው ላይ ሻኛ ያለው ደረቱ ከጉልበቱ ጋር የተጣጋ ሕመምተኛ በሽተኛ። [ዐዲስ አማርኛ መዝገበ ቃላት፤ ደስታ ተክለ ወልድ]
*2 መጋቦች= መጋቢዎች ለማለት ነው።
ስዕሉን የሰራልን፤ ሰዓሊ መሠረቱ ወንዴ ነው።