ወይዘሮ ሲልቪያ ፓንከርስት እንግሊዛዊቷ የኢትዮጵያ ጀግና፤ ኪዳኔ ዓለማየሁ ፤ ሰኔ 18 ቀን 2011 ዓ/ም

fullsizeoutput_750f

ሲልቪያ ፓንክረስት [ሚያዝያ 27፣ 1874 – መስከረም 17፣ 1953 .ኢ.አ] (ሀ) 

መግቢያ

ይህ አጭር ጽሑፍ (1) የሚያተኩረው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ወለተ ክርስቶስ ተብላ በተሰየመችው፣ የዓለም ስሟ ሲልቪያ ፓንከርስት በሆነው፣ ኢትዮጵያ በፋሺሽቶች በተወረረችበት ጊዜ ከዚያም በኋላ ሌሎች ቅኝ ገዢዎች ሊቀራመቷት በቋመጡበት ዘመን በሚያስደንቅ ጀግንነት 20 ዓመት ሙሉ በታገለችው፣ በተከበረች፣ ወይዘሮ የሕይወት ታሪክ ላይ ነው።

ሲልቪያ ፓንከርስት እ..አ በ1882 እንግሊዝ ሐገር ተወልዳ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው እ..አ መስከረም 27 ቀን 1960 አዲስ አበባ ነበር። አስከሬኗ የተቀበረውም ወለተ ክርስቶስ ተሰኝታ እንደ ሌሎች ታላላቅ አርበኞች ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ ልዑል አልጋ ወራሽ አስፋ ወሰንና ሌሎች ክቡራን በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ነበር። የ50ኛው ዓመት መታሰቢያዋ መስከረም 17 ቀን 2003 /ም በቅድስት ሥላሴ ቤ/ክ ተከብሯል።

ከዚህ በታች በዝርዝር እንደሚቀርበው ፋሺሽቶችና በጊዜው የነበረው የእንግሊዝ መንግሥት ኢትዮጵያን ለመቆራረስ የነበራችውን ዓላማ በመቃወም  ለኢትዮጵያ ነጻነት በሙሉ ቆራጥነት ባከናወነችው ከፍ ያለ ተጋድሎና ላስገኘችው አመርቂ ውጤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለውለታዋ ነው። በተጨማሪም፤ ሲልቪያ ፓንከርስት ካከናወነቻቸው ከፍተኛ ተግባሮች ውስጥ ልእልት ጸሐይ ሆስፒታልን ለማሠራት የሚያስፈለገው ገንዘብ እንዲዋጣ ማድረጓ፣ የኢትዮጵያ ሴቶች መብት እንዲከበርና ፓርላማውም እንዲሻሻል ያደረገችው ጥረት ሁሉ ይጠቀሳል።

ሲልቪያ ፓንከርስት በዜግነት እንግሊዛዊት ብትሆንም በተጨባጭ ተግባሯ ግን የኢትዮጵያ ጀግና የነበረች ናት። ይህ ጽሑፍ ስለዚህች ጀግና በቂ ግንዛቤ እንዲኖር የሚጥር ከመሆኑ ሌላ  ይህን ለመሰለ ከፍ ያለ ጥረትና ተጋድሎ ተገቢውን ዋጋ የሚከፍል ኢትዮጵያዊ ትውልድ ስላለ፣ ለወይዘሮ ሲልቪያ ፓንከርስት የጸረፋሺሽትና ጸረቅኝ አገዛዝ አቅዋም፣ ለኢትዮጵያ ያበረከተችው መስዋእትነትና አርአያነት ታውቆና ተከብሮ እንዲኖር ተገቢው ልዩ መታሰቢያ እንዲቆምላትና በስሟ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም የሚያስገኝ የመታሰቢያ አገልግሎት ተቋም እንዲቋቋም ለማሳሰብ ነው።

በተጨማሪም፤ ታዋቂው የሲልቪያ ፓንከርስት ልጅ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንከርስት፤ ለብዙ ዘመን በማስተማርና ስለ ኢትዮጵያ በመጻፍ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ያበረከተ መሆኑን ለማስታወስና ባለቤቱም ሪታ ፓንከርስት የቤተሰቡ የጀርባ አጥንት በመሆን ኑሯቸውን በአዲስ አበባ አድርገው ሁለቱም ከዚህ ዓለም በሞት ስለ ተለዩ፤ ለልጃቸው ለዶር. አሉላ ፓንከርስትና ለቤተሰቡ እግዚአብሔር ያጥናችሁ ለማለት ነው።

fullsizeoutput_750c

ሪቻርድ ፓንከርስትና ባለቤቱ ሪታ ፓንከርስት በአዲስ አበባ (ለ)

2. ሲልቪያና ኢትዮጵያ እንዴት ተገናኙ

ሲልቪያ እድሜዋ 20 ዓመት ሲሆን የሞዜይክ (mosaic) ስነ ጥበብ ለማጥናት እ..አ በ1902 ቬኒስ ከተማ፤ ኢጣልያ ሔዳ ስለ ነበር ስለሃገሩ ያደረባት ልዩ ዝንባሌ ከዚያን ጊዜ ጀመረ። በወጣትነት እድሜዋ የነበራት ትኩረትና ስትታገልለት የነበረው ዓላማዋ የእንግሊዝ ሴቶች የመምረጥ መብት እንዲኖራቸው ለማድረግ ቢሆንም እ..አ በ1919 ለጉብኝት ቦሎኛ ከተማ፤ ኢጣልያ በነበረችበት ጊዜ የሙሶሊኒ ወንበዴዎች (“ስኩዋድሪስቲ”) ተራውን ሕዝብ ሲደበድቡ ተመልክታ የትግልዋ ትኩረት ፋሺሽቶችን በመቃወም ላይ አነጣጠረ። (2) የጸረፋሺሽት አቅዋሟ ተጠናክሮ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያተኮረው ግን ኢጣልያ እ..አ ታህሣሥ 5 ቀን 1934 ወልወል፤ ኢትዮጵያ ላይ በፈጸመቺው ወረራ ምክንያት ነበር።

የሙሶሊኒ ዓላማ ኢትዮጵያን በሙሉ ለመውረር መሆኑን በመገንዘብ ሲልቪያ ፓንከርስት በጊዜው የነበረው የመንግሥቶች ማሕበር (League of Nations) ገብቶ በነበረው ቃልኪዳን መሠረት፤ ኢትዮጵያን ከኢጣልያ ወረራ እንዲያድን ብዙ የአቤቱታ ደብዳቤዎች በመጻፍ እንዲሁም ሕዝባዊ ስብሰባዎች በማኪያሔድ ከፍ ያለ ጥረት አድርጋ ነበር። ነገር ግን፤ በተጻራሪው በተለይ የእንግሊዝና የፈረንሳይ መንግሥቶች ከኢጣልያ ጋር በማበር ኢትዮጵያን ለመቀራመት ያድሙ ስለ ነበር ወረራውን የሚያበረታታው እንጂ የሚያቆመው ኃይል አልተገኘም። እንዲያውም ሲልቪያን እጅግ ያስገረማት ክስተት እ..አ በ1935 የእንግሊዝ መንግሥት ስለ ጉዳዩ እንዲያጠና በሰር ጆን ማፊ የተመራ ኮሚቲ አቋቁሞ የቀረበለት አስተያየት፤ ኢጣልያ ኢትዮጵያን ብትወር እንግሊዝን የሚጠቅማት እንጂ የሚጎዳት አለመሆኑን መጠቆሙ ነበር። ከመንግሥታቱ ማህበር አንዱዋ በነበረቺው ኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን ወረራ ድርጅቱ በነበረበት ግዴታ መሠረት ባለማስቆሙ ጠንቁ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት በተከሰተው እልቂት፤ ለአውሮፓ ለራስዋም እንዲተርፋት ሆኑዋል። ሲልቪያም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ እለተ ሞቷ ድረስ ለኢትዮጵያ መብትና ነጻነት ጸንታ ታገለች።

3. የፋሺሽቶች ግፍና የሲልቪያ ትግል

3.1 የፋሺሽቶች ግፍ፤

..አ በ1935-40 ኢጣልያ፤ ለአምስት ዓመቶች ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ በተፈጸመው ግፍ እጅግ ብዙ እልቂትና ውድመት ደርሶ ነበር። በጥይት፣ በቦምብ እንዲሁም በአውሮፕላኖች በተነሰነሰ የመርዝ ጋዝ ጭምር አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ተጨፈጨፉ። ከነዚሁ ውስጥ በ3 ቀኖች ውስጥ አዲስ አበባ ከተማ ብቻ 30,000 ሕዝብ ተገደለ። አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል እንዲሁም ሌሎች ብዙ አርበኞች ተሰዉ። 2000 ቤተክርስቲያኖችና 525,000 መኖሪያ ቤቶች ተደመሰሱ። በተጨማሪም በመርዙ ዝናብ 14 ሚሊዮን እንስሶችና ብዙ እጸዋት ወደሙ። ይህ ሁሉ አሰቃቂ ግፍ ሲከናወን ኢትዮጵያ በአርበኞቹዋ አማካኝነት ከፋሺሽቶቹ ጥቃት የመከላከል ትግልዋን አላቁዋረጠችም ነበር። አጼ ኃይለ ሥላሴም በስደት አውሮፓ ሔደው የዲፕሎማሲ ጥረታቸውን አጠናክረው ቀጥለው ስለ ነበር ከሲልቪያ ፓንከርስት ጋር የተገናኙት በዚያን ጊዜ ነበር። (3)

fullsizeoutput_74d9

 አጼ ኃይለ ሥላሴ በስደት እያሉ ከሲልቪያ ፓንክረስት ጋር (ሐ)

3.2 የሲልቪያ ፓንከርስት ትግል፤ ኢትዮጵያ በተወረረቺበት ዘመን (..1935-41)

ኢጣልያ ወልወል ላይ ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ፤ በመጨረሻም እ..አ በ1941 ድል ተመትታ እስከ ተወገደችበት ድረስ ሲልቪያ ሙሉ የሕይወቷ ዓላማና ተግባር ያደረገቺው ኢትዮጵያን ነጻ ለማውጣት ነበረ ማለት ይቻላል። ያከናወነቻቸው ተግባሮች እጅግ ብዙ ቢሆኑም አንዳንዶቹ ከዚህ በታች ይጠቀሳሉ።

3.2.1 ኢጣልያ የወልወል ትንኮሳዋን አከናውና ኢትዮጵያን በሙሉ ለመውረር በምትንቀሳቀስበት ጊዜ፤ ኢትዮጵያም መከላከል እንድትችል የመንግሥታት ማህበር በጋራ ደኅንነት (collective security) ግዴታው መሠረት ኢትዮጵያን እንዲደግፍ ከመጠየቋም በላይ ፋሺዝም ለዓለም ጠንቅ የሚያመጣ መሆኑን አስገንዝባ ነበር።

() ሲልቭያ ብዙ የአቤቱታ ደብዳቤዎችዋን ለእንግሊዝና ለሌሎች መንግሥቶች እንዲሁም ለመገናኛ ብዙኃን (ለምሳሌ ቢ..ሲ፤ ዴይሊ ኤክስፕሬስ፤ ማንቸስተር ጋርዲያን፤ ዴይሊ ቴሌግራፍ፤ ኒውስ ክሮኒክል፤ ወዘተ) በመጻፍ በኢትዮጵያ ላይ ስለ ተቃጣው የፋሺሽት ወረራ ሰፊ ግንዛቤ እንዲገኝና ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ከፍተኛ ጥረት አድርጋ ነበር። “የአውሮፓ ሕሊና ሞቷል ወይ? በእንግሊዝ ሐገር ታማኝ አስተሳስብ ጠፋ ወይ?” እያለች ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ የአውሮፓን ሕዝቦች ስሜት ለመቀስቀስ ሞክራ ነበር።

() ኢትዮጵያ በባሪያ ንግድ ትጠቀማለች በማለት ፋሺሽቶች ያሰራጩ የነበረውን ሐሰት ፕሮፓጋንዳ በመቃወም አጋልጣለች።

() ለአፍሪካም የዘለቄታ ጥቅም በማሰብ፤ በጸረፋሺሽትና ጸረኮሎኒያሊስት መርሆ ተሠማርተው የነበሩትን እነጆሞ ኬንያታን (ኬንያ)፤ ኤሚ አሽዉድ ጋርቪ (ጃሜይካ) እንዲሁም የሙሶሊኒ ተቃዋሚ የነበሩ ጣልያናዊ ታጋዮችን ጭምር በኢትዮጵያ ጉዳይ እንዲተባበሩ አድርጋ ነበር።

() በጊዜው በለንደን የኢትዮጵያ ሚኒስትር (አምባሳደር) ከነበሩት ከዶ/ር ወርቅነህ እሸቱ (ቻርልስ ማርቲን) ጋር በመተባበር እንዲሁም ከእቴጌ መነን ጋር በመጻጻፍ በኢትዮጵያ በኩልም ስለ ነበረው ሁኔታ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖራት ታደርግ ነበር።

() ለኢትዮጵያ ነጻነት ታከናውነው በነበረው ትግል እንዲረዷት ታዋቂ ከነበሩ የእንግሊዝ ምሁራን፤ ለምሳሌ ፕሮፌሰር ኤፍ.ኤል.ሉካስ፤ እንዲሁም እንደ ፊሊፕ ኖዌል ካሉ የፓርላማ አባሎች ጋር በቅርብ እየተመካከረች ትሠራ ነበር።

3.2.2 ..አ ከጥቅምት 1935 ጀምሮ ኢጣልያ የኢትዮጵያ ወረራዋን ስትቀጥል በምእራባውያን በኩል በተለይ የእንግሊዝና የፈረንሳይ መንግሥቶች የጦር መሣሪያ ለኢትዮጵያ እንዳይደርሳት ማእቀብ ሲጥሉ በሌላ በኩል ለኢጣልያ ነዳጅ ጭምር በማቀበል የግፍ ወረራው እንዲሳካላት አድርገው ነበር። በመጨረሻም ኢጣልያ አዲስ አበባንና አብዝኛዎቹን የኢትዮጵያ ከተሞች ስትቆጣጠር የእንግሊዝ መንግሥት የቅኝ ግዛት ሥልጣኗን አውቆላት ነበር። (4) ... 1935-40 ኢጣልያ ኢትዮጵያን ከሞላ ጎደል በተቆጣጠረችበት ዘመን፤ ሲልቪያ ፓንከርስት ያላቋረጠ እጅግ ከፍ ያለ የተቃውሞ ጥረት ታከናውን ነበር። ካከናወነቻቸውም አያሌ ተግባሮች ውስጥ ሊጠቀሱ የሚገባቸው፤

() ለዓለም መንግሥታት ማኅበር፣ ለዊንስተን ቸርቺል፣ ለእንግሊዙ ሊቀጳጳስ፣ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሩዝቬልትና ለሌሎችም ኃያላን የአቤቱታ ደብዳቤዎች መጻፏ፤

() ..አ በ1936 “አዲስ ዘመንና የኢትዮጵያ ዜና” (5) የተሰኘ ጋዜጣ አቋቁማ ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ግንዛቤ እንዲዳብር ማድረጓ፤

() ..አ በየካቲት 1937 አዲስ አበባ ብቻ 30,000 ሕዝብ ሲጨፈጨፍ የጦር ወንጀሉ በይፋ እንዲታወቅ ማድረጓ፤

() አጼ ኃይለ ሥላሴ ለንደን ሲደርሱ በክብር ተቀብላ በየጊዜው ቃለመጠይቆች እያከናወነች፤ ባቋቋመችው ጋዜጣ አማካኝነትና በነበራት ሰፊ ሕዝባዊ ግንኙነት ንጉሠ ነገሥቱ ድጋፍ እንዲያገኙ ከፍ ያለ ጥረት ማድረጓ፤

() የዓለም መንግሥታት ማሕበር ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ በሚወያይበት ጊዜ ጄኔቫ ድረስ በመመላለስ መልእክተኞቹን በማነጋገር ኢትዮጵያ ለጊዜው በኢጣልያ ብትወረርም የማህበሩ አባልነቷ አንደተጠበቀ እንዲቆይና ሌላ ድጋፍም እንድታገኝ ከፍ ያለ ጥረት ማድረጓ፤

() ብዙ ምሑራንን፣ የሰብአዊ መብት ደጋፊዎችን፣ የፓርላማ አባሎችን፣ የቤተክርስቲያን መሪዎችን፣ ወዘተ. በማስተባበር ብዙ አቤቱታዎችንና መግለጪያዎችን በሰፊው በማሰራጨትና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን በማከናወን የእንግሊዝ መንግሥትን ፖሊሲ ለማስቀየርና እንዲያውም ከአርበኞቻችን ጋር በመተባበር ኢጣልያኖችን ከኢትዮጵያ ለማስወገድ እጅግ ከፍ ያለ ጥረት ማድረጓ፤

() ያከናወነቺው ባለብዙ ዘርፍ ያላሰለሰ የፖለቲካ ትግል እንግሊዞች የኢትዮጵያን አርበኞች ጦር ደግፈው የኢጣልያ ግፈኛ ጦር ድል ተመትቶ እ..አ በ1941 የኢትዮጵያ ነጻነት እንዲረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቷና ሌሎችም ብዙ ምሥጉን ተግባሮቿ ሁልጊዜም የማይረሱ ናቸው። 

(ሲልቪያ ፓንከርስት በጣሊያንና ኢትዮጵያ መካከል ከ1935-40 ዓ.ፈ በተደረገው ጦርነት ኢትዮጵያን በመደገፍ ታትመው የነበረ ጋዜጣ፤)

4. የእንግሊዞች መቋመጥና የሲልቪያ ትግል

..አ በ1941 ኢትዮጵያ ከፋሺሽት ኢጣልያ ነጻ ከወጣች በኋላ ቀጥሎ ያጋጠማት ከባድ ችግር የእንግሊዝ መንግሥት ኢትዮጵያን በቁጥጥሯ ስር (protectorate) ለማድረግ፤ ይህ ሳይቻል ደግሞ ኤርትራን፣ ኦጋዴንንና ቦረናን ለመቆጣጠር መወሰኗ ነበር። በዚህም ረገድ ሲልቪያ ከአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ጋር በመተባበር ከፍተኛ ትግል አከናውና የእንግሊዝ መንግሥት እኩይ ዓላማ እንዲከሽፍ እጅግ ጠቃሚ  አስተዋጽኦ አድርጋለች፤

() በዚያን ዘመን ሲልቪያ ለእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ለፓርላማው፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴራቸውና ለሌሎችም በምትጽፋቸው አቤቱታዎችና በምታከናውናቸው የማጋለጥና የተቃውሞ ተግባሮቿ እንደ ኮሎኔል ጊልበርት ማክበረት የነበሩ ቁልፍ ባለሥልጣኖች ስለ ሲልቪያ የሚሰማቸውን ቁጣ ይገልጹ ነበር። ቢሆንም ለኢትዮጵያ ነጻነት በነበራት ጽኑ እምነት ማንም ሊያንበረካት አልቻለም።

()  በጊዜው የነበሩት የእንግሊዝ መሪዎች ቢቃወሟትም ኤርትራ ከእናት ሐገርዋ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል አስደናቂ ጥረት አድርጋ ነበር። እ..አ በህዳር 1941 የእንግሊዝ መንግሥት ኤርትራን ለኢትዮጵያ ማስረከብ ይገባታል ብላ አጠንክራ ጠይቃ ነበር።

() እንግሊዞች ኤርትራ ውስጥ በተለይ ምጽዋ የነበረውን ጠቃሚ ንብረት እያወላለቁ ሲያግዙ ሲልቪያ ተቃውሞዋን አሰምታ ነበር።

() ኢጣልያኖች ከኢትዮጵያ ከተወገዱ በኋላ እንግሊዞች የኢትዮጵያን ግዛቶች ለመቀራመት የነበራቸው ዓላማ በነሲልቪያ ጠንካራ የ14 ዓመት ትግልና በኢትዮጵያ መንግሥትም አልበገር ባይነት ሳይሳካ በመቅረቱ በመጨረሻው እ..አ በ1954 ከኢትዮጵያ አካባቢ ለቀው ወጡ።

5. ሲልቪያ ያከናወነቻቸው ሌሎች ከፍተኛ ተግባሮች

5.1 ከፋሺሽቶችና ከኮሎኒያሊስቶች ጋር በመታገል ካስገኘችው ከፍተኛ ውጤት በተጨማሪ፤

() የኢትዮጵያ ፓርላማ እንዲሻሻልና ኢትዮጵያውያን ሴቶች በሃገሩ የፖለቲካና የማኅበራዊ ጉዳዮች ያላቸው ተሳትፎ እንዲጠናከር በማሳሰብ ለአጼ ኃይለ ሥላሴ በመጻፍ አመልክታ ነበር። (6)

() ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ሥልጣኔ እየጻፈች ስለ ሃገራችን ሰፊ ግንዛቤ እንዲገኝ አድርጋለች።

() ..አ በ1956፣ በ74 ዓመቷ ከልጇ ከሪቻርድ ፓንከርስት ጋር ወደ ኢትዮጵያ መጥታ ኑሮዋን በመቀጠሏ ከራሷ እጅግ አስደናቂ አገልግሎት በተጨማሪ ልጇም የልጅ ልጇም ቤተሰቡ በሙሉ ለኢትዮጵያ ከፍተኛና የሚያስመሰግን አገልግሎት አከናውነዋል።

() ኢትዮጵያ ከመጣች በኋላም “Ethiopia Observer” የተሰኘ ጋዜጣ አቋቁማ ነበር። ቀደም ብላ ግን ኢትዮጵያ ነጻነቷን ካገኘች አገልግሎቱ አብቅቷል በማለት እንግሊዝ አገር አቋቁማው የነበረውን “New Times and Ethiopia News” የተሰኘውን ጋዜጣዋን እንዲቋረጥ አድርጋለች።

UNADJUSTEDNONRAW_mini_3cd4.jpg

() አዲስ አበባ የሚገኘው እጅግ ጠቃሚ የሆነ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያለው የልዕልት ጸሐይ ሆስፒታል የተሠራው በሲልቪያ ጥረት በተገኘው ገንዘብ ነበር። (7)

6. መደምደሚያና ማሳሰቢያ

6.1 በመጀመሪያ ፋሺሽቶችን ከኢትዮጵያ ለማስወገድ በኋላም ከቅኝ ገዥዎች ጠንቅ ለማዳን ሲልቪያ ፓንከርስት ለሃገራችን ላከናወነችው ከፍተኛ የ20 ዓመቶች ተጋድሎ የኢትዮጵያ ጀግና ልትባል ይገባታል።

6.2 አጼ ኃይለ ሥላሴ ለሲልቪያ ፓንከርስት በጻፉት ደብዳቤ ለሷ የነበራቸውን ከፍ ያለ የአድናቆትና የውለታ ስሜት ገልጸውላት ነበር። አዲስ አበባም አንድ መንገድ በሲልቪያ ስም እንዲሰየም ተደርጎላት ነበር። ይህ ሁሉ ግን መልካም ቢሆንም ካበረከተችው አገልግሎት ጋር የሚመጥን ስላልሆነ ከዚህ የሚከተሉት ሀሳቦች ቀርበዋል፤

() ለሲልቪያ ፓንከርስት ተገቢ የሆነ መታሰቢያ እንዲቋቋምላት ያስፈልጋል። ለታገለችለት ለኢትዮጵያ ሕዝብም የሚጠቅም በሷ ስም የሚሰየም ትምህርት ቤት፣ የምርምር ማእከል፣ የሕክምና አገልግሎት ወይም ተመሳሳይ ተገቢ የሆነ መታሰቢያ ቢሆን ይመረጣል።

() ያሁኑም ሆነ የወደፊቱ ትውልድ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ስለ ሲልቪያ ፓንከርስት ተጋድሎ እንዲሁም ታዋቂ የሆነ ምሁር ልጇ ሪቻርድ ፓንከርስት ስላበረከተው አገልግሎት በአማርኛና በሌሎችም ዋና የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ተጽፎ እንዲሠራጭ ማድረግ ይጠቅማል።

() ከላይ የተጠቀሱትን ሀሳቦች ለመተግበር የኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ምሁራን፣ የጥናት ማእከሎች፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ታጋይ ድርጅቶች፣ ሀሳቡን የሚደግፉ ግለሰቦችና ግላዊ ተቋሞች፤ እንዲሁም የሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካሎች የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱና በአፈጻጸምም እንዲተባበሩ በትህትና አሳስባለሁ።

6.3 በአሁኑ ዓመት የኢትዮጵያ ጀግናዋ፣ ወለተ ክርስቶስ- ሲልቪያ ፓንከርስት፤ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየች መስከረም ሲመጣ 59 ዓመት ይሆናታል። ቸሩ የኢትዮጵያ አምላክ ነፍሷን ይማርልን እንላለን። ስላበረከተችው ከፍተኛ አገልግሎት ተገቢ መታሰቢያ እንደሚቆምላት ጽኑ ተስፋ አለኝ። ለማንኛውም ዘለዓለማዊ ምሥጋና ይድረሳት። (8)

የግርጌ ማስታወሻዎች

(1) ስለ ሲልቪያ ፓንከርስት ብዙ ተጽፉዋል። ለዚህ ጽሑፍ ዝግጅት መሠረት የሆነው ዋናው መጽሐፍ፤ በሪቻርድ ፓንከርስት የተጻፈው፤ “Sylvia Pankhurst, Counsel for Ethiopia”, (2003) የተሰኘው መጽሐፍ ነው።

(2) እንዲሁም እንግሊዝ ሃገር በስደት ይኖር ከነበረው ኢጣልያዊ፤ ከሲልቪዮ ኮሪዮ ጋር ተፋቅራ ሪቻርድ ፓንከርስት ተወለደ።

(3) በዚህ አጋጣሚ መገለጽ ያለበት ታሪካዊ ሐቅ የፋሺሽቶች ጦር ወደ ኢትዮጵያ የዘመተው በቫቲካን ተባርኮ፣ በጊዜው በነበሩት በፖፕ ፓየስ 11ኛ ድጋፍ የነበረ መሆኑን ነው። ለዚህ የጦር ወንጀል ትብብሯ ቫቲካን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ ለማድረግ ዓለም አቀፍ አቤቱታ እየተፈረመ ነው። ለዝርዝር ግንዛቤ፤ “ዓለም አቀፍ ሕብረት ለፍትሕ፤ የኢትዮጵያ ጉዳይ” (Global Alliance for Justice – The Ethiopian Cause) የተሰኘው አካል በማኪያሄድ ላይ ስላለው ጥረት ድረገጹን http://www.globalallianceforethiopia.netን መመልከትና አቤቱታውንም መፈረም ይቻላል።

4) ፋሺሽት ኢጣልያ በኢትዮጵያ ላይ “ድል” አገኘች በማለት እውቅና በመስጠት የመጀመሪያዋ አገር ፖላንድ ነበረች።

(5) New Times and Ethiopia News

(6) ሲልቪያ ሪፐብሊካን መሆኗንና ኢትዮጵያንም ትደግፍ የነበረው በጸረፋሺሽትነት እምነቷ መሠረት መሆኑን ለአጼ ኃይለ ሥላሴ ግልጥ አድርጋ ነግራቸው ነበር።

(7) የልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል ወደ የጦር ኃይሎች ሆስፒታልነት ከመለወጡ በፊት የሐኪሞችና የሌሎች የጤና ባለሙያዎች የመጀመሪያው ማሠልጠኛ ተቋም ስለ ነበር ለሐገሪቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ዶክተር ወንዱ ዓለማየሁ ገልጸዋል።

(8) በዚህ አጋጣሚም ለልጇ ለዶክተር ሪቻርድ ፓንከርስት፣ ለባለቤቱ ለሪታና ለቤተሰቡ በሙሉ የእናታቸውን ፈለግ በመከተል ለኢትዮጵያ ላበረከቱትና በማበርከት ላይ ላሉት ከፍተኛ አገልግሎት ልባዊ ምሥጋና ይድረሳቸው። የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንከርስትና የክብርት ባለቤቱ የሪታ ፎቶግራፍ ከዚህ በታች ቀርቧል።

የፎቶግራፍ  ምንጮች

(ሀ) The Pankhursts – The History of One Radical Family by Martin Pugh
(ለ) Reminiscences – Early Days by Richard and Rita Pankhurst
(ሐ) Pinterest
Abstract
SYLVIA PANKHURST, THE ETHIOPIAN PATRIOT FROM BRITAIN
This article is mainly about the renowned lady from Britain, Ms. Sylvia Pankhurst (1882-1960), who due to her great service for Ethiopia’s liberation from Fascist Italian occupation (with the Vatican’s complicit support) during 1935-41, and subsequent 20-year service, deserves to be recognized as an Ethiopian patriot by erecting a monument in her name. The Italians had perpetrated the loss of one million Ethiopians, the destruction of 2,000 churches, 525,000 homes and 14 million animals as well as the looting of vast quantities of Ethiopian properties.  She had utilized various methods of appeals to the British and other Governments including USA as well as the League of Nations at the time plus establishing a newspaper to promote the cause of liberation of Ethiopia. Sylvia Pankhurst moved to Ethiopia along with her son and made numerous contributions including an assistance for the establishment of Princess Tsehay  Hospital, the promotion of women’s rights and the strengthening of the Ethiopian Parliament as well as the establishment of a newspaper called “The Ethiopia Observer”. It is now 59 years since Sylvia Pankhurst passed away and buried at the Qidst Selassie Church in Addis Ababa with a baptismal name of Wolette Kristos in the presence of the late His Imperial Majesty, Emperor Haile Selassie I and other prominent Ethiopian officials. It is the view of this author that if there is one person who deserves recognition for the fight against the criminal Fascist Italian occupation of Ethiopia, it is Sylvia Pankhurst. There were several foreigners who have made significant contributions to the cause and development of Ethiopia who deserve such recognition. The adoption of a culture of recognizing deserving individuals is a very worthy cause that the Ethiopian government needs to consider by institutionalizing a system of immortalizing such personalities. Sylvia’s son, Prof. Richard and his wife, Rita, both of whom have passed away, are briefly mentioned in the article due to their services in Ethiopia.

 

 

 

 

 

 

 

 

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.