‘አኽ፡ሹማዊት ሌሊት፥’                                                         

ከጃርሶ ኪሩቤል ሞትባይኖር

           ህዳር 2015 ዓ.ም  

            ሎንዶን፤ እንግሊዝ 

መታሰቢያነቱ፤ 

 {`ኣኽ~ሹማዊት ፡ሌሊት`፡ተረክ፥መታሰብያነቱ፥ለወላጅ፡እና፡አሳዳጊ፡እናቴ፥ለ፡’አፀደ~ማርያም፡ወልደ፡መስቀል፡ዮሓንስ’፤ ለ፡ሕይወት፡ጕደኛዬ፥ለ፡’ናኔትዬ፡ሜሪ፡ ሰዘርላንድ’፡እና፡ ኣክሱምን፡ስጎበኝ፥አብራኝ፡ለነበረችው፥ለ፡’ቀጸላ፡ሱራፌል፡በሻህ’፥ይሁንልኝ~ኣሜን!!} 

                                  ~’እም፥ኹሉሰ፡የ፡ዓቢ፥ዘ፡ተኅትመ፡በ፡ጽዎን’~ 

‘አንቀጸ ብርሃን’፤ ሰዓሊው፤ ጃርሶ ኪሩቤል ሞትባይኖር

(ገጽ፡~፩)

`አኽ፡ሹም`፥ጥንታዊ፥የ፡`ሳባዊ`፡ሥልጣኔ፡እንደነበራት፡እንጂ፥`ጥንታዊ~ሌሊት`፡እንደ፡አላት፥እስከ፡ዛሬ፡ድረስ፤ፈጽሞ፡ አላውቅም፡ነበር። ወደ ‘ኣኽሱም’ ከተማ እንድሄድ ምክንያት የሆነኝ አንዱም የአጎቴ አጎት እና አሳዳጊው ብፁዕነታቸው፥ንቡረ~ዕዱ፤ የጻፉለት የአስቸኳይ ጥሪ ደብዳቤ ነበር።

“ልጄ ፤ ወዳጄ አደራህን በአመቸህ ሁሉ ተቸግረህልኝ በቶሎ ወደ ኣኽሱም መጥተህ እንድትጎበኘኝ ይሁን። ልንመካከርበት የሚያሻ እጅግ ሃያል ጉዳይ ገጥሞኛል ” ወዘተ የሚል ብርቱ የኅሊና ተፅዕኖ በሚያሳድር ጥሪ አደሙት ። ጊዜው 1964 እ ኢ አ ሲሆን ለክርመቱ የትምህርት ቤት ዝግ ወራት ወደ አጎቴ ዘንድ ወደ አሥመራ ሄጀ እንዳርፍ ኣባቴ እና እናቴ መክረው ላኩኝ። አጎቴ የአሥመራ ከተማ ምክትል ከንቲባ ስለሆነ ኑሯችን ምቹ እና የከተማይቱ ዓየር ሰናይ በመሆኑ ከአዲስ አበባ ዝናም ጨቀጨቅ በመላቀቄ እጅጉን ፈነደቅሁኝ። የትንስዬ ‘ሮማ’ መሳይዋን ከተማ ካፌዎች ሳዳርስ ጎዳናዎችዋን ሰአሥሥ እውል ነበር።

እቅዱን ቀድሞ መናገር የማይወደው አጎቴ ምሣ ገበታ ላይ እንደተቀመጥን ፤ “በርኄን የመኪናውን ጎማ እንዲፈታትሽ ነግሬው አለሁ፤ በዚያውም እነ ‘ተኮላሽ’ን ለመጠየቅ ጥሩ አጋጣሚ ይሆነናል፤ ባለቤትዋ ‘ተሞገሥ’ም ፣ መቸ ነው መጥተህ የምትጎበኘን እያለ በስልክ ሲነዘንዘኝ ነው የከረመው፤ ወደ ኣክሱም መሄዳችን ነው” ሲል አስረዳኝ። የአያቴ፡ ወንድም፡ናቸው፥ በብርቱ፥የኅሊና፡ተጽዕኖ፡በሚያሳድር፡ደብዳቤአቸው፥በ፡አጣዳፊ፥ወደ፡`ኣኽ፡ሹም`፡መጥቶ፡እንዲጎበኛቸው፡ስለጠሩት፥ ደብዳቤው፡በደረሰው፡ሠልሥት፥ከ፡ኣሥመራ፡ተነስተን፡ነበር፡የገሠገሥነው።

ኣጎቴ፥የ፡ኣሥመራ፡ማዘጋጃ፡ቤት፡ባለ፡ሥልጣን፡ሆኖ፡ከተሾመ፡ቆየ። እኔም፤ለክረምቱ፤የትምህርት፡ቤታችን፡መዘጋት፥ለእረፍት፤ ወደ፡እርሱ፡ዘንድ፡እንድመጣ፡ስለ፡ጠራኝ፤ ኣባቴ፤ በፍጹም፡ደስታ፤ ኣውቶቡስ፡ኣሳፍሮ፡ላከኝ።

እናም፥ወደ፡`ኣኽ፡ሹም፤ ጥሪው፡ሲደርሰው፥`ሮማይስጥ`፡መሳይዋ፡ነፋሻዋ፡ኣሥመራ፡ከተማ፡ጎዳናዎች፣`ካፌ`ዎች፡እየ፡አልኩኝ፡ መዝናናት፡ከጀመርኩኝ፡ሠንባብቼ፡አለሁ።

ተሞገስ፡ የከተማው የጤና ጥበቃ መስሪያ ቤት ምክትል አስተዳዳሪ ሆኖ ሲሰራ የቆየ ቀና ሰው ነው። እናም ለእሱም አምቻ ጋብቻውን ለማጠናከር መልካም አጋጣሚ ተፈጠረለት ማለት ነው።

አጎቴን እንደ ልጃቸው አድርገው የአሳደጉት ንቡረ ዕድ ተምሮ ለሹመት እና ማዕረግ በቅቶ አኩሪ የቤተሰብ ጋሻ ሆኖ ስለወጣላቸው ከፍቅራቸውም በተረፈ ዕውቀቱን እና ትምህርቱን በማክበር ምክር እና ሃሳብ ከመጠየቅ እንደማይቦዝኑ በቤተሰቡ ውስጥ በሰፊው ይነገራል።

ከነፋሻይቱ አዲኳላ መንደር ለጥቂት ሰዓት ስናርፍ አጎቴ መሎቲ ቢራውን ሲይዝ፤ እኔ እና ሾፌሩ ‘በርኄ’ም አረንቻታችንን ተጎንጭተን እንደገና ጉዟችንን ቀጠልን። አጎቴ በተፈጥሮው ከወደ ንግግሩ ቁጥብ ሰው ቢሆንም በተለይ በጉዟችን ላይ ፈጽሞውን ልስን ብሎ በጥልቅ ሃሳብ እንደተዋጠ አስተውያለሁ። አፍ አውጥቸ ለመጠየቅ የማልደፍርበት ሁኔታ በመሆኑ እኔም በውስጥ ጥርጣሬ እንደታፈንኩኝ የማይመስለውን ሁሉ ሳንሰላስል ቆየሁ። ወደአመሻሽ ግድም አክሱም ከተማ ስንደርስ ከመንገዱ ግራና ቀኝም ሆነ ከማሃል ከተማው ትውር የምትል ነፍስ አለመታየቱ እኔን ሲደንቀኝ አጎቴ ግራ ቀኙን በአንክሮ ትኩረት እየቃኘ ጭንቅላቱን ይነቀንቃል።

‘በርኄ’ም መሪውን በቀኝ እጁ እንደጨበጠ ግራ ምዳፉን አፉ ላይ በመጫን፤ “ጎይታና፣ እንታይ ጉዱ!? ሎሚ ‘ኅዳር ጽዎን ‘ አይኾነትን እምበር!” ሲል በጮክታ ተናገረ። በገዛ ሃሳቡ የተያዘው አጎቴ፣ “እሕ ሕም!!” በማለት ጉረሮውን አጥርቶ ስራው ላይ እንዲያተኩር፤ የምንሄድበትን ሰፈር አግጣጫ አመላከተው።

እንደ፡ልጃቸው፡አድርገው፡የአሳደጓት፥`እትዬ፡ተኾላሽ`ን፤በቅርቡ፡የአገባው፥`ጋሼ፡ተሞገሥ`ም`፤ የ፡ኣኽሹም፡ጤና፡ጥበቃ፡ ተቋም፡ውስጥ፤በምክትል፡አስተዳዳሪነት፡ስለሚሰራ፥ኣምቻ፡ጋብቻውን፥ለማጽደቅ፣ ለማስመረቅ፥`መቼ፡ነው፡ታድያ፥ መጥታችሁ፡የምትጠይቁን*`፡የሚለው፥የስልክ፡ጥሪው፡በርካታ፡ነበር። እነሆ፡አሁን፡`ጊዜን~ኹነታትን`፡ገጠሙለት፡እና፡ደረስን፡ ማለት፡ነው።

`ኣዲኳላ`፤ለጥቂት፡ስዓታት፡አርፈን፥እኔ፡`ሚሪንዳ`፣ አጎቴ ፣`መሎቲ`፡ቢራ፤ ከአልን፡በሁዋላ፥ጉዟችንን፡ቀጥለን፥አመሻሽ፡ላይ፥ወደ፡ ጥንታዊቱ፡ከተማ፡ስንገባ፥በድንጋጤ፡ኣፌ፡ደረቀ። ወረርሽኝ፡እንደገባበት፡መንደር፥ትውር፡የምትል፡ነፍስ፡ከመንገድ፡አለመታየቱ፡ ሲደንቀኝ፥ኣጎቴ፡ግን፥በኣንክሮ፡እና፡ትኩረት፥ግራ፡ቀኙን፡እየተመለከተ፤ጭንቅላቱን፡ይነቀንቃል።

“ጎይታና~ዘመዶቼን፡ከጠየቅሁ፡እኮ፥ስንት፡ግዜዬ~!”~:እየ፡አልክ፡ለምትወተውተኝ፥ጥሩ፡አጋጣሚ፡ይሆንሃል”፡ብሎ፥ የመሥርያ፡ቤት፡መኪና፡ነጂውን፥`በርኄን`ም፡አስከትሎ፡ነበር፡እና፥ ሁለቱም፤በከፍተኝ፡ድንጋጤ፡እና፡ሥጋት፥ግራ፡ቀኝ፣ ዙርያውን፥በጸጥታ፡ይገለማመጣሉ።

” ጎይታና፥እንታይ፡ጉዱ!!~ሎሚ፥ናይ፡ግንቦት፡ልደታ፡ኣይኾነተን~እምበር!!”፡ሲል፥በጮክታ፡አነከረ። በሥጋት፡የታፈነው፡ ኣጎቴ፤ኣንዳች፡አስተያየት፡ከመስጠት፡እንደተቆጠበ፥ለመኪና፡ነጂው፥የምንሄድበትን፡ሰፈር፡አግጣጫ፡እየጠቆመው፥`እንዳ፡ ፋሉል`፡ከተሰኘ፡መንደር፥ሰተት፡ብለን፡ደረስን።

ከቅጥር፡ግቢው፡በራፍ፡ወጥተው፡የሚጠባበቁን፤ባልና፡ሚስት፥ለጥየቃ፥እነርሱው፡ዘንድ፡ከአለቸው፡የኣጎታችን፡ልጅ፥ከ `ሎሚታ`፡ጋር፥መኪናችንን፥ገና፡ከርቀት፡ሲያዩዋት፥”ዕልልል!!” ማለት፡ጀመሩ።

እጅግ፡ደማቅ፡እና፡ቤተ፡ሠብዓዊ፡ፍቅር፡በመላው፡መሥተንግዶ፡ተንከባክበው፤ወደ፡እልፍኙ፡በማስገባት፥በኣጸደ~ወይን፤ ድባብ፡ባማረው፡የጓሮው፡አትክልት፡ስፍራ፡አሳርፈው፥በመሦብ፡ከቀረበው፥የአማረ፡ድግስ፡እየተመገብን፥ከጠጁ፣ከጠላው፣ ከውስኪው፤በኋላ፡ቡናው፡ተፈልቶ፥ስለ፡የ፡ኣዲስ፡አበባ፡ቤተሰቦች፥ጤና፡እና፡ሠላምታ፡ሲጠረቅ፡አረፈድን።

የ፡እኔው፡ልብ፡ግን፥ከተማይቱ፤እንዲህ፥ጭጭ፡እርጭ፡የ፡አለችበትን፡ምክንያት፥ከ፡አሁን፡አሁን፡ያነሱት፡ይሆን፥በሚል፡በጉጉት፥ ተንሰፍስፎ፡ይጠባበቃል። ኣፍ፡አውጥቼ፥ኣጎቴን፡አልጠይቀው፡ነገር፥የእርሱ፡የእራሱ፤ግርታ፤አስፈሪ፡ሆነብኝ።

መኪና፡ነጂው፡`በርኄ`፤ወደ፡ጓዳ፥በትሬ፡ከቀረበለት፡ምሴት፡እየጎራረሰ፤ከቤት፡ሰራተኞች፡ጋር፤በትግርኛ፡ሲነጋገር፡ይሰማኛል። ጋሼ፡`ተሞገስ`፤በልዩ፡ትኅትና፥ማረፍያ፡ክፍላችን፡እንደተዘጋጀልን፡ሲጠቅስ፥ኣጎቴ፥በወትሮው፥ኮራ፡በአለ፡የ፡ባላ~ሥልጣን፡ አነጋገር፡ቃናው፥ምሥጋናውን፡አቅርቦ፥ሆኖም፡~”ብፁዕነታቸው፤በአስቸኵይ፡የፈለጉኝ፥አንዳች፡አጣዳፊ፡ነገር፡ቢገጥማቸው፡ስለሆነ፥ከ፡እርሳቸው፡ጋር፡በቅርብ፡ለመወያየትም፡እንዲያመች፡ብዬ፥`ኮሮኔል፡~ኣባተን`፡ሆቴል፡እንዲይዝልኝ፡በስልክ፡ አሳስቤው፡አለሁ”፡ሲል፡አስታወቃቸው። በውሳኔው፥ከ፡እትዬ፡`ተኾላሽም`፡ይልቅ፡ጋሼ:`፡ተሞገስ`፡ቅር፡የ፡አለው፡ይመስላል፡~

“~እኛው፡ዘንድ፡ብታርፉልን፥ደስታችን፤በአያሌው፡ነበር~እ~የስራ፡ሃላፊነትን፡ከአነሱ~መቼስ፡ምን፡ይደረጋል”፡ሲል፡አንገራገረ።

ብዙም፡ሳይቆይ፥የጠቀሳቸው፡`ኮሮኔል~ኣባተ`፤መኪናቸውን፡እያሽከረከሩ፡ከተፍ፡አሉ፡እና፥ከ፡ሞቀ፡የ፡ሠላምታ፡ልውውጥ፡ በኋላ፡~`ከረፈደ፡ወደ፡የደረሱበት፡ገበታ፡እንዲቀርቡ፡ጋበዟቸው። በመጀመርያ፤እንደ፡ማቅማምት፡ብሏቸው፡ነበር፥በኋላ፡ላይ፡ግን፥የተደረደረውን፡ውስኪ፡ጠርሙሶች፡ሲቃኙ፤ሃሳባቸውን፡አስለወጡ፡መሰለኝ፥መለዯዋቸውን፡አውልቀው፤ከ፡መስቀያው፡ላይ፡ በማኖር፥በገበቴ፡በቀረበላቸው፡ወኃ፤እጃቸውን፡ይለቃለቁ፡ጀመር።

~*~

(ገጽ፡~)

እትዬ፡`ተኾላሽ`፥ከተቀመጥኩበት፥ወደ፡እልፍኙ፡መጥታ፡~”ውይ !~ምነው፡ፈዘዝሽ፤`ሎምዬ`!?~፥እንግዳችንን፤አስተናግጂው፡ እንጂ”! ስትል፡`ሎሚታ`ን፡አተጋቻት። ከወደ፡ጥጉ፤ግርግዳውን፡ተደገፋ፥`በርኄ`፡እና፡ሰራተኛዋ፡የሚጨዋወቱትን፡ የምታደምጠው፡`ሎሚታም፤በ፡ቀስታ፤እየ፡አመነታች፤ወደ፡እንግዳ፡መቀበያው፡ክፍል፡ቀርባ፤ከፊት፡ለፊቴ፤ፎቴው፡ላይ፡አረፍ፡ አለች።

እትዬ፡`ተኾላሽ፤ቀደም፡ብላ፥ወደ፡እልፍኙ፡ስታስገባን፡~” የ፡`ሞገሴ`፡እህት፡ነች፥ለትምህርት፡ቤት፡እረፍትዋ፤ልትጠይቀን፡ መጥታለች” ስትል፡አስተዋውቃን፡ነበር። ዣንጥላ-ቅድ፤ ባለኣደይ፡አበባ፡ቀሚስዋን፡መቀነት፡እያፍተለተለች፤ዝም፡ብላ፡ ተቀመጠች። ቁንጅናቸው፡በሚያስከትለው፥የሰው፡ዓይን፡ትኩረት፥ዓይነ~አፋር፡ከሚሆኑት፡ልጃገረዶች፡አንደኛዋ፡እንደ፡ሆነች፥ በ፡ጉልህ፡ያስታውቃል። እንዴት፡እንደማናግራት፡ሳስብ፥እርስዋው፡ቀድማ፥በለስላሳ፡ድምጽዋ፡~

” የት፡ነው፡የምትማረው ?” ስትል፡ጠየቀችኝ
” ኮከባ~ጽባሕ`፡የሚባል፡ትምርት፡ቤት፡ነው~ኣዲስ፡አበባን፥በደምብ፡ታውቂዋለሽ?”
” በደምብ፡አላውቀውም፥ግን፤ሥሙን፥የኣጎቴ፡ልጆች፡ሲጠሩት፡ሰምቻለሁ~ስንተኛ፡ክፍል፡ደርሰሃል?”

” ዘንድሮ፥አሥራ፡አንደኛን፡ጨረስኩኝ”

” እኔ~`ናዝሬት`፡ትምህርት፡ቤት፡ነው፡የምማረው~አሥረኛ፡ክፍል፡ደርሻልሁ~ታውቀዋለህ?”
” አዎን~አንዲት፡ዘመዴ፡አለች፡እዛ፡የምትማር~ታወቅሻት፥`ድምፂት`፡ትባላለች”

“ሥሟን፡የሰማሁት፡ይመስለኛል~እሷን፡ግን፡አላውቃትም~ለ፡ስንት፡ግዜ፡ነው፡`ኣክሱም`፡የምትቆዩት?”

” እኔ፡እንጃ~እሱን፥`ጋሽዬ`፡ኣጎቴ፡ነው፡የሚያውቀው~አንቺስ?”

” እኔ፥ከፍልሰታ፡ንግሥ፡በኋላ፡መመለስ፡አለብኝ~ኣያታችን፡ዓይናቸው፡ስለታመመ፤ሚጣቅ፡ዓማኑዔል፡ጠበል፡ ውሰጃት፡ተብያለሁ~እኔ፡ግን~ትንሽ፡ብቆይ፥ደስ፡ይለኝ፡ነበር!”

ከጓሮው፡ኣጸደ~ወይን፡ጥላ፡ስር፥ኣዋቂዎቹ፡የሚነጋገሩት፡ነገር፥ኮስተር፡የአለ፡ጉዳይ፡እንደሆነ፥ከድምፃቸው፡ዝግ፡ማለት፡ ተረድቻለሁ። ምን፡እንደሆነ፥`ሎሚታን`፡ልጠይቃት፡ግን፡አልፈለግሁም። እንደ፡ውጭው፡ከተማው፡ሁሉ፥እዚህም፡ቤት፡ላይ፤ አንድ፤የ፡አልታወቀ፥ስውር፡ድር፡ነገር፡የረበበበት፡ይመስላል። `ኮሎኔል~ኣባተ`፡ከመጡ፡በኋላ፤የ፡አዋቂዎቹ፡መንፈስ፤ሰብሰብ፡ የአለ፡ይመስላል።

`አንዳች፡ሚስጢር፡ነግረዋቸው፡ይሆን?`፥ብዬ፡ጠረጠርኩኝ። እትዬ፡`ተኾላሽም`፥አልፋ፡አግድማ፡~”ውይ!!~እረ፡ በድንግሊቱ~እንዲሁ፡ብለው!?”፡በማለት፡ስታነክር፡ይሰማናል።

“እናንተ፥እንዴት፡መጣችሁ~እኛ፡እኮ፥ለሁለት፡ቀን፡ከቤት፡አልወጣንም~ሃገሩ፡ውስጥ፡ምን፡እንደገባ፡እኔ፡እንጃ!”፡በማለት፡ ትከሻዋን፡ሽቅብ፡አለች።`በርኄ`ም፡ድምፁን፡እያጎላ፥” እናታይ፡ጉዱ!!*”፡ሲል፥ከጓዳው፡ስርቅ፡እየ፡አለ፡ይሰማናል።

የ፡`ሎሚታ`ን፡ድምፅ፡መስማት፥በጣም፡ስለ፡ወደድኩት፥እንደገና፡እንድትነጋገር፡ፈልጌ፥ምን፡እንደምጠይቃት፡ሳንሰላስል፡~ ” ስንት~ብዙ፡ጕደኞች፡አሉህ?”፡የሚል፤የልጅ፡ዓይነት፥የዋህ፡ጥያቄ፡አቀረበችልኝ። ጥያቄዋ፤ከዕድሜዋ፡የአነሰ፡ቢመስለኝም፥

ልመልስላት፡እንደሚገባኝ፡በመገንዘብ፥ትንሽ፡አሰብ፡አድርጌበት፡ሳበቃ፡~

“~እ~ብዙ፡ጕደኞች፡እንኳን፡የሉኝም፥ግን፥በጣም፡የምንቀራረብ፥ጥቂት፡ጕደኞች፡አሉኝ”
” ከትምህርት፡ቤት፡ሰዓት፡ውጭ~ምን፡ስትሰሩ፡ትውላላችሁ?”
” ሲኒማ፡መግባት፡እና፤አልፎ፡አልፎ፡ደግሞ፥ሰፈራችን፡የሚገኘው፥`ኤካ፡ተራራ፡ላይ፡መውጣት፡ደስ፡ይለናል~ለምን፡ጠየቅሽኝ?”~አሁንም፡፤የልማድ፡ትከሻዋን፡ሽቅብ፡በማለት፡~
” እንዲሁ~ዝም፡ብዬ፡ነው”፡ብላ፥ባዶ፡ጣውላው፡ላይ፡አቀረቀረች።

“አንቺስ ?”~፡ስላት፤ድንግጥ፡ብላ፡~

“እኔ፡ምንም፡ጓደኛ፡የለኝም፡እባክህ!”~፡ከማለትዋ፥እትዬ፡`ተኾላሽ`፥ጭንቅላታቸውን፡ይዘው፡~”አታደርጊውም አዛኝቱ!~አታደርጊውም!”፡እየ፡አሉ፡እየ፡ጮሁ፥ከጕሮው፡የተስፈተለኩ፥እኛን፡አልፈውን፡ወደ፡መኝታ፡ክፍላቸው፡ዘልለው፡ ገብተው፥በሩን፡ጓ፡አድርገው፡ጠረቀሙት። እጅግ፡አስፈሪ፡ችግር፡እንደገጠመን፡ይሄኔ፡ነው፡የተረዳሁት።

`በርኄም፤ከሰራተኞቹ፡ኣፍ፥የሰማውን፡ሰምቶ፡እንደተራበሸ፥ብድግ፡ቁጭ፡በማለት፡መራወጽ፣መንቆራጠጥ፡ጀምሯል። ከጓሮ፡ የታሰረችው፡ኩቲ፡ውሻም፡መጮህ፣ማላዘን፡ጀመረች።

`ሎሚታ`፤መዳፌን፡ጨብጣ፡~”ኣይዞህ፡አትፍራ”፡ብላ፡አጽናንታኝ፤ወደ፡ጕዳ፣ወደ፡እትዬ፡`ተኾላሽ`፡ሄደች።

~*~

(ገጽ፡~)

ኣጎቴ፥`ጋሽዬ`፡እንዲህ፡ሲረበሽ፡አይቼው፡አላዋቅም፡ነበር፡እና፥የ፡ጉዳዩ፤ምንነት፡ባይገባኝም፥እኔም፡አብሬው፡ተረበሽኩኝ። እጅግ፡ረዥም፡ቁመናውን፥ከቤቱ፡ውስጥ፡እያንጎራደደ፡~`ኣይይ፡እንዲህ፡ከሆነ፡እማ፥በግዜ፤ወደ፡ብፁዕነታቸው፡ዘንድ፡ሄጄ፥ከ፡ እኔ፡የሚሽቱን፡ምክር፡ልሥማ፡እና፡ሁኔታውን፡እንከታተል`፡ሲል፡አስታወቀ። አብረውት፡የተረበሹት፤ጋሼ፡`ተሞገሥ`፡እና፡ ኮሮኔል፡ኣባተም፡~`ኣዎን~እንዲያ፡ቢሆን፡ይሻላል~አስጊ፡ሁኔታ፡ቢሆን፡ነው፥እርስዎንም፥ከ፡ኣሥመራ፡ድረስ፡በአስቸኳይ፡ የጠሩዎት`፡ሲሉ፤ተደራርበው፡ተናገሩ።

`ኮሮኔል፡ኣባተ፥አጅቦ፡ሊያደርሰው፡ሃሳብ፡አቅርቦ፥ለመውጣት፡ሲዘገጃጁ፤`እትዬ፡`ተኾላች`፥እየ፡አነባች፥ከመኝታ፡ክፍልዋ፡ እየተጎተተች፡ወጥታ፥በነፈረቀ፡አፍንጫ፡~`ታድያ፥ባይሆን፥ልጁ፡እዚሁ፡እኛው፡ዘንድ፡ይቆያ፡`ጋሽዬ`፥ተመልሰህ፡መጥተህ፥ የአለንበትን፡ሁኔታ፡ሳታስረዳን፡አትቀር፡መቼም~`አለችው። የቤቱን፡ዙርያ፡እና፡እኔንንም፡ጭምር፥በትኩረት፡ተመልክቶ፥ ጭንቅላቱን፡እየነቀነቀ፡ሲወጣ፥ጋሽ፡`ተሞገስ`፡ሊሸኙት፡አብረው፡ወጡ።

`በርኄ`፥የሰማውን፡ሰምቶ፥ቀድሞ፤ወደ፡ደጅ፡በመውጣት፤የመኪናውን፡ሞተር፡ቆስቁሶ፡እየጠበቀ፡ነበር። እንደ፡ግዳጅ፡ተልዕኮ፡ ስምሪት፥ከ፡ኮሮኔሉ፡ጋር፡እየተከታተሉ፤ግቢውን፡ጥለው፡ፈትለክ፡ብለው፡ወጡ።

እትዬ፡`ተኾላች`፥ከ፡አፍንጫዋ፡የሚወርደውን፡እዥ፥በነጠላዋ፡ጥለት፡እየ፡አባበሰች፥ቀረብ፡ብላኝ፤አገጨን፡በማቅናት፡~

`አይይ፡ፍርጃ~እስቲ፡ይሄ፡ምስኪን፡ልጅ፥ዘመዶቼን፡ብሎ፡ለእረፍት፡ቢመጣ~እንዲህ፡የአለ፡ጣጣ፡ውስጥ፡ይድረስ*~ግድየለም፥ እግዝዕትነ፡ማርያም፤ሁሉን፡ታበጀዋለች~ይሄ፥በዕድሜ፡ዘመናችን፡ተሰምቶ፡የማይታወቅ፡ጉድ፥ድንገት፡ ይውረድብን~ተሠዓሊለነ፡ቅድሥት`፡ስትል፥ባለ፡ቤትዋ፥የገዛ፡መደናገጡን፡ለመደበቅ፡መሰለኝ፡~`አንቺ፡ደግሞ፡ነገር፡ማግነን፡አመል፡ሆኖብሽ፡ሊቀር፡ነው፡መሰለኝ~ቤተ፡ክህነት፡እና፡መንግሥት፡መሃል፡የሚነሳ፥ጠብ፡እና፡ውዝግብ፡ጥንትም፡የነበረ፡ነገር፡ ነው*~አዲስ፡ነው፡እንዴ*~ይልቁኑ ፡እንግዳውን፡ልጅ፥ባዶ፡ሜዳ፡አታስደንግጡት~ማነሽ`~`ሎሚታ`፥ወደ፡ደጅ፡ወስደሽ፡ አጨዋውችው፡እባክሽ*`፡ሲል፡እየተቆጣ፥ወደ፡ጓዳ፡ገብቶ፡የ፡ስልኩን፡እጀታ፡አመናጭቆ፡አንስቶ፡ሲደውል፥በሩን፡ዘጋው።

`ሎሚታ`፡እንደ፡ተቆጡት፡ህፃን፡ኩምሽሽ፡ብላ፥መዳፌን፡ይዛ፡እየጎተተች፤ወደ፡ጓሮው፡ወስዳ፥ትልልቆቹ፡ጥለውት፡የሄዱት፡ ወንበር፡ላይ፡አሳረፈችኝ፡እና፡~`አይዞህ፡አትደንግጥ`፡በማለት፤ልክ፡በቅድሙ፡ድምፅ፡አጽናናችኝ።

`አልደነገጥኩም~ግራ፡ነው፡የተጋባሁት`፡አልኳት። ሳቅ፡አለች፡እና፡~`ኣማርኛ፡መናገር፥በደምብ፡ትችልበት፡አለህ`፡አለችኝ።

`ሃገሩ፡ውስጥ፥ምን፡ችግር፡ነው፡የተፈጠረው~ታውቂያለሽ’

`~እ~ጠይቄው፡ነበር፥ግን፥`ጋሽ፡ተሞገስ`፥ለልጆች፡የሚገባ፡ነገር፡ አይደለም~አርፈሽ፡ከ፡ኣክትሽ፡ጋር፥ጸሎተ፡ምኅላ፡ላይ፡በርቺ፡ብሎ፡መለሰኝ`~

`ጸሎተ~ምኅላ`፥ምንድን፡ነው*`

~ `ኅይለኛ፡ችግር፡ሲፈጠር፣ሲፈጠር፥ከቄሶቹ፡ጋር፡የሚደረግ፡ልዩ፡ጸሎት፡መሰለኝ`

`ሎሚታ`፡አዲስ፡የምትነግረኝ፥አዲስ፡ነገር፡ስለ፡አልነበራት፥ዝም፡ብላ፡ዓይን፡ኣይኔኖቼን፡ብቻ፡ትመለከታለች። ከጓዳ፤ገረድየዋ፡ እና፡ዘበኛው፤በትግርኛ፡ሲጨቃጨቁ፡ይሰማኛል። ተኩስ፡እና፡ረብሻ፡ሳይሰማ፤ሃገሩ፡እንዲህ፥ዝም፣ድርግም፡ማለቱ፤የባሰ፡ግራ፡ አጋባኝ።

`ገረዲቱ፡እና፡ዘበኛው፡የሚያወሩትን፥ሄደሽ፡ጠይቀሽ፥ለምን፡አትነግሪኝም~እነሱ፡መቼም፥አንድ፡ነገር፡ሳያውቁ፡አይቀሩም`

`ጠይቄአቸው፡ነበር~እነሱም፤ምንም፡የሰሙት፡ነገር፡የለም፥`ወደ፡ዘመድ፡ቤት፥`እንዳ~`ማይ`፡ሰፈር፡እንዳንሄድ፡ፖሊሦች፡ መለሱን`፡ብለውኛል

~ስንት፡ዓመት፡ሆነህ፡አንተ*`። ካለ፡ቦታው፡የአነሳችው፡ጥያቄዋ፡የባሰውን፡አስደነገጠኝ፡እና፡~

`ማን፡እኔ`፡ስል፡አዳገምኳት፥እንደ፡ፈገግታ፡እየ፡አደረጋት፡~`አዎን፡አንተ`፡አለችኝ። በድፍረት፥አተኩሬ፡ብመለከታት፡እንኳን፥ዓይኖችዋን፡አትቀጽብም። አስገረመችኝ። የቤተሰቡ፡መደናገጥ፤እርሷን፡ጨርሶ፡የሚመለከታት፡አይመስልም።

`ሌላ፥ከፍተኛ፡ችግር፡ውስጥ፡እየ፡አለን፥ለምን፥አሁን፤በእዚህ፡ሰኣት፥የ፡እኔን፡ዕድሜ፡ማወቅ፡ፈለግሽ`

`ዕድሜ፤ከአለህ፡ንገረኝ፡አለበለዝያ፡ተወው*`፡ብላ፡እንደ፡መመናጨቅ፡አደረጋት። ስታኾርፍ፡ግዜ፤ድንገት፡ደስ፡ብትለኝ፡ ፈራኋት።

ኣፌ፡ላይ፡የመጣልኝን፥`ዕድሜዬን፡ቆጥሬው፡አላውቅም፥ግን፡እንደምገምተው፥ኣሥራ፡ሠባት፡ሳይሞላኝ፡አይቀርም`

`ትምህርት፡ቤት፡መዘገብ፡ላይ፥የተወለድክበት፡ቀን፡እና፡ዓመት፡ይጻፍ፡የለም፡እንዴ*`

`ሳይጻፍ፡አይቀረም~አይቼው፡ስላማላውቅ፡ነው~ለ፡አንቺ፡ግን፤ዕድሜዬ፥ምን፡ያደርግልሻል*`

በመሃሉ፥በጓሮ፡በኩል፥ጉምጉምታ፡ተሰማ፡እና፤አንድ፤የባህታዊ፥የ፡ቁርበት፡ቆብ፡የደፉ፡ሽማግሌ፥ከ፡ሰራተኞቹ፡ጋር፡ሲነታረኩ፡ ቆይተው፥በመጨረሻ፡ገረዲቱ፡~`እመይቴ፥እረ፥እኒህ፥`መምሬ~ምክሩ`፡በጓሮ፡አጥር፡ሾልከው፡ገብተዋል`፡ስትል፡ጮኸች። እትዬ፡`ተኾላች`፡ቶስ፡ብላ፥ከእልፍኙ፡ወጥታ፡~`ይግቡኣ፡ታድያ~እልፍኙን፡አሳያቸው`፡ስትል፡ሰማናት።

የበግ፡ደበሎ፡የመሰለ፥ጉንግን፡ረዥም፡ጽሂማቸውን፡በኣኮፋዳ፡የተሸከሙ፡ባህታዊ፡ጎንበስ፣ጎንበስ፡እያሉ፡ገብተው፤በሩ፡ ተዘጋ። `ሎሚታም፥ድንገት፥እኔን፡ትታ፥ወደ፡ሰራተኞቹ፡ዘንድ፡ሮጠች። ግቢውም፤እንደ፡ከተማው፥የባሰውን፥ጭጭ፡እርጭ፡ አለብኝ።

የምሆነው፣የማስበው፡ቸግሮኝ፥የ፡ጋሽዬን፡ተመልሶ፡መምጣት፤አጥብቄ፡በልቤ፡ስመኝ፡ቆይቼ፥`ሎሚታ`፥እጅግ፡ቀስ፡ብላ፡ እየተጎተተች፡ተመልሳ፡መጣች፡እና፤አጠገቤ፡ጸጥ፡ብላ፡ተቀመጠች። ፊትዋ፥ልክ፥በጥፊ፡የአጮሏት፡ህፃን፡ይመስል፥ዝርግፍ፡ብሎ፡ ነበር።

`ምን፡ነገሩሽ*`። ከ፡ግቢው፡አጥር፡ውጭ፡ውጭውን፡እየተመለከተች፥በአሉታ፥ጭንቅላትዋን፡ብቻ፡ነቀነቀችልኝ።

`ሎሚታ`፥ንገሪኝ፡እንጂ~፡ምን፡አሉሽ፡ታድያ~ባህታዊውስ፡ማን፡ናቸው?`ነገር፡ጠቍሚ፡ጣትዋን፤ኣፍዋ፡ላይ፡ቀስራ፡ ~`ኡሥሥ`፡በማለት፡አስጠነቀቀችኝ። በሚሥጢር፡ልትነግረኝ፡የፈለገችው፡ነገር፡እንደ፡አላት፡ግን፡ገብቶኛል። የፊትዋ፡መዘርገፍ፥ ቀስ፡እየ፡አለ፡ሲሻለው፡ግዜ፥የበፊቱ፡ቁንጅናዋ፥ከቦታው፡ተመለሶ፡ልክ፡ገባ።

`ምንድነው፡የሚያወሩት*~ከመሥኮቱ፡ጀርባ፡ተለግተሽ፥የሚሉትን፡ስታዳምጭ፤በጓሮ፡በኩል፡አይቼሽ፡አለሁ፥ከፈልግሽ`

እንደገና፡ኣፌን፡በመዳፍዋ፡ከደነችው፡እና፥`ኡሥሥ`፡አለችኝ። ከከተማውም፡መራቆት፡የባሰ፤የእሷ፡ሁኔታ፡አስፈሪ፡ሆነብኝ። መሄጃ፡ሰለ፡የሌለኝ፡እንጂ፤አሁኑኑ፡ብሸሻት፡ደስታዬ፡ነበር። ቆንጆ፥ዕብድ፡ልጃገረድ፡መሰለችኝ።

`እኮ~ምንድነው፡ነገሩ*`። ቆንጆ፡ፊትዋን፥ላይ፡ታች፣ዙርያውን፡እያመላገጠች፡~

`ዕድሜህን፡ንገረኝ፡እና`፡ብትለኝ፥ፈጽሞ፡የምታሾፍብኝ፥ወፈፌ፡ሴት፡መሰለችኝ። በቀስታ፤ተነስቼ፤ወደ፡ሰራተኞቹ፡ዘንድ፡ ለመሄድ፡ስቃጣ፤ክንዴን፡አፈፍ፡አድርጋ፥ከመቀመጫው፡አኑራኝ፡~

`ሥማ፡እንግዲያው፥ከፈለግህ~ቄሶቹ፡ሁሉ፥ወደ፡እየሩሣሌም፡ለመሄድ፥ታጥቀው፡ተነስተዋል*`፡አለች። የትኞቹ፡ቄሦች*፣ወደ፡የትኛዋ፡እየሩሣሌም*፣እንዴት፡አድርገውስ፡ነው፡ለመሄድ፡የተነሱት*፥ፈጽሞ፡ኣእምሮን፡የሚያናውጽ፥አንዳች፤ክፉ፡ነገር፡የሰማሁ፡መሰለኝ።

`~ይሄ፥አሁን፤ቅድም፥መስኮቱ፡ስር፡ተለግተሽ፡የሰማሽው፡ነው፥በእርግጥ*`። ዙርያውን፡ተገላምጣ፡ስታበቃ፥በሹክሹክታ፡~ `ኣዎን~አትጩህ*~ከተማው፡ከተሻለው፡በኋላ፡ግን፤እዚህ፡አብረኸኝ፡መቆየት፡አትፈልግም*`

`ሎሚታ`~ጤነኛ፡ፍጥሩር፡ነሽ፤ለመሆኑ*~ነው፡ወይስ፥ችግሩ፡ኣንጎልሽን፡አዙሮብሽ፡ይሆን*` `አትጩህ፣አትጩህ*~የሰማሁትን፡ዕውነት፡ነው፡የነገርኩህ~እንድትቆይ፡የፈልግሁት፡ግን፥በጣም፡ስለወደድኩህ፡ነው`

ዦሮዬን፡ማመን፡አዳገተኝ፥ ምናልባት፤ለህክምና፡ለጸበል፡የመጣች፥የ፡ኣእምሮ፡ህሙም፡ትሆን፡ብዬም፡አሰብኩኝ። እግዜኣብሔር፡ጭንቀቴን፡ሰምቶ፡ነው፡መሰለኝ፥ድንገት፥በሩን~`ጓ`፡አድርገው፡አላግተው፤ከመኝታ፡ክፍላቸው፡የወጡት፡ አክስቴ፡`ተኮላች`፥በንዴት፡ጦፈው፣ለሚናገሩ፡ሳይመርጡ፥ለቤተኛው፡ሁሉ፣እና፡ለመላው፡ግቢ፡እና፡መንደር፡ይጮሃሉ፡~

`ጋሽዬ፡ተመልሶ፡መጥቶ፡የሚለውን፡ሰምተን*~አለበለዝያ፤እንደ፡ባህታዊው፡ነገር፡ከሆነ፥ሃገሪቱ፡አልቆላታል፡ማለት፡ ነው~አንተ፡ድሮም፤ነገርን፡ማባበል፡ትወዳለህ~ምን፡ቀረን፡ተእዚህ፡ወድያ*~`ጽላተ~ጺዎንዋ`፥ዓይናችንን፡እየ፡አየ፥ጥላን፥ሽቅብ፡ አረገች፡ነው፡እኮ፡የሚሉን~ታድያ፥ይሄንን፤ክር፡የአሰረ፡ክርስትያን፡ዦሮ፥ዝም፡ብሎ፡ይሰማዋል*`። ጋሼ፡`ተሞገስ`፡ሲጃራውን፡በንዴት፡እያቦለቀ፡ተከትሎ፡መጣ፡እና፡~`እኔ፡ነኝ፡ጥፋተኛው፥ቀድሞውን፥አንቺን፡ሰው፡አድርጌ፡ ማማከሬ፥ባህታዊው፡የዓዩትን፣የሰሙትን፡ነው፡የመሰከሩልሽ~ምን፡ያድርጉ፡ትያለሽ*`። የኣክስቴ፡`ተኮላች`፤ንዴት፡ግን፡ አልበርድ፡አለ፡~

`ውይ*~፥ይሄንን፥ጉረሮ፡የሚፍቅ፡ትግርኛችሁን፥`ተኾላች`፡አትሰማም፡ብለህ፡ነው~ሚስጥር፡የምታወራበት*~ለማንኛቸውም፡ ጋሽዬ፡ተመልሶ፡ይምጣ፡እና፡የሚለውን፡እንስማለን*~ማነሽ፡አንቺ፥`ሎሚታ`፡እንግዳውን፡ልጅ፡ወደ፡እልፍኝ፡አስገቢው፡እና፥የ፡ መክሰሥ፥ሻይ፡ቡና፡በይው፡እባክሽ*`። `ሎሚታ`፡መጥታ፤መዳፌን፡ጨብጣ፤ወደ፡እልፍኙ፡አስገባችኝ።

~*~

(ገጽ፡~)

ባል፡እና፡ሚስቱ፤ተመልሰው፤ወደ፡መኝታ፡ክፍላቸው፡ገብተው፥እንደገና፡መነታረካቸውን፡ቀጠሉ።

ቤተኛው፤ሁሉ፤በእየ፡ፊናው፡ይንሽኵሽካል። እኔ፤እንዳልደናገጥ፥እንድታበረታታ፡የታዘዘችው፥ `ሎሚታ`፥ለእራሷ፤ፈጽሞ፡ስጋት፡የገባት፡ አትመስልም። ይሄም፡መሆኑም፥እጅጉን፡ደነቀኝ። እጄን፡እየጎተተች፡ወስዳ፡የአስቀ መጠችኝ፥ሰራተኞቹ፡ከሚቀመጡበት፥ከማዕዱ፡ክፍል፡ጎን፡ ከሚገኘው፤ተዛነብ፡ስር፡ነበር፡እና፥የሚነጋገሩት፡ይሰማኛል። እርሷ፡ግን፡ተመልሳ፤ወደ፡እነ፡እትዬ፡ተኾላሽ፡መኝታ፡ክፍል፡ጥግ፡ሄዳ፡ተለግታ፡ታዳምጥ፡ጀመር። ከ፡ኣዲስ፡ኣበባ፡የመጡት፤እንጀራ፡ ጋጋሪዋ፡ባልቴት፥ትግርኛ፡ስለማይነጋገሩ፥በኣማርኛ፡እንዲያወሩ፤ሰራተኞቹን፡ ይጎተጉቷቸዋል።`ሃዳስ`፡እያሉ፡የሚጠሯት፡ ሴት፥በተኮላተፈ፡ዓምኅርኛ፡~”እቺ፡ልጅቱ፥በመጣች፡ግዜኣት፡ኖ~ሃገሩስ፡መረበሾት፡የኣለ!”፤ስትል፥

እንጀራ፡ጋጋሪዋ፡~”እህ~እርስዋ፡ምን፡አጠፋች~ኣእምሮዋ፡ስለታመመ፡ነው፥ዘመዶችዋ፤ለጸበል፡ የላኳት~ዝም፡ብለሽ~በቅናት፡ኣፍ፡ነው፡የምታወሪው” ሲሉ፡ዝም፡አሰኝዋት።

ዘበኛው፥ከውጭ፡ተመልሶ፡ገባ፡እና፥አንገቱን፡አስግጎ፡~” ጌቶቹ~አሁንም፡አልበረደላቸውም?”፡ሲል፥በቀስታ፡ጠየቀ።`ሃዳስ`፡በመዳፍዋ፤ ወደ፡እኔ፡ጠቆመችው። ምን፡ለማለት፡ እንደፈለገች፡አልገባውም፥ወሬውን፡ቀጠለ፡~ “ባህታዊውን፤ወደ፥`ክልዕተ~ጸምሪ`፡አኳያ፡አመላክቼው፡ተመለስኩኝ~ከእዝያ፡ወድያ፡ማለፍ፡ግን፡አልቻልኩም~ሃገሩ፥አሁ ንም፥ ዙርያውን፡በፖሊስ፡እንደታጠረ፡ነው”።

ስለ፡`ሎሚታ`፡ለጸበል፥ከኣዲስ፡አበባ፡መምጣት፡የተናገሩት፡ከነከነኝ። የሁኔታዋ፡መላቢስነት፥በእዛ፡የተነሳ፡እንዳይሆን፡ጠረጠርኩኝ። በበለጠ፡ለማወቅ፡በመሻት፥ባልቴትዋን፤ጠጋ፡በማለት፡~
” ታድያ፡ጠበሉን፡ተጠመቀች?~ወይስ፡እንዴት፡ሆነች፡እማማ?”፤ብል፤እጃቸውን፡እያወራጩ፡~

“ምን፡ትጠመቃለች፥ባልና፡ሚስቱ፡አልስማማ፡ብለው~ጌቶቹ፥`ዘመናዊ፡የኣእምሮ፡ ህክምና፡ነው፡የሚያስፈልጋት፥የጉርጓድ፡ውኃ፡አይደለም፡ ይላሉ~እመይቴ፤ወዲህ፥`ጠበሉ፡መቼ፡ተሞከረና፡ባይ፡ናቸው~መላው፡አልታወቀም፤እባክህ !”

`ሎሚታ`፥ካለአቅሟ፥ሙቀጫ፡እንደ፡አሳዘሏት፡ሴት፡ጉንብስ፡ብላ፤እግርዋን፡እየጎተተች፡መጥታ፡አጠገቤ፤በጸጥታ፡ተቀመጠች። ሰራተኞቹ፥ወሬ፡ለመስማት፡ጠጋ፣ጠጋ፡ቢልዋትም፤ፊት፡ነስታ፡አሸሸቻቸው። እኔም፡እንዳልጠይቃት፤ፈራኋት። ቅድም፥ጨርሶ፤ግድ፡የማይሰጣት፡ልጅ፡መስላ፡ስታስደነግጠኝ፡ቆይታ፤አሁን፡ደግሞ፥የዕድሩ፡ኣባዜ፡የሰፈረባት፡መስላ፡መጣችብኝ።ዝምታዋ፡ሲያፍነኝ፡ግዜ፡~
” ምነው፤ምን፡ሰማሽ?” በማለት፥እራሴው፡ተነፈስኩኝ። ትክሻዋን፡ሽቅብ፡መታ፡አድርጋ፡~

” ስትናገር~አትጩህ፡አላልኩህም!”፡ስትል፡ተቆጣችኝ። እንኳን፡ልጮህባት፡ቀርቶ፥ድምፄ፤ከክፍሉ፡እርቆ፡አይሰማም፡ነበር፡እና፥የልጅቱ፡ አነጋገር፡እያስፈራኝ፡መጣ። ተነስቼ፤ወደ፡ጕሮው፤አጸደ~ወይን፡ጠለል፡ሄጄ፥ለብቻዬ፡ተቀመጥኩኝ። ከእርቀት፡የታዘቡን፡ባልቴት፥ኣሳዘንኳቸው፡መሰለኝ፥በቀስታ፡ጠጋ፡ብለው፡ቀርበውኝ፡~”አይዞህ፡የእኔ፡ልጅ~በንግግር፡አስቀየመች፡መሰለኝ~እሷ፥ለሁላችንም፥እንዲሁ፡ነች፥ በትዕግሥት፡እለፋት፥ሆድዋ፡ውስጥ፤የሚሰማት፡የራዲዮ፡ጋኔን፡አለ፡ይላሉ”

ዘወር፡ብዬ፡ብገላምጣቸው፥የተናገሩት፡ከልባቸው፡እና፤በኅዘኔታ፡ጭምር፡እንደሆነ፤ከገጻቸው፡ተረዳሁ። መዳፌን፡ጨብጠው፤በእናት፡ዓይን፡ በማስተዛዘን፡~

“የሃገሩ፡ትርምስ፡ሲበርድ፤ለጠበሉ፡ሳይወስዷት፡አይቀሩም፥እስከዛ፡ድረስ፥አርቀህ፡ያዛት”

`ሎሚታ`፥የሚያቀርቧት፣የሚያርቋት፡ፍጡር፤ሳትሆን፥በገዛ፡ጉልበትዋ፡እና፡ዕልህዋ፡የምትመራ፡ስለሆነች፥መንቀር፣መንቀር፡እየ፡አለች፡ መጥታ፤አጠገቤ፡ልጥፍ፡ብላ፥ትከሻዬን፡እየደባበሰች፡~” ኣታኩርፍ~ኹርፍያ፡መጥፎ፡ነው~ሲመሽ፡በኋላ፥የማሳይህ፡ነገር፡ስለ፡አለኝ፥በትዕግሥት፡ጠብቅ”። ልክ፥የቤቱ፡እመቤት፡ የሆነች፡ይአክል፡ነበር፡ትእዛዝ፡አሰጣጥዋ።

ብዙ፡ሴቶች፡ባላውቅም፥ከማውቃቸው፥ጥቂት፡ሴቶች፡ተለምዶዬ፥ቆንጆ፡ሴቶች፥ፈጽሞ፡የሚያብዱ፡አይመስለኝም፡ነበር። የእዚህችኛዋ፡ግን፥ የኮረዳነት፡ዓመል፡ቅብጠት፡ሳይሆን፡አይቀርም፤ብዬ፡ገመትኩኝ። ተጠጋግተው፡ተቀምጠው፤ከእርቀት፡የሚነፅሩን፡ሰራተኞች፥የፖሊስ፡መኪና፡ጩኸት፡ሲሰማ፤አንዴ፡በርግገው፡ተበታተኑ። እትዬ ፡`ተኾላችም፤በሩን፡በርግዳ፡ወጣታ፡~

” የት፡ናችሁ!?~ሃገር፡ደህና፡አይደለም፡እንዴ!?”፡በማለት፤የገዛ፡ፍርሃትዋን፥በቁጣ፡ለመሸፋፈን፡ሞከረች። `ሃዳስ`፡ብቅ፡ብላ፡~”ደኅን፡ጽቡቅ፡አለና~እመይቴ~እዚኣ፡ምገጎ፡ተበላሲአ፡ኔራ~~”ወዘተ፤በማለት፡መሸፋፈን፡ቀጠለች።

~*~

(ገጽ፡፭)

ስለ፡`ሎሚታ`፡የሰማሁት፡ጭምጭምታ፥በጥርጣሬ፡ዓይን፡እንድ፡አያት፡የሚገፋፋ፡ቢሆንም፥የእርስዋ፡የእራስዋ፡ሁኔታ፡ግን፥አንድ፡አንድ፤ ድርጊትዋ፥በጥቂቱ፡ከማስፈራቱ፡በስተቀረ፥እጅግም፡የሚያገሽሽ፡አልሆነብኝም። እንድያውም፥ለጉጉ፡አንጎሌ፥የባሰውን፡መስዕብ፡ነው፡የሆነኝ። በእዚህም፡ላይ፡ደግሞ፥እርስዋን፡እራስዋን፡ የሚታወቃት፡አይመስልም፡እንጂ፥ከልክ፡ሲያልፍ፤ቆንጆ፡ነች።

ዘበኛው፥`ኣቦይ~ገዝሙ`(እርሳቸው፡ግን፡`ኣቦይ`፡መባሉን፡አይወዱትም)፥ከእራሳቸው፡ጋር፡እየተነጋገሩ፥የጓሮውን፡አትክልት ፡ሲኮተኩቱ፥ ድምፃቸውን፡በመስኮት፡የሰማችው፥`እትዬ~ተኾላች`፥ረዥም፡አንገትዋን፤በመስኮቱ፡ሰገግ፡አድርጋ፡~ ” እኮ~ምን፡የሚሉት፡ፈሊጥ፡ነው፡ይሄ!?~ሃገር፤በምኅላ፡ክርያላሦን፡ሲጨነቅ፤ጎንደርኛ፡ማንጎራጎር!~እኮ፡ምን!?”፡ብትላቸው ፥መኮትኮቻውን፥ባሬላው፡ላይ፡አኑረው፥ካኪ፡ባርኔጣቸውን፡አውልቀው፡~”ቢጨንቀኝ፡ነው፡እመይቴ!~፣የምሆነው፡ቢቸግረኘ፡ነው!~ኸ፡ከተማው፡የምንሰማው፡ሁሉ~የደግ፡አይመስልም !”፡ሲሉ፡ አልጎመጎሙ። የምላሽ፡ግሳጼ፡ብታሰማም፥ በመሃሉ፥የእነ፡ጋሽዬ፡መኪና፡ተከታትሎ፡ጥሩምባውን፡እያጮኸ፡ስለመጣ፥ዘልለው፡ሄደው፡ የቆርቆሮውን፡የግቢ፡በር፡ብርግድግድ፡አድርገው፡ከፈቱት።

ኮሮኔሉ፡ከመኪናቸው፡እንደወረዱ፥ወደ፡ጋሽዬ፡መኪና፡በመጠጋት፥የመኮንን፡ኮፍያቸውን፡አውልቀው፥በሰጋ፡መንፈስ፥ክፈፉን ፡እየጠራረጉ፥ ከንፈራቸውን፡እየነካከሱ፡ማውራት፡ጀመሩ፡~

” ብፁዕነታቸው፥ንቡረ~ዕዱ፡የሚሉትን፡ሁሉ፥እስከ፡ዳሩ፡አድምጠን፡ቢሆን፡መልካም፡ይመስለኛል~ጉዳዩን፥`ሲኖዶሱ`፡እስከ፡አሁን፡ ውሳኔ፡ላይ፡አልደረሰበትም፡እና`፡በማለት፤እየ፡አመነቱ፡መሆናቸው፥ያስታውቃል~መቼም፡ያው፥በመሠረቱ፥መንፈሳዊ፡መነኩሴ፡ናቸው፡እና~~”።

ጋሽዬ፤ወደ፡እልፍኙ፡ለመግባት፡አልፈለገም። ከ፡ቬረንዳው፡ላይ፡ከሚገኘው፡ሳጠራ፡ወንበር፡ላይ፡አረፍ፡በማለት፥የሚጠጣ፡ነገር፡አቅርቡ፡ ለማለት፥በእርቀት፤ለ፡`በርኄ`፡የእጅ፡ ምልክት፡ሲሰጠው፥ ተፍ፡ብሎ፡ወደ፡እልፍኝ፡ገብቶ፤የቢራ፡ጠርሙዞች፡ከብርጭቆ፡ጋር፡በትሬ፡ይዞ፡ ተመለሰ። እትየ፡`ተኾላች`፤እስሩ፡የተዟዟረ፡ሻሽዋን፡እያጠባበቀች፡መጥታ፥ጸጥ፡ብላ፡አጠገቡ፡ተቀመጠች። ጋሼ፡`ተሞገስ`፤ክፉ፡ ላለመስማት፡የፈለገ፡ይመስል፤ከመኝታ፡ክፍላቸው፡ውስጥ፡ይንጎራደዳል።

ኮሮኔል፥የቀረበላቸውን፡የቢራ፡ጠርሙዝ፡አንስተው፥በኣንድ፡ትንፋሽ፡ገሽረው፥ቅጥር፡ግቢውን፡ዙርያ፡ከቃኙ፡በኋላ፡~

” ~እንደ፡ብፁዕነታቸው፡ፈቃድ፥እዝያው፤ከተዘጋጀልህ፡ማረፍያ፡ሆነህ፥ምክሩን፡በቅርቡ፡ብታካሂደው፡መልካም፡መሰለኝ~መቼም፥ በጥድፍያ፥ከኣሥመራ፡የ፡አስጠሩህ፥በዙርያቸው፡የአሉትን፥ ሊቀ፡ካህናት፡እና፡ሹማምንት፡ተዓማኒነት፡ቢጠራጠሩ፡ነው”። የጋሽዬ፡መንፈስ፤ በእራሱ፡ችግር፡እንደተጠመደ፥የ፡መኮንኑን፡ሃሳ ብ፤እጅግም፡የሚከታተል፡አይመስልም። ኮሮኔሉ፡ግን፥የስጋት፡ ንግግራቸውን፡አላቍረጡም፡ ~ “~የበጌምድሩም፥`ኣቡነ~ማስያስ`፤ዛሬ፡ጠዋት፥`ሄሊኮፕተር፡ተልኮላቸው፥እንዲገቡ፡ተደርጓል~ክቡር፡እንደራሴውም፥`ከ፡እዮቤልዩ፡ ቤተ፡መንግሥት፥የሚሰጠውን፥የዘውድ፡ምክር፡ቤትን፡ውሳኔ፡ሳልሰማ፥ጥቂት፡ካህናት፡እና፡ገበዞች፤በዕብነ~በረድ፤ድንጋይ፡የተነሳ፡ኣምጸዋል፡ ብዬ፥ሃገር፡ላይ፥ታላቅ፡ጉዳትን፡ሊያደርስ፡ የሚችል፡ኣጉል፡ውሳኔ፡ውስጥ፡አልገባም`~፡ባይ፡ናቸው~ከሸዋ፡ሰዎች፡ጋር፡የአላቸውን፡ሆድ፡ እና፡ጀርባ፡ሁኔታም፥ከአንተ፡የተሰወረ፡አይመስልም”

ኮሮኔሉ፡ጋሽዬን፡እንደ፡ጓደኛ፡ማነጋገሩ፡ሲደንቀኝ፥እንደመጣን፥ምሳ፡እየተበላ፡ሳለ፡~`ከ፡`ኣባተ`፡ጋር፡እኮ፥ቀደም፡በአለው፡ ግዜ፥ ኮሌጁን፡አቋርጦ፡ኣባ፡ዲና፡ፖሊሥ፡ኮሌጅ፡ከመግባቱ፡በፊት፡አብረን፡ተምረናል`፡ብሎ፤ለ፡ጋሼ፡`ተሞገስ`፡ሲናገር፡ሰምቼዋለሁ። ባለሥልጣኖች፡ሁሉ፥እርስ፡በእርስ፡ይተዋወቃሉ፡ማለት፡ነው፥ብዬ፡አስብኩኝ። ሳይሆን፡አይቀርም።

ጋሼ`፡ተሞገስ`፥የጸሎት፡መጽሐፉን፤በጣቶቹ፡እልባት፤እንደያዘ፥ጋቢውን፡ኣጣፍቶ፡መጥቶ፥ጋሽዬ፡አጠገብ፡አርፍ፡አለ። የሚነጋግሩት፡ነገር፡ የአጡ፡ይመስል፤እንደ፡ተኮራረፉ፡ትልቅ፡ሰዎች፥ጸጥ፡ብለው፥በእየ፡እራሳቸው፡ሃሳብ፡ተጠምደው፡ቆይተው፡~

“~እ~ብፁዕነታቸው፥እዝያው፤ግቢ፡አርፌ፥በምክር፡እንዳግዛቸው፡ስለጠየቁኝ~ለእራት፡እየተጠበቅሁኝ፡ነው”፡ብሎ፤ብድግ፡ ሲል፥እትዬ፡ `ተኾላች`፡እዬዬዋን፡ማቅለጥ፡ብትጀምር፥ባልዋ፤እየተቆጣ፥ክንድዋን፡ይዞ፡እየጎተተ፤ወደ፡እልፍኙ፡አስገባት።

“~ማንነቱ፡የአልታወቀን፡ሰው፥ከቅጥራችሁ፡እንዳታስገቡ~ነገሩ፡ከረር፡የ፡አለ፡ይመስላል~ለማንኛቸውም፥ስልክ፡እየደወልኩኝ ፤ሂደቱን፡ አሳውቃችኋለሁ~ልጁም፥እስከ፡ግዜው፡እዚሁ፡ይቆይ”፡ከማለቱ፥`እትዬ~ተኾላች`፡አሻፈረኝ፡ብላ፥ተመልሳ፡መጥታ፡እየነፈረቀች፡~ “

“እ~መሆኑን፡ግን፡ጋሽዬ!~እ~የ፡`ዋሻ፡ሚካዔል፡`መግብያ፡ደንግያው፡ተከፈተ፡የሚሉት፤በእርግጥ፡ነው!?”፡ስትለው፥እንደ፡ማረጋጋት፤ ትከሻዋን፡ያዝ፡አድርጎ:~”ስሚ፥`ተኮላች`፤እናንተ፡አሁን፡ማድረግ፡የአለባችሁ፥በጸሎታችሁ፡መትጋት፡ብቻ፡ነው~በእርግጥ፥ጥቂት፡ካህናት፥ ምዕመናንን፡ለማሳደም፡እየጣሩ፡እንደሆነ፡አውቀናል፥በተረፈ፥በእንዲህ፡በመሰለ፡ግዜ፥የሚወራው፡ሃሰት፡አያሌ፡ስለሆነ፥በወሬ፡ ተሸብራችሁ፡እንዳትፈቱ፡መበርታት፡ነው!”፡አላት። ጋሼ፡`ተሞገስ`፡ቬረንዳውን፡ላይ፡እየተንቆራጠጠ፡~

” ጥንትም፥በታህሣሡ፡ግርግር፡ወቅት፥`ሃገር፡ጠፍታለች፣መንግሥት፡ተገልብጧል~የምፅዓት፡መድረሻው፡ምልክት፡ነው`፡ብለው፥ ሕዝቡን፥`ሕዝበ፡ክርስትያን፡አልቆልሃል፥ሆ፡ብለህ~ተነስ`፡በማለት፥ወደ፡ዋሻው፡ኮልኩለውት፡እንደነበር፡እናውቃለን!”፡አለ ።

~*~

(ገጽ፡~)

ውቢቱ፥ትንስዬ፡ሮማ፡መሳይዋ፥አሥመራ፡የጀመርኩት፤መልካም፡የእረፍት፡ሣምንት፤በ፡`ኣክሱም`፡ጉብኝት፡ደሞቆ፥ወደ፡ ኣዲስ~ኣበባ፡ስመለስ፥ለዘመድ፣ለጕደኞቼ፡ሁሉ፤የምነግራቸውን፥የማያልቅ፡ታሪክ፡በልቤ፤ስቀምር፣ሳውጠነጥን፥ድንገት፡ሳይታሰብ፥ይሄንን፡የመሰለ፤ሥጋት፡እና፡ምንነቱ፡የአልታወቀ፡ውጥረት፡ውስጥ፡መግባቴ፤እራሴውኑ፡አሳዝኖኝ፤አቀርቀሬ፡ስተክዝ፥ ጋሽዬ፥ጠጋ፡ብሎ፥እራሴን፡እያሻሸኝ፥`ጭንቅሎ፥አይዞህ፡አትደንግጥ~የሚያልፍ፡የመንግሥት፡ጉዳይ፡ነው`፡ብሎኝ፤ወደ፡ መኪናው፡ዘው፡ብሎ፡ገብቶ፥ልክ፡እንደ፡አመጣጣቸው፥በ፡ጥድፍያ፡እየተከታተሉ፥ሽርር፡ብለው፡ሲወጡ፥የመኪናቸው፡ጎማ፤የአስነሳው፡ኣቧራ፥ግቢውን፡ሁሉ፤እፍንፍን፡ሲያደርገው፥`ሎሚታ`ን፡በዓይኔ፡ዙርያውን፡ፈልጌ፡አጣኋት።

እትዬ፡`ተኾላች`፥እራስዋን፡ማበረታቻ፡አዲስ፡ጉልበት፡የአፈራች፡ይመስል፥ጮክ፡ብላ፡~”ማነሽ~፡`ሃዳሥ`፥ጎይታና፡ከጸሎቴ፡ አታቍርጡኝ፡ብሏል፡እና፤ለ፡እንግዳው፡ልጅ፡ድራሩን፤ከማደርያ፡ክፍሉ፡አቅርቡለት~ለ፡`ገዝሙም`፥ማንነቱ፡ለ፡አልታወቀ፡ እንግዳ፥የግቢውን፡በር፡እንዳይከፍት፡ንገሪው~ያቺ፡ጉድ፡ደግሞ፡ወዴት፡ገባች፡ይሆን?~አንቺ፡`ሎሚታ`!”፡ብላ፡ከመጮኋ፤ወይዘሪት፡ግድ~የለሽ፥የጓሮ፡ወፍ፡ፉጨት፡የአልሰማች፡ይአክል፥ቀሰስ፡እያለች፤ከወደ፡እልፍኙ፡ብቅ፡ብላ፥” እመት~ኧረ፡ እዚሁ፡ነኝ~አለሁ”፡ስትል፡ተነፈሰች። እትዬ፥መረበሽዋን፣መደናገጥዋን፡ሁሉ፥`ሎሚታ`፡ላይ፡ለመወጣት፡እየጠኸየች፡~

“~ኧ!~ይሄ፡መተራሳችን፡እና፡የሃገር፡ረብሻ፥ለ፡አንቺ፥ምንሽም፡አይደል፡መሰለኝ!?~ኧ~እንድያው፡ለወጉ፡ይአክል፡እንኳን፥ ጠጋ፡ብለሽ፥`አይዟችሁ~በርቱ`፡አይባልም?ከጕዳ፡ምን፡ይወሽቅሻል!?~ያንኑ፡የፈረደበትን፡ራዲዮሽን፡እየጎረጎርሽ፡ነው፡መቼም፥አይደል?!”። `ሎሚታ`፤ወደ፡ግቢው፡እርቀት፥አሻግራ፡ እየተመለከተች፡~” ዓርብ፡ዓርብ፡የሚተላለፍ፥የአድማጮች፡የዘፈን፡ምርጫ፡አለ~እሱን፡እየፈለግሁኝ፡ነበር”፡ስትል፤እትዬ፥ኣፏን፡ በነጠላዋ፡ሸፍና፥በከፊል፡ሳቅ፡~

“ይሄንን፡ጉድ፡ትሰሙልኝ፡አላችሁ፡ዘመዶቼ!?”፡ብትልም፤ከአጠገብዋ፥ከ፡እኔ፡በቀር፥ሌላ፡ሰው፡አልነበረም። ወደ፡እልፍኙ፡ ዞራ፡~

“~ሕዝበ፡ክርስትያን፤በ፡ኪሪያላይሦን፡ምኅላ፡ይታመሳል፥አጅሪት፥ወይዘሪት፥የፈረንጆች፡ዘፈን፤በራዲዮ፡ታዳምጥልኝ፡ አለች!~እኔ፡ነኝ፡ጥፋተኛዋ፥አንቺ፡ምንም፡አላደረግሽም!~ባለቤቱ፥`የ፡እዚህች፡ልጅ፡ሁኔታ፡በጠበል፡የሚድን፡ዓይነት፡ አልመሰለኝም፥በግዜ፡ወደ፡ኣዲስ፡ኣበባ፡እንሸኛት`፡ሲለኝ~ከመጣች፡አይቀር፤ፍልሰታን፡አብራን፡ውላ፡ትመልስ፡ብዬ፣ደግ፡ የዋልኩልሽ፡መስሎኝ!”።

ከመኝታ፡ክፍሉ፡ሆኖ፥ጩኸቱን፡ሁሉ፡በመስኮቱ፡ሲኣደምጥ፡የነበረው፥ጋሼ፡`ተሞገሥ`፤በሚያመነታ፡የድምፅ፡ቃና፡~ ” ተኾላች፥ተያት፡እባክሽ!~፥አሁን፡ችግርዋ፤በውል፡ታውቋል~በቃ!~፥ሃገር፡በረድ፡ሲልለት፤በቶሎ፡እናሳፍራታለን፥ እስከዝያው፥እንደ፡ዓመልዋ፡መያዝ፡ነው~እኔንም፡ጸሎቴን፡አታስተጓጉሉኝ”፡ሲል፡አሳሰበ።

በታዘዘችው፡መሰረት፥`ሃዳስ`፥ከዋናው፡እልፍኝ፡አጠገብ፡በተዛነብ፡ከተቀየሰው፡ማደርያ፡ክፍሌ፡አስገብታኝ፡ሄደች፡እና፥እንደ፡ አኾረፈች፡ተመልሳ፡መጥታ፥አንከርፍፋ፡የያዘችውን፥ትሬ፡ከሰደቁ፡ላይ፡እያኖረችልኝ፡~”ኸጂ፥ናይ፡ፍልሰታ፡ፆም፡አለና”፡ብላኝ፡ ወጣች። የቀረበልኝን፥ጎመን፡እና፡ቀይ፡ምሥር፡ወጥ፥ከሁለት፡ጉርሻ፡በላይ፡መንካት፡አቃተኝ። ከጀርባዋ፡ተከትላት፡የገባችው፡ `ሎሚታ`፥ክፍሉ፡መሃል፡እንደቆመች፥ቁልቁል፡እየተመለከተችኝ፡~”ሞኝ፡አትሁን፥ይልቁኑ፥እራትህን፡ጥርቅም፡አድርገህ፡ ብትበላ፡ይሻልሃል፥~እነሱ፡እንደሆነ፥በትንሹም፣በትልቁም፡ሲበሳጩ፤ሰው፡ላይ፡ማጓራት፡ልማዳቸው፡ነው”፡አለች።

ንግግርዋ፡የሚያጽናና፡ባይሆንም፥በእዚህ፡ሁሉ፡ጭንቅ፡እና፡ትርምስ፡መሃል፥አንዲት፡ነቁጣ፡ፍርሃት፡ይሉት፡ድንጋጤ፡ አለማሳየትዋ፤እየቆየ፥ይብሱን፡ትገርመኝ፡ጀመር። ህፃን፡አይደለች፥በሃገር፡የሚካሄደው፡ሽብር፡አይገባትም፡አትባል፣ ~ኣክስታችን፡ስታለቅስ፣እነ፡ጋሽዬ፥ላይ፡ታች፡ሲራወጹ፤እየ፡አየቸው፡ነው~የእዚህች፡ፍጡር፤ነገርዋ፡ምን፡ይሆን?

የባልና፡ሚስቱ፡ንትርክ፥የቤቱን፡ሰራተኞች፥ከውጭው፡ረብሻ፡ይበልጥ፡እያሰቀቃችው፡እንደሆነ፡ያስታውቃል። ከመደንዘዝም፡ ይሁን፣ከመፍዘዝ፥ወይም፤በሌላ፡ምክንያት፡የተነሳ፡መሆኑ፡ባይለይም፥ሁሉንም፡ንቃ፣ርቃ፡የአለችው፡`ሎሚታ`፡ብቻ፡ነች።

`ኣቦይ~ገዝሙ`፡ጨለምለም፡ከአለው፡አትክልት፡ስፍራ፥ላይ፡ታች፡እየተንቆራጠጡ፡~” የ፡ዕንጀራዬ፡ነገር፡ሆነብኝ፡እና፥የ፡ ጌቶቹን፥የድሮ፡ውለታ፡አስቤ፡እንጂ፥~!እኔ፡`ገዝሙ~አማረ`፥ከ፡ምቹ፡ትድረቴ፤ከ፡`ብቸና`፡ተፈናቅዬ፥እዚህ፡ቁልቍል፡ምድር፤ መቼ፡እንዲህ፡እራበሽ፡ነበር~ዋ፡ዕህል~ውኃ!”~፡በማለት፡ሲዝቱ፥`ሃዳስ`፡እና፡እማማ፡`ጻዲቄ`፡ከማዕድ፡ቤት፡ሆነው፡እየ፡ አደመጡ፥ሲሳሳቁባቸው፡ይሰማኛል።

~*~

(ገጽ፡~)

`ሎሚታ`፥እተኛሁበት፣ቁልቁል፡አተኹራ፣ነድላ፡ተመልክታኝ፡ስታበቃ፥እንደ፡አመጣጥዋ፡ሁሉ፥ድንገት፤ተመልሳ፡ትታኝ፡ሄደች። ባል፡እና፡ሚስቱ፡የሚጨቃጨቁበት፡ነገር፥ከ፡ከተማው፡ረብሻ፤ተጨማሪ፤የቤት፡ውስጥ፡ጉዳይ፡እንዳለው፥አልፎ፡አልፎ፥ስርቅ፡ እየ፡አሉ፥ከዦሮዬ፡በሚደርሱት፡ቃላት፡ተረድቻለሁ፡~” የአንተው፡እናት፡ናቸው~`የልጅቱ፡ነገር፤ከቤት፡እየወጣ፡ነው~ሆድዋ፡ ውስጥ፡ይሰማኛል፡የምትለው፡ራዲዮ፥የሃገር፣የዕድር፡መሳቅያ፡አድርጎናል፥በግዜ፡የምታደርጉትን፡አድርጉ!~`ብለው~~”

ጋሼ፥`ተሞገሥ`፡የመረረው፡ይመስላል፡~”~አንቺ፡ሴት!~፥ኣፍ፡አለኝ፡ብለሽ፥ይሄንን፡ወሬ፥ከ፡እንግዳቸን፡ጌቶች፡ዦሮ፡ታደርሽ፡ እና፡ወዮልሽ!~የትዳርሽ፡ማብቃያው፡እንደሆነ፡እወቂያት!”።

በለቅሶ፡ሳግ፡እና፡ኅቅታ፡የተቀላቀለው፡ምላሽዋ፡ግን፡በጥራት፡አልሰማህ፡አለኝ። ተነዛንዘው፣ተነዛንዘው፥መለፋለፉ፡ደከማቸው፡ መሰለኝ፥ድንገት፡ሁለቱም፡ጸጥ፡አሉ።

ዕንቅልፍ~፡አልመጣልህ፡ብሎኝ፡እየተገላበጥኩኝ፥በመስኮት፡የሚገባውን፥የጨረቃ፡ብርሃን፡ጨረሮች፡ፍርግርግ፡ስቆጥር፣ግቢው፡

ጥጋት፡ላይ፡የታሰሩትን፡ሁለት፡ውሾች፥የተኹላ፡መሰል፥የሟርት፡ማላዘን፡ሳደምጥ፥~`ውስጥ፡ውስጡን፥ወደ፡እየሩሣሌም፡

ያደርሳል`፡የተባለውን፥`ሚካዔል~ዋሻ`፡የአሉትን፡ተዓምራዊ፡ስፍራ፥በዓይነ~ኅሊናዬ፡ለመሣል፡ስሞክር፥የክፍሉ፡በር፤ሲጢጥ፡

እንኳን፡ሳይል፣የሰው፡እግር፡ዳና፡ሳይሰማ፥እንዴት?፣በየት?፡እንደገባች፡ሳይታወቅ፥`ሎሚታ`፥ነጠላ፡እንደተከናነበች፡~”በል፡ና፡

ቶሎ”፡ብላ፡እጅዋን፡ዘርጋታ፤መዳፌን፡ይዛ፥ከአልጋው፡ውስጥ፡አወጣችኝ። በምን፡ፍጥነት፡ልብሴን፡እንደለበስኩኝ፡እና፡

እንደተጫማሁ፡ሳላውቀው፥ጤፍ፡በሚያስለቅመው፡ብሩኅ፡ጨረቃ፡ብርሃን፡እየተመራን፥በጓሮው፡አጥር፡በኩል፤አሾልካ፡ እየጎተተች፥ሽቅብ፡ይዛኝ፡ነጎደች።

” ወደ፡የት፡ነው፡የምትወስጅኝ ?~ለምንድን፡ነው፡እጄን፡የምትጎትችው ?”፡ለማለት፤ኣፌን፡ምን፡እንድለጎመብኝ፡አላውቅም። እናቱን፥ወደ፡ጸሎት፡ቤት፡እንደሚያጅብ፡ህፃን፥ዝም፡ብዬ፤ከጀርባዋ፡መከተል፡ብቻ፡ሆነ። ዘወር፡ብላ፤የመጣንበትን፡መንገድ፥ ወደ፡ኋላ፡ተመለከተች። እቺን፡ልጅ፥የውስጥ፡ልቤ፤በመልካም፡መንፈስ፡ባያስባት፡ኖሮ፥ገና፡ድሮውን፥ጥያት፥ የኋልዮሽ፡ፉዲዲ፡ለማለት፡አልመለስም፡ነበር። በመሃከላችን፥ፈጽሞ፡ንግግር፡የለም፥አልፎ፡አልፎ፡ብቻ፥እግሬ፡ድንጋይ፡ወይ፡ እንጨት፡ብጤ፡ነገር፡ሲያነቅፈኝ፡~”አይዞህ፡በርታ፣ደርሰናል”፡ትለኛለች።

ቅጥር፡ግቢውን፡እርቀን፡ሄደን፥ወርቻ፡ቀና፡መሰሉን፡ዳገት፡አልፈን፤ኾረብታውን፡ተወጣጥተን፡ስንጨርስ፥እጅግ፡ለሽ፣ለጥ፡የ፡አለ፤ ሰፊ፡ለምለም፡መስክ፤ከፊት፡ለፊታችን፡ፍንትው፡አለ። ቀኑን፤ከ፡እነ፡ጋሽዬ፡ጋር፥በመኪና፡ተጉዘን፡ስንመጣ፡የአልታየኝ፡ልምላሜ፥ የት፡ተደብቆ፡ቆይቶ፥አሁን፡ከወዴት፡እንደተከሰተ፤ሊረዳኝ፡አልቻለም። መዳፌን፡ለቀቅ፡አድርጋ፥በመዳፍዋ፡ዓይኖችዋን፡አጥልታ፡ እርቀቱን፡እየነፀረች፡~” አሁንስ፡ደርሰናል፣አይዞህ!”፡አለችኝ።

አልፈራሁም~አሁን፡ግን፥`አልደነገጥኩም`፡ማለት፥እራሴን፡መደለል፡ይሆንብኛል። እንዴት፡ቢሆን፡ግን፡~”እረ፡ምነው!?፣ እንዴት?!፣ለምን!?” የመሳሰሉ፤ተገቢ፡ጥያቄ፡እንዳላቀርብ፤ልሳኔን፡ምን፡ወሰደብኝ ?። ይሄም፡ሆኖ፥ትንግርታዊ፡ጉዞኣችን፡ በእዚህ፡አላበቃም። የ፡ሠማዩን፡ጠገግ፥ግጥም፡አድርገው፡የሸፈኑ፥ነጫጭ፡ኣሞሮች፤በኣናታችን፡ላይ፡አንዣብበው፡ሲያልፉ፥ቀና፡ብላ፡ተመልክታ፡~” ነጮቹ፡ቁራዎች፡ደረሱ፡ማለት፡ነው!”፡ብትል፥ይሄው፤ለልሳኔ፡መከፈቻ፡ምክንያት፡ሆነኝ፡ መሰለኝ፡~

” ነጭ፡ቁራ፤የሚባል፡ነገር፡አለ፡እንዴ?”፡ሲል፥የገዛ፡ድምጼን፡ሰማሁት። ዘወር፡ብላ፡ተመልክታኝ፥በ፡ኣዎንታ፥ጭንቅላትዋን፡ ብቻ፡ነቅንቃልኝ፤መዳፌን፡እንደገና፡ጨብጣ፥ቁልቁለቱን፡ይዛኝ፡ተንደረደረች።

`አክሱም`፥ከእርቀት፤በዓይነ፡ገባችን፡ስትከሰት፤አሁን፡ቅድም፤ትተናት፡የመጣነው፡ከተማ፡ሳትሆን፤የእሩቅ፡ምድር፣የጥንት፡ ሥልጣኔ፡ወጋጋን፡መስላ፡ታየችን።`ሎሚታ`፡ግን፥አንዳች፡የመገረምም፡ሆነ፤የስጋት፡መልክ፡አይታይባትም።ቆም፡አለች፡እና፡~

” ቁራዎቹ፡ካልጮሁ፤የተኛው፡ህዝብ፡እንደሆን፥እስከ፡ተነገ፡ወድያም፡አይነቃም!”፡አለች። ለሌላ፡ሰው፡የተናገረች፡መስሎኝ፤ ዙርያዬን፡ስቃኝ፡አስተውላ፥እንደ፡መሳቅ፡ሞከራት።በእዚሁ፡ሰዓት፤እስከ፡አሁን፤በጥድፍያ፡መንፈሴ፡የአላስተዋልኩትን፡ነገር፥ ድንገት፡ቀና፡ብዬ፡አሰብኩኝ፡~ከ፡ሠማይ፡ላይ፥ጨረቃይቱ፡አትታይም~ቷህ፡ብሎ፡የሚያበርው፡ብርሃንዋ፡እንጂ፥እርስዋ፥ ከጠፈሩ፡ኅዋህው፡የለችም። ሠማዩም፥ድሮ፡የማውቀው፣ከስሩ፡የኖርኩበት፡ሠማይ፡አልመስልህ፡አለኝ።

~*~

(ገጽ፡~)

ከኾረብታማው፡አድማስ፡ስር፥የሚንቀሳቀሱ፡ሾጣጣ፡ቅርጾች፡ብናይ፤ሁለታችንም፤እቆምንበት፡ተገትረን፥እርስ፡በርስ፡ተያየን። ቅርጾቹ፥ረዣዥም፥የህንፃ፡ፍራሾች፡ሲመስሉ፤ቅልጥፍናቸው፡ግን፡ይደንቃል።

እየቀረቡን፡በመጡ፡ቁጥር፤የኣክሱም፡ሃውሎቶች፡እንደሆኑ፡በጉልህ፡ለየ።

እንደ፡አመጣጣቸው፤ወደ፡እኛ፡ከመቅረብ፡ይልቅ፥ወደ፡ጎን፡አዘምብለው፥አድማሱን፡አሳብረው፥ጉዞአቸውን፤በረዥሙ፡ አተርትረው፡ቀጠሉ። `ሎሚታ`፤አንዳች፡ነገር፥በኣንስኅሥኆ፡ስታልጎመጉም፡ቆይታ፡~

” በትክክል፥አንድ~መቶ~አሥራ~አንድ፡ናቸው!”፡ስትል፡አረጋገጠች። ሀውልት፡ነፍስ፡ዘርቶ፡ሲንቀሳቀስ፥በህልሜም፣በሲኒማም፡ አይቼ፡አላውቅም~ይሄ፡ነገር፡ምንድን፡ነው?`እየ፡አልኩኝ፡ሳስብ፥የሆዴን፡ሰምታ፡መሆን፡አለበት፡~

” በህልምም፣በሲኒማ፡አይታዩም~በእንደ፡እዚህ፡የመሰለ፥ልዩ፡ዕውን፡ብቻ፡ነው፡የሚከሰቱት~እሱም፤ለሁሉም፡ሰው፡የታደለ፡ እንዳይመስልህ!~፥`አልፈራም`፡ብለኸኛል፥ቢሆንም፡አትደንግጥ~ኣባትህ፡ወይ፡ኣያትህ፡ጸሎተኛ፡መሆን፡አለባቸው~ዕድለኛ፡ነህ!~” የንግግርዋ፡ለመራቀቅ፡መሞከር፡አናደደኝ፡እና፡~ ” አልደነግጥም!~ይሄንን፡ጉድ፡ከ፡አዩ፡በኋላ፤ምን፡ድንጋጤ፡አለ!?”ሰው፡ የሚላት፣የሚናገራት፡ነገር፤ፈጽሞ፡ቀሚስዋን፡እንኳን፡የሚዳሥሣት፡አትመስልም። ዝግት፡አድርጋኝ፡መንገድዋን፡ቀጠለች። የምትሄድበትን፤አስቀድማ፣ጠንቅቃ፡የአወቀች፡በመሆንዋ፥አረማመድዋ፡ሳይቀር፤መሬቱን፡አጥብቆ፡የቆነጠጠ፡ነው።

እየደጋገመች፤አንጋጥጣ፡ሠማዩን፡ቃኝታ፡~” መቼ፡ይሆን፤የቁራዎቹ፡ጩኸት፡የሚሰማው?”~፡ስትል፤እራስዋን፡ጠየቀች። ብርታቱን፤ከወደየት፡እንዳገኘሁት፡ሳላውቅ፡~”አሁንስ፤ሊደክመኝ፡ነው፡መሰለኝ~ወደ፡የት፡እየወሰድሽኝ፡ነው!?”፡ስል፡ጠየቅኋት። እንደ፡ቁጣ፡በሚቃጣው፡ፊት፡ገላምጣኝ፡~”የአንተ፡ስራ፥ዝም፡ብለህ፤እኔን፡መከተል፡ብቻ፡ነው~ምን፡አስቸኮለህ፥ስንደርስበት፡ታየው፡የለ?!”።ስሜትዋ፥እንዴት፤በእየ፡ደቂቃው፡እንደሚቀያየር፡እየተገረምኩኝ፥በዝምታ፡መከተሌን፡ቀጠልኩ። የጨረቃው፡ብርሃን፡ብሩኅነት፡ሲደንቀኝ፥ከ፡ለምለሙ፡ኾረብታ፡ጀርባ፥የ፡ምሥር፡ክክ፡የመሰለ፥ብርሃን፡ፍንጥቅ፡አለ። ከሠማዩ፡ጸፈጸፍ፡ላይ፤የነጫጮቹ፡አሞራዎች፡ክንፍ፡ገጥሞ፥የመልክዓ~ምድር፡ቅርጽ፡አበጅቷል። የግዜ፡ሂደት፡ትብትቡ፤ከኣንጎሌ፡ቢዟዟርብኝ፡~”~እህ!~እንደመሸ፡ግድም፡አይደለም፡እንዴ፥ከቤት፡ይዘሽኝ፡የወጣሽው!~እንዴት፤ገና፡ከአሁኑ፡መሽቶ፡ሊነጋ፡ቻለ?!~ወይስ፤በእርቀት፥ችቦ፡የሚያበሩ፡ሰዎች፡አሉ?”፡ብላት፥ሽንጥዋን፡ገትራ፣ቆንጆ፡ፊትዋን፡አኮሳትራብኝ፤በሞጋች፡አንደበት፡~” ማዶ፡የሚታይህ፥የንጋት፡ብርኅን፡ነው፥የ፡አለህ፡ሰው፡ አለ?!”፡ስትል፡ተቆጣችኝ። ለሃገሩ፡እንግዳ፡ከመሆኔም፡በላይ፤አሁን፡የአለሁበትን፡ስፍራ፡አለማውቄ፥የቁም፡እስረኛዋ፡አደረገኝ፡ እንጂ፥ቦታዋን፡አስይዛት፡ነበር~ምን፡ይሆናል!።ደግሞ፥ስትቆጣ፥ድምፅዋ፡ስለሚቀየር፡አያምርባትም። መረግረጓን፡ቀጠለች፡~

~”ሀውልቶቹ፡ነፍስ፡ዘርተው፡ሲረማመዱ፥በዓይኖችህ፡እየ፡አየህ፥የአልደነቀህ፥የ፡ኣዲስ፡ኣበባ፡ጎረምሳ፥የ፡አዲስ፡ዓይነት፡ብርኅን፡ ከ፡እርቀት፡መታየት፡ገረመህ!~በ፡እርግጥ፡እንደ፡ነገርከኝ፥እድሜህ፡ኣሥራ፡ሥድስት፡ሞልቶሃል~ወይስ~?”።

የወትሮው፥ድፍረቴ፡እና፡ቅልጥፍናዬ፡ዘለስ፡እየ፡አለ፡ሲሄድ፡ታወቀኝ፡~” ምን፡ላድርግ፡ብለሽ፡ነው~ለሃገሩ፡እንግዳ፡ነኝ፣ የከተማችሁ፡ሕዝብ፥`ታቦተ~ጽዎንን፡ይዘን፤በዋሻ~ሚካዔል፡ውስጥ፡ለውስጥ፥ወደ፡እየሩሣሌም፡እንጓዛለን፡ብለው፡ተንስተዋል፡ ሲሉ፡ሰምተሻል~የቤታችሁ፡ሰዎችም፡እየተራበሹ፡እንደሆነ፥አንቺም፡እራስሽ፡አይተሽዋል~”፥ተንደርድራ፡መጥታ፥የ፡አተኮሰ፡ ግንባርዋን፤ግንባሬን፡አስነክታ፡~” ብሰማስ፡ታድያ!?~ምን፡ይጠበስ!?~የሰማችሁትን፡ሁሉ፡እመኑ፤የሚል፡ትእዛዝ፡ከየትኛው፡ ደብር፡ነው፡የተላለፈው!?”

” እሺ፤እሱስ፡ይሁንልሽ~አሁን፡ቅድም፤በዓይናችን፡የአየናቸው፡የሚረማምዱት፡ሃውልቶችስ፡ፍቺው፡ምንድን፡ነው?”

እርሷው፤ታላቄ፡የሆነች፡ይመስል፥አገጬን፡በመዳፍዋ፡ሽቅብ፡ቀና፡አድርጋ፤በፉተታ፡አነጋገር፡~” ወይ፡ምስኪኑ፡ወንድሜ፥ ከእናንተ፡ትምህርት፡ቤት፥`ቦጋና፡እና፡ቆንጮራው`~`ማሞ፡ቂሎ`~የትንቢት፡ቀጠሮ`~፡በስተቀር፥ሌላ፡ነገር፡አላስተማሯችሁም፡ ማለት፡ነው?”

” የእኔን፡እድሜ፡ትጠይቂ፡አለሽ፡እንጂ፥ጨቅላውስ፡አንቺው፡ነሽ!~ሰውነትሽን፡ሲመለከቱሽ፡ግን፥የበሰለች፡ሴት፡ትመስያለሽ” ዘልላ፥እላዬ፡ላይ፡ክምር፡ብላ፡~ኧ!~ምን፡አልክ!?~ሰውነቴን፡ደግሞ፡ምን፡ግዜ፡ነው፡የአስተዋልከው?!”፡ስትል፥ቡግ፣ቱግ፡አለችብኝ።

” ምን፡ማስተዋል፡ያሻዋል፥በግልጽ፡የሚታይ፡ነው”~ስላት፥ጡቶችዋን፡በመዳፎችዋ፡እንደ፡መከለል፡እየ፡አለች፡~

” ~ወየው፡ጉድ!~ምን፡የአለው፡ፍጡር፡ነው፥እንግዳ፡መስሎ፡የመጣብን፡በሉ!?~በል፥አሁን፡ጸጥ፡ብለህ፡ ተከተለኝ~አለበለዝያ~ዋ!”:

ፊት፡እና፡ኋላው፡የማይታወቅ፡ጉዞ፡ውስጥ፡ገብቼ፥በእላዩ፤ከእዚህች፡ቆንጅዬ፡ወፈፌ፡ጋር፡መነታረኩን፡አልፈልግሁም። የሚሆነው፡ሆኖ፡እስኪለይለት፡ድረስ፥በዝምታ፡እየተከተልኳት፥መንገዳችንን፡ቀጠልን።

~*~

(ገጽ፡~)

ሁለተኛውን፡ኾረብታ፡አሻቅበን፤እንደተወጣን፥ከስራችን፤እችም፡የአለ፡ቁጥቋጦ፡የለበሰ፤ሰፊ፡ጋሻ፡መሬት፤ተዘርግቶ፡ገጠመን፡~

” እግርህ፡በተንሳፈፍ፡ቢሆንም፥አልፈህ፡አልፈህ፤ምድሪቱን፡መንካትህ፡አይቀርም፡እና፡እየተጠነቀቅሕ፥የምታየው፡ብሩህ፡ ቁጥቋጦ፡በሙሉ፥ጌታ፡በነደ~እሳት፡ለሙሴ፡የተገለጠበት፥`ዕፀ~ጳጦሥ`፡ነው። አንዲትዋን፡ቅጠል፤በሥህተት፡እንኳን፡ ብትበጥስ፥`እርርሪ`፡ብላ፡ነው፡የምትጮኸው፥ይሄንን፡ዕወቅ!”:ስትል፤በጥብቅ፡አስጠነቀቀችኝ።

የገዛ፡እራስዋ፡አረማመድ፡ግን፥ልክ፥ኣሜኬላን፡ከምድር፡እንዳትረግጥ፥የምትጠነቀቅ፡ዓይነት፡ነበር። የ፡እግሮቼን፡ከምድር፡ከፍ፡ ብሎ፡መንሳፈፍ፡መጀመር፤እንዴት፡እንደምጠይቃት፡ሳውጠነጥን፤እርስዋው፤ቀድማ፡በመጥቀስዋ፡ተበራትቼ፡~

” ከ፡ቅድም፡ጀምሬ፥እጅግ፡የተጨነቅሁበትን፡ነገር፥አንቺው፡ማንሳትሽ፥ኧረ፥እግዜር፡ይስጥሽ!~ታድያ፡ለምድን፡ነው፥እግሬ፡ ከመሬት፡ከፍ፡ብሎ፡እየተንሳፈፈ፡የምንጕዘው?~የአንቺው፡እንደሚታየኝ፤ምድሪቱን፡አጥብቆ፡የተረገጠ፡ነው?”

መኮሳተር፡ሲፈልጋት፡እንደምትሆነው፥ቆም፡አለች፡እና፥ማዶ፡ማዶውን፡እያስተዋለች፡~” ከ፡እናንተው፡ትምህርት፡ቤት፥ታሪክን፥ በከፊል፡ድብብቆሽ፡ነው፡የሚያስተምሯችሁ፡መሰለኝ~ `ኸብረ~ነገሥት`፡ሲባል፡ሰምተሃል?፥የታቦተ~ጽዎን፤ወደ፡ኢትዮጵያ፡የመጣበት፡ገድል፡መጽሐፍ?~ሁለት፡መቶ፡ሃያ፡ኣምሥት፡ ነገሥትን፥ዳዊት፡ዙፋን፡ላይ፡የአስቀመጠ፡መጽሐፍ?”

” አላየሁትም፡እንጂ፥ሲባል፡ግን፡ሰምቻለሁ”፡በማለት፤ሳልግደረደር፥የዕውነቱን፡አውጥቼ፡ነገርኳት። በማስተዋል፥ዙርያዬን፡ አተኩራ፡እየ፡አየችኝ፡~” እዛ፡ውስጥ፡ተጽፎልሃል~ታቦቱን፤ከምድር፡ከፍ፣ከሠማይ፡ዝቅ፡አድርገው፡ተሸክመውት፡ነው፡ የአመጡልን።”

“ታድያ፤ለምን፡እኔ፡ብቻ፡እንሳፈፋፍ፡አለሁ፥አንቺ፤የብስ፡ላይ፡እየተረማመድሽ?”

” አንተ፡ልጅ~ይሄ፥ከእኔ፡ጋር፡ኣጉል፡መፎካከር፡ይቅርብህ፡አላልኩህም!?~አንተን፡ምን፡ገደደህ፥እኔን፡እንደ፡አሻኝ፡ብጕዝ፥ ይልቁኑ፤ከስርህ፡የሚንቦገቦገውን፡ቅጠል፡ተጠንቀቅ~ከፊሉ፡~`ዕፀ፡ዘዌ፣ከፊሉ፡`ዕፀ፡ሕይወት፣ከፊሉ፡~`ዕፀ፡ገነት`፡ ናቸው~የሁሉንም፡ሥም፡ጠቅሼልህ፡አልዘልቅም፥ደግሞ፥በስሕተት፥ዘውገድ፡ብለህ፥ገነት፡እንዳትገባብኝ። በስሕተት፡ የሚፈጸመው፡የጅል፡ስራ፡ብዙ፡ነው~የማታውቀውን፡ቅጠል፡ተረግጠህ፤በኋላ፥እግርህ፡ወደ፡ሠማይ፣እጆችህ፤ከምድር፡ ተገላብጠህ፥በመዳፍህ፤ወደ፡ቤት፡እንዳትመለስ፡እና፤እኔን፡እንዳታስወቅሰኝ!” አለች።

ተገላብጬ፥በእጆቼ፡ስረማመድ፡ታየኝ፡እና፤ሳቄ፡እንደመምጣት፡አለብኝ።

የ፡እርቀቱ፤ቀይ፡ውጋጋን፡ኣድማስ፥በቀረብነው፡ቁጥር፤ይብሱን፡እየበራ፡እንጂ፥እየቀረበን፡አይመጣም። በአለህበት፡ተራመድ፡ነው፡ እንዳልል፤የምትራመደው፡እርስዋ፡እንጂ፥የእኔማ፡ዕጣ፡ፈንታ፤መንሳፈፍ፡ከሆነ፡ቆይቷል። ልጠይቃት፡ቃጣሁ፡እና፤ደግሞ፡የባሰ፥ ጭንቅላትን፡የሚያዞር፤ስውርውር፡ታሪክ፡ታሰማኛለች፡ብዬ፡ተውኩት።

የሚያብረቀርቁ፡ኅመሚል፡ዕፅዋቱ፡የአለበሱትን፥የተንጣለለ፡ጋሻ፡መስክ፡እንደ፡ጨረስን፥በረድፍ፡ተሰድረው፡የሚታዩ፤ከቋጥኝ፡ ፈለፈል፡ውስጥ፡የሚንቆረቆሩ፥ጥሉል፡ምንጮች፡አጠገብ፡ደረስን። የፏፏቴው፡ውኃ፤ከስሩ፡ክትር፡ኩሬ፡ላይ፡ሲንፎለፎል፡ግን፥ አንዳች፡ድምፅ፡የለውም። ደረታቸው፡ብጫ፡ኣረንጕዴ፡ቀለም፡ሽልም፤ድምቢጥ፡ወፎች፡ትርር፡ብለው፡እየመጡ፤በትንስዬ፡ቀይ፡ መንቆራቸው፡ቀስመው፤ብርር፡ይላሉ።ይሄንን፡ልታሳየኝ፡ይሆን፥ከተኛሁበት፡ጎትታ፡የአመጣችኝ፡እያልኩኝ፤ቆሜ፡ስታዘብ፡~

” ምን፡ይገትርሃል !?~ከመጣህበት፡ሃገር፥የውኃ፡ምንጭ፡አይተህ፡አታውቅም?!”፡ስትል፡አሾፈችብኝ። ለ፡ፍላፃ፡ውግ፡ ንግግርዋ፥ተገቢውን፡አጠፌታ፡መልስ፡መስጠት፡አቁሜአለሁ። ባተት፡ብዬ፡እየተከተልኳት፡~”ምንጩ፡ሳይሆን፥ውኃው፡ቁልቁል፡ሲፈሥሥ:ድምፅ፡አለማሰማቱ፡ገርሞኝ፡እንጂ!”

” አትገረም~ገና፡ብዙ፡ተኣምር፡ታያለህ፥በቁጥር፡ሃምሣ፡ናቸው፥በጥንቱ፡ሳባዊ፡ቋንቋ፥`ኣኽ`፡ይሰኛሉ። ምናልባት፤ብትገርልኝ፥ በጽሞና፡የመውደድ፤ሠናይ፡አንደበት፡እስኪ፡ልቅረባት፡ብዬ፡~

” ~እኔ፡የምለው፡ግን፡`ሎሚታዬ`፥ኣንቺ፡ይሄንን፡ሁሉ፡ምን፡ግዜ፡ነው፡የተማርሽው፥ገና፡የ፡`ናዝሬት~ስኩል`፡አሥረኛ፡ክፍል፡ ተማሪ፡ነኝ፥የአልሽኝ፡መስሎኝ?”። አረማመድዋን፡ፈጠን፣ፈጠን፡እየ፡አደረገች፡~

” ከሞጋችነትህ፡ይብስ፤የጥያቄዎችህ፡ብዛት~በ፡እዚሁ፡ነገረኛነትህ፡ከገፋህበት፥ስታድግ፥ጥሩ፡ጠበቃ፡ሳይወጣህ፡ አይቀርም!~ለቅስና፡እንኳን፥ጥቂት፡ኣደብ፡ይጎድልሃል~ለማንኛቸውም፥ቅድም፥`መቼ፡ነው፡ይሄንን፡ሁሉ፡የተማርሽው?`፥ብለህ፡ ለጠየቅኸኝ~እ~እናቴ፡ማኅፀን፡ውስጥ፡እየ፡አለሁ፥ሀኪሞቹ፡በማዳመጫቸው፡ሆድዋን፡ሲዳስሱ፥እንደምሰማቸው፡ስለ፡አወቁ፥ ይህች፡ልጅ፡ስትወለድ፥ጥሩ፡ተማሪ፡ሳይወጣት፡አይቀርም፤ብለው፥ዘጠኝ፡ወር፡ተኩል፡ሙሉ፥ታሪክ፣ሥነ~ልቡና፣ ምስጢረ~ዕፅዋት፡እና፡ቀልደኛነትን፡አስተማሩኝ።~`ምነው፤ባሕላዊውን፡ቅኔ፣ዜማ፡እና፡ግሡን፡ለምን፡ነፈጋችሁኝ?`፡ብል፥ “እሱን፤ከተወለድሽ፡በኋላ፡እንደ፡ብቃትሽ፡ታይቶ፥ትምህርት፡የማያግርሽ፡ሴት፡ከሆንሽ፥`የ፡`ዋድላ፡ደላንታ`፣`የጎንጅ፡`የዋሸራ`፡ የሚባሉ፡የቅኔ፡ትምህርት፡ቤቶች፡አሉ፤ወደ፡እዝያ፡እንልክሽ፡አለን`፥አሉኝ፡እልሃለሁ~ከረዥሙ፡በአጭሩ፡ይኸው፡ነው!”

ምነው፥እግሬ፤ምድር፡በነካችልኝ፡እና፥አንድ፡ስፍራ፡ትንሽ፡አረፍ፡ብዬ፤ሳቄን፡በተወጣሁት፥ብዬ፡ተመኘሁ። ወይዘሪት፡ግን፥እኔን፡ በቀለድ፡ማጃጃልዋን፡ጨርሳ፤ገና፡ድሮ፥ሃሳብዋ፤ማዶ፡ተሻግሮ፥የርኁቁን፡ሁኔታ፡እየመረመረ፥የሚያምር፡የቀይ፡ዳማ፡ግንባርዋን፡ ቅጭም፡አድርጋለች። ከ፡አሁን፡አሁን፡~`ይህች፡ጉድ፥ደግሞ፡ምን፡ታሰማኝ፡ይሆን?፣`የት፡ልትወስደኝ፡ይሆን?፡ብዬ፥ጉጉቴን፡ ሳልጨርስ፥~ከሠማይ፡ሲወርድ፡የአላየነው፣ከምድር፡ሲፈልቅ፡የአልተመለከትነው፥ግዙፍ፥ሠማይ፡ጠቀስ፡ቁመት፣ከ፡ቢጫ፡ ዕብነ~በረድ፡የታነፀ፡ህንፃ፤ከፊት፡ለፊታችን፥እንደ፡የደመና፡ዓምድ፡ግድግድ፡ብሎ፡አገኘነው። ጉልላቱ፤በሚያብረቀርቅ፥የወርቅ፡ እና፡የብር፣የከበሩ፡ደንግያ፡ትርስት፡ኣሻኩራ፡እና፡ምሥለ፡ኮከብ፡ቅርጽ፡እና፡መሥቀል፡ተሞግሧል። ዘወር፡ብል፥`ሎሚታ`፡ ከመሬት፡ተደፍታ፡~

” ቅድሥት፡ወ፡ብፅዕት~፣ስብህት፤ወ፡ቡርክት፣~ክብርት፡ወ፡ልዕልት፡~አንቀጸ፡ብርኅን፣~መዐርገ፡ሕይወት፣~ወ፡ማኅደረ፡ መለኮት፣~ቅድስተ፡ቅዱሣን፡አንቲ፡ውእቱ!!~`፡ከማለትዋ፥ቀድሞውን፡የአልታዩን፡ሠባት፡የገነት፡አእዋፍ፡እና፤ባዘቶ፡ደመና፡ ሲወርዱ፡ከመሃላቸው፥እንደ፡ሄለል፡ፀሃይ፡ተፈልቅቃ፣እንደ፡ጨረቃ፡ደምቃ፥የምትታይ፡ፍጡር፥ከ፡ህንፃው፡መቅደላ፡ላይ፡ ተከሰተች። የ፡`ሎሚታ`፡የ፡አንስኅሥኆ፡ጸሎትም፡ቀጠለ፡~`የዝሆን፡ጥርስ፡ግንብ፣የኅዙናን፡ሁሉ፡ናዛዥ፣የኅጥኣን፡መማጠኛ~~`

~*~

(ገጽ፡~፲)

ከሥግደትዋ፡ቀና፡ስትል፥ገጽዋ፥ከመግደላው፡ላይ፡በሚወርደው፡ብርኅን፡ጨረር፡ተጥለቅልቆ፤እርስዋም፤እንደ፡ጨረቃ፡ታበራ፡ ጀመር። ከሠማዩ፡ላይ፡ጨረቃይቱ፡አትታይም፣ምድሪቱን፡የአለበሳት፡ብርሃን፡ግን፥የሰምበሌጥን፡ጥላ፡ሳይቀር፡ያሳያል~ እስከ፡አሁን፥ብርኅንዋን፡እንጂ፥ከሠማይ፡ገኒኃትዋን፡የአላየናት፡ጨረቃ፥ለካስ፥እዚህ፡ውስጥ፥በኅቡዕ፡ተከልላ፡ነበር፤ማለት፡ነው`ስል፡አሰብኩኝ። ከ፡ብጫው፡ዕብነ~በረድ፡ህንፅ፡ላይ፤በ፡ዓምደ፡ደመና፡እና፤በገነት፡አእዋፍ፡የተከበበችውን፡ለባሲተ~ፀሃይ፤በሙሉ፡ዓይናችን፡ማየት፡አልቻልንም። `ሎሚታ`፡ወደ፡እኔ፡ዘወር፡በማለት፡~” የዛሬይቱን፡ዕለት፡ብቻ፡እንዳትረሳ !” ስትል፥አጥብቃ፡አሳሰበችኝ።

ፍርሃት፡እና፡ድንጋጤ፥መንፈስን፡ሲወርሱ፥ሃሳብን፥ከመረበሽ፡ይልቅ፡ያሰሉት፡ይመስል፡~`ይሄንን፡ዕብነ~በረድ፡አትንኩብኝ፤ብለው፡መሆን፡አለበት፥ካህናቱ፥`በዋሻ፡ለዋሻ፤ወደ፡እየሩሣሌም፡እንሄድ፡አለን`፥ብለው፡የተነሱት፤ማለት፡ነው`፡እያልኩኝ፤በሆዴ ፡ሳልጎመጉም፥`ሎሚታ`፡መዳፌን፡ይዛ፥የ፡ዕበነ~በረዱን፡ህንፃ፡ዓውደ፡ምኅረት፡ታዞረኝ፡ጀመር።

“ዋ!~እንዲህ፡ብለህ~ቀና፡ብዬ፤በሙሉ፡ዓይኖቼ፡አያታለሁ፡ብለህ፡ትንጠራራ፡እና~ወዮልህ!፥ንስኅ፡ሳትገባ፥የሰራኸው፡ኅጢዓት፡ በሙሉ፡ድንገት፡ነው፡የሚገነፍልብህ!”፡ስትል፡አስፈራራችኝ። በእዚህን፡መሰል፥ነፍስን፡አስደንጋጭ፡ሁኔታ፡ውስጥ፡እንኳን፡ሆነንም፥ውረፋዋ፡አለመብረዱ፡አናደደኝ፡እና፡~”እኔ፡ምንም፡የሰራሁት፡ኅጢአት፡የለኝም~እናቴ፡ሆድ፡ውስጥ፡ሆኜ፡ነው፡የተማርኩት፡የምትይውን፡ሁሉ፥እኔ፡ላይ፡አትለማመጅብኝ!~እሺ፡የእኔ፡ እህት!?”፡በማለት፡ጮህኩባት። ቆም፡በማለት፥ለምስኪን፡ፍጡር፡በሚሰነዘር፤የኅዘኔታ፡አተያይ፥በጎን፡አወራርዳኝ፥በረጋ፡አነጋገር፡~

“አንተ፡የከተማ፡ልጅ~`ከ፡እኔ፡ጋር፤ኣጉል፡ክርክር፡ይቅርብህ`፡አላልኩህም!?~በል፡አሁን፡መዳፌን፡ብቻ፡አንዳትለቅቅ”፡ብላኝ፥ዙርያ፡ዑደታችንን፡ቀጠልን። ከ፡ኣጸደ~ግቢው፤አንዳች፡የሰው፡ፍጡር፡አለመታየቱ፤እጅጉን፡አሳሰበኝ። የልቡና፡ጸሎትዋን፤በ፡ድንገት፡አቋርጣ፡~” `ምዕመናኑ፡፤ወደ፡የት፡ናቸው?*`፤የሚል፡ጥያቄ፡ብቻ፡እንዳታነሳብኝ~እሺ?”፡ስትል፡አሳሰበችኝ። እርስዋም፡ባትለኝ፥ጥያቄ፡ለማቅረብ፡የሚበቃ፥የሰከነ፡አንጎል፡አልነበረኝም፡እና፤በዝምታ፡አሳለፍኩት።

የሕንፃው፡መግብያ፥ኣንቀጸ፡ደጃፍ፥በሁለት፡ታላላቅ፡የምሠሦ፡ዓምዶች፡የተጠበቀ፡ሲሆን፥ክፍት፡ይሁን፡ዝግ፡የማያስለይ፡የ፡ብርኃን፡ጸዳል፡ይታያል። ወደ፡ታችኛው፡ደጃፍ፡መስክ፡ የሚያደርሱ፥ከ፡እዝያው፡ኣይነት፥ወይባማ፡ዕብነ~በረድ፡የተገነባ፥ሠማንያ፡ኣንድ፡ደረጃ፡ቆጠርኩኝ።

እንደገና፥ጸሎተ፡ልቡናዋን፡ቆርጣ፥ዘወር፡ብላ፡ተመልክታኝ፡~ ” አሁን፤የደረጃ፡እርከን፤የመቁጠርያ፡ሰኣት፡አይደለም~ዋ~አንተ፡ሰው!” አለች። መልስ፡አልሰጠኋትም። ወደ፡ኣንቀጸ፡ደጃፉ፡ስንቃረብ፥ከውስጥ፡~”ዲው!~ድልቅ!~ዲው!፡ድልቅ!”፡የሚል፡ከበሮ፡ተሰማ። ቅዳሴው፡ከውስጥ፡እየተካሄደ፡መሆኑን፥ሁለታችንም፥ተረዳን። ከሠማዩ፡ጸፈጸፍ፥የ፡መልክዓ~ምድር፡ቅርጽ፡ሰርተው፥ዙርያ፡ሲሽከረከሩ፡የነበሩት፥ነጫጭ፡ቁራዎች፥ወደ፡ታች፡ዝቅ፡እየ፡አሉ፡ ረብበው፣ከ፡ቀደሙት፡የገነት፡ወፎች፡ጋር፥ህብር፡ፈጥረው፥በባዘቶ፡ኅምራዊ፡ቀለም፡ደመና፡ብርኃን፡የተከበበችውን፡ክስተት፡እየ ፡አጀቡ፥ይዘዋት፥ሽቅብ፡ማረግ፡ሲጀምሩ፥ከወደየት፡እንደፈለቀ፡የአላየነው፥ዕጣን፡ቡልቅ፡ቡልቅ፡እየ፡አለ፥ዙርያ፡ቅጥሩን፡እንደ፡ ጉም፡ሸፍኖ፡ሲያውደው፡ቆይቶ፥በ፡ገነት፡ወፎች፡እና፡በ፡ኅምራዊ፡ባዘቶ፡ደመና፡የታጀበችው፡ክስተት፤ከዓይናችን፡ስትርቅ፥ዕጣኑም፡ተመልሶ፥በሻኹራው፡እግርጌ፥ወደ፡ህንፃው፡ሲከተት፥ከውስጥ፡የሚሰማው፥የከበሮው፥”ዲው!~ድልቅ!~ዲው!፡ድልቅ!”፡ቀጠለ።

ነቃሁ፡እንዳልል፥ተኝቼ፡አልነበረም፣ባነንኩኝ፡እንዳልል፥ህልምም፣ቅዠትም፡አላየሁም~እንዲሁ፥በ፡መጠርያ፡ሥም-የለሽ፡መንፈስ፡እንደታፈስኩኝ፥ወደ፡የመጣንበት፡አግጣጫ፡ተመልሰን፥የቀድሞዎቹን፡ኮረብታዎች፡ስንወጣጣ፥ነፍስ፡ዘርቼ፤እራሴን፡አወቅሁኝ። የ፡አሁኑ፡አረማመዴ፡ግን፥ምድሪቱን፡የተረገጠ፣ሳር፡ቅጠሉን፡የቆነጠጠ፡መሆኑ፡ታውቆኛል። ጎንበስ፡ብዬ፡እግሬን፡ በማየትም፡አረጋግጥኩኝ። የሠርዶው፡ሳር፡ልምላሜ፡እና፡ላዛ፥የበቆሎ፡ጸጉር፡ኅር፡አይነት፡ነው።

በዓይነ-ገብ፡የሚታይ፡ፍጥረት፥~ኅመልማል፡ዕጽዋት፡እና፡ምስር፡ክክ፡ቀለም፡የተኾላው፡ሠማይ፡ብቻ፡ናቸው። ቀድሞ፡ድምፅ፡የአልነበራቸው፡የውኃ፡ምንጮች፡ፏፏቴ፥ከእርቀት፡ሲንሿሿ፡ተሰማን።`ሎሚታ`፡አሁንም፤ጸሎተ~ልቡናዋን፤ በኣንስኅሥኆ፡ስትጸልይ፥ነፋስ፤ስርቅ፡እየ፡አደረገ፥አንድ፡አንዱን፡ቃላት፡እና፡ሐረግ፡ከዦሮዬ፡ያደርሳል፡~

“~~ሠማያት፡ይነግራ፥ስብኅተ፡እግዚኣ፡ብሔር~ወ፡ግብረ፡እደዊሁ፥ያየድኣ፡ሠማያተ~~~~”

~*~

(ገጽ፡~፲፩)

ቅጥር፡ግቢው፥ልክ፥ትተነው፡ስንወጣ፡እንደነበረው፥ክችች፡ብሎ፡ነው፡የጠበቀን። የንጋት፡ብርሃን፡እየሠረቀ፡ቢሆንም፥የቤተኛው፡እንቅስቃሴ፡አይታይም።`ሎሚታ`፥ይሄንን፡አስቀድማ፡አሳምራ፡የአወቀችው፡ይአክል፥በጓሮው፡በር፡አሾልካ፡ስታስገባኝ፥ጥንቃቄም፣ስጋትም፡አልነበራትም። ገርበብ፡እንደ፡አለ፡የተውነውን፥የመኝታ፡ክፍሌን፡በር፤በትከሻዋ፡ገፋ፡አድርጋ፡አስገብታኝ፥እንደ፡ቀድሞው ሁኔታዋ፤የኋልዮሽ፡እየአፈገፈገች፡ወጣች።

ስነቃ፥የመላው፡ሰውነቴ፡መጓጎል፡እና፤ዝለት፡ሲሰማኝ፡ነው፥ምን፡ዓይነት፡ድብን፡የአለ፡ዕንቅልፍ፡እንደተኛሁ፡የታወቀኝ። ቤተኛው፡ነቅቷል፣የዶሮዎቹ፡ቋቋታ፡እና፤የሳፋ፡መንጓጓት፥ከ፡ወደ፡ጓሮው፡ይሰማል።

እትዬ፥`ተኮላች`፡~” ማነሽ፡አንቺ~እ~`ሃዳስ`!~ኧረ፡እባክሽ፥እንግዳውን፡ልጅ፡ሂጂ፡እና፡እይልኝ~በደህናው፡ነው፥እስከ፡ቀትር፡ድረስ፡መተኛቱ!?”፡ከማለትዋ፥`ሃዳስ`፡በሩን፤ በቀስታ፡ገፋ፡አድርጋ፤አንገትዋን፡አስግጋ፡ተመልክታኝ፡~” ብ፡ደኅን፡አሎ፡ይመስለኒ~”፡ስትል፡ሰማኋት።

“~አይይ፥እንግድያውስ፥መረበሹ፡እና፡ድንጋጤው፡አዳክሞት፡ቢሆን፡ነው!~መውጣት፡ከ፡አልፈለገ፥ቁርሱን፡እዝያው፡አድርሽለት”፡አለቻት። ከ፡ኣክስቴ፥`ተኾላችም፡ነገር፡እና፤ ከድካሜም፡ይልቅ፥ሌሊቱን፤የአየሁትን፡እና፡የሆንኩትን፡ሁሉ፥በነቃ፡ኅሊና፡ለመረዳት፥መቼ፥`ሎሚታን፡አግኝቼ፡አነጋግሬአት፤የሚል፥የልብ፡ትርታ፣የኣንጎል፡ንዝረት፡እና፡የኣእምሮ፡ስጋት፥ ጥምርምር፡ስሜቶች፡ነበሩ፡የወጠሩኝ።

`ሃዳስ`፥ሻይ፡በብርጭቆ፡እና፡ኣምባሻ፡በእርቦ፡ይዛልኝ፡እንደገባች፥በእዝያው፡እግር፡ተከትሎ፥የቅጥሩ፡ቆርቆሮ፡በር፡ተንኳኩቶ፥ሁለቱ፡መኪናዎች፡ተከታትለው፡ሲገቡ፡ተሰማ።

በጥድፍያ፡ተነስቼ፤ልብሴን፡አጠላልቄ፤ወደ፡አትክልት፡ስፍራው፡ቧንቧ፡ሄጄ፡ፊቴን፣ክንዴን፡ተጣጠብኩኝ።ጋሽዬ፥አርፍጄ፡መነሳቴን፡አውቆ፥ምናልባት፤በጥያቄ፡ቢይዘኝ፥ምን፡የምለው፡ነገር፡አለኝ!?~እርሱ፡ለእራሱ፥መንፈሱ፥ከመናወዙ፤ብዛት፥አንዳቸውንም፤የግቢውን፡ሰው፡ለማነጋገርም፡ፋታ፡አይታይበትም። የቀረበለትን፡ቀዝቃዛ፡`መሎቲ`፡ቢራ፤ፉት፡እየ፡አለ፥ከ፡ቆዳ፡ኣኹፋዳው፡ ውስጥ፡የአወጣውን፡የወረቀት፡ሰነድ፥ደጋግሞ፡እየአገላበጠ፥ጭንቅላቱን፡ይነቀንቃል። `ኮሮኔሉ`ም፥ወደ፡ጋሼ፡`ተሞገሥ`፡መኝታ፡ክፍል፡ገብተው፥በዝግታ፡ሲያጉተመትሙ፡ይሰማል።

እትዬ፡ብቻ፡ነች፥ጭንቀቷን፡ለመደበቅ፡የማትሞክረው፥ከ፡እልፍኙ፤ወደ፡ሰራተኞቹ፡መደዳ፡ቤት፡በገባች፣በወጣች፡ቁጥር፥ከ፡ፊትዋ፡የገጠማት፡ሰው፡ላይ፤ብስጭትዋን፡በመወጣት፡ ~” `ኣቦይ~ገዝሙ`!~ለምን፡አንደኛውን፥የመኝታ፡ኬሻዎን፤ወደ፡ደጅ፡አውጥተው፡አይተኙበትም!?~፥ግቢውን፡ጥበቃ፡እንደሆን፡ትተውታል!”~~

“~`ሃዳስ`~አንቺም፡ትተሽን፥ወደ፥ጸሎተ፡ምህላው፡ሄደሻል~ወይስ፡አለሽ!?”፡ትላለች።

ጋሽዬ፤ግቢው፡አትክልት፡ስፍራ፡እየተንቆራጠጠ፤በኣናት፡በኣናቱ፥ሲጃራውን፡ይለኩሳል። ቀርቦ፡የሚያነጋግረው፡ሰው፡እንኳን፡አልተገኘም። ከወደ፡ብፁዕነታቸው፥`ንቡረ~ዕዱ`፡ሰፈር፥ ነገሩ፡እጅግ፡እየተካረረ፡ቢሆን፡ነው፤ስል፡ገመትኩኝ። የ፡`ሎሚታ`ስ፡ድምፅ፥ምነው፤ከቅጥር፡ግቢውም፣ከቤቱም፥ጭርሱን፡አልሰማ፡አለ*~በድህና፡ነው። ነገር፡ሁሉ፥በ፡ስውር፡የሚጎናጎን፡መሰለኝ።

`ኮሮኔል`፡እና፡ጋሼ፡`ተሞገሥ`፥ወደ፡ቬረንዳው፡ወጥተው፥የቀረበላቸውን፡ቡና፡ፉት፡እየ፡አሉ፥በትካዜ፡ዝምታ፥ዳቦ፡ቆሎውን፡ሲቆረጥሙ፥ከ፡አትክልቱ፡ስፍራ፡ሆኜ፤በ፡እርቀት፡ይታዩኛል። ሁሉም፡ሰው፥በእየ፡ነፍስያው፡ጭንቅ፡ተጠምዶ፡እየተንከላወሰ፡መሆኑም፡ግልጽ፡ነው።`ሎሚታ`፡ግን፡ወደ፡የት፡ገባች?።

ለዶሮዎቹ፡ዕህል፡ለመበተን፤ወደ፡ደጁ፡የመጡትን፥እማማ፡`ጻዲቄን`፥ለመጠየቅ፡አጋጣሚ፡ረዳኝ፡እና፥ጠጋ፡ብዬ፡~”`ሎሚታ`፡ወደ፡የት፡ሄደች፡እማማ፡`ጻዲቄ`?”፡ብላቸው፥በጎን፡ አሾልቀው፡እልፍኙን፡ቃኝተው፥ወደ፡ጓሮ፡ዘወር፡እንድል፤በ፡እጃቸው፡አመላከቱኝ፡እና፡አጠገባቸው፡ስደርስ፥ወላቃ፡ጥርሳቸውን፤በነጠላቸው፡ጥለት፡እየከለሉ፡~” ልጅቱን~ከክፍልዋ፡እንዳትወጣ፡አድርገዋታል~`ከ፡ዕምብርቴ፡በላይ፡ራድዮን፥ይሰማኛል`~፡የምትለው፡የልክፍት፡ወፈፍታ፥ሲነሳባት፣ሲነሳባት፥ይሄው፡ነው፡ደንባቸው`፡በማለት፥ አንሾካሽከውልኝ፡ሄዱ።

`በርኄ`፡የተሰጠውን፡ሰነድ፡አጣጥፎ፤ከጉያው፡እንደሸጎጠ፥ወደ፡መኪናው፡ገብቶ፥ተመልሶ፡በጥድፍያ፡ግቢውን፡ለቅቆ፡ወጣ። አነጋገራቸው፥የባልቴት፡አልመስልህ፡ቢለኝ፥እርሳቸውም፤በሁከቱ፡ተረብሸው፡እንዳሆን፡ሰግቼ፡አዘንኩላቸው። የልቤን፡ልናገረው፡ብል፡ግን፥የ፡እኔን፡ችግር፡እና፡ጭንቅ፡የአባሰው፡~ከ፡`ሎሚታ`፡ክፍልዋ፡መዘጋት፡እና፡ከ፡ከተማውም፡መረበሽ፡ይልቅ፥ሌሊቱን፡ወስዳ፡የኣሳየችኝ፥ትንግርት፡ተኣምር፡ሚስጢር፡ነው። ርዕይ፡ይሁን፣ኅልም፥ወይም፥ከ፡ዓለም፡ተደብቆ፡የኖረ፥ልዩ፡ትዕይንት~እኔ፤ምኑን፡አውቄው!!

`በርኄ`፡እንደ፡አወጣጡ፤እየሾረ፡ተመልሶ፡መጣ፡እና፤የታሸገ፡ቦስጣ፡ነገር፤ለጋሽዬ፡አስረክቦ፥ወደ፡ሰራተኞቹ፡ዘንድ፡ሲሄድ፡ተከትየው፡ገባሁ። እማማ፡ጻዲቄ፤ብርጭቆ፡ጠላውን፡አቅርበውለት፥ አገጩ፡ስር፡ሄደው፡በማንጋጠጥ፤የሚለውን፡ይጠባባቁ፡ጀመር። በከፊል፡ትግርኛ፡እየቀላቀለ፡ከሚነግራቸው፡እንደተረዳሁት፡~

” መላው፥የ፡ከተማው፡ኗሪ፡ሕዝበ፡ክርስትያን~ከጽዎን፡ቤተ፡ክርስትያን፡ዓውደ~ምኅረት፡ላይ፡እንደተኮለኮለ፥የልቅሦ፡እግዚዖታ፡ምኅላ፡ጸሎት፡እንደጀመረ”፡ገባኝ።

የ፡ሽንኩርት፡ከተፋው፡ፈለግ፤ ባዶለደማቸው፥ጣቶች፥ጸጉራቸውን፡እየፎከቱ፡~” እህ~በ፡አዛኝቱ!~፥ምን፡መዓት፡ወረደብን፡ደግሞ፡በ፡አናቱ!?~`ክርያላይሦኑም፡ቀረ፡እና፡ልቅሦ ?!!”

~*~

(ገጽ፡~፲፪)

`በርኄ`፥ከተቀመጠበት፥እንጣጥ፡ብሎ፡ተነስቶ፡~” ኸጂማ~ተወሳኽና!ተወሳኽና!”፡እየ፡አለ፡ሲንቆራጠጥ፤ክፍሉን፡ትቼ፤ወደ፡ደጅ፡ወጣሁ። በ፡ሕይወቴ፥ብዙ፡ሕዝብ፡ተሰብስቦ፡ሲያለቅስ፡የ፡አየሁት፤የቀብር፡ለቅሶ፡ላይ፡ብቻ፡ነው፥እነሱም፤ቢበዛ፤በመቶ፡የሚቆጠሩ፡ቢሆኑ፡ነው። የ፡አንድ፡ከታማ፡ነዋሪ፡ሕዝብ፡ግልብጥ፡ብሎ፡ወጥቶ፥ቤተ፡ክርስትያን፡ደጃፍ፡ላይ፥እዬዬ፡ሲል፥በዓይነ፡ኅሊና፡ቢታየኝ፥መላው፡ኣከላቴ፡ተናወጸ።

ወደ፡መኝታ፡ክፍሌ፡ሮጬ፡ልገባ፡ስል፥ከ፡በሩ፡ላይ፥ከ፡`እትዬ፡`ተኾላች`፡ጋር፡ተጋጠምን። መዳፌን፡ይዛ፤ወስዳ፡አልጋዬ፡ዳር፡አኑራኝ፤በኅዘኔታ፡ዓይኖች፡አተኩራ፡ተመልክታኝ፡~” አይዞህ፥የ፡እኔ፡ልጅ፡አትደንግጥ!፥እመ~ብርኅን፤በምልጃዋ፡ታሳልፈዋለች!~ሃገሩ፡ሁሌም፡እንዲሁ፡ነው፥የኅይማኖት፡ነገር፡ከተነሳ፤መተራመስ፡ነው~ልጅቱም፡ትታህ፤ከክፍልዋ፡ተዘግታ፡ቀረች፡አይደል~ጥቂት፡ታገሳት~ሲነሳባት፡እንዲሁ፡ነች~መቼም፥ለጠበል፡ብለን፡እንደ፡አመጣናት፥እስከ፡አሁን፤ሳታጫውትህ፡አትቀ ርም~በመሀሉ፤ሃገሩ፡እንዳይሆን፡ሆነብን፡እንጂ~አይዞህ፡በርታ፣ያልፋል፥ብቸኝነት፡እንዳይሰማህም፤~`ሞገሤ`፡ክፍል፤ብዙ፡ጋዜጦች፡አሉልህ፥እሱን፡አገላብጥ”፡ብላኝ፡ሄደች።

ጋሽዬ፥አንዲት፡ቃል፡ሳይተነፍስ፥የቀረበለትን፡ዕህል፥ለዓመል፡ነካክቶ፡ሲያበቃ፤እጁን፡ተጣጥቦ፡ሲጨርስ፤ወረቀቱን፡እየ፡አጣጠ ፈ፤ወደ፡መኪናው፡ሲያመራ፥`በርኄ`፡ተንደርድሮ፡ደርሶ፡ገብቶ፡ሞተሩን፡ቆሰቆሰ፣ወድያው፥ኯሮኔሉም፡ተከተሉ።

የ፡እኔ፡ልብ፡ግን፥ከ፡`ሎሚታ`፡ላይ፡መነቀል፡አቅቶታል።`መቼ፡ተሽሏት፥ከ፡ክፍልዋ፡ትወጣ፡ይሆን?፣ሌሊቱን፡የዓሳየችኝን፡ተዓምር፥ዛሬም፡ትደግምልኝ፡ይሆን?~አለበለዝያ፥ዕውን፡መሆኑን፡እንዴት፡አውቅ፡አለሁ?`።

ጋሼ፥`ተሞገሥ`፡ብቅ፡ብሎ፡~”`ተኾላች`፥ልጁን፥ለእራት፥ከኛው፡ጋር፡አቅርቡት፡እባካችሁ~ብቸኝነቱ፡እንዳይጎዳው፥የ፡ከተማው፡ነገር፡እንደሆን፥በቶሎ፡የሚያበቃለት፡ጉዳይ፡አልመሰለኝም~እዬዬው፥`ደበረ~ታቦር`፡ድረስ፡ይሰማል፡ነው፡የሚሉት!”፡ሲል፡አነከረ። ገበታው፡እንደቀረበ፥መጨቃጨቅ፡ጀመሩ፡~

“~ኣቤቱ!~ቀድሞን፤ከ፡የት፡የሰማኸውን፥የተረጋገጠ፡ወሬ፡ነው*~ጋሽዬ፡እንደሆን፥ቃል፡ትንፍሽ፡ሳይል፡ነው፤ተመልሶ፡የሄደው ~የዝያውኑ፤የኮሮኔሉን፡አንጀባ፡ይዘህ፡እንዳይሆን*`

`አንቺማ፥ምን፡አለብሽ፥ነገር፡ቢከፋም፥ሻንጣሽን፡ጠራርፈሽ፤ወደ፡ዘመዶችሽ፡ውልቅ፡ነው~ይሄንንስ፥አስቀድመን፡አውቀናል~~`
`እስቲ፡ቀድሞ፡ነገር፥አገር~ምድሩ፡ይትረፍ፡እና፥ከእዛ፡በኋላ፥ትድረታችን፡የሚሆነውን፡እናያለን፡ግድ፡የለም~ልጅቱም፥ተነስቶባት፥ሌሊቱን፡በሙሉ፥ከክፍልዋ፡እንደተዘጋች፥ከ፡እነ፡ኣጅሬ፥`ሥም~አይጠሬዎ`ቹ፡ጋር፥በሚስጢር፡ቋንቋቸው፤እየተነጋገረች፡ነው፡መሰለኝ~`ጠበሉን፡በግዜ፡ትጠመቅ`፡ስልህ፡ኣሻፈረኝ፡አልክ፥ይኸው፡ለየላታ*`

`ልጅቱ፥በልጃገርድ፡የ፡ኮረዳነት፡ስሜት፡የምትጫወተውን፡ሁሉ፥እንደ፡ልክፍት፡እየቆጠራችሁባት፥ኋላ፥ለባሰ፡ጦስ፡ትዳርጓት፡እና፥ወዮላችሁ`። ነገሩን፤እንደ፡አልሰማችው፡መስላ፤ወደ፡እኔ፡ዘወር፡በማለት፡~

`ጥኽሎ፡አልለመድክም*፥ሞክረው፡እስቲ`፡በማለት፡ስታጎርሰኝ፥ብድግ፡ብሎ፡ተነሳ፡እና፡~`አጉል፥የውሸት፤ልጁን፡ማሞላቀቅሽን፡ተይው፡እና፥ይልቁኑ፥ልጅቱ፡በደህና፡እንደሆነች፡ሄደሽ፡እያት~ማልጎምጎሙ፡ሰጥ፡ብሏል፥የጤና፡አልመሰለኝም`፡ቢል፥ብርር፡ብላ፡ሄዳ፥እየጮኸች፡ተመለሰች።

`ሎሚታ`፥ ከክፍልዋም፣ከቤቱም፣ከግቢውም፡ብትፈለግ፥አንዱም፡ስፍራ፥ልትገኝ፡አልቻለችም። የገባችበት፡አልታወቀም።

ቤተኛው፡በሙሉ፤በድንጋጤ፡ቀዝቅዞ፤ኣፉ፡እንደ፡ተለጎመ፤ከ፡ግቢ፣እልፍኝ፥ላይ፡ታች፡ይተላለፋል። `በጠፋ፡ከተማ፥ወደ፡የት፡ተብሎ፡ፍለጋ፡ይኬዳል፡እንግዲህ፡አሁን~ስለ፡ነፍስ፤አንድ፡ምከሩኝ፡እንጂ*`።

ጋሼ፡`ተሞገሥ`፡ጋዜጣውን፡ገልጦ፥ለይምሰል፡እየ፡አነበበ፡~`ኣይዞሽ*፣ያልፋል*፣ሎሚዬ*ምንትሴ*፥እያልሽ፤ስታቆሻብያት፥ ጭርሱን፡ትታሽ፡ሄደች፥እረፊው*`

`ጋሽዬ፡ተመልሶ፡ሲመጣ፥ኮሮኔሉን፡እንዲያፈላልጉን፡መጠየቅ፡ነዋ~ሌላ፡መቼስ፡ምን፡ማድረግ፡ይቻላል` `የት፡ብሎ፡ነው፡የሚያፈላልግሽ*~ለእራሱ፤ግራ፡ተጋብቶ፥ጭንቅላቱ፥ኮፍያው፡ውስጥ፡እየተሽከረከረበት፡ነው`

ደረጃው፡እግርጌ፡የቆሙት፥እማማ፡`ጻዲቄ`፡~`ምናልባት፥መንፈሱ፥ወደ፡አንዱ፡ገዳም፡አስመልክቷትሥ፡ቢሆን፥እሜቴ`፡ቢ ሉ፥ቁልቁል፡እየተመለከተች፡~`እርሶ፡ደግሞ፤ከ፡አለ፡ገዳም፥ሌላም፡አይታሰቦት፥ይሂዱ፡ወድያ፤ወደ፡ጋገራዎ*`፡በማለት፡ስታመናጭቃቸው፥በኣፋቸው፤ቁርባን፡እንደተቀበሉ፡ያህል፤አጎንብሰው፤በጸጥታ፤ወደ፡ማዕድ፡ቤታቸው፡አመሩ።

ከተማዋን፡የወረሳት፥የቀን፡ጭለማ፥በኣናቱ፥ምሽት፡ቢደረብበት፥ቅጥሩን፥ልዩ፡ግራጫ፡ዘወፍ፡የተመረገበት፡መሰለ። ከ፡ክፍሌ፡ገብቼ፥`ሎሚታ`፡የሄደችበትን፡ሳንሰላስል፥ከ፡ዓይነ፡ኅሊናዬ፡የሚሣለው፥ያው፥ሌሊቱን፤በድብቅ፡ወስዳ፡ የ፡አሳየችኝ፤የምድር~ገነት፡ስፍራ፡ብቻ፡ሆነብኝ። ዓይኔን፥በትራሱ፡ብሸፍነው፡እንኳን፥ከፊቴ፡አልዞርልህ፡አለኝ።

ኾሽ፡በአለ፡ቁጥር፥የግቢው፡ቆርቆሮ፡በር፡እየመሰለኝ፥`ተመልሳ፡መጥታ፡ይሆን*`፡እየ፡አልኩኝ፡ስንሰፈሰፍ፥እትዬ፥አምጥታ፤ከክፍሌ፡የ፡አኖረቸው፡ራዲዮ፥የምሽቱን፡የመድኅኒት፡ቤት፡ተረኞች፡አስታውቆ፥በመክፈቻው፡የዋሽንት፡ዜማ፤ዝግጅቱን፡አብቅቶ ፥`ጺጺውው`፡ሲል፥በማንጎላጀት፡ውስጥ፡እንደ፡አለሁ፥እጆቼን፡ሰድጄ፤መዘውሩን፡ፍለጋ፡ስዳሥሥ፥`እሕሕህም`የሚል፤የሰው፡ጉሮሮ፡ከውስጡ፡ተሰማኝ። ብድግ፡ብዬ፤መብራቱን፡አብርቼ፥በመስኮቱ፣በበሩ፡ብቃኝ፤አንዳች፡የሰው፡እስትንፋስ፡ይሉት፡ጠረን፡እንኳን፡የለም።

ግቢውም፥እንደ፡ከተማው፥ጥቁር፡ዳስ፡እና፡ግራጫ፡ደመና፡እንደለበሰ፡ነው። የሥጋት፡ዦሮዬ፡አስተጋብዖ፡መሆን፡አለበት፡ብዬ፤ተመልሼ፤አልጋዬ፡ላይ፡አረፍ፡በማለት፥መዘውሩን፡ባንቃቃም፥`ህምሕምታው`፡አላቆምም፡አለ።

የውስጥ፡ብልሽት፡የፈጠረው፡ችግር፡እንደሆነ፡በ፡መጠርጠር፥ዘቅዝቄ፡ባትሪዎቹን፡ሁሉ፡አውጥቼ፡ብመለክት፥`ሕምሕምታው `፡ይብስበት፡ጀምር። የጨነቀው፡ሰው፡አይሞክረው፡የለውም፥እኔም፡መልሼ፡~`እሕሕምም`፡ብል፡~`እየ፡አዳመጥከኝ፡ነው*`፡የሚል፥ኮለል፡የ፡አለው ን፡የሎሚታን፡ድምጽ፡ስሰማ፡ተስፈንጥሬ፤ከአልጋዬ፡ወጥቼ፥መስኮቱን፣የልብስ፡ቁም፡ሳጥኑን፣በሩን፡ከፍቼ፥መተላለፍያውን፡ ብፈትሽ፥አንዳች፡የሰው፡ምልክት፡አጣሁ። እራሴን፡በመጠራጠር፥ተመልሼ፡አልጋዬ፡ላይ፡እንዘፍ፡ስል፡~`እዚሁ፡ነኝ፥ወደ፡ሌላ፡ፍለጋ፡አትሂድ`፡አለችኝ። አንድ፡ጥግ፡ተደብቃ፡እየ፡አሾፈችብኝ፡መሆኑን፡ጠርጥሬ፡~ `እዚሁ፥ማለት፡የት፡ነው*`፡ስል፡ጅል፡ጅልኛዬን፡ጠይቅኋት።

በጭለማው፡በ፡የማይታየኝን፡ፈገግታ፡~`እሕህም`፡አለች፡እና፡~`አንተ፡ልጅ፥ይሄ፥ከ፡እኔ፡ጋር፡ክርክር፡ይቅርብህ፡ብዬ፥ስንት፡ግዜ ፡ነው፡የመከርኩህ*~እዚሁ፣እዚሁ፡ነዋ*`

`እ~`እዚሁ`፡ምን፡እየ፡አደረግሽ፡ነው*`። መልስ፡ሳትሰጠኝ፡ቆይታ፣ቆይታ፥ሄዳለች፡ብዬ፡ሳስብ፤ተመልሳ፡~ ` አንተን፡እየጠበቅሁኝ፡ነዋ`፡አለችኝ
`የት፡ብዬ፡እንድመጣ*`
`እዚሁ፡ነዋ*`

በእዚሁ፥አስጊ፡ቅጽበት፡~ድንገት፤አንዱ፡የቤት፡ሰው፡ከተፍ፡ቢልብኝ፣ወይ፡ሲተላለፍ፤ቢሰማኝ፥ምን፡ሊውጠኝ፡ነው*። የልጅቱ፡ህማም፡ተሥቦ፡ተጋብቶበታል፡ብለው፥ለሰሞኑ፡ጠበል፡እንደሚያዘጋጁኝ፡አያጠራጥርም።

ለማንኛቸውም፡ብዬ፥በሩን፡ገርበብ፡አድርጌ፡ተውኩት። ድንገት፤ሰው፡ሲተላለፍ፡እንኳን፡ቢታየኝ፤ራዲዮውን፡በመከዳው፡ለማፈን፡ተዘጋጀሁ። ደግነቱ፥የቀኑ፡ጭንቅ፡እና፡ንጭንጭ፡የ፡አዳከመው፡ቤተኛ፡በሙሉ፤ለሽሽ፡ብሎ፡ዕንቅልፉን፡እየለጠጠ፡ነው።

`እሕህምም` `አለሁ~እዚሁ፡ነኝ~አንቺው፡ነሽ*`

`ኋላ፥ማንን፡ጠብቀህ፡ኖሯል*`

`~እ~እኔ፡ምን፡አውቃለሁ*~~እ~ትላንትና፡ሌሊት፡ወስደሽ፡የአሳየሽኝ፡ሰፈር፡ከሆነ፡የአለሽው*~መንገዱን፡ጠቁሚኝ፡እና፡መምጣት፡እችላለሁ`። እንደገና፥`ጺጺጺው`፡የሚል፡ድምፅ፡ተሰምቶ፥ደግሞ፡ሄደች፡ብዬ፡ሳስብ፡~

`የሌሊት፡ልብሥህን፡ሳትቀይር፣ጠዋት፡ሾልከን፡በገባንበት፡የጓሮው፡በር፡ውጣ፡እና፥እንደ፡ባትሪ፡የምታበራልህ፡የጨረቃ፡ብርኅንን፡ተጠባበቅ። ልክ፡እግርህ፡ስር፡በርታ፡ስታያት፥ግራ፣ቀኝ፡ሳትገላመጥ፤ፋናዋን፡ብቻ፡እየተከትልክ፡ሰተት፡ብለህ፡ሂድ። አንድ፡ስፍራ፡ከደረስክ፡በኋላ፡ደግሞ፥የሚለጥቀውን፡መርኆ፡ትሰማለህ~እሺ*`

`እንዴት፡ይሰማኛል~ራዲዮውን፡ይዤ፡ካልመጣሁ` `ክርክሩን፡ለ፡አሁኑ፡ተወው፡እና፡የምነግርህን፡ብቻ፡ተከተል~ሰምተኽኛል*`

`አዎን~በደንብ፡ሰምቼሽ፡አለሁ~እ~መሆኑን፡ግን፡ያው~እ~`ሎሚታ`፡ነሽ፥አይደል*`

`ምነው~ድምፄ፥አልመስልህ፡አለህ፡እንዴ*`

`ድምፅሽ፡እንኳን፡ያው፡የአንቺው፡ነው~ግን~እኔ፡እንጃ~እ~`

`አንተ፡ልጅ*፥ይሄ፡~`እኔ፡እንጃ`፣`ምናምን`፣`እ`፣`አለ፡አይደል`፡የሚሉ፡ቃላትን፡መንተባተብ፡ተው*፥ሃሳብክን፡ይሰርቁብሃል*`፡ አላልኩህም፣ብዬሃለሁ*`

`እሱስ፤ብለሽኝ፡ነበር~ግን፡ማቆም፡አስቸገረኝ፡እና፡ነው`

`በል፥አሁን፥ሳታዛንፍ፥የ፡ግራ፡እግርህን፡በማስቀደም፤መራመድህን፡ጀምር`። የበሩን፡ደፍ፡አልፌ፥ምድሩን፡ከመረገጤ፥የ፡ባውዛ፡ብርኅን፡የመሰለ፡ጨረር፤ከመጫሚያዬ፡ፊት፥ቷህ፡ብሎ፡በርቶ፤እንደ፡የብርሃን፡ጅረት፡እየፈሰሰ፤እየቀደመ፡ይመራኝ፡ጀመር። የኣእምሮ፡መረበሽ፡ይሉት፡ፍርሃት፣የልብ፡ድንጋጤ፡ይሉ፣የመንፈስ፡ሥጋት፥አንዳቸውም፤ከውስጤ፡አልነበሩም።

ዓይኔ፡እያየ፥የአንድ፡ከተማ፡ነዋሪ፡ሕዝብ፤በሙሉ፤በ፡ነቂስ፡ወጥቶ፣ምድር፡ባድማ፡መስላ፣ከ፡ሠማዩ፥ድምቢጥ፡ወፍ፣ከምድር፡ ጭር፡ያለች፡ዶሮ፡የማትታይበት፡ሃገር፡መጥቼ፣የምዕመናን፤እዬየ፡ለቅሶ፤እንደ፡ሐምሌ፡ዶፍ፤ከ፡ተከዜ፡ወንዝ፡በኣሻገር፡እየተሰማ፥እንዲሁም፤ሌሊቱን፡ያየሁትን፡ጉድ፤ከአየሁ፡በኋላ፥ምን፡አእምሮ፡ጎደለብኝ፡ብዬ፡ነው፤የምፈራውስ፣የምሰጋውስ*~ይሄውም፤የሰብዓዊ፡ተፈጥሮ፡ነገር፡ሆኖብኝ፡ነው*።

የሚመራኝ፥የጨረቃዋ፡ፋና፥ዳገቱን፡እየ፡አሻቀበኝ፣ቁልቁለቱን፡እየ፡አዘቀዘቀኝ፡ወስዶ፡ወስዶ፥አንድ፡ኣፋፍ፡ላይ፡ሲደርስ፥እንደ ፡ግዙፍ፡ዓምደ፡ብርኅን፥አሻቅቦ፣ግድግድ፡ብሎ፡ተገትሮ፡ቆመ።

በመንገዳችን፡ላይ፤እንደ፡አስጠነቀቀችኝ፤ቀና፡ሳልል፡አቀርቅሬ፡አሱውኑ፡ስከተል፤ግራ፡ቀኙን፡ዓለም፡ዘንግቼው፡ኖሮ፥ቀና፡ስል፥ ዓይኖቼ፤ሌላውን፡ነገር፡ነጥለው፡መነፀር፡አዳገታቸው፡እና፤ግዑዝኛዬን፡እንደቆምኩኝ፡~

`አንተ፡ልጅ~ትሰማኝ፡አለህ*`፡አለችኝ

`አዎን፡እሰማሽ፡አለሁ~የት፡ነሽ፡የአለሽው`

`አይዞህ፡~እዚሁ፡ነኝ`

`እዚሁ፡የት፡ነው`
`እዚሁ፡እዚሁ፡ነዋ*~ይገርማል~ገና፡ከመድረሥህ~ክርክርህን፡ጀመርከኝ፡አይደል`

`ትላንትና፡ይሁን፡በቀደም፡ዕለት፥እኔ፡እንጃ~አምጥተሽ፡የአሳየሽኝ፡ሰፈር፡ግን፥ፈጽሞ፡ይሄንን፡አይመስልም`

`ገና፡ድሮህን~ማነፃፀሩን፡ጀመርክ~ከትምህርት፡ቤታችሁ፥የክርክር፡ክበብ፡አባል፡ሳትሆን፡አልቀረህም`

`~ኣይይ~እ~እሱስ፡አባል፡አልነበርኩም~ከባቢው፡ግር፡ቢለኝ፡ግዜ፡እኮ፡ነው`

`~ግድ፡የለም~የጎበዝ፡ምልክቱ፡ግርታ፡ነው~~አሁን፡ግን፡የምነግርህን፡በጥንቃቄ፡አድምጠኝ`
`እሺ`~

`እዛ፡ማዶ~ከ፡እርቀቱ፡ኣምባ፥ነጭ፡ህንፃ፡ይታይሃል*~ኣይኖችህን፡በመዳፍህ፡አጥላ፡እና፡ትክ፡ብለህ፡ተመለከት`

እንደ፡አለችኝ፡ባደርግም፥ምንም፡የተከሰተልኝ፡ነገር፡አልነበረም። ማመንታት፡ስጀምር፥ጥቂት፡ቆይቶ፥ልክ፥ጭጋግ፡እንደገለጠው፡መስሎ፥ወተት፡ነጭ፥የ፡ዕብነ~በረድ፡እና፡ብርጭቆ፡የታነጸ፣ጉልላቱ፡ሾጣጣ፡እና፡ሽቅብ፡ወደ፡ሠማያት፡የአሞጠሞጠ፡ንድቅ፡ተአየኝ።

`~እ~አሁን~እየታየኝ፡ነው፥በብርጭቆ፡ወይ፡በመስታወት፡የታነጸ፡መሳይ፡ታላቅ፡ህንፃ፡ነው~አይደል*`

`ብርጭቆም፣መስታወትም፡አይደለም~ኣልማዝ፡ነው*`፡አለች

`ጠጋ፡ብዬ፥ብመለከተውስ*`

`ድንገት፥ለሚጠተ፡ብርኅኑ፡ዓይኖችህ፡ሲጋለጡ፥ጨረሩ፡እንዳይጎዳህ፡ተጠንቀቀ፡እንጂ~መቅረቡንስ፡ትችላልህ።`

በስንዝር፡ምትር፡ቀስታ፤መቅረብ፡ስጀምር፥ከእግሬ፡ስር፡እንደ፡ዜማ፡ነገር፡ይሰማኝ፡ጀመር። ላስታውቃት፡ታሰበኝ፡እና፤መልሼ፡ተውኩት። እርስዋ፤ከ፡ዕንብርቷ፡በላይ፡የራዲዮ፡ድምፅ፡ከሰማች፥እኔን፡እግሬ፡ስር፡ዜማ፡ቢሰማኝ፡ምን፡ደነቀ*~አርፈህ፡ተራመድ*

`አቤት፥ነገርን፡ማገናዘብ፡ስታውቅበት*~ጥሩ፥የሰዋስው፡ተማሪ፡ሳትሆን፡አልቀረህም`።የሆድ፡ውስጥ ሃሳቤን፡ማድመጥዋ፡አስደንግጦኝ፡~`እንዴት፡አወቅሽ`*፡ስል፡በጮክታ፡ጠየቅኋት።

`አንተ፡ልጅ፥ተው~ይሄ፥ከ፡እኔ፡ጋር፡መከራከር፡ቢቀርብህ፡ይሻልሃል፡ተው*`

`መቼ፡ተከራከርኩሽ*~እህ*~ጎበዝ፡የሰዋሰው፡ተማሪ፡እንደሆንኩኝ፤እንዴት፡አወቀች፡ብዬ፡ነው፡ የአሰብኩት~እሱንም፤ለእራሴው፡በሆዴ፡ነበር፡የአልኩት*~እንደ፡ወደድኩሽ፡አውቀሽ፡ነው፡የምትቆጭኝ፡አይደል።`

በሆድዋ፡ስትሥቅ፤ሳቅዋ፥አየሩ፡ጸፈጸፍ፡ላይ፡ወጥቶ፡የሚሰጣ፡ይአክል፡ያስታውቃል።

`በል፡እስቲ፡ይሁንልህ*~አሁን፡ይልቁኑ፤የምትረግጠውን፡እየተጠነቀቅህ፤በዜማው፡ብዛት፤ናላህ፡ዞሮ፤ታርግ፡እና፥ደግሞ፥`እኔ፡ እኮ፥ቅዱሥ፡ያሬድ፡ነኝ`፡እንዳትለኝ`

`ቅዱስ፡ያሬድ፡ማን፡ናቸው*`

`እሱን፥በኋላ፡አረፍ፡ስትል፥በጽሞና፥የደም፡ሥሮችህን፡ጠይቃቸው~እሺ*`

`እሺ`፡ብዬ፥የጥንቃቄ፡እርምጃዬን፡ገፋሁ። ጥዑመ፡ዜማው፥ልብን፤ትን፣ብን፣ህስ፡እያደረገ፥ነፍስን፡የሚዳሥሥ፡ዓይነት፡ነው ። የዓልማዙ፡ህንፃ፥ስቀርበው፥የውኃ፡ሠማያዊ፡እና፡የውኃ፡ኣረንጕዴ፡ጨረር፡ፍርግርግ፡አሳየኝ። የትንፋሼ፡ሁኔታ፥ቁርጥ፡ቁርጥ፡ ማለት፡እንደ፡ጀመረ፥ቆምኩኝ።

`አሁንስ፥ምን፡ሁን፡ትይኝ፡አለሽ*~ህንፃውን፡ስቀርበው፡ግዜ፥እስትንፋሴ፡ይቆራረጥብኝ፡ጀመር`

`እስትንፋሴ~እባክሽን፡አትቆራረጭብኝ*`፡ብለህ፡ጠይቃት፥ትሰማህ፡አለች።’

በመጀመርያ፥የአስለመደችኝ፥የቀልድ፡አነጋገርዋ፡መስሎኝ፡ነበር፥ልሞክረው፡ብዬ፡ብናገረው፡ግን፥በዕውነትም፤እንደ፡አለችው፥እስትንፋሴ፥ሰጥ፣ለስ፡ብላ፥እንድያውም፤ከ፡ነጭ፡ዕብነ~በረድ፡ዓልማዝ፡ስሪ፡ህንፃው፡ጋር፤ተሠምላ፤አብራ፡እንደተለሰነች፥ሥምም፡ሆና፡ትተነስልኝ፡ቀጠለች።

ከሁሉም፡ሁሉም፡የደነቀኝ፥በሁለት፡ትናንሽ፡ዓይኖች፥ከግንባር፡በታች፣ከአፍንጫ፡መሃል፡በሚገኙ፥የ፡ብንተ~ዓይን፡ እና፡የብሌን፡ስንጥቦች፥ይሄንን፡የሚያክል፥የሠማይ፡ክፋይ፣ደመና፡መሀል፡የታነፀን፡ቤተ፡መቅደስ፡ማየት፡መቻሌ፡እንጂ*።

`ምን፡እየሆንክ፡ነው*`

`~ኧረ~እኔስ፥ምንም፡እየሆንኩኝ፡አይደለም~አለሁኝ፡እዚሁ፡ነኝ`፡አልኳት። እንደገና፡ፈገግ፡ብትል፥ፈገግታዋ፤ነፋሱ፡ወለል፡ላይ፡ተጸፍጽፎ፡ታየኝ።

~*~

(ገጽ፡~፲፫)

የ፡አንድ፡ትንግርታዊ፡ርዕይ፡ከአለፈ፡በኋላ፥የሰው፡አእምሮ፤እራሱን፡ለበለጠ፡ርዕይ፡ለማዘጋጀት፥የ፡ውስጣዊ ው፡ኅሊና፡ጽሩይ፡ጉልበት፡ይረዳዋል፡መስሎኛል። የሠማይ፡ክፋይ፡የሚያክለው፣ከዓልማዝ፣ከሰምጴር፡እና፡ከነጭ፡ዕብነ~በረድ፡የታነጸው፡መቅደስ፡ስር፡ቆሜ፥ቁርጥርጥ፡እስትንፋሴን፡እየቆጠርኩኝ፡ሳለሁ፥መንበር፡ተሳልማ፡እንደተመለሰች፡ምዕመን፣ሳትኮራ፣ሳትፈራ፥በዝግታ፡እርምጃ፡እየቀረበችኝ፡መጥታ፡~”ምነው፡ግትር፡ብለህ፡ቀረህ!?~ድንጋጤን፡እስከ፡አሁን፡አልለመድከውም!?”፡ብትለኝ፥የተዘነጋኝ፡የደስታ፡ስሜት፡ተመልሶልኝ፤ልቤ፡ሰከን፡አለች።

መግብያ፣መውጫው፡ከማይለየው፡ቤተ~መቅደስ፤ከወዴት፡እንደፈለቀች፡ስገረም፥መዳፌን፡ይዛ፥ዙርያውን፡ዑደት፡አሂዳኝ፥እንደ፡ሄላል፡ጨረቃ፡የሚያበራ፡ኣንቀጸ፡ብርኅን፡ፊት፡ለፊት፡ስንደርስ፡ቆምን። ከንድቁ፡ ትርስት፡እና፡ዙርያ፡ክፈፍ፡የሚጸናጸሉት፤የልብ፡ቅርጽ፡የኣላቸው፡የዓልማዝ፡ድንጋዮች፡የሚወጣቸው፡ቃጭል፥የመረዋ፡ቅኝት፡ነበረው።

” `እስከ፡አሁን፥እንዴት፡ነበር፡የምታነጋግሪኝ?`፥ብለህ፡እንኳን፡አትጠይቅም~ምን፡ነካህ?!”

“~እህ~ሃስቤን፡ቀድመሽ፡እየተረዳሽው፡ምን፡ጥያቄ፡ያስፈልገኛል?~የምትይውን፡መስማት፡ብቻ፡እንጂ!”

ጭንቅላትዋን፡ብቻ፡በኣንክሮ፡ነቅንቃልኝ፤ማዶ፡ማዶውን፡መመልከት፡ጀመረች። ከአሁን፡አሁን፥`ወደ፡ውስጥ፡ልታስገባኝ፡ይሆን?~ውጭው፥እንዲህ፡እንደ፡ገኒኅተ፡ፀሃይ፡የሚያበራ፡ቤት~ መቅደስ፥ውስጡ፡ምን፡ሊሆን፡ነው?~ደግሞስ፥`እስከ፡አሁን፥እንዴት፤አንዳች፡ሰብዓዊ፡ፍጡር፡ሳናይ?`። ጸጥ፡ብለን፡ከቆምንበት፥ለጥቂት፡ግዜ፡ቆየን። `ከ፡ኣዲስ፡~አበባ፥ለጠበል፡ነው፡የአስመጣናት`፡የሚሉት፡የባል፡እና፡ሚስቱ፡ወሬ፤ከውስጤ፡በንኖና፣ተንኖ፡ከጠፋ፡ቆይቷል~ሆኖም፡ግን፥እስከ፡አሁን፤ስለ፡ልጅቱ፡ማንነት፥በምትኩ፡ማብራራያ፡አላገኘሁለትም።`ማሪያም`፡ተመስላ፣ተለውጣ፡መጥታብኝ፡ይሆናል፥ብዬ፡እንኳን፡እንዳልገምት፥የሁለታችንም፤ስጋ፡ለባሲ፡የትሥብዕት፡ዓይኖች፡እየመሰከሩ፥በቀደም፡ቀን፥ከብጫው፡የዕብነ~በረድ፡ቤተ፡ክርስትያን፡መቅደላ፡ላይ፤በኅምራዊ፡ኅመልማሎ፡ደመና፡ተጀቡና፣በነገደ፡መላዕክት፡ተንከባክባ፤ሽቅብ፥ወደ፡ሠማየ፡ሠማያት፡ስትፈልስ፡ አይተናታል። ደግሞም፤ወደ፡ሕያው፡ፍጡራን፡ምድር፡ተመልሰን፣ከሰዎች፡ጋር፡ውለን፡አድረንም፡ተነስተናል። ህልምም፣የቁም፡ቅዠትም፣ምጡቅ፡ምናብም፤እንደ፡አልሆነ፡አረጋግጠና። ታድያ፤ምን፡ይባላል?

በመላ፡ኣካላቴ፡ላይ፡እየሠለጠነብኝ፡የ፡አለው፡ሰላም፡እና፡ፀጥታ፥በራዲዮ፡ሲነገር፣በመጽሐፍት፡ሲነበብ፣ሲቀደስበት፡የኖረውን፤ስንሰማው፡የኖርነውን፡የቅዱሳን፡ታሪክ፡አስታወሰኝ። እኔ፡ግን፤ከእዛ፡እጅግ፡ሩቅ፡በመሆኔ፥የገጠመኝን፡ሁኔታ፡ለመረዳት፡እየቸገረኝ፡ነው።`ሎሚታ`፥እጅግ፡ከማማርዋ፡ብዛት፥የህንፃው፡ነጸብራቅ፡ብርኅን፤እላይዋ፡ላይ፡ተቀፍሎ፡የቀረባት፡መሰለኝ።

“እንግዲህ፥ለዛሬው፥ይሄንን፡ይአክል፡ከአየን፡ይበቃናል!~ሃገር፡እና፡ቤተ፡ሰብ፡እየታወከ፥እኔ፡እና፡አንተ፡ለብቻችኝ፥ከዔደን~ገነት፡ደጃፍ፡ብንመናሽ፥እግዜሩም፡ይቀየመናል~ስለ፡እዚህ፤ወደ፡ምስኪን፡ዘመዶቻችን፡ዘንድ፡እንመለስ፡እና፥የደረሱበትን፡አይተን፤ባይሆን፡ከሰሞኑ~እንደ፡አመልህ፡ሁኔታ፡ታይቶ፤ተመልሰን፡እንመ ጣበታለን~እሺ?”

‘እኔማ፥ምን፡አንደበት፡አለኝ፥እንዲሁ፡ብቻ፥ሰምቼሽ፡አለሁ`፡ለማለት፡ይአክል፥በ፡ኣዎንታ፡ጭንቅላቴን፡ነቀነቅሁላት። አጸደ~ግቢውን፡እየራቅነው፡በሄድን፡ቁጥር፥ከ፡ጀርባችን፥የ፡ህንፃው፡ብርሃን፤ደመና፡እንደሚከልላት፡ለጋ፡ጨረቃ፡ውጋጋንዋ፡እየደከመ፡ሲሄድ፡~”ዋ!፥ነግሬህ፡አለሁ!፥አንድ፥ዘወር፡ብሎ፡ማየት፡የለም!~እ ሺ?!”፡~

“እሺ”

“ወደ፡መንደራችን፡ስንመልስ፡ግን፥እግረ፡መንገዳችንን፤በከተማው፡መሃል፡አልፈን፥`ጽዎን`፡ቤተ፡ክርስታን ፡ዙርያ፡ተኮልኩሎ፡እዬዬ፡የሚለውን፡ሕዝብ፡ሁኔታ፡መመልከት፡አለብን~`ታቦተ~ጽዎንን፡ተሸክመን፥በሚካዔል~ዋሻ`፥ወደ፡እየሩሣሌም፡እንጓዛለን`፡ብለው፡የተነሱትን፡ካህናትም፡ነገር፡እንመልከት፡እስቲ~ምን፡ ይመስልሃል?”

” እ~እኔ፡እማ~ምን፡ይመስለኛል፡ብለሽ፥`ሎሚታዬ`!~ሁሉንም፡ነገር፡የምታካሂጅው፡አንቺው፡ነሽ”

“መልካም፡ነው~ክርክርህንም፡እየተውከው፡ነው!~የፍርሃት፡ነው፤ወይስ፤ልብህ፡በመንፈስ፡ቅዱስ፤እየተቃኘችልህ፡ይሆን?”። የምለው፡ቸግሮኝ፡ዝም፡ብል፡~

” ለጥያቄዬ፤የሚመስል፡መልስ፡እፈልግ፡አለሁ!”፡አለችኝ።

“ለእዚህስ፡መልስ፡የለኝም~ይልቁኑ፥ሳይነጋብን፡ብንደርስ፡ጥሩ፡ይመስለኛል፥ከመኝታ፡ክፍሌ፡ፈልገው፤ከአጡኝ፤ከአንቺው፡ጋር፡እንደ፡ኮበለልኩኝ፡ሳይጠረጥሩ፡የሚቀሩ፡አይመስለኝም”

“እንዳሰኛቸው፡ይጠርጥሩዋ!~መላው፡ሃገሬ፡ተሰብስቦ፤የ፡ምኅላ፡እዬዬ፡ለቅሶ፡የሚጮህባት፡ምድር፥ሁለት፡ ወጣቶች፤በርግገው፤ከቤት፡ቢጠፉ፡ምን፡ያስገርማል!?”

” `ጋሽዬ`፡እንዲቀየመኝ፡አልፈልግማ~ሃገር፡ሊያስጎበኘኝ፡አምጥቶ፤ከኮረዳ፡ጋር፡ስኮበልል~ምን፡ይባላል? “

“ስለ፡እሱስ፡አታስብ~`ጋሽዬ`ህም፤ወደ፡አሥመራ፡ተመልሼ፡ልዑል፡እንደራሴውን፡እንዳነጋግር፡ኣቡኑ፡ስለተማጸኑኝ፤በሄሊኮፕተር፡መሄዴ፡ነው~ቆይታዬ፥ለሁለት፡ቀናት፡ብቻ፡ስለ፡ሆነም፥ልጁም፡እዚሁ፡ከእናንተው ፡ይቆይ፥ጉዳዩ፤ግርማዊነታቸው፡የዘውድ፡ምክር፡ቤት፡ስለ፡ደረሰ፥መንግሥት፡ሰግቶበታል፡`:ብሎ፡ሲነግራቸው፡ዦሮዬ፤ከ፡እርቀት፡ሰምቷል~እስከ፡አሁንም፡ሳይሄድ፡አልቀረም “፡አለችኝ።

~*~~*~

   (ገጽ፡~14) 

  ዳገት፣ቁልቁለቱን፥እንደ፡ዳልጋ፡አንበሳ፥እመር፣እነር፡ስትልበት፥በአረም፣በጉልጕሎ፡የአደገችበት፡የ፡ትውልድ፡ሐገርዋ፡ወረዳ~ኣውራጃዋ፡ይመስላል። በየት፡በየት፡አቆራርጣ፡እንደ፡አደረሰችን፡ሳላስተውል፥ የምልዐተ፡ሕዝቡ፥ነጭ፡ሸማ፥እንደ፡የባሕር፡ሞገድ፡አረፋ፡ከተንጣለለበት፥ጽዎን፡ማርያም፡ዓውደ~ምኅረት፡ላይ፡አረፍን። 

   ” ዋዮው!”~፣”እዬዬው!”፡ማላዘኑ፥ከከበሮ፡እና፡ነጋሪት፣ከ፡ጸናጽል፡ሻሻታ፡ጋር፣የ፡መረዋው፡እና፡ደወሉ፡ጕውጕታ፤ተቀላቅሎበት፥የምጽዓት፡ነጋሪ፡ኣዋጅ፡መስሏል። ከ፡ወደ፡የት፡ እንደፈለቀ፡የማይለይ፤የዕጣን፡ጉም፤ዙርያ፡ዓውዱን፡ሽፍኖታል። ከ፡ቤተ፡ክርስትያኑ፡በር፡አፍ፡መግብያ፡ደረጃ፡ላይ፥የድምጽ፡ማጉያ፡የያዙ፡ካህን፥በ፡ሲቃ፡ድምጽ፡ይጮሃሉ፡~ 

  ” በይ~እንግዲህ፥አንዱንም፡ሳታስቀሪ፥በደንብ፡አድርገሽ፤እንድትተረጉሚልኝ!”፡ስላት፤በ፡ምጸት፡ዓይን፥የጎንዮሽ፡ተመልክታኝ፡~”እዚህ፡ከደረሱ፡በኋላ፥የቋንቋ፡ችግር፡አይኖርም፥ የ፡`በዓለ፡ኅምሣን`፡ሚስጢር፥የግብረ~ገብ፡አስተማሪህ፡እንኳን፡አልነገሩህም~ሁላችንም፥የሣባዊት~ግዕዝ፡ሕዝቦች፡ነን!”፡አለችኝ። 

 በዕውነትም፡እንደ፡አለችው፥ቄሱ፡በትግርኛ፡የሚናገሩት፥ወደ፡ኣምሃርኛ፤ኾለል፡ብሎ፡እየተተረጎመ፤ይሰማኝ፡ነበር፡~” እላንት፤የምስለ፡ፍቁር፡ወልዳ፡ምዕመናን!~የኣባቶቻችንን፡ቅርስ፣የ፡ ኣበውን፡ውርስ፣የ፡ቅዱሳኑን፡መበዓ፡ስትጠብልቅን፡የኖረች፥እመ~ብርኅን፥እነሆ፡ደረሰችልን!~እነሆን፥በ፡ኣክሱም፡ከተማችን፡ዙርያ፡ተዳፍነው፡የኖሩት፥ኅምሣ፡የወኃ፡ጉርጓዶች፥ፈልቀው፣ ደምብቀው፤ምድሪቱን፡እየ፡አጠጧት፡ይገኛሉ፣የ፡ዕብነ~በረድ፥ማዕድናችንን፡ሃብትም፥በ፡ቤተ፡ክህነቱ፡አስተዳደር፡ስር፡እንዲውል፤ከመንግሥት፡ጋር፥ስምምነት፡ላይ፡ደርሰናል~~!”። 

ይሄንን፡የሰማው፡ሕዝበ~ክርስትያን፥ለቅሶውን፡ደስታ፡ውጦበት፥የሚሆነው፡ተስኖት፤ሲተራመስ፥ከመጣበት፡የ፡አልታየ፡የ፡አንበጣ፡መንጋ፥ሠማዩን፥ከ፡አድማስ፡እስከ፡አድማስ፡ገጥሞ፤~ “ዉርብርብርብ!!”~፡እየ፡አለ፡ሲቀርበን፥ ኅዘኑን፡ሳይጨርስ፣ደስታ፣ደስታውን፡ሳይጨርስ፤ሽብር፡የተፈራረቀበት፡ሕዝብ፡ዙርያውን፡ሲተራመስ፥መንግሥት፡ለ፡ሰላም፡ጥበቃ፡የ፡አሰማራቸው፥ ዙርያውን፡የከበቡት፡ወታደሮች፤በርግገው፥ጠብ፡መንጃቸውን፥ሽቅብ፡ማንዷዷት፡ሲጀምሩ፥አየሩም፡ታወከ፣ምድሪቱም፡ቀውጢ፡ሆነች። 

  `ሎሚታ`፥ሳትሸሽ፣ሳትረበሽ፥እንደ፡አዋጊ፡መኾንን፥በ፡ዝምታ፥ትዕይንቱን፤ስትመለከት፡ባያት፥እኔም፥ደንዝዤ፡ፈዝዤ፤እርስዋኑ፡መመልከት፡ጀመርኩኝ። ሽቅብ፡ወደ፡ሠማዩ፡ጠቆመችኝ። 

በቀደም፡ዕለት፡ሌሊት፡የ፡አየናቸው፤ነጫጭ፡ቁራዎች፤ ክንፋቸውን፡እንደገጠሙ፡ደርሰው፥የኣንበጣውን፡መንጋ፡ሲጨረግዱት፥ክንፋቸው፡እየተበጣጠሰ፤ ከምድር፡ላይ፡እየወደቀ፤እንደ፡ሥሥ፡ ሰሌን፡ይነጠፍ፡ጀመር። ኁከት፣ግራ፡መጋባት፡እና፡ነውጽ፡የአደፈረሰው፣አግጣጫ፡እና፡መሄጃ፡የ፡አጣው፡ሕዝብ፤አዙሪት፡ውስጥ፡ገብቶ፡ሲሽከረከር፥በርግጎ፥ወደ፡`ሚካዔል~ዋሻ`፡አቅንቶ፡የነበረው፡ወገን፤የኋልዮሽ፡እየ፡አፈገፈገ፡ሲመለስ፥የ፡ንኅብ፡መንጋ፡መኣት፡ከዋሻው፡ውስጥ፡እየተመመ፡ወጥቶ፥በሐገር፡በምድሩ፡ላይ~” ዕዉዉዉዉ!!”፡ይልበት፡ጀመር። 

 የ፡ኣንበጣው፡መንጋ፡እምሽቅ፡ብሎ፡ሲያልቅ፤ ንኅቦቹ፤ምዕመናኑን፡ሳይተናኮሉ፥ዙርያውን፤ጽዎን፡ቤት፡ክርስትያንን፡ዑደት፡ሲዞሩ፥የወርቀ፡ዘቦ፡ድባብ፡መሰሉ። ብፁዕነታቸው፥  በ፡ዥንጥላ፡እና፤ በ፡ካህናት፡እንደታጀቡ፥ወደ፡ሠገነቱ፡ሲቀርቡ፥የተበተነው፡ሕዝብ፥ለሽ፣ሰጥ፡ብሎ፤በቀስታ፤ከተበተነበት፡ሲመለስ፥ከ፡ቤተ~ክርስታያኑ፡መግደላ፡ላይ፥በቀደም፡ወደ፡ሠማያት፡ ስትፈልስ፡የ፡አየናት፤ብርኅን፡የተላበሰች፡ክስተት፡ስትታይ፥ እስትንፋስ፡የአለው፡ፍጡር፡በሙሉ፡በጉልበቱ፡በርከክ፡ማለት፡ሲጀመር፥አንዱ፡ካህን፥በጥንቃቄ፡የአቀረበላቸውን፡የ፡ድምፅ፡ማጉልያ፡ጠጋ፡በማለት፥በኣረጋዊ፡ድምጻቸው፡~ ” ~ሠላም፡ለኪ!~፥ጎሥዓ፡ልብየ፡ቃለ፡ሠናይ~ጎሥዓ~ወ፡ኣነ፡አየድዓ፡ውዳሴ፡ለድንግል!”፡የሚለው፡የቡራኬ፡መክፈቻቸው፤በግራ፡ዦሮዬ፡ሲሰማኝ፥`ሎሚታ`፥ዓይኖችዋን፥ከምልዓተ፡ ምዕመናኑ፡ጋር፥አሁንም፡የ፡ቤተ፡ክርስትያኑ፡ጣራያ፡ላይ፡የተከሰተችው፡ብርኅን፡ላይ፡እንደተተከለ፥ወደ፡ቀኙ፡ዦሮርዬ፡ጠጋ፡በማለት፡~ 

  ” ይኸውልሃ!~አላልኩህም!?~ደረሰችላቸው!”፡ብትለኝ፥ከቃላትም፡ይልቅ፥ልቤ፡ላይ፡የተነፈሰችባት፡ሆኖ፡ተሰማኝ። 

  ~*~   ~*~   ~*~   ~*~   ~*~   ~*~   

“አንቀጸ ብርኀን” የተስኘውን ምስል የሳለው ደራሲው ጃርሶ ኪሩቤል ሞትባይኖር ነው።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.