ሰሚ ነው እንጂ ተቸጋሪ፤
ሰሚ ነው እንጂ ተቸጋሪ፤
ደንቆሮ መልካም ኗሪ፤
ደንቆሮ መልካም ኗሪ።
(በዓለማየሁ ፋንታ የበገና ዝማሬ እንደሚሰማው)
በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት አንድ ጊዜ በጐንደር ክፍለሃገር እጅግ በጣም የሚያስገርም ታሪክ እንደተሠራ ይነገራል፡፡
ንጉሡ ከአዘዞ አይሮፕላን ማረፊያ ወደ ጐንደር ቤተመንግሥት ታጅበው በሚሄዱበት ጊዜ ብዙ ባላገሮች በመንገድ ላይ ተሠልፈው፤ “አቤት! አቤት!” ሲሉ የንጉሱ መኪና ተግ ብሎ እልፍኝ አስከልካዩ ይወርድና፣
“ኧረ ምን ሁናችሁ ነው፣ ምን በደል ደረሰባችሁ?” ኧረ ምን ሁናችሁ ነው፣ ምን በደል ደረሰባችሁ?” ብሎ ይጠይቃል፡፡ ከአቤት ባይዎቹ መካከል በዕድሜ ላቅ ያሉት አረጋዊ የሚከተለውን መልስ ይሰጣሉ፡-
“አይ ኧረ ምንም አልሆን – እንዴት ንጉሥ
ሲያልፍ ዝም አሉ እንዳንባል ነው እንጂ”
በሃይማኖት ሳቢያ ተጭኖን በቆየው ልማድ መሠረት ንጉሥ (ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ) የእግዚአብሔር ወኪል ሁኖ የሚመለክበት ሰው በመሆኑ አቤቱታ ማሰማት እንደ ጸሎት ያለ ትሩፋት ነው።
እንደነዚህ ላለው ሕዝብ ይመስለኛል አለመማር ፣ አለማወቅና አለመመራመር ምክንያት ሆኖ፣
“ደንቆሮ መልካም ኗሪ” የተባለው።
ምንም እንኳን በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የነበረው ሥርዓት ወደ ውጭ ሃገር ሂዶ በመንግሥት ወጭ የመማርን ዕድል የሚሰጠው ለመሣፍንቱና ለመኳንንቱ ልጆች ቢሆን፣ ኢትዮጵያ ከጠላት ወረራ ወዲህ በታሪክ አጋጣሚ ከደሃውም ወገን የተማሩ ልጆች ማፍራት ጀምራለች።
በወታደራዊው አቋም ረገድ (በክብር ዘበኛ በኩል ብቻ የተፈጸመውን እንደምሣሌ ለመጥቀስ) ሠራዊቱ የተማሩ መኮንኖች እንዲኖሩት ፣ ንጉሱ ከስዊድን መንግሥት በተላኩላቸው ከፍተኛ መኮንኖች አማካይነት ሶስት ኮርስ በማከታተል ያስመረቀውን የክብር ዘበኛን ሚሊተሪ አካዳሚ እንዲመሠረት አድርገዋል፡፡
በ1953 ዓ.ም ገርማሜ ንዋይና ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ባደረጉበት ጊዜ ወታደሩም ሆነ ሲቪሉ በደርግ ቋንቋ ልጠቀምና “የፖለቲካ ንቃተ ህሊና” ያገኘበት ዘመን ይመስላል።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይግባውና፣ የተማሩ የተመራመሩና ያወቁ ሰዎች ቁጥር እያደገ ሲሄድ ይታይ ነበር፡፡የበገናውም ዝማሬ እኮ እንደነዚህ ያሉትን ኢትዮጵያዊያን ይሆናል፤
“ሰሚ ነው እንጅ ተቸጋሪ” ያለው።
የ1953 ዓ.ም መፈንቅለ መንግሥት
የታኀሣሥ ጉዳይ ከተነሳ ዘንድ ፣ አቶ ጳውሎስ አሰፋ ስለ ራሴ እንድጽፍ ስለጠየቀኝ መልሴን በሚከተሉት ዘርፎች ግርጌ አስፍሪያለሁ።
- ጠቅላላ አስተያየት
- በግል የተሰጠኝ ግዴታ
- ቤተ መንግሥት
- የሽሽት ጊዜ
- 4ኛ ክፍለ -ጦር (መሿለኪያ)
- ወህኒ ቤት
- ግዞት
ጠቅላላ አስተያየት
የታኀሣሥ መፈንቅለ መንግሥት፣ በኔ ግምት በገርማሜ አእምሮ ብቻ የተጠነሰሰ ይመስላል፤ ለአፈጻጸሙ ግን የወታደር ኃይል ስለሚያስፈልግ የጀኔራል መንግሥቱ ፈቃድ መጨመር ነበረበት።ሁለቱ ወንድማማች ለብዙ ጊዜ መሣፍንቱና መኳንንቱ ግፈኛውን መንግሥት መከታ አድርገው በሃገሪቱ ላይ ስላደረሱት ጥፋት ሲመካከሩ እንደኖሩ መገመት ይቻላል።
ገርማሜ ሠራዊቱ እንደሸሸና ሙከራው እንዳልተሳካ በተረዳበት ሰዓት (ግር በጧት)? በቤተ መንግሥት የተገኙትን ጥቂቶች መኮንኖች ሰብስቦ ባሰማው ንግግር እንደዚህ አለ፡-
“ምንም እንኳን ሁሉም ነገር እንዳሰብነው ሳይሳካ ቢቀር፣ ከሃገሪቱ ላይ እነዚህን አረመኔዎች (የሚገደሉትን መኳንንት) አስወግደን ማለፋችን መልካም ነገር ስለሆነ አትዘኑ።”
መኳንንቱ ከመገደላቸው በፊት ወይም ከተገደሉ በኋላ እንዲያውም በሚገደሉበት ጊዜ እንኳን በፊቱ ላይ የድንጋጤና ፍርሃት ወይም የማወላወል ባህሪ አይታይበትም ነበር።
?የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ አልተሳካም ቅኝ ??አላገኘም የሚሉ ሰዎች ይኖራሉ፡፡እውነት ነው ይህ አስተያየት።
ግን ይህ አስተያየት በግዙፍ ባህሪው ሲመረመር ብቻ ነው አልተሳካም የሚያሰኝ።
የመለኮትነት ኃይል ተሰጥቶት ሲመለክበት የቆየው የዘውድ ጣኦት ፣ በደርግ ዘመን ተፈረካክሶ ሊወድቅ የቻለው የታኀሣሱ እንቅስቃሴ ዋና ፈለግ ሁኖ ይመስለኛል።
በግል የተሰጠኝ ሥራ
ረቡዕ ጧት ሥራ እንደገባሁ ጀኔራል መንግሥቱ “እንኳን ደስ አለህ” አሉና እጄን ጨበጡኝ፤ እኔም (ከፍርሃት ወይም ከአክብሮት የተነሣ ሳይሆን) ከልብ አምኘበት “አሜን” ብዬ ተቀበልኩ።
ከሠላምታ ልውውጥ በኋላ ትንሽ ከሰዎች ዘወር ብለን ቆም አልንና በየክፍሉ ተለያይተው በእስር መልክ የተያዙትን መኳንንት በጥብቅ መቆጣጠር ዋና ግዴታዬ መሆኑን አስረዱኝ።
እኔ ከመድረሴ በፊት በየክፍሉ ላሉት ዕሥረኞች አንዳንድ መሣሪየ የያዙ መኮንኖች ተመድበው ነበር፡፡
የምስጢር ተካፋይነት ባይኖረኝም የመፈንቅለ መንግሥቱን ዓላማ ሙሉ በሙሉ ደጋፊ ነበርኩ።
ዳሩ ግን እንዲያው በደመ ነፍስነት ላለመመራት ስል ብቻ የልብ ጓደኛዬ ከሆነው በሻለቃ ተፈራ ወልደ ተንሣይ ጋር ተወያይቼ ስለመፈንቅለ መንግሥቱ የሥራ አያያዝና ስለሠራዊቱ ጠቅላላ አቀማመጥ መጠነኛ ግንዛቤ አግኝቻለሁ።
ከኮርያ ጦርነት ጊዜ ጀምሮ ተፈራ በክብር ዘበኛ ሠራዊት ስሙ ከፍ ከፍ እያለ እንደሄደ የሚነገርለት ሰው ነው፡፡
ኮርያ ባደረገው የጀግንነት ተጋድሎ ኢትዮጵያ ያገኘችው ልዕልና ተወስቶ አሁንም አምጿል የተባለውን የጦር ሠራዊት ደምስሶ መሪዎቹን እነጀኔራል መርዕድ መንገሻን ማርኮ እንዲመለስ የታዘዘው እሱ እንደሆነ ቀደም ብዬ ተረድቼ ነበር።
በዚህ በከብር ዘበኛ መሥሪያ ቤት የነበረብኝ ግዴታ ሐሙስ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ግድም ተፈጸመ፡፡ታሥረው የነበሩትን መኳንንት ሁሉ በባየ ጥላሁን ኃላፊነት ወደ ቤተ መንግሥት እንዳስተላልፍ ከጀኔራል መንግሥቱ ትዕዛዝ ደርሶኝ ነበር።ቀደም ብሎ ከጀኔራሉ በተሰጠኝ ትዕዛዝ መሠረት እኔ ከዚያው ክብር ዘበኛ መሥሪያ ቤት አድሬ ዓርብ ጧት በቤተ መንግሥት መገኘት ነበረብኝ።
ቤተ መንግሥት
ዓርብ ጧት ቤተመንግሥት እንደደረስኩ በዚያም በዚህም እምሰማው ፡-እገሌም ከዳ- እገሌም ከዳ ነበር የሚባለው። ከዓርብ ጀምሮ የተሰጠኝ ልዩ ሥራ የለም።ከገርማሜ በስተቀር በሰው ሁሉ ፊት የሚታየውም ተስፋ መቁረጥ ያስደነግጥ ነበር።
ወርቅነህ ባንድ ክብር መዝገብ ላይ፣ ቃል በቃል የማላስታውሰው ጽሑፍ አሠፈረ።የጽሑፉ መንፈስ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጀመረውን እንቅስቃሴ ወደ መልካም ግብ ለማድረስ ጥረት እንዲያደርግ ነበር፡፡ ጀኔራል መንግሥቱ በወርቅነህ ትከሻ ላይ ሰግደድ ብለው አነበቡና “ እንፈርምበት -ጥሩ ነው” አሉና ከወርቅነህ ቀጥለው ፈረሙ። ከዚያ ገርማሜም ፈረመ።በመጨረሻ ሻለቃ ዮሐነስ ምስክር ፈረመ። ሻለቃ ተሰማና እኔ እንዲሁ ችላ ብለን ሳንፈርም ቀረን ፤እንድንፈርምም የጠየቀን ሰው አልነበረም።
ከዚህ ቀጥሎ ጀኔራል መንግሥቱ ከፊታቸው የነበርነውን ጥቂቶች መኮንኖች አስከትለው ዙሪያውን ቀድመው ቤተ መንግሥቱን ይጠብቁ የነበሩትን ወታደሮች ለመጐብኘት ወጣን።
ጉብኝታችን ጨርሰን ሰንመለስ ሠራዊቱ ውጡ ብሎ ቦታውን ለቅቆ ሸሸ።ቤተ መንግሥቱም ያላንዳች መከላከያ ፟ኃይል ፈግጐ? ቀረ።
ጀኔራሉ ከዚህ ቀጥሎ የወሰዱት እርምጃ እቴጌይቱ ከነቤተሰቦቻቸው በጥበቃ እሥር ከነበሩበት (ከአሜሪካ ኤምባሲ አጠገብ ቤታቸው) ወደ ቤተ መንግሥት እንዲመለሱ ማድረግ ነበር።
በጀኔራሉ ትዕዛዝ ለጥበቃው ኃላፊ ለነበሩት ለኮሎኔል አንጋጋው ኃይሌ ወስደን የሰጠነው ሻለቃ ተሰማና እኔ እንዲሁም የማላስታውሳቸው ሁለት መኮንኖች ነበርን።
ኰሎኔለ አንጋጋው መልዕክቱን እንደሰሙ “እኔ የማውቀው ነገር የለም ዘወር በሉ፣ ተመለሱ” ብለው በጩኸት እንደተናገሩ በዕድሞው ዙሪያ ጐድበው ከተሠለፉት ወታደሮች አቅጣጫ የተኩስ በረዶ ወረደብን። ወደ ጐደቡበት በጣም ተጠግተን ስለነበረ ከመካከላችን አንድም ሰው እንኳ ሳይሞት ወይም ሳይቆስል መቅረቱ የሚያስደንቅ ነገር ነው።
ምናልባት ተኩሱን በከፈቱ ወታደሮች ህሊና ታዳጊነትን አግኝተን ይሆናል እያልኩ አስባለሁ።በሄድንበት ተመልሰን ስድስት ኪሎ ሃውልት እንደደረስን የአሜሪካ ጀት መኪኖችን እየተከታተለ ካዘነበብንተኩስ አምልጠን ወደ ቤተ መንግሥት ለመግባት በቃን።
ወዲያው እንደገባን የኰሎኔል አንጋጋው ኃይሌን መክዳት ለጀኔራል ነገርን።
በአሁኑ ሰዓት የክብር ዘበኛ እንቅስቃሴ እየደከመና እየመነመነ ሲሄድ፣ የጦር ሠራዊት ኃይል ደግሞ በሕዝብ ውካታ እየተደገፈና እያየለ መሄድ በጉልህ ይታይ ነበር።
ከዚህ በኋላ የክብር ዘበኛ በቤተ መንግሥት አስሮ ከያዛቸው በስተቀር በየቦታው የነበረውን የበላይነት እያጣ መሄዱ ተረጋገጠ።
በዓይነ ቁራኛ ይጠበቁ የነበሩት ጀኔራል ጽጌና ኰሎኔል ወርቅነህ በየፊናቸው በግዴታም ሆነ በውዴታ ያበረከቱትን ሥራ ለማውሳት የጽሑፌ ዓላማ አይደለም።እኔን በሚመለከት ግን ከወርቅነህ ጋር ሁለት ጊዜ ተነጋግረናል፡-
ረቡዕ ጧት ክብር ዘበኛ መሥሪያ ቤት ሳለን፣ እሱ በእንቅስቃሴው ፕላን እንደሌለበት ሲነግረኝ በኔም በኩል የማውቀው ነገር እንደሌለ ገልጨለት ተለያይተን ነበር።ዓርብ ጧት ደግሞ (የአሜሪካን አምባሳደር ወደ ቤተ መንግሥት ከመምጣቱ በፊት) ወርቅነህ ትንሽ ከሰዎች ዘወር አድርጐ እንደዚህ ሲል መከረኝ፡-
“ያሬድ እስከአሁን ድረስ እዚህ ምን ታደርጋለህ፣
ውጣና ልጆችህን አሣድግ፣ ለምን በከንቱ ትሞታለህ?”
ከጥቂት ሰዓት በኋላ የተለመደው ሹክሹክታ ይሰማ ጀመር፡-
ወርቅነህ ከዳ፣ ወርቅነህ ከዳ ለካስ የአሜሪካን አምባሳደር ወደ ቤተመንግሥት ወጥቶ ከተነጋገረ በኋላ ወደ ኤምባሲው ሲመለስ ወርቅነህና ተሰማ ዋቅጅራ “አምባሳደሩን እንሸኘው” ብለው እንደወጡ አልተመለሱምኑሯል።
ከሰዓት በኋላ በዘጠኝ ሰዓት ግድም፣ ቤተመንግሥቱን የምንጠብቀው ቁጥር (እስረኞቹን ሳንጨምር) ከሃያ አምስት እስከ ሰላሣ ብንሆን ነው።
እሥረኞቹ ከሁለት ተከፍለው ፣ አልጋ ወራሽና ራስ እምሩ በደርቡ ላይ ባንድ ክፍል፣ የቀሩት በምድር ቤትባንድ ክፍል ይገኛሉ። የጦር ሠራዊት እየገፉ ቀርቦ ቤተ መንግሥቱን ከቦ ይዟል።የተኩሱ ልውውጥ ከሁለቱም ወገን እየተፋፋመ ሂዷል።ይዞታው ለጨበጣ ውጊያ የተዳረስን ይመስል ነበር።
ገርማሜ ጧት እንደተናገረው ከምድር ቤት የነበሩት መኳንንት አንድ አሥር ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተገደሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ሁላችንም ወደ ደርቡ ወጥተን ጉድብ በመያዝ ውጊያውን ቀጠልን።
የጦር ሠራዊት በግራም በቀኝም ተጠግቶ ያለንበትን ክፍል በታንክ መደብደብ ሲጀምር፣ ረቡዕና ሐሙስ ለክብር ዘበኛ ይሰግድ የነበረው የከተማ አውደልዳይ የንጉሱን ስም እያወደሰ የክብር ዘበኛን ስም እያወገዘ በማርቆስ በር “ሆ” እያለ መግባት ጀመረ።
ጀኔራል አውቶማቲክ መሣሪየ ብድግ አድርገው ተኩስ ሲከፍቱ አንድ ሦስት ያህል ሰዎች ሲወድቁ አየሁ።መሣሪያውን ዘወር አድርገው አስቀመጡና በብስጭት አነጋገር፤ “ለዚህ ሁሉ ኃላፊ ንጉሱ ናቸው” አሉ።እኔ ደግሞ በበኩሌ በሠገነቱ ላይ ለሁለት ሦስት ሰከንድ ያህል ቆም ብየ ያለንበትን ክፍል በሚደበድበው ታንክ አናት ላይ የጣልኩት የእጅ ቦምብ ሳይፈነዳ ቀረ።
እምብዛም አላዘንኩ፣ እንዲያውም እየቆየሁ አንኳን አልፈነዳ እያልኩ አብሰለስል ነበር።
በከባድ መሣሪያ ለብዙ ሰዓት የተደበደበው ክፍላችን ጽንአቱ ስላሰጋቸው፣ ጀኔራል “ቤቱ ተጭኖን ከምንሞት ወጥተን እየተታኰስን መሞት ይሻላል” አሉና “ተከተሉኝ” ብለው በጀርባ በኩል ለመውጣት ሞከርን።ደረጃውን እየወረድን ሳለ ከኋላችን አንድ ተኩስ ተሰማ “ጀኔራል ጽጌ ራሣቸውን ገደሉ” አለ አንድ አየኋቸው የሚል መኮንን።
ቤቱን ፈጽመን ከመልቀቃችን በፊት ምድር ቤት ባንድ ትንሽ ክፍል ተሰበሰብን፤ ወዲያው ከዚያው ከመካከላችን አንድ ጥይት ተተኮሰ። “ሻለቃ ዮሐንስ ምስክር ራሣቸውን ገደሉ፡” የሚል ቃል ተሰማ።በቀኝ በኩል ቁሞ እንደነበር ስለማስታውስ ወደቀኝ ዘወር አልኩ ፤ ሬሣውን አየሁ።
የሽሽት ጊዜ
ቤተ መንግሥቱን ለቅቀን ስንወጣ በስተጀርባ (በምዕራብ) የጦር ሠራዊት ኃይል አልገጠመነም።ወንዙን ተሻግረን በቀጨኔ መድኃኔዓለም አድርገን ወደ ራጉኤል አቅጣጫ አመራን።ከእንግዲህ ወዲያ ያለውን ስራችንን “የሽሽት ጊዜ” ብየ ሰይሜዋለሁ።
ቀጨኔ መድኃኒዓለምን አለፍ እንዳልን፣ ጀኔራል መንግሥቱ ባርኔጣቸውን አውልቀው፣ ነጠላ ቢጤ በራሣቸው ላይ ጣል ማድረግ ፈለጉ፣ እንጨት ባህያ ጭኖ ወደ ከተማ ይጓዝ ለነበረው ባላገር የነጠላውን ዋጋ በብር ከፈልኩትና ጉዟችንን ቀጠልን።
ራጉኤል ቤተክርስቲያን ስንደርስ ድግዝግዝ ማለት ጀመረ። ከዚህ አካበቢ ለማደር ተወስኖ ስለወደፊቱ ጉዟችን ለመወያየት ትንሽ ስብሰባ አደረግን።
ከኢትዮጵያ በሁለት አቅጣጫ ለመውጣት በጐጃም አድርጐ ወደ ሱዳን -በውጋዴን አድርጐ ወደ ሱማሌ እስከጠረፍ በምን ሁኔታ ለመድረስ ይቻላል የሚል ጥያቄ ተነስቶ በሰፊው ተወያየን።
በብርሃን እየተደበቁ በጨለማ ቢከድ፣ ወይም በቀን ባላገሩን እየመሰሉ ለማለፍ ቢሞከር፣ ሁለቱም አደጋ ያለበት መሆኑን ተረዳን። በተለይ በቀን መንቀሳቀሱ በጠጉረ ልውጥነት ምክንያት ከሚፈጠረው ክስተት መሰወር እንደማይቻል ተገነዘብን።
ጉዛው በጨለማም ሆነ በቀን፣ በቡድን እየተግተለተሉ ከመታየት ይልቅ፣ ሽሽቱ ለብቻ ለብቻ ቢሆን የተሻለይሆናል ብየ ያመንኩበትን ሃሣብ ለማካፈል አልፈቀድኩም።
ምክንያቱም ቤተ መንግሥቱን ከለቀቅንበት ሰዓት ጀምሮ በየጊዜው ከኛ እየተለዩ ራሣቸውን ችለው በሚሸሹት ሰዎች ላይ ገርማሜም ጀኔራልም መልካም አስተያየት እንዳልነበራቸው አውቅ ስለነበር ነው፡፡
ሌሊት ከተኛንበት አንድ ጥይት ተተኮሰ፤ በሁኔታው ተደናግጠን ስንጠያየቅ የጀኔራል ሹፌር “ታከለ ራሱን ገደለ” ተባለ።
ከዚያ ትንሽ ቆየት ብለን ወገግ ሲል (ቅዳሜ) በራጉኤል ቤተክርስቲያን ጀርባ ጥቅጥቅ ካለ ጫካ ገብተን ተቀመጥን።
ቀረብ ካለው መንደር ትንሽ የሚበላ ነገር ገዝተን በመመገብ ለዓይን እስኪይዝ ድረስ በዚሁ ቦታ ቆየን።ቅዳሜ ማታ ተረተሩን ተከትለን ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ እስከመንፈቀ ሌሊት ግድም ተጓዝን፡፡ድካም በጸናብን ጊዜ ትንሽ ዕረፍት አደረግንና በዚያው መተኛት ጀመርን።
አሁን ዕዳሪ የምወጣ መስየ ለመለየት ቻልኩ።
ስንዴ እሸት እየበላሁ፣ ቀን እየተኛሁና በጨለማ እየተጓዝኩ በየረር ተራራ አጠገብ ከሚኖር የዘመድ ቤት ሰኞ ጧት ደረስኩ። በዚህ ቦታ ተቀምጨ እጃቸውን የሚሰጡ የክብር ዘበኛ መኮንኖች በምን ሁኔታ እንደተያዙ በሰላይ ካስመረመርኩ በኋላ ረቡዕ ጧት በፈቃዴ እጄን ሰጥቼ መሣሪያዬን አስረከብኩ።
በዚህ እጄን በሰጠሁበት ቦታ (ሦስተኛ ሻለቃ ሠፈር) ውየ ከሰዓት በኋላ ወደ ፍል ውሃ ቤተ መንግሥት ተወሰድኩ።ንጉሱ በአሁኑ ሰዓት ዋና ሥራቸው የሞቱትን ሰዎች ፊት (እንደነ ወርቅነህ ያሉትን) ማየትና ከተያዙት መኮንኖች መካከል ደግሞ በከባድ ኃላፊነት ተሰማርተው የነበሩትን ማነጋገር ነበር።ቀደም ብለው ለጥያቄ ከቀረቡት መካከል ሻለቃ ተፈራ ወልደ ተንሣይ ዋናው ነበር።
ንጉሱ “ተፈራ ትከዳን!” ብለው ላቀረቡለት ጥያቄ ሻለቃ ተፈራ የሚከተለውን አጉል መልስ ያለጊዜው ይናገራል፤
“ጃንሆይ አኔ አልከዳሁም፡፡አለቃችሁን ታዘዙ አላሉነም ራስዎ? ይልቅስ በአሁኑ ሰዓት እኔን የሚያሳዝነኝ፣ አለቃየ ባዘዙኝ መሠረት እነ ጀኔራል መርዕድን ሳልማርክ መቅረቴ ነው።”
ሻለቃ ይህን መልስ በሚሰጥበት ጊዜ እነ ጀኔራል መርዕድና ሌሎቹም ከፍተኛ መኮንኖች በንጉሱ ዙፋን ግራና ቀኝ ቁመው ነበር።
ሻለቃ ተፈራ የ15 ዓመት ጽኑዕ ዕሥራት የተፈረደበት፣ በመጸጸት ፋንታ ይህን ዓይነት ኃይለ ቃል በመናገሩ ነው ይባላል።
እኔ ግን ወደ ንጉሱ ለጥያቄ ሳልቀርብ፣ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ሁሉም መኮንኖች ወደታሰሩበት ወደ 4ኛ ክፍለ ጦር (መሿለኪያ) ተወሰድኩ።
በዚህ በራሴ አስተዋጽኦ ሐተታ እንደሚታየው ፣ እኔ በታኀሣሥ የታሪክ ዛፍ አንዲት ቅንጣት ቅጠል ነኝ።በዚህም ምክንያት ሊሆን ይችላል ወደ ንጉሱ ከመቅረብ የዳንኩ።
4ኛ ክፍለ ጦር (መሿለኪያ)
በፍርድ ወይም ያለ ፍርድ በጽኑዕ እሥራት ወደ ልዩ ልዩ ወህኒ ቤቶች ከመላካችን በፊት ሁላችንም ለስድስት ወራት ያህል በዚህ ቦታ ታስረን ቆይተናል።
የምርመራ ኮሚሽን ተቋቁሞ በነፍስ ወከፍ ወይም በቡድን የሠራነው ሁሉ እየተመረመረ ነው።የምርመራው ሥራ እንደተገባደደ፣ የተለየ ወንጀል ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረ ወይም በቂ ማስረጃ እጅ ከፍንጅ የተገኘበት ሰው ወደ መደበኛ ፍ/ቤት እየቀረበ እንዲፈረድበት ንጉሱ የፖለቲካ ውሣኔ ሰጥተው ሥራው ተጀምሯል።
ከዚህ የፍርድ ቤት ሥራ አንዱ ጉዳይ እኔን የሚመለከት ይሆናል፡-
የመቶ አለቃ ድጋፍ ተድላ መኳንንቱን ተኩሰው ከገደሉት መኮንኖች አንዱ ነው ተብሎ ሶስተኛ ተከሣሽ ሁኖ ከነጄኔራል መንግሥቱ ጋር ፍ/ቤት ቀርቧል።
አቃቤ ሕግ የመቶ አለቃ ድጋፍን ክስ የመሠረተው በተገደሉት ሰዎች ላይ ተኩስ ሲከፈት አንዱ በአጋጣሚ ከጥይት የተረፈ ሰው ፣ “ድጋፍ ተድላ ሲተኩስ አይቸዋለሁ፡”
ብሎ በተናገረው የዓይን ምስክርነት ቃል ነው።
የመቶ አለቃ ድጋፍ ተድላ መኳንንቱ በተገደሉበት ሰዓት በቤተ መንግሥት ላለመኖሩ አብሮት የነበረውን መኮንን በመከላከያ ምስክርነት ቢጠራው፣ አብሬ ነበርኩ ማለቱ ራሱን በነፍሰ ገዳይነት ስለሚያስጠረጥረው ለመመስከር ፈቃደኛ አልሆነም።
ችግሩን ራሱ ድጋፍ ገልጾልኝ እንድመሰክርለት ይጠይቅ ወይም እምቢ ካለው መኮንን ጋር ሲነጋገሩ ልስማ ለይቼ አላስታውስም።
በዓይነ ሕሊናዬ እስከአሁን የማይረሳኝ ግን፣ “እኔ እመሰክርልሃለሁ” ብየ ፈቃደኛነቴን በገለጽኩለት ጊዜ በድጋፍ ተድላ ፊት ይታይ የነበረው ብሩህ ፈገግታ ነው።
ምስክርነቴ በራሴ ለይ ሊያስከትል ስለሚችለው ሁኔታ እምብዛም የተገለጸልኝ ነገር አልነበረም።እኔ ከዓርብ ጧት እስከ ሰዓት በኋላ 10 ሰዓት ግድም (ቤተ መንግሥቱን እስክንለቅ ድረስ) ከዚያው የነበርኩ ስለሆነ የኔ ምስክርነት ድጋፍን እንደሚያድነው ጥርጣሬ አልነበረኝም።
በፍርድ ቤቱ እለተ ቀጠሮ ሦስት ዳኞች በተቀመጡበት ችሎት ቀርቤ፣ መኳንንቱ በተገደሉ ጊዜ የድጋፍን አለመኖር በማያጠራጥር አነጋገር አስረዳሁ።
ከሦስቱ ዳኞች አንዱ ከፍተኛ የጦር መኮንን ሲሆን ሁለቱ ሲቪል ነበሩ።ጄኔራል መንግሥቱን ከመሞታቸው በፊት ለመጨረሻ ጊዜ አሁን አየኋቸው።የድጋፍን አለመኖር ራሣቸው ያውቁ ስለነበር፣ እኔ በምሰጠው የምስክርነት ቃል መደሰታቸውን በፈገግታቸው ተረዳሁ።
በመጨረሻ የጦር መኮንኑ ዳኛ የኔን ምስክርነት ቃል በብቃት በመቀበል፣ በፍርድ ውሣኔ ጊዜ በሃሳብ ተለይቶ ድጋፍን ከሞት ፍርድ ለማዳን ችሏል።
ምናልባት “ለታኀሣሥ አስተዋጽኦ ምን አደረግክ” ብባል ልበ ሙሉ ሁኜ የምናገረው ስለድጋፍ የሰጠሁትን ምስክርነት ብቻ ይሆናል።
ከጦር ሠራዊትና ከፖሊስ መኮንኖች በተውጣጡ የተቋቋመው የምርመራ ቡድን የራሱን ድርሻ ከአጣራ በኋላ ጉዳያችን በከፍተኛ ደረጃ ለተመደበው ኮሚሽን ይተላለፍ ነበር።
የወታደሩ ቡድን ምርመራውን ያተኮረው በመፈንቅለ መንግሥቱ የምስጢር ተካፋዮች ይሆናሉ ተብሎ በተጠረጠሩት ጥቂቶች መኮንኖች ላይ ነበር። እነዚህ መኮንኖች ከሃያ የማይበልጡ እንደነበሩ እገምታለሁ።
በከንቱ ከተጠረጠሩት አንዱ እኔ ስለነበርኩ የማውቀው ምስጢር እንዲሌለ በተለያየ መልክ ለማስረዳት ሞከርኩ። ከቀረበልኝ ጥያቄ ሁሉ እጅግ በጣም አስግቶኝ የነበረው የሚከተለው ነበር፡-
- ቀደም ብለህ በሰጠኸው ቃል መሠረት ከቤተመንግሥት ከጧት እስከማታ ድረስ ነበርክ። ይኸ ከሆነ ዘንድ ደግሞ መኳንንቱ ሲገደሉ አይተሃል ማለት ነው።ወይስ የት ነበርኩ ትላለህ?
መኳንንቱ ተገደሉ የሚባለው በምድር ቤት እንዳሉ ነው።እኔ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ የነበርኩት በደርቡ (ፎቅ) ሲሆን፣ ጊዜው በምድር ቤት የተፈጸመውን ተኩስ ከውጭ ከሚመጣው ተኩስ የማይለይበት ሰዓት ነበር።
- ለመሆኑ መኳንንቱ መገደላቸውን ምን ጊዜ አወቅህ – ከማንስ ሰማህ?
ነጋሽ ነው የነገረኝ አልኩ፣ (በዚያን ጊዜ እጁን ሳይሰጥ እንዳመለጠ አስታውሸ፡፡)
ራሴን በነፍስ ገዳይነት ከመጠርጠር ለማዳን ስል ከዚህ በላይ እንደተመለከተው አድርጌ መልስ ሰጥቻለሁ፤በትክክል የነበርኩበት ሁኔታ ግን እንደሚከተለው ነበር፡-
እኔ በምድር ቤት ነው የነበርኩ። ሰዎቹ የተገደሉት በሁለት ተከፍለው ነው።ራስ አበበና አቶ መኮንን ሃብተ ወልድ (ሌላ መኖሩን አላስታውስም) ተለቅቃችኋል ውጡ ተብለው በበራፉላይ እንደደረሱ በጀርባቸው ነው የተመቱት። በሳሎን የተገደሉት በምን ሁኔታ እነደነበር አላየሁም።እንዲገደሉ ያዘዙት ግን ሁለቱ ወንድማማቾች ይሆናሉ ብየ ገምቻለሁ።
ገርማሜና ጀኔራል መንግሥቱ የግድያውም ተካፋዮች ሁነው አይቻለሁ።ሌላ ሰው ግን ቃታ ስቦ ሰው ሲገድል ያየሁት የለኝም።
የምርመራው ጊዜ ካለቀ በኋላ ነጋሽ ተይዞ ለፍርድ ሲቀርብ `በምርመራ ጊዜ ስለሱ የተነጋገርኩትን በፍ/ቤትእንድመሰክር ተጠይቄ ፈቃደኛ ባለመሆኔ የማስፈራራት ቃል ተሠንዝሮብኝ ነበር።በኋላ ግን ተረሣልኝ መሰል ።
የምርመራውን ጉዳይ ልቀጥልና፡-
በእሥራት ጊዜ አጅግ ከባድ የሚሆነው ነገር ከሰው ተለይቶ መቀመጥ ነው።ሰው ታስሮም ቢሆን ከሌላ ሰው ጋር መነጋገር ከቻለ ይህ መብት ታላቅ ፀጋ ነው።
ከባድ ምርመራ በተደረገበት ሰሞን፣ ጥቂቶች መኮንኖች ሁሉም እሥረኛ ከሚገኝበት አዳራሽ ወጡና በሌላ ቦታ በተለያየ የጨለማ ክፍል እንዲታሰሩ ተወሰነ።
ከሰው ጋር መተያየት መነጋገር ቀረ። ከክፍሉ ጨለማ ክብደት የተነሣ ቀኑንና ሌሊቱን መለየት አይቻልም ነበር፡፡ በከንቱ ከተጠረጠሩት ከነዚህ እሥረኞች መካከል አንዱ እኔ ነኝ።
አሥራስምንት ቀን ሙሉ በጨለማ ቤት ስቀመጥ እጀን በሰንሰለት ታስሬ እህል ስበላ ብቻ ይፈታልኝ ነበር፤
ወደ ምርመራ ክፍል የምወሰደው ማታ ማታ ሲሆን ከምርመራ በኋላ የምሸኘው በሚያስፈራ ዛቻ (በግልጽ አነጋገር አይሁን እንጂ)“ትደበደባለህ!” በሚል ቃል ነበር።
ብፈራም ለሚቀርብልኝ ጥያቄ የምሰጠው መልስ በከፍተኛ ጥንቃቄ ነበር።
ከሁሉ ነገር ይበልጥ የረዳኝ ግን፣ ከምረመራው ቡድን ይቀረብልኝ የነበረው የጥያቄ ዓይነት እንደሚከተለው ያለ ልኩስኩስ መሆኑ ነው፡-
- ወደ ህንድ አገር ለሚሊተሪ ኮለጅ ተልከሃል፣
- ከትምህርት ስትመለስ አዲስ መኪና ተገዝቶልሃል፣
- ልዩ መምሪያ በተሰኘ ቢሮ ተቀምጠህ የጀኔራል አማካሪ ነበርክ
- መኳንንቱን እንዲጠብቁ ሌሎች መኮንኖች አዝዘሃል።
የዚህ ሁሉ ድምር –
“ባለሟል ነበርክና ምስጢር ተውቃለህ” ነው።
አልሳካላቸው ሲል በመጨረሻ በድብደባ ወደሚያሳምኑ ልዩ ሰዎች ተላኩኝ።እነዚህ ሰዎች ከቡድኑ ቀርቦልኝ የነበረውን ጥያቄ መልሰው መልሰው አሰሙኝ ፤ መልሴ ያው ሲሆንባቸው የእጅ ብረት አቀረቡ፡። እንደዚህ ያለ የእጅ ብረት አይቼ አላውቅም።
ሁለት እጄን የኋሊት አስረው ማጥበቅ ጀመሩ፤ ቆም ይሉና ጥያቄውን ይደግማሉ።
ከዚያ እያጠበቁ፣ እያጠበቁ ሲቀጥሉ ከመድከሜ የተነሣ መልስ መስጠት ያቅተኛል።
በአሁኑ ሰዓት ፍርሃት የሚባል ነገር ከአይምሮዬ ጠፍቷል።
ስቃይም አልነበር የሚሰማኝ፣ ብቻ ደሜ ሁሉ በጣቴ ፈስሶ- ፈስሶ ያለቀ መስሎኝ ነበር። ሌላው የማስታውሰው ሰውነቴ በላብ ተጠምቆ እንባዬ እነደ ጐርፍ ይወርድ ነበር።በመጨረሻ ወደ ጨለማ ክፍሌ እንዴት እንደተመለስኩ አላስታውስም።በበነጋው ግራ እጄ ሰልሎ አገኘሁት።
ከጨለማው ቤት ወጥተን (ወደ ቀሩት እሥረኞች ከተጨመርን በኋላ) ስንወያይ በኔ የደረሰው ስቃይ ዓይነት ያልገጠመው ሰው አልነበረም።
አንዳንዶቹ እንደነሻለቃ ተፈራ ወልደተንሣዬ ያሉት የበለጠ ስቃዩ ደርሶባቸው ነበር።
በዚህ በደረሰብኝ ድብደባ ምክንያት እስከ አሁን ድረስ በግራ እጄ ትንሽ እጣት ዳስሶ የመለየት ኃይል የለኝም።
በዚህ ሁኔታ ጉዳት የደረሰባቸውን መኮንኖች ለማከም የቀይ መስቀል አስፈቅዶ ገብቸ ነበር።
ተሰጥቶኝ የነበረው የሚዋጥ መድኃኒት ምን ያህል እንደረዳኝ መገንዘብ ባልችልም፣ የነበረውን የፖለቲካ ተጽዕኖ ተቋቁመው በዚያ ክፉ ቀን የደረሱልንን የሕክምና ሰዎች አመሰግናለሁ።
ወንጀላችን በወታደራዊው የምርመራ ቡድንና በዋናው ኮሚሽን ተጠናቆ እንዳለቀ፣ ፍርዳችን በሁለት መልክ ተሰጠ፡፡
- በቂ ማስረጃ ተገኝቶባቸዋል የተባሉት መኮንኖችና ሲቪሎች በግል እየተከሰሱ ወደ መደበኛ ፍ/ቤት በመቅረብ ቅጣታቸው እንዲወሰን፣
- በቂ ማስረጃ ያልተገኘብን ሰማኒያ የምንሆነው፣ የሶስቱን ዓመት ጽኑዕ እሥራት የሰማነው ከፈረደብን ፍ/ቤት ሣይሆን በችሎት ካልተቀመጡ ከጦር ሠራዊት መኮንኖች ነው።
የክብር ዘበኛ ተራ ወታደሮችና ባለሌላ ማዕረጐች ለጥቂት ቀናት ያህል በጥበቃ ሥር ከቆዩ በኋላ በዋስ በነጻ ተለቅቀው በየቦታው በሚገኘው የጦር ሠራዊት ኃይል ተመድበው በወታደራዊ አገልግሎት እንዲቆዩ ተደርጓል።
የሰምና ወርቅ መጽሔት አዘጋጅዎች ማሳሰቢያ፤
ሻለቃ ያሬድ ቢተው ለአቶ ጳውሎስ አሰፋ ይህን ጽሑፍ የላኩት ስለአባቱ ስለአቶ አሰፋ ዱላ የሚያውቁትን እግረመንገዳቸውን በጽሑፍ እንዲያሰፍሩ የራሳቸውን የግል ታሪክ እንዲጽፉ ባነጋገራቸው መሠረት እንደነበር ራሱ አቶ ጳውሎስ ነግሮናል። አቶ ጳሎስ አሰፋ ደግሞ ይህን ጽሑፍ እንዲታተም ለመጽሔቱ አዘጋጅ ለአቶ ፈንታሁን ልኮለት ጽሑፉ ተተይቦ ለህትመት ከተዘጋጀ ብዙ ዘመን አልፏል። ይህ የሆነበት ምክንያት የሻለቃ የእጅ ጽሑፍ አንዳንድ ቦታ ላይ ለማንበብ አስቸጋሪ ስለነበር እርሳቸውን ጠይቀን ለማስተካከል በነበረን ሃሳብ ምክንያት ነበር። ሻለቃ በዋሺንግተን ዲሲ ዋና ከተማ እንደሚኖሩ በአቶ ጳውሎስ ከተጠቆመልን ጊዜ አንስቶ እርሳቸውን በአካል ተገናኝተን ጽሑፉን አስተካክለን ለማውጣት ብዙ ሙከራ አድርገን አልተሳካልንም። አሁን ግን የጽሑፉን ታሪካዊ ፋይዳ በመመልከት አትመን ለማውጣት ተስማምተናል። ለማንበብ በተቸገርንበት ቦታ ላይ የጥያቄ ምልክት አድርገንበታል።
በጽሁፉ ውስጥ የተካተቱት ቁምነገሮች የመጀመሪያ ደረጃ ምልከታ ምዝገባ ተብለው ከሚጠቀሱት የታሪክ ማጣቀሻ ማስረጃዎች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው። የታሪክ ማስረጃው ለአንባቢያን ከሚሰጠው ጠቀሜታዎች ውስጥ አንዳንዱን ለመጠቃቀስ ያህል፦
በስነ-ጽሁፍ አቀራረብ ረገድ በወቅቱ የነበረውን የጦማር አጻጻፍ ስልት አጉልቶ በማሳየት በዘመናት መካከል የተፈጠረውን የደብዳቤ እንዲሁም ታሪክ አዘጋገብ የእድገት ወይም ውድቀት ደረጃ አጉልቶ የሚያሳይ በመሆኑ ለስነጽሁፍ ተመራማሪዎች የሚሰጠው ፋይዳ ቀላል አይሆንም።
ከታሪክ አንጻር የወሰድነው እንደሆነ በወቅቱ የተሟላ ማስረጃ ያልተገኘላቸውን እውነታዎች ለህብረተሰባችንና ለታሪክ ተመራማሪዎች በመስጠቱ ረገድ የላቀ አስተዋጻኦ ይኖረዋል:: በዋናነትም የግለታሪክ ዘጋቢው በኩነቱ ወቅት እርምጃው በተወሰደባቸው ቀናት ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ በመሆናቸው በአይናቸው የተመለከቱትን የዘገቡ በመሆኑ ከዚህ በፊት ኩነቱን አስመልክቶ የተጻፉ የጥናትና ምርምር ስራዎች ጉድለት በማሟላቱ ረገድ ፋይዳው የጎላ ነው።
በመጨረሻም የታሪኩ ዘጋቢ ከሁነቱ በፊት በነበረው ሂደት ያልተሳተፉ ነገርግን የኩነቱ አራማጆች የባለታሪኩ አስተዋጽኦ ያስፈልጋል ብለው ባሰቡት የድርጊቱ ቀንና ሰአት በቦታው እንዲገኙ መደረጋቸው በተገደበ ቦታና ጊዜ የሆነውን ብቻ የዘገቡ በመሆኑ ለእውነታው እጅግ የቀረበ ሆኖ አግኝተነዋል።



