“የዘርአ ያዕቆብ (ወርቄ) እና የሬኔ ዴካርት ፍልስፍና” (ፈንታሁን ጥሩነህ)

ዘርአ ያዕቆብ ከአክሱም የመነጨ ፈላስፋ ነው። ዴካርት ደግሞ ከፈረንሳይ ሀገር ይመነጫል። ሁለቱም ፈላስፋዎች በአንድ ዘመን ኖረዋል። በትውልድ ዓመትም ብዙ አይራራቁም። … ሬኔ ዴካርት የሚታወቀው የመጀመሪያ ፈረንሳዊ ብሎም አውሮጳዊ ፈላስፋ በመሆኑ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ዘርአ ያዕቆብ እስካሁን ያለውን መጠነኛ ታዋቂነት ያገኘው ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ ከግዕዝ ወደአማርኛ ተርጉመው ባሳተሙት ፤ ሐተታ ዘዘርአ ያዕቆብ አክሱማዊ ወወልደ ሕይወት እንፍራዛዊ በተሰኘው መጽሐፍ ሳቢያ ነው።

ፍልስፍናና ፈጠራ

ኢትዮጵያውያን የራሳቸው ፍልስፍና ሆነ የመፈላሰፊያና የፈጠራ ዘዴና ዘይቤ የላቸውም የሚል አስተሳሰብ ለብዙ ጊዜ ሲነገር የቆየ ነው። ብዙዎቻችን ይህንን አስተሳሰብ ያለምርምር አምነንበት ኖረናል። ይህ በኢትዮጵያውያን ላይ የተሰነዘረው አመለካከት ምንጩ የት እንደሆነ ማወቅ ባያዳግትም በተጨባጭ ለማሳየት የሚረዳንን የጀርመኑን ፈላስፋ የሔግልን ጽሑፍ እንጠቅሳለን። ሔግል ስለአፍሪቃውያን በጅምላ የሰጠው አስተያየት እንዲህ ይላል፤