“ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ” (ገ/ኢ ጐርፉ)

image

የአቶ ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ አጭር የሕይወት ታሪክ

ከገ/ኢ ጐርፉ

 

አቶ ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ ከአባታቸው ከነጋድራስ አብርሃ ወልዱ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ወለላ ተክሉ በዓድዋ ከተማ እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር በ1905 ዓ.ም. ተወለዱ። አባታቸው ነጋድራስ አብርሃ በከተማው ከነበሩት ታዋቂ ነጋዴዎች መካከል አንዱ ነበሩ። ልጃቸው የቤተ ክህነትን ትምህርት በዘመኑ ገናና ወደ ነበረው የዓድዋ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አስገብተው (ከፊደል መቁጠር ዳዊትና ወንጌል ንባብ ቀጥሎም ለድቁና የሚያበቃውን የቃልና የዜማ ትምህርት) እንዲማሩ አደረጉ።

ይሁንና ገና የዐሥራ ሦስት ዓመት ወጣት እያሉ አባታቸው በድንገተኛ የወባ ሕመም ስለሞቱ ትምህርታቸውን አቋርጠው ሕፃናት የሆኑ ታናናሽ ወንድም እህቶቻቸውን ለማሳደግና እናታቸውን ለመርዳት በሥራ መሰማራት ግድ ሆነባቸው። ንግዱም ከዓድዋ ከተማ ወደ አሥመራ፥ ጎንደር፥ ደሴ፥ መቀሌ እያሉ በበቅሎ ጭነት ማንኛውንም ቀላል ሸቀጣ ሸቀጥ ማዘዋወርና መቸርቸር ነበር። ስለዚህ ዘመን ትዝታ ሲያነሱ፥

“….የመረብ ወንዝ ጎርፍ ሲሞላ የበቅሎ ጅራት የሙጥኝ ብለን ይዘን ነበር የምንሻገረው።… የደባርቅ ቆፈን ምኑ ቅጡ! ጥዋት ከወንዙ ንጹሕ መስተዋት መስሎ የተጋገረውን በረዶ በድንጋይ ሰብረን ውሃ ይቀዳል።…” ይሉ ነበር።

አቶ ዘመንፈስ ቅዱስ እውነትን ለማወቅ መጻሕፍትን ለመመርመር የነበራቸው ምኞትና ጥማት በአባታቸው ሞት ቢሰናከልም እንኳን ንቁ አእምሮ፥ ቅንና ብሩህ ልቦናን ስለታደሉ፥ አዘውትረው ለማንበብና ለመመራመር፥ ከሊቃውንትና ከካህናት ጋር መነጋገርና መከራከር ይወዱ ነበር። ክርክራቸውም ለዘብ ባለ ቀልድና ጨዋታ የተዋዛ እንጂ እንዲሁ ደረቅ የእልህ ክርክር አልነበረም። አገር አገር እየዞሩ ሲነግዱም ከትግርኛና ከግዕዙ ሌላ የጎንደሩንና የወሎውን አማርኛ፥ ዐረብኛና ጣልያንኛ አጥርተው ለማወቅና ለመነጋገር መልካም የሕይወት ትምህርት ቤት ሆነላቸው።

ንግዱ በሚገባ ደርቶ በዓድዋ ከተማ ከታናሽ ወንድማቸው ጋር በመተባበር በጊዜው ድንቅ የተባለ ዘመናዊ ቤት አሠሩ። የንግድ ሱቅም ከፈቱ። ሕፃናት የነበሩ ወንድም እህቶቻቸውንም አሳድገው፥ ለዐቅመ አዳምና ለዐቅመ ሔዋን አድርሰው ዳሩ። እርሳቸውም የአለቃ ተወልደ መድኅን ገብሩ የልጅ ልጅ የነበሩትን ወይዘሮ ሐረጉን አገቡ።

ይህ ሁሉ ሲሆን ዓድዋ በደጃች ገብረ ሥላሴ ልጅ በደጃች ተክለ ሃይማኖት ትተዳደር ነበር። ታላቁ የዓድዋ ሊቅ አለቃ ተወልደ መድኅን ገብሩም ትምህርት ቤት ከፍተው ወንጌልን ስላስተማሩ፥ “ጸረ ማርያም” ተብለው ከተከታዮቻቸው ጋር ብዙ እስራት፥ ንብረት መወረስ፥ ግርፋት፥ በርበሬ መታጠን ሌላም ብዙ ስቃይ ያዩበት ዘመን ነበር። በጊዜው፥ “ጸረ ማርያም” በማለት በትግራይ አነጋገር ለፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታይ የዘለፋ መጠሪያ ነበር። ይኸውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን “ማርያም ታድናለች፤ ታማልዳለች፥” ብላ ስለምታስተምርና እነርሱ ደግሞ፥ “ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌለው ነው፥” በማለት ስለማይቀበሉት፥ “ጸረ ማርያም (የማሪያም ጠላት)” የሚል ስም አተረፉ።

አቶ ዘመንፈስ ቅዱስም ሁሉን ረጋ ብለው መመርመር እንጂ ሌላ ጠላው፥ ወደደው ብለው በሰው ስለማይመሩ፥ ለመማርና ለመመራመር ወደ አለቃ ተወልደ መድኅን ተጠጉ። በዚህማ ምክንያት የአባታቸው የነጋድራስ አብርሃ ንብረት በሙሉ ተወርሷል። አለቃ ተወልደ መድኅን የወጣቱን የዘመንፈስ ቅዱስን አስተዋይ አእምሮ፥ ብሩህና ንቁ ልቡና ተመክልተው፥ “ዛሬ ገና የመንፈስ ልጄን አገኘሁ፥” በማለት ከሁሉ ይበልጥ በማቅረብ የመጻሕፍትን ምስጢር ያስተምሯቸው ነበር። (ስለእኚህ መጽሐፍ ቅዱስን በግእዝ ከዕብራይስጥና ከሲዊድንኛ ቋንቋዎች አመሳክረው ወደ ትግርኛ ቋንቋ ስለ ተረጎሙት ሊቅ፥ ሌላ ራሱን የቻለ ሙሉ ጽሑፍ ለወደፊት ማቅረብ ይቻላል።)

አለቃ ተወልደ መድኅን ሸምግለው ስለነበር አልጋ ላይ ጋደም ብለው፥ አቶ ዘመንፈስ ቅዱስም አጠገባቸው ወንበር ላይ ተቀምጠው “ተግሣጽና ምክር” ከተባለው መጽሐፋቸው አንድ አንድ ምንባቦችን እየመረጡ፥ በተለይ ግጥሞችን እያነበቡላቸው ሳለ እኔ ልጃቸው አዳምጥ ነበርና የግጥም ድምፀ ቃና ለመጀመሪያ ጊዜ በአእምሮዬ የተቀረጸበት በመሆኑ ፈጽሞ አልረሳውም። ታዲያ መጽሐፉ ገና ታትሞ ያልወጣ ስለ ነበር ሁለቱም አንድ አንድ ነጥቦችን ይዘው እየተጨዋወቱና እየተመካከሩ፥ እየተከራከሩና እየተወያዩ ሲያመሹ ያኔ እኔ የአራት ዓመት ወይም የአምስት ዓመት ልጅ ነበርሁ። ይኽን ሁሉ ከመሬት አጎዛ ላይ ተቀምጨ እሰማና እመለከት ነበር።

ዓመት አልቆየም መጽሐፉም ታትሞ ወጣ። ጠዋት ቁርስ ስንበላ የሆነ ሰው ውጭ ሲጣራ ሰማን። አባቴን ጣቢያ እንደሚፈለጉ ነግሮ ይዟቸው ሄደ። አባቴ ታሠሩ። በጨርቅ የተቋጠረ ምሳ ተሸክሜ እስር ቤት ሳመላልስ ትዝ ይለኛል። በዋስ ተፈትተው ቤት ቢመለሱም እንኳ፥ የታተመው “ተግሣጽና ምክር” መጽሐፍ በጠቅላላ ተይዞ የትም እንዳይሸጥ ጥብቅ ትእዛዝ ተላለፈ። በአባቴም ላይ፥ “ቤተ ክርስቲያንን ተሳድቧል” የሚል ክስ ተመሥርቶባቸው ፍርድ ቤት ቀረቡ። ጉዳዩ ይግባኝ እየተባለ ከዓድዋ ወደ መቀሌ፥ ከዚያም አዲስ አበባ ከጠቅላይ ንጉሠ ነገሥት ፍርድ ቤት ድረስ ደረሱ።

“ተግሣጽና ምክር” በፕሮቴስታንትና በኦርቶዶክስ ሃይማኖት መካከል ባሉት ልዩነቶች ቢያተኩርም እንኳን በጣሙን የሚዘልፈው መሠረተ ሃይማኖቱን ሳይሆን ልማድ ይዘው፥ ሃይማኖትን ተመርኩዘው በቤተ ክርስቲያኑ የነበሩትን ጉልህ ጥፋቶች ነው። ከእነዚህም ጥቂቶቹን ለመጥቀስ፥ የፍልሰታ፥ የሁዳዴ፥ የረቡዕና ዐርብ አጽዋማትን፤ የቅዱሳንን ስም እየጠሩ የበዓላትን ቀን በማክበር የሥራ ቀናትን መቀነስ፤ ሰው ሲሞት የሣልስት፥ የአርብዓ፥ የሙት ዓመት ተዝካር ወዘተ… እያሉ የሟች ቀሪ ቤተሰቦች የሚተዳደሩበትንና ልጆች የሚያድጉበትን ንብረት ማባከን፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ከቶ ያልተጠቀሱትንና ፍጹም ሊታመኑ የማይችሉትን ገድልና ድርሳናት መስበክንና ማስተማርን በጥብቅ ይነቅፋል። ታዲያ ጥቅማቸው የተነካ ብዙ የቤተ ክህነት ሰዎች ስለተናደዱ አባቴን እስከ ጠቅላይ ንጉሠ ነገሥት ፍርድ ቤት ድረስ አደረሷቸው። የታተመው መጽሐፋቸውም ታስሮ እንዳይሸጥ ተከለከለ።

አቶ ዘመንፈስ ቅዱስ ከጠቅላይ ንጉሠ ነገሥት ፍርድ ቤት ቀርበው ምንም ጠበቃ ይሁን ነገረ ፈጅ ሳይፈልጉ በአንድ እጃቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው፥ በሌላው ጥቅሶችን እያወጡ በመጠቆም ከመላው የቤተ ክህነት መሪዎች ጋር ፊት ለፊት፥ ዐይን ለዐይን ተፋጥጠዋል። በኋላም ከጃንሆይ ችሎት ፊት ቀርበው ንጉሡ፥ “በሉ እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ጠቅሶ ይሄው ይከራከራችኋል፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅሳችሁ ነው መልስ መስጠትና መርታት…” ቢሏቸው አጥጋቢ ጥቅስ አቅርበው ሊከራከሩና ሊረቱአቸው አልቻሉም። በዚህ ጊዜ ጃንሆይ፥ “እንግዲያውስ በቂ መልስ ከሌላችሁ የተያዘው መጽሐፍ ነጻ እንዲለቀቅ አዝዘናል መልስ አለን የምትሉ ከሆነ መጽሐፍ ጽፋችሁ ዓጸፋውን መልስ ስጡት፤ እስካሁን ለተጉላላው እናንተ በግዳችሁ ትከፍሉታላችሁ፥” ብለው ፈረዱላቸው።

የንጉሰ ነገሥቱን ውሳኔ ሰነድ ለመመልከት እዚህ ይጫኑ

ፍርዱን የሰማ ከጥግ የቆመ አንድ ባሕታዊ በንዴት ተንደርድሮ ከአጠገቡ የነበረውን የክብር ዘበኛ በጥፊ ጆሮ ግንዱን ማጎኑ ይነገራል። አቶ ዘመንፈስ ቅዱስን ያገኘ መስሎት ይሁን ወይም ንጉሡን እንጃ፤ በወታደሮች ተይዞ ከችሎት ወጣ። አባቴ ሙግቱን ረትተው ቤት ሲመለሱ በታላቅ ደስታ ነበር የተቀበልናቸው። ጃንሆይ “ለተጉላላኸው እኔ ልክፈልህ እንጂ ካህናቱስ አይከፍሉህም፥” ብለው የሸለሟቸው አንዲ ሺህ ብር፥ ከሊቀመኳሱ እጅ አምስት መቶ ሆኖ እንደተቀበሉ ይናገራሉ። በዕለቱ በዓድዋ ቤታችን ትልቅ ፈንጠዝያና ድግስ ነበር።

“ተግሣጽና ምክር” በይፋ ይሸጥ ጀመር። ብዙዎች በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባህላዊ ሰንሰለት ታስረው የነበሩ ሰዎች የሕሊና ነጻነት በማግኘታቸው፥ ከሩቅ እሳቸውን በደብዳቤና በማጠያየቅ እየፈለጉ ይተዋወቁ፥ ያመሰግኑ፥ ይመርቁ፥ ልዩ ልዩ ስጦታዎችና ማስታወሻዎችንም ይልኩላቸው እንደነበር አስታውሳለሁ። ከውጭም ከኢየሩሳሌም፥ ከሱዳንና ከኬንያ ጭምር የሚያመጡላቸው ደብዳቤዎችና ብዙ ስጦታዎችም ነበሩ።

አቶ ዘመንፈስ ቅዱስ በመጽሐፍ መጻፍ ብቻ ቢሰማሩ ኖሮ እኛ ልጆቻቸው በረኃብ እናልቅ ነበር። ግን ትጉሕና ታታሪ ነጋዴ ስለ ነበሩ ቀን ቀን በንግድ፥ ማታ ማታ ደግሞ መጻሕፍትን ሲያነቡ፥ ሲመራመሩና ሲጽፉ ያነጉት ነበር። በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ድካማቸውን እየተመለከቱ፥ “አለቃ መች ይሆን የሚያርፉት?” ሲሏቸው የዘወትር መልሳቸው “ዕረፍት በመቃብር” የሚል ነበር።
“ተግሣጽና ምክር” ተሽጦ ስላለቀ በድጋሚ ሁለተኛ እትም አሳትመው አወጡ። በሁለተኛው እትምም ተጨማሪ ሐሳቦችንና ግጥሞችን ጽፈዋል።

ከጻፏቸውም ግጥሞች መካከል፦

“ተግሣጽና ምክር መልካም ገሰገሱ፥
መልክና ታምርን በገድል እየጣሱ፥
ሾላ መነጠሩ፥ ተራራ አፈረሱ፥
በስንት መከራ ካቡን ቤት ደረሱ፥
እውነት ስለያዙ የትም ተከሰሱ፥
ዳኛው ቅዱስ መጽሐፍ ሲበይን ለእነርሱ፥
ብሎ ነገራቸው ተፈሪ ቅዱሱ፥
መልስማ ለመስጠት የትኛውን ሊጠቅሱ፥
ማጉረምረም ብቻ ነው ወጋቸው እነርሱ።
ተግሣጽና ምክር ምንኛ በረቱ፥
12 ዓመት ታስረው ቢንገላቱ፥
ተስፋ ባለመቁረጥ ጨክነው ሞገቱ
ግን የማታ የማታ አቶ እውነት ረቱ።….”

የሚል የደረሰባቸውን ግፍ የሚገልጽ ይገኝበታል።

እንደገናም ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ጠላት፥ ጸረ ማርያም የሚሉ ትችቶች ተሰነዘሩባቸው። እርሳቸው ግን ቤተ ክርስቲያንን የሚወዱና እንድትታደስ የሚመኙ እንጂ ጠላትዋ እንዳልሆኑ ሲጽፉ፦

“ወዳጆቼ ሆይ! ዓለም መካሪውን እንደሚጠላ ሁላችሁም በክርስቶስ ላይ የደረሰውን ሁሉ አይታችኋል። እኔም ደግሞ በትንሹ ዐቅሜ አገሬ ይልቁንም አሮጌዋ ቤተ ክርስቲያናችን ከዕንቅልፍዋ ነቅታ፥ የወንጌል ቀንዲልዋን አብርታ የቤትዋን ጉድፍ ጠርጋና ተሰናድታ፥ ጥበብ በተባለው እንዶድና ሥልጣኔ በተባለው ሳሙና፥ ልማድ ያሳደፈውን ልብስዋን አጥርታ፥ ንጽሕት ሆና እንድታምርና እንድታጌጥ ብዬ ሕጻናዊ በሆነው፥ በትምሕርት ባልበሰለው አዕምሮዬ ጥቂት ኃይለ ቃላትን ጨመር አድርጌ ስለዘለፍኋት፥ ባለማወቋ ክፉ ስም ሰጥታ እንድታዝንብኝና እንድትጠላኝ አልስተውም። ‘እኔ ግን እናትህ ባረጀች ጊዜ አትናቃት…. ክፉውን በበጎ አሸንፉት እንጂ አትቃወሙት… ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚረግሟችሁ መርቁ፤ ስለሚያሳድዷችሁና ስለሚጠሏችሁ ጸልዩ።…’ የሚለውን ቃል ተምሬያለሁና ከቶ አልቀየማትም።… በጎውን ነገር ብቻ እመኝላታለሁ እንጂ እርሷ ብትጠላኝም… “አባት እናቱን ያልተወ የኔ ተማሪ ሊሆን ብቁ አይደለም።…” የሚለውን ባታውቅ ነውና እኔስ ምንም አልጠላትም። እኔ በማን ጡት ባደግሁ ነው እሷን የምጠላ? እርግጥ ነው፥ ንጹሕና ነጭ የሆነውን የጤፍ እንጀራ (ወንጌልን) ባገኘሁ ጊዜ የተፍረቀረቀውን የዘንጋዳ ቂጣዋን (ገድል፣ ተአምርዋን) አምዘግዝጌ በመጣሌ ብትቀየመኝም ይቅርታዋን ከመለመን በቀር የማደርግላት ነገር እንደሌለኝ ኅሊናዬና አምላኬ ያውቃሉ።…” በማለት የደረሰባቸውን ዘርዝረው ለመግለጽ ችለዋል።

አቶ ዘመንፈስ ቅዱስ ሃይማኖትን ተመርኩዞ፥ ባህልን ተቆራኝቶ ኅብረተሰብን የሚጎዳውን ሁሉ እንዲቀር የሚጥሩ፥ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ተመሥርታና ታድሳ እንድትጸና የታገሉ ቢሆንም እንኳን፥ እንዲሁ ለመታደስ ብቻ ተብሎ ባሕል ይሁን፥ ልማድ ይለወጥ፥ አዲስ አዲሱን እንያዝ የሚሉ ሰው አልነበሩም። ይልቁንም ሁሉን ነገር በመመርመር፥ መልካም መልካሙንም በመከተል፥ መጥፎ መጥፎውንም በማራቅ የሚያምኑ፥ የሁለቱንም ልዩነት ወንጌል እንዳለው፥ “በፍሬው ታውቁታላችሁ” የሚሉ ነበሩ። በዚህም አያይዘው “ኢትዮጵያ የፈረንጁን ጎረምሳ ከነንፍጡ ዐቅፋ ሳመችው።…” እያሉ፥ “ዘመናዊ የሆነ ሁሉ ጠቃሚ አይደለም፤ መምረጥና መለየት ደግሞ የተጠቃሚው ፈንታ ነው” ይሉ ነበር።

በአሥመራ ከተማ ወደ ሃያ ዓመት ገደማ ሲቀመጡ፥ በሃይማኖት ጉዳይ ከአሥመራ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ካህናት ጥቂት፥ ከካቶሊክ ቤተክርስቲያንና ከፕሮቴስታንትም ጭምር በየጊዜው ከቤታችን ጠርተው እያመጡ፥ “ሁላችንም የክርስቶስ አካል ከሆንን እንዴት ተለያይተን እንኖራለን?” እያሉ ሊተባበሩ የሚችሉበትን መንገድ ያነጋግሩ፥ ያወያዩም ነበር። ሊቃውንቱም ተሰብስበው ከአንድ ማዕድ እየቆረሱ የሚለያዩበትን ነጥቦች በመተው በሚቀራረቡበት ነጥቦች ላይ በማተኮር ሲወያዩ ያመሻሉ።

“ተግሣጽና ምክር” በታተመ በግምት ሰባት ዓመት ያህል ቆይቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ወገን በሆኑት በመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ (ዘዲማ ጊዮርጊስ ጎጃም) ተጽፎ፥ “ኰኲሐ ሃይማኖት (የሃይማኖት ዐለት)” በሚል ርእስ የተዘጋጀ የመልስ መጽሐፍ ታትሞ ወጣ። ከመጽሐፉም መግቢያ ላይ፥ “…ነፋስ ነፈሰ፤ ዝናብ ዘነበ፤ ጐርፉም ጐረፈ፥ ቤተክርስቲያንዋንም ሊያፈርሳት ቃጣ። ቤተክርስቲያንዋ ግን በጽኑ መሠረት፥ በኰኲሐ ሃይማኖት የቆመች ስለሆነች ሊያናውጣት አልቻለም።…” ይላል። ታዲያ ዘመንፈስ ቅዱስ የብዕር ስማቸው እንጂ የመጠሪያ ስማቸው “ጐርፉ” ስለሆነ አባቴ ከጓደኞቻቸውና በቅርብ ከሚያውቋቸው ሊቃውንት ጋር ስለዚህ ሲያነሡ “ጐርፉ እንዳይወስዳችሁ።…” እያሉ ይቃለዱና ይጫወቱ ነበር።

መልአከ ብርሃን አድማሱ በመጽሐፋቸው ብዙውን ያተኮሩት በተግሣጽና ምክር ደራሲ ላይ ስለ ነበር ቅር ለማሰኘትና ለማስቀየም የሚበቁ ብዙ ክፍሎች ነበሩት። አቶ ዘመንፈስ ቅዱስ ግን “ኰኲሐ ሃይማኖት” ታትሞ በመውጣቱ የተሰማቸው ደስታ ወሰን አልነበረውም። ጸሐፊው ከእርሳቸው ጋር ሳይተዋወቁ መጽሐፋቸውን ብቻ በማንበብ የጽሑፍ መልስ አትመው በማቅረባቸው፥ አባቴ የአድናቆት እንጂ የሐዘን ይሁን የቅሬታ ስሜት አልነበራቸውም።

በየጊዜው አዲስ አበባ ሲመላለሱ ከተዋወቋቸው የሥነ ጽሑፍ ጓደኞቻቸው መካከል አቶ ዓለማየሁ ሞገስ የተባሉ በቀዳማዊ ኅይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ የቅኔ መምሕር ነበሩ። መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ለግል ሥራ ወደ አሥመራ የመምጣታቸውን ወሬ ሰምተው ለአባቴ ነገሯቸው። አባቴም ይህንን ሲሰሙ ያረፉበትን ቦታ አጠያይቀው በማግኘት “ጐርፉ እባላለሁ። መጽሐፍዎን አንብቤ የተደሰትኩ አድናቂዎ ነኝ።…” ብለው ተዋውቀው ለምሳ ቤት ይዘዋቸው መጡ።

ምሳ ተበልቶ፥ ማዕድ ተነሥቶ ብዙ ከተጨዋወቱ በኋላ አባቴ፥ “…ተግሣጽና ምክርን የጻፍኩ ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ ማለት እኮ እኔ ነኝ፥” ሲሏቸው መልአከ ብርሃን በጣም ተደናግጠው፥ “እኔማ ማንም ዘመናዊ ጎረምሳ መሰለኝ እንጂ እንዲህ የመሰለ ሊቅ፥ ጨዋ ባለትዳር ሰው መሆንዎን መች ዐውቄ፥…” በማለት ይቅርታ ለመጠየቅ ከተቀመጡበት ተነሱ።
አባቴም ልብሳቸውን ይዘው፥ “…የለም ይቀመጡ፥” ብለው በማስቀመጥ በመጽሐፉ ይዘት እንጂ በስድቦቹና በዘለፋው እንዳልሆነ ገልጸው ጨዋታው ቀጠለ። ከዚያ በኋላ ሁለቱም ወዳጆች ሆነው በተደጋጋሚ እየተገናኙ ብዙ ተጠያይቀዋል። በሁለቱም መካከል ምንም ቂምም ሆነ ቅሬታ አልነበረም።

አሥመራ በሚገኘው ቤታችን ለመጠየቅ የሚመጡ አባቴም አዲስ አበባ ሲሄዱ ፈልገው የሚጠይቋቸው ብዙ ደራሲያንና የሥነጽሑፍ ሰዎች ወዳጆች ነበሯቸው። ከእነዚህም ከብዙ በጥቂቱ ከላይ የተጠቀሱት አቶ ዓለማየሁ ሞገሥ፥ መምህር ይኄይስ ወርቁ፥ አቶ አቤ ጉበኛ፥ አለቃ መሠረት ስብሐት ለአብ (“ስምዓ ጽድቅ ብሔራዊ”ን የጻፉት)፥ አዝማች ክንፉ ኪዳኔ (የወርቅ ሠሪና “ጥንታውያን የአክሱም ነገሥታትና የአሠሯቸው ገንዘቦች” የሚለውን መጽሀፍ የጻፉ)፥ የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌን “መዝገበ ቃላትና መጽሐፈ ሰዋሰው” አዘጋጅተው በአርትስቲክ ማተሚያ ቤት ያሳተሙት አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ፥ አቶ አማረ ማሞ እና ለጊዜው የዘነጋኋቸው ብዙዎች ስለ ማኅተምም ሆነ ስለ መጻሕፍት ምርምር፥ ስለ ስነ ጽሑፍ አስተያየታቸውን ለመጠየቅ የሚመጡ ነበሩ። ሁሌ አባቴ በሐሳብና በምክር የሚያውቁትን ያህል ሁሉን ሳይቆጥቡ ስለሚለግሷቸው በምሳ በእራትም ጊዜ ቤታችን እንግዳ ምንም አይለየውም ነበር።

አቶ ዘመንፈስ ቅዱስ ከባለቤታቸው ዐሥር ልጆችን ወልደው፥ ዘጠኙን ትተው አልፈዋል። በንግድና በሥነ ጽሑፍ ሥራ፥ ልጆችንም አስተምረው፥ ቀጥተው በማሳደግ ደከመኝ ሳይሉ በታታሪነት በኖሩት ኑሮ በድንገተኛ የዐናት በሽታ (TONSIL) አሥመራ ከተማ በሚገኘው እቴጌ መነን ሆስፒታል ለዐሥር ቀን ያህል ተኝተው ሕመሙ ስለጸናባቸው በተወለዱ በ58 ዓመታቸው አረፉ። “ዕረፍት በመቃብር…” እያሉ ሲመኙት እንደነበሩም ፈጣሪ “ይብቃህ ልጄ፥ ና ወደ ዕረፍቴ ግባ፥” ብሎ እንደጠራቸው ይመስላል። መቃብራቸውም በአሥመራ ከተማ ቤተ መኻእ በተባለው ቦታ ነው። “የሰው ዕድሜ መርዘምና ማጠር እንደ ቢላ መርዘምና ማጠር ነው። ቁም ነገሩ ግን ከርዝመቱ ወይም ከእጥረቱ ሳይሆን ከስለቱ ነው፥” እያሉ ሁሌ ሲናገሩት የነበረ ንግግር ነው።

“ተግሣጽና ምክር” የኣባቴ የመጀመሪያ መጽሓፍ ቢሆንም እንኳን ከዚያ ቀጥለው ብዙ መጽሓፎችን ጽፈዋል፣ ከብዙዎቹ ጥቂቱን ለመጥቀስ፤

1) ሓተታ መናፍስት ወዓውደ ነገሥት – የጥንቆላን ጥበብና ዘዴ ለማጋለጥ፣ ማንኛውም ሰው በጠንቋዮች እንዳይታለል ሲሉ፣ ከጥንታዊ የብራና ጥራዙ ገልብጠውና ከዘመናዊ ስዕሎች ጋር ኣቀነባብረው ለመጀመሪያ ጊዜ ኣሳተሙት፣

2) ሓተታ ዘዘርዓ ያዕቆብ ኣክሱማዊ ወወልደ ሕይወት እንፍራዛዊ – የሁለት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ምርምር ከጥንታዊ የብራና ጥራዙ ገልብጠውና ኣሻሽለው፣ በተጻፈው የግዕዝ ቋንቋና ወደ ኣማርኛም በመተርጐም ለመጀመሪያ ጊዜ ኣሳተሙት፣

3) ሱንዳርሲንግ ህንዳዊ ሰማዕት- በኣማርኛ

4) መጽሓፍ ምዕዶ -በትግርኛ፣

5) ግዕዝ – መጽሓፈ ስዋስው ዘኣለቃ ታየ፣

6) ትንሽ የመጽሓፍ ቅዱስ መክፈቻን ኣሳተሙ።

እግዚአብሔርን በክርስቶስ ስለሰጣቸው ዕረፍት አመሰግነዋለሁ

ገ/ኢ ጐርፉ

Abstract: This is a brief biographical account of Zemenfes Kidus Abraha, (Gorfu), an Ethiopian author of several spiritual books, the most prominent of which is: Tegsatsna Mikir (Reproof and Advice), a book that exposed many of the traditional practices of the Ethiopian Orthodox Church unsupported by the Bible. Zemenfes Kidus Abraha faced persecution and imprisonment, and his book was confiscated and banned from the market for twelve years. After a lengthy court trial that ended at the Imperial Crown Court, he won over his adversaries and was exonerated.

court document attached here

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.