ከሊቀ ማእምራን ታምራት አማኑኤል
1936 ዓ.ም
ማሳሰቢያ።
ከዚህ በታች የቀረበው የሊቀ ማእምራን ታምራት አማኑኤል ጽሑፍ በሰምና ወርቅ መጽሔት እንዲታተም የአዘጋጅው ክፍል የወሰነው ጽሑፋ መሰረታዊ ተብለው ከሚመደቡት አንዱ ነው ብለን ስላመንን ነው። ይህ ጽሑፍ በሌሎች መድረኮች ላይ ታትሞ ታይቷል፤ ሆኖም ግን በተለይ የኢትዮጵያን የአማርኛ ሥነጽሑፍ አስመልክቶ ያለፈውን ዘመን ታሪክ ባንድ ላይ አስሮ ከመልካም ትንተና ጋር የቀረበበት ስለሆነ ለመጽሔታችን ተከታታዮችና በዚህ መስክ ምርምርና ጥናት ለሚያካሂዱ ጠቃሚ ነው ብለን አምነናል። ስለዝህም በመጽሔታችን የሥነ ጽሑፍ አምድ እንዲካተት ማድረጋችን ለደንበኞቻችን አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል ብለን በማመን ነው። ለወደፊትም ተመሳሳይ ግዝፈት ያላቸውን እና ዘመን ዘላቂ የሆኑትን የቆዩ ጽሑፎች በተመሳሳይ ሁኔታ ለደንበኞቻችን የምናቀርብ መሆኑን እናስታውቃለን።
መቅድም።
ጽሑፉ፡የፕሮፌሰር፡ታምራት፡አማኑኤል፡ነው። ፕሮፌሰር፡ታምራት፡ከዛሬ፡ኻያዐምስት፡ዓመታት፡በፊት፡በትምርትና፡ሥነጥበብ፡ሚኒስቴር፡አማካሪ፡ኾነው ይሠሩ፡ነበር። ነገር፡ግን፡በዚያን፡ጊዜ፡ፕሮፌሰር፡በመባል፡ፈንታ፡ሊቀማእምራን፡ይባሉ፡ነበር። ትዝ፡እንደሚለኝ፡ባ፲፱፻፴፮፡ዓ.ም፡በቱርክ፡አገር፡የሚገኝ፡አካዳሚ፡ይኹን፡ወይም፡የደራሲያን፡ማ ኅበር፡ስለኢትዮጵያ፡ሥነጽሑፍና፡ስለኢትዮጵያዊያን፡ ደራሲያን፡ጠይቆ፡ስለነበረ፡ጥያቄውን፡የመለሱት፡ሊቀ ማእምራን፡ታምራት፡አማኑኤል፡ነበሩ። በዚህ፡ምክንያት፡ስለኢትዮጵያ፡ሥነጽሑፍና፡ ስለኢትዮጵያዊያን፡ደራሲያን፡ከብዙ፡በጥቂቱ፡የምታመለክተውን፡ይህችን፡ጽሑፍ፡ሊቀማእምራኑ፡በዐማርኛ፡ አዘጋጅተው፡አቀረቡ። ነገር፡ግን፡ጠያቂው፡የውጪ አገር፡ድርጅት፡በመኾኑ፡መጠን፡መግለጫውም፡በውጭ፡ቋንቋ፡መዘጋጀት፡ነበረበት። ስለዚህ፡ጽሑፊቱ በእንግሊዝኛ፡እንድትተረጐም፡በዚያን፡ዘመን፡እኔ፡ጽሑፎችን፡በማረም፡ሥራ፡አገለግልበት፡ወደነበረው፡ክፍል፡ተላከች። የፕሮፌሰሩ፡ዐማርኛ፡ጽሑፍም፡በዚያን ጊዜ፡እንግሊዝኛ፡ተርጓሚ፡ለነበሩት፡ለአቶ፡እንግዳ፡ ጽጌሐና፡ጥቂት፡ከባድ፡ኾኖ፡የዐማርኛውን፡አስተሳሰብ በእንግሊዝኛ፡አስተካክለው፡ለመግለጥ፡አስቸጋሪ፡ስለኾነባቸው፡በማስረዳቱ፡ሥራ፡እንድረዳቸው፡ታዝዤ፡ ዐብረን፡ከሠራን፡በኋላ፡እንግሊዝኛው፡ሲላክ፡ይህ፡ ዐማርኛው፡ግን፡እኛው፡ዘንድ፡ቀረ።
የጽሑፉ፡አሰካክና፡አገላለጥ፣የታሪኩም፡አቀራረብና፡ውበት፡ደስ፡ስለሚለኝ፡ጽሑፉን፡ዐልፎ፡ዐልፎ እመለከተው፡ነበር። ነፍሳቸውን፡ይማርና፡በሕይወት፡ ቢኖሩ፡ኖሮ፡ከዚህም፡የተሻለ፡ጽሑፍ፡ለአገራቸው፡ ሕዝብ፡እንዲያበረክቱ፡ማሳሰብ፡ይቻል፡ነበር፡ይኾናል። ባለመኖራቸው፡አልተቻለም። ካኹን፡ቀድሞም፡‘ማህአትማ፡ጋንዲ’፡ከሚባለው፡በቀር፡በስማቸው፡ታትሞ፡ የወጣ፡ሌላ፡ጽሑፍ፡መኖሩን፡አላውቅም። ይህችም፡ጽሑፍ፡በመጽሐፍነት፡ለመውጣት የሚያበቃት፡መጠን፡ባይኖራትም፡በኾነው፡መንገድ፡ ቁምነገር፡ላይ፡ብትውል፡ያንኑ፡ያኽል፡ለስማቸው፡ መጠሪያ፡ልትኾን፡ትችል፡ነበር፡እያልኹ፡በማሰላስልበት፡ጊዜ፡በቀዳማዊ፡ኀይለሥላሴ፡ዩኒቨርስቲ፡ለሚገኘው፡ለኢትዮጵያ፡ቋንቋዎችና፡ሥነጽሑፍ፡ክፍል፡ብትቀርብ፡ለምርምርና፡ለጥናት፡ትረዳለች፣በመጽሔትም ታትማ፡ትወጣና፡ለፕሮፌሰሩ፡ዝክረ፡ስም፡ትኾናለች በሚል፡አስተሳሰብ፡ከሥራ፡ጓደኛዬ፡ካቶ፡አሰፋ፡ገብረ ማሪያም፡ጋር፡ከተመካከርንበት፡በኋላ፡በዚሁ፡ተግባር ላይ፡እንድትውልላቸው፡የኒህን፡ታላቅ፡ምሁር፡ስምና ሥራ፡የምታስታውሰውን፡ይህችን፡በ፳፩፡ገጽ፡የተጻፈች ትንሽ፡ጽሑፍ፡ለዚሁ፡ድርጅት፡አቀረብኋት።
ከበደ፡ደስታ ፲፱፻፷፩ ዓ.ም
ስለኢትዮጵያ፡ደራሲያን።
ፕሮፌሰር፡ታምራት፡አማኑኤል
የጥንቱ፡የኢትዮጵያ፡አፈታሪክ፣አንድ፡ሽህ፡ ዓመት፡ያኽል፡ከልደተ፡ክርስቶስ፡በፊት፣ባገራችን፡ ሊቃውንትና፡መምህራን፡የነበሩበት፡ከዚያ፡ዠምሮ፡እስከዛሬ፡ድረስም፡ሊቅ፣መምህርና፡ደራሲ፡አልጠፋበትም፡ይላል። ቢኾንም፡አፈታሪኩ፡ሽህ፡ዓመት፡ከክርስቶስ፡ልደት፡በፊት፡ከብሉያት፡በቀር፡ሌላ፡ዐይነት፡መጻሕፍት፡መኖር፡አለመኖራቸውን፡አያመለክትም። ኢትዮጵያዊው፡ስለሰው፡ዘር፡በጠቅላላው፡በተለይም፡ስለኢትዮጵያ፡ወይም፡ስለሐበሻ፡ሕዝብ፡የጥንት፡ታሪክ፡ የተነገረው፡ኹሉ፡ስንኳ፡ገና፡ባይመረመር፣ለታሪክ፡ ምርመራ፡እስከዛሬ፡የተደከመበት፡ሥራ፣ከዚህ፡በላይ የተመለከተውን፡አፈታሪክ፡መሠረት፡የሌለው፡አስመስሎ፡ያሳየናል። አፈታሪካችን፡በሰሎሞን፡ዘመን፡ከሕዝበ እስራኤል፡ጋራ፡ግኑኝነት፡እንደነበረ፣ንግሥተ፡ሳባ፡ዛሬ፡ኢትዮጵያ፡(ሐበሻ)፡የምንለውንና፡ከዐረብ፡አገር፡ የደቡቡን፡ክፍል፡ትገዛ፡እንደነበረች፣ኢየሩሳሌም፡ድ ረስ፡ኼዳ፡ከሰሎሞን፡ጋር፡ተዋውቃ፡ከርሱ፡፩ኛ፡ምኒልክ፡የተባለ፡ወንድ፡ልጅ፡እንደወለደች፣ ፩ኛ፡ምኒልክም፡እስከዛሬ፡ድረስ፡ላሉት፡ነገሥቶቻችን፡አባት፡መኾኑን፣እርሱም፡አባቱን፡ሰሎሞንን፡ለማየት፡ኼዶ፡ከየሩሳሌም፡ሲመለስ፣ጽላተ ሙሴንና፡እስከሰሎሞን፡ዘመን፡ከእስራኤላዊያን፡የተጻፉትን፡መጻሕፍት (ብሉያትን) ይዞ፡እንደመጣ፡ይነገራል። ይህን፡አፈታሪክ፡የሚነግሩ መጻሕፍት፡ባገራችን፡መጻፍ፡የጀመሩ፡ከሽ፫፻ኛው፡ ዓመተምሕረት፡ወዲህ፡ነው።
ሽህ፡ዓመት፡ያኽል፡ከዚያ፡በፊት፡ለሕዝቡ፡ወንጌል፡ ተሰብኮለት፡ነበር። በሽህ፡ዓመት፡ውስጥ፡የመጽሐፍ፡ቅዱስ፡አሳብ፣በአሕዛብነት፡የነበረበትን፡ዘመን፡እንዲጠየፈው፡የሕዝበ እስራኤልን፡መጻሕፍትና፡አሳብ፡እንዲወድ፡አድርጐት፡ስለ ነበረ፡ጥቂት፡በጥቂት፡የገዛ፡ታሪኩን፡እየዘነጋ፡የእስራኤል፡ልጅ፡ነኝ፡ከማለትና፡የእስራኤል፡ሕዝብ፡የጻፍዋቸውን፡መጻሕፍት፡አያቶቼ፡የጻፏቸው፡ናቸው፡ከማለት፡ደርሷል። በሰሎሞን፡ዘመን፡የእስራኤልና፡የኢትዮጵያ፡ሕዝብ፡ግኑኝነት፡ኑሮዋቸው፡ይኾናል፡ቢባል፣ ማስረጃው፡ስንኳ፡ባይገኝ፣ ሳይኾን፡አይቀርም፡በማለት በተቀበልነው። በሰሎሞን፡ዘመን፡ከብሉያት፡መጻሕፍት አንዳንዶቹ፡እስከኢትዮጵያ፡ደርሰው፡በዚያው፡ዘመን፡ የኢትዮጵያ፡ሕዝብ፡ተቀብሎ፡የሃይማኖት፡ሥራ፡አስይዟቸዋል፡ለማለት፡ግን፡ማስረጃው፡እስኪገኝ፡ድረስ ልብወለድ፡የመጣ፡ሐሳብ፡ነው፡እንላለን።
የዛሬው፡ዘመን፡የመጽሐፍ፡ቅዱስ፡ትምርት፡ቤት፣የቀረው፡ቀርቶ፡ስለዐምስቱ፡ብሔረ ኦሪት (Pentateuque)፡ስንኳ፡በዛሬው፡አኳኋን፡ተሰብስበው፡ባንድነት፡መገኘት፡የጀመሩ በሰሎሞን፡ዘመን፡ብቻ፡ነው፡ይለናል። የዚህ፡ክርክር ገና፡ሳይጨረስ፣አፈታሪካችን፣መጽሐፈ፡ኦሪት፡በሰሎሞን፡ዘመን፡ካገራችን፡ደርሰው፡ነበር፡ሲል፣ለራሱ፡ ክብረት፡በመጓጓት፣ታሪክ፡ጥሶ፡የተራመደ፡ኾኖ፡ይታየናል። ይህም፡ከወገን፡ለጊዜው፡የበለጠ፡መስሎ፡የታየውን፡እየመረጡ፡ወገኔ፡ነው፡ማለት፡የዛሬ፡ሳይኾን የጥንት፣የኛ፡ብቻ፡ሳይኾን፡በኹሉም፡የደረሰና፣ታሪክ ተመርምሮ፡ወሬው፡ትክክለኛ፡አለመኾኑ፡ሲታይ፡የሚቀር፡ነው። በግሪኮች፡ሥልጣኔ፡ንጹሕ፡ቅንዓት፡ያደረባቸው፡ሮማዊያን፡የግሪኮች፡መዐርግ፡ተካፋይ፡ለመኾን፣የኤኔአን፡ተረት፡ፈጥረዋል። በመጽሐፍ፡ቅዱስ፡ ስለሕዝበ እስራኤል፡የተነገረው፡ኹሉ፡ደስ፡ሲያሰኛቸው ከነበሩት፡እንግሊዞች፣አንዳንዱ፡ባለታሪክ፣ስደት፡የኼዱት፡የ፲ሩ፡ነገደ እስራኤል፡የልጅ፡ልጆች፡ነን፡ሲል፡ ነበር። ዛሬ፡ግን፡ሮማዊያንም፡ከግሪኮች፡ጋር፡ዝምድና፡ቢኖራቸው፡ባለታሪክ፡ሌላ፡ማስረጃ፡ያመጣል፡እንጂ፡የኤኔአን፡ተረት፡መሠረት፡አያደርገውም። የባለታሪክ፡ስምና፡መዐርግ፡ያለው፡ሰው፡ደግሞ፣በእንግሊዝ፡ደሴቶች፡ከምሥራቅ፡የመጣ፡ሕዝብ፡ሰፍሮበት፡ኑሮ፡ይኾናል፡ስንኳ፡ቢል፣አንግሎሳክሶን፡ያሥሩ፡ነገደ እስራኤል፡ልጆች፡ናቸው፡አይልም። እንደዚኸው፡ኹሉ የኢትዮጵያን፡ታሪክ፡በዐዲሱ፡ምርመራ፡አካኼድ፡የሚከታተል፡ሰው፡ከሐበሻ፡ሕዝብ፡የሴም፡ዘር፡መቀላቀሉንና፡የሥልጣኔው፡መሠረት፡ሴማዊ፡መኾኑን፡ስንኳ ቢረዳ፣ከዚህም፡በላይ፡የኢትዮጵያ፡ሕዝብ፡ከሕዝበ፡ እስራኤል፡ጋር፡ግኑኝነት፡እንደነበረው፡ባይጠራጠርበት፣ ታሪኩን፡በሌላ፡መንገድ፡ያስረዳል፡እንጂ፣ስለንግሥት ሳባና፡ስለሰሎሞን፡የሚነገረውን፡መሠረት፡አያደርግም። ስለዚህም፡ከልደተ፡ክርስቶስ፡በፊት፡መጻሕፍት፡በኢትዮጵያ፡ኑረው፡እንደኾነ፡የደረሱበትን፡ለማወቅ፡ቸግሮናል፡እንላለን፡እንጂ፣ሕዝበ እስራኤል፡በሰሎሞን፡ዘመን፡የሙሴን፡መጻሕፍት፡ዛሬ፡በሚገኙበት፡አኳኋን፡ መሰብሰብ፡ገና፡ሲጀምር፣እነዚህ፡መጻሕፍት፡ድሮ፡ ባገራችን፡ነበሩ፡ለማለት፡ይቸግረናል።
የጽሑፍ፡ሥራ፡በኢትዮጵያ፡ገና፡ከልደተክርስ ቶስ፡በፊት፡ተጀምሮ፡ነበር፡እንላለን። ማስረጃው፡ግን በጣም፡ችግር፡ነው። እርግጥ፡የምናውቀው፡ክርስቶስ በተወለደበት፡ዘመን፡አቅራቢያ፡በትግሬ፡አውራጃ፡ከሐውልትና፡ከጸሎት፡ቤት፡የተጻፈ፡አንዳንድ፡ቃል፡ መገኘቱን፡ነው። ቀደምት፡የተባሉት፡ጽሕፈቶች፡የሚገኙ፡በሳባና፡በግሪክ፡ቋንቋ፡ነው። ከክርስቶስ፡ልደት በኋላ፡፫፻ኛው፡ዘመን፡ሲጀምር፡ግን፣ጽሕፈቱና፡ንግግሩ፡የተጣራ፡በግእዝ፡ቋንቋ፡ከሐውልት፡ላይ፡የተጻፈ፡መታሰቢያ፡አለ።
ስለዚህም፡ከሊቃውንት፡አንዳንዱ እንዲህ፡ይላል፦የኢትዮጵያ፡ሕዝብ፡የጽሕፈት፡ቋን ቋው፡ፊት፣ግሪክ፥ቀጥሎ፣ሳባ፥ኋላ፣ግእዝ፡ኹኑዋል። ለዚህ፡አሳብ፡ብዙ፡ተቃራኒ፡አልተነሣበትም። ነገር፡ግን፣ገና፡የመንን፡ሳይለቅ፡ባገሩ፡ቋንቋና፡ፊደል፡ሲጽፍ፡የነበረ፡ሕዝብ፡ወደኢትዮጵያ፡ሲመጣ፡ለምን፡በግሪክ፡ጻፈ? ደግሞም፡እስከዛሬ፡ድረስ፡በቤተክርስቲያን፡ሥራ፡የተያዘበት፡ሴማዊ፡የኾነው፡የግእዝ፡ቋንቋ፡እጅግ፡የተጣራ፡በመኾኑ፣ለግሪክና፡ለላቲን፡ቋንቋ፡ተወዳዳሪ፡ሊኾን፡ይቃጣዋል። ይህን፡የመሰለ፡ ቋንቋ፡እያለው፡ባገር፡ውስጥ፡ላለው፡ጕዳይ፡ለምን፡በግሪክ፡ይጽፋል? የዚህ፡ምክንያቱ፡እስኪገለጥ፡ድረስ፡ ከዚህ፡በላይ፡የተነገረው፡አሳብ፡ትክክለኛ፡ነው፡ላይባል ነው።
በርሱ፡ፈንታም፡ከዚህ፡ቀጥሎ፡የሚመጣውን፡ አሳብ፡መበገር፡ይቻላል፤ የኢትዮጵያ፡ሕዝብ፡የጽሕፈት፡ቋንቋው፣ፊት፣ሳባ፥ቀጥሎ፣ግእዝ፡ኑርዋል። የግሪክ፡ቋንቋ፡ከእስክንድር፡ጀምሮ፡ሮማዊያን፡ግብጽን እስከያዙበትና፡ከዚያም፡በኋላ፡እስከብዙ፡ዘመን፡ለግብጽና፡ለታናሽ፡እስያ፡ሕዝብ፡ዋና፡ቋንቋ፡ኹኖ፡ስለነበር፣ለኢትዮጵያ፡ደግሞ፡ከሠለጠነው፡ዓለም፡ጋር፡ መገናኛ፡ቋንቋ፡ኹኖላት፣የደብዳቤና፡ዐላፊ፡አግዳሚ ከሚያየው፡ሐውልትዋ፣ባሕር፡ተሻግሮ፡ለሚገበያዩበት ገንዘብዋ፡ይህነንም፡ለመሰለ፡ልዩ፡ጕዳይ፡የጽሕፈት፡ ቋንቋዋ፡ኑሮ፡ይኾናል።
በኢትዮጵያ፡ከ፬ኛው፡መቶ፡ዓመተምሕረት፡ በፊት(ይህ፡ማለት፡ወንጌል፡ባገሩ፡ሳይሰበክ)፡በሳባ፡ኾነ፡በግሪክ፥በግእዝ፡ኾነ፡በሌላ፡ቋንቋ፡የተጻፈ፡መጽሐፍ፡ኑሮ፡እንደኾን፡ወሬው፡ከኛ፡አልደረሰም። ዛሬ በእጃችን፡ያሉት፡መጻሕፍት፣ከ፬ኛው፡እስከ፡ሽህ፯፻ኛ ው፡ዓ.ም፡በግእዝ፣ከዚያ፡እስከዛሬ፡በግእዝና፡በዐማርኛ፡የተጻፉ፡ናቸው።
ግእዝ፡የሴም፡ቋንቋ፡መኾኑን ከዚህ፡በፊት፡አመልክተናል። ከዐረብ፡በስተደቡብ፡ከነበሩት፡ሴማዊያን፡ያንዱ፡ነገድ፡ቋንቋ፡ኑሮ፡ይኾናል ይባላል። ምናልባትም፡ከዚሁ፡ነገድ፡አንድ፡ክፍል፡ዛሬ፡አጋሜ፡በምንለው፡አውራጃ፡ይኖር፡ኑርዋል። ድንገት፡ደግሞ፡ከትግሬ፡አውራጃ፡ካሉት፡ነገዶች፡አንዳንዶቹ፡ይነጋገሩበት፡ኑረው፡ይኾናል። በኢትዮጵያ፡ያሉት፡የሴም፡ቋንቋዎች(ትግርኛ፥ትግረ፥ዐማርኛ)፡ከርሱ የመጡ፡ናቸው፡የሚሉ፡ሊቃውንት፡አሉ። ይህን፡አሳብ፡የማይቀበሉ፡በዚህ፡ፈንታም፣ከዐረብ፡በስተደቡብ ሲኖሩ፡ከነበሩት፡የሴም፡ነገዶች፣አንዳንዶቹ፡ወደ፡ኢትዮጵያ፡ሲመጡ፣ልዩ፡ልዩ፡የሴም፡ቋንቋ፡ኑርዋቸው፡የእያንዳንዱ፡ነገድ፡ቋንቋ፡ራሱን፡እንደቻለ፣በኾነለት፡መጠን፡እየደረጀ፡ኺድዋል፡እንጂ፣ግእዝ፡በኢትዮጵያ፡ላለው፡ልዩ፡ልዩ፡የሴም፡ቋንቋ፡አባቱ፡አይዶለም፡የሚሉ፡አሉ።
በግእዝ፡ከተጻፉት፡በብዙ፡ሽህ፡ከሚቆጠሩት መጻሕፍቶቻችን፣ጥቂቶች፡ሲቀሩ፣ኹሉም፡ከክርስቲያናዊ፡ግሪክና፡ዐረብ፡ከሌላም፡ቋንቋ፡የተተረጐሙ፡ናቸው። ደግሞም፡የዓለምንና፡የኢትዮጵያን፡ታሪክ፡ከሚነግሩት፡ከጥቂቶቹ፡በቀር፡ኹሉም፡የሃይማኖት፡መጻሕፍት፡ናቸው። ስለዚህ፡የኢትዮጵያዊነታችንን፡አሳብ፡የሚገልጥ፡አንድ፡መጽሐፍ፡አይገኝባቸውም። ዋናው፡ መጽሐፋችን፡‘መጽሐፍ፡ቅዱስ’፡ነው። ይኸውም፡ብሉይና፡ሐዲስ፡እግዚአብሔር፡በዓለምና፡በእስራኤል፡ላይ፡የሠራውና፡የሚሠራውን፡እስራኤላዊያን፡በታያቸው ዐይነት፡የሚገልጽ፡መጽሐፍ፡መኾኑን፣ኹሉም፡ያውቀዋል። ምስጋና፡ለዚህ፡መጽሐፍ፣የኢትዮጵያ፡ሕዝብ፣ በሃይማኖትና፡በምግባር፡ከፍ፡ካለ፡ደረጃ፡ደርሶ፣በያዘው፡መንገድ፡እየገፋበት፡እንዲኼድ፡ብርቱ፡ኀይል፡ ተሰጥቶታል። ደግሞም፡የግእዝ፡ቋንቋ፣መጽሐፍ፡ቅዱስ፡ወዳገራችን፡ሳይመጣ፡ገና፡ፊት፡አስቀድሞ፡ራሱን፡የቻለ፡እንደነበረ፡በሐተታ፡ስንኳ፡ብንረዳው፣ የግእዝ፡ቋንቋ፡ጽሑፍ፡ምስክሩ፡ባላባቶቹ፡የጻፉት፡መጽሐፍ፡መኾኑ፡ቀርቶ፡የመጽሐፍ፡ቅዱስና፡የሌሎች፡ መጻሕፍት፡ትርጕም፡ነው።
ማናቸውም፡የሠለጠነ፡ሕዝብ፡ለቋንቋው፣ለሰዋስው፡ማስረጃ፡ባላባቶቹ፡የጻፉትን፡ሲጠቅስ፣ግእዝ፡ለሰዋስው፡ማስረጃ፡የሚጠቅስ፣ ከባዕድ፡ቋንቋ፡የተተረጐሙትን፡መጻሕፍት፡ነው። በግእዝ፡ከጻፉት፡ካገራችን፡ደራሲያን፡ይቅርና፡በአሳብ፥ በአጻጻፍ፡ስንኳ፡መጽሐፍ፡ቅዱስን፡ቃል፡በቃል፡ሳይ ከተሉ፡የጻፉ፡የሚገኙ፡አይመስለኝም። ይህም፡ልምድ የሃይማኖት፡አሳባቸውን፡በሚገልጹበት፡ጊዜ፡ብቻ፡ሳይኾን፡ስለአገራችን፡ታሪክና፡ማናቸውንም፡ጕዳይ፡በሚጽፉበት፡ጊዜ፡ጭምር፡ነው። ይህም፡የአጻጻፍ፡አካኼድ፡ኢትዮጵያ፡ገንዘብ፡ካደረገችው፡ከመጽሐፍ፡ቅዱስ፡አሳብ፡ጋር፡የተስማማ፡ንግግር፡ለማምጣት፡የተመቸ፡ከመኾኑ፡በላይ፣መጽሐፍ፡ቅዱስን፡ሳንቀበል፡ ከነበረብን፡አሕዛባዊ፡ከኾነ፡ምሳሌና፡ንግግር፡አርቆናል።
ይኹን፡እንጂ፡ኢትዮጵያዊ፡የኾነ፡አሳብ፣ኢትዮጵያዊ በኾነ፡ንግግር፡የመግለጹ፡ዕድል፡ለግእዝ፡ቀርቶ፡ላማርኛ፡ኹንዋል። ዛሬ፡ዘመን፡በግእዝ፡እግር፡ተተክቶ፣የመንግሥትና፡የሕዝብ፡ጕዳይ፡የሚሠራበት፡የዐማርኛ፡ቋንቋ፡ነው።
የኢትዮጵያ፡ሕዝብ፡በዐማርኛ፡መጻፍ፡ከዠመረ፡ስድስት፡መቶ፡ዓመት፡ኹኖታል። ዐማርኛ፡ከዚያ፡ጀምሮ፡እስከዛሬ፡ድረስ፡ያለውን፡አካሔድ፡በ፫ት ዘመን፡ቢከፍሉት፡ይኾናል።
፩ኛውን፡ዘመን፣ዐምደጽዮን፡፲፫፻፴፮-፲፭፻፺፱(1344-1607)
፪ኛውን፡ዘመን፣ሱስንዮስ፡፲፭፻፺፱-፲፮፻፵፯ (1607-1655)
፫ኛውን፡ዘመን፣ቴዎድሮስ፡፲፰፻፵፯-፲፱፻፴፫(1855-1941) ቢሉት፡ይኾናል።
ባ፩ኛው፡ዘመን፡በዐማርኛ፡የተጻፈው፡ሥራ፡ እጅግ፡ጥቂት፡ነው። የተጻፈውም፡ላንዳንድ፡ነገሥታት ምስጋና፡ደራሲው፡ካልታወቀ፡የተገጠመ፡ቅኔ፡ነው። ቅኔውም፡በዘመናት፡ውስጥ፡አንድ፡ቋንቋ፡እንደምን፡ ኹኖ፡እየተለዋወጠ፡ለመኼዱ፡ዋና፡ምስክር፡ከመኾኑ በላይ፣ በዚያ፡ዘመን፡የነገሥታቱ፡ሥልጣንና፡የተዘረጋበት፡የሰፊው፡አገር፡ኹኔታ፡እንዴት፡እንደነበረ፣ ለታሪክና፡ለዦግራፊም፡ማስረጃ፡ለመኾን፡ይረዳል። ዐማርኛው፡ዛሬ፡ዘመን፡የማንናገርበትና፡የማንጽፈው፣ለማስተዋሉም፡የሚያስቸግረንና፡የሰዋስው፡አካኼድ፡የተለዋወጠ፡ብዙ፡ቃልና፡አገባብ፡አለበት። እርሱን፡የመሰለ፡ዐማርኛም፡በየዘመኑ፡እየተጻፈ፡ምናልባት፡እስከ፡ ፲፭፻፺፱-፲፮፻፯፡ደርሶ፡ይኾናል።
ነገር፡ግን፡ከ፲፭፻፶፭፡እስከ፡፲፭፻፺፱(1563-1607)፡በዐማርኛ፡የተጻፈ፡ምስክር፡አይገኝም፤ ቢገኝም፡ከዚህ፡በፊት ያመለከትኹትን፡የመሰለ፡ግጥም፡ሳይኾን፡አይቀርም።
ከ፲፭፻ኛው፡ዓመት፡በኋላ፡ከኢትዮጵያ፡ሕዝብ እስላምና፡ዐማራው፡ወገን፡ለይቶ፡ዐልጋ፡ለመያዝ፡እርስ፡በርሱ፡ሲዋጋ፣በአንድ፡ወገን፡ደግሞ፡ቱርኮችና፡ ፖርቹጋሎች፡በኤርትራ፡ባሕር፡ሥልጣናቸውን፡ለመዘርጋት፡ይፈካከሩ፡ነበር። ቱርኮች፡በኤርትራ፡ዙሪያ፡ላለው፡ፖለቲካቸው፡የኢትዮጵያን፡እስላም፡ሲረዱ፣ክርስቲያኑ፡የኢትዮጵያ፡ቤተመንግሥት፡የፖርቱጋልን፡ዕርዳታ፡መለመን፡ግድ፡ኾነበት። ጀግንነታቸው፡የሚመሰገን፡አራት፡መቶ፡ያኽል፡ጠመንጃ፡የያዙ፡ፖርቱጋሎ ች፡ወደኢትዮጵያ፡መጥተው፡በተዋጉበት፡ጊዜ፣ድል ለክርስቲያኑ፡ወገን፡ኾነ። የፖርቱጋል፡መንግሥት፡ከኢትዮጵያ፡ጋር፡ግኑኝነት፡ሲዠምር፡ያገሩ፡ካህናት፡ በኢትዮጵያ፡ለማስተማር፡እንዲፈቀድላቸው፡ተነጋግሮ ነበርና፡በስምምነታቸው፡የካቶሊክ፡ካህናት፡በኢትዮጵያ ማስተማር፡ዠመሩ። የሚያስተምሩበትና፡የሚጽፉበት፡ ቋንቋ፡ዐማርኛ፡ነበርና፡የኢትዮጵያ፡ቤተክህነት፡ደግሞ፡ሕዝቡ፡ካቶሊክ፡እንዳይኾንበት፡ግእዝን፡ሳይተው፡ በዐማርኛ፡መተርጐምና፡መጻፍ፡ዠመረ። በዚያው፡ዘመን፡ለመጻሕፍት፡ትርጕምና፡ለስብከት፡የተጀመረው ዐማርኛ፡ገና፡ከግእዝ፡ነጻ፡ያልወጣ፡አንዳንዱም፡ንግግር፡ግእዝ፡ላልተማረ፡ሰው፡በፍጹም፡የማይሰማ፡ነበር። እንደዚኸው፡ኹሉ፡በዚያው፡ዘመን፡ሲጻፍ፡የነበረው፡የነገሥታት፡ታሪክ፡ግእዙ፡ዐማርኛ፡ቅልቅል፡ነበር። ያም፡ኹሉ፡ኹኖ፡እንኳንስና፡ለውጭ፡አገር፡ሕዝብ፡ የሚተርፍ፣ካገራችን፡ውስጥ፡ከፍተኛ፡አሳብ፡የሚያሳድር፡በታረመ፡ዐማርኛ፡የተጻፈ፡መጽሐፍ፡ለማግኘት ችግር፡ነው። መጻሕፍቱ፡የፈጸሙት፡ጕዳይ፣በሕዝቡ ላይ፡ከመጣበት፡ከሃይማኖት፡ተወዳዳሪ፡መከላከልና፣ የባላገር፡ቋንቋ፡የነበረውን፡ዐማርኛ፡ጽሑፍ፡ሥራ፡ለማስያዝ፡መዠመራቸው፡ነው። አብዛኛውን፡ጊዜ፡ደራሲው፡ወይም፡ተርጓሚው፣ ለትሕትና፡ሲል፡ስሙን፡አያመለክትም፡ነበርና፡የመጻሕፍቱን፡ፍሬነገር፡መዘርዘር ደራሲው፡ወይም፡ተርጓሚው፡ማን፡እንደነበር፡መርምሮ፡የሕይወቱን፡ታሪክ፡ማመልከት፡አስፈላጊ፡ኹኖ፡ስላልታየን፡ትተነዋል።
ዐማርኛ፡ከዚህ፡በላይ፡ባመለከትነው፡አኳኋን ሲጎላደፍ፡ቆይቶ፡፫ኛ፡ብለን፡ወደሰየምነው፡ዘመን፡ይደርሳል። ይኹን፡እንጂ፡፪ኛ፡ብለን፡ከሠየምነው፡አካኼድ፡በጭራሽ፡ነጻ፡ወጥቶ፡ደራሲ፡የኾነ፡ኹሉ፡ግእዝ፡ባልተቀላቀለበት፡ዐማርኛ፡ብቻ፡መጻፍ፡የዠመረ፡ አኹን፡በቅርቡ፡በግርማዊ፡ንጉሠነገሥት፡፩፡ኀይለሥላሴ፡ዘመን፡ነው። ነገር፡ግን፡ፊተኛ፡ኹኖ፡ንጹሕ፡በኾነ፡ዐማርኛ፡የተጻፈው፡መጽሐፍ፡የዐጤ፡ቴዎድሮስ (፲፰፻፵፯-፲፰፻፷(1855-1868)፡ታሪክ፡ነው።
ደራሲው፡ ያጤ፡ቴዎድሮስ፡ጸሓፌ፡ትእዛዝ፡አለቃ፡ዘነብ፡የተባለው፡የሽዋ፡ሰው፡ነው። የሞተበትን፡ዘመን፡ማወቅ፡አ ልተቻለኝም፤ነገር፡ግን፡ባ፲፰፻፹፡ዓ.ም፡ግድም፡ትግሬ፡ኹኖ፡ከንጉሥ፡ምኒልክ፡ጋር፡ሲጻጻፍ፡እንደነበር እርግጥ፡ነው። እንደዚኸው፡ኹሉ፣ባጤ፡ቴዎድሮስ፡ ዘመን፡የነበረ፡የሽዋ፡ሰው፡አለቃ፡ወልደማሪያም፣ዐጤ፡ቴዎድሮስ፡ከሞቱ፡በኋላ፡ታሪካቸውን፡በዐማርኛ ጽፈዋል።ኹለቱም፡ባለታሪኮች፡የሚመሰገኑበት፡ፊተኞች፡ኹነው፡በተቻለ፡መጠን፡አጣርተው፡በዐማርኛ፡ መጻፋቸው፡ነው፤ቃል፡ለማሳመር፡ስንኳ፡ባይጣጣሩ፣ ግእዝ፡ሳይጎትታቸው፡ዐማርኛን፡ራሱን፡እያስቻሉ፣ ከተፈጥሮ፡በተቀበለው፡ጠባዩ፡አስኪደውታል።
ዐጤ፡ቴዎድሮስ፡አእምሯቸው፡በትክክል፡ባልሠራበት፡ሰዓት፡በኢትዮጵያ፡ሕዝብ፡ያወረዱት፡ጭካኔ፣ ስላሠቃያቸው፡ ከ፲፯፻፺፪(1800)፡ዓ.ም፡ጀምራ፡በብዙ፡መሳፍንት፡ስትገዛ፡ለነበረችው፡ኢትዮጵያ፡ባንድ፡ንጉሠነገሥት፡እንድትስተዳደር፡በእርሻና፡በንግድ፣በትምርትና፡በአድሚኒስትራሲዎንም፡እንድትሻሻል፡የነበረባቸውን፡ድካም፣ይኸውም፡ሥራ፡ጀማሪው፡እርሳቸው፡ኹነው፣ለወደፊት ሊከታተሉት፡የሚገባ፡ሰፊ፡ፕሮግራም፡መኾኑን፡ባለታሪኮቹ፡በሚገባ፡መጠን፡አልተገነዘቡትም። ስለዚህም፡ ካጻጻፋቸው፡ላይ፡ደኅና፡አድርገው፡አላጎሉትም። ግን ደግሞ፡በሰላም፡መኖርን፡ልምድ፡አድርጎ፡የኖረ፡ሕዝብ፡ሳያስበው፡እንደመብረቅ፡መዓት፡ያወረደበትን፡ንጉሥ፡ደግነቱንና፡ጨካኝነቱን፡ለማመዛዘን፡ባይችል፡አይፈረድበትም። የተወለደበትንና፡የሞተበትን፡ዘመን፡ለማወቅ ያልተቻለ፡አለቃ፡ዘወልድ፡ባ፲፰፻፺፩(1899)ዓ.ም፡አቅራ ቢያ፡‘ፊተኛይቱና፡ኋለኛይቱ፡ኢትዮጵያ’፡ብሎ፡ሰይሞ፡ ከዚህ፡በፊት፡በግእዝና፡በዐማርኛ፡ታሪክ፡ከጻፉት፡ደራሲዎቻችን፡በተለየ፡አስተያየት፡ስለኢትዮጵያ፡ኹኔታ ጽፏል።
አቶ፡ዐጽሜ(ተ፲፱፻፯/1914)፡የሽዋ፡ሰው፡ናቸው፤ ስለጋሎች፡የጻፉት፡ታሪክ፡እንግዲህ፡ወደአርባ፡ ዓመቱ፡ተቃርቦታል። ጋሎች፡ወደኢትዮጵያ፡የመጡበትን፡ዘመንና፡አኳኋናቸውን፡ለመግለጥ፡በብዙው፡ተጣጥረውበታል። አፈታሪኩን፡በብዙ፡ሥፍራ፡አጣርተውታል። ደግሞም፡በጻፉበት፡ዘመን፡የኤውሮጳ፡ሊቃውን ት፡ስለጋሎች፡ታሪክ፡ማጣራት፡የጀመሩትን፡አንዳንድ ጊዜ፡መሠረት፡አድርገውታል። ከኤውሮጳ፡ትምርት፡ ቤት፡በጣም፡ርቆ፡ለሚኖር፡ኢትዮጵያዊ፡በዚያ፡ዘመን፡ከርሳቸው፡በበለጠ፡አገላለጥ፡መጻፍ፡ይገባው፡ነበር፡ለማለት፡አይቻልምና፡ካገላለጣቸው፡አንዳንዱ፡ትክክለኛ፡ኹኖ፡ስንኳ፡ባይታይ፡የመጽሐፋቸው፡ረዳትነት የማይካድ፡ነው። በካቶሊክ፡ሃይማኖት፡ያዲሱ፡ትውል ድ፡ዘመን፡ሰው፡ስለነበሩ፡ለሃይማኖታቸው፡የነበረባቸው፡ቅንዓት፡በኦርቶዶክሳዊው፡ወገን፡ላይ፡ምክንያት፡ ባገኙ፡ቁጥር፡ከልክ፡ያለፈ፡የተግሣጽ፡ቃል፡አስጽፏቸዋል። አንዳንድ፡ጊዜም፡ታሪኩ፡መንገድ፡ሳይሰጣቸው፡በኦርቶዶክሳዊያን፡ላይ፡የኀይል፡ቃል፡ለመጻፍ፡ ምክንያቱን፡በግድ፡ፈልገው፡ያመጡት፡ይመስላል። ከዚህ፡በቀር፡ባገራችን፡በነበሩበት፡ዘመን፡የባለታሪክ፡ስም፡የተገባቸው፡ደራሲ፡ናቸው።
አለቃ፡ታየ፣(…ተ፲፱፻፲፮/1924)፡በጌምድሬ፡ና ቸው። በኢትዮጵያ፡ትምርት፡ተምረው፡የጨረሱትን፡ስንኳ፡ለማወቅ፡ባይቻል፡የስብከትና፡የድርሰት፡ስጦታ፡ እንደነበራቸው፡የታተሙትና፡ያልታተሙት፡መጻሕፍቶቻቸው፡ይመሰክሩላቸዋል። እርሳቸውም፡ለፕሮቴስታንት ሃይማኖት፡ዐዲስ፡ምእመን፡ነበሩና፡የያዙትን፡ሃይማኖት፡እውነተኛነት፡ለማስረዳት፡‘መዝገበ፡ቃላት’፡የሚባል፡መጽሐፍ፡ጽፈዋል። በዚህ፡መጽሐፍ፡ጦርነት፡ያነሡበት፣ከመጽሐፍ፡ቅዱስ፡ጋራ፡የማይስማማ፡ኹኖ የታያቸውን፣ሲወርድ፡ሲዋረድ፡የመጣውን፡ባገራችን ውስጥ፡ያለውን፡ልዩ፡ልዩ፡ባህል፡እንደዚኸውም፡ኹሉ፡መጽሐፍ፡ቅዱስን፡በፕሮተስታንት፡አካኼድ፡ባልተመለከተ፡ሊቅና፡አዋልድ(አፖክሪፍ)፡በምንላቸው፡መጻሕፍት፡ላይ፡ነው። በመዝገበ፡ቃላቱ፡እንደአቶ፡ዐጽሜ፡ያለ፡የዘለፋ፡ቃል፡የለበትም። ቢኖርም፡መጽሐፉ የተጻፈ፡ለታሪክ፡ሳይኾን፡ለሃይማኖት፡ማስረጃ፡ነውና፡ ሥፍራው፡ነው፡ያሰኛል። መጽሐፉ፡ስንኳ፡በኦርቶዶክሳዊያን፡ላይ፡ቢጻፍ፡ንግግሩ፡አብዛኛውን፡ጊዜ፡ሰው፡ የማያስቀይም፡የሊቅ፡አነጋገርና፡ስለሃይማኖት፡ክርክር ለሚጽፍ፡ሰው፡አብነት፡የሚኾን፡ነው።
አለቃ፡ታየ፡ከጥንት፡እስከ፡፲፱፻፲(=1918)፡ያለውን፡የኢትዮጵያ፡ታሪክ፡ጽፈዋል። መጽሐፉ፡ባለመታተሙ፡ከጥቂቶች፡ሊቃውንት፡በቀር፡የመረመረው፡የለም። መዝገበ፡ቃላትና፡ይህ፡ታሪክ፡ጠላት፡አገራችንን፡ከወረረው፡ወዲህ(፲፱፻፳፰-፲፱፻፴፫/1936-1941)፡የደረሱበት፡አልታወቀም። ሕዝቡ፡የሚያነበው፡አለቃ፡ታየ፡ስለኢትዮጵያ ሕዝብ፡ከብዙው፡በጥቂቱ፡የጻፉትን፡ነው።
በዚህ፡መጽሐፍ፡ውስጥ፡መሠረት፡አድርገው፡የሚከታተሉት፡
፩ኛ፣ መጽሐፍ፡ቅዱስን፣
፪ኛ፣ በኢትዮጵያ፡ስለታሪክ፡የ ሚናገሩትን፡መጻሕፍትና፡ከኹሉ፡ይልቅ፡ክብረነገሥትን፣
፫ኛ፣ የግሪክን፥የላቲንን፥የዐረብን፡ሊቃውንት፤
፬ኛ፣ በዛሬ፡ዘመን፡በኤውሮጳ፡የተጻፉትን፡ነው።
መጽሐፍ፡ቅዱስን፡የቀድሞ፡ሰዎች፡ባስተዋሉት፡መንገድ፡ ስለተከተሉት፡መንፈሳዊውን፡እንጂ፡ታሪካዊውን፡ጥቅሙን፡በጭራሽ፡አላገኙትም። እንደዚሁ፡ኹሉ፡ክብረነገሥታችንና፡ የቀሩትን፡የኢትዮጵያን፡መጻሕፍት፡የግሪክንና፡የላቲንን፡የዐረብንም፡መጻሕፍት፡ከኹለት፡መቶ ዓመት፡ወዲህ፡የኤውሮጳ፡ሊቃውንት፡አጣርተው፡የደረሱበት፡ፍጻሜ፡ከነወሬው፡ሳይደርስላቸው፡ቀርቶ፡ቃል፡በቃል፡ተከታትለውታል። በቅርብ፡ዘመንና፡ዛሬውኑ በኤውሮጳ፡ስለኢትዮጵያ፡መሠረት፡ባለው፡አካኼድ፡ የገለጡትን፡ሊቃውንት፡ግን፡ያንዳንዶቹን፡ስንኳ፡ስማቸውን፡ቢጠሩ፡ከነዚሁ፡ሊቃውንት፡አሳብ፡አንድዋ፡ ከጆሮዋቸው፡እንዳልደረሰች፡መጽሓፋቸው፡ድንቀኛ፡ አድርጐ፡ይመሰክራል። በሊቃውንቶቹ፡ፈንታ፡የታሪክ፡ ሊቃውንት፡መስለዋቸው፡ከኤውሮጳ፡ከዲፕሎማሲና፡ከጋዜጣ፡መልእክተኞች፡ያንዳንዱን፡አሳብ፡ተከትለዋል።
ይህ፡ኹሉ፡ቢኾን፡በሃይማኖት፡እንዳደረጉት፣በታሪክ እውነት፡ኹኖ፡በታያቸው፡አሳብ፡አንዳች፡ሥጋት፡ሳያድርባቸው፡በቅንነት፡አሳባቸውን፡ያስታወቁ፡ሰው፡ናቸው። ነገር፡ግን፡ኅሊናቸው፡የተረዳውን፡የሚቃወም ታሪክ፡ሲገጥማቸው፡ባንደበታቸው፡ጥራት፡መጠን፡ማስረጃ፡መስጠትን፡ያኽል፣‘የልጆች፡ጨዋታ፥የባልቴት ተረት’፡እያሉ፡አልፈውታል። እንዲህ፡ከሚሉት፡አብዛኛውንም፡ተረት፡ነው፡ቢሉት፡የተገባ፡ነው። ነገር፡ግን፡ የሚናገርና፡የሚጽፍ፡ሰው፣የማይስማማውን፡አሳብ፡ተረት፡እያለ፡ቢኼድ፣ሰሚና፡አንባቢ፡ደግሞ፡ማፍረሻውን፡አስረዳን፡ማለት፡እንዳለባቸው፡አለመዘንጋት፡ነው፤እንዲሁም፡በታሪክ፡ጻፊ፡እውነት፡ኹኖ፡ከሚታየው፡አንዳንድ፡ለሰሚው፡ግራ፡ኹኖ፡የሚታየው፡ይኖር ይኾናል። ባለታሪክ፡በእንዲህ፡ያለው፡ጊዜ፣የሚመታውን፡መላ፡ወይም፡ታሪኩን፡የሚመሠርትበትን፡ማስረጃ፡ማመልከት፡ዋና፡ሥራው፡ነበር። በዚህ፡ፈንታ፡አለቃ፡ታየና፡እስከዛሬ፡ከተነሡት፡ታሪክ፡ጻፎች፡አንዳንዶቹ፣አንባቢው፡ባይረዳው፡እነርሱ፡ለብቻቸው፡የተረዱትን፡‘እንደሃይማኖት፡ተቀበሉ!’፡ያልተረዱትን፡አሳብ ‘እኛ፡ተረት፡ካልነው፡አትቀበሉት!’፡ብለው፡የሚያዙ፡ ኹነው፡ይታዩናል። አንዳንድ፡ጊዜ፡ማስረጃ፡ብለው፡የሚያመጡት፡ንግግር፡ግን፡ከዚህ፡በፊት፡እንዳልኹት የታሪክን፡አካኼድ፡ያጣሩትን፡ሊቃውንት፡ሥራ፡ዙረው፡እንዳላዩት፡ንግግራቸው፡ያስረዳል። ይኹን፡እንጂ የመጽሐፍ፡አካኼድና፡መልክ፡ላለው፡ሥራቸው፡ለመጽሐፍ፡አጻጻፍ፡ንድፍ፡በመስጠታቸው፡ለአለቃ፡ታየና በዚህ፡ስማቸውን፡ለማነሣቸው፡ደራሲያን፡ኹሉ፡ያገራችን፡ሕዝብ፡ባለወረታቸው፡ነው።
አለቃ፡ታየ፡ወደኤውሮጳ፡እየተሻገሩ፣ባገራቸውም፡ከሕዝባቸው፡ማኽል፡ኹነው፡ሲጽፉና፡ሲያስተምሩ፡በነበሩበት፡ጊዜ፣ፊት፡ኤውሮጳ፥ኋላም፡ኢትዮጵያ፡ኹነው፡ላማርኛ፡አጻጻፍና፡ንግግር፡ብዙ፡ትጋት ያሳዩ፡ፕሮፌሰር፡አፈወርቅ፡ገብረየሱስ፡ናቸው።
በወጣትነታቸው፡ለትምርት፡ወደኤውሮጳ፡በመኼዳቸው፣በነገር፡አስተያየትም፡መልክ፡ባለው፡ንግግር፡አሳብን፡በጽሕፈት፡በመግለጥ፡ልዩ፡ስጦታ፡ያላቸው፡ደራሲ፡ናቸው።
የሕይወታቸው፡ታሪክ፡ግን፡እጅግ፡የሚያሳዝን፡ነው። የዛሬ፡፶ዓመት፡አቅራቢያ፡ዕድለኛ፡ኹነው፡ከጃንሆይ ዐጤ፡ምኒልክ፡ተመርጠው፡ለትምርት፡ወደኤውሮጳ፡ ተላኩ። የጣሊያን፡የጦርአለቃ፡ባራቲዬሪ፡፲፰፻፹፰/1896 መልሶ፡ወደሮማ፡እስኪልካቸው፡ድረስ፣ከኢትዮጵያ፡ ጠላት፡ጋር፡ተሰልፈው፡ዐዲግራት፡ድረስ፡መጡ። ኢትዮጵያ፡ይህን፡ኹሉ፡ሳትረሳ፣ይቅርታ፡አድርጋ፡በልጅ፡ኢያሱ፡ዐልጋ፡ወራሽነት፡ጊዜ፡ለትልቅ፡ሥራ፡አ ጨቻቸው። ለዚህ፡ወረታ፡ወጣቱን፡የኢትዮጵያ፡ዐልጋ ወራሽ፡ልጅ፡ኢያሱን፡በሚያምር፡ንግግር፡በማሞገስ፡ ደስታቸውን፡ገለጡ። በውነትም፡ልጅ፡ኢያሱ፡ባልኾኑ ካጤ፡ምኒልክ፡ጋራ፡የሠሩት፡መሳፍንትና፡መኳንንት ኹሉ፡ተቀይመዋቸው፡ነበርና፡አሳባቸው፡የነበረ፡በቤተ መንግሥት፡ሥራ፡ለማስያዝ፡ይቅርና፡የኢትዮጵያን፡ መሬት፡እንዳይረግጡ፡ለማድረግ፡ነው።
የኢትዮጵያ፡ ባላባቶች፡የልጅ፡ኢያሱ፡ሥራ፡አጀማመር፡ስለኢትዮጵያ፡ነጻነት፡ብዙ፡የሚያሠጋ፡ኹኖ፡ታይቶዋቸው፡ሥልጣናቸውን፡እንዲያስረክቡ፡ባስገደድዋቸው፡ጊዜ፡ፕሮፌሰር፡አፈወርቅ፡ከዚያ፡ኹሉ፡ሰው፡አብልጠው፡ለኢትዮጵያ፡የተቈረቆሩ፡መኾናቸውን፡ለማስረዳት፣የሚያምረውን፡ግጥማቸውን፡የልጅ፡ኢያሱ፡መስደቢያ፡በማድረጋቸው፡አበላሹት። እንኳን፡ይህን፣ከጠላት፡ጋር፡ አገራቸውን፡ሊወጉ፡የተሰለፉትን፡በደል፡የቤተመንግሥት፡አስተዳደሮች፡ትተውላቸው፡ነበርና፣አኹንም፡ንግሥት፡ዘውዲቱና፥ ጃንሆይ፡ቀዳማዊ፡ኀይለሥላሴ፡ዐልጋ፡ወራሽ፡ኹነው፡የመንግሥቱን፡ሥራ፡ሲያካኺዱበት፡በነበረ፡ጊዜ፣ ከፍተኛ፡የመንግሥት፡ሥራ፡ተቀበሉ፤ ከቶውንም፡በሚኒስትርነት፡ሥራ፡ወደሮም፡ተላኩ።
ጠላት አገራችንን፡ሲያጠፋት፣ አኹንም፡ተመልሰው፡ለጣልያን ዋና፡ሠራተኛ፡ኾኑለት፤ አገርን፡ለያዘ፡ጠላት፡ሳያስፈልግ፡ማገልገል፡እንኳ፡ከመነቀፍ፡ቢያደርስ፣ ይህ፡አልበቃ፡ብሎ፡ለጠላት፡ታማኝነታቸውን፡ለመግለጥ፡አኹንም፡ስላገሩ፡በሚከላከለው፡ላይ፡ከንጉሠ፡ነገሥቱ ጀምሮ፡እስከተራው፡አርበኛ፡ድረስ፡የማይጠጋውና፡ያልኾነ፡ቃል፡በመጻፍ፡ብዕራቸውን፡አበላሹ። ተራ፡ጸሓፊ፡በኾኑ፡የሚያሳዝነውን፡የሕይወታቸውን፡ታሪክ፡ሳላነሣው፡በቀረኹ፤ነገርግን፡ፕሮፌሰር፡አፈወርቅ፡እኛ ላለንበት፡ትውልድ፡ዋና፡ደራሲው፡ናቸውና፡ለሰው፡ ከደራሲነቱ፡ይልቅ፡ስሙንና፡ክብሩን፡በመጠበቅ፡ከኹሉ፡የበለጠ፡አክሊል፡እንደሚገባው፡ማስታወስ፡ግድ፡ ይለናል።
ፕሮፌሰር፡አፈወርቅ፡ባማርኛ፡ከጻፍዋቸው፡ መጻሕፍት፣‘የዐጤ፡ምኒልክ፡ታሪክ’ን፥‘ልብወለድ፡ታሪክ’፡ዋና፡ኹነው፡ይታዩናል። የነርሱን፡አኳኋን፡ከማስታወቅ፡በፊት፡የዐማርኛ፡ቋንቋ፡ሕጉንና፡ሕዝቡ፡የሚወደውን፡የንግግር፡ወይም፡ያጻጻፍ፡ዐይነት፡ብናመለክት፣ ከሕጉ፡ርቀው፡ዐዲስ፡አካኼድ፡የሰጡትን፡ደራሲያንና፡የተለምዶውን፡ንግግርና፡አጻጻፍ፡ሳይለቁ፡ጣዕም፡ያለበት፡ለማድረግ፡የቻሉትን፡ካልቻሉት፡ለመለየት፡ይረዳናል።
የዐማርኛ፡ቋንቋ፡ከብዙው፡ሕግጋቱ፡አንዱ፣ ማሰሪያ፡አንቀጽን፡ከንግግር፡መጨረሻ፡ማግባት፡ነው። ከጽሕፈት፡ላይ፡ባንድ፡ማሰሪያ፡አንቀጽ፡ውስጥ፡ባሉት፡ቃላት፡ማኽል፡ጣልቃ፡እያገባ፡ልዩ፡ልዩ፡አሳብና ንግግር፡በሚጨመርበት፡ጊዜ፡ዋናውንና፡ጣልቃ፡የገባውን፡ከውኖ፡ለማስተዋል፡እንዲመች፡ሊያደርጉ፡የቻሉ፡ስጦታ፡ያላቸው፡ደራሲያን፡ብቻ፡ናቸው።
ደራሲው፡ሙሉውን፡ንግግር፡ባማርኛ፡ባሕርይ፡በሚያስኬድበት፡ጊዜ፡ደግሞ፡ሰነፍ፡አንባቢ፡እንዳይታክተው፡ለማድረግ፡ያሰበበት፡እንደኾን፣ንግግሩን፡ባጭር፡ባጭሩ፡ በማሰሩ፡ላንባቢ፡መመቸቱ፡እርግጥ፡ነው፤ ቢኾንም፡ ደራሲ፡በፊተኛው፡(በረጅሙ)አካኼድ፡ሲጽፍ፡አንባቢው በውጥን፡ጭርስ፡አካኼድ፡አስሮ፡ለንግግሩ፡ደራሲው፡ ያላሰበውን፡አሳብ፡ከመስጠት፡የሚደርስበት፡ጊዜ፡አለ። ደራሲው፡በኹለተኛው፡አካኼድ(ባጭሩ)፡ሲጽፍ፣አንባቢው፡አኹን፡ካመለከትነው፡ስሕተት፡አይደርስም፤ ግን ንግግሩ፡ባንድ፡ማሰሪያ፡አንቀጽ፡ሊጠቀለል፡ሲቻል፣ ደራሲው፡እያቋረጠ፡በመናገር፡አንደበቱን፡ያልፈታ፡ሕፃን ሊመስል፡ነው። ንግግሩም፡በመጠኑ፡ካማርኛ፡ባሕርይ የራቀ፡ሊያደርገው፡ነው።
ዋና፡ደራሲ፡የምንለው፣በረዥሙም፡ኾነ፡ባጭሩ፡አካኼድ፡ጽፎ፣ ንግግሩ፡ግልጽና፡ጣዕም፡ያለው፡ሲኾን፡ነው። የኢትዮጵያ፡ሕዝብ፡ብቻ፡ሳይኾን፣ ሲበዛም፡ ሲያንስም፡በልዩ፡ልዩ፡ሕዝብ፡ይልቍንም፡በምሥራቃዊያን፡የተመለደ፡አካኼድ፡በኹለት፡በሦስት፡ፍች፡የሚተረጕም፡ቃል፡እየፈለጉ፡ከንግግር፡ማግባት፡ነው። እንዲህ፡ያለው፡አካኼድ፡‘ዐማርኛ’ወይም፡‘ስለምን’፡ይባላል (equivoque, jeu de motis, Claortour)። ይህም፡ በኢትዮጵያ፡እጅግ፡የተወደደና፡የተለመደ፡ንግግር፡ ኹኖ፡እንዲህ፡ያለውን፡ንግግር፡የሚያመጣ፡ሰው፡ኹሉ፡የንግግር፡ዕውቀት፡ያለው፡ሰው፡በመኾኑ፡የሚከራከርበት፡አይገኝም።
ኹለተኛ፣በአሳብ፡ከልብ፡ፈጥሮ፡ደጉንና፡ክፉውን፡በምሳሌ፡በሚገልጥበት፡ጊዜ፣ ክፉውንና፡ደጉን የሚገልጡትን፡ሰዎች፡አንባቢው፡ወይም፡ሰሚው፡በተሠራው፡ግብራቸው፡ባሕርያቸውን፡ስንኳ፡ቢለይ፣ ደራሲው፡በአሳቡ፡የፈጠራቸውን፡ሰዎች፡‘አቶ፡ክፉ፡ሰው’፥ ‘አቶ፡ደግ፡ሰው’፥‘ወይዘሮ፡ዓለሚቱ’፥ ይህነንም፡የመሰለ፡ስም፡ይሰይማቸዋል። እንዲህ፡ያለው፡አካኼድ አብዛኛውን፡ጊዜ፡ችክ፡ይላል። ስለኾነም፡በደራሲዎችና በሕዝቡ፡ተለምዷል፤ተወዷልም።
ፕሮፌሰር፡አፈወርቅ፡ከዚህ፡በላይ፣‘ስለምን’ና ‘የምሳሌ፡ስም’፡ያልነውን፡አካኼድ፡በብዙው፡አይከተሉትም። በተከተሉበት፡ጊዜም፡አንባቢውን፡ሳይሰለች፡ሃሳባቸውን፡እንዲያስተውል፡አድርገዋል። ሙሉ፡ንግግራቸው(Proposition) ያማርኛን፡ባሕርይ፡እየተከተለ፡በረዘመበት፡ጊዜም፡ቢኾን፣ ግልጥና፡ያማረበት፡ነው። አንዳንድ፡ጊዜ፡ብቻ፡ቅጽል፡ሲያበዙ፡ነገሩ፡ጉት፡ይኾንባቸዋል። ፕሮፌሰር፡አፈወርቅ፡በደራሲነታቸው፡ሙቀት ያለበት፡ንግግር፡ማምጣት፡ዋና፡ባሕርያቸው፡ነው። ሙቀቱም፡የሚገባ፡ወይም፡ተሸጋጋሪ፡በመኾኑ፣ አንባቢው፡አሳባቸውንም፡በማይቀበልበት፡ጊዜ፡መሞቁ፡አይቀርም። በጽሑፍ፡ሥራቸው፡የሚያነሡት፡ሰው፡ወይም፡እንሰሳ፣ ጫካ፡ወይም፡በረኻ፡ኹሉም፡ሕይወት፡ያለበት፡ኹኖ፡ይታያል።
ፕሮፌሰር፡አፈወርቅ፡አንድ፡‘የዐጤ፡ምኒልክ ታሪክ’ና፡አንድ፡‘ልብወለድ፡ታሪክ‘ *(Roman)፡ጽፈዋል። የቀሩት፡በጣልያንና፡በፈረንሳይ፡ቋንቋ፡የጻፏቸው፡መጻሕፍት፡የዐማርኛን፡ሰዋስውና፡የኢትዮጵያን፡ኹኔታ፡ የሚያስታውሱ፡ናቸው።
ፕሮፌሰር፡አፈወርቅ፡የዐጤ፡ምኒልክን፡ታሪክ ሲጽፉ፣ንጉሠነገሥቱ፡ከደረሰባቸውና፡ከሠሩት፡ዝርዝር ሳይገቡ፡ዋና፡ዋናውን፡ብቻ፡አመልክተዋል። ጥቂት፡ ዝርዝር፡ያለበት፡ስለዐጤ፡ምኒልክ፡የኢጣልያ፡መንግሥት፡መልእክተኞች፡የሚናገረው፡ክፍል፡ነው። የዐጤ ምኒልክን፡ታሪክ፡ባጭሩ፡ካመለከቱ፡በኋላ፡የጣልያን፡ መንግሥት፡መልእክተኞች፡ፕሮፌሰር፡አፈወርቅን፡እንዲረዱዋቸው፡በገንዘብ፡ሳይቀር፡ሊያባብልዋቸው፡እንደ ሞከሩ፣እርሳቸው፡ግን፡ሳይታለሉላቸው፡በመቅረታቸው የንጉሣቸውን፡ፖለቲክ፡እንደደገፉ፡ለማስረዳት፡ይጣጣራሉ። በንግግራቸው፡ለምኒልክና፡ለሽዋ፣ሲኾን፡ቁልምጫውንና፡ቃለአጋኖውን፡ማብዛታቸው፣ለሌላው፡ወረዳ ባላባትና፡ሕዝብ፡ሲኾን፡ማዋረዳቸውና፡መሣቂያ፡ለማድረግ፡መታገላቸው፣ ለባለታሪክ፡የተገባውን፡እውነተኛ፡ሚዛን፡የያዙ፡በመኾን፡ፈንታ፣ ከዳተኛ፡ካለቸቻው፡አገራቸው፡ጋር፡ለመቃረብና፡የመንግሥቱን፡የ ያዙትን፡ደስ፡ለማሰኘት፡የተነሡ፡ያስመስላቸዋል። ግን ደግሞ፡ከባለታሪክ፡ልዩ፡ሥራ፡አንዳንዱን፡እንዳልዘነጉትና፡ለታሪክ፡ንግግር፡ዐዲስ፡መንገድ፡እንደጠረጉለት ዐጭሩ፡የምኒልክ፡ታሪክ፡እንደሚያስረዳ፡ማስታወቅ፡ይገባናል።
‘ልብወለድ፡ታሪክ’፡ለኢትዮጵያ፡የሮማን፡መዠመሪያ፡መጽሐፍዋ፡ነው።* ከዚህ፡በፊት፡እንዳለመለከትኹት፣ያገራችን፡ደራሲ፡አሳቡን፡በጽሕፈት፡ለመግለጥ፡ባሰበበት፡ጊዜ፡ባሳቡ፡የሚፈጥራቸው፡ሰዎች፡የግብራቸውን፡ስም፡የተጸውዖ፡ስም፡አድርጎ፡‘አቶ፡መልካም፡ሰው፥አቶ፡ክፉ፡ሰው’፡የሚሉትን፡አካኼድ፡ብቻ፡ይከታተል፡ነበር። የፕሮፌሰር፡አፈወርቅንና፡የኤውሮጳን፡መጻሕፍት፡በማንበቡ፡ልብወለድ፡ታሪክ(ሮማን) ለመጻፍ፡ይጣጣራልና፡በር፡ከፋቹ፡ፕሮፌሰር፡አፈወርቅ፡በመኾናቸው፡ምስጋና፡ይገባቸዋል።
የፕሮፌሰር፡አፈወርቅ፡ልብወለድ፡ታሪክ፡የሚነግረን፡የኹለት፡ወጣቶችን፡ፍቅር፡ነው። ኹሉም፡ኢትዮጵያዊያን፡ኹነው፣ ሃይማኖታቸው፡የወንድየው፡እስላም፥የሴቲቱ፡ክርስቲያን፡ነው። ከኹለት፡በፍቅር፡ድል ኾኖ፡የወዳጁን፡ሃይማኖት፡የተቀበለ፡ወንድየው፡ነው። መጽሐፉ፡የፍቅር፡ኀይል፡ብርቱ፡መኾኑንና፡የንጹሕ ፍቅር፡አካኼድ፡እንዴት፡መኾን፡እንደሚገባው፡ከሚያስተምረን፡በላይ፡እግረ፡መንገዱን፡ደግሞ፡የዛሬ፡ሰባት፡ወይም፡ስምንት፡መቶ፡ዓመት፡በኢትዮጵያ፡ሲደረግ፡ከነበረው፡ሥራ፡ከብዙው፡ጥቂቱን፡ያመለክተናል። ደራሲው፡የጽሕፈት፡አገላለጣቸው፡ደግ፡ሲኾን፣ምክንያት፡ለመፍጠር፡ብዙ፡መንገድ፡አልተገለጣቸውም። ባሳባቸው፡የፈጠሩዋቸው፡ሰዎች፡ለሚፈጽሙት፡ኹለት ሦስት፡ልዩ፡ልዩ፡ሥራ፡አንድ፡ምክንያት፡ሰጥተው፡ያንኑ፡አንዱን፡ምክንያት፡ሳይለውጡ፡ኹለት፡ሦስት፡ጊዜ፡ደጋግመውታል። ይህንና፡ሌላውን፡ብልኀት(የቴክኒክ ጣጣ)፡የዋናው፡ሥራቸው፡ንድፍ፡(ፕላን)፡ተስተካክሎ ለመኼዱ፡አንባቢው፡ከሌለ፡ይቆጥረዋል። ይህም፡አንድ፡ኪነጥበብ፡ነው።
ፕሮፌሰር፡አፈወርቅ፡ኹለት፡ሦስት፡ያኽል፡ቲያትር፡ጽፈዋል። ነገር፡ግን፡እስካኹን፡ድረስ፡ሰው፡በቲያትር፡ጨዋታ፡አላያቸውም፤ ደግሞም፡አልታተሙም። እንደዚሁ፡ኹሉ፣ብዙ፡ደራሲያን፡ጽፈው፡ያላሳተሙ፡አሉና፡ሥራቸው፡በሕዝብ፡ስላልታወቀ፡ስለነርሱ፡ለመጻፍ፡ከዚህ፡ ቦታው አይዶለምና፡እንተወዋለን።
ቢኾን ም፡ከነዚህ፡ያንዱን፡የበጅሮንድ፡ተክለሐዋርያትን፡ስም ፡ማስታወስ፡የተገባ፡ነው። አገራቸው፡ሸዋ፤ የተወለዱበ ት፡ዘመን፡ባ፲፰፻፸፭፡ግድም፡ነው። እርሻና፡የወታደርነት፡ሥራ፡በሞስኮብና፡በፈረንሳይ፡አገር፡ተምረው፡በኢትዮጵያ፡መንግሥት፡ከፍ፡ባለ፡ልዩ፡ልዩ፡ሹመት ላይ፡ኑረው፡በመጨረሻ፡ጊዜ፡በፓሪስና፡በዤኔቭ፡የኢትዮጵያ፡መንግሥት፡ሚኒስትር፡ኹነው፡ነበር። ፍጹም፡ዐማርኛ፡በኾነ፡ግጥም፡ጥቂት፡ተረት፡ጽፈው፡ካሳተሙና፡በተረት፡ዐይነት፡ቲያትር፡ከጻፉ፡በኋላ፣አኹንም፡ንጹሕ፡በኾነ፡ዐማርኛ፡ስለዕርሻ፡ትምርት፡ጽፈዋል። በዚህም፡መጽሐፍ፡በዐማርኛ፡ቃል፡ላልተገኘለት፡ለአልኺሚና፡ለሌላው፡ዕውቀት፡የተመረጠ፡ቃል በመገኘቱ፡ዕውቀትን፡በእውነት፡እጅ፡ካደረጉት፡ለደራሲ፡ቋንቋን፡እንደልቡ፡ማዘዝ፡እንደማያስቸግር፡ያስረዳል። በጅሮንድ፡ተክለሐዋርያት፡ለኢትዮጵያ፡ሕገመንግሥት፡መግለጫ፡የተናገሩትና፡የጻፉት፡ደግሞ፡የደራሲና፡የተሰወረን፡አሳብ፡ለመግለጥ፡ችሎት፡እንዳላቸው፡ያስረዳል።
ነጋድራስ፡ገብረሕይወት፡ትውልዳቸው፡ትግሬ ኾነው፡የሞቱበት፡ከዛሬ፡፴ዓመት፡በፊት፡ነው። በልጅነታቸው፡ነምሳ፡አገር፡ብዙ፡ተቀምጠው፡በትምርታቸው፡ሳሉ፡ስለዐጤ፡ምኒልክና፡የኢትዮጵያ፡ሕዝብ፡በሐማሴን፡ሲታተም፡ከነበረ፡ጋዜጣ፡አሳትመዋል።‘የመንግሥትና፡የሕዝብ፡አስተዳደር’፡ብለው፡የሰየሙትን፡ መጽሐፍ፡ከሞቱ፡በኋላ፡ወዳጆቻቸው፡አሳትመዉታል። በኹለቱም፡ኹሉ፡መጻሕፍት፡ኢትዮጵያዊ፡በሚረዳው አካኼድ፡የቤተመንግሥቱ፡ሥራ፡መሻሻል፡እንዳለበት፡ሰብከዋል። ኹለቱም፡መጻሕፍት፡ደራሲው፡በልበሙሉነት ስለሚገልጡት፡ከፍተኛ፡አሳብና፡ስለንግግራቸው፡ጥራት፡በዛሬይቱ፡ኢትዮጵያ፡ብዙ፡ጕዳይ፡ለማሠራትና፡ ለወደፊት፣ሕግንና፡ልማድን፡እያሻሻሉ፡ለማደስ፡ስላለብን፡ሥራ፣ብርቱ፡አሳብ፡የሚያሳድሩ፡የሚያስፈጽሙም፡መጻሕፍት፡ናቸው።
ብላቴን፡ጌታ፡ኅሩይ፡ሸዌ፡…(ተ፲፱፻፴፩=1939 በባት፡ከተማ፡በእንግሊዝ፡አገር።) በኢትዮጵያ፡ከፍተኛውን፡ትምርት፡ፈጽመው፡በቤተክህነት፡ሲያገለግሉ፡ ኑረው፡ሠላሳ፡ዓመት፡ያኽል፡በቤተመንግሥት፡ልዩ፡ልዩና፡ከፍ፡ያለ:ሹመት፡ተቀብለው፡ከባድ፡የኾነ፡የኀላፊነት፡ሥራ፡የፈጸሙ፡ሰው፡ናቸው። የአኹኑ፡ማስታወሻ፡ስለደራሲነታቸው፡ብቻ፡የሚናገር፡በመኾኑ፡በሹመታቸው፡ስላስኬዱት፡ትላልቅ፡ሥራ፡ከዚህ፡ማንሣት የለብንም። ከጽሑፍ፡ሥራቸውም፡ዋና፡ኹነው፡የሚታዩን፡‘ወዳጄ፡ልቤ’ና፥‘ጎሐ፡ጽባሕ’፡‘ሀገረ፡ጃፓን’፥ በመኾናቸው፡የቀሩት፡መጻሕፍቶቻቸው፡ግን፡ለኢትዮጵያ፡ሕዝብ፡ስንኳ፡በብዙው፡ቢጠቅሙት፡አሳባቸውንና፡ደራሲነታቸውን፡በሦስቱ፡መጻሕፍት፡ማግኘት፡ስለ ተቻለ፡ስለነርሱ፡ብቻ፡ባጭሩ፡እናመለክታለን። ብላቴን፡ጌታ፡ኅሩይ፡በጻፉት፡ኹሉ፡ዋና፡አሳባቸው፤
፩. በአርኣያ፡እግዚአብሔር፡የተፈጠረ፡ሰው፡ኹሉ፡በፈጣሪውና፡በመንግሥት፡ዘንድ፡አኳያ፡መኾኑን፡ነው። የውነት፡ነው። ሲፈጠር፡ብልኅና፡ሞኝ፡ኹንዋል፤በሥራ፡ዕውቀትና፡ዕድለኛ፡በመኾን፡ከሰው ፡የተሠራ፡አስፈላጊ፡የኾነ፡የመዐርግ፡ከፍተኛነትና፡ ዝቅተኛነት፡ይህንንም፡የመሰለ፡ብዙ፡ልዩነት፡አለ። ነገር፡ግን፡በምንፈርድለትና፡በምንፈርድበት፡ጊዜ ፡ መሠረት፡ልናደርገው፡የሚገባነ፡ኹሉም፡ትክክል መኾኑን፡ነው።
፪. በዘርና፡በሃይማኖት፡የመጣውን፡ልዩነትም፡እርስ በርሳችን፡ተቻችለን፡ከሌለ፡መቍጠር፡ይገባናል።
፫. የክርስቲያን፡ሃይማኖት፡በዓለም፡ከታወቁት፡ሃይማኖቶች፡ለመንፈሳዊና፡ለሥጋዊ፡ኑሮ፡የሚስማማ፡ነው።
፬. ሰው፡በማናቸውም፡ሰዓት፡ሞት፡እንደሚመጣበት፡ማሰብ፡ይገባዋል። ፟
፭. ሰው፡የልማድ፡ባሪያ፡ሳይኾን፡በነጻነት፡ሕጉንና፡ ሥርዐቱን፡እያሻሻለ፡መኼድ፡አለበት።
ብላቴን፡ጌታ፡ኅሩይ፡ከጻፍዋቸው፡መጻሕፍት ከኹሉ፡ይልቅ፡ዕድለኛ፡ኹኖ፡ሕዝቡ፡አንብቦ፡የማይጠግበው፡‘ወዳጄ፡ልቤ’ን፡ነው። እንዲህ፡ያለውን፡መጽሐፍ፡የሚጽፍ፡የእንግሊዙን፡ደራሲ፡የዮሐንስ፡ቡንያንን፡መጽሐፍ፡ያነበበ፡ሰው፡ብቻ፡መኾኑን፡የምንረዳው፡የዚሁኑ፡ደራሲ፡‘የክርስቲያን፡መንገድ’፡የተባለውን፡መጽሐፉን፡ስናነብ፡ነው።
ብላቴን፡ጌታ፡ኅሩይ፡ግን፡ንድፉን(ፕላኑን)፡ስንኳ፡ከእንግሊዙ፡ደራሲ፡ቢቀበሉ የጽሑፋቸውን፡ሕንጻ፡መልክና፡ጠባይ፡በፍጹም፡ኢትዮጵያዊ፡ያውም፡የሚያምር፡ኢትዮጵያዊ፡አድርገውታል። ባሳባቸው፡የፈጠሩት፡‘ወዳጄ፡ልቤ’፡የተባለው ሰው፡የርሳቸው፡ራሳቸው፡ወይም፡የክርስቲያንን፡ሕግ ለመጠበቅ፡የሚታገል፡ሰው፡ምሳሌ፡ነው። ወዳጄ፡ልቤ፡ለብቻው፡ኹኖ፡የእግዚአብሔርን፡ህላዌና፡የሕዝበ አዳምን፡በተለይም፡የነፍስን፡ኹኔታ፡በሚያስብበት፡ጊዜ፣ ወይም፡እግር፡ጥሎት፡ከልዩ፡ልዩ፡ሰዎች፡ጋር፡ተገናኝቶ፡ክፋታቸውንና፡በጎነታቸውን፡በሚገልጥበት፡ጊዜ፡ ሥጋ፡በለበሰ፡ኹሉ፡ላይ፡በተለይም፡በክርስቲያን፡ላይ የሚመጣበትን፡መከራ፡ሲያስታውስ፣ተስፋ፡ሊቆርጥ፡ ሲቃጣና፡በርትቶ፡ሲታገል፡ከባልንዠሮቹ፡ጋርና፡ለብቻው፡መሰንቆውን፡ይዞ፡ሲያንጐራጕር፣በሰርግ፡አስመስሎ፡ስለክርስቲያን፡ሃይማኖት፡አዠማመርና፣ድል እየነሣ፡በኼደበት፥በሚኼድበትም፡ዘመን፡ኹሉ፡ያለበትን፡መከራ፡ሲተርክ፣ፍጹም፡ክርስቲያናዊ፡ነው።
‘ወዳጄ፡ልቤ’፡‘ሰው፡በየሱስ፡ክርስቶስ፡ካመነ፡በኋላ፡ከኀጢአት፡ላይ፡ላለመውደቅ፡ምን፡ቢሠራ ይሻላል?’፡ብሎ፡የሚጠይቅ፡ወይም፡የዚህን፡አሳብ፡ የሚያሳድር፡ኹኖ፡ይታያል። አንባቢው፡ቍልፉን፡ወይም መልሱን፡አገኘኹ!መጽሐፉ፡ሊነግረኝ፡ነው፡ብሎ፡ሲጓጓ፣‘ብፁዐን፡እለ፡ተኃድገ፡ሎሙ፡ኃጢኣቶሙ’፡ ብሎ፡ያሰናብተዋል።
ብላቴን፡ጌታ፡ኅሩይ፡ስለሃይማኖትና፡ስለፖለቲክ፥ስለልዩ፡ልዩ፡ጕዳይም፡ያሰቡትን፡ኹሉ፡ካንድ፡ላይ፡ሰብስበው፡ጽፈው፡ያወጡትን፡መጽሐፍ፡‘ጎሐ፡ጽባሕ’፡ብለው፡ሰይመውታል። ጎሐ፡ጽባሕ፡ስለሃይማኖት የሚገልጠው፡አሳብ፣ንግግሩም፡ልዩ፡ቢኾን፡ከወዳጄ ልቤ፡አይለይም። ሕግንና፡ልማድን፡ማሻሻል፡ብላቴን ጌታ፡ኅሩይ፡ሥራዬ፡ብለው፡የቆሙበት፡ዋና፡ሐሳብ በመኾኑ፥ ስለቅዱሳት፡መጻሕፍት፡ቍጥር፣ ስለምንኵስናና፡ስለጋብቻ፡ሥርዐት፥ ስለጸሎትና፡ስለንስሐ፡ከጻፉት ክፍል፡የኢትዮጵያ፡የሃይማኖት፡ሥርዐት፡እየተሻሻለ፡ የሚኼድበትን፡መንገድ፡መሠረት፡ባለው፡አካኼድ፡ አስረድተዋል። ከቤተክህነት፣ ቤተመንግሥትን፡መምራት ይገባኛል፡እያለ፣በመነፈሳዊውና፡በሥጋዊው፡ጕዳይ፡ ላይ፡የበላይ፡አስተዳዳሪ፡ልኹን፡የሚል፡እንደማይጠፋ ስለተረዱት፡የኹለቱንም፡ሥልጣን፡ወስነው፡ኹሉም፡ በየክፍሉ፥ በየሥራው፡አላፊነት፡እንዳለበት፣ የኹሉ፡የበላይ፡ግን፡መንግሥት፡መኾኑን፡አደላድለው፡ወስነዋል። ወገን፡ለሌለው፥ በዘር፡በሃይማኖት፡ለተለየ፡ሰውና፡ለእንሰሳ፡ርኅራኄ፡እንዲገባ፡በብዙው፡ሰብከዋል። ለዛሬ ው፡ትውልድ፡ኢትዮጵያዊ፡አንዳንዱ፡ስንኳ፡የዚህ፡ዐይነት፡ምክር፡ባያስፈልገው፡ካገራችን፡ሕዝብ፡ላብዛኛው፡ዐዲስ፡ነገር፡ኹኖ፡ታይቶት፡ከአሳባቸው፡አንዳንዱ፡ለመቀበል፡የሚያስቸግር፡ኹኖ፡ሳይታየው፡የማይቀር፡ነውና፣ መጽሐፉ፡ለእንደዚህ፡ያለው፡ክፍል፡ብርቱ፡አሳብ፡የሚያሳድርበትና፡ጥቅም፡ያለው፡ክርክር፡የሚያስነሣ፡ነው።
ብላቴን፡ጌታ፡ኅሩይ፡ገና፡ወደጃፓን፡የመንግሥት፡መልእክተኛ፡ኹነው፡ሳይኼዱና፡ከዚያ፡በኋላ፡ ከኢትዮጵያ፡ውጭ፡ስላይዋቸው፡አገሮች፡ኹኔታ፡የጻፏቸው፡መጻሕፍት፡አሉ። በተስተካከለ፡ዐማርኛና፡ያላዩትን፡አገርና፡ሕዝብ፡ካዩት፡በሚያስቈጥር፡አነጋገር፡ የመንገዳቸውን፡አኳዃን፡የገለጡበት፡መጽሐፍ፡ግን፡ ‘ማኅደረ፡ብርሃን’(ሀገረ፡ጃፓን)፡ብለው፡የሰየሙት፡ነው።
መጽሐፉ፡ከማያስፈልግና፡ከሚያታክት፡ዝርዝር፡ ሳይገባ፡በወሬ፡የምናውቀው፡የጃፓን፡አገርና፡ሕዝቡ፣ ሃይማኖቱ፣ያገሩ፡ልማድ፣ሥልጣኔውና፡አስተዳደሩ፡ ምን፡እንደኾነ፡ነግሮ፡የሚያጠግብ፡ነው። ደራሲው፡የተላኩበት፡ሥራ፡ከሕዝብና፡ከትላልቅ፡ሰው፥ ከንጉሠነገሥትና፡ከንግሥቲቱ፡ጋር፡የሚያገናኝ፡በመኾኑ፣የሆቴሉንና፡የባላገሩን፥የሚኒስትሮቹንና፡የቤተመንግሥቱን ዕልፍኝ፡ታዳራሽ፡ወጉንና፡ሥርዐቱን፡አይተዋል። ከዚህም፡ኹሉ፡ጋራ፡ጃፓን፡ሕዝብ፡መኾን፡ከዠመረበት ዘመን፡አንሥቶ፡እስከዛሬ፡ድረስ፡ያለውን፡ታሪኩን፡እንድናውቀው፡ከሌላ፡ባለታሪክ፡እየጠቀሱ፡ባጭሩ፡ተርከውልናል። የባሕሩንና፡የመሬቱን፣ የጫካውን፡ኹኔታ፡የሚነግረው፡ክፍል፣ ደኅና፡ሥዕል፡ሣይ፡በሚስማማ፡ቀለም፡ነድፎ፡ያቀረበው፡ሠሌዳ፡ይመስላል። ክርስቲያኑ ኅሩይ፣ ክርስቲያን፡ያይደሉትን፡ወገኖች፡አምልኮና፡ባህል፡የሚያዩት፡እጅግ፡ከፍ፡ባለ፡አስተያየት፡ነው። የጃፓን፡አምልኮም፡እንደሌላው፡አምልኮ፡የእግዚአብሔርን ምስጢር፡ለማግኘት፡የሚጣጣር፡ኹኖ፡ስለታያቸው፣ ያገራችን፡ሕዝብ፡ደግሞ፡ባይቀበለውም፡በሰፊው፡እንዲመለከተው፡አድርገው፡ገልጠውታል።
ከዚያ፡በፊት፡ልዩ ልዩ፡መጻሕፍት፡በመጻፍ፡ ብዙ፡ትግል፡ያየው፡የብላቴን፡ጌታ፡አእምሮ፡ዐማርኛ፣ ሀገረ፡ጃፓንን፡በጻፈበት፡ጊዜ፣ ደርጅቶ፡ከፍ፡ካለ፡ደረጃ፡የደረሰ፡ኹኖ፡ይታያል። ዐማርኛ፡ማሰሪያ፡አንቀጹን፡አርቆ፡ከማኽሉ፡ ልዩ፡ልዩ፡አሳብ፡ጣልቃ፡ማስገባት፡የተፈጥሮ፡ጠባዩ ነው፡ብለናል። ብላቴን፡ጌታ፡ኅሩይ፡አብዛኛውን፡ጊዜ ይህን፡ሳይከተሉ፡ንግግሩን፡ባጭር፡ባጭሩ፡ማሰር፡ልዩ ባሕሪያቸው፡ነው። ከዐማርኛ፡መርማሮች፡አንዳንድ፡ ሰው፡ብላቴን፡ጌታ፡ኅሩይ፡ዐማርኛን፡በውጭ፡አገር፡ (በኤውሮጳ)፡ንግግር፡ዐይነት፡እንጂ፡በተፈጥሮ፡ጠባዩ አያስኬዱም፡ብሎ፡ጽፎባቸዋል። ነገሩም፡እውነት፡ይኾናል፤ግን፡ደግሞ፡ደራሲ፡መከተልና፡ማሻሻል፡የሚገባው፡የሚጽፈበትን፡ቋንቋ፡ጠባይ፡ነው፡ስለተባለ፣ ይኸው፡ደራሲ፡የሚጽፈው፣ የንግግር፡ጣዕም፡ያለውና፡ በፍጥነት፡የሚያስተውሉት፡ከኾነ፣ ከተራው፡ሕዝብ፡ተለይቶ፡ማዕርግ፡ያለው፡ደራሲ፡ነው፡መባልን፡አያግደውም። ብላቴን፡ጌታ፡ኅሩይ፡ለሕፃናትና፡አእምሮ፡ለዋጭ፡የሚኾኑ፡ልዩ፡ልዩ፡መጻሕፍት፡ትተውልናል። እንዲያውም፡ከመጻሕፍት፡ዐይነት፡በጽሕፈት፡በመግለጥ፡ያልሞከሩት፡ጥቂት፡ነው፡ማለት፡ይቻላል።
በሥራ የተፈነው፡የተፈጥሮ፡ባሕሪያቸው፡ትዕግሥተኛ፡ሲኾን፣ ጽሕፈት፡ሲልዋቸው፡ፍጥነታቸው፡የመኪና፡ያኽል፡ስለነበረ፣ ካማርኛቸው፡በቀር፣ለወጣቱ፡ኢትዮጵያዊ፡ላንዳንዱ፡የጻፉት፡ታሪክና፡ልብወለድ፡ታሪክ፥ ሌላውም ኹሉ፡አብዛኛውን፡ጊዜ፡ውዝፍ፡ኹኖ፡ይታየዋል። ምክንያቱም፡በቤተመንግሥት፡የነበረባቸው፡ከባድ፡ሥራ፣ ለሚጽፉት፡መጽሐፍ፡የተገባውን፡ምርመራ፡ለማጥለቅና፡ለማስፋፋት፡ፋታ፡አልሰጣቸው፡ስላለና፡ላገራቸው ሕዝብ፡በነበረባቸው፡ፍቅር፣ እርሳቸው፡ካወቁት፡ከብዙው፡ጥቂቱን፡ሳያስታውቁት፡ቢቀሩ፡‘ዘደፈነ፡ወርቅ፡ እግዚኡ’፡እንዳይኾኑ፡ሲሉ፡ይኾናል። የሒሳብና፥ የፍልስፍና፡የሕክምና፡የሥነፍጥረት፡ይህንም፡የመሰለው፡ልዩ ልዩ፡ዕውቀት፡የተጻፈበትን፡ጽሑፍ፡ሥራ፡ቋንቋው የተጣራ፡ቢኾን፡ያንኑ፡ዕውቀት፡የተማረ፡ሰው፡ካልኾነ፡በቀር፣ በሌላ፡ዕውቀትም፡ሊቅ፡የኾነ፡ሰው፡አያስተውለውም። የድርሰት፡ስጦታቸው፡አንዳንድ፡ሰዎች፡ግን፣ እንኳንስና፡የተማረ፡ሰው፡ተራው፡ሕዝብ፡ሳይቀር በሚያስተውለው፡ንግግር፡ልዩ፡ዕውቀታቸውን፡ለመጻፍ ተችሏቸዋል።
ቃለእግዚአብሔር(theologie)፡የሚያስተምሩና፡የሃይማኖትን፡መጻሕፍት፡የሚተረጕሙ፥ ስለሃይማኖትም፡የሚጽፉት፡ሊቃውንት፣ ምስጢሩ፡ግድ፡እያላቸው፡ንግግራቸው፡ወይም፡አጻጻፋቸው፡ዐማርኛ፡ዐወቅኹ፡ለሚል፡ኹሉ፡የማይደፈር፡ኹኖ፡ይኖራል። ደግምም፡ትምርት፡ሲባል፡ከጥንት፡እስከዛሬ፥ ያገር፥የመንግሥት፡ወሰን፣ የማያግደው፡አገሩና፡መንግሥቱም ቢለያዩ፡ሰንደቅዓላማው፡ወይም፡ወገኑ፡አንድ፡የኾነ፡ ነው። ለጊዜው፡ያገራችን፡ሊቃውንት፡ከኢትዮጵያ፡ወደ ውጭ፡ያለው፡ትምርትና፡ዕውቀት፡ባዕድ፡ኹኖባቸዋል።
አለቃ፡ኪዳነወልድ፡ክፍሌ፡ትውልዳቸው፡ሸዋ፣ ትምርታቸው፡ጐንደር፡ነው። ዕድሜያቸው፡፸፫ዓመት ይኾናል። በኢትዮጵያ፡መጻሕፍት፡ካላቸው፡ከሰፊው፡ ዕውቀታቸው፡በላይ፣ላገራችን፡መጻሕፍት፡ምስጢርና (Sens) ታሪክ፡አስፈላጊ፡የኾነውን፡የመጽሐፍ፡ቅዱስን፡ ዕብራይስጥ፡ጨምረውበታል። የሕዝቅኤልን፡ትንቢት፡ ዕብራይስጡን፡ወደዐማርኛ፡ገልብጠው፡ባማርኛ፡የጨመሩበት፡መግለጫ፣ ከኹሉ፡በፊት፡ላገራችን፡ሊቃውንት፡ከግሪክ፡ተተርጕሞ፡በግእዝ፡ተቀብለውት፡የሚኖሩትን፡የብሉያትን፡መጻሕፍት፣ ዋናውን፡አብነት፡ዕብራይስጡን፡እያዩ፡ማቃናት፡እንዳለባቸው፡አነቃቅተዋቸዋል። ዳግመኛ፡ትምርቱም፡መጠነኛ፡ቢኾን፥ዐማርኛ ያወቀ፡ኹሉ፡ሊያስተውለውና፡ሊያጣጥመው፡በሚችል ንግግር፡በመግለጣቸው፡ተራውን፡ሕዝብ፡ሳይቀር፡ከሊቃውንቱ፡ዕውቀት፡እንዲካፈል፡አድርገውታል።
እግረ መንገዳቸውንም፡ልዩ፡ለኾነው፡ከባድ፡ዕውቀት፣ልዩ የኾነና፡ያጌጠ፡ዐማርኛ፡ፈጥረውለታል። እርሳቸው፡ከዛሬ፡ሠላሳ፡ዐመት፡በፊት፡ኢየሩሳሌም፡ኼደው፡ዕብራይስጥ፡በተማሩበት፡ዘመን፡የነበረውን፡ችግር፡ያስተዋለ፡ሰው፡ብቻ፡ድካማቸውን፡ሊመዝነውና፡ሞያቸው ትልቅ፡መኾኑን፡ሊረዳው፡ይችላል።
ፍቅርና፡አንድነት በተሰበከበት፡አገር፡በኢየሩሳሌም፡ጠብና፡መለያየት፡ ተዘርቶበት፡ነበር። ዛሬውንም፡ገና፡አላለፈለትም። ከዚያ፡የነበረው፡የኢትዮጵያ፡መነኮሳት፡ማኅበር፡ከጸሎት በቀር፣ ትምርት፡መቀጠል፡የማያስፈልግ፡ሥራ፡ኹኖ ሲታየው፣ እስራኤላዊ፡ደግሞ፡በዓለም፡ያለ፡ሕዝብ፡ዐሥር፡ቢማር፡እንደማያፈቅረው፡ተረድቶት፡ቋንቋውን ሊማርለት፡የመጣውን፡ክርስቲያን፡መርዳት፣ እባብን፡ ከመቀለብ፡ይቈጥረው፡ነበር። ስለዚህም፡አለቃ፡ኪዳነ ወልድ፡ዕብራይስጥ፡የተማሩት፡በኹለት፡ፊት፡ሥቃያት፡እያዩ፡ነው። ይህ፡ኹሉ፡ድካማቸው፡በክርስቲያን ሊቃውንት፡ጭምር፡ስለብሉያት፡መጻሕፍትና፡ታሪክ፡ ያመጡትን፡ዐዲስ፡መግለጫ፡ለመከታተል፡ቢቸግራቸው፣ዐማርኛው፡ከተሰናዳው፡መግለጫቸውም፡በክርስቲያንነታቸው፡የጸኑት፡ሊቃውንት፡ከደረሱበት፡የታሪክና የትርጕም፡ዐዲስ፡አካኼድ፡ለመድረስ፡ቢያቅታቸው፡ አይፈረድባቸውም።
የኢትዮጵያን፡የጥንቱን፡ትምርት፡ከሚያውቁት ሊቃውንት፡ዐማርኛንና፡ግእዝን፡ለማጣራት፣ያለቃ፡ ኪዳነወልድን፡ያኽል፡የሚደክም፡ብዙ፡አልተገኘም። ዐማርኛ፡ለግእዝ፡ልጁ፡በመኾኑ፣ ከግእዝ፡የተቀበላቸውን፡ቃላት፡ልክ፡እንደግእዝ፡አድርጎ፡መያዝ፡አለበት፡የሚል፡አሳብ፡ስላለባቸው፣ ይህንኑ፡ውሳኔ፡ለመግለጥ፡የታተመና፡ያልታተመ፡ብዙ፡መጽሐፍ፡ጽፈዋል። አሳባቸውን፡ተቀብሎም፡ለማስቀበል፡የሚጣጣር፡በያገሩ፡ብዙ፡ደቀመዝሙር፡አውጥተዋል። ሠላሳ ዓመት፡ያኽል፡የደከሙበት፡ዋናው፡መጽሓፋቸው፡ግእዝን፡ባማርኛ፡የሚተረጕም፡መዝገበ፡ቃላት(Dictionnaire) ነው።
ጠላት፡አገራችንን፡በወረረበት፡ዘመን፡እርሳቸው፡ሲታሰሩ፡ሲጋዙ፣ያን፡ያኽል፡የደከሙበትን፡ሥራ ፡የሚከውነው፡አጥቶ፣የብልና፡የምስጥ፡ምግብ፡ኹኖ፡መቈነጻጸሉ፡ጉዳቱ፡የራሳቸውና፡የመላ፡ኢትዮጵያ፡ብቻ፡ሳይኾን፣ ወሰን፡ሳያግደው፡ሰንደቅዓላማ፡ሳይለየው፣ ወገን ለኾነው፡በዓለም፡ላለው፡የትምርት፡ወዳጅ፡ለኾነው፡ ሰው፡ኹሉ፡ነው። ከሰው፡ተለይተው፣ ፈቃድ፡አጥተው፡ሲኖሩ፡ሳለ፣ ዕውቀታቸውን፡እንዲያካፍሉ፡ከችግር አስጥለዋቸው፡የነበሩ፡ንጉሠ ነገሥት፡ቀዳማዊ፡ኀይለሥላሴ፡ናቸው። ዛሬም፡ንጉሠነገሥታችን፡የኢትዮጵያን፡ ዐልጋ፡መልሰው፡ሲይዙ፣ አለቃ፡ኪዳነወልድን፡አስፈልገው፡የዕለት፡እንጀራቸውን፡በመዐርግ፡እንዲያገኙና፡ ያቋረጡትን፡ሥራ፡እንዲዠምሩ፡አድርገዋልና፡ፈቃዱ ኹኖ፡የኢትዮጵያ፡ወጣቶች፡የግእዝን፡ቋንቋ፡ከሥር እስከመሠረቱ፡ለማወቅ፡ከገዛ፡አገራቸው፡ሊቅ፡በተጻፈው፡መዝገበ፡ቃላት፡ይመረምሩታል፡እያልን፡ተስፋ እናደርጋለን።
በግጥም፡ወይም፡ቤት፡ሳይመታ፣ቃሉ፡ያላጋደለ፣የተመዛዘነ (Rythmique) በኾነ፡ንግግር፡አሳብን፡ መግለጥ፣ ሰው፡አንደበት፡ከፈታ፡ዠምሮ፡የነበረ፡ልማድ፡ነው። በጽሕፈት፡ያልገባው፡ያገራችን፡የጥንት፡ ወግና፡ታሪክ፣ ብዙ፡ግጥም፡አለበት። ሌላ፡የቀድሞ፡ሕዝብ፡የቤተመንግሥቱን፡ሕግ፡ሳይቀር፡ቤት፡እያስመታ ጽፎ፡በተማሪ፡ቤት፡በዜማ፡እንዲማሩት፡አድርጓል። በኢትዮጵያ፡ማናቸውንም፡የግእዝ፡ስንኳ፡በዜማ፡ማንበብ ልምድ፡ቢኾን፣ ሕግን፡በግጥም፡መጻፍ፡አልተለመደም። ነገር፡ግን፡ቤት፡የሚመታ፡የሕግ፡ዐይነት፡ምሳሌ አይጠፋም።‘
ይካስ፡የበደለ፥ይሙት፡የገደለ’፣
‘ያባት ዕዳ፡ለልጅ፥
ያፍንጫ፡እድፍ፡ለእጅ’፣
‘አልሞት፡ባይ፥ ተጋዳይ’።
ይህንም፡የሚመስል፡ባንድ፡ፊት፡ምሳሌ፣ እግረመንገዱን፡ደግሞ፡ሕግ፡ኹኖ፡የሚጠቀስ፥ቤት፡ የሚመታ፡ብዙ፡ንግግር፡አለ።
በቀድሞ፡ዘመን፡አንዳንድ፡ጊዜ፡ከሳሽና፡ተከሳሽ፡ተከራክረው፡ሲጨርሱ፥ዐጭር፡ኹኖ፡ቤት፡በሚመታ፡ንግግር፡ጕዳያቸውን፡ለዳኛ፡ያቀርቡ፡ነበር።
ከትች፡ላይ፡ዛሬውንም፡ቢኾን፡ በግጥም፡የሚተች፡አለ፤ የበገናና፡የመሰንቆ፡ልዩ ልዩ፡ ዝማሬ፥ባላገሩ፡ለአምላክና፡ለድንግል፡ማርያም፥ለመልአክና፡ለጻድቅ፡የሚያቀርበው፡ልመናና፡ምስጋና፡በግጥም፡ነው። ቀረርቶና፡ዘፈን፣እንጕርጐሮሽና፡ልቅሶ፡ ኹሉም፡በግጥም፡ነው።
ነገር፡ግን፡ልዩልዩ፡ሕዝብ፡ ፊት፡አስቀድሞ፡ቤት፡እየመታ፡ወይም፡በሕግ፡በተወሰነ፡ሚዛን (Rythmie) አሳቡን፡የሚገልጥበትን፥ጽሑፍ ሥራው፡ሲደራጅ፡ባገራችን፡ጽሑፍ፡ሥራ (Litterature) ግጥም፡የኋሊት፡ቀርቱዋል። ስለኾነም፡አኹን፡በቅርቡ ጊዜ፡ብዙዎች፡ሰዎች፡በግጥም፡መጻፍ፡ዠምረዋል። አብዛኛው፡ስላልታተመ፡ስለዐማርኛ፡ግጥምብዙ፡የምናመለክተው፡የለነም። ያሳተሙትና፡ያላሳተሙት፡ያማርኛ፡ቅኔዎች፡በግጥም፡የሚገልጡት፡አሳብ፡አብዛኛውን ምክር፡ነው(didactique)። የሰውን፡ሐዘንና፡ደስታ፡የሚገልጠው(poesie lyrique) እጅግ፡በጥቂቱ፡ኹኖ፣የወንድንና፡የሴትን፡ፍቅር፡የሚያነሣ፡በጭራሽ፡የለበትም።
የጣልያኖች፡ወረራ፣ስለአገርና፡ስለንጉሠ ነገሥት፡ፍቅር፣ ዐመፀኝነት፥ ስለሚሠራበት፡ግፍ፥ ስለነጻነትም፡ናፍቆት በግጥም፡የሚያናግር፡አሳብ፡ቀስቅሰዋል። የተጻፈው፡ገና፡ስላልተመረመረ፣ የሚያምረውን፡ከማያምረው፡ለመለየት፡ለጊዜው፡አልተቻለም። ስለዐማርኛ፡የቅኔ፡ባሕርይ፡ግን፡ከዚህ፡በፊት፡እንዳመለከትነው፡ብዙ፡‘ስለምን’፡ወይም፡‘ዐማርኛ’(Calembour jeu de mots) ይወዳል። አብዛኛውን፡ጊዜ፡አያሌውን፡መሥመር፡Vers ባንድ፡ ፊደል (lettre, syllable) ቤት፡ያስመታል (Monorime)። አንዱን፡መሥመር (vers) በኹለት፡ሐረግ (hemstiche) ከፍሎ፡ላንዳንዱ፡ሐረግ፡፮፥ለኹለቱ፡ሐረግ (ላንዱ መሥመር)፡፲፪፡ፊደል፡ይሰጣል። ፊደል፡ሲቆጥር፡አብዛኛውን፡ጊዜ፡እንደዕብራይስጡ፡ ቅኔ፡ሳድሱን፡ከሌለ፡ይቆጥረዋል።
የኢትዮጵያ፡ሕዝብ፡በአሳቡና፡በንግግሩ፡ስንኳ ቅኔ፡ወዳጅና፡ቅኔ፡ፈጣሪ፡ኹኖ፡ቢታይ፣ ባማርኛ፡እስከዛሬ፡ጽፈው፡ካሳተሙት፡ግጥም፡ገጣሚዎች፣ትዕግሥት፡ሰጥቶዋቸው፣ሽኽ፡መቶ፣መቶ፡ሽኽ፡መሥመር፡የጻፉና፡ያሳተሙ፡ያሉ፡አይመስለንም። በርከት፡አድርጐ፡የጻፈ፡ቢኖርባቸው፡ለፍርድ፡ይመች፡ነበር።
ይኹን፡እንጂ፡ዐጭርም፡ቢኾን፡እኔ፡ለራሴ፡ሥራቸውን፡የማደንቅላቸውና፡የማመሰግንላቸው፡ብዙ፡ወጣቶ ች፡አሉ። ከነዚህ፡አንዱ፡ከበደ፡ሚካኤል፡ነው። ቅኔ፥ ምሳሌ፥ተረት፡ከውጭ፡አገር፡ደራሲ(ከፈረንሳይ)፡በሚተረጕምበት፡ጊዜ፡አሳቡና፡ንግግሩ፡ዐማራ፡ኹኖ፡ከተረጐመበት፡ቋንቋ፡ጋራ፡ሲያስተያዩት፡አንዳንድ፡ጊዜ ተወዳዳሪው፣ አንዳንድ፡ጊዜም፡አርሞ፡ያቃናው፡ኹኖ ይገኛል። ምክንያቱን፡ከራሱ፡አፍልቆ፡በሚፈጥረው፡ግጥም፡ከልብ፡የወጣ፡ከልብ፡ይገባል፡እንደተባለው፡ኹሉ፡ልብን፡የማይነካ፡የሚገኝበት፡ኹኖ፡አልታየኝም። አብዛኛውን፡ጊዜ፡ካገራችን፡ባለቅኔዎች፡ግእዝን፡ወይም የውጭ፡አገርን፡ቋንቋ፡እጅ፡ያደረጉ፡ሲኾኑ፣ ወደዚያው፡እየሳባቸው፡ንግግራቸውን፡ለማስተዋል፡እንቸገርበታለን። ወይም፡ደግሞ፣ሌላ፡ባለግጥም፡ያወጣውን፡ንግግር፡ዐማርኛው፡ካማረ፡ብለው፡ያለቦታው፡ሲጥሉት ቅር፡ያሰኛሉ።‘ስለምን’፡ያልኹትን፡ንግግር፡አምጥተ ው፡አንባቢ፡በተሎው፡እንዳያስተውለው፡ያደረጉ፡እንደኾን፡ሰው፡ሊያስተውለው፡ያልቻለ፡ትልቅ፡ጥበብ፡ የተገለጠላቸው፡ይመስላቸዋል።
ከበደ፡ሚካኤል፣ሌሎች፡ካበጁት፡ወይም፡ከውጭ፡አገር፡ንግግር፡ሳይጨምር፡በራሱ፡ዐማርኛ፣ዐማራ፡የኾነ፡ኹሉ፡ሊያስተውለው፡የሚችል፡አገላለጥ፡በመምረጡ፡ለወደፊት፡ለሚነሡት፡ያማርኛ፡ባለቅኔዎች፡አብነታቸው፡ለመኾን፡ተስ ፋ፡የሚያስደርግ፡ልጅ፡ነው። በዚህም፡ተስፋ፡ስለዐማርኛ፡ደራሲያን፡ከብዙው፡ጥቂቱን፡ያስታወስነውን፡መጨረሳችን፡ነው። ለንግግራችን፡ፍጻሜ፡ስንሰጥም፡ደግመን፡የምናስታውሰው፦
፩. በዐማርኛ፡መጻፍ፡ከዠመርነ፡ስድስት፡መቶ፡ ዓመት፡ስንኳ፡ቢኾን፡በብዙው፡የተጻፈበት፡ዘመን ከ፲፮፻ ዓ.ም. በኋላ፡መኾኑን፣
፪. ካ፲፮፻ዓ.ም. ዠምሮ፡በዐማርኛ፡የሚጻፈው፡አብዛኛው፡የሃይማኖት፡መጽሐፍ፡ኹኖ፡ከንግግሩና፡ከአሰካኩ፡ከግእዝ፡ነጻ፡ያልወጣ፥ብዙ፡አካኼድ፡ እንደነበረበት፥ይህም፡የአጻጻፍና፡የንግግር፡አካኼድ፡ዛሬውን፡ሳይቀር፡አንዳንድ፡ጸሓፊዎች፡ እንደሚከተሉት፣
፫. ዐማርኛ፡ራሱን፡አስችለው፡መጻፍ፡የዠመሩት፡ ደራሲያን፡በዐጤ፡ቴዎድሮስ፡ዘመን፡፲፰፻፵፯-፲፰፻፷ መኾኑን፣ ጭራሽ፡እየተጣራ፡የኼደበት፡ግን፡በኀይለሥላሴ፡ዘመን፡መኾኑን፣
፬. ዐማርኛ፡ጽሑፍ፡ሥራውን፡በግጥም፡ዠምሮ፥ይኸው፡የግጥም፡ሥራ፡ዛሬ፡የኋሊት፡መቅረቱን፣
፭. የዛሬ፡ዘመን፡ደራሲያን፡ከሚጽፉት፡አብዛኛው፡ መጽሐፋቸው፡የታሪክና፥የሃይማኖት፥ የልብወለድ :ታሪክም፡መኾኑን፣ የኹሉም፡አሳብ፡ትምርትን፡ሥራንና፡ልማድን፡እያሻሻሉ፡መኼድ፡ዋና፡መኾኑን፣
፮. የኢትዮጵያ፡ሕዝብ፡ከፍጥረቱ፡የቅኔ፡መንፈስ፡ ያደረበትና፡በግጥም፡አሳቡን፡እንደገለጠ፡መኖሩን፣ ሙግቱንና፡ትቹን፡ሳይቀር፡በግጥም፡ማምጣት: ልማዱ፡መኾኑን፣ በዚህኛውም፡የተፈጥሮ፡ልማዱ: ቤት፡እያስመታ፡የሚኼድ፡ደራሲ፡በብዙው፡መገኘቱን፥ነገር ግን፡በዐማርኛ፡ያወጣውን፡ግጥም፡ያሳተመ፡ደራሲ፡ጥቂት፡መኾኑን፡ነው።
—————————————————–///———————————————///——————————————————
*ልብወለድ ታሪክ የተሰኘው በፕሮፌሰር አፈወርቅ ገብረ እየሱስ የተደረሰው መጽሐፍ ጦቢያ በመባልም ይታወቃል። ይህ ልብወለድ መጽሐፍ በሮም ከተማ የታተመ ቢሆንም በኢትዮጵያ የሥነጽሑፍ ታሪክ የመጀመሪያው ነው።