
ከሰምና ወርቅ አዘጋጅዎች ፡–
ይህን የኣቶ ዳምጤ አሰማኸኝን በራሳቸው የተጻፈ የህይወት ታሪክ ያገኘነው ከአቶ መሰለወርቅ ግርማ ነው። ለዚህም አስተዋጽዖ አቶ መሰለወርቅን እናመሰግናለን፡፡
ጽሑፉ ለአንድ ለጻፉት ሰፊ መጽሐፍ መግቢያ እንዲሆን ያዘጋጁት ነበር። መጽሐፉን የሚያትም ወይም የሚያሳትም እስኪገኝ ድረስ ታሪካቸውን አትመን እንዲታወቅ ማድረግ ስለፈለግን የአቶ መሰለወርቅን ፈቃድ ጠይቀን ስልተፈቀደልን አትመነዋል። የታዋቂ ግለሰቦች ግለታሪክ እንዲጻፍ፣ የተጻፈውም እንዲታተም የምናበረታታውን ያህል፣ ተጽፈው ያገኘናቸውን አትመን እንዲታወቁ ማድረግ ካለን ዓላማ ጋር የተያያዘ ነው።
አቶ ዳምጤ በኖሩበትና በሰሩበት ሁሉ ያጋጠማቸው ገጠመኝ ሁሉ እጅግ የሚያስገርም ከመሆኑ ሌላ እግረመንገዱን አያሌ ጠቃሚ ታሪካዊ ቁምነገሮችን ያቀፈ በመሆኑ ለታሪክ ማሟያ ይሆናል ብለን እናምናለን። እርሳቸው በጻፉት ላይ ስህተት አለ የሚል ተቃዋሚ ቢኖር ጽፎ ከላከልን የምናትም መሆናችንን እናስታውቃለን።
ከመሰለወርቅ ግርማ
አቶ ዳምጤና እኔ የተገናኘነው በባለቤቴ አባት በኮረኔል ካሳዬ ወልደ ጊዮርጊስ በኩል ነበር። አቶ ዳምጤ አጅግ በጣም ግሩም ሰው ነበሩ። የብዙ ልጆች አባትም አንደሆኑ ነግረውኛል። እዚህ አርሊንግተን ቨርጂኒያ አብረዋቸው ሳሉ በቅርብ የማውቃቸው ሴት ልጃቸውንና ባለቤቷን ነበር።
አቶ ዳምጤ አለባበሳቸው ለየት ያለ እንደነበር ትዝ ይለኛል። ከባርኔጣቸው ጀምሮ አስከ ጫማቸው ድረስ ቀለሙ አንድ አይነት እና ድብልቅ የሌለበት ልብስ ይለብሱ ነበር። ከላይ እስከታች አረንጓዴ ለብሰው የሚወጡበትን ቀን ሳስበው ይገርመኛል። እንዲያም ሆኖ ግን ሽክ ብለው ሳይለብሱ አይቻቸው አላውቅም።
አቶ ዳምጤ ጨዋታ አዋቂ ነበሩ። ቀልዳቸውም ሆነ ቁም ነገራቸው ጊዜና ቦታውን የሚመጥን መልክ ነበረው። በኮርያ፣ በኮንጐ የነበረውን ወታደር ለማበረታታት ይጽፏቸው የነበሩትን አስቂኝ ቀልዶቻቸውን፣ ሁለት መቶ ገጾች ካሉት መጽሀፋቸው ውስጥ ለቡና በተገናኘን ቁጥር ያነቡልኝ ነበር። የሰሙትን ሰብስቦ የማጠናቀር ችሎታቸውም እንዳደንቃቸውና እንድቀናባቸው ያደርገኝ ነበር።
አኝህ ትልቅ ሰው ደራሲ፣ ገጣሚ እና ተርጓሚ ነበሩ። ከሃገራችን ቋንቋዎች አማርኛና ኦሮሚኛ፣ ከውጭው ደግሞ ጣሊያንኛና አንግሊዝኛ ተናጋሪና አስተርጓሚ ነበሩ። በተጨማሪም፣ “ወታደርና ጊዜው” የሚባለውን መጽሔት ከሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ ጋር በመተባበር ያዘጋጁ ነበር።
ወደ አሜሪካም ሲመጡ ከቃጠሎ ያተረፏቸውን አራት የታተሙ መጻሕፍት ለlibrary of congress ማበርክታቸውን ነግረውኛል፡፡
አቶ ዳምጤ የሕይወታቸውን ዘመን በአስተማሪነት፣ በጦር ሜዳ ጋዜጠኝነት፣ በአስር ቤትና በበቀል ቅጣት እንግልት፣ በመጨረሻም በስደት እንዳሳለፉት አውግተውኛል። “ከውድ ባለቤቴና ልጆቼ ጋር መልካም ጊዜ ሳይኖረኝ አዚህ ደረስኩ” አያሉ አይናቸው አንባ አዝሎ ሲያጫውቱኝ፣ “አይዞዎት” ከማለት በስተቀር መጥፎ ትዝታዎቻቸውን የምበርዝባቸው ሻካራ ህይውታቸውን የማለሰልስባቸው ቃላት ይጠፉኝ ነበር።
“የተዘጋው ምዕራፍ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ከዳግማዊ ሚኒሊክ እስከ ታህሳስ ግርግር” የተሰኘውን፣ በ1992 ዓም ተዘጋጀቶ ያልታተመውና የእጅ ጽሑፍ መጽሐፋቸውን፣ የመጀመሪያውን መድብል ተይቤ በህይወት እያሉ አስረክቤአቸዋለሁ። በአደራ የሰጡኝ እኔ በኮምፒውተር የሰራሁላቸው አሁንም ቅጅው ከእኔ ዘንድ ይገኛል። መጽሐፉን ለማሳተም ሳይችሉ ከዚህ አለም በሞት ተለዩን።
የዚህ መጽሐፍ ቀሪዎቹ ስድስት መድበሎች በእጃቸው እንደነበሩ ኣስታውሳለሁ። ዝርዝሮቹንም አዚሁ መጽሐፍ መግቢያቸው ላይ አኑረውታል።
የሕይወት ታሪካቸው ባጭሩ ይህን ይመስል ነበር። ያልታተመው መጽሐፋቸው ተረስቶ የመቅረት እድል እንዳያጋጥመው እፈራለሁ። ታትሞ ማየት እጓጓለሁ፡፡
መሰለወርቅ ግርማ
መስክረም 2013 ዓም (9/22/2020)



















የአቶ ዳምጤ ታሪክ በጣም መሳጭ ነው።ስላደረሳችሁልን በጣም እግዜር ይስጣችሁ። ነገር ግን ይኸው ብቻ ነው ወይ ? አምስቱ (ስድስቱ) ቮሊዩምስ ? የት ነው የሚገኘው ? እግዜር ይስጥልኝ !አስታጥቄ ለገሠ።Sent from my T-Mobile 4G LTE Device
LikeLike
ሰላም አቶ አስታጥቄ፤ ይህ የአቶ ዳምጤ አጭር የህይወት ታሪክ የተገኘው አቶ ዳምጤ ከአቶ መሰለወርቅ ጋር ተገናኝተው በነበረ ጊዜ አቶ መሰለወርቅ አማርኛ የመተየብ ችሎታ ስለነበረው እባክህ ጽሑፎች አሉኝ በመጽሐፍ መልክ ማውጣት የምፈልጋቸው ብለው ጠይቀውት እሺታውን ካገኙ በኋላ ከነበሯቸው የመጻህፍት ንድፎች መካከል የመጀመሪያው የሆነውን “የተዘጋው ም ዕራፍ ” ብለው የሰየሙትን መድብል እንዲተይብላቸው በሰጡት ጊዜ ከዚህ የመጀመሪያው መድብል መግቢያ ላይ ይህ የርሳቸው አጭር የህይወት ታሪክ ተገኘ። ይህን እንደመግቢያ ተጠቅመው ተያይዞ ግን አንደኛው የኢትዮጵያ ታሪክ መድብል ይቀጥላል። አቶ መሰለወርቅ ይህን አንዱን መድብል ተይቦ እንደጨረሰው ለራሳቸው መልሶ ሰጥቷቸው ነበር። ወደሁለተኛው መድብል ሳይገቡ እርሳቸው በሞት ተለይተዋል። የመጀመሪያው መድብል ቅጅ ግን ከአቶ መሰለወርቅ ጋር እንዳለ ነግሮናል። ይህን አጭር ታሪካቸውን ያወጣንበት አንደኛው ምክን ያት ምንልባት ቤተሰቦቹ ወይም እነርሱን የሚያውቅ ሰው እንዲነግራቸውና በእጃቸው ያለው ስድስት መድብል ታትሞ እንዲወጣ ለማበረታታት ስንል ነው። ስለዚህ ቤተሰቦቹን የሚያውቅ ሰው ቢያገኛቸውና ቢያበረታታቸው የርሳቸው ልፋት ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር ሁላችንም ተባብረንም ቢሆን እንዲታተም የማድረጉን ጥረት እናዳርግ ነበር። አቶ መሰለወርቅ በበኩሉ በእጁ የሚገኘውን የመጀመሪያውን መድብል እንዳያሳተመው የቤተሰቡ ፈቃድ አስፈላጊ ስለሆነ ገደብ ሆኖበታል። ባጭሩ ታሪኩ እንደዚህ ነው። ምኞታችን 6ቱ መድብሎች ተራ በተራም ሆነ ባንድነት እንዲታተሙና ለህዝቡ እንዲቀርብ ነው። ስለአስተያየቶት በጣም እናመሰግናለን።
የሰምና ወርቅ የጥናትና ምርምር መጽሔት አዘጋጅ ክፍል።
LikeLike