
አንድ ሰው ከሰማውና ካየው በቀር የሐሠት ነገርና ክፉ የማይወጣው ጥንቁቅ ሰው ነበር ይላሉ። ሁልጊዜ ከሐሠት ይጠነቀቅ ነበርና ሰዎች ሊፈትኑት ፤ አንድ ጎበዝ ግማሽ ራሱን ላጭቶ ግማሹ ጉተና የሆነ፤ አንድ ፈረስ ግማሹ ጎን ሐመር፣ ግማሽ ጎኑ ነጭ በለቅ? የሆነ ያንን ጎበዝ አስበው እሱ በሚያልፍበት መንገድ ሂድ አሉት ። ጎበዙም የተላጨውን በወዲያ፣ ጉተናውን በሰውየው በኩል ፤ እንዲሁም የፈረሱን ሐመር ጎኑን በሰውየው በኩል እየሳበ አለፈ። ከዚህ በኋላ የፊተኞቹ ሰዎች እውነት ተናጋሪውን ሰው መጡና “እንዴት ውለሃል”አሉት ። “በዚህ መንገድ ጉተና ጎበዝ ሐመር ፈረስ የሳበ ሲሄድ አየህን” አሉት ። እርሱም “እኔ በማየው ጎበዙ [ልጁ] ራሱ ጉተና ነው፤ በማላየው በኩል ልጩ ቢሆን ወይም ጉተና ቢሆን አላውቅም፤ ፈረሱም እኔ በማየው በኩል ጎኑ ሐመር ነው። እኔ በማላየው በኩል ጎኑ ሐመር ወይም ሌላ ቢሆን አላውቅም አላቸው።

ደግሞ ሁለተኛ አንዲት ሴት ልጅ የወንድ ልጅ ልብስ አልብሰው፣ ሱሪ አስታጥቀው፤ አንድ ጎፈር በግ ግማሽ ጎኑን ሸልተው በዚህ በሰውየው ፊት በጉን እየሳብሽ እለፊ አሏት፤ ልጅቱም እንደአዘዟት በፊቱ እየሳበች አለፈች ። ከዚህ በኋላ ፈታኞች መጥተው “እንዴት ዋልክ”አሉት ። “ጥቁር ጎፈር በግ የሳበ ልጅ አየህን?” አሉት ። እርሱም፣ “እኔ በማየው በኩል በጉ ጥቁርና ጎፈር ነው፤ እኔ በማላየው በኩል በጉ ጥቁር ወይም ነጭ ቢሆን አላውቅም ። የተሸለተ ቢሆን ወይም ጎፈር ቢሆን አላውቅም፤ ልጁ ግን እንደ ወንድ ልጅ ታጥቋል፣ ለብሷል ። በውነት ወንድ ልጅ ቢሆን ወይም ሴት ልጅ ብትሆን አላውቅም”አላቸው።

ደግሞ በዚህ እንዳሸነፋቸው ባዪ ጊዜ ለሶስተኛ ጊዜ አንድ ወንድ ልጅ የሴት ልብስ አልብሰው እንደ ሴት ልጅ ትጥቅ አስታጥቀው፣ በመልካም ሞሰብ ውስጥ በዝብዱ* ገንፎ አድርገው ያንን ልጅ አሸክመው በዚህ ሰውየ ፊት እለፍ አሉት ። ልጁም እንዳዘዙት አድርጎ ሞሰቡን ተሸክሞ በፊቱ አለፈ። ከዚህ በኋላ እንዳመላቸው ፈታኞቹ መጡና ፣ “እንዴት ዋልህ”አሉት፡፡ “ በዚህ በመንገድ እንጀራ በመሶብ የተሸከመች ልጅ ስታልፍ አየህን?” አሉና ጠየቁት ። እርሱም፣ “የሴት ልጅ ልብስ ለብሳለች፤ እንደሴትም ታጥቃለች፤ በውነት ግን ሴት ልጅ ብትሆን ወይም ወንድ ልጅ ቢሆን አላውቅም። መሶብ መሸከሟን አይቻለሁ፣ በውስጡ ያለው እንጀራ ቢሆን ወይም ሌላ ነገር ቢሆን አላውቅም”አላቸው። እነርሱም አፍረው ተመለሱ ይላሉ።

ምሳሌው፤ አዋቂ ይበሉኝ ብለህ ያላየኸውን አየሁ አትበል። የማታውቀውን አውቃለሁ ማለት አይገባም።
ስዕሎቹን የሳለልን፤ መሠረቱ ወንዴ
የቅንብሩ ተባባሪ፤ ወ/ት መቅደስ
ዝብድይ= እግራም ጣባ፤ ወይም ወጭት፤ የዝባድ ፣ የለስታ ቅቤ መቀበያ


