በጌቴ ገላዬ (ዶ/ር)
ኢ-ሜይል፣ ggelaye@gmail.com
የአማርኛ ቋንቋ እና የአፍሪቃ/የኢትዮጵያ ሥነቃል/ፎክሎር መምህር የአፍሪቃ እና ኢትዮጵያ ጥናቶች የትምህርት ክፍል እስያ-አፍሪቃ ጥናት ተቋም፣
ሐምቡርግ፤ ጀርመን
የአቶ ሰይፉ መታፈሪያ የሥነግጥም መድብሎች፣ የጥናት እና የምርምር ሥራዎች እና ለኢትዮጵያ የፎክሎር ጥናት እና ለአማርኛ ቋንቋ ዳብሮት ያበረከቱት አስተዋጽኦ
አቶ ሰይፉ መታፈሪያ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው 17ኛው ዓለማቀፍ የኢትዮጵያ ጥናት ጉባኤ፣ አቃቂ ግቢ (Nov. 2-5, 2009)
የዕውቁ ገጣሚ፣ መምህር እና የፎክሎር ባለሙያ የሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው መታሰቢያ ልዩ ዝግጅት ላይ በቪዲዮ ተቀርፆ የቀረበ።
የካቲት 19 ቀን፣ 2014 ዓ.ም. [February 26 2022]
የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም፣ ራስ መኰንን አዳራሽ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ ኢትዮጵያ።
ሰላም፣ ጤና ይስጥኝ! የተከበራችሁ የአቶ ሰይፉ ቤተሰቦች፣ ክብርት እናታችን ወ/ሮ አማረች መንግሥቱ፣ እኅታችን ወ/ሮ ሠምራ ሰይፉ መታፈሪያ፣ የተከበራችሁ ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች፣ የአቶ ሰይፉ መታፈሪያ የሥራ ባልደረቦች፣ የቀድሞ ተማሪዎች እና የሥነግጥም አፍቃሪዎች፣ ክቡር ዶ/ር ታከለ መርእድ፣ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ ዳይሬክተር፣ ክቡራን እና ክቡራት፤
በቅድሚያ በዛሬው ዕለት ለታላቁ ገጣሚ፣ መምህር እና የፎክሎር ተመራማሪ ለአቶ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው ልዩ የመታሰቢያ ዝግጅት ላይ በአካል መገኘት ባልችልም፣ ከቤተሰባቸው ጋር በመመካከር አጭር የቪዲዮ መልእክት እንዳስተላልፍ ስለተፈቀደልኝ ከልቤ አመሰግናለሁ።
ከቤተሰቦቻቸው እንደሰማችሁት፣ ዛሬ የአቶ ሰይፉ መታፈሪያን ሕይወት፣ የሥነ ግጥም መድብሎቻቸውን እና የጥናት እና የምርምር ሥራዎቻቸውን የምንዘክርበት ልዩ የመታሰቢያ ዝግጅት ነው።
አቶ ሰይፉ እጅግ የማደንቃቸው የቀለም አባቴ፣ መምህሬ፣ አማካሪዬ፣ እና ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የሥራ ባልደረባዬ፣ እንዲሁም ለበርካታ ዓመታት እጅግ የማከብራቸው ወዳጄ ናቸው።
እንደ ቤቴ ብለው በሚያዩት እና ከ50 ዓመታት በላይ ባስተማሩበት እና በተመራመሩበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዛሬው ዕለት የመታሰቢያ መርሐ ግብር ስለተዘጋጀላቸው እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል።
ንግግሬን በአራት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚከተለው አቀርባለሁ።
1. ዕውቁ ገጣሚ ሰይፉ መታፈሪያ እና የግጥም መድብሎቻቸው
2. መምህሩ እና የፎክሎር ተመራማሪው ሰይፉ መታፈሪያ
3. ሰይፉ መታፈሪያ ለአማርኛ ቋንቋ ዳብሮት ያበረከቱት አስተዋጽኦ
4. ሰይፉ መታፈሪያን እና ሥራዎቻቸውን ወደፊት እንዴት እናስታውሳቸው?
1. ዕውቁ ገጣሚ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው እና የግጥም መድብሎቻቸው
ገጣሚ፣ መምህር እና የፎክሎር ተመራማሪ የሆኑት ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው በኢትዮጵያ ውስጥ አንቱ ከሚባሉ አንጋፋ ምሁራን እና ስመጥር ገጣሚያን መካከል አንዱ ናቸው። ሰይፉ መታፈሪያ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በሀገራችን ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ የፎክሎር እና የሥነ ጽሑፍ ተማሪዎችን እና ምሁራንን አፍርተዋል። የሥነ ግጥም የፈጠራ ጥበባቸውን እና አሻራቸውን በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በወጣት ገጣሚያን ላይ እንዳሳረፉ ከልዩ ልዩ የግጥም እና የጃዝ ምሽት ዝግጅቶች፣ የግጥም ንባብ እና የውይይት መድረኮች መረዳት እንችላለን። በቀድሞው ሐረርጌ ክፍለ ሀገር ወደዚች ዓለም የመጡት ሰይፉ መታፈሪያ በግጥም ሥራዎቻቸው፣ እጅግ በርካታ እና ረቂቅ ሐሳቦችን አንሥተው የጻፉ፣ እሳቸው እንደሚሉት “ዘራእንስሳን እና ዘራተፈጥሮን” የሕይወትን ምስቅልቅል በግጥሞቻቸው ውብ አድርገው በተመረጡ ቃላት እና ስሜትን ሰቅዘው በሚይዙ ስንኞች ያቀረቡልን ገጣሚ ናቸው። አቶ ሰይፉ እንደሚነግሩን
በረጅሙ የመምህርነት ዘመናቸው በሐረር እና በአዲስ አበባ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና በቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እና የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም በካርቱም ዩኒቨርሲቲ አማርኛ፣ ሥነግጥም፣ ፎክሎር፣ ሥነቃል፣ በሳል ድርሰት፣ የጥናት የምርምር ርእስ መረጣ ሴሚናር፣ ወዘተ. የተባሉ ኮርሶችን አስተምረዋል።
የአቶ ሰይፉ ሥነጥበባዊ ሕይወት እሳቸው እንደሚሉት “ጠቅላላውን ከድርሰት በተለይም ከሥነግጥም አባዜ፣ ልክፍት-በሽታ ጋራ የተሳሰረ ነው። የሕይወትን (የዘራሰብን እና የዘራንስሳን) የትመጣ ለማወቅ ወይም ለመረዳት መነሻውን፣ እኔነቱን፣ አኪያኼዱንና መድረሻውን፣ ከራሳቸው ውስጣዊ ሰብእና፣ ዓይነልቦና እና ጥልቅ ተመስጦ ጋር እጅጉን ያጣምሩታል። ሰይፉ መታፈሪያ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በኢትዮጵያ እጅግ የተለየ የግጥም አጻጻፍ ስልትን ያስተዋወቁና ያስፋፉ ዕውቅ ገጣሚ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት የግጥማቸው የአጻጻፍ (ዓይነት) „በብዙ ረገድ ባህል-ከተል አይደለም። በዚህ
ያጻጻፍ አዲስነት አስገዳጅነትም ስም ስላስፈለገው „ስንኝ አጠፍ ግጥም“ የሚል ስያሜ ሰጥተውታል።(1995)
የሰይፉ መታፈሪያ የሥነግጥም መድብሎች በርካታ የሥነጽሑፍ ምሁራንን አስተውሎት የሳቡ ሲሆን ለብዙ የጥናት እና የምርምር ጽሑፎች ዋና መሠረት በመሆን ለምሁራዊ ውይይት እና ክርክር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ወደፊትም ያደርጋሉ። ሰይፉ መታፈሪያ ከ1964 እስከ 2001 ባሉት ጊዜያት ስድስት የሥነግጥም መድብሎችን አሳትመዋል። በታተሙት መድበሎቻቸው ውስጥ በሺህ የሚቆጠሩ ልዩና ውብ ግጥሞችን ደርሰዋል። በግጥሞቻቸው ውስጥ ትኩረታቸውን እና ዓይነ ልቦናቸውን ከሳቧቸው ዋና ዋና ርእስቶች መካከል፣ ሕይወት፣ ተፈጥሮ፣ ዘራስሳት እና ዘራፅዋት፣ እኔነትና ሰዋዊ መስተጋብር፣ የገጣሚ ጭንቀት፣ የዕለት ተለት ረቂቅ ቅጽበቶች፣ ወዘተ. ይገኙበታል። እነዚህን ውብ እና አመራማሪ ግጥሞች ማንኛውም ሰው እንዲረዳቸው ካስፈለገ፣ የአቶ ሰይፉን ሰብእና፣ በተለይም ለሰው ልጅ እና ለሕይወት ያላቸውን እጅግ ደግነት፣ ሩሕሩሕነት እና ቅን አሳቢነት ማወቁ አስፈላጊ ይመስለኛል። ይኸ ደግሞ ቀላል አይደለም። ምክያንያቱም የሕይወት ታሪካቸው፣ ልዩ የቋንቋ ፈጠራ ጥበባቸው እና ችሎታቸው በዝርዝር አልተጻፈምና። ይኸ ወደፊት ከቤተሰባቸው፣ ከቅርብ ጓደኞቻቸው እና ወዳጆቻቸው፣ ከሥራ ባልደረቦቻቸው እና ከተማሪዎቻቸው ጋር በቅርበት በመመካከር የሚጠናቀር ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡
ከቅርፅ አንጻር፣ የአቶ ሰይፉ ልዩ የግጥም ሐሳብ ወይም ጭብጥ ከሁለት መሥመር ስንኝ ማለትም፣ “ገጣሚ ሲቆጣ” (ዐባይ ፈንጆ የቀበረ ውኀ፣ 2001 ዓ.ም. ገጽ፣ 116) ከሚለው ግጥም አንሥቶ “የመተሐራው ባላባት” እስከሚለው ረጅም እና ባለ 15 ገጽ ግጥማቸው (ዐፈር ያነሣ ሥጋ፣ 1964 ዓ.ም፣ ገጽ፣ 41-55 ድረስ ይዘልቃል።
ገጣሚ ሲቆጣ፣
መጻፍ፣ መጻፍ አለኝ ማቅለም ወረቀት፣
ብእሬን ማስቆጣት ቀይ ደም ማስተፋት።
አቶ ሰይፉ እንደሚሉት “የግጥም ጭብጥ የተዳፈነ እሳት ነው። ከልብ አይጠፋም። ቆይቶ፣ ቆይቶ አንድ ቀን ቦግ ይላል። “የተፈጥሮ እርስበርስዋ” ግጥም ጉዳይም እንዲያ ያለ ነበር። የ1990 ፈረንጅ ዓመት (ፈ.ዓ.) የመጀመሪያው ንድፍ አልጥም ብሎኝ ከተውኩት በኋላ፣ ቆይቶ ቆይቶ፣ ባንድ ባላሰብኩት – ምክንያት አግኝቶ – ቀጨም! አረገኝ። ገጣሚ የመጣልኝ (inspiration) ባሪያ ነው፣ ስለዚህም ግጥም የሚያስጽፍ ገጠመኝ ሲመጣበት ወይም ሲመጣለት፣ ያለው ምርጫ “እሺ!” ብሎ መጻፍ ብቻ ነው። እና መጻፍ ጀመርኩ – ከ1990 እስከ 2000 ፈ.ዓ. በያዝ ለቀቅ ዓይነት አንቀራበጥሁት” ይሉናል። (ከራስ ድንበር ባሻገር፣ 2003 ፈ.ዓ.፣ ገጽ፣ VI)
ሰይፉ መታፈሪያ የገጣሚን ወይም የባለቅኔን ጭብጥና ጭንቀት በሚመለከት በተለይ ዐባይ ፈንጂ የቀበረ ውኀ (2001 ዓ.ም.) በተሰኘው መድብላቸው ብቻ፣ የሚከተሉትን ርእሶች መርጠው አእምሮን አመራማሪ፣ ስሜትን ኮርኳሪና መሳጭ ግጥሞችን ጽፈዋል።
1. እይታ ያባነነው ገጣሚ (ገጽ፣ 61)
2. ገጣሚ አለፈ (ገጽ፣ 224)
3. ገጣሚ (ገጽ፣ 237)
4. ነፍሰ ገዳዩ ገጣሚ (ገጽ፣ 243)
5. ገጣሚ ሲለከፍ (ገጽ፣ 289)
6. ገጣሚነት ጭንቁ (ገጽ፣ 505)
7. የግጥም ቃልኪዳን (ገጽ፣ 556)
በአቶ ሰይፉ መድብሎች ውስጥ በልዩ አሰነኛኘት ስልት የተደረደሩት ግጥሞችና የገጽ ብዛት ማሳተም ከጀመሩበት ዘመን ከ1964 ዓ.ም. አንሥቶ እስከ 2001 ዓ.ም. ድረስ እያደገ ይመጣል፣- ማለትም፣ ከ84 (ውስጠት) ወደ 608 (ዐባይ ፈንጅ የቀበረ ውኀ)።
2. መምህሩ እና የፎክሎር ተመራማሪው ሰይፉ መታፈሪያ
ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው በፎክሎር /ሥነቃል የጥናት መስክ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የድኅረ ምረቃ ተመራቂ እና ምሁር እንደሆኑ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ለዚሁም እ.ኤ.አ. በ1978/79 በካርቱም ዩኒቨርሲቲ፣ የአፍሪቃ እና የእስያ ጥናት ተቋም፣ ለፎክሎር የትምህርት ክፍል ለማስትሬትያቀረቡት እጅግ ጥልቅ የሆነው የጥናትና የምርምር ሥራቸው ነው። ይህንን የጥናት እና የምርምር ሥራ በቀድሞው የምሥራቅ ሐረርጌ ክፍለ ሀገር፣ በተለያዩ የገጠር አካባቢዎች ተዘዋውረው የመስክ ጥናት በማከናወን የገበሬዎችን ልዩ ልዩ የሥራ ዘፈኖች፣ ግጥሞችና ዜማዎች ከኦሮምኛ ወደ እንግሊዝኛ በመተርጐምና ሰፊ ሐተታ በማካተት ያዘጋጁት ጥልቅ የጥናት እና የምርምር ሥራ ነው። ይህ ጥናት በቅርቡ ለሕትመት እንደሚበቃ ተስፋ አለኝ። ጋሽ ሰይፉ የፎክሎርን የዕውቀትና የጥናት መስክ በጥልቀት በማጥናት፣ በመመርመር እና በማስተማር፣ እንዲሁም ወጥነት ያለው የምርምር ጥናት በማካኼድ “የፎክሎር መዝገበ -ቃላት ጥንቀራ ቅድመ ዝግጅት” በሚል ርእስ በኢትዮጵያ ጥናት መጽሔት Journal of Ethiopian Studies (1993) ላይ ያሳተሙት ረዥም የምርምር ጽሑፍ በዋናነት
ተጠቃሽ ነው። ይህ ጥናታዊ ጽሑፍ ልዩ ልዩ የፎክሎር ሙያ-ነክ ቃላትን በመሰብሰብ፣ በመፍጠር፣ ክያኔያዊ እና ዐውዳዊ ብያኔ በመስጠት የጥናት መስኩ ወጥነት እንዲኖረው ያቀረቡት እጅግ የሚደነቅ የምርምር ውጤት ነው። በመጽሐፍ መልክ የማሳተም ዕቅድ
እንደነበራቸው ነግረውኛል። ለምሳሌ፣ ተረትን በሚመለክት የፈጠሯቸውን ሙያ-ነክ ቃላት እንደሚከተለው ያቀርቡልናል፣ ተረታተረት (tales)፣ አድባሬ ተረት (fairy tale)፣ ሞኜ ተረት (noodle story)፣ እንስሴ ተረት (animal tale) ወዘተ.።
አቶ ሰይፉ በተለያዩ የሥነቃል ዘርፎች (ቃል ግጥም፣ ምሳሌያዊ አነጋገር፣ ተረቶች፣ ወዘተ.) ላይ በርካታ የጥናት እና የምርምር ሥራዎችን በማዘጋጀት በተለያዩ ዓለማቀፍ የጥናት እና የምርምር መጽሔቶች ላይ ያሳተሙ ታላቅ ምሁር ናቸው።
3. ሰይፉ መታፈሪያ ለአማርኛ ቋንቋ ዳብሮት ያበረከቱት አስተዋጽኦ
አቶ ሰይፉ በርካታ ያገራችንን እና የአውሮጳን ቋንቋዎች አጥርተው የሚናገሩ እና ጠንቅቀው የሚያውቁ ልሳነ ብዙ ምሁርና ተመራማሪ ናቸው። አማርኛ፣ ግዕዝ፣ ኦሮምኛ፣ ሶማልኛ፣ ዐረብኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ግሪክኛ፣ ላቲን፣ እና ጣሊያንኛ ቋንቋዎችን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ጀርመንኛንም በመጠኑ ያውቁ ነበር። ይኸው ልዩ የቋንቋ ተሰጥዖአቸውም አዳዲስ ሙያ-ነክ ቃላትን በመፍጠር ያማርኛን ቋንቋ በማሳደግ እና ለማኅበረሰባችን በማስተዋወቅ ረገድ እጅግ የላቀ ሚና የተጫወቱ ምሁር ናቸው። ለዚህም በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ „ብእሮጋዊ መግቢያ“ (introductory essay) በሚል ርእስ ለሥነግጥም መድብሎቻቸው የጻፏቸውን ረዣዥም ጽሑፎች እና ያሳተሟቸውን ምርምራዊ መጣጥፎች (1993) ማመሳከር ይቻላል።
የአቶ ሰይፉ እጅግ የተለየ የቋንቋ ተሰጥኦ አዳዲስ ቃላትን የመፍጠር ልዩ ችሎታቸው ነው። ይኸንን አስመልክተው ገጣሚው እንዲህ ይሉናል። „በብዙዎቹ ግጥሞቼ ውስጥ ተውሼ፣ ፈጥሬ፣ ወይም ጨፍልቄ እምጠቀምባቸው አማርኛ ቃላት፣ አንባቢን እንደሚያነጫንጭ ዐውቃለሁ፤ የግጥም አጻጻፍ ስልቴ አስገድዶኝ ነው፤ ይህን ማድረጉ ደግሞ ላማርኛ ዳብሮት ያለኝን ጉጉት ያረካልኛል። … ፍጥርና ጭፍልቅ ቃሎቼ ካማርኛ ሕግ እስከዚህም የራቁ አለመሆናቸው ይታያል።“ (1995)
አቶ ሰይፉ ለፈጠሯቸው አዳዲስ ቃላት ሰፊ ማብራሪያ እና አንዳንድ ጊዜም ከእንግሊዝኛ አቻቸው ጋር የሚጽፉት “ሙዳዬ ቃላት” ወይም (Glossary) ብለው በመጽሐፎቻቸው መጨረሻ ላይ በሚያቀርቡት ርእስ ሥር ነው።
በሥነ ጽሑፍ ተማሪዎቻቸው እና በተመራማሪዎች ዘንድ በስፋት የሚደነቁላቸው እርሳቸው የፈጠሯቸው ሙያነክ ቃላት፣ እንዲሁም ባለፉት ዓመታት በሥነግጥም መድብሎቻቸው ውስጥ ካስተዋወቋቸው አዳዲስ ቃላት መካከል አንዳንዶቹን ለአብነት ያህል እንደሚከተለው አቀርባለሁ።
መጣጥፍ፣ በሳል ድርሰት፣ ትየባ፣ ተዝናኖት፣ ትጥበት፣ ኑረት፣ ሩጠት፣ ጡፈት፣ ውስጠት፣ ዝልቀት፣ ቃላውድ (context) ፣ ማወነት (እውነት ማድረግ)፣ ሰባትካት (የጥንት ዘመን ሰዎች)፣ አብሮነት፣ አብሮኛ ብ.ቍ. አብሮኞች (የሕይወት ተጋሪ፣ አብሮ ሆኖ የተገኘ)፣
እንጃኝልሽ (“እንጃኝልሽ ንቢት” ግጥም ውስጥ)፣ አንተየሻ (አንተ ሆዬ)፣ ተመስጦ፣ አበርክቶ፣ ተስተላልፎ፣ ተዋስጦ፣ አስተናግዶ፣ ሥንከን (art)፣ ሠንካኝ፣ ምጥቃለም (space)፣ ኅብራድምፅ (sound harmony) ሠረወ፣ ሥርወት (etymology) ምታመት፣ ዐይነልቦና (imagination) መልሰኛ፣ መርካቶኛ፣ እንጃማሞች (እንጃ ባዮች)፣ ጆሌ ቢያ (ያገር ልጅ፣ ከእንግሊዝኛ)፣ ስጆግ (መጆግ) በእግሬ ስኼድ፣ ባቦት (nostalgia)፣ መጣልኝ (inspiration)፣ ቆምታ (pause) ወዘተ. ይገኙበታል። አቶ ሰይፉ የፈጠሯቸውን አዳዲስ ቃላት በጥንቃቄ ሰብስቦ በሚገባ ማጥናት እና ፈለጋቸውን መከተል ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ።
በተጨማሪም በ1980ዎቹ ዓመታት በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የባሕል እና የትምህርት ድርጅት (ዩኔስኮ) የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት በዚያን ጊዜው የባህል ሚኒስቴር ሥር በነበረው የ“ኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዳሚ” በተካኼደው “የሳይንስና ቴክኖሎጂ የቃላት ሥያሜ እና ትርጉም ፕሮጀክት” ውስጥ በአማካሪነት እና በዋና አዘጋጅነት ተሳትፈዋል። ሰይፉ መታፈሪያ በዚህ ሙያዊ የቃላት ፈጠራ እና የትርጕም ፕሮጀክት ውስጥ ሰፊ የቋንቋ ክሂሎታቸውንም ለሌሎች ምሁራን በማካፈል፣ ለአማርኛ ቋንቋ ዳብሮት እና ዘመናዊነት እጅግ ጠቃሚ የሆኑ የሥያሜ ቃላት ሥራዎችን ሠርተዋል፣ የአተረጓጐም ስልቶችን እና ዘዴዎችን አስተዋውቀዋል።
ሰይፉ መታፈሪያ አብዛኛውን ሕይወታቸውን በመምህርትነት ሙያ ላይ ቢያሳልፉም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ውስጥ በዋና ጸሐፊነት አገልግለዋል። በተለይም በ1960ዎቹ አጋማሽ ላይ በአዲስ አበባ የተደረገውን የምሥራቃዊ ወይም የ“ኦሬንታል” አብያተ ክርስቲያናት ታሪካዊ ጉባዔ በማስተባበር እና በማዘጋጀት የጎላ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
4. ሰይፉ መታፈሪያን እና ሥራዎቻቸውን ወደፊት እንዴት እናስታውሳቸው?
ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው በአሁኑ እና በወደፊቱ ትውልድ እንዴት ይታሰባሉ? ለአቶ ሰይፉ የሥነግጥም አሻራ ሕያውነት፣ ለቋንቋ እና ባህል ጥናት ልፋታቸው መታሰቢያነት አስፈላጊ ናቸው ብዬ ያዘጋጀኋቸውን ሐሳቦች እንደሚከተለው አቀርባለሁ።
1. እስካሁን ድረስ ያልታተሙ ሦስት የሥነግጥም መድብሎቻቸውን ማሳተም፣ እነዚህም
1.1. የወዲያው በኩል፣
1.2. ዋዜማ፣
1.3. ???
2. ያልታተሙ የትርጕም እና የምርምር ሥራዎቻቸውን ማሳተም፤
2.1. እላይ የጠቀስሁት ከምሥራቅ ሐረርጌ ማኅበረሰቦች ሰብስበው ያጠኗቸውን በርካታ የሥራ ግጥሞች፣ ዘፈኖች፣ ዜማዎች፣ ምርቃቶች፣ ወዘተ. እና ለካርቱም ዩኒቨርሲቲ የአፍሪቃ እና እስያ ጥናት ተቋም፣ የፎክሎር የትምህርት ክፍል ያቀረቡትን ጥልቅ የምርምር ጥናት ማሳተም፣
2.2. ከእንግሊዝኛና /ከግሪክኛ ወደ አማርኛ የተረጐሙትን የሐተታማልክት መጽሐፍ ማሳተም፣
2.3. የዕለትውሎ ማስታዎሻዎቻቸው እና ከተለያዩ ወዳጆቻቸው ጋር የተጻጻፏቸውን ደብዳቤዎች ከሕይወት ታሪካቸው ጋር ባንድ ቅጽ ማሳተም፣
3. አቶ ሰይፉ ለአማርኛ ቋንቋ ዳብሮት ያበረከቱትን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ዕውቅና እና አክብሮት በመስጠት፣ ከተቻለ እና ጥሩ የሥነ ጽሑፍ ተሰጥኦ ያለው ተርጓሚ ከተገኘ ከስድስቱ መድብሎቻቸው ውስጥ የተወሰኑ ግጥሞችን መርጦ ወደ እንግሊዝኛ በመተርጐም አንድ የሥነ ግጥም መድብል አሳትሞ ለዓለማቀፍ አንባቢያን ማቅረብ፣
4. ለአቶ ሰይፉ መታፈሪያ መታሰቢያ፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመመካከር የታላቁን የጥበብ ሰው፣ የዕውቁን ገጣሚ እና መምህር ዝክረ ሕይወት በማስታወስ ጥቅምት 24 ከተቻለ እና ዐቅም በፈቀደ መጠን በያመቱ የሥነግጥም እና የውይይት ሲምፖዚዬም ማዘጋጀት የሚሉ ናቸው።
ክቡራን እና ክቡራት፣ በመጨረሻም፣ ስለ ታላቁ የቀለም አባቴ፣ ስለ አቶ ሰይፉ አንዳንድ የግል ገጠመኞችን ባጭሩ እንደሚከተለው በማቅረብ ንግግሬን አጠናቅቃለሁ።
አቶ ሰይፉን እኔ እንደማውቃቸው፤
1. ለሰው ልጅ እጅግ አዛኝ፣ አሳቢ፣ ሩኅሩኅ እና ሰው አክባሪ ናቸው።
2. ፊታቸው ሁልጊዜ በፈገግታ እና በሣቅ የተሞላ ነው። ንግግራቸው እጅግ መሳጭ በሆኑ ምሳሌያዊ አነጋገሮች እና ውብ ቃላት የተሞላ ነው።
3. አቶ ሰይፉ “ፎክሎር በውስጤ አለ” ብለው የሚያምኑ፣ ይኸንንም በተግባር ያሳዩ መምህር፣ ተመራማሪ እና ምሁር ናቸው። ለመምህርነት ሙያቸው እና ለተማሪዎቻቸው እጅግ ከፍተኛ አክብሮት፣ ጭንቀት እና ፍቅር ያላቸው ናቸው።
4. በደስታ፣ በአክብሮት እና በፍቅር የተሞላው “የትዳር ሕይወታቸው አርአያነት ያለው ነው። ከባለቤታቸው ከወ/ሮ አማረች፣ እሳቸው “አሚ” በሚል የቁልምጫ ስም ከሚጠሯቸው እጅግ ደግ የትዳር አጋራቸው ጋር እንደ “እኅትና ወንድም”፣ እንደ “እናትና አባት”፣ እንደ “ጓደኛ” ሆነው በፍቅር እና በስስት የሚተያዩ አርአያ ወላጆች እና ቤተሰቦች ሆነው በማየቴ እጅግ ዕድለኛ እና ደስተኛ ነኝ። ይኸንንም ልዩ የትዳር እና የፍቅር ሕይወት በግጥሞቻቸው ከማሳየታቸውም በተጨማሪ አሜሪካ አገር በኖሩባቸው ዓመታት፣ በአትላንታ ጆርጂያ ለኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ አባላት፣ ለወጣቶች እና ለታዳጊዎች እንዲሁም ለቤተሰቦች በመምክር እና በማስተማር ሰፊ የሕይወት ተሞክሯቸውን ሳይሰስቱ አካፍለዋል። ከፍተኛ አክብሮት እና አድናቆትም ተችሯቸዋል ።
5. አቶ ሰይፉ ጸሎተኛ እና እጅግ መንፈሳዊ አባት ነበሩ።
እግዚአብሔር የአቶ ሰይፉን ነፍስ በአጸደ ገነት ያሳርፍልን!
በጥሞና ስላዳመጣችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ።
የአቶ ሰይፉ መታፈሪያ የሥነግጥም መድብሎች እንደታተሙበት ዘመን ቅደም ተከተል፣ ዝርው መጽሐፎቻቸው እና ሌሎች የጥናት እና የምርምር ሥራዎቻቸው ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል።
ሀ. የሥነ ግጥም መድብሎች (መጻሕፍት) ዝርዝር
1. 1964 ዓ.ም.፤ ዐፈር ያነሣ ሥጋ። ተስፋ ገብረ ሥላሴ ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ። (154 ገጾች)።
2. 1967 ዓ.ም.፤ የተስፋ እግር ብረት ግጥሞች። ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ። (195 ገጾች)።
3. 1983 ዓ.ም.፤ ውስጠት። አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ። (84 ገጾች)።
4. 1987 ዓ.ም.፤ የተጉዋጎጠ ልብ። ቦሌ ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ።
5. 1995 ዓ.ም.፤ ከራስ ድምበር ባሻገር። አትላንታ፣ አሜሪካ። (587 ገጾች)።
6. 2001 ዓ.ም.፤ ዐባይ ፈንጂ የቀበረ ውኀ። ደረኮ አሳታሚ፣ ቦስተን። (608 ገጾች)።
ለ. ዝርው መጻሕፍት
7. 1989 ዓ.ም.፤ ኮልፌ-ሰንዳፋ-ኮልፌ የአዲስ አበባው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀል- ወለድ ትራጀዲ ለታሪክ። የታተመው በዩናይትድ ስቴት ዘአሜሪካ፣ 147 ገጾች።
8. Ha-Hu in America. ለልጆች እና ለወጣቶች ማስተማሪያ የተዘጋጀ መጽሐፍ። አትላንታ፣ ጆርጂያ።
ሐ. ጥናታዊ/ ምርምራዊ መጣጥፎች
1. 1972፤ የባሪያ ስም ባማራው ባህል። Journal of Ethiopian Studies.X,2, ገፅ127-200.
2. 1973, (with Getatchew Haile), “Regional Variations in Amharic: The Dialect of Gojjam”, Journal of Ethiopian Studies. XI, 2, 113-129.
3. 1974, “Sixteen Letters of Ras Mäkonnen and his Sons to Haji Ahmad Aboññ of Harar. Journal of Ethiopian Studies. XII, 2, 179-199.
4. 1978. The Eastern Oromo (K‘ottus) of Ethiopia and Their Time Reckoning “System”, AFRICA. Rivista trimestrale di studi e documentazione dell’Istituto Italo-Africano. Anno XXXIII N. 4, 476-508.
5. 1973 ዓ.ም. [= 1980] “ሥነ/ኪነተቃል በኢትዮጵያ“፣ ለኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍል የትውፊት ሴሚናር የቀረበ፣ አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1-3።
6. 1981.“LocalContributiontotheDevelopmentofFolkloristicsinEthiopia”. Addis Ababa University. Department of Ethiopian Languages and Literature. Mimeographed.
7. 1984. “Oral Literature of Ethiopia as Source Material for Children’s Books: A Sample Study”. Rassegna di Pedagogia. I, 2: 45-72.
8. 1986. “Verse-Talk in an Ogaden Front of 1934 Folkloric Study of a Text”. International Conference of Ethiopian Studies, Moscow.
9. 1993. “የፎክሎር መዝገበ ቃላት ጥንቀራ ቅድመ ዝግጅት“፣ Journal of Ethiopian Studies. XXVI, 1, 73-116.
10. 1999 ዓ.ም.፤ “መንገድ ስጡኝ ሰፊ (የገብረ ክርስቶስ ደስታ የግጥም መድብል ግምገማ)”። አንድምታ፣ ቁ.7፣ መጋቢት-ግንቦት፣ ገጽ፣ 4-7።
11. 1999 ዓ.ም.፤ [2017] “ሳይቸግር ጤፍ ብድር” (ወግ) አንድምታ የሥነጽሑፍ መጽሔት፣ የካቲት፣ ገጽ፣ 1-8።
መ. ወደፊት የሚታተሙ
1. የወዲያው በኩል፤ የግጥም መድብል።
2. ዋዜማ (የግጥም መድብል)
3. TheWork Poetry of the Eastern-Oromos (Qottus) of Ethiopia. Dissertation submitted to in Candidature for the Folklore Department, Institute of African and Asian Studies, University of Khartoum. (Revised and edited in 2019 and ready for publication), ca. 588 pages.
4. በጥንታዊ የግሪክ ሐተታማልክት ላይ የተመሠረተ የትርጕም መጽሐፍ፤ (February 25, 2023) በ ሥነጽሑፍ፣ የሕይወት ታሪክ፣ ጥናትና ምርምር.
————————————————————///————————————————///——————————– Edit
አቶ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው እ. አ. አ November 3, 2022 በአትላንታ፣ ጆርጂያ (አሜሪካ) በ88 ዓመታቸው አርፈው እ. አ. አ November 10,2022 ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል
እግዚአብሔር የአቶ ሰይፉን ነፍስ በአጸደ ገነት ያሳርፍልን! በጥሞና ስላዳመጣችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ።
መጋቢት 2015 ዓም።