ተዝካረ ሕይወት – አህመድ ኑር (1949 – 2014 ዓ.ም)

አቶ አህመድ ኑር፤ የሃገሩ ነገር የሚያንገበግበው ፣ የሚቆረቁረው፣ እምነቱንም የሚወድና የሰውን ልጅ ባጠቃላይ የሚያከብርና ጓደኞቹን የሚወድ፤ ባንፃሩ ደግሞ በሰው ዘንድ ተወዳጅ የነበረ ወንድማችን ነበር። የአቶ አህመድ ኑር ነገር አዋቂነት በወዳጆቹ ዘንድ ይታወቃል። ተረትና ምሳሌ በየንግግሩ መሃል እያስገባ የሚናገርበት ልዩ ብሂል ነበረው። ባማረ ጥርሱ ስቆ ማሳቅን ያውቅበት ነበር። በሚጽፋቸው ግጥሞቹ ግጥም የመግጠም ልዩ ችሎታ እንደነበረው ገላጭ ናቸው። በተለይም ስለኢትዮጵያ ስብሰባ ሲደረግ ሁሉንም ነገር ጥሎ የሚሳተፍ ነበር። በየስብሰባዎች ላይ የሚያነሳቸው ጥያቄዎቹ ሁሉ ጥበብን የተሞሉና ማንንም የማይጎዱ ከአሽሙርና ከአግቦ አገላለጾች ነፃ የሆኑ ቀጥተኛ ነበሩ። ከወሎ ማደጉን እንደትልቅ ነገር የሚያወሳው አቶ አህመድ ኑር የወሎን ዙሪያ ባህልና የንግግር ዘዬ አሳምሮ መግለጽ በመቻሉ የወሎ አምባሳደር የሆነ ያህል ያስቆጥረው ነበር። በተለይም ወሎን የሚመለከት ማኅበር ሲቋቋም ሳየመነታ አባል የመሆንና የመሳተፍ ጉጉት ይታይበት ነበር። እንዲሁም ኢትዮጵያን አስመልክቶ በሚቋቋሙ ማኅበራት አባል ሆኖ በሚቻለው ለመሳተፍ ሳያመነታ ስለሚጥር ሰምና ወርቅ መጽሔት በተቋቋመበት ጊዜ እንዳወቀ አባል መሆንና የማገዝ ፍላጎት በማሳየቱ የመጽሔቱ የቦርድ አባል ሆኖ አገልግሎት አበርክቷል። ከዚህም በተጨማሪ የመጽሔቱ የስርጭት ኃላፊ በመሆን ተግቶ ሰርቷል።

አቶ አህመድ ኑር የተወለደው በደሴ ከተማ፣ ወሎ፣ ኢትዮጵያ በ1949 ዓም ላይ ነበር። አቶ አህመድ በወጣትነቱ ከታላቅ ወንድሙ ጋር በደሴ ከተማ ልዩ ስሙ “ጀምስ ቦንድ” ተብሎ በሚታወቅ የልብስ መደብር ሲሰራ ይታወቃል። በአብዪቱ ወቅት በኢ ሕ አ ፓ ውስጥ የተሳተፈ

መሆኑን የገለጸልን አቶ አህመድ ኑር በተሳትፎው ምክንያት ለስደት እንደበቃና በፈረንሣይ ሃገር ከመሰል ኢትዮጵያውያን ጋር በስደት ለብዙ ዓመት በቆየበት ጊዜ በተለያየ መንገድ ስደተኞችን እያዝናና እና እያገለገለ ተወዳጅነትን እንዳተረፈ ብዙዎች ይመሰክሩለታል። ከዚያም ወደ ሰሜን አሜሪካ ተሰዶ ከመጣ ወዲህ በቨርጂኒያ እስቴት ከወ/ሮ ገነት ጋር ትዳር መስርተው ልጆች አፍርተዋል፤ የልጆቻቸው ስሞችም፣ ብሌን አህመድ፤ ሳራ አህመድ፤ አይዳ አህመድ ይባላል።

የኢ ሕ አ ዴ ግ ወደ መንግሥት ሥልጣን መውጣት በኋላ አቶ አህመድ በሽርክና ይሰራበት የነበረውን ንግድ ዘግቶ ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ተነሳ። አዲስ አበባ ተመልሶ በሄደበት ጊዜ [ለመሄድ ሲንደረደር] “አንድ ኢትዮጵያ?” የሚል ግጥም ደርሶ በየሚዲያው አሰምቷል። ይህ ግጥም በህይወቱ ላይ ጉልህ የሆኑ ለውጦችን አሳይቷል። በ1993 ዓም ለህዝብ ተወካዪች ምክር ቤት ምርጫ ባቲ ወረዳን በመወከል ለመመረጥ ጥረት አድረጓል። የወከለው ድርጅት ስም “የኢትዮጵያ ሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ [ኢሰዲፓ]” አርማውን ጀበና አድርጎ ነበር ለምርጫ ያቀረበው።

ለጥቂት ዓመታት አዲስ አበባ በኖረበት ጊዜ የልብ ምች[ ድካም] አደጋ ስለገጠመው ወደሰሜን አሜሪካ ተመልሷል። በቨርጂኒያ እስቴት ህክምና በሚያደርግበት ረጅም ዓመት የተለመደ ትጋቱን ከማሳየት አልተቆጠበም። ሆኖም ግን በልብ ምች [ድካም] ምክንያት ግራ እጁንና እግሩን ሸምቅቆ የያዘው በሽታ በጠና አሰቃይቶታል ፤ የልቡንም ለመፈጸም እክል ፈጥሮበታል። በተከታታይ ዘመኖቹ ከታክሲ መንዳት ሥራ አቋርጦ፣ በመንግሥት ድጎማ የሚተዳደር ሰው ሆነ። ህመሙ እየቀጠለ ሲሄድ በህመምተኝነት ለረጅም ጊዜ በሆስፒስ እየተረዳ ቆይቶ[ January 30, 2022] ላይ በ65 ዓመት እድሜው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። በቀብሩ ሥርዓት ቁጥራቸው በርከት ያሉ አብረውት ፈረንሳይ ሃገር የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን ተገኝተዋል። የተቀበረበት እለት [February 2፣ 2022] ሲሆን የቀብሩን ሥነ ሥርዓት ያቀነባበረው – ፈርስት ሄጂራ ፋውንዴሽን ድርጅት ነው። የተቀበረበት አድራሻም፤ 9900 Braddock Road Fairfax, VA 22032 ነው።

የውድ ወንድማችንን ነብስ ፈጣሪ በገነት ያሩርልን፤ ቤተሰቦቹንና ወዳጆቹን ሁሉ መጽናናትን እንመኝላቸዋለን።

የሰምና ወርቅ መጽሔት ዝግጅትን በመወከል፣ ፈንታሁን ጥሩነህ ።

ከዚህ ቀጥሎ የታወቀበትን ግጥሙን ማስታወሻ ይሆን ዘንድ አቅርበነዋል።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.