እንሰት – ከቆጮና ቡላ ባሻገር

የእንሰት (ቆጮ ቡላ አሚቾ፤ ኮባ) ምግብነት መድኃኒትነትና የኢንዱስትሪ  ግብአትነት አስተዋጽኦዎች

ገብርኤል ዳንኤል (አክሊለ /ጊዮርጊስ)

(ታህሳስ 2018)

መግቢያ

 ይህ ጽሁፍ የእንሰትን ዘርፈብዙ ጠቀሜታና ታሪክ በተለይም መድኃኒትነቱ ላይ  ያተኮረ ይሆናል። እንሰት፤ በሳይንሳዊ ስሙ እንሰት ቬንትሪኮሰም (Enset ventricosum or edule) ከዓለም ሁሉ በኢትዮጵያ ብቻ በምግብነት ጥቅም ላይ የዋለ ዘረ ሙላዱም ከኢትዮጵያ የሆነ የተክል ዓይነት ነው።

የአገሪቷ አንድ አምስተኛ (20%) የሚሆነው ሃያ ስድስት ሚሊዮን (26 ሚሊዮን) ሕዝብ የእንሰት ተጠቃሚ እንደሆነ ይገመታል።

ተክሉና ዝርያው ከሙዝ ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ በእንግሊዝኛ “የውሽት ሙዝ” (false banana) ተብሎ ይታወቃል።  ግንዱ፤ ስሩ፤ ቅጠሉ (ኮባው) እና ቃጫው በብዛት ጥቅም ላይ ይውላሉ።

እንሰት ከአስር ሺህ ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ሰሜን፥ ደቡብና ምዕራብ የታወቀና ጥቅም ላይ የዋለ እንደሆነ ታሪክ ይናገራል።  በጣና ሐይቅ፣ በሰሜን ተራራዎች ዙሪያ እንዲሁም እስከ ሰሜን አዲግራትና በደቡብ ኤርትራ በማእከላዊና ሰሜን ደጋማ አካባቢዎችም ያድግ እንደነበር ታሪክ ያስታውሳል።

እንሰት ከሶስት መቶ በላይ የተለያዩ ዝርያዎች አሉት። እንደ ዝርያዎቹ ዓይነት ጠቀሜታዎቻቸውም እንዲሁ ይለያያሉ፤ ለምሳሌም ድርቅንና በሽታን ለመከላከል፤ ለመድኒትነት፤ ለምግብነት፤ ለቤት መገልገያ፤ ለኢንዱስትሪ ግብአትነት ወዘተ።

ወፍ ዘራሹ እንሰት በብዛት ከፍሬው የሚበቅል ሲሆን በእርሻ የሚገኘው ግን 2-3 ዓመት ከሆነው ከአሚቾ የሚበቅለው ነው። ወፍ ዘራሹ እንሰት ከናይጄሪያ አንስቶ ሱዳንን ይዞ እስከ ደቡብ አፍሪቃ ድረስ እንደሚበቅል ተጽፏል። ነገር ግን በነዚህ አገሮች እንሰት ለምግብነት አይውልም።

እንሰት በጉራጌ እሴት/እሰት፥ በሲዳሞ ዊሴ፥ በዳውሮና ወላይታ ኡጦ፥ በጌዴዎ ዎርኪቻ፥ በሃዲያ ስልጤና ከምባታ ዊሳ፥ በትግሬ ጉና ጉና በመባል ይታወቃል። ለብዙ የቤት አገልግሎት የሚውለው ቅጠሉ ኮባ ይባላል።  በምግብነት የሚቀርበው ደግሞ እንደ አካባቢው ቆጮ (ዉሳ፥ ዋሳ፥ ወርቄ…)፥ አሚቾ፥ቡላ ወዘተ እየተባለ ይጠራል።

እንሰት በተለየ መንገድ ከሕዝቡ ስነ ልቦናና ባህል ጋር ቁርኝት አለው፥ በአንዳንድ አካባቢዎችም መንፈሳዊ ገፅታ ተሰጥቶት ይገኛል።

እንሰት ዓመት ከዓመት (እስከ 12 ዓመት) የሚበቅልና ለምግብነት ከተዘጋጀ በኋላ ለወራት ሊቆይ የሚችል፤ ለቤተሰብ ዋንኛ የምግብ ዋስትና የሚሰጥ፤ የአየር ለውጥን የሚቋቋም፤ እራሱን በራሱ የሚተካ፤ ብዙ መሬት የማይፈልግ ሁለገብ ተክል ነው። እንሰት “ጸር ረሃብ ወይም ነፍስ አድን” ተክል ተብሎ ይታወቃል። በተጨማሪም ለመድኒትነት፤ ለአካባቢ ውበት፤ ለአፈር እርጥበትና ለምነት፤ ለእንስሳት መኖነት፤ ለባህላዊ ቤት ሥራ፤ ለኢንዱስትሪ ግብአትነት ወዘተ ይጠቅማል።

የእንሰት መድኒትነት፤ ባህላዊ ፤ እምነታዊና ስነልቦናዊ እሴቶች እንደአካባቢዎቹ የተለዩ ናቸው። በልደት፤ ሃዘን፤ ደስታ ጊዜ የእንሰት ምርቶች በምግብነትም ሆነ በሌሎች መንገዶች ጥቅም ላይ ይውላሉ። አንዳንድ እንሰቶች መጥፎ መንፈስን እንዲከላከሉ ቤት በራፍ ላይ ይተከላሉ።

እንሰት ቢጫማ ቀለም ያለው ትናንሽ ሙዝ የሚመስሉ ግን የማይበሉ ፍሬዎች ግንዱ ጫፍ ላይ እድሜው ሊያበቃ ሲል ያፈራል። ከፍሬዎቹ ውስጥ የሚገኙት ለዘር ሊሆኑ የሚችሉ እንክብሎች ይገኛሉ። ፍሬው ተተክሎ ችግኝ ማፍራት ቢቻልም የተለመደውና የተሻለው የእርሻ ዘዴ ግንዱን ዝቅ አድርጎ በመጉመድ ወይም ከአሚቾው ችግኞች እንዲወጡ/እንዲፈሉ በማድረግ ነው። ከሙዝ ተክል የሚለየው ፍሬው እንደ ሙዝ አለመበላቱ ነው።

የእንሰት ጥቅሙ በተወሰኑ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በመሆኑ እንደሌሎቹ የምግብ አዝርእቶች ትኩረት አልተሰጠውም።

እንሰት በታሪክ

የእንሰት እርሻ ከአስር ሺህ ዓመታት በፊት ዖሞቲክና ምስራቃዊ የኩሽ ዘሮች (ሲዳሞ ዘሮች) ተጀመረ የሚሉ ታሪክ ጸሐፊዎች አሉ። ሌሎችም ከጉራጌ፥ ከከፋ ተጀመረም የሚሉ አሉ። በኋላም የአገው ሕዝቦች በሰሜኑ አካባቢ እንዳስፋፉት የሚናገሩ አልጠፉም።

ከ1600 እስከ 1800 ዓም በኢትዮጵያ የተጓዙ ያውሮፓ ሰዎች (እንደ ማኑኤል ደ አልሜይዳ፥ ፋዘር ጆሮኒሞ ሎቦ፥ ዋልተር ፕላውደንና ጄምስ ብሩስ ያሉት) እንሰት በሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢዎች  እንደሚበቅልና ለምግብነትና ለሌላ ጥቅሞች እንደሚውሉ በጽሑፎቻቸው አስፍረዋል። በደረስጌ ሁለት ዐይነት እንሰት እንደታየና አንዱ ጉናጉና የሚባል እንደሆነም ተጠቅሷል። ጉናጉና የሚባለው በትግራይ ሰሜን ክፍል የሚገኘው ቦታ ስም ከዚህ የተወሰደ ሳይሆን አይቀርም። ከ1850ዎቹ ገደማ ጀምሮ ከሰሜኑ ተመናምኖ በደቡቡ ተስፋፍቶ ይገኛል። ከሰሜኑ መጥፋቱ በድርቅ፥ በበሽታ ወይም  በአካባቢ ሠላም መጥፋት እንክብካቤ በማጣቱ ይሆናል የሚሉ መላ ምቶች ይሰነዘራሉ። አሁንም በአንዳንድ ሰሜኑ አካባቢዎች እንሰት ይታያል። ለአብነትም የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከጣና ሐይቅ ፏፏቴ ሥር የእንሰት ተክል እዚህ በሚታየው ፎቶግራፍ መዝግቦታል።

ስለእንሰት ጠቃሚነት ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት አንስቶ ጥንታዊ ከሆነው ከእናሪያ ሕዝብ ሲነገር የቆየው፤ “የእንሰትን ተክል የድሮ ሰዎች ተርበው ሳለ በድንገት ከደን አግኝተው ሥሩን ነቅለው አሚቾ የተባለውን እንደ ድንች ያለውን ጠብሰው በልተው ስለ ጠገቡና ጤና ስለ ሆናቸው በዚያው ተለምዶ በዙሪያው ያለ ሕዝብ ሁሉ ጥቂት በጥቂት ሲል መደበኛ ምግብ አደረገው” የሚል ነው። (ብዕለ ገራህት)

በእንሰት ዙርያ  የሚነገሩ አፈ ታሪኮች

የአፄ አምደ ፅዮንን ጦር ተክትለው ጉራጌ አገር ለአርባ ዓመታት የኖሩ አባ ዜናማርቆስ የተባሉ መነኩሴ ከሙኸር ጉራጌ ወደ ሌላ አካባቢ ለአጭር ጊዜ ለመሄድ ሲነሱ ላማቸውን ለአንድ ሰው አደራ ሰጥተው ይሄዳሉ። ከሄዱበት ሲመለሱ የሰጡትን ሰው ላሟን ቢጠይቁት መሞቷንና እንደቀበራትም ይነግራቸዋል። ሄደው የተቀበረችበትን ቦታ ሲያዩ የተለየ፥ ሰፋፊ ቅጠሎች ያሉት ተክል በቅሎበት አዩ። ቢበሉትም መልካምና መዐዛ ያለው መሆኑን አይተው ይህ የአምላክ እሴት ነው አሉ። ከዚህም በኋላ እንሰት/እሴት የሚለውን ስም ያዘ ይባላል። የህይወት ዛፍ በመባል ከጉራጌ ህዝቦች ህይወት ጋር ይተሳሰራል። ከመንግሥተ ሰማይ የመነጨ የአምላክ ስጦታም በመባል በየወሩ እንደ በዓል ይታሰባል። ከዚህ ጋር የሚቀራረበው ታሪክ ደግሞ የአምደ ጽዮን ጦር ይዞት መጥቶ ያስተዋወቀው ነው የሚል ነው።

ሌላው አፈታሪክ እንዲሁ በአንድ የጥንት ንጉሥ ጊዜ አንድ ሰው አካባቢውን ትቶ እንዲሰደድ ይታዘዛል። ቤተሰቡን ይዞ አንዲት ላም ከነጥጆቿ እየነዱ በወተቷ እይተጠቀሙ ቆዩ። በጉዟቸው በጣም ስለጠቀመቻቸው ወርቄ (የኔ ወርቅ) ብለው ላሟን ሰየሟት። በመቃብሯም ላይ ለየት ያለ ሰፋፊ ቅጠሎች ያሉት ሲመገቡት የሚጥም ተክል በቀለ። ምግቡንም በላሟ ስም ወርቄ አሉት ይባላል። በሲዳሞ አካባቢ እንሰት ዋሳ ወይም ወርቄ ተብሎ ይታወቃል።

ሌላው አፈ ታሪክ ደግሞ እንሰትን ከሰማይ እንደ መጣ ይናገራል። አዳም በገነት ሲኖር ላም ነበረችው፥ ከእበቷም አንድ ትንሽ እንሰት በቀለች፥ ፍሬዋን ጃርት በላችው፥ ጃርቷም በተፀዳዳችበት ቦታ ሁሉ ችግኙ ፈላ ይባላል።

የእንሰት ምግብነት

በምግብነት የሚታወቁት ሶስቱ የእንሰት ዋና ዋና የምግብ ዐይነቶች ቆⶐ፥ ቡላና አሚቾ ናቸው።

ቆጮ ከእንሰት የሚገኘው ዋናውና በብዛት ለምግብ የሚውለው ነው። ከፍተኛ የካርቦሃይድሬትና ስታርች (carbohydrate and starch) ምንጭ ነው። መጠነኛ ፕሮቲን (protein) ስላለው በሰውነት ገንቢነቱ እምብዛም አይታወቅም::  በርካታ አሚኖአሲዶች (aminoacids) ይገኙበታል። በተለምዶ ቆጮ ሲበላ ከጎመን፤ ስጋ/ክትፎ፤ አይብ ጋር ስለሆነ የተሟላ የምግብ ዓይነት ያደርገዋል።

ቆጮ

ቆጮ ከእንሰቱ የግንድ ሽፋን ተፍቆ የሚገኘው ውጤት ነው። ጭማቂው በኮባ (የእንሰት ቅጠል) በጉድጓድ እንዲቦካ ተጠቅልሎ ይቀመጣል። ቆጮው ቶሎ እንዲብላላ (ferment) አሚቾ ተከታትፎ ይጨመርበታል። ውሃውን በመጭመቅና በውስጡ ተቀላቅሎ የሚገኘውን ቃጫ ለማስወገድ በመክተፍና በማፅዳት ይዘጋጃል። ተቆፍሮ ከተቀበረው ቆጮ እየተቆነጠረ በመውሰድ በተለያየ መንገድ ለምግብነት ተዘጋጅቶ ይቀርባል። ቆጮው እንደ ቂጣ/ዳቦ (በሲዳምኛ ቄቄሎ፥ ዱባሜ/ዱዋሜ ወዘተ)፥ ፍርፍር  (በሲዳምኛ ፉርፉራሜ፥ ፊንጢራሜ፤ቡሩሳሜ)፥ እንደ እንጀራ (በሲዳምኛ ኦሞልቾ) መልክ ተዘጋጅቶ ለምግብነት ይውላል።

ቡላ

ከግንዱ ከተፋቀው ፍሳሽና ከአሚቾ ተቀላቅሎ ለብቻው እንደ ውሃ ኩል ብሎ ወጥቶ፤ ዝቃጩ ተጣርቶ የሚገኘው ንጹሑ ዱቄት ቡላ ይባላል። ቡላ ጠቃሚነቱን ለመግልጥ በጉራጌ “የእንሰት ቅቤ” ይሉታል። ለምግብነት በሚውልበት ጊዜ በተለያየ መልኩ ተዘጋጅቶ ይቀርባል።  ቡላ (በጉራጌ አጥሜጥ) በቂጣነት፥ በፍርፍር፥ በገንፎ፥ በአጥሚት መልክ በቅቤ፥ በአይብ፥ በክትፎ ይበላል። ቡላ ጥሩ ገንቢ ምግብ ነው። ለደም ማነስ፥ መልክን ለማሳመር፥ ክብደትን ለመቆጣጠር ቡላ ይረዳል።  የቡላ ሙቁ በቅቤ ተሰርቶ ሳል ለማቆም ይረዳል፥ ፍርፍሩም በቅቤና ሚጥሚጣ ለተቅማጥ ማቆምያ ይረዳል።

አሚቾ  (ሃሚቾ/Corm)

አሚቾው የእንሰቱ ስር እንደ ዋልታ ሆኖ የሚያቆመው ድንች/ቦይና መሰሉ ክፍል ነው።  ለቆጮ፤ ለቡላና መሰል ምግቦች መሥሪያነት ያገለግላል። ስሩ በሰሎና ተቆራርጦ እንደ ድንች ይበላል።  ካልስየምና ብረት (calcium and iron) እንዲሁም አርጂኒን (arginine) የሚባለው አሚኖአሲድ (aminoacid) በብዛት ስላለው የአጥንት ስብራትና ተመሳስይ ችግሮችን ለማከም ይረዳል።

አሚቾ ከምግብነቱና (እንደ ድንች) መድኃኒትነቱ በተጨማሪ የእንሰት ችግኞችንም የማፍያ/ማራቢያ መንገድ ነው። አሚቾው ሁለት ሶስት ቦታ ተከፍሎ ሲቀበር እስከ 200 መቶ ያህል ችግኞች ይፈላሉ፤ እነዚህ እንደገና ራቅ ራቅ ተደርገው በተደጋጋሚ እንዲተከሉ በማድረግ አዳዲስ እንሰቶች ይባዛሉ። አሚቾ  ለምግብም እንደችግኝ ማፍያም ስለሚውል ተፈላጊነቱን ከፍ ያደርገዋል። ስለዚህም አሚቾን በብዛት ማግኛ ዘዴዎች ቢጠኑ አሚቾን እንደልብ በተፈለገው መጠን ለማግኘትና ጥቅሙን ለማስተዋወቅ ይረዳል።

በእንሰት ምግቦች ውስጥ የሚገኙ ጠቃሚ ንጥረነገሮች

የእንሰት የተለያዩ የምግብ አይነቶች ጥሩ የጉልበት ሰጭ ካርቦሃይድሬት (carbohydrate) ምንጭ ናቸው። በጣም ጠቃሚ የሆኑ መዓድናት (minerals) እንደ  ካልስየም፤ ፖታስየም፥ አይረን፤ ማንጋኒዝ፥ ዚንክ፤ ኮፐርና ፎስፎረስ (calcium, potassium, iron, manganese, zinc, copper, phosphorus) ያሉ ለሰውነት ጠቃሚ የሆኑ ይገኙበታል።  የተላያዩ የፕሮቲን መሰረቶች የሆኑ አሚኖአሲዶች (aminoacid)፤ መጠነኛ ቪታሚኖችና (vitamins)፤ ከፍተኛ ፋይበርም (fiber) ይገኙበታል። በተጨማሪም ፋይቶኬሚካሎች (phytochemicals) እንደ አልካሎይዶች (alkaloids)፤ ፊኖሎች (phenols)፤ ፍላቪኖይዶች (flavonoids) ወዘተ ያሉ ስለአሉባቸው ለጤና በጣም ጠቃሚ ናቸው።

የእንሰት መድኃኒትነት

የአገሬው ህዝብ የትኛው እንሰት ለምግብ፤ የትኛው ለመድኃኒትነት፤ የትኛው ደግሞ ለእምነት እንደሚውል ያውቀዋል።

በአብዛኛው ቀያማ ቅጠል ያለው እንሰት የመድኃኒትነት ጥቅም አለው የሚል አመለካከት አለ።

ከእንሰት የሚሰሩ ምግቦች መድኃኒትነት በአገር በቀል ዕውቀት ላይ የተመሠረተና የተለያዩ የእንሰት ዓይነቶችና ክፍሎች  ለተለያዩ ሕመሞች ማስታገሻ/ማዳኛ ጥቅም ላይ እንደሚውል የአገር መድኃኒት ዐዋቂዎች የሚመሰክሩለት ነው።

የእንሰት አስተዋጽኦዎች ለአጥንትና ተዛማጅ ሁኔታዎች (ስብራት፥ ውልቃት፥ እብጠት፥ ቁርጥማት ወዘተ)፤ በወሊድ ዙርያ ላሉ ችግሮች (የእንግዴ ልጅ ለማስወጣትና ለማስወረድ፥ ድሕረ ፅንስ ደም ማቆም)፤ ከመተንፈሻ አካላት (ሳል) ለተገናኙ ችግሮች፤ ከሆድ ዕቃ ጋር ለተገናኙ (የልብ ቃር/የሆድ ትላትል)፥ ለዐይን (መቅላት)፥ ለወሲበ ስንፈት፤ ክብደት ለመቀነስ፥ ለደም ማነስ፥ ለአባለዘር በሽታዎች፤ ለካንሰር፤ ለጉበት በሽታ፤ ለጥርስ ህመም፤ ወዘት ጠቀሜታ እንዳላቸው ጥናቶች ያሳያሉ።

በአሚቾ ውስጥ በብዛት የሚገኙት እንደ ካልሲየም፥ ፖታስየም፥ ብረት፥ ኮፐር፥ ዚንክ፥ ማንጋኒዝ፥ ማግኒዚየም፥ ፎስፎረስ ያሉት መዓድናትና  እንደየጠባያቸው የተጠቀሱትን የጤና ችግሮች ለማስወገድ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።  አርጂኒን የሚባለው አሚኖአሲድ በከፍተኛ መጠን አሚቾው ውስጥ ስለሚገኝ ለአጥንትና ጅማት ግንባታ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።

በመስኩ የተሰማሩ ባለሙያዎች በሳይንስ/ጥናት መረጃ የተደገፈ የእንሰት ተክል አፈራረጅና አስተዋጽዖ የሚያደርጉት ንጥረ ነገሮች ምንነትና መጠን በሰፊው ቢጠኑ የእንሰት ውጤቶችን በዘመናዊ መንገድ ለማቅረብ ያስችላል።

ከዚህ በታች ባለው ሰንጠረዥ የተለያዩ የእንሰት ዝርያዎች ከነ መድኃኒትነት ጠቀሜታዎቻቸው ጋር ቀርቦአል።

የእንሰቱ ይነት መድኃኒትነት አጠቃቀም/አስተያየት
አስታራ ለአጥንት ስብራት፥ ለውልቃት፥ ለእብጠት፥ መግል ለማውጣት ይጠቅማል።

 

 

ለዓይን ህመም ደረቅ ቅጠሉን አቃጥሎ ጢሱን መታጠን ይበጃል።

አጠቃቀሙ፥ አሚቾው ተቀቅሎ ከአጓት  ጋር መብላት ነው።

 

አስታራ የእንሰቶች ሁሉ ንጉሥ፥ እናት፥ የአካላት አስታራቂ፥ ወጌሻ ተብሎ ይታወቃል።

ቅብናር ለተጎዱ የውስጥ አካሎች፥ ለአጥንት ስብራት፥ ወለምታ፥ እብጠት።

የልብ ቃርና ሳልን ያክማል።

አጠቃቀሙ፥ አሚቾው ተቀቅሎ በወተትና በአይብ መብላት ነው።

 

በአስታራ ከታከሙ በኋላ ቢበሉት የተሻለ ውጤት ይሰጣል።

ጓርየ ለአጥንት ስብራት፥ ለቁስል ማድረቅ፥ ለጅማት መዞር፥ ለወሲብ ሽንፈት… በገብስ መብላት ይጠቅማል። በበግ ጠቦት፥ ዶሮ፥ ቅቤ ቢበሉት ወሲብን ያሻሽላል።

ቅብናርና ጓርየ ተቃራኒ ናቸው። ለውልቃት ጥሩ አይደለም።

አጋዴ ጉልበት ሰጭ፥ ለወሲብ ስንፈት አሚቾውም ቆጮውም ይጠቅማል።

ወንድ ከብቶች እንስቶችን ለማጥቃት ጥንካሬና ፍላጎት እንዲያገኙ አጋዴ ይሰጧቸዋል።

የደም አርጥ (ደምጠብ) ለጨብጥ፥ ለጉበት በሽታ አሚቾው ተቀቅሎ ይበላል።
ቋሽቋሽየ ሰውነት ውስጥ ተሽንቁሮ የተደበቀን ነገር መዝምዞ ያወጣል
የወረት ለጨጓራ ህመም
ጠረቄት ለዐይን ህመም የቆላ ዝንብ ያቆሰላቸው ከብቶችም ይድኑበታል።
ሣፓራ ምጥ ማስታገሻ አዋላጅ ይባላል። እርጉዟ በእጆቿ ቅጠሉን ማሽትና ሰውነትን መቀባት በሠላም ባጭር ጊዜ እንድትገላገል ይረዳል
የቆየ (የበሰለ) ቆጮ ለሆድ ቁርጠት ማስታገሻ ይረዳል።

ከዚህ በላይ በሰንጠረዡ የሚታዩት በጉራጌ ህብረተሰብ አካባቢ ያሉ ዝርያዎች ስሞች ናቸው።

በተመሳሳይ በሌሎች አካባቢዎች ለመድኃኒትነት የሚውሉት ታዋቂ የሚባሉት ከሞላ ጎደል በሚከተሉት ስሞች ይታወቃሉ።

አካባቢ የእንሰት ዝርያ/ዓይነት
ጌዴዎ ካኬ፤ ቃራሴ፤ ዲሞዬ
ባስኬቶ ሾካ
ሃዲያ መኬልዌሳ፤ ቂንዋር፤ ሼሌኬ
ከምባታ-ጠምባሮ ቀጊሌ፤ እቲኔ፤ ጦሳ
የእንሰት የመሬት እና ሥነ ምህዳራዊ ጠቀሜታ

የእንሰት ተክል ለም አፈር በንፋስና በጎርፍ ታጥቦ እንዳይወሰድ የመከላከል አቅሙ ከፍተኛ ነው። ከዚህም ባሻገር የአፈር ለምነትን እና እርጥበትን ጠብቆ በማቆየት አስተዋጽኦ አለው።

እንሰት የተለያዩ የአየር ሁኔታዎችን ተቋቋሞና አስታርቆ የማደግ ጠባይ አለው። ያፈርን ለምነትና ካርቦንን የማዋሃድ፤ ውሃን በሽፋኑ ውስጥ የመያዝና የአፈርን መሸርሸር የማቆም ጠባይ ስላለው በተጨማሪ የካርቦን ክሬዲት (carbon credit) ማስገኛ መንገድ የመሆን ዕድል አለው።

አልባሳትንና መገልገያ ቁሶችን ለመፍጠር በርካታ ተፈጥሯዊ ያልሆኑ ሰው ሰራሽ ፋይበሮች ጥቅም ላይ ስለሚውሉ የሚያስከትሉት የአካባቢና የአየር ብክለቶች ስጋት እየጨመረ መጥቷል። ይህን ስጋት ለመቀነስ ታዳሽ፤ በበቂ ሁኔታ ሊገኝ የሚችል፤ ርካሽ፤ የጤና ጉዳት የሌላቸው፤ ባህላዊ፤ ከተፈጥሮ የሚገኙ ህይወት ካላቸው አማራጮች የሚገኙ የፋይበር ዓይነቶች ትኩረት አግኝተዋል።  ስለዚህም የእንሰት ተረፈ ምርትን አካባቢን በማይጎዳ መልኩ ለአዳዲስ ጥቅሞች መጠቀም ዝቅተኛ ገቢ ላለው ገበሬ ተጨማሪ ገቢ በማስገኘት የገጠሩን ኤኮኖሚ የሚደግፍ ይሆናል።

የእንሰት ተረፈ ምርቶች ለኢንዱስትሪ ግብአትነት

ከእንሰት ለምግብነት የሚውሉት እንደ ቆጮ፣ ቡላ፣ አሚቾ ያሉት ከወጡ በኋላ የግንዱ ሽፋንና ቅጠሉ (ኮባው) በተለምዶ እንደ ተረፈ ምርት ከሚጣል ይልቅ ለብዙ ኢንዱስትሪዎች ግባትነት ሊያገለግል የሚችል ነው። የእንሰት ቃጫ ከተለመዱት አገልግሎቶች (እንደ ገመድ፤ ዶንያ፤ ቅርጫት፤ ወረቀት፤ የአልጋ ገረብ፤ ለከብት መኖ፤ ለስጋጃ፤  ለልብስነት፤ ለቤት መስሪያ ወዘተ) በተጨማሪ ለተለያዩ አዳዲስ ጥቅሞች የመዋል ዕድሎች እንዳሉት ታውቋል።

የአየር ብክለትን ታሳቢ ያደረጉ የተፈጥሮ ግብአትን በመጠቀም ሊገኙ ከሚችሉ ነገሮች በኢትዮጵያ በስፋት የሚገኘው አንዱ የእንሰት ተረፈ ምርት የእንሰት ቃጫ (ፋይበር) ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ፋይበር በተለምዶ ከጥጥ፤ በግ ጸጉር፤ ኩሻ (ከሾላ)፤ ከሱፍ፤ ከጭረት ሰጪ ሬት/ሲዛል (sisal) ተክል ወዘተ ለማውጣትና ለተለያዩ ጥቅሞች ለማዋል በጥናትና ምርምር ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። ካለው ተስፋ ሰጪ ጥቅሞች አንጻር እንሰት ተገቢውንና እሴት ጨማሪ ጉልበቱ በተገቢው መጠን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

በኢትዮጵያ ከእንሰት ብቻ በብዙ መቶ ቶን ቃጫ ወይም ፋይበር (fiber) ይመረታል ተብሎ ይገመታል። ይህ ከፍተኛ የሆነው ተረፈምርት በቀላሉና ብዙ ወጪ በማይጠይቅ እንዲሁም ሥነ ምህዳራዊ ተስማሚነት ባለው መንገድ ሰው ሰራሽ ፋይበርን መተካት እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ። ለአገር ፍጆታም ለውጪ ገበያም በማዋል የአገርንና የአምራቹን ገቢ ሊጨምርም ይችላል። ሌሎች የተለያዩ ፋይበር ያላቸው አትክልቶች በብዛት ቢኖሩምና ጥቅም ላይ እየዋሉ ቢገኙም የእንሰት ፋይበር ግን ለተለያዩ አዳዲስ ጥቅሞች ተመራጭ የሚያደርጉት በጎ ጎኖች ስላሉት የዓለም አቀፍ ትኩረትን እየሳበ ነው። ለምሳሌም በእንሰት ፋይበር ውስጥ የሚገኘውን ሴሉሎስ (cellulose) በመጠቀም እንደ ቡታኖልና ሃይድሮጅን (butanol & hydrogen) ያሉ ባዮፊውሎችን (biofuel) ለማመንጨት፤ ናኖሰሉሎስ (nanocellulose/cellulosic nanocrystals) መስሪያ ቁስ አካልነት፤ ተስፋ አለው።  በተጨማሪም ካፕሮኤት (caproate) የሚባል መካከለኛ ሰንሰለት ፋቲአሲድ (fatty acid) ሊመረትበት ይችላል። ካፕሮኤት ለመድኃኒቶች (pharmaceuticals)፤ ለምግብ፣ ለመዋቢያዎች (cosmetics) መስሪያ በጣም ተፈላጊነት ያለው ግብአት ነው።

በተጨማሪም ከቆጮው (በአብዛኛውም ከአሚቾው) የሚገኘው የእንሰት ስታርች (starch) ለክኒን መፈብረክ ግባእትነት፤ ለወረቀት/ክርታስ መስሪያ፤ ለአልባሳት፤ ሙጫ ለመስሪያ እና ለተለያዩ ምግቦች መስሪያ ግብአትነት ያገለግላል። የእንሰት ስታርች ትኩረት ቢሰጠው የተሻል አይነት ስታርች ጥቅም ላይ ከማዋል በተጨማሪ፤ አሁን አገሪቱ በስታርች ግዥ የሚውለውን የውጭ ምንዛሪን ከማዳን አልፋ ለውጭም ገበያ ልታቀርብ ትችላለች።

የእንሰት በሽታዎችና መፍትሔዎቹ

የእንሰት በሽታዎች ምርት እና ምርታማነትን የሚገዳደሩ ጉልህ ምክንያቶች ናቸው። ዋንኛ የሚባሉት እንሰትን የሚያጠቁ በሽታዎች በባክቴሪያ፣ ፈንገስ፣ ቫይረስ (bacteria, fungus, virus) ምክንያት የሚከሰቱ ሲሆኑ፤ ስሩን/አሚቾውን የሚያጠቁት ደግሞ ትላትል፣ ፍልፈል፣ ጃርት፣ ምስጥ ወዘተ ናቸው።

አስከፊውና መላ የእንሰትን እርሻ ሊያጠፋ የሚችለው ቅጠሉን በማጠውለግና በማወየብ የሚጀምረውና ብሎም እንሰቱን የሚገለው በሽታ ዛንቶሞናስ ካምፔስትሪስ (Xanthomonas campestris)  በሚባለው ባክቴሪያ የሚከሰት በኢትዮጵያ በብዛት የሚገኘው የእንሰት ባክቴሪያ ዊልት በሽታ (bacterial wilt disease) ነው።  ይህ ባክቴሪያ በተመሳሳይ የሙዝ ተክልንም ያጠቃል።

በሽታው ካንዱ ወደሌላው በመዛመት እርሻውን እንደ ሰደድ እሳት ያጠፋዋል። በአሁኑ ጊዜ በሽታውን የሚፈውስ ወይም ባክቴሪያውን የሚገድል መድኃኒት  አልተገኘም። የተበከሉ እንሰቶችንና አፈርን የነኩ መቆፈሪያዎችና የእርሻ መገልገያዎች በሽታውን ያስተላልፋሉ። ስለዚህም የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል፣ የተበከሉ የእርሻ መሳሪያዎችን መልሶ አለመጠቀም፣ በበሽታው የተለከፉ ተክሎች አካባቢ እንስሳት እንዳይደርሱ ማድረግ፣ የተበከሉ ተክሎችን በማቃጠል ማስወገድ ወይም በጥንቃቄ መቅበር፤ ለአካባቢው ኗሪ ትምህርት መስጠት አስፈላጊ ነው። በዘላቂነትም መንግሥት የዕፅዋትና የተለያዩ የምርምር ድርጅቶችን በማበረታታት ምርምርንና ጥናትን በተደራጀ መንገድ በማካሄድ እንደነዚህ ያሉትን ተግዳሮቶች ለመመከት ትኩረት መስጠት ይገባዋል። ለምሳሌም በሽታውን የሚቋቋሙ ዝርያዎችን ማዘጋጀት፤ ማዳቀልና ማባዛት ለገበሬውም ማዳረስ ተገቢ ነው።

እንሰትና ሴቶች 

ኢትዮጵያ ውስጥ የእንሰት ስራ በባህል የሴቶች ድርሻ ተብሎ ይወሰዳል። ሴቶች ማዳበሪያ/ፍግ በማድረግ፤ በማረም፤ እንሰቱን በመፋቅ፤ ቡላውን በማዘጋጀት፤ አሚቾ በመቆራረጥና ዱቄት በማድረግ፤ ቆጮውን አዘጋጀቶ በማቅበርና በየጊዜውም አውጥቶ በተለያዩ መልኮች አብስሎ ለምግበነት በማቅረብ የአንበሳውን ሚና ይጫወታሉ።

በጣም አድካሚውና አስቸጋሪው መፋቅ (scraping/decortication) የሚባለው ተግባር ነው።  በእንሰቱ ዙሪያ ያሉትን ለምግብነት ዕድሜ የደረሱትን ሽፋኖች ልጦ አውጥቶ፤ በእንጭት ሳንቃ (ዋታር) ላይ አሰደገፎ፤ ከቀርቅሓ በተዘጋጀ ጎራዴ መሳይ መፋቂያ (ስቢሳ) በመጠቀም የእንሰቱን ሽፋኖች ተራ በተራ መፋቁ ነው። የተፋቀው ፈሳሽና ቃጫ በኮባ ቅጠል ላይ ይጠራቀምና መጨመቅ ይጀመራል። ይህ ተግባር ከተፋቀው ውስጥ ለቆጮውና ቡላው የሚሆነው ፍሳሽ ከአሰሱ ቃጫ መለየትን ይጨምራል።  በተጨማሪም አሚቾውን በመከትከትና እንደ ዱቄት በማድረግ (pulverization) ከተፋቀው ጋር በማደባለቅ ቆጮውን ማዘጋጀት ሌላው ዋንኛ ተግባር ሲሆን ፤ ከተፋቀው ቅሪት ፈሳሽ ደግሞ ዱቄታማውን ቡላ ማዘጋጀት ነው።

የወንዶች ሚና የእንሰት ችግኞችን የተለያዩ የእድገት ጊዜያቸውን እየተከታተሉ ማፍላት፤ ዘርዝሮ መትከል፤ ለመቆረጥ የደረሰውን እንሰት መንቀል ላይ ያተኩራል።

የእንሰት አመራረትና አዘገጃጀት ለማዘመን የሚደረጉ ጥረቶች

በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ የምርምርና የሙያ ተቋማት፤ ባለድርሻ አካላት የእንሰትን ማምረት፤ አዘገጃጀት፤ ገቢ ለመጨመር፤ በሽታን መከላከል ወዘተ ለማሻሻልና ለማዘመን የተለያዩ ጥረቶች እያደረጉ  ይገኛል።

ቴክኖሎጂ እንሰትን ወደ ምግብነት ለመቀየር ሴቶች የሚያደርጓቸውን የተለያዩ ጫና የተሞላባቸውን ተግባራት ለማቅለል፤ ቅልጥፍናን ለማምጣት፤ ከብክለት የጸዳ ለማድረግ ይረዳል።

ይህን የሴቶች አድካሚና ጊዜ የሚጠይቅ ስራ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በዘመናዊ ዘዴ እንዲገለገሉ የማድረግ ጥናቶችና ፈጠራዎች በየጥናት ተቋማት እየተካሄዱ ቢሆንም፤ ለተጠቃሚዎቹ ማዳረስ ላይ ግን ክፍተት እንዳለ ይታያል። በስራ ላይ የዋሉት ቴክኖሎጂዎች በብዛት፤ በጥራትና የተጠቃሚውን የገቢ አቅም ያላማከሉ ከሆኑ ከሙከራነት አያልፉም።

ላልለመደው ተጠቃሚ የቆጮ ሽታም ተግዳሮት ተደርጎ ይታሰባል። ይህ ሽታም ቆጮ ተቀብሮ በሚቆይበት ጊዜ በበቂ ሁኔታ ባለመብላላቱ የሚከሰት ነው። ለምሳሌ በሸኪቾ/ቤንች አካባቢ የሚገኝ የማንዲሎ ተክል ግንድ (Mandillo – Crassocephalum macropappum) ቆጮ በሚዘጋጅበት ጊዜ እንደ እርሾ (yeast) በመሆን ባጭር ጊዘ ተበላልቶ (fermented) ለምግብ እንዲደርስና የቆጮውን ሽታ እንደሚቀንስ ተመዝግቧል።  በዚህ ዙርያ ተጨማሪ ጥናት ማድረግና ወደ ሌሎች አካባቢዎች ዘሩን ማስተዋወቅ ጠቃሚ ይሆናል።

አንዳንድ እንሰት አብቃይ አካባቢ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች (እንደ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ፤ ሶዶ ግብርና ኮሌጅ፤ አረቃ የምርምር ማእከል ወዘተ) እና የኢትዮጵያ የብዝሃ ሕይወት ኢኒስቲትዩት (Ethiopian Biodiversity Institute) ከኪው ሮያል ቦታኒካል ጋርደንስ (Kew Botanical Gardens) ጋር በመተባበር የተለያዩ ስራዎችን በማካሄድ ይገኛሉ። ከነዚህም ድርቅን፤ ተውሳክንና በሽታን ለመከላከል፤ ምርታማነትን ለመጨመር፤ በብዝሃ ሕይወት ኢንፎርማቲክስ ለመጠቀምና፤ ዘረመል ጥናትና ስርጭት ማከናወን የሚጠቀሱ ናቸው።

የተቀናጀ አሰራርን ለማዳበርና ጥናትና ምርምርን ለማስፋፋት እንዲሁም እንደ አርባምንጭ የእንሰት ዘር ባንክ (Enset seed bank)፤ የእንሰት ልህቀት ማእከል (Enset Center of Excellence) ተቋቁሞ ስራ መጀመሩ ውጤታማ እንደሚሆን ይታመናል።

ጥናቶችና ትብብሮች ለእንሰት ምርታማነትና በእንሰት ዙርያ ለሚንቀሳቀሰው ኢኮኖሚ፤ የእንሰት የአምራችና የንግድ ማኅበራት እንዲፈጠሩ፤ ኢንዱስትሪና የገበያ ግንኙነት እድገት እንዲሁም የገበያ መረጃ  እንዲዳብሩ ወሳኞች ናቸው።

የእንሰትን ጠቃሚነት እንደሌሎች አዝእርቶች  እውቅና መስጠት፤ የወደፊቱ አንዱ የግብርና ምሰሶ ማድረግ፤ በዋጋ ዝቅተኝነትና አትራፊ የሆኑ ምርቶች ላይ በማትኮር የእንሰት ግብርና እንዳይመነምን የእንሰት አምራቾች እንዲበረታቱ ማድረግ ይገባል።

የቆጮና ቡላ ፍላጎት ከአገርም አልፎ በውጭ አገራትም እየጨመረ ስለመጣና የእንሰትም ተረፈ ምርት ፍላጎት ስለሚጨምር፤ እንሰትን በኢንዱስትሪ ደረጃ ለማምረትና ለመላ ኢትዮጵያ ህዝብ በምግብነት ለማዳረስ ብሎም ለውጭ ገበያ ስርጭት እንዲውል ጥረት ቢደረግ በሁሉም መስፈርት አኳያ የሚያዋጣ ስለሚመስል ቢታሰብበት መልካም ይሆናል።

ይህ ጽሑፍ በብዙ መልኩ የተሟላ ላይሆን ስለሚችል ከዚህ በታች የተጠቀሱትን ዋቢ ጽሑፎችና የእንሰት አምራች አካባቢ ዐዋቂዎችን ማማከር አስፈላጊ ይሆናል።

Enset a Multi-Purpose Ethiopian Plant – “The Tree Against Hunger”

Summary

This article focuses on the importance and history of Enset ventricosum (known as “false banana”).

For more than 10,000 years, it has been used in the north, south and west Ethiopia. There are more than 300 different species. It is a versatile plant that grows year after year (up to 12 years) and is edible, provides food security for the family, is resistant to climate change, replaces itself, and does not require a lot of land. It is also used for medicinal,  soil fertility, animal feed, traditional housework, industrial inputs, environmental beauty, etc. It is estimated that one-fifth (20% or 26 million) of the country’s population uses Enset. The three main produces of Enset used for food are locally known as Qocho, Bulla and Amicho. Some of the most important minerals in Qocho, Bulla and Amicho are calcium, potassium, iron, manganese, zinc, copper, phosphorus and various amino acids, vitamins, and high fiber. In addition, phytochemicals such as alkaloids, phenols, flavonoids are reported to be present. Recent studies have shown Enset fiber as having promising industrial uses including as source of biofuels, cellulosic nanocrystals and medium-chain fatty acid called caproate which has use in pharmaceuticals and cosmetics. Amicho is a good source of starch.

Gabriel Daniel – January 2026

ዋቢ ጽሑፎች

መጽሓፍት (Books)

  1. Gabreyesus Hailemariam, The Gurage & Their Culture, Vantage Press, New York, pages 73-97, 1991
  2. Frederick J Simons, Northwest Ethiopia, Peoples and Economy,  The University of Wisconsin Press, Madison, pages 89-99, 1960
  3. ዓለማየሁ ነሪ ውርጋሶ፤ ኧሰት 3ኛ መጽሐፍ፣ አዲስ አበባ 1998 ዓ.ም.።
  4. ተስፋ ገብረየስ ዝምድረ ከብድ፤ አይመለል የጉራጌ (የሶዶ ጎርዳና) ህዝብ አጭር የታሪክ ማስታወሻ የክስታኔ መጣፍ ገጽ 29-35፤ 1987 ዓ.ም.።
  5. ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል፤ ለ ገራህት፤ አርቲስቲክ ማተሚያ አዲስ አበባ፤ ገጽ 117-122፤ 1959 ዓ.ም.

መጽሄቶች (Journals)

  1. Borrell S. et al., “EnsetBased Agricultural Systems in Ethiopia: A Systematic Review of Production Trends, Agronomy, Processing and the Wider Food Security Applications of a Neglected Banana Relative.” Plants, People, Planet, Volume 2, Issue 3, Pages 212-228, May 2020
  2. Dirk Hölscher et al., Phenylphenalenones from Enset ventricosum. Phytochemistry. 49(7), 2155-2157. December 1998
  3. Teli, M.D. & Terega, J.M. Chemical, physical and thermal characheterization of Enset ventricum plant fiber, International Journal of Engineering and Technology. 4(12), 67-75 (2017)
  4. Mitiku Muanenda et al., Harnessing the Medicinal Potential of Enset (Ensete ventricosum) in Ethiopian Traditional Medicine: A Synthesis of Current Knowledge, Food Science & Nutrition. 25 Nov 2025
  5. Temesgen Negassa, Exploring indigenous knowledge and practices of the Gurage community on the biosystematics and utilization of Enset landraces for bone fracture and regeneration: the case of Gurage Zone, NIH Frontiers in Pharmacology; 2025
  6. Assefa et al., “The Ethnobotanical Study and Distribution Patterns of Enset Landraces (Ensete ventricosum(Welw) Cheesman) in Aleta Chuko District, Sidama Zone, South Nation Nationality People and Regional State, Ethiopia.” Research and Reviews: Research Journal of Biology, 2016.
  7. Marjun C. Alvarado et al., Review of nanocellulose production from agricultural residue through response surface methodology and its applications, Nano Trends, Vol. 8, December 2024
  8. B K Dejene, Enset ventricosum: An emerging natural fiber with distinct properties, promising potentials, challenges and future prospects – a critical review, Journal of Natural Fibers, Vol 21, no.1, 2024
  9. Tamiru Dibaba, Assessment and evaluation of Enset processing technologies, International Journal of Research Publication and Reviews, Vol 5, no 5 pages 8317-8324, May 2024.

ቴክኒካዊ ዘገባዎች (Technical Reports/Proceedings and Others)

  1. The Tree Against Hunger, Enset-based agricultural system in Ethiopia, American Association for the advancement of science with Awassa Agricultural Research Center, Koyoto University Center for African Area Studies and University of Florida, 1997
  2. National Enset Development Flagship Program (NetDfP) 2024 – 2030, Ministry of Agriculture, December 2024, Addis Ababa, Ethiopia
  3. Mersha Yilma, Proceeding of A National Dialogue on Ethiopian Food and Agricultural Systems: Policy and Practice. August 2021
  4. Shank R., The Enset culture: A technical report on Enset ventricosum or “False Banana”. Addis Ababa, Ethiopia: United Nations-Emergencies Unit for Ethiopia, 1994
  5. Enset-based sustainable agriculture in Ethiopia. Proceedings from the international workshop on enset (pages 250-255). Addis Ababa, Ethiopia: Institute of Agricultural Research, December 1993

3 thoughts on “እንሰት – ከቆጮና ቡላ ባሻገር”

  1. I remember an Ethiopian PH. D. student that came from Sweden in 1991/92 to study Enset. She came with her parents to the National Herbarium to ask for a favor, which was to ask for a vehicle to carry out field studies. We offered one of our land cruisers and she was able to complete her work. I wonder if you had seen that PH. D. theses.

Leave a Reply to Fekadu FullasCancel reply

Scroll to Top

Discover more from ሰምና ወርቅ

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading