“የግማደ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ መምጣት” (ጌታቸው ኃይሌ)

የግማደ መስቀል መገኘት በብዙ ታሪክ ተመዝግቧል። ይህ ጽሑፍ እንደሚያሳየው፥ ከእኛ ዘንድ የተገኘው ታሪክ በሁለት ነገር ይለያል። አንደኛ፦ መስቀሉን አፈላልጋ ስላገኘችው ስለ ንግሥት እሌኒ ታሪክ የሚነገረው ከሌላ ዘንድ የሌለ ሰፋ ያለና ሲያነቡት የሚጥም ነው። ሁለተኛ፦ ስለግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ብዙ የታሪክ ሰነዶች መስክረዋል።

ባህልና ሕዝብ (ይርጋ መንግሥቱ እስጢፋኖስ)

የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ከ81 (ሰማንያ አንድ) በላይ የሆኑ የብሔር፣ የብሔረሰብና የማህረሰብ ቅንብር ያላት መሆኑ ግልጽ ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ አባላት ብቻ ከአላቸው ባህላቸውና የዝርያቸው ሐረግ ሊዋጥና – ጨርሶም ሊጠፋ ጥቂት ከቀራቸው ማህበረሰቦች አንስቶ፣ ብዙ ሚሊዮን አባላት እስከ አሏቸው አያልና ሠፋፊ መሬት እስከ ያዙት የኦሮሞና የአማራ ብሔሮች ባህሏን የሚያበለጽጉና ሕብረሰባዊነቷን የሚያጠናክሩ፣ ሕብሯን የሚያሞሽሩ ህዝቦች የሚኖሩባት አገር ነች።

ባህል ሥነጽሑፍና ኪነጥበብ

በኢትዮጵያ ከየብሔረሰቡ የሚፈልቁ ብዙ አሸብራቂና አስደሳች ትርጉም የሚሰጡ የባሕል ቅርሶች አሉ ። ብዙ ዓይነት ጣዕመ ዜማ ያላቸው የሙዚቃ መሳሪያዎችም ቁጥራቸው በርካታ ነው። ብሔራት የባህላቸውን ምንነት የሚገልጹባቸው የራሳቸው የሆነ የስእልና የቅርጻ ቅርጽ አቀራረጽ አሳሳልና ልዩ ልዩ ብልሃት ሞልቷል። ይህ ሁሉ አስደናቂ ነገር አብይ ቅርስ ስለሆነ ይህ ትውልድ የራሱ የሆነውን ቅርሳዊ ሃብት ኮርቶበት ለመጪው ትውልድ በቂ መሰረት ለማቆየት አካባቢውን አጥንቶና መርምሮ ማወቅና ማሳወቅ ማቆየት ይገባዋል።

ፖለቲካና ኢኮኖሚ

ፖለቲካና ኢኮኖሚን አስመልክቶ ስለኢትዮጵያ የሚደረግ ምርምር ጥናትና ትንተና አላማው በሀያኛው ክፍለ ዘመን የዚህች ሃገር ኢኮኖሚ እጅግ ማዘቅዘቅ ከምን ሁኔታና ምክንያት ጋር እንደሚያያዝ መፍትሄ ለማግኘት መሆን ይገባው ይሆናል ። በህገሪቱ ውስጥ ከብዙ ዘመናት ሲጥመለመል የቆየው የፖለቲካ ሂደት ከጊዜ ወደ ጊዜ አስከፊ ውጤት እያስከተለ መሄድ ሃገሪቷ ከነበረችበት አንጻራዊ መደላደል ወደባሰ አለመደላደል ማዘቅዘቁ የፖለቲካ ባህል እያደር እያደገ በመሄድ ፋንታ የተለያዩ ቅራኔዎች መፋፋምና በቅራኔው አፈታት ላይ የተወሰዱት እርምጃዎች ፣የተፈጠሩት ችግሮች …ወዘተ የእነዚህ ሁሉ ምክንያት በምርምር መልስ ማግኘት አለበት ።