ዘረመላዊ ሀብቶች አቅርቦትና ጥቅም ተካፋይነት
(Genetic Resources Access and Benefit Sharing)
[ጤፍ፥ ቨርኖኒያና እንዶድ]
.
ገብርኤል ዳንኤል
(ነሐሴ 2010)
.
ይህ መንደርደሪያ ጽሑፍ የተዘጋጀው ከዛሬ ሃያ አመት በፊት በሰምና ወርቅ ቅጽ 1 ቁጥር 2 ሰኔ 1979 ዓም በሰይፉ በላይ “የፕላስቲክ ኪነ ጥበብና የዘይት ፍሬ ዘሮች” በሚል አርዕስት ሥር ታትሞ ቨርኖንያ ላይ አተኩሮ የወጣውን ጽሑፍ ለማስታወስ ነው። ከዚያም በተጨማሪ በተለያዩ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ሀብቶችና ተመሳሳይ ሁኔታዎች ላይ የተጻፉ ጽሑፎችን ለመዳሰስ ነው።
በከፍተኛ ብዝሀ ሕያወት (biological diversity) ፀጋ የታደለች አገር ናት። ብዝሀ ሕይወት በጣም ሰፊና የተወሳሰበ ዓለም አቀፋዊ ቀልብ የሳበ ከፍተኛ የሀብት፥ ምግብ ዋስትናና ንግድ ተፅእኖ ፈጣሪ ጉዳይ ነው። በኢትዮጵያ ከስድስት ሽህ በላይ የአዝርዕት ዝርያ እንዳሉ ይታወቃል። በባለቤትነት ወይም በብሔረ ሙላድነት (origin) የምትታወቅባቸው የብዝሀ ሕይወት ዝርያዎች በርካታ ናቸው። ከነዚህም መካከል ጤፍ (Teff/ Eragrostis tef)፥ ቡና (Coffee/Coffea arabica)፥ኑግ (Noug or Niger seed/Guizota abyssinicum)፥ቨርኖንያ (Vernonia galamensis)፥ እንሰት (Ensete venticosum)፥ገብስ (Barley/Hordeum vulgare)፥ጫት (Khat/Catha edulis)፥ ዳማከሴ (Ocimum lamifolium)፥ሬት/እሬት (Aloe debrana)፥ ጤናዳም (Herb of Grace/Ruta chalepensis)፥ እንዶድ (Endod/Phytolacca dodecandra) ጥቂቶቹ ናቸው። በኢትዮጵያ እነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች በተለያዩ መንገዶች ለሀገር ፍጆታም ሆነ ለውጭ ንግድ ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ይታወቃል። በአዃያው የነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች ጥበቃ፥ እንክብካቤና ለንግድ በሚውሉበት ወቅት የማኅበረሰቡ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በሚገባው መጠን እንዳልሆነ ይገመታል። ሕጋዊና ሕጋዊ ባልሆኑ መንገዶች እየወጡ ያሉ ዘረመላዊ ሃብቶች (genetic resources) በሂደት ከአገሪቱ ባለቤትነት እጅ የመውጣት ዕድላቸው እንዳለም ይገመታል። ይህም አገሪቱ በነዚህ ላይ ያላትን መብትና ተጠቃሚነት ይጎዳል። ባለፉት ዓመታት የዚህ ዓይነቱን ችግር ለመቀነስ የዓለሙ ኅብረተሰብ ተወያይቶበት የባለቤትነትና የጥቅም ተካፋይነት/ተጋሪነት ሥርዐትና ደንብ እንዲተገበር የተለያዩ ሕጎች ወጥተዋል። ኢትዮጵያ እነዚህን ሕጎች በመቀበል ተግባራዊ ለማድረግ በመጣር ላይ ብትገኝም በርካታ ተግዳሮቶችም ገጥመዋታል።
ይህ ጽሑፍ ስለ ኢትዮጵያ ዘረመላዊ ሃብቶች ፥ ብዝሀ ሕይወት፥ ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶች፥ ዘረመላዊ ሀብቶች አቅርቦትና ተጠቃሚነት፥ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የተፈራረመቻቸው የአቅርቦት (የአርክቦት) ስምምነቶች፥ እንዲሁም ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ዙሪያ ላይ መጠነኛ ግንዛቤ ለመስጠት የተዘጋጀ ነው። ለምሣሌነትም ጤፍን፥ እንዶድንና ቨርኖንያን ትኩረት በመስጠት ከላይ በተጠቀሱት ዙሪያ ያለውን ሁኔታ በመጠኑ ያብራራል። የነዚህ ሶስት ዘረመላዊ ሀብቶች ጉዳይ ተመሳሳይ የሚያደርጋቸው ከኢትዮጵያ ወጥተው ከፍተኛ ለሆኑ ዓለም አቀፍ ችግሮች መፍትሔ መሆናቸው ነው። ስለዚህም ለተጠቃሚዎቹ በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገቢ ያስገኛሉ። በተጨባጭ በአካባቢ ጥበቃ አዃያ ቨርኖንያ ለበካይ ኬሚካል ቅነሳ ፥ በጤና አዃያ እንዶድ ለቢላርዚያና፥ ጤፍ ለሲሊያክና ክሮንስ በሽታዎች ባላቸው አስተዋፅኦ ሶስቱም በምጣኔ ሀብትና ህብረተሰብ ደህንነት ጉልህ አዎንታዊ ሚና ይጫወታሉ። ነገር ግን ኢትዮጵያ ከነዚህ ትሩፋቶች እምብዛም እንዳልተጠቀመች የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ። ይህ ጽሑፍ ለመንደርደሪያነት እንዲያገለግልና አንባቢዎች ከዚህ ተነስተው ሰፋ ያለ ዕውቀት እንዲያዳብሩ፥ ጥናት እንዲያካሄዱ ለመገፋፋት ብሎም የጉዳዩን አሳሳቢነትና ጠቃሚነት ተገንዝበው ተቆርቓሪነትን፥ ጥበቃንና ተከራካሪነትን እንዲያስተናግዱም ነው።
.
ስለ ቨርኖንያ በመጠኑ
ቨርኖንያ በአካባብያው አጠራር ፈረንኩዼላ፥ ዽንፋሬ ወይም ኖያ ተብሎ ይታወቃል። በኢትዮጵያ የቨርኖንያ ታዋቂነት የሚጀምረው በ1956 ዓ.ም. የአሜሪካ የእርሻ ሚኒስቴር (ዲፓርትመንት ኦፍ አግሪካልቸር) ባልደረባ የአትክልት ዐዋቂ ሮበርት ፐርዱ ሃረር ውስጥ የአዝርዕት ማጣሪያ ምርመራ (እስክሪኒንግ) ሲያካሄድ ነበር። ፐርዱ መንገድ ዳር እንደአረም የበቀለውን የቨርኖንያ ተክል ፍሬ ወደ አሜሪካ አምጥቶ ለማብቀል ቢሞክርም፥ የአሜሪካ አየር ለቨርኖንያ አመች ስላልሆነ ሙከራው አልተሳካም።
ቨርኖኒይ በተለያዩ የአፍሪቃና ሌሎች አገሮች ይበቅላል። ከአንድ ሽህ ዝርያዎች በላይ ያሉት ተክል ነው። ቨርኖንያ ጋላመንሲስ ኢትዮጲከስ (Vernonia galamensis/ethiopicus) ተብሎ የሚታወቀው ይህ የዘይት አዝርዕት ዝርያ ለኢንዱስትሪ ግብአት ጉልህ ስፍራ ያለውና ተፈላጊነቱም ከፍተኛ ነው። ኢትዮጲከስ የሚለው ቅጥያ ስሙም ሥረ መሠረቱ ከዚሁ ከኢትዮጵያ መሆኑን ጠቓሚ ነው። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ካሉት የዘይት ፍሬ ዓይነቶች መካከል የቨርኖንያ ፍሬ ብቸኛው በተፈጥሮ ኤፖክሲ የተዋሀደው (ኤፖክሲዳይዝድ– epoxidized) የሆነ ቨርኖሊክ አሲድ (vernolic acid) የሚባል አሲድም በውስጡ አለው። ሌሎች የዘይት ፍሬ አሲዶች (ለምሳሌ ከአኹሪ ዐተር [soybean] እና ተልባ [flax] ጥራጥሬ ዘይቶች) የሚገኙት ለተመሳሳይ ጥቅም የሚውሉ ቢሆኑም ይህ ዐይነት ስጦታ በተፈጥሮ አልተሰጣቸውም። ፍሬው ከፍተኛ የዘይት መጠን (40%) ሲኖረው፥ በዘይቱም ውስጥ እስከ 80 በመቶ የሚደርስ ቨርኖሊክ አሲድ ይገኝበታል።
የቨርኖንያ ተክል ምስል
አሲዱ ለተለያዩ የቀለም፥የፕላስቲክ፥የመድኅኒት ወዘተ… መሥሪያ ግብአትነት ያገለግላል። ሌሎቹ የዘይት ፍሬዎች በኬሚካል መንገድ ኤፖክሲ (epoxy) መጨመር (ኤፖክሲዳይዝድ መሆን) ያስፈልጋቸዋል። በዚህ ሂደት የሚያስከትሉት የሀብት ወጭና የአየር ብክለት በቨርኖሊክ አሲድ ስለማይከሰት ቨርኖንያን በጣም ተመራጭ ያደርገዋል። የቨርኖንያን ከፍተኛ ጠቀሜታ በሚመለከት አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፥ አንድ ፓይንት (240 ሚሊ ሊትር) የቨርኖንያ ዘይት በአሜሪካ በዓመት የሚመረተው 325 ሚሊዮን ጋሎን መጠን ቀለም ውስጥ ሲጨመር 72,575 ቶን የአየር ብክለት እንድሚቀንስ ያሳያል። ለቀለም፥ ለሙጫ/ማጣበቂያና ለፕላስቲክ የኤፖክሲ የዓለም ሽያጭ $15 ቢልዮን የአሜሪካ ብር እንደሚደርስ ይነገራል። በተጨማሪም የፕላስቲክ እቃዎች (የህፃናት ጡጦ፥ ፕላስቲክ ሳህንና ተመሳሳይ መገልገያዎች) በሚሠሩበት ወቅት ኤፖክሲን ለማግኘት በሚደረገው ሂደት የሚውለው ቢስፌኖል ኤ (bisphenol-A) የሚባል ንጥረነገር መጠቀም ግድ ይላል። ቢስፌኖል ኤ ካንሰር የማስከተል ሁኔታ ስለሚኖረው፥ ቨርኖንያን በመጠቀም በህፃናት ላይ ሊከሰት የሚችለውን የካንሰር ስጋት ይቀንሳል። ኬሚካሎችን በማምረት ረገድ ከፍተኛ የኤኮኖሚና የአካባቢ ጥበቃ ጠቀሜታ ስላለው የቨርኖንያ የወደፊት ተፈላጊነት በጣም ከፍተኛ እየሆነ የመሄድ ዕድል አለው።
ስለ ጤፍ በመጠኑ
የጤፍ ሳይንሳዊ መጠሪያው ኤራግሮስቲስ አቢሲኒካ ወይም ኤራግሮስቲስ ቴፍ (Eragrostis tef/abyssinica) ይባላል። አቢሲኒካ የሚለው ተቀጥላ ስም መሠረተ–ግንዱ ኢትዮጵያ/አብሲኒያ እንደሆነ ያመላክታል። በኢትዮጵያ ከሦስት መቶ በላይ የጤፍ ዝርያዎች እንዳሉ ይነገራል። ጤፍ ለብዙ ሽህ ዓመታት የኢትዮጵያ መሠረታዊ የምግብ ዓይነት እንደሆነ የታወቀ ነው። የጤፍ ፍሬ የተለያዩ ለሰውነት ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ–ነገሮች አሉት፥ ለአብነትም ፕሮቲን፥ ካርቦሃይድሬት፥ ስብ/ፋት፥ መዐድናት፥ ፋይበርና ቪታሚኖች ይገኙበታል። ጤፍ በእንጀራ መልክና እንዲሁም በቂጣና ገንፎ መልክ ተሠርቶ ይበላል። ለእንጀራም ማባያ የተለያዩ የስጋ፥ የጥራጥሬና የአትክልት ወጣወጥ ስለሚውሉ እንጀራውና ማባያው ተጣምረው ለሰውነት ተስማሚ ምግብ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። የጤፍ ምርት አከመቻቸትና ለምግብ አዋዋል በሚደረገው ሂደት ውስጡ የሚገኘውን ግሉተን (Gluten) የሚባል ፕሮቲን እንዲጠፋ ያደርጋል። ግሉተን በብዙ ጥራጥሬ (ስንዴ፥ ገብስ ወዘተ…) ውስጥ የሚገኝ ሲሆን አንዳንድ ሰዎች ግሉተንን ሰውነታችው ስለማይቓቓመው ሲሊያክና ክሮንስ (Celiac and Crohn’s Disease) ለሚባሉ የሆድ በሽታዎች ምክንያትነት ይጠቀሳል። ጤፍ ግን ግሉተን ስለሌለው (gluten-free) በነዚህ በሽታዎች ለሚጠቁ ሰዎች መፍትሄ ይሆናል ይባላል። ይህም ጤፍን እኛ በተለምዶ ከምንገምተው በላይ በጤናው ዘርፍ ተፈላጊነቱን ከፍ ያደርገዋል። በተጨማሪም የጤፍ ተክል ለከብት መኖነት/ምግብነትና ለቤት ግንባታ ጠቃሚ ነው።
የጤፍ እና የእንጀራ ምስል
ስለ እንዶድ በመጠኑ
የእንዶድ ሳይንሳዊ መጠሪያው ፋይቶላካ ዶዴካንድራ (Phaytolacca dodecandra) ይባላል። እንዶድ በኢትዮጵያ በተለያዩ የገጠር አካባቢዎች እንደ ሳሙና ለልብስ ማጠቢያ ያገለግላል። በ1956 ዓ.ም. ታዋቂው የባዮሎጂ ዶክተር የነበረው አክሊሉ ለማ ለሥራ አድዋ ትግራይ በሄደበት ጊዜ በአጋጣሚ ብዙ ቀንድ አውጣዎች (fresh water snails) በወንዝ ዳር ሞተው አስተዋለ። ምክንያቱንም ሲያሰላስል ሴቶች እንዶድ ተጠቅመው ልብስ ሲያጥቡ የተከሰተ መሆኑን ይገነዘባል። ዶክተሩ የእንዶዱን ቅጠልና ፍሬ በላቦራቶሪ በማጥናት ቀንድ አውጣዎቹን እንደሚገድል አረጋገጠ። ሌላው መረጃ ዶክተር አክሊሉ መጀመሪያ ስለ እንዶድ ቀንድ አውጣ ገዳይነት የሰማው በአራት ኪሎ ኮሌጅ በጥበቃ ይሠሩ ከነበሩ የሰፈር መድኃኒት ቆራጭ ‘ሆድ ቆዝር፥ ደም አስቀምጥ” የሚባለውን ከውሃ የሚገኝ በሽታ እንዶድ ይከላከላል ብለው ነግረውት ነውም ይባላል።
እንዶድ ዕጽዋትና ፍሬ ምስል
ለዚህ ምክንያት የሆነውን መርዛማ ቶክሲን በላቦራቶሪ በመደገፍ ለይቶ አውጥቶታል። በዚህም ግኝት የተነሳ የቶክሲኑ መጠሪያ ለማ ቶክሲን (Lemma Toxin) ተብሎ በራሱ ስም እንዲሰየም ሆኗል። ከሁሉም በላይ ይህን ግኝት ዓለም አቀፋዊ ጠቀሜታ የሚሰጠው 76 የሚሆኑ አገሮች የሚጎዳውንና ስድስት ሚሊዮን ሰዎችን ለበሽታ የሚያጋልጠውን፥ ብሎም ለሁልት መቶ ሽህ ሰዎች ሞት ምክንያት የሚሆነውን ቢላኻርዚያሲስ ወይም ሺስቶሶሚያሲስ (Bilharziasis or Schistosomiasis) የሚባለውን የሆድና የሽንት መተላለፊያ በሽታዎችን መንሳኤ መከላከሉ ነው። ቢላኻርዝያን በአብዛኛው የሚያስከትለው ሽስቶሶማ ማንሶናይና ሄማቶቢየም (Schistosoma mansoni & heamatobium) የሚባሉ ትል መሰል ተውሳኮች (Schistosoma fluke) የሚተላለፈው በቀንድ አውጣው ነው። ስለዚህም ቀንድ አውጣውን ማጥፋት የበሽታው መተላለፊያን ማጥፋት ስለሆነ በሽታው የመተላለፊያ ሰንሰለቱ ስለተበጠሰ መፍትሄው ተገኘ ማለት ነው። ዶክተር አክሊሉ ለማና ባልደረባው ባዮሎጂስት ዶክተር ለገሰ ወልደ ዮሃንስ በዚህ ግኝታቸውና እንዶድ በኅብረተሰቡ ደረጃ ጥቅም ላይ እንደሚውል ስላረጋገጡ በጋራ ዝነኛውን አማራጭ ኖቤል ሽልማት (Alternate Nobel Prize) ራይት ላይቭሊሁድ ሽልማት (Right Livelihood Award of Sweden) በ1981ዓ.ም. እንዲሰጣቸው ሆኖአል። እንዶድ ቀንድ አውጣን እንደሚገድል ሁሉ በአሜሪካ አይዳሆ ዩኒቨርሲቲ ( Idaho University) በተደረገ ጥናት ለዜብራ መስል (Zebra mussel) ማጥፊያም እንደሚጠቅም ተረጋግጧል። ዜብራ መስል በውሃ ውስጥ የሚኖር ሲሼል (seashell) ነው። ዜብራ መስል በውሃ ቱቦች/መተላለፊያ ውስጥ በመጣበቅ ቱቦችን የሚዘጋና የውሃን ፍሰት የሚገታ፥ ለዓሳዎች ምግብነት የሚያገለግሉ አልጌዎችን (algae) የሚበላም ነው። ዜብራ መስል የዓሳ ምርትን መቀነስ ስለሚያስከትል (ዓሳዎችያ የሚመገቡት አልጌዎችን ስለሆነ) ለብዙ አገሮች ከፍተኛ የኤኮኖሚ ጉዳት ያስከትላል። ከመርከቦች ስርም ስለሚጣበቅ የመርከቡን ቅዝፈት ችሎታም ይቀንሳል። የኢትዮጵያ መረከቦችም ሆኑ የኤርትራ የባሕር ሀብቶች ይህ ክስተት ሊመለከታቸው ስለሚችል በዚህ ረገድ ጥናት ማካሄድ ይጠቅማል።
የኢትዮጵያና የብዝሀ ሕይወት (ባዮዳይቨርሲቲ) ዳሰሳና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች
ዘረመላዊ (ጀነቲክ) ሀብት እንዲጠበቅና በዘላቂነት ጥቅም ላይ እንዲውል እንዲሁም ማኅበረሰቦች ያዳበሩት ልማዳዊ ዘረመላዊ ሀብት ክብካቤና አጠቃቀም ሥርዓት እንዲዳብር ልዩ ትኩረት ያስፈልጋል። በቀደሙ ዓመታት በርካታ ዘረመላዊ ሀብቶች በተለያዩ መንገዶች ከሀገር ተወስደው ጥቅም ላይ ውለው ከፍተኛ ገንዘብ እየተገኘባቸው ሲሆን የዘረመላዊ ሀብቶቹ ምንጭ አገሮችና ሕዝቦች ግን የጥቅሙ ተቓዳሾች አልነበሩም። ለዚህም ነው በተባበሩት መንግሥታት አማካኝነት ይህን ዐይነት ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ስምምነቶች የተዘጋጁትና አገሮቹ የፈረሟቸው።
ኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወትን የሚመለከቱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ከተቀበሉና ከፈረሙ አገሮች መካከል ትጠቀሳለች። ከስምምነቶቹ ጥቂቶቹ፥ በተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት የምግብና ግብርና ዕፅዋት ዘረመላዊ ሀብት ዓለም አቀፍ ስምምነትና (International Treaty on Plant Genetic Resources for Food and Agriculture)፥ የብዝሀ ሕይወት ኮንቬንሽን (Biodiversity Convention) ናቸው። ኮንቬንሺኑን ተግባራዊ ለማድረግ የወጣውን የናጎያ ፕሮቶኮልንም (Nagoya Protocol) ኢትዮጵያ ተቀብላለች። ይህ ፕሮቶኮል የዘረመላዊ ሀብቶች አቅርቦትና (አርክቦትና) ሀብቶቹን ከመጠቀም የሚገኙ ጥቅሞች ሚዛናዊና ተመጣጣኝ ተጋሪነትን (Access to genetic resources and fair and equitable sharing of benefits arising from their utilization) ለማስጠበቅ የወጣ ሲሆን ይህም ሰኔ 2004ዓ.ም. በወጣ ዐዋጅ ጸድቓል። እነዚህን በበላይነት ለመምራት ፥ ስምምነቶችን ለመደራደር፥ ለመፈራረምና ለማስተባበር የኢትዮጵያ ብዝሀ ሀብት ኢንስቲትዩት (Ethiopian Biodiversity Institute) በ1996 ዓ.ም. ተሻሽሎ ተቓቁሟል። ይህ ኢንስቲትዩት ከዚህ በፊት የታዩትን የአሠራር፥ የብቃት፥ የግልፅነት፥የቅልጥፍና ወዘተ… ተግዳሮቶች የሚቀርፍ ይሆናል የሚል ተስፋ አለ።
የዘረመል ወይም የጥራጥሬ ባንኮች (Gene or Seed Banks)
ዘረመላዊ (ጀኔቲክ) ሀብቶችንና ብዝሀ ሕይወትን ለመንከባከብና ለመጠበቅ ከሚወሰዱ እርምጃዎች ዋንኛው የዘረመል ባንክ መፍጠር ነው። በድርቅ፥ አዝርዕት በሽታ፥ ለኢንቬስትመንት በሚወሰድ የእርሻ መሬት፥ የገበሬዎች ወደ ከተማ መፍለስ ወዘተ… የተነሳ የብዝሀ ሕይወት መመናመን ጎልቶ የሚታይ ክስተት ነው። በችግር የተነሳ ገበሬው የዘር እህሉን ይሸጠዋል ወይም ለዘር ሳያስተርፍ ለምግብ ያውለዋል። እንዲህ ዐይነቱ ሁኔታ ሲባባስ ሀገራዊ ችግር ይሆንና አገሪቱ የምግብ እህል ተመጽዋች ትሆናለች። ከውጭ በእርዳታ የሚሰጡት የእህል ዘሮች የተዳቀሉ ወይም የተሻሻሉ የሚባሉ (ጀኔቲካሊ ሞዲፋይድ) ናቸው። ገበሬው ያለው አማራጭ እነዚህን መዝራት ስለሆነ ወደፊት ዋናው የአገሪቱ ዝርያ ጠፍቶ በሌላው ይተካል ማለት ነው። አንዳንዴም ተዳቀሉ/ተሻሻሉ የሚባሉት ዓይነቶች ለአልተላመዱት አዝርዕት በሽታ መጋለጥን ፥ የዓየር ለውጥ አለመቓቓምን፥ መሰረተ ሙላድ (origin) ማዛባትን፥ የብዝሀ ሕይወትን ተደጋግፎ/ተጣጥሞ አለመኖርን ያስከትል ይሆናል። እንዲህ ዐይነቱን ሁኔታ ለመከላከልና አገር በቀል የሆኑትን ሃብቶች ለማዳበርና ለማቆየት ነው ዘረመል ባንክ ጠቀሜታው። ገበሬው ከባንኮቹ ጋር በቅርብ በመስራት እንደዚህ ዐይነቶቹን ተግዳሮቶች የመቅረፍ አቅም ሊያዳብር ይችላል።
ኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወትን ለመጠበቅና ለመንከባከብ በጥሩ ምሣሌነት የምትጠቀስ አገር ናት። ይህን በሚመለከት ከወሰደቻቸው እርምጃዎች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ። ሰባት የብዝሀ ሕይወት መአከላት (biodiversity centers)፥ ሁለት የአትክልት ቦታዎች (botanical gardens)፥ ሁለት ዘረመል ባንኮች (gene banks)፥ ሃያ ሦስት የማኅበረሰብ ጥራጥሬ ባንኮች (community seed banks)፥ ዐስራ ሰባት የመስክ ዘረመል ባንኮችና(field gene banks) ዐስራ ስድስት የጫካ ዘረመላዊ ሀብቶች መጠበቂያ ሥፍራዎች(forest genetic resources protection sites)። እነዚህ እርምጃዎች ዝርያዎችን ለመጠበቅና ለገበሬው በማቅረብ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። በብሔራዊ የዘረመል ባንክ 1,021 ዝርያዎች (species)፥ ከመቶ ሽህ በላይ ዘረመል ወይም ዘረመላዊ ቁሳዊ ጥርቅሞች (accessions) ይገኛሉ። የኢትዮጵያ የዘረመል ባንክ አሉ ከሚባሉት የዓለም ዘረመል ባንኮች መካከል አንዱና ትኩረት የተጣለበት እንደሆነ ይነገራል።
ዘረመላዊ ሀብቶች አቅርቦት (አርክቦት) ስምምነቶች
ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ዐስራ ሦስት የሚሆኑ ዘረመል ዝርያዎች/ ዘረመላዊ ሀብቶች አርክቦትና ሃብቶቹን የመጠቀም ስምምነቶች (access and benefit sharing agreements-ABS) ከተለያዩ ኩባንያዎች ጋር ተፈራርማለች።
ዋንኞቹ ስምምነቶች ጤፍን፥ ቨርኖንያን፥ ሞሪንጋን፥ ባሕርዛፍን፥ግዛዋን፥ ቀረጥን፥ ግራርንና ሬትን ይመለከታሉ። ከዚህ በፊት በርካታ የሆኑ ዘረመላዊ ሀብት ዝርያዎች በይፋና በፈቃድ ከአገር የወጡ መሆናችው የታወቀ ሲሆን፥ በድብቅና ህጋዊ ባልሆነ መንገድም (ባዮፓይሬትድ ሆነው) ከአገር የወጡና የባለቤትነት መብት (ፓተንት) ያገኙ እንዳሉ ይታወቃል። ይህ ማለት ኢትዮጵያ እነዚህ የአገር ብርቅዬ ንብረቶች ከእጇ ስለወጣባት መልሳ የማግኘት ዕድሏዋ አስተማማኝ አይደለም። በሁለቱም መንገዶች የወጡትን ዝርያዎች በሕግ ወይም በስምምነት የማስመለስ ወይም የመጋራት ተግባር ተገቢነት ስለሚኖረው የሚመለከተውና ያገባኛል የሚል ሁሉ ሊያተኩርበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ዘረመላዊ ሀብት ጥበቃ በመሠረቱ በተለያዩ በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ምክንያቶች የመጥፋት ወይም የመመናመን አደጋን ለመታደግ የታቀደ ነው። ቢሆንም የብዝሀ ሀብቱ ሕጋዊና ሃገራዊው ባለቤት ካልተሳተፈበትና የማኅበረሰቡ እሽታ (community consent) ከአፋዊነት አልፎ ወሳኝ ሚና የማይጫወት ከሆነ የንብረቱ ባለቤትነት መረጋገጥና ተጠቃሚነት አይኖረውም።
አንዳንዴ ስምምነቶቹ ሕጉን ተከትለው የተፈረሙ ቢሆኑም ቴክኒካዊና ሕጋዊ የማስፈፀምም ሆነ የክትትል ብቃት ወዘተ… ተግዳሮቶች እንደሚታዩባቸው ይታወቃል። ለአብነትም ተግዳሮቶቹ ጎልተው የታዩባቸውን ሁኔታዎች በጤፍ፥ በቨርኖንያና በእንዶድ የታዩትን ክስተቶች በመዳሰስ ችግሩ ምን ያህል ዘርፈ ብዙና ውስብስብ እንደሆነ ከዚህ በታች ማይት ይቻላል።
ቨርኖንያን በተመለከተ
ኢትዮጵያ የቨርኖንያ የዐስር ዓመት ብቸኛነት ያለው (exclusive) ስምምነት የፈረመችው ቨርኒክ ባዮቴክ (Vernique Biotech) ከሚባል የእንግሊዝ ኩባንያ ጋር በ1998 ዓ.ም. ነበር። ኩባንያው በገባው ስምምነት መሠረት ቨርኖንያን በኢትዮጵያ አምርቶ ፍሬውን በመጭመቅና በማዳበር በገበያ ላይ ማዋል ነው። ይህን በሚያደርግበት ጊዜ በመጀመሪያ ቅድመ ክፍያ ማድረግ ከዚያም ሮያልቲና (royalty) ከንግዱ ከሚገኘው ትርፍ ለአገሪቱና ለማኅበረሰቡ ማካፈልና የተለያዩ እንደ ሥልጠና ያሉ ነገሮችን ማሟላት ነው። በተጨማሪም የሚደረጉ ጥናቶችና ግኝቶችን ከአገሪቱ ጋር ማካፈልን ያካትታል።
በተግባር የታየው ሐቅ ግን ከዚህ የተለየ ሆኖ ተገኝቷል። ኩባንያው ተክሉን በእርሻ ሙከራ ቀደም ብሎ አድርጎ አዋጭነቱን ካረጋገጠ በኋላ ነበር ስምምነቱን በ 1998 ዓ.ም. የተፈራረመው። ሲፈራረምም 4,000 ዩሮ (4,000Euro) ብቻ የመጀመሪያ ክፍያ ከፍሏል። ከዚያ በኋላ ግን ክፍያም ሆነ ሌሎች በስምምነቱ የተካተቱ ግዴታዎች ሳይሟሉ መቅረታቸው በተለያዩ ጽሑፎች ታይተዋል። በ2001 ዓ.ም. የውሉ ዐስር ዓመት ከመገባደዱ ቀደም ብሎ ኩባንያው ራሱን ከኩባንያነት በሕጋዊ መንገድ አስወጥቷል። ይህን ወሳኝ ድርጊት ሲወስድ ኢትዮጵያን አላስታወቀም። ኢትዮጵያም ከኩባንያው ጋር የስምምነቱን ተግባራዊነት በቅርብ ክትትል ባለማድረጟ በስምምነቱ መሰረት ማግኘት የነበረባትን ጥቅሞች ሳታገኝ ቀርታለች። ኢትዮጵያ ካለፉትም ሆነ ወደፊት ኩባንያው ከሚያገኘው ጥቅሞች ተካፋይ የመሆን ዕድሏ የመነመነ የሚያደርገው ኩባንያው ኩባንየነቱን ስለሰረዘና አዲሱ በሌላ ስም የተቓቓመው ኩባንያ ስምምነቱ ስለማይመለከተው ነው። አዲሱ ኩባንያ የወረሰውን ዘረመላዊ ሀብት በተለያየ መልክና ሥም በየትም አገር የመጠቀም ዕድል አለው ማለትም ነው። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ይህን የቨርኖንያ ዘይት በመጠቀም የቆዳ በሽታን ለማከም የሚያስችል መድኅኒት እንደተሠራና የባለቤትነት ዕውቂያ (patent) ቨርኖሊክስ ሊሚትድ (Vernolix Ltd) ለሚባል (በፊተኛው ስምምነት ያልተካተተ) ኩባንያ በ2003 ዓ.ም. እንደተላለፈ ታውቓል። በተመሳሳይም በተፈጥሮ የሚገኝ ኤፖክሲዳይዝድ ሞለኩይል (molecule) ራሱን ችሎ በ2002ዓ.ም. ፓተንት ተሰጥቶታል። በኢትዮጵያ በኩል ይህን ጉዳይ በሚመለከት ምን እየተሠራ እንዳለ የታወቀ ነገር እንዳለ ማወቁ ተገቢ ይሆናል።
ጤፍን በተመለከተ
በ1870ዎቹ የእንግሊዙ ኪው ሮያል ቦታኒክታ ጋርድንስ (Kew Royal Botanic Gardens) ጤፍን ከኢትዮጵያ ወስዶ ለሌሎች አገር የተክል ስፍራዎች (ጋርድኖች) በመስጠት ጤፍን በዓለም እንዲተዋወቅ ሚና ተጫውቷል። በአሁኑ ጊዜ ጤፍ በስፋት በአሜሪካና ሆላንድ ተመርቶ ለንግድ ውሏል። የአሜሪካውን በእርሻ መልኩ ለመጀመርያ እንዲስፋፋ ያደረገው በሰላም ጛድነት (Peace Corps) በ1960ዎቹ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው ሰው ወደ አገሩ ሲመለስ ይዞ በወጣው የጤፍ ፍሬ ወይም አንዳንዶቹ እንደሚሉት ዝርያውን ከአንድ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ በማግኘት ነው። እርሻውን በማስፋፋትና “መስቀል ጤፍ” በሚል ስም ጤፍን በተለያዩ የአሜሪካ እስቴቶች በማሰራጨት ንግዱን እያካሄደ ነው። አልፎ አልፎም ዘሩን ለኢትዮጵያ ገበሬዎች እንዲተክሉ በነፃ እንደሚሰጥ ይነገራል። ይህ ሰው “ደሴ” የሚባለውን የጤፍ ዝርያ በ1988ዓም ከሚመለከተው የአሜሪካ መንግስት ቢሮ ለ20 ዓመታት እንደ ፓተንት ያለ ሰርቲፊኬት አውጥቶበት ብቸኛ ባለቤትነትን እንዳገኘበት ይነገራል። ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት ደግሞ አንድ የደች ኩባንያ ሄልዝ ኤንድ ፐርፎርማንስ ፉድ ኢንተርናሽናል (Health and Performance Food International) የሚባል ጤፍን ለተለያዩ ጥቅሞች እንዲያውል አርክቦትንና ጥቅም ተካፋይነትን (Access and Benefit Sharing) ባማከለ መልኩ ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ተፈራርሟል። የኩባንያው ስያሜ የጤፍን ለአትሌቲክስ ጠቃሚነት ለማስተዋወቅና ገበያውን ለማስፋፋት የታቀደ ይመስላል። ዋናው ጥቅሙ ግን ያተኮረው ጤፍ ግሉተን አልባነቱን (gluten-free) በማጉላት ማስተዋወቅና ጤፍን በተለያየ መልክ በማቅረብ ገበያን ማስፋፋትና መነገድ ነው። ግሉተን በስንዴ፥ ገብስ ወዘተ… ውስጥ የሚገኝ ፕሮቲን ሲሆን ብዙ ሰዎች ግሉተን ስለማይስማማቸው ሲበሉት ሲሊያክና ክሮንስ የሚባሉ ህመሞች (Celiac and Crohn’s diseases) ሊያጠቃቸው ይችላል ይባላል። ጤፍ ግሉተን ስሌለው ስንዴና ገብስ ለማይስማማቸው መልካም አማራጭ ሆኖ ተገኝቷል። በዚህ ከፍተኛ ተፈላጊነት በመነሳት የደቹ ኩባንያ ጤፍን በተለያዩ አገሮች በስሙ የባለቤትነት ፓተንት ማወጣቱና ብቸኛ ተጠቃሚ (exclusive beneficiary) መሆኑ ታውቓል። ይህ ሲሆን ግን በአብዛኛው ስምምነቱን ባማከለ መልኩ እንዳልሆነና ኢትዮጵያም ባላወቀችበት አካሄድ እንደሆነ ይገመታል። በመጨረሻም ኩባንያው ከስሬአለሁ (bankrupt) በማለት ራሱን ከስምምነቱ ቢያገልም ዘረመላዊ ሀብቱና የተገኙ የጥናት ውጤቶች በአዲስ ስም ለተፈጠረው ኩባንያ በመተላለፉ ኢትዮጵያ ሕጋዊ መብትዋን ለማስከበር ደንቃራ ሆኖባታል። በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ከዚህ ኩባንያ ጋር በፍርድ ሂደት ውስጥ ትገኛለች። የስምምነቱ አግባብም ሆነ አሠራሩ ክፍተት ስለነበረው፥ ጉዳዩም ውስብስብ ስለሆነ የሕጉ መንገድ አዋጭነት ምን ያህል እንደሚሳካ የሚታወቅ ነገር የለም።
እንዶድን በተመለከተ
እንዶድ ሌላው ከኢትዮጵያ የተወሰደ ዘረመላዊ (ጅኔቲክ) ሀብትና ፓተንት ወጥቶበት አገሪቱም ሆነ ማኅበረሰቡ ተጠቃሚ ሆኑ አልሆኑ የማይታወቅበት ክስተት ነው። በ1982 ዓ.ም. ዶክተር አክሊሉ የክብር ዶክተርነት ለመቀበል አሜሪካ ቶሌዶ ዩኒቨርሲቲ (Toledo University) በሄደበት ጊዜ ከአንድ ባዮሎጂስት ወዳጁ ጋር በነበረ ጭውውት እንዶድ ዜብራ መስል (Zebra mussel) ላይ ምን ሊያስከትል ይችል ይሆን ብለው ይወያያሉ። በአጋጣሚ ዶክተር አክሊሉ እንዶድ ፍሬ ይዞ ስለ ነበር ሙከራውን እዚያው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አደረጉ። እንዶድ ዜብራ መስሉን እንደሚገድል አረጋገጡ። ከዚህ በኋላ ዩኒቨርሲቲው ጥናቱን በስፋት አጠናቆ በጊዜው የዩኒቨርሲቲው አጥኞችና እነ ዶክተር አክሊሉ የፓተንቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ በሚል መግባባት መሠረት እንዶድ የዜብራ መስል ማጥፊያ ተብሎ በአሜሪካ ፓተንት ወጥቶበታል። እነ ዶክተር አክሊሉም ሆኑ አገሪቱ ከዚህ ምን ጠቀሜታ እንዳገኙ ተጨማሪ ጥናት ይጠይቃል። በሌላ ወገን ዩኒቨርሲቲው ያወጣውን ፓተንት ተመጣጣኝ ገንዘብ ተከፍሎት ለኢትዮጵያው እንዶድ ፋውንዴሽን (Ethiopian Endod Foundation) ለማስተላለፍ ፈቃደኛ ነበር ቢባልም መጨረሻው እንዴት እንደሆነ መፈተሽ ይገባል።
የብዝሀ ህይወት ተመክሮዎችና የተገኙ ትምህርቶች
ኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወትዋን ብቻ ሳይሆን በርካታ ሌሎች ንብረትዋን በተለያዩ መንገዶች ከሌሎች አገራት ጋር ስታካፍል ወይም ሲዘረፍባት (biopiracy) ቆይታለች። ከአገር በስምምነትም ሆነ ያላግባብ የተወሰዱ ሀብቶችዋን ለማስመለስ በቅርቡ ጥረቶች እየተደረጉ ያሉ ሲሆን ትልቁ ውጤት የታየው ከሮማ የአኽሱሙ ሃውልት መመለስና በስታርባክስ (Starbucks) ሊወሰድ የነበረው የቡና ንግድ ምልክት (trademark) ባለቤትነት አለመሳካት ናቸው። በብዝሀ ሕይወት መመለስና ጥቅም የመጋራት/መካፈል ጉዳይ ላይ ያተኮረ ጥናት፥ዕቅድ፥ግፊትና በተግባር የተደገፈ ክንውን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። የብዝሀ ሕይወት እንክብካቤና በነዚህ ዙርያ የሚደረጉ ከኢትዮጵያ ወደ ሌላ አገሮች የሚደረገው ዝውውር አግባብ ለብዙ ሰዎች እንግዳና ተገቢው ግንዛቤ ማነስ የሚታይበት ነው። የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢኒስቲትዩትና (Ethiopian Biodiversity Institute) በታዋቂው የአካባቢ ደኅንነትና ዘረመላዊ ፓይረሲ (genetic piracy) ታጋይና የራይት ላይቭሊሁድ አዋርድ (Right Livelihood Award) ተሽላሚ ዶክተር ተወልደ ገብረእግዚአብሔር የሚመራው የኢትዮጵያ አካባቢ ክብካቤ ኤጀንሲ (Ethiopian Protection Agency) ሌሎችም የሚመለከታቸው በስፋት ግንዛቤ መስጠታቸውን ብያጧጥፉ ሕዝቡ የአገሪቱን ንብረት ከመጠበቅም አልፎ ሕጉ የማይፈቅደውን ተግባር እንዳይሠራ ይቆጠባል።
በአጠቃላይ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ የአርክቦትና ጥቅም ተጋሪነትን (access and benefit sharing) መርህ በመመርኮዝ ዐስራ ሦስት የሚሆኑ ስምምነቶች ከተለያዩ ሃገር በቀልና የውጭ ሃገር ኩባንያዎች ጋር ተፈራርማለች። ስምምነቶቹ የተፈረሙት በኢትዮጵያ ወገን ከኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩቱ ጋር ሲሆን ዘረመላዊ ሀብቱ ከመጣበትም ማኅበረሰብ እሽታና ተጠቃሚነት ( community consent and benefit sharing) ጋርም የተቆራኘ መሆኑና መረጋገጡ የተጠበቀ እንደሆነ ይገመታል።
ከዚህ በታች የተጠቀሱት ኢንስቲትዩቱ ስምምነት ከተፈራረማቸው ዝርያዎችና ኩባንያዎች አንዳንዶቹ ናቸው።
ስምምነት የተፈረመባቸው ዕፅዋት |
የተፈራረሙት ኩባንያዎች |
ጤፍ/Teff (Eragrostis tef) | Health and Performance Food International (Dutch) |
ቨርኖኒያ/Vernonia (Vernonia galamensis) | Vernique Biotechnologies (UK) |
ግራር /Grar (Dichrostachys cineria) |
DOCOMO Ltd (India/USA) |
ቀረጥ/QereT (Osyris quadripartitum) | |
ግዛዋ/Gizawa (Withania sominfera) | |
ሬት/Ret (Aloe debrana) | G Seven Trade and Industry plc (Ethiopia) |
የተለያዩ/Miscellaneous (herbs, medicinal plants etc.) | Ariti Herbal Products (Ethiopia) |
የተለያዩ/Miscellaneous (herbs and medicinal plants etc.) | Ecopia – ecological products of Ethiopia (Ethiopia) |
ማሳሰብያ ፡ ከላይ የተጠቀሱት የዓመት አቆጣጠሮች በኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር መሠረት ናቸው።
.
የቃላት ትርጉም
አርክቦት/አቅርቦት – Access
ማኅበረሰብ/ኅብረተሰብ – Community
ብዝሀ ሕይወት – Biodiversity
አዝርዕት ዝርያ – Plant species
ብሔረ ሙላድ – Origin
ዘይት ፍሬ – Oil seed
አኹሪ ዐተር – Soybean
አየር ብክለት – Air pollution
ቀንድ አውጣ – Snail
ዘረመል – Gene
የዘረመል ቁሳዊ ጥርቅሞች – Accessions
ዘረመላዊ ሀብት/ጀነቲክ ሀብት – Genetic resource
ዘረመል ባንክ – Gene bank
ብዝሀ ሕይወት መአከል – Biodiversity center
የአካባቢ ክብካቤ ኤጀንሲ – Environmental protection agency
ጥራጥሬ ባንክ – Seed bank
የማኅበረሰብ ጥራጥሬ ባንክ – Community seed bank
የመስክ ዘረመል ባንክ – Field gene bank
የአትክልት ቦታ – Botanical garden
የጫካ ዘረመላዊ ሀብቶች መጠበቂያ ሥፍራ – Forest genetic resources protection site
ባዮፓይሬሲ – Biopiracy (በድብቅ/ሕጋዊ ባልሆነ ዘዴ ሕይወተ-ሀብትን/ ዘረመላዊ ሀብትን መውሰድ/መስረቅ (unethical/unlawful obtaining of biological materials)
ባለቤትነት – Ownership
ክብካቤ – protection
ጥቅም ተካፋይነት/ተጋሪነት – Benefit sharing
ብቸኛ ተጠቃሚ – Exclusive beneficiary
የማኅበረሰብ እሽታ – Community consent
የሰላም ጛድ – Peace Corps Volunteer (American)
ተግዳሮት – Challenge
.
ዋቢ ጽሑፎች
- “የፕላስቲክ ኪነጥበብና የዘይት ፍሬ ዘሮች” ፥ ሠይፉ በላይ፥ ሰምና ወርቅ፥ 1979 ኢአ።
- ብዕለ ገራህት፥ ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል፥1959 ዓ.ም. ኢአ።
- Plant Genetic Resources of Ethiopia, Engels, Hawkes and Worede, 1991.
- Ethiopia: Country Report to the FAO International Technical Conference on Plant Genetic Resources, 1995.
- Global Potentials and Challenges of Some Ethiopian Germplasm, the Plant Genetic Resources: Review, Eshetayehu Tefera.
- “Material Transfer Agreements on Teff and Vernonia – Ethiopian Plant Genetic Resources”, Journal of Politics and Law, Abeba Tadesse Gebreselassie, 2009.
- The Access and Benefit Sharing Agreements on Teff Genetic Resources: Facts and Lessons, Regine Andersen & Tone Winge, 2012.
- “The interface between access to genetic resources, benefit sharing and intellectual property right laws in Ethiopia: Analysis of their synergies”, Nega Mirete, Addis Ababa University, Dec. 2010.
- Starbucks vs Ethiopia: Corporate strategy and ethical sourcing in the coffee industry, Donald DePass, The Kenan Institute for Ethics.
- Vernonia galamensis : a new crop for Ethiopia, Tesfaye Baye, 2006.
- Oil plants in Ethiopia, Seegeler, 1983.
- A Glossary of Ethiopian Plant Names, Wolde Michael Kelecha, 1987.