መጽሐፈ ምሳሌ ዘጨዋ ተረት  

ይህ መጽሐፍ ያልታተመና በዩናይትድ ስቴትስ የኮንግሬስ ቤተመጻሕፍት ውስጥ በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ዋና ክፍል የኢትዮጵያና የኤርትራ ሃገራት የመጻሕፍት ክምችት ክፍል ከሌሎች ካልታተሙ የግእዝ፣ የአማርኛና የትግርኛ መጻሕፍት ጋር ይገኛል። የተጻፈው በ1911 ዓ.ም ሲሆን ተረቶቹን በጽሑፍ ያሰፈረው የንጉሥ ወልደጊዮርጊስ አሽከር ነኝ የሚለው ነጋዴው አቶ አበሩ የተባለ  የማጂ ከተማ ነዋሪ ሰው ነው። ይህን ያጠናቀረውን የጥንት ተረት መድብል ለወዳጁ  ለእንግሊዝ መንግሥት መኮንን ለሜጀር አጥሒል [Athil] ሲያበረክት በመጽሐፉ ላይ ተጽፎ እንደተገኘው፣ “ ይህን እያዩ እንዲያስታውሱኝ” ከሚል ማሳሰቢያ ጋር ነበር። በዚህ መድብል ውስጥ በወረቀት ላይ ተጽፈው የተገኙ ተረቶች አስራ ሁለት ያህል ናቸው።

እነዚህን ጥንታዊ ተረቶች አንድ ባንድ አከታትለን የምናወጣበት ምክንያት የምንወርሳቸውንና የማንወርሳቸውን ለይተን ለማወቅ እንዲረዳን ነው። በተረቶች ውስጥ ታምቀው የሚገኙት አስተሳሰቦች ተረቶቹ በተፈጠሩበት ዘመን የነበረውን ደማቅ አስተሳሰብ ለመሰለቅ ሆን ብለው የተፈጠሩ ናቸው። በተረት መልክ ሲቀርቡም ለዛ እንዲኖራቸውና ለወጣት ልጆችም አስተሳሰቡን ለማስተላለፍ ቀላል እንዲሆን በማሰብ ነው። እነዚህ በተለያዩ ተረቶች አማካኝነት የቀረቡልን አስተሳሰቦች ላሁኑ ዘመን የሚጠቅሙ መሆን አለመሆናቸውን ለይቶ ማወቅ የኛ ፋንታ ነው።ይጠቅማል አይጠቅምም የሚል የተለያየ የአመለካከት ዘርፍ ሊኖር ይችላልና ተረቶቹ ቀርበው መነበባቸው ጥቅም- አልባ አይደለም ብለን እናምናለን።  ያም ሆነ ይህ፣ ትርክቶች ለብዙ ዓይነት ጥናትና ምርምር ጠቃሚ ስለሆኑ ይህን አምድ ከፍተን ዘመናዊ እና ጥንታዊ ተረቶችን እንደተገኙ እያተምን እናስነብባለን። 

የሰምና ወርቅ መጽሔት አዘጋጆች 

ስዕሉን የሰራልን ሰዓሊ መሠረቱ ወንዴ

ተረት  ተረት፤ 

  

አንድ ድኃ ሰው ነበረ ፤ ሰባት ልጆች አሉት ።  ከነሚስቱ ዘጠኝ ሁኖ መደብር ተከራይቶ ዘግቶ ከልጆቹና ከሚስቱ ጋር ሁኖ በመብራት ልብስ ሲሰፋ ነበረ ይላሉ። የሀገሩ ንጉሥ ሕዝቡን ለመሰለል ጨርቅ ልብስ ለብሶ ከቢትወደዱ ጋር  ማታ፣ ማታ ሽርሽር ይሄድ ነበር ይላሉ። ከዚያ ከድኃ ቤት ደርሶ ቁልፍ በሚያስገባበት ቀዳዳ ጎንበስ ብሎ ቢያይ ያ ድኃ ከነልጆቹ ሲሰፋ“እግዚአብሔር ያልሰጠው ሰው አይከብርም” እያለ ልብስ ሲሰፋ ንጉሡ ሰማው። ንጉሡም ለቢትወደዱ “ይህን ድኃ ሰው ክቡር አደርገው ዘንድ እችላለሁ፤ አሳዝኖኛልና” አለው፤ ቢትወደዱም “እንጃ፣ ይሆንልዎ አይመስለኝም” አለው። ንጉሡም “ይህን ሁሉ ግዛትና ገንዘብ በእኔ እጅ ሁኖ እንዴት አልችልም!” አለውና የዚያን የድኃ ቤት በማኅተሙ ከመዝጊያው አተመበትና ወደቤቱ ሄደ። በማግስቱም ንጉሡ እንዲህ ያለ ቦታ ማኅተሜን ታገኛላችሁና  ያንን ድኃ አምጡት ብሎ አዘዘ። ያም ድኃ ምን ተሰምቶብኝ ይሆን እያለ ሲንቀጠቀጥ ሄደ። ንጉሡም “አይዞህ አትፍራ፤ ትላንትና ማታ ምን ትናገር ነበር” አለው። ድኃውም “እግዚአብሔር ያልሰጠው ሰው አይከብርም” እያልሁ እሰፋ ነበር አለው። ይህ ንጉሥ አንድ እንክብል ወርቅ ለቡኸር* አጉርሶ ከሆዱ ወርቁን ያገኝለት መስሎት እንካ ወስደህ አርደህ ብላ ብሎ ሰጠው። ያም ድኃ የዚያ የቤቱ ኪራይ ደርሶበት ነበርና ለቤቱ ጌታ ማማለጃ እንዲሆነው ቡኸሩን ሰጠው። የቤቱ ባለቤትም ቢያርደው ተጠቀመ። ንጉሡም ይህን ነገር ሰምቶ ተናደደና ደግሞ አጋዘን** ወርቅ አጎረሰና አርደህ ብላ ብሎ ሰደደለት፤ ድኃውም እንደፊተኛው  ለቤቱ ጌታ ማማለጃ ሰጠው። ንጉሡም ይህን ሰምቶ ተናደደና ሶስተኛ ወርቅ በዳቦ ውስጥ አድርጎ ለዚያ ድኃ ስጡት እርቦታልና ይብላ ብሎ ላከበት ። ያም ድኃ ባዶ ባዶውን ለራሱ አስቀረና ያን ወርቅ ያለበትን ዳቦ ለዚያ ለቤቱ ጌታ ማማለጃ ሰጠው። ንጉሡም ይህንን ሰምቶ ተናደደና በሀገሩ አዋጅ አደረገ፤ድኃ ሁሉ እንዲሰበሰብ አዘዘ። ከዚያ ሁሉ ከተሰበሰበ ድኃ ያ ልብስ ሰፊ ሰው ቀረ። ንጉሡም ያንን ድኃ አምጡት ብሎ አስመጣውና አምስት ድንጋይ ወርቅ አሳየው። “ይህ ሁሉ ደንጊያ ወርቅ ነው፤ ቤት የምትሰራበት ቦታ እንድሰጥህ፣ በል ድንጋይ አንሳና ወርውረህ ባረፈበት ቦታ ከልዬ እሰጥሃለሁ” አለው። ያም ድኃ ድንጋዩን አነሳና ሲወረውረው የገዛ ራሱ አሰናከለውና ከፊቱ አረፈ። ያም ንጉሥ ቢትወደዱ “እንጃ ይሆንልዎ አይመስለኝም” ብሎት ነበርና ነገሩን አደነቀለት ።  እግዚአብሔርም ለንጉሡ፤ “እኔ ያልሰጠሁትን አንተ ታከበርከው ልግደለውና አስነሳው” ብሎ ድኃውን ሰው ገደለው። 

ይልቁንም ይባላል፤ ክብረት*** አለእግዚአብሔር ፈቃድ አይገኝም

*  ቡኸር ወይም ብሖር፣- የዋላ የድኩላ ዐይነት፤ የበረሓ የዱር ፍየል። [ዐዲስአማርኛ መዝገበ ቃላት፤ ደስታ ተክለ ወልድ] 

** አጋዘን –  የዱር በሬ፣ ቀንዳም፣ ቀንደ ረጅም። [ዐዲስ አማርኛ መዝገበ ቃላት፤ ደስታ ተክለወልድ] 

*** ክብረት – ሃብት፣ ንብረት፣ መከበር

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.