የዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ የሕይወታቸው መጨረሻ ሰዓት እና የመቅደላ ዝርፊያ

በስፍራው በአካል በመገኘት የአሜሪካን ጋዜጠኛ የዘገበው

ትርጉም፤ በቆንጂት መሸሻ

ሁለት የእንግሊዝ  ወታደሮች ከሳር ድርቆሽ ክምር አጠገብ አንድ ሽጉጥ የጨበጠ  ሰው ይመለከታሉ። ሊተኩሱ ሲደቅኑበት በአያቸውም ጊዜ ከክምሩ በስተጀርባ ይሰወራል። ቀጥሎም በእርግጥ ተኩስ ይሰማሉ። ተኩስ ከሰሙበት ቦታ ሲደርሱ ከሳሩ ድርቆሽ ክምችት አጠገብ ያዩት ሰው መሬት ላይ ወድቆ፣ ተዘርግቶ በቀኝ እጁ ሽጉጡን እንደጨበጠ ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ ላይ ሆኖ ያገኙታል።

ሽጉጡ ሰደፍ ላይ በብር የተለበጠ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:-

ከታላቋ ብሪታንያ እና አየርላንድ ንግሥት፤

ንግሥት ቪክቶሪያ፤

    ለአገልጋዬ ፕላውደን ለለገሱት ርህራሄ

ምስጋና  ይሆን ዘንድ፤ ይህ አነስተኛ መታሰቢያ

            ለቴዎድሮስ የአቢስኒያ ንጉሠ ነገሥት

ተበረከተ

1854

ይህ ፍንትው ብሎ የተገለጸ ታሪክ፣ በ1874 [1866 ዓ.ም]  ሄንሪ ኤም. እስታንሊ የተባለው የኒውዮርክ  ሄራልድ ጋዜጣ ተቀጣሪ  እንደ አውሮፖ አቆጣጠር በ1868 በጄኔራል ሮበርት ናፕዬር የተመራው የእንግሊዝ ጦር ጋር ወደ ኢትዮጵያ  በመጓዝ ያከናወነውን “ኮማሲ እና መቅደላ” በተሰኘው የሚመስጥ መጽሐፉ የመዘገበው ነው። ይህ አጭር ጽሑፍም የተጻፈው የንጉሡን ሕይወት ማለፍ ተከትሎ እስታንሊ በገጽ  449-464 ያሰፈረውን ሀተታ ማስረጃ  መሰረት በማድረግ ነው። በተጨማሪም በእውን ያያቸውን ከመቅደላ የተዘረፉትን ቅርሶች ገጽ 454-462 በዝርዝር ያስቀምጣል። የእንግሊዝ ጦር ወደ ኢትዮጵያ የዘመተበት ምክንያት ንጉሡ ለንግሥት ቪክቶሪያ የሁለቱ ሃገራት ወዳጅነት መመስረት እና መጠናከር በተመለከተ ለጻፉላቸው ደብዳቤ መልስ ስለተነፈጋቸው፣ በአጸፋው ያሰሯቸውን የእንግሊዝ መልክተኞች ከእስር ለማስፈታት መሆኑ ሊታወስ ይገባል።

 ጸሐፊው እስታንሊ በመቀጠል እንዲህ ይተቻል:-

የአጼ ቴዎድሮስ ሬሳ የእንግሊዝ  ጦር ከቆመበት መሀከለኛ ስፍራ ተወስዶ ነበር። በሰዓቱ የእንግሊዝ ሰራዊት መቅደላን በሙሉ ተቆጣጥረው በደስታ “ንግሥታችን  ትባረክ!” እያሉ ሲደነፉ እና  በደስታ ሲጮሁ ይሰማ ነበር።

በዚህ ሰዓት ንጉሡ ክፉኛ ቆስለው በማጣጣር ላይ ቢሆኑም ሕይወታቸው አላለፈም ነበር። ይህን የተመለከቱ የሐገሩ ሰዎች ስማቸውን እየጠሩ ሲጮሁ ማንነታቸው ተገለጸ።

ጸሐፊው ሲቀጥልም በድኑን በዚህ ዓይነት ይገልጸዋል: ….” የሃገሩ ተወላጅ: ሰውነቱ በረሃብ የተዳከመ፣ ከወገቡ በላይ መናኛ ያገለገለና የተቀደደ እጀጠባብ የለበሰ፤ ከውስጥ ደግሞ አዳዲስ  ልብስ” በዒላማ ተኳሽ እንዳይመታም ተራ ሰው በመምሰል ሲዋጋ የነበር።

መልኩ ጠይም፣  ከንፈሮቹ ቀጠን ጠበብ ያሉ፤ ጥርሶቹ በጣም የነጡ ናቸው። ስልክክ ያለ አፍንጫውም ትንፋሽ እየከዳችው መሆኑ ይታያል። ፊቱ ሰፋ  ያለ፤ ጉንጭ እና ግንባሩ  የጎላ፣ ቅንድቡ የተሟላ ነው። ጸጉሩም ለሦስት ተከፍሎ ከፊት ወደ ኋላ ሹርባ ተሠርቶአል።

ሰውነቱም ደረተ ሰፊ እና ጡንቻማ  ሲሆን የበድኑ ቁመትም “5ፊት ከ8 ኢንች” (1.8 ሜትር) ይሆናል።”

ወዲያው በተደረገው የሬሳ ምርመራ:  “ቀኝ እግራቸው ቀላል  ቁስል ሲታይበት  በአፍ ወደ ውስጥ የተተኮሰው ጥይት ግን የውስጥ አፋቸውን አቃጥሎ፣ ላንቃቸውን አውድሞ፣ ማጅራታቸውን በስቶ እንደ ገደላቸው ታወቀ።” በዚህም ሕይወታቸው ያለፈው ጥይት በመጠጣት መሆኑ ተረጋገጠ።”

የንጉሥ ቴዎድሮስ በድን መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ፡..

“የአየርላንድ ወታደሮች እግራቸውን በመያዝ እያንገላቱ ጎትተው ወደ ድንኳኑ ወሰዱት፣ በዚያም የመጨረሻ ትንፋሻቸውን ተነፈሱ።”

በቦታው የነበሩት የእንግሊዝ ወታደሮችም ያላግጡባቸው ነበር።  “ነገር ግን ከመሃከላቸው አንዱ እርቃናቸውን ሸፍኖ፣ ክንዳቸውን አጥፎ፣ እጃቸውን ደረታቸው ላይ አሳረፈ።”  ወዲያውም ለማየት  የተሰበሰበው ሰው ብዛት እየጨመረ ሔደ፤ ከሰዎቹ መሃከልም የቀድሞ  እስረኞቹ ተመልክተው ማንነታቸውን አረጋገጡ።

ሰር ናፕዬር በፈረስ ተቀምጠው ሬሳውን ለማየት መጡ፤ ተመለከቱ። ምንም ዓይነት የርህራሄ ቃል አልተናገሩም።

ጸሐፊው ሲቀጥልም፣ ” እኔም  በሸራ ቃሬዛ ላይ ያረፈው የመቅደላው ጌታ ሬሳ ወደ አለበት ስፍራ በዝግታ ተራመድኩ።  ቅጥ ያጣ የወታደር ስብስብ እና ሌሎችም ሰዎች እርስ በእርስ እየተጋፉ በደም የተለወሰውን የቴዎድሮስ እጀ ጠባብ ቁራጭ ጨርቅ ለመውሰድ ሲታገሉ አየሁ። እርቃኑን እስኪቀር ድረስ ለሬሳው ጠባቂ አልተደረገለትም። በቃሬዛው እንደተንጋለለ የአእምሮ  ደካሞችና ባለጌዎች መዘበቻና መቀለጃ  ተደረገ።”  ጉዳዩን ሰር ናፕዬር እንደሰሙ ሬሳው እንዲለብስ እና ለማግስቱ ፍትሃት እንዲሁም ቀብር  እንዲዘጋጅ አዘዙ። ንግሥቲቱ በጠየቁት መሰረት በማግስቱ ሬሳው በግል ቄሳቸው ተፈትቶ በመቅደላ በሚገኝ ቤተክርስቲያን ተቀበረ።

የአጼ ቴዎድሮስ የሕይወታቸው የመጨረሻ ዕለት April 12 ቀን 1868 [ሚያዝያ 5 ቀን 1860 ዓ.ም] እኩለ ሌሊት ላይ የእንግሊዝ ጦር መሪ ጄኔራል  ናፕዬር  በማግስቱ፣ April 13 [ሚያዝያ 6 ቀን]  ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት እጅ ካልሰጡ ጦሩ እንደሚወጋቸው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሲደርሳቸው ይጀምራል።

ሚያዝያ 6 ቀን ጠዋት ቦግ ያለ ፀሀይ፣ ረፈድ ሲል ከባድ ዝናብና መብረቅ፣ ቀጥሎ ደግሞ ፀሀይ ስትጠልቅ  ድንቅ ውበት የታየበት ቀን ነበር።

የእንግሊዙ ጦር  አዝማች ንጉሡ እጅ እንዳልሰጡ እና ወደ ጎጃም ምድር አምልጠዋል የሚል የተሳሳተ መረጃ በመቀበላቸው የተነሳ ንጉሡን በሕይወት ወይንም በድናቸውን ይዞ ለሚያስረክብ የ50,000 ዶላር ሽልማት እንደሚያደርጉ መልእክት አስተላለፉ። ንጉሡ በመቅደላ ጀርባ እንዳያመልጡ ጥንቃቄ በማድረግ ሦስተኛ ድራጎን ብርጌድ የተባለውን “እንደ አጥር አሰለፉት።” በዚህ ዕለት ሚያዝያ 6 ቀን የእንግሊዝ ጦር ሙሉ በሙሉ ለጦርነት ዝግጁ ነበር። ጦሩ 1,600 አውሮፓውያን፤ 800 ቤሉቺስ፣ 800 ፑንጃቢስ፣ 42 ዝሆኖችና ሌሎችም ጭነት ተሸካሚ እንስሳት የተካተቱበት ነበር።

አዳዲስ መሳሪያ የታጠቀው  የእንግሊዝ ጦር በፍጥነት ገስግሶ የሥላሴን የፋላን ኮረብታዎች ተቆጣጥሮ ከቀኑ ስምንት ሰዓት መቅደላ ምሽግ በር ደረሰ። የመቅደላ መግቢያ በርን በሜዳ መድፍ ደበደቡት። ጸሐፊው እስታንሊ እንደጻፈው:- በዚህ ሰዓት ቴዎድሮስ በነጭ ፈረስ ተቀምጦ እየተዟዟረ የጠላትን ግስጋሴ እየተመለከተ የተመናመነ ጦሩን በጀግነት እንዲዋጋ ያበረታታ ነበር ይለናል። ንጉሡ ከፍ ባለ ድምፅ ሰራዊቱን “ግፉ! ተዋጉ! ሴት ይመስል እነዚህን ጥቂት ጦረኞች ለማጥቃት ፈራችሁ?” ይሉ ነበር። ይሁን እንጂ ከቅርብ የሚተኮሰው የመድፍ ብረት ኳስ ተዋጊውን ስለበተነው በአስቸኳይ ወደኋላ እንዲያፈገፍጉ ተገደዱ። ሆኖም ከጥቂት ታማኞች ጋር ሆነው የመቅደላን  ምሽግ ሰብሮ እስከገባበት የመጨረሻው ሰዓት ድረስ የጠላትን ጦር ገጠሙት።

አጼ ቴዎድሮስ ባለንጣዎቻቸው ላይ ይፈጽሙት የነበረ የጭካኔ ድርጊትን ለማሳየት በሚመስል አጻጻፍ እስታንሊ በApril 9 [ሚያዝያ 2 ቀን] 309 የተቀናቃኝ ሰዎችን ሬሳ ተመለከትሁኝ በማለት ይመሰክራል።

ከንጉሡ አሳዛኝ ሞት ቀጥሎ ዲሲፒሊን የነበረው የእንግሊዝ ጦር መረን ለቆ “ልዩ ልዩ የወታደር ቡድኖች ” በመፍጠር ለዘረፋ ተሰለፈ። እነእዚህ ለዝርፊያ የወገኑ ወታደር ቡድኖች  በመላው መቅደላ አምባ ተሰራጩ። የንጉሡን እቃ ቤት ግልብጥብጡን አወጥተው በዘበዙ። ወደ ንጉሡ መኖሪያ ቅጥር ግቢ ገብተው “የፈለጉትን ሲያነሱ ሲጥሉ፣ ኪሳቸው ሲከቱ፣ ያልፈለጉትን ሲወረውሩ በማከታተል ዘረፉ።”

እንደገለጻው የመቅደላ አምባ ላይ አልፎ አልፎ የሚታዩ ብዙ ልዩ ልዩ ዓይነት መኖሪያዎች ነበሩ።  በሀር ወይንም በሸራ የተሠሩ ድንኳኖች፣ ጎጆዎች፣ ዛኒጋባዎች እና የመንገድ አልጋዎች፣ ሌሎችም ነበሩ። “እያንዳንዱን መኖሪያ የከበበው ዘራፊ ቡድን ዓይናቸው ያየውን እቃ ሁሉ  ሲመረምሩ፣ ሲወያዩ፣ሲያነሱ፣ የመሰላቸውን ኪሳቸው ሲያስገቡ፣ ሌላውን ደግሞ እንደአሰኛቸው ሲጥሉ፣ ሲቀድዱ፣ ሲያወድሙ ይታያሉ።”  በዚያ የሚሆነውን ሲደመድምም:-….ልዩ ሆነው በተተከሉ ቋሚ ድንኳን ቤቶች ታላቅ ስብስብ ነበር። በእነዚህ የቅርስ ክምችት በያዙ ድንኳኖች ዙሪያ ታላቅ ረብሻና ግርግር  ነግሧል። በስፍራው ያየውን ሲያጋልጥ፣:… “ከዘራፊ ወታደሮች ጎን ሦስት ስግብግብ ሚሽነሪዎች፣ እንዲሁም ትውልዳቸው አንዱ ከፕረሽያ፣ ሁለተኛው ከጀርመን፣ ሦስተኛው ከሩስያ የሆነ መካኒኮች አስቀድመው በስፍራው በመድረስ ቅርሱን ተከፋፍለው ይዘውት ነበር..” ይላል።

በጠቅላላው ከመቅደላ የተዘረፈውን ቅርስ  እንደሚከተለው ይተነትናል:-

እስታንሊ ዝርዝሩን ከማቅረቡ በፊት እንዲህ ይተቻል፤ “በየቦታው ወድቆ ያለውን እቃ አንድ አስረኛውን እንኳ ለመዘርዘር አድካሚ እና ፍሬ ቢስ ነው” ይላል፤ ሆኖም ከፊቱ የተነጠፈው የቅርስ ክምችት መሀል ዋና ዋና የመሰሉትን ለይቶ ይጠቅሳል።

    ” አንደኛው ድንኳን ውስጥ በአማረ ቀለማም ክሮች የተሰራ የኢትዮጵያ መንግሥት መታወቃያ የሆነው የይሁዳ አንበሳ  ምስል፤:…ሌላው ውስጥ እንዲሁ የአንበሳ ምስል የተቀረፀበት የንጉሡ ማህተም ተገኘ።  ከንፁህ ወርቅ የተሰራ ፅዋ በሚስተር ሆልምስ እጅ ገባ። ፅዋዉ ላይ የሚከተለው ጽሁፍ  በጥንቱ የኢትዮጵያ  ቋንቋ ተቀርፆበታል፤

የልዕልት ብርሃን ሞገሳ ልጅ የንጉሥ አዲያም ሰገድ ፅዋ፤

 የስጋና የነፍስ ድኅነት ይሆንላቸው ዘንድ፤

ለቅድስት ቁስቋም  ቤተ መቅደስ ተበረከተ።

ሦስት መቶ ዓመት እድሜ ያካበተው ከንፁህ ወርቅ የተሰራ ምንአልባትም ክብደቱ ከስድስት ወይንም ሰባት ትሮይ አወንስ የማያንስ የአቡኑ አርዌ ብርት፤.. አራት የነገሥታቱ  ዘውዶች ከእነዚህም መሀል ሁለቱ በረቂቅ የፊሊግሪ ጥበብ የተሠሩ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስገኙ እና በእንግሊዝ ሙዝየም ሊቀመጡ የበቁ፤…ከሚያማምሩ እቃዎች መሀከል ከአውሮፖ መንግሥታት የተጻፉ በቆንጆ ማህደር የተሸፈኑ ደብዳቤዎችን፤ የሀገር ውስጥ መረጃ  ወረቀቶችን የያዘች አነስ ያለች በፐርል ዶቃ ያጌጠች የቢሮ ጠረጴዛ፤ ..ለመቁጠር የሚከብድ  ከወርቅ፣ ከብር፣ ከነሀስ የተሰሩ ቆንጆ መስቀሎች፣ ፅናዎች፤…የወርቅና የብር ምግብ ማቅረቢያዎች፤ ማንቆርቆሪያዎች፣ ሳህኖች፣ ድስቶች፣ አያሌ ትልቅና ትንሽ ፍንጃሎች፣ በወርቅና በብር ያጌጡ ዋንጫዎች፤….ቦሂሚያን ብርጭቆዎች፣ ሴቨር ቻይና፣ የእስታፈርድሻየር  ሸክላ ሳህኖች፣ የሻምፔን (ፈርንሳይ) ወይን ጠጅ፤…. የግሪክ፣ የስፔን የእየሩሳሌም ወይንጠጅ፣ በርጋንዲ፣.. የዮርዳኖስ ወንዝ ውሀ፤ .. አረቄ እና ጠጅ በገምቦ፤…ሳጥን ሙሉ ልዩ ልዩ ዓይነት እቃዎች፤ እንዲሁም ጽጌ ረዳ፣ ነጭ: እና ሌሎች ቀለሞች የሆኑ የሀር ድንኳኖች፤….የፐርዢያ  የኡሻክ ብሮሳ ኪድሚንስትር የሊዮንስ አበባ ምንጣፎች፤… የጎፈር ካባዎች፤ የአንበሳ ጋማ ለምድ፤ የነብርና የቀበሮ ቆዳዎች፤…ግሩም ሆነው የተሰሩ በወርቅ በብር ያሸበረቁ ኮርቻዎች፤…  በብር የተለበጡ በጣም ብዙ ጋሻዎች፤…ጎንደርና ጎጃም ያፈራቸው የተዋቡ የክብር ጃንጥላዎች፤… ሰይፎች፤ ሾተሎች፤ ጎራዴዎች እንዲሁም በሁለት በኩል ስለት ያላቸው የስኮትላንድ ጎራዴዎች፤ ቢላዎች፣ አያሌ የእግርና የእጅ ብረቶች፤..

ከፐርዢያ፣ ከደማስከስ፣ ከህንድ: ሀገራት የመጡ በጥልፍ  ያጌጡ፣ በወርቅ የተለበጡ ቀለማቸው የሚያበራ የጨርቅ፣ የቆዳ ማህደር የለበሱ ጩቤዎች፤ በሚያንጸባርቅ ቀለም የተሳሉ ስዕሎች የሚታይበት የብራና ቁልል፤… መጽሐፍ ቅዱስ፤ የቅዳሴ የፀሎት መጻህፍት ክምር፤…ለቁጥር የሚከብድ አልበሞች፤ የእንግሊዝ፣ የአሜሪካ፣ የፈረንሳይ፣ የጣሊያን መልክዐ ምድር ፎቶግራፎች፣ ግማሾቹ መስተዋት ላይ የተነደፉ፤…ጥበበኛ የቀረጻቸው የቢሮ ወንበርና ጠረጴዛዎች።”

 ጸሐፊው ያያቸውን እቃዎች በዝርዝር ካስቀመጠ በኋላ በዚያ አምባ ላይ የተሰራጨው ሀብት እና ቅርስ፣ የነበረውን ሽብር እና ግርግር ምን ያክል እንደ ነበር ሲተች…. ” ይህ ነው ብሎ ለመገመት በሚያዳግት ሁኔታ ጠቅላላው የመቅደላ አምባ ዳር እስከ ዳር ድረስ ዳገቱን ጨምሮ  ከዚያም ሁለት ማይል  (3.2 ኪሎ ሜትር) ርቀት አልፎ እስከ ካምፕ ድረስ በሺ የሚቆጠሩ እቃዎች ወድቀው ተዝረክርከው ይታዩ ነበር” ብሏል።

የሀራጅ ሽያጭ ከመጀመሩ አስቀድሞ እያንዳንዱ መኮንን ለሚመራው ጦር ተስማሚ የመሰለውን መታሰቢያ እቃ መረጠ።

በሦስተኛው ቀን ማለዳ ጠዋት የተዘረፈው ሀብት ተዘጋጅቶ ለሀራጅ ሽያጭ ቀረበ። የእቃው ክምችት ግማሽ ኤከር (4,047 ካሬ ሜትር) ስፋት ያለውን መሬት ሸፍኖታል። በዚያ የተገኙት ሰዎች ስም ዝርዝር … ሚስተር  ሆልምስ፣ የእንግሊዝ ሚዩዚየም ወኪል፤..ኮለኔል ፍሬዠር፣ የኃብታም ጦር መሪዎች ክበብ ሀብት ገዢና ሰብሳቢ፤  እንዲሁም ለጨረታ ተሰናድተው የመጡ ኃብታም ግለ ሰቦች ነበሩ። በጊዜው የነበረውን የሞቀ ጨረታ ለአንባቢው በሚገልጹ ቃላት እስታንሊ ጽሑፉን እንዲህ ይቀጥላል….

“በአበጠ ኪሱ የተመካው ሚስተር ሆልምስ ዋና ዋና በተባሉት ቅርሶች የጨረታው አሽናፊ ነበር።

የቴዎድሮስ የልጅነታቸው ጋሻ ለሽያጭ ሲቀርብ ውድድሩ ጋለ። በአስር ዶላር የጀመረው ጨረታ ከሞቀ ውድድር በኋላ ኮሌኔል ፍሬዠር በ200 ዶላር ገዛው።”

የሀራጅ ሽያጩ በሁለት ቀናት ተጠናቀቀ:: የተሰበሰበውም ገንዘብ ለተራ ወታደሩ ተከፋፈለ።

ሽያጩ ከተፈጸመ በኋላ እቃውን ከኢትዮጵያ ለማውጣት በሚያመች ዘዴ በ15 ዝሆኖችና 200 በቅሎዎች ጀርባ ተጭኖ ለረጅሙ ጉዙ ተደራጀ።

መቅደላ በእንግሊዞች እጅ በገባች በአራተኛው ቀን 30,000 ኢትዮጵያውያን የመቅደላን አምባ ለቀው ወደ አምባላጌ ወረዱ። የዚያኑ ዕለት ከሰዓት በኋላ ተመልካቾች አንድ ሺህ ያርድ (915 ሜትር) ርቀት ያለው የሥላሴ ኮረብታ በስተደቡብ ዳገት ጥግ ጥጉን ይዘው ሲጠብቁ፣ የእንግሊዝ  መንግሥት ኤንጅነሮች የመቅደላን አምባ እሳት ለኩሰው አወደሙት። እሳቱም በንፋስ ስለተዛመተ 3,000 ቤቶች ከነንብረታቸው ተቃጠሉ፣ ተደመሰሱ።

እስታንሊ ዘገባውን በመቀጠል…..”በባለሙያዎች ወደ እሳቱ የተወረወረው ጥይት የጎረሰ ሽጉጥ፣ ጠመንጃ እና ቀለህ፣ እንዲሁም ተወንጫፊ የጦር መሳሪያ ባስነሳው ኃይለኛ ሙቀት ምክንያት ከፍንዳታው እየተስፈነጠረ የሚበረው ቁርጥራጭ ብረት እያፏጨ በአጠገባችን ያልፋል። ድምፁም ጆሮ ይደፍን ነበር። አንድም ጎጆ ከእሳቱ ማእበል  አላመለጠም፤” ይላል።

የእንግሊዝ ጦር መቅደላን በእሳት ማእበል ከደመሰሰ በኋላ የዘረፈውን ሀብት ጭኖ ወደ ጠረፍ ጉዞ ጀመረ። የሠራዊቱ 6,000 አባላት የኋላ ደጀን ጦር “ዳገቱን ወርደው ብቅ ሲሉ ከፍ ባለ ድምፅ መዝሙር እና ፉከራ  ያሰሙ ነበር።”

ከመቅደላ የተዘረፈውን ንብረት ለማስመለስ በኢትዮጵያውያን እና ሌሎችም ሃቀኛ ታሪክ ተመራማሪዎች የሚደረገው ጥረት ዘመን ተራማጅ ዘመቻ ሆኗል። የተጋዙትን ታሪካዊ ጽሑፎች እና መጻህፍት፣ እንዲሁም የአጼ ቴዎድሮስ የግል ንብረቶች ስናስብ በጊዜው በዶክተር ሪቻርድ ፓንከርስት መሪነት የተካሔደው የንብረት ማስመለስ ትግል ድጋፍ የሚገባው ነበር። አ.ፍ.ሮ.ሜ.ት የተባለው ይህ ድርጅት በኢትዮጵያ እና በታላቋ ብሪታንያ ቅርንጫፍ የመሰረተ ሲሆን ባደረገውም ትግል የአጼ ቴዎድሮስን የአንገት ክታብ አስመልሶ ለኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት ተቋም አስረክቧል። በተጨማሪም ለንጉሡ ሐውልት እንዲቆምላቸው እየሠሩ ነው። የእስኮትላንድ ተወላጅ የሆኑት ሬቨራንድ ማክሉኪይ በተባሉት በኤደንበሮ የቅዱስ ዮሐንስ ኤፒስኮፖል ቤተክርስቲያን ኃላፊ  በጎ ሥራ የቅዱስ ሚካኤል ፅላት በ February 2002 [የካቲት 1994 ዓም] ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል። ተመሳሳይ ጥረት እና ማስተዋል የሚጠይቅ ሌላ ጉዳይ በእየሩሳሌም የሚገኘው የኢትዮጵያ ንብረቶች ሁኔታ ነው። በኢየሩሳሌም ብቻ ሳይሆን በጄሪኮ፣ እንዲሁም በሌሎች የእስራኤል ከተሞች የሚገኙ ታሪካዊ ይዞታዎች ሁሉ ሊጠበቁ ይገባል።

የአርቆ አስተዋዩ አወዛጋቢው እና አነጋጋሪው አጼ ቴዎድሮስ ሕይወት በዚህ ሁኔታ ተፈጸመ።

ጸሐፊው የሕይወታቸው መጨረሻ ቀን የሆነውን ሁሉ በሚመስጠው ጽሁፉ ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦታል። የመጽሐፉ ዋና ዓላማ  የእንግሊዝ ጦር በኢትዮጵያ ያገኘውን ድል መተንተን እንዲሁም 61 እስረኞችን ከ187 አሽከሮቻቸው ጋር፣ 323  እንስሳትን ጨምሮ ከእስር ማስፈታት መቻላቸውን ማስረዳት ነው። ሆኖም የእስታንሊ ሥራ ታላቅ ድክመት  የእንግሊዞች ድል የተገኘው በጊዜው ንጉሡ በጭካኔአቸው ምክንያት ብዙ የህዝብ ደጋፍ እንዳልነበራቸው እና ተፎካካሪዎቻቸው መሪዎችም በግል ሥልጣን ማስፋፋት ተጠምደው እንደነበር አለመግለጹ ነው። የእንግሊዝን ጦር  የመቅደላ ጉዞ እንዲሳካ ምግብ በማቅረብ መንገድ በመምራት ከረዱት ከ”ልዑል ካሣ” [በኋላ አጼ ዮሐንስ] በስተቀር እስታንሊ ስለ ኢትዮጵያውያን ያለው አስተሳሰብ የተቀዛቀዘ ይመስላል፤ ይሁን እንጂ ጄነራል ናፕዬር ከአካባቢው  ባለስልጣናት ጋር  ከጠረፍ እስክ መቅደላ አምባ ድረስ ጦሩ ያለአንዳች እንቅፋት እንዲጓዝ የተሳካ ድርድር ማድረጉን ያስረዳናል።

አንደነቷን የጠበቀች እና በእስራኤል ያላትን ንብረቶች በተለይም የደር ሡልጣን ገዳምን የምታስከብር ጠንካራ ኢትዮጵያን ማየት የቴዎድሮስ ራዕይ  እንደነበር ሁሉ የትናንት እና የዛሬም ትውልድ ሁሉ ምኞት ሆኖ ቀጥሎአል።

______________________________________________________________________________

1. የጦርነቱ ዘመን በእስታንሊ ጽሁፍ እንደሰፈረው በአሮፓውያን አቆጣጣር  ነው። ለአንባቢ እንዲመች በማለት በቅንፍ የተቀመጡ ተጨማሪ ማብራሪያዎችም ይገኙበታል።

2. ይህ ጽሑፍ  ወደ አማርኛ የተተርጎመው  በኪዳኔ ዓለምአየሁ እና ቆንጂት መሸሻ  “THE LAST DAY OF EMPEROR TEWODROS II’s LIFE AND THE LOOT OF MAGDALA”  በሚል አርእስት በ2011 ላይ ከሰፈረው የድረ ገጽ ጽሑፍ በመነሳት ነው።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.