አቶ ታምራት ገብረመድኅን ጥቅምት 1945 ዓ.ፈ ተወለደ። ነሐሴ 2024 ዓ.ፈ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየን። የቀብሩ ሥነ ሥርዓት Fairfax Memorial Funeral Home በ9900 Braddock Road, Fairfax, Verginia በSeptember 5, 2024 ተፈጽሟል።አቶ ታምራት ከ1970ዎቹ ዓመት ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ በቨርጂኒያ አካባቢ ኖሯል። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አጠናቆ የመጀመሪያ ዲግሪውን ተቀብሏል። ወደ ዩናይትድ እስቴትስ ከመጣ በኋላ በGeorgetown University የማስትሬት ዲግሪውን በምሕንድስና ምህዳር ትምህርት ተቀብሏል።
በ1980ዎቹ ዓመታት የትዳር ባለቤቱን ወ/ሮ ሄዋን ደነቀን አግብቶ ሶስት ሴት ልጆች፣ አደይ፣ ሊያ፣ እና ገሊላን አፍርተዋል።
አቶ ታምራት በራሱ የሚተዳደር ሰው ቢሆንም በአሜሪካ በተቀመጠበት ዘመን ሌሎች ኢትዮጵያውያንን በማበረታታና በመርዳት ነበር የኖረው። “Little Ethiopia” [ታናሿ ኢትዮጵያ] የተባለውን ድርጅት እንዲቋቋም በርትቶ የገፋበትና የመጀመሪያው ሊቀመንበር የሆነው እርሱ ነበር። በዚህም በምዕራቡ ዓለም የሚኖሩ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን የሃገራቸውን ታሪክና ባህል እንዳይረሱ ለማነቃቃት ድርጅቱን ተጠቅሞበታል። ለሌሎች አፍሪካውያን ስደተኞች አብነት ለመሆን ሳይታት ሰርቷል። በዚህ ትጋቱና በሌሎች ማህበራዊ ተሳትፎው በዋሺንግተን ዲሲ ከተማ ከንቲባ እጅ Pan- African Bridge Builder Award የተሰኘ ሽልማት ተቀብሏል። እንዲሁም የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት /Crown Council of Ethiopia/ የተሰኘውን ተቋም በሊቀመንበርነት በሚመሩ ልዑል ኤርምያስ ሳህለ ሥላሴ እጅ The Centenary Medal of Adwa የተሰኘ ሜዳልያ በ2020 ዓም ተሸላሚ ሆኗል።
ቀደም ሲል ከአፍሪካ ወጥተው በአሜሪካ እንዲኖሩ የተገደዱትን አፍሪካን አሜሪካኖችን ታሪካቸውን እንዲያውቁና ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ያላቸውን ቁርኝት ለማዘከር በየዓመቱ በAfrican American Civil War ማዘከሪያ ሃውልት ላይ የአበባ ማስቀመጥ ሥነ ሥር ዓት በማቋቋም ይታወቃል። የሚተዳደርበት ዋናው ሥራው ቤቶችን የመሸጥ ሥራ ስለነበር በዚህ ተግባሩ ብዙ ኢትዮጵያውያንና አፍሪካን አሜሪካኖች የግል ቤት ባለቤቶች እንዲሆኑ በርትቶ ሰርቷል።
አቶ ታምራትን በቅርብ የተዋወቅሁት ዋሺንግተን በስደት ከመጣሁ በኋላ ነው። አዲስ አበባ ግን በቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በሩቅ ከመተያየት በቀር ቅርበት አልነበረንም። በ1981 ዓ.ፈ ወደ ዋሺንግተን በስደት ከመጣሁ በኋላ ብዙ የፖለቲካ ስደተኞች ወደአሜሪካና ወደተለያየ የዓለም ክፍል የተዘሩበት ጊዜ ስለነበረ፣ ተበታትነን እንዳንቀር፣ በተለይም ከሩቅም ሆነን ስለሃገራችን ከማሰብና እድገቷን ለማጎልበት በሃሳብ ተግተን እንድንሰራ በነበረኝ ምኞት፣ አንድ ድልድይ ሆኖ የሚያገናኝ መጽሔት ለማቋቋም አስቤ ሥራ ላይ ለማዋል በተነሳሁበት ጊዜ ሁነኛ ሰዎችን ሳፈላልግ በዶክተር ያእቆብ ኃይለማርያም አማካኝነት ከአቶ ታምራት ገብረመድኅን ጋር ለመተዋወቅ በቃን። ከአቶ ታምራት ጋር የተመሠረተው ግንኙነት ፍሬያማ ነበር። መጽሔቱን በጽኑ መሠረት ላይ ለማቋቋም በነበረኝ ዓላማ የመጽሔቱን ተግባር የሚያስተዳድር የዲሬክተሮች ቦርድ አስፈላጊ ነበር። የመጀምሪያው የዲሬክተሮች ቦርድ በአራት አባላት ተቋቋመ። ከነዚህ መሥራች አባሎች መካከል አቶ ታምራት ገብረመድኅን ይገኝበታል። አቶ ታምራት የመጽሔቱ ስያሜ ሰምና ወርቅ፤ ነፃና ሁለገብ የጥናትና የምርምር መጽሔት እንዲሆን በመስማማት ድምፅ ከሰጡት መሃል ነበር። ስለዚህም ሰምና ወርቅ መጽሔት እ.ኤ.አ በጥር 1987 ላይ ተቋቋመ።
አቶ ታምራት የመጀመሪያውን እትም ለማሳተም የተጠየቅነውን ዋጋ ለመክፈል ከኪሳችን ገንዘብ እንድናዋጣ ተስማምቶ የበኩሉን ድርሻ አበርክቷል። መጽሔቱም ከታተመ በኋላ በገባነው ቃል መሠረት ተከታታይ እትሞች ጊዜያቸውን ጠብቀው እንዲወጡ እና የመጽሔቱ ሥራ በትጋት እንዲሠራ፣ በመጽሔቱ ቦርድ ስብሰባዎች ሁሉ ላይ በመገኘት ጉልህ አስተዋጽዖ አድርጓል። በግልም እየደወለ ያበረታታኝ ነበር። የመጽሔቱ መሥራችና ዋና አዘጋጅ ስለነበርኩ በየጊዜው የማበረታቻ ቃል ያካፍለኝ ነበር። በግል እንድንገናኝም ስልክ እየደወለ አብረን ምሳ ወይም እራት እንድንበላ እየጋበዘኝ ብዙ ቁም ነገር አዘል ምክሮች ለግሶልኛል። የምትሰራው ለሃገር ጠቃሚ ስለሆነ ማንም ተስፋ እንዳያስቆርጥህ በርታ በማለትም ያስጠነቅቀኝ ነበር። ከተለያዩ ሰዎች ጋር በማስተዋወቅ ሞራሌን ለመገንባት ሳይታከት ደክሟል።
ከእኔ ቀድሞ ወደአሜሪካ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ያቋቋመው የቤቶች አሻሻጭ ድርጅት ስለነበረው አንድ ቀን ለእኔ አስቦ መሥሪያ ቤቱ ቀጠሮ ሰጥቶኝ አንድ ቅዳሜ ጧት በመሥሪያ ቤቱ ተገኘሁ። እርሱም ስለቤት መግዛት አስፈላጊነት መልካም የሆነ ምክር ለገሠኝ። ለቤት ኪራይ በየወሩ የምታወጣው ገንዘብ እንደወጣ የሚቀር ገንዘብ ነው፤ አንተ ለቤት ኪራይ የምታወጣውን ገንዘብ ቤት ገዝተህ በሞርጌጅ መልክ ብትከፍለው ከጊዜ በኋላ ባንክ ከምታስቀምጠው ገንዘብ ይልቅ ብዙ እጥፍ ገንዘብ ከማግኘትህ ሌላ ቤቱም ያንተ እንደሆነ ማቆየት ትችላለህ መሸጥ ካልፈለግህ እያለ ሲመክረኝ፣ በዚያን ጮርቃ ጊዜ በነበረኝ ደካማ የገንዘብ ግንዛቤ የተነሳ፤ “ ስለኔ ሃብታም መሆን አታስብ፤ እኔ በዚህ ሃገር ተደላድየ የመኖር ምኞት የለኝም። ነገ ከነገ ወዲያ ጥየው ለምሄደው ኑሮ አልጨነቅም፤ ስለሃሳብህ ግን አመሰግንሃለሁ” ብየው ከቢሮ ወጥቸ ሄድኩ። ለጥቂት ወራት ስልክ እየደወለ ተማጠነኝ። እርሱ በገንዘብ የተነሳ ተላላ መሆኔን ተገንዝቧል፤ ስለዚህ በየጊዜው እየደወለ ሃሳቤን እንድቀይር ጠየቀኝ። ኮምፒውተሩን ከፍቶ ያሰየኝ የቤት ዝርዝር የሚያስጎመጅ ነበር፤ ሆኖም እኔ በዚያን ጊዜ የነበረኝ አመለካክት ትቸው ከመጣሁት ትግል አንጻር ስለነበረና የብዙ ጓደኞች በሞት መለየት ጥሎብኝ የሄደው የአደራ ሸክም ስለራሴ መደርጀትና ሃብት ማከማቸት ለማሰብ ፈጽሞ የሚያስችል አልነበረም።
ከ20 ዓመት በኋላ በነበረኝ አዲሱ አመለካከት ስልክ ደውዬ ሳጣው፤ “ያን ያልከኝን ቤት መግዛት አሁን አምኘበታለሁና እንድንነጋገር ይህን መልዕክት እንዳገኘህ ቶሎ ደውልልኝ” ብዬ ለተውኩት መልዕክት መልስ አልሰጠኝም። ከወራት በኋላ በደወለው ስልክ የተወልኝ መልዕክት “ያለሁት ኖርዝ ካሮላይና ነው፣ ቤት እየሸጥኩ። ስመለስ እራት እጋብዝሃለሁ” የሚል ነበር። የነገሩ ቅኔ ስለገባኝ በራሴ ላይ መሳቄን አስታውሳለሁ።
የወንድማችን የአቶ ታምራት ገብረ መድኅንን ነፍስ ፈጣሪ አምላክ በተቀደሰው እቅፉ ያኑርልን። አሜን!!!
ፈንታሁን ጥሩነህ፤
በሰምና ወርቅ ኮርፖሬሽን አባላት ስም።
In memory of
Mr. Tamrat G. Medhin
Addis Ababa, Ethiopia
Oct 12, 1945 – Aug 25, 2024



