“ብላታ መርስዔ ኀዘን ወ/ቂርቆስ” (አምኃ መርስዔ ኀዘን)

ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ መጋቢት 17 ቀን 1891 ዓ.ም. ሸዋ ጅሩ ውስጥ እምቧጮ መግደላዊት በተባለ ስፍራ ተወለዱ። አባታቸው አለቃ ወልደ ቂርቆስ አልታመን ይባላሉ። እሳቸውም በደብረ ሊባኖስና በእንጦጦ ማርያም የቤተ ልሔምን መዝገበ ድጓ ሲያስተምሩ የነበሩና በዜማ መምህርነት የታወቁ ናቸው። እናታቸው ወይዘሮ የሸዋ ወርቅ ምናጣ ይባላሉ። የአባታቸው አጎት አለቃ ገብረ ክርስቶስ የብሉይና የሐዲስ ሊቅና የቅኔ መምህር የነበሩ በንጉሥ ኃይለ መለኮት፣ በአጼ ዮሐንስና በአጼ ምኒልክ ቤተ መንግሥት እጅግ የተከበሩ ሰው ነበሩ።

“የግማደ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ መምጣት” (ጌታቸው ኃይሌ)

የግማደ መስቀል መገኘት በብዙ ታሪክ ተመዝግቧል። ይህ ጽሑፍ እንደሚያሳየው፥ ከእኛ ዘንድ የተገኘው ታሪክ በሁለት ነገር ይለያል። አንደኛ፦ መስቀሉን አፈላልጋ ስላገኘችው ስለ ንግሥት እሌኒ ታሪክ የሚነገረው ከሌላ ዘንድ የሌለ ሰፋ ያለና ሲያነቡት የሚጥም ነው። ሁለተኛ፦ ስለግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ብዙ የታሪክ ሰነዶች መስክረዋል።

“የዘርአ ያዕቆብ (ወርቄ) እና የሬኔ ዴካርት ፍልስፍና” (ፈንታሁን ጥሩነህ)

ዘርአ ያዕቆብ ከአክሱም የመነጨ ፈላስፋ ነው። ዴካርት ደግሞ ከፈረንሳይ ሀገር ይመነጫል። ሁለቱም ፈላስፋዎች በአንድ ዘመን ኖረዋል። በትውልድ ዓመትም ብዙ አይራራቁም። … ሬኔ ዴካርት የሚታወቀው የመጀመሪያ ፈረንሳዊ ብሎም አውሮጳዊ ፈላስፋ በመሆኑ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ዘርአ ያዕቆብ እስካሁን ያለውን መጠነኛ ታዋቂነት ያገኘው ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ ከግዕዝ ወደአማርኛ ተርጉመው ባሳተሙት ፤ ሐተታ ዘዘርአ ያዕቆብ አክሱማዊ ወወልደ ሕይወት እንፍራዛዊ በተሰኘው መጽሐፍ ሳቢያ ነው።

ርዕሰ አንቀጽ

መሠረተ: ሐሳብ፤

ሰምና ወርቅ መጽሔትን መልሶ ማቋቋም ለምን አስፈለገ?

ሰምና ወርቅ መጽሔት በአማርኛ ቋንቋ እየታተመ የሚወጣ የምርምርና የጥናት መጽሔት ሆኖ በ1979 ዓ.ም. መታተም ጀመረ። በዚያን ወቅት ከኢትዮጵያ እየፈለሰ የሚወጣው ኢትዮጵያዊ እጅግ ብዙ ነበር። ነገር ግን እርስ በራስ ለመገናኘት፥ ሐሳብ ለሐሳብ ለመገበያየት የሚያስችል መድረክ ባለመኖሩ የስደቱ ኑሮ ለብዙኅኑ አሰልችና ተደጋጋሚ የሆነ ፈሊጥ ወደ መሆን ደርሶ ነበር። በዚህ መካከል አንዳንድ ምሁራን የአማርኛ ፊደልን በኮምፒውተር የመጠቀም ችሎታን ስለፈጠሩና እያሳደጉ በመምጣታቸው ለህብረተሰቡ አንድ አገናኝ የሆነ መጽሔት የማቋቋሙ አስፈላጊነት እጅግ ጎልቶ ይታይ ነበር።…

“ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ” (ገ/ኢ ጐርፉ)

አቶ ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ ከአባታቸው ከነጋድራስ አብርሃ ወልዱ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ወለላ ተክሉ በዓድዋ ከተማ እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር በ1905 ዓ.ም. ተወለዱ። አባታቸው ነጋድራስ አብርሃ በከተማው ከነበሩት ታዋቂ ነጋዴዎች መካከል አንዱ ነበሩ። ልጃቸው የቤተ ክህነትን ትምህርት በዘመኑ ገናና ወደ ነበረው የዓድዋ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አስገብተው ከፊደል መቁጠር ዳዊትና ወንጌል ንባብ ቀጥሎም ለዲቁና የሚያበቃውን የቃልና የዜማ ትምህርት እንዲማሩ አደረጉ። ይሁንና ገና የዐሥራ ሦስት ዓመት ወጣት እያሉ አባታቸው በድንገተኛ የወባ ሕመም ስለሞቱ ትምህርታቸውን አቋርጠው…

ባህልና ሕዝብ (ይርጋ መንግሥቱ እስጢፋኖስ)

የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ከ81 (ሰማንያ አንድ) በላይ የሆኑ የብሔር፣ የብሔረሰብና የማህረሰብ ቅንብር ያላት መሆኑ ግልጽ ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ አባላት ብቻ ከአላቸው ባህላቸውና የዝርያቸው ሐረግ ሊዋጥና – ጨርሶም ሊጠፋ ጥቂት ከቀራቸው ማህበረሰቦች አንስቶ፣ ብዙ ሚሊዮን አባላት እስከ አሏቸው አያልና ሠፋፊ መሬት እስከ ያዙት የኦሮሞና የአማራ ብሔሮች ባህሏን የሚያበለጽጉና ሕብረሰባዊነቷን የሚያጠናክሩ፣ ሕብሯን የሚያሞሽሩ ህዝቦች የሚኖሩባት አገር ነች።

ተዝካረ ሕይወት

ዶክተር ማይገነት ሺፈራው ሰምና ወርቅ የጥናትና የምርምር መጽሔት የመጀመሪያ እትሙን ለማውጣት ዝግጅት በሚያደርግበት ጊዜ የሙያዋ ክፍል በሆነው ትምሕርት አንጻር አንድ መጣጥፍ አዘጋጅታ አበርክታለች። ይህ ጽሑፍ በኢትዮጵያ ውስጥ እስከ 1980 ዓ.ም. የነበረውን የትምሕርት ሥርዓትና አሠጣጥ የሚገመግምና የሚዳስስ ጠቃሚ ጽሑፍ ነበር። በሰምና ወርቅ መጽሔት አባልነትም አብራን ቆይታለች። የዶክተር ማይገነትን ነፍስ ከአብርሃምና ከሳራ ከጻድቃን ጋር ያኑርልን።