የአስማት ጸሎት (ሳዶር አላዶር) ጌታቸው ኃይሌ ኒው ዮርክ ከተማ፤ ዩናይትድ ስቴትስ ሚያዝያ 15 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጸሎት የማንኛውም ችግር መፍትሔ እንደሆነ ታስተምራለች። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸልይዋል። ደቀ መዛሙርቱም እንዴት እንደሚጸልዩ ጠይቀውት አቡነ ዘበሰማያትን እዚያው እፊታቸው ደርሶ አስጠንቷቸዋል። ደቀ መዛሙርቱ በጸሎት ኀይል ብዙ ተአምራት ሠርተዋል። እኛንም፥ “ከናንተ ማህል ማንም መከራ ቢደርስበት ይጸልይ፤ ደስተኛም ከሆነ፥ የምስጋና መዝሙር ይዘምር። የታመመም ካለ፥ ካህናትን ይጥራና አከላቱን በዘይት ቀብተው የጌታን ስም ጠርተው ይጸልዩበት። የእምነት ጸሎት በሽተኛን ያድናል” ይሉናል (ያዕ ፭፡፲፫፲፭)። ይኸ ብቻ አይደለም። ተራ ወይንና ተራ ዳቦ ወደ ቅዱስ የጌታ ደምና ሥጋ የሚለወጠው በጸሎት መሆኑ ከጥንት ጀምሮ የምናምነው ነው።

የጸሎቱ ዓይነቶች በብዙ ጥንቃቄ እንዳልደረሱን ከአንዳንድ ሁኔታዎች ለመታዘብ ይቻላል። ለምሳሌ፥ ከቅዳሴ በፊት የምትነገር “[በእንተ] ትምህርተ ኅቡኣት” የምትባ አጭር ጸሎት አለችን። የስሟ ትርጓሜ፥ “[ስለ] ድብቅ ነገሮች ትምህርት” ማለት ነው። በዚህ ጸሎት ውስጥ “ተገምረ በማኅፀነ ድንግል ተኀቢኦ ለኵሉ ኀይል እለ በሰማያት ማኅደር ወለእለ ይትቃወማ ኀይል በኢያእምሮ ሰወሮ . . .” (ማደሪያቸው በሰማያት ከሆነው ኀይል ሁሉ ተደብቆ በድንግል ማኅፀን ተቻለ፤ [ታምሩን] የሚቃወማትን ኀይልም በአለማወቅ ደበቀው . . .) የሚል አንድምታ የሚያሻው ንግግር አለበት። ድብቁ ከማን ነው? ከሰይጣን ከሆነ የሰይጣንን ኀይል ማጋነን ነው።

አንዳንድ ደብተራዎች ከዚህ የሚረዱት ሰይጣን የሚሸነፈው በምስጢር ኀይል ነው የሚል ነው። በዚህ ላይ፥ ቅድስት ማርያም የጸለየቻቸው ጸሎቶች ናቸው የሚባሉ “ባርቶስ” እና “ሰኔ ጎልጎታ” የሚባሉ ንኡሳት መጻሕፍት አሉን። እነዚህና “ነገረ ማርያም”፥ አምላክ የሚሰማው ስውር ስሞቹን (አስማት) እየጠሩ ሲጸልዩለት ነው የሚል ስሕተት አሉባቸው። ድርሳነ ሚካኤልም የሚጸዳ ነገር አለበት።

አምላክ የምስጢር ስም የለውም፤ የመጸለያ ምስጢር ስሞች የሚባሉ ቃላት የሉም” ሲሏቸው፥ ክርስቶስ የኢያይሮስን ልጅ ሊያድናት ሲጸልይ፥ “ጣሊታ ኩሚ” (ማር ፭፡ ፵፩)፥ በመስቀል ላይ ሆኖ ሲጸልይ፥ “ኤሎሄ ኤሎሄ ኤልማስ ላማ ሰበክታኒ” (ማቴ ፳፯፡፵፮) ብሎ ስውር ቃላት ተጠቅሟል ይላሉ። ግን እነዚህ ሁሉ ሳይተረጐሙ ተጠቅሰው ነው እንጂ፥ አስማት አይደሉም። ክርስቶስ ይናገርበት በነበረው ቋንቋ የተናገራቸው ናቸው። ተተርጕመው ቢሆን ኖሮ “ጣሊታ ተነሽ ቁሚ”፥ “አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ?” ማለቱን እናይ ነበረ።

በባህል ሲወርድ ሲዋረድ እንደደረሰን፥ አይሁድ ክርስቶስን ሲሰቅሉት በአምስት ምስማሮች (ችንካሮች) ቸንክረውት ነበር። እነዚህ ምስማሮች (ችንካሮች) በግሪክኛ ስም አላቸው፤ (1) ሳዶር፥ (2) አላዶር፣ (3) ዳናት፥ (4) አዴራ፥ (5) ሮዳስ ይባላሉ። እነሱንም የችንካሮቹ ስሞች እንደሆኑ ከማቆየት አልፈው፥ የአምላክ የምስጢር ስሞች ከሚሏቸው አስማት ጋራ ደባልቀው፥ ለመፍትሔ ሥራይ (መርዝና ድግምት ማርከሻ መዳኒት) የጸሎት ክፍል አደረጓቸው።

ሥራይ የመርዝ ማርከሻ መዳኒት ቢባልም፥ አብዛኛውን ጊዜ በሽታው ርኩስ መንፈስ (ጋኔን) ነው። ጋኔን ሰውን ይይዛል፤ በሽታ ያስለክፋል። በባህላችን እምነት፥ ማናቸውም በሽታ ምንጩ ጋኔን (evil spirit) ነው። ጋኔን የአምላክ ስም ሲጠሩበትና መስቀል ሲያሳዩት ይተናል። ስመ አምላክ ጠርቶ የተጸለየበት ጠበል ጋኔን ካመጣው በሽታ መፈወስ ይቻላል። ጸሎቱን በብራና ላይ ጽፎ በልጅ አንገት ላይ ቢያንጠለጥሉት፥ አጋንንትን ያርቃል። አጋንንት ከሚያመጡት በሽታ ይከላከላል።

ችግሩ ጸሎቱ ምስጢራዊ ስመ አምላክ መያዙ ነው። አንዳንዶቹ ስሞች ትርጕማቸውና ምንጫቸው አይታወቅም። አንዳንዶቹ ምንጮቻችው ዐረብኛ ነው። ዐረቢኛውን ደኅና አድርገው ካላወቁ፥ እምነትን የሚያናጋ ነገር ሳይቀር ሊቀዱ ይችላሉ። ለምሳሌ አንድ የአስማት ጸሎር ውስጥ “መሐመድ ስይዱነ” (መሐመድ ጌታችን ነው) የሚል ነገር አገኘሁበት። አንዳንዶቹ ደብተራዎቹ የፈጠሯቸው ይመስላሉ። ለምሳሌ አንድ መጽሐፍ ውስጥ፥ “የመሸን ቀነሸን ያፈዝ ጠርበጡ ራባት ማይ ወልህ ሜድ ርርባል ሚን ካራፉን አሉፍ ፍኑን ሰቂጹን ያህድድ አሴር እምህልና አመጀ በሰልማና አሜን” ይላል። ከዐረብ የጥንቆላ መጽሐፍ ሥርዓት ጠብቆ በጥንቃቄ ያልተቀዳ ሐረግ ሳይሆን አይቀርም።

ጉዳዩ የጥንትና ሊወገድ የማይቻል የቤተ ክርስቲያናችን ችግር ነው። የተከበሩ መምህራን ሳይቀሩ የዚህ መጥፎ ልምድ ሰለባ ሲሆኑ ይገኛሉ። ባህሉን አጥብቀው ከተቃወሙት ዋናው ከ1426 እስከ 1460 .ም የነገሠው አፄ ዘርአ ያዕቆብ ነው። ተጋድሎውን (በግዕዝ) እንዲህ ሲል ነግሮናል፤

“ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ፥ ስሙ፥ እንንገራችሁ፤ በቤተ መንግሥት የነበረውን ዓመፅና ጥንቈላ ከናንተ የደበቅሁት የለም፤ ሁሉንም ነገር ጻፍኩላችሁ እንጂ። ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ፍቅርና ከአምልኮቱ የማበልጠው ነገር የለም። አሁንም በቤተ መንግሥት ስላገኘሁት፥ በወንድሜ በይሥሐቅ ዘመን ስለተጻፈ የአስማት መጽሐፍ እገልጽላችኋለሁ። መጽሐፉ ሁለት ሰዎች ተሸክመውት ሊሄዱ የማይችሉት ትልቅና ከባድ ነው። ተስቦና ማናቸውም ዓይነት በሽታ ሲነሣ፥ የቤተ መንግሥቱ ካህናት ያነቡት ነበረ። ስሞቹ ግን የእግዚአብሔር ሳይሆኑ፥ የሚጠራቸውን እስኪያጠፉት ድረስ የሚረዱ አጋንንት ስሞች ናቸው። እነሆ፥ በእግዚአብሔር ኀይል ደመሰስኩት። ማንኛውንም ሐዋርያት ቈጥረው በሲኖዶሳቸው በሰጡን በሰማኒያ አንድ የሕግ መጻሕፍት ውስጥ የማይገኘውን ስም ከቤተ መንግሥት አጠፋሁ። ወንዶቹንም ሴቶቹንም ልጆቼን እግዚአብሔርን ከማምለክ የሚያስወጡ በሰማኒያ አንዱ የሕግ መጻሕፍት ውስጥ የማይገኙትን ስሞች እንዳይዙም እንዳይደግሙም አስማልኳቸው። ምክንያቱም፥ በጸሎት ጊዜ የጋንንት ስም መጥራት፥ በሌላም ጊዜ ለእርዳታ ማንበብ አጋንንትን ማምለክ ነው። እናንተም የወንጌል ልጆች ሆይ፥ በሰማኒያ አንዱ የሕግ መጻሕፍት ውስጥ የማታገኙትን ስም አትቀበሉ። ሌላ አምላክ በማምለክ እግዚአብሔርን ከማምለክ እንዳይወጡ ኢያሱ የእስራኤልን ልጆች እንዳስማላቸው፥ እኔም የአጋንንትን ስም በመጥራት እግዚአብሔርን ከማምለክ እንዳትወጡ፥በእግዚአብሔር አብ፥ በልጁ በክርስቶስ፥ በሦስተኛው በመንፈስ ቅዱስ አስምላችኋለሁ። ከጦርና ከሌላ አደጋ በአስማት ትድናላችሁ የሚሏችሁን አትስሟቸው። በአስማት ከጦር ይዳን ቢሆን ኖሮ፥ በኮሮጆ በዓሥራ ሁለት ስንዝር፥ በዓሥር ስንዝር በስምንት ስንዝር ክርታስ የተመላ የአጋንንት አስማት ይዞ የመጣው የጥፋት ልጅ በድላይ በዳነ ነበር። በእግዚአብሔር ኀይል በጦር ሜዳ ወደቀ። እኔንም፥ “በጦርነት ጠላትክን የምታሸንፍበትን አስማት እናምጣልህ” ብለውኝ ነበር። እኔ ግን ከእግዚአብሔር ሌላ የሚያድን እንደሌለ ዐውቄ አልተቀበልኳቸውም። እግዚአብሔር በእመቤቴ ማርያም ድንግልና አማላጅነት የጠላቶቼን ድምሳሴ አሳየኝ።”

የሚጠራቸውን እስኪያጠፉት ድረስ የሚረዱ አጋንንት ስሞች ናቸው” ያለው እምነቱን ከመጽሐፈ ቀሌምንጦስ ወስዶ ነው። እዚያ መጽሐፍ ውስጥ አብዛኛው ታሪክ የተጻፈው በምኅጻረ ቃል (በኮድ (code) ስለሆነ፥ ኮዱን የሚፈታው ታሪክ ብቻ ነው። ግን፥ አንድ ቦታ ላይ፥ “ ይነግሥ” (“ ይነግሣል”) ስለሚል አንዳንድ የትግራይ ካህናት ይኸንን ሲያነቡ፥ “ለስ ይነግሣል” የሚለው ደረሰልን ብለው ተደስተው ነበር። ኮዱ ሲፈታ የሚለው ግን “ሐመድ ይነግሣል” ነው። የተጻፈው ነቢዩ መሐመድ ሲነሣ በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰውን ሥቃይ ለማሳየት መሆኑን ልብ አላሉትም። ትንቢቱ ስለ መለስ ባይሆንም የሚደርሰው ሥቃይ በመለስ እጅ ተፈጽሟል። የመለስ መግለጫ (Manifesto) እንደነገረን፥ መለስ የነገሠው የክርስቲያኑን መቋሚያ ለመስበር ነበር።

በመቀጠል ስለ በአንድ ጻድቅ ላይ የደረሰውን እንዲህ ሲል ይተርካል፤ አንድ ጻድቅ ሰው ነበረ፤ ችግር ሲደርስበት አንድ ጽድቅና የማይወድ መንፈስ ከተፍ ይልና ከችግሩ ያወጣዋል። ሰውየው ይህ በጎ ሥራ ሲደጋገምለት ሲያይ፥ “ኧረ ለመሆኑ ማነህ አንተ?” ብሎ ጠየቀው። “ስሜ እስከ ማእዜኑ ነው፤ ደግ ሰው መሆንክን አይቻለሁና ሁልጊዜም እረዳሃለሁ። አንዳች ችግር ሲገጥምህ ‘እስከ ማእዜኑ’ ብለህ ጥራኝ፤ እደርስልሃለሁ” አለው። ሰውየው በእስከ ማእዜኑ በመተማመን በሕይወቱ ተረጋጋ። አንድ ቀን ሳያስበው፥ እገደል ሊገባ ደረሰ። እንደምንም ብሎ ራሱን በማዳን ፈንታ፥ ተዝናንቶ “እስከ ማእዜኑ” ብሎ ጠራው። “እስከ ማእዜኑ” ማለት “እስከ መቼ?” ማለት ነው። አሁን እንግዴህ፥ እስከ ማእዜኑ ደጉን ሰው ለማጥፋት ሲቀናው፥ “እስከ ይእዜ” ብሎ ገፈተረው። “እስከ ይእዜ” ማለት “እስከዚህ ቅጽበት” ማለት ነው።

አፄ ዘርአ ያዕቆብ ያን ያህል ጥሮ፥ የተቀበለው አላገኘም። እንዲያውም፥ ጸሎቱን ቅዱስ ጸሎት ለማስመሰል፥ ከሐዲስ ኪዳን፥ በተለይም፥ ከዮሐንስ ወንጌል የመጀመሪያውን ቃላት፥ “በመጀመሪያ ቃል ነበር፡ ያምቃል እግዚአብሔር ዘንድ ነበር . . .” የሚለውን ጥቅስ የአስማት ጸሎት ክፍል ያደርጉታል። ጸሎቱንና ስሞቹን አምላካዊ ለማስመሰል እንደማንኛውም ቅዱስ ጸሎት፥ “በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ዱ አምላክ ። ጸሎት በእንተ መፍትሔ ሥራይ” እያሉ ይጀምራሉ። ለምሳሌ አንድ ደብተራ አንድ ከሰኞ እስከ እሑድ የሚጸለይ መልክዐ ኢየሱስ ሲደርስ፥ እንዲህ ሲል ይጀምራል፤

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ዱ አምላክ። ጸሎት በእንተ መፍትሔ ሥራይ፤ ሩህ እልቁድሳን ኢላህን።

ሰላም ለሥዕርተ ርእስከ ዘስሙር አብቋሉ፤

ሳዶር፤ ወጽፉቅ ጥቀ ለአርዘ ሊባኖስ አምሳለ ቈጽሉ፤

አላዶር፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናት ዘላዕሉ፤

ዳናት፤ ይጽሐፍ በልሳንየ [ዘአምላክ ቃሉ።]

አዴራ፤ . . . .

ሮዳስ፤ . . .

ትርጕሙም፤

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ፩ አምላክ። ስለ መርዝ መዳኒት ማርከሻ ጸሎት። [በዐረብኛበስመ አብ ወወልድ ወ]መንፈስ ቅዱስ [አሐዱ] አምላክ።

አበቃቀሉ ለሚያምር ለራስህ ጠጉር ሰላም [እላለሁ]

ሳዶር፤ በጣም ጭፍቅ ያለ የሊባኖስ ጥድ ቅጠል ምሳሌው፤

አላዶር፤ ኢየሱስ ክርስቶስ የላይኛው ሊቀ ካህናት።

ዳናት፤ [የአምላክ ቃልን] በምላሴ ላይ ይጻፍ።

አዴራ፤ . . .

ሮዳስ፤ . . .

የአስማት ጸሎቶች “መፍትሔ ሥራይ” ይባላሉ። ብዙ ዓይነት ናቸው። ለዓይነ ጥላ፥ ለራስ ምታት፥ ለጎን ውጋት፥ ለሆድ ቍርጠት፥ ፅንስ፥ ላለማስወረድ (ሾተላይ)፥ ለሚልፈሰፈስ የወንድ ብልት፥ ለትምርት የሚረዳ፥ የሚያፋቅር፥ ወዘተ አሉ። አንዱ ጸሎት “መርበብተ ሰሎሞን” ይባላል። ሰሎሞን ሰይጣናትን የሚያጠምድበት ጸሎት ማለት ነው። አጋንንቱም እንደ ሰው ብሔር አላቸው። ዓይነ መሃይምናን፥ ዓይነ ጋላ፥ ዓይነ ቅማንት ወጋፋት፥ ዓይነ ወይጦ፥ ዓይነ ማያ፥ ወዓይነ ደዋሮ፥ ወዓይነ ዳሞት፥ ሥራየ ጎንደር ወበጌምድር፥ ሥራየ ዳውንት ወመቄት፥ ሥራየ ዋድላ ወመቅደላ፥ ሥራየ ደላንታ ወላስታ፥ ሥራየ አምባሰል ወወገራ፥ ሥራየ አረሚ ወአምሐራ ወዢራ፥ ሥራየ እስላም ወክርስቲያን. . .

የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ተመራማሪዎች (እኔንም ጨምሮ) የተቻለውን ያህል አጥንተዋቸዋል። ግን ብዛታቸው ከፍ ያለ ስለሆነ ገና ብዙ ምርመራ ያስፈልጋቸዋል።  

* * * 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.