ተዝካረ ሕይወት – አህመድ ኑር (1949 – 2014 ዓ.ም)
አቶ አህመድ ኑር፤ የሃገሩ ነገር የሚያንገበግበው ፣ የሚቆረቁረው፣ እምነቱንም የሚወድና የሰውን ልጅ ባጠቃላይ የሚያከብርና ጓደኞቹን የሚወድ፤ ባንፃሩ ደግሞ በሰው ዘንድ ተወዳጅ የነበረ ወንድማችን ነበር። በሚጽፋቸው ግጥሞቹ ግጥም የመግጠም ልዩ ችሎታ እንደነበረው ገላጭ ናቸው። በየስብሰባዎች ላይ የሚያነሳቸው ጥያቄዎቹ ሁሉ ጥበብን የተሞሉና ማንንም የማይጎዱ ከአሽሙርና ከአግቦ አገላለጾች ነፃ የሆኑ ቀጥተኛ ነበሩ። ከወሎ ማደጉን እንደትልቅ ነገር የሚያወሳው አቶ አህመድ ኑር የወሎን ዙሪያ ባህልና የንግግር ዘዬ አሳምሮ መግለጽ በመቻሉ የወሎ አምባሳደር የሆነ ያህል ያስቆጥረው ነበር።