የባህል መድኃኒቶች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እና የመድኃኒት ዕፅዋት እንክብካቤ አስፈላጊነት በኢትዮጵያ -(በቅርብ ጊዜ ታትሞ ከወጣው የመጻሕፍት ስብስቦች የተቀዳ) -(ዶ/ር ፈቃዱ ፉላስ)

ዋሺንግተን ዲ ሲ ፤ መጋቢት 2016 ዓም

1- የባህል መድኃኒቶች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች

የሰሜን አሜሪካ (ዩናይትድ ስቴትስና ካናዳ) ባህል መድኃኒት በአሁኑ ጊዜ የአሜሪካ ባህል መድኃኒት ነው ብሎ መናገር ያስቸግራል። አሜሪካን ቀይ ህንዶች (ነባር/አገሬያዊ አሜሪካኖች)፣ አውሮፓውያን፣ ጥቁር አሜሪካውያን፣ ሂስፓኒክ፣ እስያውያን፣አፍሪካውያንና ሌሎች የፈለሱ ነዋሪዎች የሚገኙበት ሃገር በመሆኑ፣ አንድ ወጥ የሆነ የባህል መድኃኒት ሥርዓት አለው ማለት አይቻልም። ሆኖም ባህል መድኃኒትን አንደዋናው መሠረት አድርጐ መመልከት ይቻላል።

ዳኰታ፣ ዊኔባጐ፣ ፒማ፣ አፖቼ፣ ኮማንቼ፣ ማስከሬሎና እንዲሁም ሌሎች የአሜሪካ ነባር ዜጐች የተለያዩ የባህል መድኃኒቶችን ሲጠቀሙ ቆይተዋል። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፣ ለትኩሳት ዊሎው (Salix spp.) እና ሲንቾና (Cinchona spp.)፣ ሆድ ለማጥራት ካስካራ ሳግራዳ (Cascara sagrada) እና አሎ (Aloe spp.) (ሬት)፣ ለተቅማጥ ሬድ ኦክ (Quercus Robur) እና ሴና (Senna spp.)፣ ለአስም ሎቤሊያ (Lobelia) ለሆድ ቁርጠት ቨርቢና (Verbena) (አቱች)፣ ለማሸናት ሳርሳፓሪላ (Smilax spp.)፣ ጀኒፕር (Juniperus spp.) እና ዊንተርግሪን (Gaultheria procumbens) ተጠቅመዋል። 20 የቼረኪ ህንዶች በአንድ ዘመን ወደ 800 የሚጠጉ የዕፅዋት መድኃኒት ይጠቀሙ ነበር።

የነባር ህንዶች አሜሪካዊ ባህል መድኃኒት ለአሜሪካ ኢፊሴላዊ የመድኃኒት ስንክሳር (United States Pharmacopeia (USP) and the National Formulary (NF)) መፈጠር ያደረገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ በነባር ህንድ አሜሪካውያንና በመጤ ነጭ አውሮፓውያን ሰፋሪዎች መካከል የባህል ግጭትና መወራረስ ታይቶባቸዋል ። እነኚህ ግንኙነቶች የባህል መድኃኒትንም ይመለከታሉ። ለምሳሌ በ1820 ዓ.እ. በታተመው ዘመናዊ የመድኃኒት ስንክሳር (The Pharmacopoeia of the United States of America) ከተዘረዘሩት 296 መድኃኒቶች ውስጥ 130 ከነባር ባህላዊ መድኃኒት የተወረሱ ነበሩ ።

በ20 ኛው ምእተ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ በዚሁ የመድኃኒት ደረጃ መጽሐፍ 170 የዕፅዋት ደረጃዎች ተጠቃለው ነበር። አብዛኛዎቹ ከነባር ህንዶች የተወሰዱ ዕፅዋትን ያጠቃልላሉ። በ20ኛው ምእተ ዓመት የዕፅዋተ መድኃኒት ዝግጅቶች ተቀባይነት እየቀነስ ሄደ። በምትካቸው ዕፅዋት የተጣሩ መድኃኒቶች ምንጭ ብቻ ሆነው ተወሰዱ። ዘመናዊ መድኃኒቶች በብዛት ብቅ ማለት ጀመሩ። በቅርቡ በ1990ዎቹ ዓመታት (ዓ.እ.) የዕፅዋት ዝግጅቶች ቁጥር ወደ 58 ቀንሷል። ይህ ቁጥር በ United States Pharmacopeia (USP) ውስጥ ከተዘረዘሩት 2894 ደረጃዎች፣ 2% ብቻ ይዞ ነበር። በ2004 ዓ.እ. የታተመው USP 27/NF22 ከ19 የዕፅዋት ዝርያዎች የተዘጋጁ የመድኃኒት ደረጃዎችን አካቷል። እነኚህ ደረጃዎች ዘመናዊ ፋብሪካዎች የመድኃኒትነት ጥቅም ያላቸውን የምግብ ተጨማሪ ውጤቶች (ዕፅዋት) ሲያመርቱ እንዲከተሏቸው የሚረዱ ቢሆኑም ፋብሪካዎች እነዚህን የጥራት ደረጃዎች የመከተል ህጋዊ ግዴታ የለባቸውም።

በአጠቃላይ አሜሪካ ውስጥ የዕፅዋት መድኃኒት አጠቃቀምን በሶስት ዘርፎች መክፈል ይቻላል። አንደኛው፣ ግለሰቦች ከጓሮ እርሻ ሰብስበው (ቆርጠው) የሚያዘጋጇቸውና የሚጠቀሙባቸው ዕፅዋትን ሲያጠቃልል፣ ይህ ዘርፍ በተለምዶ «የቤት ፈውሶች» (Household Remedies) ተብሎ ይታወቃል። ሁለተኛው የዚህ ተቀራራቢና እውነተኛ የባህል መድኃኒት ተብሎ ሊወሰድ የሚችለው የነባር ህንዶች የዕፅዋት ጥቅም ባህል ነው። ከላይ እንደተገለጸው ይህ ባህል ለዘመናዊ የዕፅዋት ዝግጅቶች መሠረት ሆኗል። ሶስተኛው ዘርፍ ዘመናዊ ፋብሪካዎች በእንክብል፣ በፈሳሽ፣ በቅባት፣ ወዘተ… መልክ በብዛት እያዘጋጁ ለገበያ የሚያቀርቧቸው የዕፅዋት መድኃኒት ዝግጅቶችን ያጠቃልላል። እንደ ቤየር፣ ዋርነር-ላምበርት፣ እና አሜሪካን ሆም ፕሮዳክሽን የተባሉት ግዙፍ ዘመናዊ ፋብሪካዎች የዕፅዋት መድኃኒት በዘመናዊ መልክ አደራጅተው ይፈበርካሉ። እንዲሁም ቁጥራቸው ከ300 በላይ የሆኑ ኩባንያዎች እነኚህን የተፈበረኩ የዕፅዋት መድኃኒቶች ለአሜሪካ ገበያ ያቀርባሉ ።

በአሜሪካ የጤና አጠባበቅ አገልግሎት መንግሥታዊ አካል «የምግብና የመድኃኒት ማስተዳደሪያ መሥሪያ ቤት» (ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መሆኑ ነው) ተብሎ ይጠራል። የሕዝብ ጤና አገልግሎት በዚህ መሥሪያ ቤት የሚገኝ ቅርንጫፍ ሲሆን በሥሩ ከሚገኙ ስምንት አካሎች አንዱ የብሔራዊ ጤና ተቋሞች (National Institutes of Health [NIH]) ነው። በ1992 ዓ.እ. በኮንግሬስ ውሳኔ መሠረት የአማራጭ ህክምና ቢሮ በብሔራዊ ጤና ተቋሞች ሥር ተቋቋመ። ይህ የተተኪና (ደጋፊ) አማራጭ ህክምና ማዕከል በNIH ከሚገኙት 25 ክፍሎች አንዱ ነው ። NIH ለስድስት የምርምር ዪኒቨርስቲዎች የዕፅዋት ውጤቶችን ይዘትና ጠቀሚነታቸውን እንዲያጠኑ ከ1999 ዓ.እ. ጀምሮ በየአምስት ዓመታት የሚታደስ የገንዘብ ድጋፍ ሲስጥ ቆይቷል። የዚህ ፕሮግራም ውጤት ገና ያልታወቀ ቢሆንም ብዙ የሳይንስ ዘርፎችን ያካተተና ባልሙያዎችን የሚያሳትፍ ጥረት በመሆኑ ተስፋ ተጥሎበታል።

በአሜሪካ ውስጥ የመድኃኒት ዕፅዋት፣ ማዕድናትና የእንስሳት ውጤቶች ተጠቃለው የምግብ ተጓዳኞች ወይም ተቀጥላዎች (Dietary Supplements) በሚል መጠሪያ ይታወቃሉ። እንደአጠቃቀማቸው የምግብ ተጓዳኞች ወይም የህመም መፈወሻ ሊሆኑ ይችላሉ። የመንግሥት ምግብና መድኃኒት መቆጣጠሪያ አካል (Food and Drug Administration (FDA) እነኚህን ውጤቶች በተወስነ ደረጃ ይቆጣጠራል። የውጤቶቹን ይዘት፣ የፈዋሽነት ችሎታቸውን እንዲሁም በምግብ ተጨማሪነት ወይም በመድኃኒትነት የመለየቱ ተግባር ለዚህ መሥሪያ ቤት አስቸጋሪና እሾሃማ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። በአንፃሩ ግን ዘመናዊ መድኃኒቶች ይዘታቸውም ሆነ ፈዋሽነታችው ስለሚታወቅ ገበያ ላይ ከመውጣታቸው በፊትም ሆነ ገበያ ከዋሉ በኋላ FDA ሊቆጣጠራቸው ይችላል።

አማራጭ መድኃኒቶች (በታዳጊ ሃገሮች ባህላዊ መድኃኒቶች ተብለው የሚታወቁቱ) በአሜሪካ ህዝብ ዘንድ ከብዙ ዓመታት ጀምሮ ተቀባይነት እያገኙ መጥተዋል። በተለያዩ ጊዜዎች የታተሙ ጥናታዊ ቅኝቶች ይህን ሁኔታ አረጋግጠዋል። በ1990 ዓ.እ. የተካሄደ አንድ ጥናት አንዳመለከተው 33.8% የሚሆነው የአሜሪካ ህዝብ አማራጭ ህክምናዎችን ተጠቅሟል። ከነዚህ ህክምናዎች ውስጥ የዕፅዋት መድኃኒት ከፍተኛ ድርሻ ነበረው። በ1997 ዓ.እ. የታተመ የዚህ ተከታታይ ጥናት ደግሞ 42.1% አሜሪካውያን አማራጭ የህክምና ዘዴዎችን እንደተጠቀሙ ገልጧል። ከ1990 እስከ 1997 ዓ.እ. ባለው ጊዜ ውስጥ መጠነኛ ዕድገት አሳይቷል። በዚሁ ወቅት ከሁሉም የአማራጭ ሕክምና ዘርፎች ከፍተኛውን ዕድገት ያሳየው የዕፅዋትመድኃኒት ጥቅም ነው። በቅርብ ጌዜ የተካሄደ የቴሌፎን ቅኝት እንዳመለከተው 49% የሚሆነው የአሜሪካ ህዝብ ከጥናቱ በፊት ባለው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ቢያንስ በአንድ የዕፅ መድኃኒት ተገልግሏል። በዚህ ወቅት 24% የሚሆነው ህዝብ ባልተቋረጠ ሁኔታ ዕፅዋትን ለጤና አጠባበቅ ተጠቅሟል። ህዝቡ በብዛት የሚገለገልባቸው የዕፀዋት ውጤቶች፣ “ጂንሴንግ”፣ “ጊንኮ”፣ “ነጭ ሽንኩርት”፣ “ሴንት ጆንስ ወርት”፣ «ኤኪኒስያ» የመሳሰሉት ናችው። ባጠቃላይ ይህ ሁሉ የሚያመለክተው መድኃኒተ-ዕፅዋት በአሜሪካ ህዝብ ተቀባይነት እያገኙ መምጣታቸውን ነው።

ካናዳ ውስጥ የዕፅዋት መድኃኒቶች «ትውፊታዊ መድኃኒቶች» በሚል መጠሪያ ስም ይጠቃለላሉ። አንድ የስታቲስቲክ ዘገባ እንዳመለከተው 55% ካናዳውያን በሽታን ለመከላከል የተፈጥሮ ውጤቶችን ተጠቅመው ነበር ። በ2000 ዓ.እ. የታተመ ጥናት ደግሞ 2/3ኛው የካናዳ ህዝብ በሽታን ለመከላከልና ጤናን ለመጠበቅ ዕፅዋት ጠቃሚ መሆናቸውን እንደሚያምኑ ዘግቧል። በካናዳ ህክምና ባለሞያዎች ሳይቀር የተፈጥሮ ውጤቶች የመድኃኒትነት ጠቀሜታ ተቀባይነት እያገኘ ነው ።

2- የኢትዮጵያ ባህላዊ መድኃኒት
ኢትዮጵያ አፍሪካ ውስጥ ባላት መልክአ ምድራዊ አቀማመጥና ልዩ ታሪክ የተነሳ የሃገሪቱ ባህል መድኃኒት የተለያዩ
ባህሎች ውህደት፣ መወራረስና ግጭት የሚታይበት ነው። ይህም በመሆኑም በኢትዮጵያ ባህል መድኃኒት በርከት ያሉ ባህሎችና ልምዶች ይንጸባረቃሉ። የአማራን ባህላዊ ህክምና ማወቅ የኢትዮጵያን ባህላዊ ህክምናን ማወቅ ነው የሚል የተሳሳተ አስተሳስብ አለ። የአማራው የባህል መድኃኒት ሥርዓት በተሻለ ሁኔታ የተጠናና የተመዘገበ ቢሆንም፣ ሌሎቹ ማህበረሰቦች አስተዋጽኦቸው ዝቅተኛ ነው ማለት አይደለም። ነገር ግን ይልቁንም መጠናትና መመዝገብ እንዳለባቸው የሚያመለክት ሃቅ ነው ።

በ1987 ዓ.እ. የተቋቋመው የኢትዮጵያ ባህል መድኃኒት ባለሙያዎች ማህበር 9,000 አዋቂዎች፣ የባህል መድኃኒት
ሻጮችና ሰብሳቢዎች በአባልነት ይገኙበታል። ይህ ቁጥር የተወሰኑ የሃገሪቱን አካባቢዎች ብቻ ያጠቃልላል። ነገር ግን በመላው ሃገሪቱ የሚገኙ በባህል መድኃኒት ሙያ ላይ የተሰማሩ (ሃኪሞች፣ የመድኃኒት ዕፅዋት ቆራጭና ሻጮች) ወደ 80 ሺህ እንደሚጠጉ አንድ ግምት ይጠቁማል ።

የኢትዮጵያ ባህል መድኃኒት የኩሽ፣ የዓረብና የዐማራ ልምዶች የተዋሃዱበት ባህል ነው። በምሥራቅ ኢትዮጵያ ሐረርጌ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው በዚህ አካባቢ ያለው የባህል መድኃኒት የዓረብ፣ የዐማራ፣ ቅብጢ (ግብፅ) እና ነባር የኩሽ የባህል መድኃኒት ሥርዓቶች የሚንጸባረቁበት ነው። ነባሩ የኩሽ ባህል መድኃኒት የዳበረው በ16ኛው ምእተ ዓመት በኦሮሞዎች እንቅስቃሴ ወቅት ነበር። በዚህ ንኡስ ሥርዓት ውስጥ ቃልቻዎች እንደ መንፈሳዊ የመድኃኒት አዋቂዎች ሲታዩ፣ የዓረብ ሥርዓት ደግሞ ከመካከለኛው ምሥራቅ የመነጨ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ የገባው በ12ኛውና 13ኛው ምእተ ዓመታት ከእስልምና ሃይማኖት ጋር ተጣምሮ ነው። ይህ ሥርዓት በተለይም በ19ኛው ምእተ ዓመት አጋማሽ ላይ ይበልጥ ተስፋፋ። እንዲሁም ነባር ከሆነው የኩሽ ባህል
ጋር በመዋሃዱ በሐረርጌ ዋናው የባህል መድኃኒት ሥርዓት ሆነ። የሥርዓቱ አዋቂዎች ሼክ፣ ወይም ሼካ በሚል መጠሪያ ታወቁ። የአማራው የህክምና ሥርዓት ደግሞ በመካከለኛው ዘመን ከመሃል ሃገር ደጋ አካባቢዎች ተነስቶ በመላው ሃገሪቱ ተሰራጨ፤ እስከ ሐረርጌም ደረሰ። ይህ ሥርዓት በቤተ-ክርስቲያን በከፊል በግዕዝ ቋንቋ በካህናት አማካይነት ተመዝግቦ ቆየ። ሆኖም በምሥራቁ የሃገሪቱ ክፍል (ሐረርጌ) ቢታወቅም በዚህ አካባቢ እንደ ዓረብ ህክምና አልዳበረም። የዚህ ሥርዓት መሪዎች ደብተራ፣ መጽሐፍ ገላጭ፣ ዛርና ወጌሻ በሚል መጠሪያ ይታወቃሉ ።

በአጠቃላይ የባህል ህክምና አዋቂዎች የኦሮሞው አጌሳ፣ የአማራው ወጌሻ የተለየ ብልሃትና ዘዴ ስላላቸው አጥንት
መጠገን፣ ቀላል ቀዶ ህክምና፣ እንዲሁም ግርዘት ያከናውናሉ። ለህክምናቸው የመድኃኒት ዕፅዋትና ሌሎች መድኃኒቶችን ይጠቀማሉ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ የተማሩ ቅጠል በጣሾች፣ የልምድ አዋላጆች፣ ቃቢራ፣ ደብተራ፣ አጌቲ ተብለው ሲታውቁ በተፃፈና በቃል በሚነገር የህክምና ዘዴዎች ይገለገላሉ። በህክምና አገልግሎታቸውም ዕፅዋትን፣ ማዕድናትንና እንስሳትን ይጠቀማሉ ። የሃይማኖት መሪዎች፣ኮከብ ቆጣሪዎች፣ ምሥጢራዊ አዳኞች?፣ ቃሉ፣ ሼክ፣ መጽሐፍ ገላጭ፣ ዛር፣ ሃኪምና ጠንቋይ በሚሉ ስሞች ሲታወቁ አብዛኛዎቹ የአእምሮ መቃወስ ህክምና አዋቂዎች ናቸው። በማዳን ሥነ ሥርዓታቸው ወቅት ክታብ፣ ቀርጣሳ፣ ማሽላ፣ ቡና፣ ጫትና ዕጣን በመጠቀም መጥፎ መናፍሳትን (ዛሮችን) ያስወግዳሉ ።

ማጠቃለያ
የባህል መድኃኒት በሰሜን አሜሪካና በታዳጊ ሶስተኛ ዓለም ሃገሮች የተለያየ ትርጉም አለው:: ሥልጣኔ ወደ ምዕራቡ ዓለም ጠልቆ ከመግባቱ በፊት የነበሩ ኗሪዎች የባህል መድኃኒትን ልክ ዛሬ በታዳጋው የዓለም ክፍል በሚጠቀሙበት መልክ ይካሄድ ነበር:: ዞሮ፣ ዞሮ የማይካድ ጉዳይ ቢኖር ባህላዊ መድኃኒት ለዘመናዊ ህክምናና መድኃኒት መሠረትና እርከን መሆኑ ነው:: ዛሬም ቢሆን የባህል መድኃኒት ለዘመናዊ መድኃኒቶች ምንጭ መሆኑ ቀጥሏል:: ማስረጃዎችም በብዛት ያንኑ ያረጋግጣሉ:: የኢትዮጵያ ባህል መድኃኒትም ባግብቡ ከተጠናና ከተደራጀ፣ በሳይንሳዊ ጥናት ተደግፎ በቴክኖሎጂ እገዛ በዘመናዊ መንገድ ሊዘጋጅና ሊፈበረክ ይችላል:: ከላይ የተቀሰው ሃሳብ የተወሰደው ከሚከተለው ምንጭ ነው:–

ዋና ግብአት
– Fekadu Fullas (2024). A Treatise on Ethiopian Traditional Medicinal Plants; Amazon; Middletown, DE;
USA, pp 438-441; 446-447.
ሌሎች ጠቃሚ ግብአቶች፤
– Anonymous. Canadians anticipate natural products 3rd. Category. Natural Pharmacy 1999; 3(8):1.
– Johnston BA. Two-thirds of Canadians say Natural Herbal Supplements are effective as
prescription drugs or over-the-counter Remedies. Herbal Gram 2000; 48:66.
– Desalegn Desissa. Uses and conservation of Medicinal Plants used by Sinasha people. May 2000.
http://www.members.lycos.co.uk/Ethiopianplants/sinasha.html (accessed 13 March 2003).
– Eisenberg DM, Kessler RC, Foster C, et al, Unconventional medicine in the United States: prevalence,
costs, and patterns of use. New Eng J Med 1993; 328: 246-252.
– Eisenberg DM, Davis KB, Ettner SL, et al. Trends in alternative medicine use in the United States, 1990- 1997 Results of a follow-up survey. JAMA 1998; 280: 1569-1575.
– Fekadu ፤Fullas, Bisrat Hailemeskel. The dilemma of In-patient dietary supplement use. Natural Health Partners Newsletter. 2002; 1(15).
– Fekadu Fullas. Counseling should cover supplements. Drug Topics. 2002; 146(5): 19.
– Johnston BA. Prevention Magazine Assesses Use of Dietary supplements. Herbal Gram 2000; 48:65.
– Mekonnen Bishaw. Promoting Traditional Medicine. A Brief Historical Review of Government Policy.
Soc Sci Med 1991; 33(2): 193-200.
– Murray L. USP to reevaluate its position on botanicals. AJHP 1998: 35(15): 2330-2341.
– Slikkerveer LJ. Rural Health Development in Ethiopia. Problem of utilization of Traditional Healers. SocSci Med 1982; 16: 1859-1872.
– Tyler VE. Herbs of Choice. The Therapeutic use of phytomedicinals. New York, Haworth Press; 1994; p27.
– USP 27/NF22. The United States Pharmacopeia/The National Formulary 2004. Rockville, MD: United
States Pharmacopeia Convention, Inc.
– Vogel VJ. American Indian Medicine. Norman, USA: University of Oklahoma Press; 1990; p 404.
– Williamson JS, Wyandt CM. The herbal generation; legal and regulatory considerations. Drug Topics
1999; 143(8): 101 110.

3- የመድኃኒት ዕፅዋት እንክብካቤ አስፈላጊነት በኢትዮጵያ

የባህል መድኃኒት ዕፅዋት ቁጥራቸው እየመነመነ መሄድ፣ በተለይም የመድኃኒት ዕውቀት ያላቸው አረጋውያን ዕልፈተ-ሕይወት አሳሳቢ መሆኑን ኢትዮጵያውያን አጥኚዎች ጥላሁን በላቸው፣ ዘመዴ አስፋውና ሰብስቤ ደምሰው በአርባ ምንጭ አካባቢ ባደረጉት ጥናት ጠቁመዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በልዩ ልዩ ምክንያቶች መላ ማህበረሰቦች ከጊዜ ወደ ጊዜ መፈናቀላቸው፣ የመድኃኒት አዋቂዎች በዕድሜ መግፋትና ወጣቱ ትውልድ ከአረጋውያኑ ለመማር ፈቃደኛ አለመሆኑ ይህን ጠቃሚ ባህል የማቆየቱና የማስተላለፉን ችግር አባብሶታል። የደን መራቆት ትልቅ ችግር አስከትሏል። በአሁኑ ወቅት የሃገሪቱ ማዕከላዊና ሰሜናዊ አካባቢዎች ከቶውኑ ደን-አልባ ወደ መሆን ተቃርበዋል። የተቀሩት ደኖች የተከማቹት በደቡብና ምዕራብ ኢትዮጵያ ነው ።

ከአንድ መቶ ዓመታት በፊት 40% የኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች ከፍታ ባላቸው ደኖች ተሸፍነው እንደነበር ይገመታል ። ባንድ ወቅት ከሃገሪቱ 1.112 ሚሊዩን ካሬ ኪሎ ሜትር መሬት ውስጥ 38% የሚሆነው (42 ሚሊዮን ሄክታር ወይም 0.42 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር) በደን የተሸፈነ ነበር ። ይህ ደን እየተራቆተ ሄዶ በ1952 ዓ.እ. 16%፣ በ1980 ዓ.እ. 2.7%፣ በ1990 ዓ.እ. ደግሞ 2.4% ብቻ ሆኗል ። በዚህ ፍጥነት ከቀጠለ በ 2020 ዓ.እ. ሃገሪቱ ያላትን የደን ሃብት በሙሉ ታጣለች፣ ሌጣ ትሆናለች የሚል ስጋት አለ።

ለደን መራቆት ምክንያት ከሆኑት ለመጥቀስ፤ ደን ምንጠራ (ለቤት ሥራ፣ ለማገዶና ለመሳሰሉት)፣ የዘመናዊ እርሻዎች መስፋፋት፣ የአዳዲስ ከተሞች ምሥረታ፣ የሰደድ እሳትና የመሳሰሉት ተፈጥሮአዊ ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው። በተለይም የሰደድ እሳት ትልቅ ጥፋት አስከትሏል። በየካቲት 2000 ዓ.እ. ለሶስት ወራት ሲቀጣጠል የከረመው የሰደድ እሳት በባሌ፣ ቦረና፣ ጅማ፣ ኢሉባቡር፣ ምሥራቅ ወለጋ፣ ምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ አርሲ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላና የደቡብ ክልሎች ደኖችን አውድሟል። በዚህ አደጋ ወደ 300 ሺህ ሄክታር የተገመተ ደን ጋይቷል። ይህ ቃጠሎ በ1984 ዓ.እ. 308 ሺህ ሄክታር ደን ካወደመው እሳት ጋር ይመሳሰላል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በጦርነት ሳቢያ ከፍተኛ የደን ውድመቶች ደርሰዋል። ዮዲት ጉዲት (849-897 ዓ.እ.) ወታደሮቿና ህዝቡ ከትግራይ እስክ ጐንደርና ወሎ የተዘረጋውን ደን እሳት እንዲለቁበት ትዕዛዝ ሰጥታ ነበር። ይህን ያደረገችው ተቀናቃኟ የነበረው የንጉሥ ድልናዖድ ሠራዊት ደኖቹን ተገን አድርጎ እንደሚዋጋት በመገመት ነበር ይባላል። ግራኝ መሐመድም (1527-1542 ዓ.እ.) ከምሥራቅ ኢትዮጵያ ቆላማ ክፍል ጀምሮ እስከ ማዕከላዊ ደጋማ ክፍሎች የሚገኘውን የደን መሬት በእሳት እንዲያጋዩት ለወታደሮቹ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። የንጉሥ ልብነ ድንግል ሠራዊት በደኖቹ ውስጥ ሆነው ይዋጉት ስለነበር መጠለያ ለማሳጣት የተደረገ ዘዴ ይመስላል።

በአንፃሩ ደግሞ ጥቂት የኢትዮጵያ መሪዎች ደኖችን ለማስፋፋት የማይናቅ ጥረት አድርገዋል። ለምሳሌ ንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ (1435-1468 ዓ.እ.) የጥድ፣ የወይራና የዝግባ ዛፎች ደብረሲና አጠገብ ከሚገኘው የወፍ ዋሻ ደን ተሰብስበው በመናገሻ ተራራ እንዲተከሉ ትዕዛዝ ስጥተው ነበር። ዳግማዊ ምኒልክም እንዲሁ በ1895 ዓ.እ. የባህር ዛፍ ከአውስትራሊያ አስመጥተው ሌጣ በነበረው አዲስ አበባ አካባቢ እንዲተከል አደረጉ ። እነኚህ ደን የማስፋፋት ታሪካዊ ምሳሌዎች የመሪዎቹን አርቆ አሳቢነት የሚያሳዩ ቢሆንም፣ የደን ጥበቃና እንክብካቤ ራሱን የቻለ ዕቅድ፣ አፈፃፀምና ክትትልን የሚጠይቅ ሰፊ ጥረት ነው። ምንም እንኳን ደኖችን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ዕቅድ ቢወጣም እስካሁን ግልጽ የሆነ ኦፊሴላዊ ፖሊሲ አልተነደፈም ።

የኢትዮጵያ ደኖች ያሉበት ሁኔታ ከላይ የተጠቀሰው ስጋት ያለ ምክንያት አይደለም። ከደን መራቆት ጋር ተያይዞ የመድኃኒት ዕፅዋትም አብረው ይጠፋሉ የሚለውን ሃሳብ በአጽንኦት ለመግለጽ ነው። ዛሬ የኮሶ ዛፍ፣ መተሬና ድንገተኛ ብዛታቸው በአሳሳቢ ሁኔታ እየመነመነ ሄዷል።

“ትራፊክ ምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ» የተሰኘው ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ እየመነመኑ የሄዱትን የመድኃኒት ዕፅዋት በሶስት ከፍሎ ዘርዝሯቸዋል። በመጀመሪያ ዝርዝር ውስጥ የተመደቡት በህዝብ ዘንድ በብዛት የሚፈለጉት ሲሆኑ፣ የኮሶ ዛፍ፣ ዝግባ፣ ጤና አዳም፣ ቀበርቾ፣ ዕንቀቆ፣ ግዛዋ፣ ዳማካሴና ብሳና ይገኙበታል። ሁለተኛው ምድብ አልፎ አልፎ የሚገኙ እንደ ዕፀ መናሄ፣ አሜራ፣ ዕፀ-ልቦና እና የመሳሰሉትን ያጠቃልላል። በመጨረሻው ዝርዝር ውስጥ ደግሞ ጨርሶውኑ ለማግኘት አስቸጋሪ እየሆኑ የመጡ እንደ መተሬ፣ ዕፀ-ጳጦስ የመሳሰሉትን ጠቃሚ ዕፅዋት ያካትታል።

ለመድኃኒትነት የሚውሉ የዕፅዋት ክፍሎች አሰባሰብ ሁኔታ የዕፅዋቱን በብዛት መገኘት ወይም ያለመገኘት ከሚወስኑት ምክንያቶች አንዱ ነው። ዳዊት አበበና አሃዱ አየሁ ከዘረዘሯቸው 240 የመድኃኒት ዕፅዋት ዓይነቶች መካከል 47% ሥራቸው፣ 17% ቅጠላቸው፣ 11% ቅርፊታቸው፣ 8% ግንዳቸው መድኃኒቶችን ለመቀመም ይጠቅማሉ። እንዲሁም በጃንሰን ከተዘረዘሩት ወደ 350 የሚጠጉ ዕፅዋት መካከል ለመድኃኒትነት የሚሰበሰቡት ክፍሎች 48% ቅጠል፣ 26% መላው ዕፅና ግንድ፣ 25% ሥር፣ 6% ቅርፊት ናቸው። በሁለቱ የመድኃኒት ዕፅዋት ዝርዝሮች ጥቅም ላይ የሚውሉት ክፍሎች አንፃራዊ ብዛት ቢለያይም ሥሮች፣ ቅርፊቶችና ግንዶች በብዛት እንደሚሰበሰቡ መመልከት ይቻላል። በአጠቃላይ የሥሮች፣ አኩራች፣ ሥረ ግንዶች መሰብሰብ የመላውን ዕፅዋት መጥፋት ስለሚያስከትል እነዚህ ዕፅዋት ልዩ እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል። ከመድኃኒት አገልግሎታቸው ባሻገር እንደ ኮሶ ዛፍ የመሰሉ ዕፅዋት ለጣውላና ለቤት ሥራ አገልግሎት ይውላሉ። ለምሳሌ በዚሁ ምክንያት በወሎ ውስጥ የኮሶ ዛፍ እየመነመነ ሄዷል። በተጨማሪም በዚሁ አካባቢ በብዛት ከመቆረጣቸው የተነሳ ብሳና፣ አቱች፣ መቅመቆና ድግጣ ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ ሄዷል።

የመድኃኒት ዕፅዋት ጥፋትን ለማዳን ብዙ አቅጣጫዊ እርምጃዎች መወሰድ ይኖርባቸዋል። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፤

1ኛ/ የመድኃኒተ-ዕፅዋት ዐፀዶችን በየቦታው መጀመር ያስፈልጋል። ዐፀዶች እየጠፉና እየተዳከሙ ያሉት ዕፅዋት የሚበቅሉባቸውና እንክብካቤ የሚደረግላቸው ቦታዎች ናቸው።**??

2ኛ/ ደን ውስጥ መድኃኒተ-ዕፅዋት ተመንጥረው እንዳያልቁ ከተፈጥሮ መካነ ሕይወታቸው ውጪ በዘመናዊ ተክሎች እርሻ መልክ ማራባት ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ በተፈጥሮ ደን ላይ የሚፈጠረውን ውጥረትና ጫና ለመቀነስ ይረዳል።

3ኛ/ መድኃኒተ-ዕፅዋት ለግል ጥቅምም ሆነ ገበያ ለማቅረብ ህዝቡ በዘፈቀደ ደኖችን እንዳይመነጥር እርምጃዎችን መውሰድና የሚጠበቁ ፓርኮችን ማቋቋም አስፈላጊ ይሆናል።

4ኛ/ መድኃኒተ-ዕፅዋት በተለይም ህዳጦ (ብርቅዬ) ዝርያዎች ጨርሶ እንዳይጠፉ የዘረ-መል(በራሂ) ባንኮች ማቋቋም ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ በርካታ የብዝሃ ህይወት ሀብቶች አሏት። እነዚህ ሃብቶች በተለያዩ ሥርዐተ ምህዳሮች ውስጥ በሃገሪቱ ልዩ ልዩ ክፍሎች ተሰራጭተው ይገኛሉ። አብዛኞቹ የመድኃኒት ዕፅዋት በቁጥቋጧማ ደኖች ውስጥ ሲገኙ፣ ሌሎቹ ደግሞ በደረቅ ተራሮች ደንና ተራራማ የሣር መሬት (ገሣገር) ሥርዓተ ምህዳሮች ውስጥ ይገኛሉ ።

“ብዝሃ ህይወት” ማለት ባጭሩ የዘረ መል፣ ዓይነቴዎችና ደቂቀ ዘአካላት፣ የሥርዓተ ምህዳሮች፣ የባህል ተለያይነትና የማህበረሰባዊ ዕውቀት ድምር ነው። “ሥርዓተ ምህዳር” ደግሞ የዕፅዋትና እንሰሳት ዓይነቶች ስብስብና የነርሱ መኖሪያ ስፍራ ማለት ነው። የዕፅዋትና እንሰሳት ዓይነት፣ የመሬቱ አቀማመጥ፣ ከፍታው፣ የአካባቢው ሙቀትና እርጥበት መጠን፣ እንዲሁም የአፈሩ ዓይነት የሥርዓተ ምህዳሩን ዓይነትና ባህርይ ይወስናሉ ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ አሥር የሚጠጉ ሥርዓተ ምህዳሮች ይገኛሉ። እነሱም የሚከተሉት ናቸው፦

1. የተራራማ የሣር መሬት ሥርዓተ ምህዳር፣
2. የደረቅ ተራሮች ደንና ቅጠላቸው የማይረግፍ ቁጥቋጦች ሥርዓተ ምህዳር፣
3. የውርጭና ውርጭ-ቀመስ ሥርዓተ ምህዳር፣
4. የግራር-ከርቤ ሥርዓተ ምህዳር፣
5. የእርጥባማ ተራሮች ደን ሥርዓተ ምህዳር፣
6. የአባሎና አኩማ ሥርዓተ ምህዳር፣
7. የቆላማው ክፍል ሥርዓተ ምህዳር፣
8. የበረሃማና ከፊል በረሃማ ሥርዓተ ምህዳር፣
9. የእርጥባማ መሬቶች ሥርዓተ ምህዳር፣
10. የውሃ አካላት ሥርዓተ ምህዳር።

ጃንሰን የዘረዘራቸውን ወደ 350 የሚጠጉ የመድኃኒተ ዕፅዋት በነዚህ ሥርዓተ ምህዳሮች ያላቸውን ሥርጭት በአንድ ጥናት መርምሯል። በጥናቱ መሠረት ከ350ው ዕፅዋት ወደ ግማሽ የሚሆኑት የሚገኙት በተራራማ የሣር መሬት ሥርዓተ ምህዳር ውስጥ ነው። ይህ ሥርዓተ ምህዳር በፍጥነት እየመነመነ የሄደ ሲሆን በውስጡ የሚገኙት የመድኃኒት ዕፅዋት ቁጥቋጧማ፣ ዳሂዎች ወይም የአመልማል ባህሪያት ያላቸው ናቸው። ዕፅዋቱ በሌሎች ትላልቅ ዛፎች ሽፋን ሥር ተጠልለው ይገኛሉ። በደረቅ ተራሮች ደን ሥርዓተ ምህዳር ውስጥ የሚገኙት መድኃኒተ-ዕፅዋት በተራራማ የሣር መሬት ሥርዓተ ምህዳር ውስጥ ከሚገኙት ጋር ሲዳመሩ ከ350ው መድኃኒተ ዕፅዋት ከግማሽ በላይ ይሆናሉ ።

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክና የባሌ ተራራሮች ብሔራዊ ፓርክ የሚገኙት በውርጭና ውርጭ-ቀመስ ሥርዓተ ምህዳር ውስጥ ነው። የእነዚህ እንደ ሰንሰለት የተቆላለፉ ተራሮች ሰማይ ጠቀስ አናቶች «በአየር ላይ የተንሳፈፉ ደሴቶች» የሚል ተቀጽላ ስም አግኝተዋል። ይህ ሥርዓተ ምህዳር ከሁሉም ያነሰ የደን ሽፋን ቢኖረውም ብርቅዬ ከሆኑት ዕፅዋት 20% የሚገኙት በዚህ አካባቢ ነው። እንደ ኮሶና ጅብራ ያሉት ዕፅዋት በብዛት ይገኙበታል ። ቀደም ብለው የተጠቀሱት 350 መድኃኒተ-ዕፅዋት በተዘረዘሩት ሥርዓተ ምህዳሮች ውስጥ በተለያየ ብዛት ተሰራጭተው ይገኛሉ።

ማጠቃለያ
`የደን እንክብካቤ አስፈላጊነት የማያጠያይቅ ጉዳይ ነው። በቅርብ ጊዜ የተካሄደው የዕፅዋት ተከላ ዘመቻ የሚደገፍ
ቢሆንም ዕፅዋቱ እንዴት እንደሚመረጡ፣ የት እንደሚተከሉ፣ ክትትሉ ምን ያህል እንደሆነና፣ በተለይ ደግሞ የመድኃኒት ዕፅዋት
ምን ያህል ትኩረት እንደሚሰጣቸው የሚያመለክት መረጃ የለም። ሆኖም፣ ባጠቃላይ ዝንባሌው ተስፋ ሰጪ ይመስላል።

* * * * * * * * * * * *

ከላይ የቀረበው ጽሑፍ በቅርብ ጊዜ ከታተመው መጽሐፍ፤ Fekadu Fullas (2024). A Treatise on Ethiopian
Traditional Medicinal Plants; Amazon; Middletown, DE; USA,  ገጽ 467-70  የተወሰደ ሲሆን በሚከተሉት ዋቢ
ጽሑፎች የተደገፈ ነው።

ዋና ዋና ግብአቶች
– ጌታቸው ተስፋዬና በሪሁን ገብረመድህን፤ የሥርዓተ ምህዳር አጠባበቅ ዘዴና ብዝሃ ሕይወት በኢትዮጵያ፤ አዲስ አበባ፣
ኢትዮጵያ፦በሥርዓተ ምህዳር ጥበቃና ምርምር መምሪያ ሕይወታዊ ሀብት ጥበቃና ምርምር ኢንስቲትዩት ለልማት ሠራተኞች፣
ለተማሪዎችና ለአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ማስተማሪያ እንዲውል የተዘጋጀ፣ ሚያዝያ 1996 ዓ.ም.
– Belachew Wassihun, Zemede Asfaw, Sebsebe Demissew. Ethnobotanical study of useful plants in Daniio
Gade (Home-Garden) in southern Ethiopia. http://www.ibcet.org/ibc/pubn/files/Ethnobotanical-study-of-
useful-plants-in.htm (accessed 7 Jan 2008).
– Abebe Demissie. Biodiversity Conservation and Sustainable use of Medicinal Plants: problems and
prospects. In: Conservation and sustainable use of Medicinal plants in Ethiopia. Medhin Zewdu, Abebe
Demissie (Eds). Addis Ababa: Institute of Biodiversity and Research; 2001; pp 56-64.
Anon. Ethiopia loses 200,000 Hectares of Forest Annually. The Ethiopian Herald. Feb 8,2007 (Addis
Ababa).
– Dawit Abebe, Ahadu Ayehu, Medicinal and Enigmatic Health Practices in Ethiopia. BSPE; 1993; p 32.
Dechassa Lemma. Forest fires in Ethiopia: Reflections on socioeconomic and environmental effects of
fire in 2000. United Nations Development Program Emergencies Units for Ethiopia (UNDP-EUE); 2001.
http://www.telcom.net.et/-UNDPue/reports/wildfire2000.doc (accessed 24 Dec 2008).
– Desalegn Desissa. Preliminary valuation of medicinal plants in Ethiopia: Trade, volume and price. In:
conservation and sustainable use of medicinal plants in Ethiopia. Medhin Zewdu, Abebe Demissie (Eds)
Addis Ababa: Institute of Biodiversity Conservation and Research; 2001; pp 76-91.
– Edwards S. The Ecology and conservation Status of Medical Plants in Ethiopia. What do we know? In:
Conservation and sustainable use of medical plants in Ethiopia. Medhin Zewdu, Abebe Demissie. (Eds).
Addis Ababa: Biodiversity Conservation and Research; 2001; pp 46-55.
– Ethiopia: County Report to the FAD International Conference of Plant genetic resources, Addis Ababa,
Ethiopia, April 1995. http://www.fao.org/ag/AGP/agps/pgfa /pdf/ethiopia.pdf.
– Haile Yineger, Delnesaw Yehwalaw, Demel Teketay. Ethnomedical plant knowledge and practice of the
Oromo ethnic group in southwestern Ethiopia. J Ethnobiol Ethnomed. 2008; 4:11.
Mesfin Tadesse. Neglected Treasure: An overview of Ethiopia’s Vegetation. Ethiopian Register 1997;
4(4):26-20
– Mirutse Giday. An ethnobotanical study of medicinal plants used by the Zay people of Ethiopia. CBM: s
Skriftserie 2001; 3: 81-99.

Vietter J de. Forest genetic resources of Ethiopia. In: Plant Genetic Resources of Ethiopia. Engles JMM,
Hawkes JG, Melaku Worede (Eds). Cambridge: Cambridge University Press; 1991; pp 82-100.
– Yohannes Raphael. Caring for the Environment. Addis Tribune. 10/29/04. .
– Zemede Asfaw. The Role of Gardens in the Production of and Conservation of Medicinal Plants: In:
Conservation and Sustainable use of Medicinal Plants in Ethiopia. Medhin Zewdu, Abebe Demissie
(Eds), Addis Ababa: Institute of Biodiversity and Research; 2001; pp 56-64.

*ዓእ የሚለው ማኅፀረ ቃል “ዓመተ እግዚእ” ወይም በላቲን AD የሚለውን የምዕራቡን ዓለም ቀን መቁጠሪያ የሚያመለክት ነው።

— ***—-

 

 

1 thought on “የባህል መድኃኒቶች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እና የመድኃኒት ዕፅዋት እንክብካቤ አስፈላጊነት በኢትዮጵያ -(በቅርብ ጊዜ ታትሞ ከወጣው የመጻሕፍት ስብስቦች የተቀዳ) -(ዶ/ር ፈቃዱ ፉላስ)”

Leave a Reply

Scroll to Top

Discover more from ሰምና ወርቅ

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading