አውሮጳ እና ኢትዮጵያ፤ አመራርና የሥልጣኔ ፖለቲካ

ሞገስ ገብረማርያ፤ ዶ/ር፤ ሰሜን አሜሪካ።

(የካቲት 2015/February 2023)

ለመንደርደሪያ ያህል

በዘመነ መሳፍንት ስድሳ አምስት ዓመት ሙሉ በማይረባ ምክንያት የተከፋፈለውን፣ የዘቀጠውን፣ የባለገውን ህዝባችንን ከወደቀበት መቀመቅ አውጥተው ኢትዮጵያን ወደጥንት ታላቅነቷ ለመመለስ የኢትዮጵያን ነገሥታት፣ መጀመሪያ አፄ ቴዎድሮስ፣ ቀጥሎ አፄ ዮሐንስ በኋላም አፄ ምኒልክ ያውሮጳን መንግሥታት ድጋፍና ወዳጅነት አጥብቀው ይፈልጉ፣ ይማጠኑ ነበር። አውሮጳውያን ግን የሚፈልጉት የኢትዮጵያን ውድቀቷን፣ ክፍፍሏን፣ ንብረቷንና መሬቷን እንጅ የሕዝቧን ነፃነትና ብልጽግና ስላልነበር በነዚህ ቅን ነገሥታቶች ላይ በየጊዜው ተደጋጋሚ አሳፋሪ ሸርና ተንኮል፣ ሴራና ተራ ማጭበርበር ይፈጽሙባቸው ነበር።

አፄ ቴዎድሮስ ለተቀደሰ አላማቸው የእንግሊዝን ወዳጅነት አጥብቀው ቢፈልጉ እነሱ ግን በክራይሚያን (Crimean) ጦርነት ሳቢያ ለቱርክ አዳልተው ችላ ብለው ቴዎድሮስ ተቆጥተው ሚሲዪናውያንን ቢያስሩ እንግሊዞች ጦር ልከው መቅደላ ላይ ራሳቸውን እንዲገድሉ ካደረጉ በኋላ ከምፅዋ ድረስ እየመሩ ላመጧቸው ለአፄ ዮሐንስ ብዙ የጦር መሣሪያ ከነአሰልጣኙ ትተውላቸው እንዲነግሡ አመቻቹላቸው። አፄ ዮሐንስ በዚህ ምክንያት የልብ ወዳጅ መሆናቸውን እያወቀ እንግሊዝ በተንኮል መጀመሪያ ከግብፅ፣ ቀጥሎ ከድርቡሽ ሱዳን፣ በኋላም ከጣሊያን ጋር አቆራርጦ የህይወታቸውን መጥፊያ ቀየሰላቸው።

እኤአ በ1875 በእንግሊዝ ምክርና ፈቃድ ግብፅ ከሜዲትራንያን አስከ ሕንድ ውቅያኖስ ድረስ ግዛቷን ለማስፋፋት፤ በእስማኤል ፓሻ አዝማችነት ኢትዮጵያን ብትወር፣ አፄ ዮሐንስ ጉንዳጉንዲት ላይ ድል አደረጓት ።

በ1876 እንደገና በእስማኤል ፓሻ ልጅ፣ በሐሰን ሙላይ ፓሻ ልጅ አዝማችነት ኢትዮጵያን ብትወር፣ አፄ ዮሐንስ እንደገና ጉርዓ ላይ አሸነፏት ።

ከዚህ ወረራ ጀርባ የነበረችው እንግሊዝ ሳትጠራ ሸምጋይና ገላጋይ መስላ፣ ግብፅ ምንም እንኳ በጦርነቱ ብትሸነፍ በሃይል ከያዘችው ከምዕራብ ኤርትራ (ከቦጎስ)) ሳትወጣ በዓመት 8000 ፓውንድ እየከፈለች አንድትቆይ ወዳጇን አፄ ዮሐንስን አሳመነች፣ አስፈረመች ።

እንግሊዝ ከግብፅ ጋር ሆና Anglo-Egyptian Sudan የተሰኘ ቅኝ ግዛት ለመመስረት ቀደም ብላ የጀመረችውን ወረራ በመቀጠሏ በማሃዲ የሚመሩ ሱዳኖች (Dervish) የእንግሊዝን ጦር አሸንፈው ለመጨረስ ምሥራቅ ሱዳን ላይ ከበቧቸው።

እንግሊዝ ባስቸኳይ Admiral Hewitt የተባለውን ሰው ልካ፣ የእንግሊዝ ወዳጅ የዮሐንስ፣ የእንግሊዝ ጠላት የዮሐንስ ብላ አድዋ ላይ Hewitt Treaty of Adwa የተባለውን ስምምነት አፄ ዮሐንስን አስፈረመቻቸው። አፄ ዮሐንስ ምንም ያልነኳቸውን የሱዳን ድርቡሾች ለእንግሊዝ ብለው ሄደው ወግተው የተከበቡትን የእንግሊዝ ወታደሮች አስለቅቀው በምፅዋ በኩል ወደሃገራቸው በመሸኘታቸው እንግሊዝ ለአፄ ዮሐንስ ሁለተኛ ጠላት ሱዳንን ፈጠረችላችው።

በ1884 አውሮጳውያን በቢስማርክ ሊቀመንበርነት በርሊን ላይ ተሰባስበው እርስበርሳቸው ሳይጣሉ እየተስማሙ አፍሪቃን እንዲቀራመቱ ተስማሙ ። በዚህ ውል መሠረት በቀጣዩ ዓመት የአፄ ዮሐንስ ውለታ ገና ዓመት ሳይሞላው ግብፅ የለቀቀችውን ምፅዋን ገና ለገና ፈረንሳይ ትይዘዋለች ብላ በመስጋት “ውለታህን በጥፊ” እንዲሉ በታላቅ ንቀት አይናቸው እያየ ምፅዋን ለጣሊያን ሰጠችና ለአፄ ዮሐንስ ሶስተኛውን ጠላት ጣሊያንን ዳረገችላቸው።

ጣሊያኖች ከምፅዋ ተነስተው እየተስፋፉ ደጋ ደጋውን ሃማሴንን ሲይዙ የአፄ ዮሐንስን እጅግ ለዘብተኛ፣ ዘገምተኛ የልመና ዲፕሎማሲ ያልወደዱ ራስ አሉላ ሶስት ዓመት ከታገሱ በኋላ በርሳቸው አነሳሽነት በ1888 ዶጋሊ ሜዳ ላይ 450 ጣሊያኖችን ገደሉ። አፄ ዮሐንስም ሳታስፈቅድ ተዋጋህ ብለው ራስ አሉላን ሻሯቸው።

የነዚህ 450 ጣሊያኖች በጥቁር ኢትዮጵያውያን መገደል በአውሮጳውያን ጎራ ከፍ ያለ ድንጋጤ፣ ሽብርና ፍርሃት ፈጠረ። ጣሊያኖች ድምፃቸውን አጥፍተው፣ ጥርሳቸውን ነክሰው ከእንግሊዝ ጋር መክረው፣ በጊዜው የእንግሊዝ ግዛት ከነበረው ከሕንድ አገር ከቦምቤይ ከተማ መርከብ ልከው መርከቧ (በ1888) ምፅዋ ደርሳ ከውስጧ ሁለት ላሞች ወጥተው በሃማሴን ምድር ተለቀቁ።

በዚህ ዓመት አፄ ዮሐንስ የተማጽኖ ዲፕሎማሲያቸውን አሟጠው ጣሊያንን በጉልበት ለማስወጣት 200 ሺህ ወታደር ይዘው ምፅዋ አጠገብ ሰሃጢ ላይ ሰፈሩ። ሶስት ወር ሙሉ ከበባ አድርገው ጣሊያን ከምሽጉ ወጥቶ አልዋጋ ቢላቸው ከብታቸው ባዲስ በሽታ ሲያልቅባቸው፤ “እንግዲህ ጣሊያን እንደቀበሮ ከጉድጓዱ አልወጣ ካለኝ ምናባቱ አረገዋለሁ” ብለው ወደመቀሌ ሲመለሱ ነገር አለሙ ተቀይሮ ያገኙታል።

አንድ ልጃቸው ራስ አርአያ በበሽታ ሞቱባቸው።

በሂዊት ውል ምክንያት ራሳቸው የተነኮሱት ሁለተኛ ጠላታቸው ድርቡሽ (ሱዳን) በጌምድርን ወርሮ፣ ደምቢያን አጥፍቶ፣ ንጉሥ ተክለሃይማኖትን ሳር ውሃ ላይ አሸንፎ፣ በግምት አርባ ሺህ የሚሆን ሠራዊታቸውን ገድሎ፣ ደምቢያ ውስጥ 200 አቢያተ ክርስቲያናትን አቃጥሎ፣ ጎንደር ገብቶ ተጨማሪ 69 ቤተክርስቲያናትን አቃጥሎ፣ 15 ሺህ ሕፃናት እና ሴት አረጋውያንን እንደበግ አርዶ፣ 10 ሺህ የሚሆኑ የጎንደር ወንዶችን በጃቸው ብረት፣ ባንገታቸው ሰንሰለት አስገብቶ ለባርነት ወደሱዳን ነድቶ ወስዶ፣ ንጉሥ ተክለሃይማኖት ሞራላቸው ላሽቆ አፄ ዮሐንስን ከድተው ቢያገኙ፣ እርሳቸው ጎጃም ወርደው ንጉሥ ተክለሃይማኖትን አሳምነው ከዚያ በኋላ ፊታቸውን ወደምዕራብ በማዞር የክርስቲያንን ደም ለመበቀል መተማ ወርደው በደንብ ከተዋጉ በኋላ አሸንፈው እያሉ፣ ነገር ግን በበራሪ ጥይት ትመትተው፣ በመጨረሻም አንገታቸው በድርቡሽ ጎራዴ ተቆርጦ ህይወታቸው አለፈ። በዚህም ኢትዮጵያ አፄ ዮሐንስን ልክ እንደ አፄ ቴዎድሮስ ገበረች።

ከአንድ ዓመት በፊት በ1888 (1880 ዓም) ጣሊያኖች በሃማሴን ምድር የለቀቋቸው ከሕንድ የመጡ ሁለት ላሞች ጤነኞች አልነበሩም። የመጡበትም ስውር ምክንያት ነበረ። እነዚህ ሁለት ላሞች ደስታ በሽታ በሚባል በሪንደርፔስት ቫይረስ (Rinderpest Virus) በሚመጣ በሽታ የተለከፉ ነበሩ። ይህ ቫይረስ የቀንድ ከብት፣ በግ፣ ፍየል፣ ላም፣ በሬ፣ ሚዳቋ፣ ድኩላ ይገድላል። የቀንድ ከብት ኮቪድ ወይም ኮሮና ሊባል ይችላል። እንደኮቪድ በትንፋሽ፣ በምግብ፣ በንክኪ ከከብት ወደሌላ ከብት እየተላለፈ በፍጥነት ይገድላል። አለቃ ለማ ኃይሉ እንደዘገቡት፤ በ1880 ዓም በግንቦት ወር የሃማሴን ከብት አለቀ፤ በሰኔ ወር የትግሬን ከብት ጨረሰ፤ በሐምሌ ወር የቤጌምድር ( የዛሬው ጎንደር) ፤ በነሐሴ ላስታና ወሎ፤ በመስከረም የጎጃም ከብት ሙሉ በሙሉ አለቀ። በህዳር ወር ሸዋ ገብቶ የሸዋ ከብት አንድ ሳይቀር አለቀ ይላሉ።1 እንግዲህ ከዚህ በኋላ ወደአርሲ፣ ቦረና፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ አፍሪቃ ድረስ አስር ዓመት ሙሉ የአፍሪቃን የቤትና የዱር እንስሳትና የቀንድ ከብት ፈጀው።

በኢትዮጵያ ላምና በሬ ከነነፍሱ ማየት ብርቅ ነገር ሆነ። አለቃ ለማ ከጎጃም ወደሸዋ ሲጓዙ ያዩትን ሲመሰክሩ፤ “በምንገድ ላይ አንዲት ጥቁር ጥጃ ብቻ አየን፤ አንደዜ ወዲህ አንደዜ ወዲያ ትሄዳለች ። ይህም ምንገደኛው ስደተኛው ጎጃሜ፣ “መንታ ውለጅ፤ ዘር ውለጅ፤ ዘር ያርግሽ፣ ይባርክሽ” እያለ እየመረቃት ይሄዳል። የእኔ አባት 300 ከብት ነበራቸው፤ አንዲት ጥጃ ተረፈቻቸው።”2

በዘመኑ ከሚገመቱት ከ20 ሚሊዮን የቀንድ ከብት ዘጠና በመቶው በዚህ በሽታ አለቀ። የከብቱን ሬሳ የሚቀብረው ወይም የሚያቃጥለው ስላልነበረ አገር መሬቱ ገማ፣ ሸተተ፣ ጠነባ። አባቶች ይህን ዘመን “የከብት በሽታ ዘመን” ይሉታል።

በኢትዮጵያ እርሻ የሚደረገው በበሬ ስለሆነ በሬውም በበሽታ ስላለቀ ማረሻ ጠፍቶ እህል ስላልተዘራ በሃገሪቱ ረሃብ ገብቶ ዘመነ ፍዳ፣ ዘመነ መከራ ተጀመረ። በቀጣዩ ዓመት ያልተቀበረውን ከብት የሚበላ ዝንብ አገሩን ሞላውና ተላላፊ በሽታ ተስቦ (Typhoid, Typhus) ይህንን ደካማ ህዝብ ረፈረፈው። ከዚያ የተረፈውን ህዝብ dysentry እና Cholera የሚባል አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ ጨረሰው። በሁለተኛው ዓመት ዝናብ ቀረና ድርቅ ሆነ።

በሶስተኛው ዓመት ፈንጣጣ የሚባል ቸነፈር ገብቶ ታዳጊ ሕፃናትን፣ ደካማና አሮጊት እንዲሁም ሽማግሌውን ሁሉ በመደዳ ጠረገው። በዚህ ዓመት የነፋስ በሽታ የሚሉት ኢንፍሉዌንዛ ገብቶ ያንን መከረኛ፣ ችግረኛ፣ በሽተኛ የኢትዮጵያ ህዝብ መረፍረፍ ተያያዘ።

በአራተኛው ዓመት ድንገት በመዶሻና በእንጨት ተቆፍሮ፣ ተዘርቶ በድብቅ የበቀለውን እህል ያንበጣ መንጋ ተነስቶ አገሪቱን ወርሮ ስለመደመደው እህል ከነምልክቱ በሀገሪቱ ጠፋ። ምስኪኑ ህዝብም በሞት ተረፈረፈ።

እነዚህን አራት የፍዳ ዘመናት (1880-4 ዓም) አዛውንት “የክፉ ቀን ዘመናት” ይሉታል። በእነዚህ አራት ዓመታት የኢትዮጵያ ከብት ዘጠና በመቶ አለቀ። ያገሪቱ ህዝብ ሰላሳ አምስት በመቶ ወይም ሶስት ሚሊዮን ህዝብ በበሽታና በረሃብ ሞተ። በሃገሪቱ ታሪክ ላይ ታላቅ ጠባሳ ትቶ የሄደ፣ ሃገሪቱን እጅግ ያራቆተ፣ ያገሪቱን ህዝብ የበላ እና ታይቶ የማይታወቅ ቸነፈርና ወረርሽኝ የሃገሪቱን ህዝብ ባህርይ ክፉኛ የለወጠና የተጠናወተ ፈተና ነበር።

አለቃ ለማ እንዲህ ያስቀምጡታል፤ “[አዲስ አበባ] አሁን ሥላሴ የተሰራበት ላይ የራስ ደስታ አባት ቤት ነበረ፤ እኛ እዚያ ባንዱ ቤት ነበርን። ሌሊት ‘ወሰደኝ! ወሰደኝ!ወሰደኝ!’ ሲል ያድራል። በበነጋው ማልዳ ጉባኤ ስኼድ፣ አለቃ ወልደ ያሬድ ፤ ‘ ለማ ዛሬ ሌሊት ጅቡ ስንት ሰው ወሰደ?’ ይሉኛል። እኔም አምስት፣ ስድስት እስከ ሰባት ድረስ ወሰደ፤’ እላለሁ፤ በድምጡ በጩኸቱ እየለየሁ ‘ይህን ያህሉ ወንድ፣ ይህን ያህሉ ሴት’ እላለሁ። ጅብ ሊከለክል ማን ይወጣል። አድናለሁ ብሎ ቢወጣ እሱን ራሱን ቢወስደው፣ ማን ያስጥለዋል። ሁሉም ደካማ ራብተኛ ነው። ከኛ ዘንድ ጋይንቴ ደስታ የሚባል ሰው ነበረና አንዲት ኮረዳ ዘመዱን ወደ ፍል ውሃ ቢልካት ያ ሁላ ራብተኛ የተሰበሰበው እዚያ ሰፍሮ ነበርና ያቺን ልጅ ተቀብሎ እያረደ ተከፋፍሎ በላት። ሰው እህል አጥቶ ፍራፍሬ፣ ቅጠል፣ አህያ፣ ፈረስ ሁሉን በላ። ያልተበላ ቅጠል፣ ያልተበላ አውሬ የለም። እናቶች ጥቃቅን ልጆቻቸውን አርደው በሉ።”3

ድሃውና ሀብታሙ እኩል ተራቡ፣ ተቸገሩ፣ ረገፉ። ምኒልክ እህል በየመኳንንቱ ቤት እየተደበቀ ድሃው ብቻ እንዳይሞት ብለው በጠቋሚ እየተፈለገ ከጉድጓድ እየተቆፈረ ወጥቶ ለድሃው እንዲታደል አደረጉ። እንጦጦም ትልቅ አዳራሽ አሰርተው ለድሃው ግብር አበሉ። ከብት ስላለቀም አርአያ ለመሆን አካፋና ዶማ አበጅተው እራሳቸው መሬት እየቆፈሩ እህል መዝራት ጀመሩ።

ያገራችን አርሶ አደር ገበሬው አርብቶ አደር ዘላኑ፣ ካህኑ፣ ወታደሩ፣ ድሃው፣ ሃብታሙ፣፣ ክርስቲያን እስላሙ ከምባታው ፣ሃዲያው፣ አማራ ትግሬው፣ ኦሮሞ ፣አፋሩ፣ ሱማሌው ሁሉም እኩል ረገፈ። የእግዜር ፍጡር ሁሉ በረሃብና በቸነፈር ተቀጣ።

ሚስትና ልጆቹ አይኑ ፊት ሲሞቱበት በአይኑ እያየ መቻል ቢያቅተው አባወራ ራሱን ሰቀለ። ግማሹ ገደል ተወርውሮ ራሱን ገደለ። ከፊሉ ዓለም ለምኔ ብሎ ለምናኔ ገዳም ሲገባ፣ ረሃብ ተከትሎ አባሮ ገዳም ውስጥ ገደለው። ለልጇ የምትሞት እናት አንዱን ልጇን ለማዳን ስትል የሌላውን ልጇን ሥጋ በላች ። እንሳሮ መራቤቴ አንዲት ሴት ልጇን አርዳ በላች ተብላ ተከሳ አፄ ምኒልክ ፊት ቀረበች። አፄ ምኒልክም እውነት የገዛ ልጅሽን ሥጋ በላሽን ብለው ጠየቋት ። እርሷም አዎ ጃንሆይ እግዜር ያሳይዎ፤ ረሃቡ ቢጠናብኝ፣ አንጀቴ ቢታጠፍብኝ፣ ጡቴ ቢደርቅብኝ፣ ልጀ ቢደክምብኝ፣ እኔም እሱም መሞታችን ካልቀረ ብዬ የሶስት ዓመት ልጄን ገድዬ በልቼ ከሞት ዳንኩ ብትላቸው፣ አፄ ምኒልክም እንባቸው ቁርዝዝ ብሎ እያለቀሱ፤ አዬ እንዴት ድሃዬ ተጎዳብኝ፣ አለቀብኝ ብለው ለዚያች ሴትም የምትበላውን አዝዘው የተረፈውም ልጇ እንዲማርላት ለአቶ ሮባ ወደ አታክልት ሰደዱት ።

ባገራችን ረሃቡ ትንሽ ቀለል ያለለት ቆጮ/እንሰት የሚበላው የጉራጌና የአካባቢው ማህበረሰብ ነበረ። ቆጮ በበሬ የማይታረስ ተቀብሮ ቅይቶ ተቆፍሮ የሚወጣ በመሆኑ ይህንን እሴቱን አይተው፣ ነፍስ አድንነቱን ወደው፣” የክፉ ቀን ደራሽነቱን አድንቀው ምኒልክ እንዲያው እባካችሁ ይህን ወርቅ ነገር ከዛሬ ጀምሮ ወርቄ”፣ “ወርቅዬ” በሉልኝ እንጅ ቆጮ አትበሉኝ አሉ።

በ1884 ዓ.ም ከብቶች ከውጋዴንና ከባሌ እየተሰበሰቡ፣ እየተነዱ ለየመኳንንቱና ለገበሬው እየታደሉ ስለተባዙ ቀስ በቀስ ማገገም ተጀመረ። ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ለመዳን ከአሥር ዓመት በላይ ወሰደ።

ቸነፈሩ ባቆመ በአራተኛው ዓመት (በ1888 ዓም) በዓድዋ ዘመቻ ጊዜ ረሃብ ገና ከትግራይና ከወሎ አልወጣም ነበር። ከቸነፈሩ የተረፈው ህዝብም አካለ ጎደሎ፣ ገመምተኛ፣ በሽተኛ ነበር። አድዋ ከዘመተው መቶ ሺህ ወታደር ቁጥሩ 26 ሺህ የሚሆነው ጤና ቢስና አካለ ጎደሎ ነበር።

ያገር ጥሪና የንጉሥ ትዕዛዝ ሆኖበት በሽታውን ተቋቁሞ፣ ስንቁን ቋጥሮ፣ ጦርና ጋሻውን አንግቦ፣ የሌለው ደግሞ ቆመጡን ይዞ ከአራቱ ማዕዘን ወደአድዋ ሲተም ወደአንድ ሺህ የሚገመተውን ዘማች ኃይል ረሃብ፣ ተቅማጥ፣ ንዳድ፣ ተስቦ በየቀኑ ይረፈርፈው፣ ያስቀረው ነበር። የተረፈው ተርፎ ፋኖ የሟቹን፣ የጓዱን ጦርና ጋሻ፣ ነፍጥና ጎራዴ ከሬሳው ላይ አንስቶ፣ ሰውነቱን ብርድና ሃሩር እየተፈራረቀበት፣ ገላውን ተባይ እየበላው፣ ሆዱን ረሃብ እየሞረሞረው፣ ባዶ እግሩን እሾህ፣ አሜከላና ሙጀሌ እያቆሰለው፣ ልቡ በሃገር ፍቅር እየነደደ፣ ወኔው እየተንቦገቦገ አድዋንና አድዋን ብቻ እያየ ዘመቻውን ቀጠለ። በተለይ እግሩን እያቆሰለች አላራምድ ያለችውን ሙጀሌ “አማከለች ድንቁ” እያለ እያሾፈባት ፣

አማከለች ድንቁ ነፍስሽን አይማረው፣

እግሬ ቆሞ ቀረ መሄድ እያማረው።

እያለ እየፎከረና እየሸለለ፣ እንደአንበሳ እያገሳ፣ እምቢኝ ለሃገሬ ብሎ የሞት ሞቱን እንደምንም ብሎ አድዋ ደርሶ ጠላቱንና ያርባ ቀኑን እድሉን መጠባበቅ ጀመረ።

እለተ ቀኑ ሲደርስ አራት ዓመት ሙሉ በበሽታ፣ በቸነፈርና በረሃብ የተፈተነው ዘማች ኃይል፣ ፈጣሪ ወደኢትዮጵያ ፊቱን ስላዞረ ሁሉ ነገር አምሮ፣ አሳምሮ፣ አስተካክሎ፤ ለጠላት ግን ሁሉን ነገር አደናግሮ፣ እንዳይሆን፣ እንዳይሆን አድርጎ የካቲት 23 ቀን 1888 ታሪክና ተዓምር ተሰራ። ኢትዮጵያውያን ጠላታቸውን ድል መቱ። ነፃነታቸውንም አረጋገጡ። ኢትዮጵያ ለአፍሪቃና ለመላው ጥቁር ህዝብ አለኝታና መመኪያ ሆነች ። አባቶች ያቺን የድል ቀን በማስታወስ፤

ለጠላቶች ዘንቦላቸው፣ ዘመኑ ሆነ መኸራቸው፤

ለኛም ደግሞ ዘንቦ አማረ፣ ደመና ሆኖ አልቀረ። በማለት ተቀኝተውበታል።

ትንተናና መደምደሚያ፤

ጣሊያኖች ከብቶቻችንን በሪንደርፔስት ቫይረስ ጨርሰው፣ ብዙ ህዝባችንን በረሃብ ከምድረ ገጽ አጥፍተው፣ ሃገራችንን ለመንጠቅ ሆን ብለው ከእንግሊዞች ጋር መክረው ይህንን ስነህይወታዊ የዘር ማጥፋት ጦርነት (Biological Warfare, Holocaust, Genocide) እንደፈጸሙብን ግልጽ ቢሆንም፣ አሁን ከ120 ዓመት በኋላ እንደ አዲስ ነገር ክስ መመስረት ከባድ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ይህ በታሪካችን ታይቶ ተሰምቶ የማይታወቅ በሽታ፣ ይህ የኢትዮጵያን ሶስት ሚሊዮን ህዝብ የፈጀ በሽታ፣ ይህ 20 ሚሊዮን የሚገመት ከብት የጨረሰ በሽታ፣ ይህ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ትልቅ ጠባሳ ትቶ የሄደ ወደር የማይገኝለት ቸነፈር እንዴት ከተስፋፊ ጠላቶቻችን ጋር ገባ ብሎ አለመጠየቅ ይቅርታ የማይደረግለት ስንፍና እና ድንቁርና እንደሆነ ይሰማኛል።

ይህ አንገብጋቢ ጉዳይ እስከዛሬ አለመነሳቱ እውነትነቱን አያሳንሰውም። ይህ ክስተት መጠናት፣ መነገር፣ መዘከር፣ መፍረጥረጥ፣ መተንተን ያለበት አቢይ ጥያቄ ነው።

አራት ነጥቦችን እናንሳ፤

1ኛ – ኢትዮጵያ በዚህ በክፉ ቀን ዘመን ውስጥ 4 ዓመት ሙሉ ይህን ያህል ሰውና ከብት ሲረግፍ ሁሉን ነገር የሚያውቁት አውሮጳውያን በመንግሥት ደረጃ አንዲት ነገር ትንፍሽ አላሉም፤ አንድ መግለጫ እንኳ አላወጡም። በግለሰብ ደረጃ የጣሊያን ምሁሮች፣ የሃይማኖት አባቶች ሲጠየቁ የሚሰጡት መልስ እርስ በርሱ የሚጋጭ ተራ ማስተባበያ እንደሆነ በግልጽ ይታያል። በመጀመሪያ ከዶጋሊ በኋላ እነዚያን ሁለት ላሞች በምፅዋ በኩል አስገብተው ሐማሴን ምድር ላይ መልቀቃቸውን አይክዱም፣ ያምናሉ። ችግሩ በሚቀጥለው ጥያቄ ላይ ነው። የቀንድ ከብት በተትረፈረፈባት ሀገር ከኢትዮጵያ የተሻለ የከብት ዘር ከሌለባት ከህንድ ሃገር በምን ምክንያት እነዚያን ሁለት ላሞች አስመጣችሁ? ለርቢ ወይስ ለወተት ብለው እንደሆነ ሲጠየቁ የሚመልሱት መንተባተብ ብቻ ነው። አንዳንዴ እኛ ያስገባነው የጭነት በቅሎና ፈረስ ነው ይላሉ። ሪንደርፔስት የቀንድ ከብት እንጅ የጋማ ከብት በሽታ አይደለም ስንላቸው ላሞቹ ባጋጣሚ ከፈረሶቹ ጋር ተጭነው መጡ የሚል የማይመስል ምላሽ ይሰጣሉ። አንዳንዴም ደግሞ እንዲያውም የከብቱ ነገር እንዳጋጣሚ ሆኖ ነው እንጅ በሽታውን ያመጡት ለሀጂ መካ ደርሰው የተመለሱት የናንተው ሙስሊም ዜጎች ናቸው ይሉናል። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መካ ሄደው ላምና ጥገት ይዘው ተመለሱ የሚባል ነገር አናምንም፣ አይሆንም፣ አይሰራም። በገላቸው ይዘውት መጡ እንዳይሉ ሪንደርፔስት ቫይረስ በቀንድ ከብት እንጂ በሰው ገላ አይተላለፍም።

2ኛ- በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያ 4 ዓመት ሙሉ በረሃብና በቸነፈር ህዝቧ ሲረግፍ፣ 3 ሚሊዮን ያህል ህዝብ ሲያልቅ፣ የአውሮጳ መንግሥታት ጣሊያን፣ ፈረንሳይም ሆነ እንግሊዝ ለናሙና እንኳ አንዲት ሊሬ፣ አንዲት ፍራንክ፣ አንዲት ሽልንግ፣ ለበሽታው አንዲት ክኒን ሆነ አንድም ነርስ ወይም ሃኪም እርዳታ አላበረከቱም።

የስዊድን መንግሥት ሳይሆን የስዊድን ሚስዮን ግን በትግራይ ምንኩሉ ገዳም አካባቢ 20 ሺህ የስዊድን ብር (ክሮና) የሚያወጣ እርዳታ ለ800 ሰዎች ሰጥተው ገንዘቡ ሲያልቅ እንዳቆሙ፤ የካቶሊክ ሚሲዮን በትግራይ ትንሽ እርዳታ እንደሞከረ ተዘግቧል።4 በመንግሥት ደረጃ ግን ምንም ከየትም ሃገር አልታየም።

3ኛ- ጣልያኖች በሽታውን በደንብ ስለሚያውቁት በያዙት በኤርትራ ግዛት በፍጥነት ተቆጣጥረውት እህል በብዛት ከውጭ አስመጥተው ለግዛታቸው ማስፋፊያና ማረጋጊያ ጥሩ መሣሪያ አርገው ተጠቀሙበት ። ከአፋር፣ ከትግራይና ከወሎ እህል ፍለጋ ወደምፅዋ የተሰደዱትን ኢትዮጵያውያን ግን መግቢያ ፈቃድ ከለከሉ። ቀደም ብለው የደሩስትን የትግራይ ረሃብተኞች እነ ጋንዶልፊኒ ከምፅዋ ወደብ ላይ በጭካኔ ያለምህረት ጠራረጓቸው፣ አባረሯቸው።

ማርቲኒ (Martini) የተባለው የኤርትራ አገረ ገዥ የተሰበሰበውን የስደተኞች ብዛት ተመልክቶ በመጠየፍ፤

“በሩቁ አንዳንድ ሊሬ ወረወርኩላቸው ግና ነገ ጠኔ ለሚጠርገው ችጋራም የእኔ አንድ ሊሬ ምን ይረባዋል። ነገ ድብን ይላት የለምን። እንዲያውም እኮ እነዚህ ችጋራም ብቻ አይደሉም፣ ሰነፎችም ናቸው። ዛሬ የረባ እርዳታ ብናደርግላቸው ነገ ደግነታችንን የሰማ ድፍን ሃበሻ ግልብጥ ብሎ ይመጣብናል፣”5 እያለ ተመጻድቆ ሊሬውን ወርውሮ ወደቤቱ ገባ።

4ኛ- ኢትዮጵያውያን በዚህ በሰው ሰራሽ ረሃብና በሽታ ሲያልቁ አውሮጳውያን ግን በበርሊን ኮንፈረንስ ውል [1884-85] መሰረት አንድ ጊዜም እንኳ ሳይጋጩ በሚገባ ተስማምተው በየፊናቸው ግዛታቸውን በቀላሉ ማስፋፋት እና አፍሪቃን መቀራመት ቀጠሉ። ጣሊያን ለኤርትራ ግዛት እውቅና አገኘችበት፤ ሊብያን፣ ሞቃዲሾን ያዘችበት ። ቀደም ብላ አፄ ምኒልክን የውጫሌ ውል አስፈረመችበት ። ፈረንሳይ ታጁራን፣ ጅቡቲን ያዘች። እንግሊዝ ሱዳንን፣ በርበራን፣ ኬንያን ያዘች ። ኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዘን ተከበበች ።

አፄ ምኒልክ በደከመ ጉልበታቸው እየተፍጨረጨሩ፣ እየተራወጡ እንደምንም ብለው ከነዚህ ጉልበተኞች ጋር እየተፋለሙም፣ እየተፈራረሙም ዳር ድንበራቸውን ማስከበር ላይ አተኮሩ። ረሃብና በሽታው ህዝባቸውን ክፉኛ ጎዳው። በአድዋ ዘመቻ ጊዜ የምግብ እጥረት ስለነበረባቸው በየቀኑ ከጦራቸው አንድ ሶስተኛው (በግምት ሰላሳ ሺህ) ከጦሩ ሜዳ ርቆ በየትግራይ መንደር ውስጥ ምግብ ፍለጋ ይርመሰመስ ነበር።

ዋይልድ (Wylde) የተባለው ታሪክ ዘጋቢ እንዲህ ጽፏል፤ ጣሊያኖች ቸኩለው ጦርነቱን በየካቲት 23 ከመጀመር ይልቅ ትንሽ ታግሰው አምስት ቀን ቆይተው በየካቲት 28 ቢጀምሩ ኖሮ፣ የምኒልክ ሠራዊት በረሃብና በችጋር ተፈትቶ፣ ተሸንፎ ያገኙት ነበር ብሏል። በርግጥም ከአድዋ ድል በኋላ ምኒልክ ኤርትራ ዘምተው ጣሊያንን እንደገና ወግተው ለማባረር ያልጣሩበት ምክንያት ዋናው ምሥጢሩ እዚህ ላይ ነው።

አፄ ምኒልክ ከጦርነቱ በፊትና በኋላ ያሳዩት ደግነት፣ ጀግንነት ፣ ምህረትና ቸርነት፣ የሰላም ጥረት ድፕሎማሲ ኢትዮጵያውያን ከአውሮጳውያን እኩል ወይም በይበልጥ ስልጡን ህዝብ መሆናቸውን አስመስክሮ የዓለምን መንግሥታት ግንዛቤ መቶ በመቶ ቀየረው። ስለኢትዮጵያ በሮም፣ በፓሪስ፣ በለንደን እና በበርሊን ከተማዎች የምርምር እና ጥናት ተቋሞች መቋቋም የጀመሩት በዚያን ጊዜ ነው። ኢትዮጵያ ማለት ስልጡን፣ ትሁት፣ ጀግና፣ ዓይናማ ማለት ሆነ። ስምንት ዓመት ሙሉ በረሃብና በበሽታ ሃገሪቱ ስትቀጣ በፀጥታ ሲመለከቱ የነበሩ ሁሉ የገንዘብና የህከምና እርዳታ ለማበርከት የአውሮጳ መንግሥታት እርስ በርሳቸው ይሽቀዳደሙ ጀመር። ሩስያ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን ሳትቀር የህክምና ቡድኖችን መላክ ጀመሩ። ይህንን ጋጋታ የታዘበ የእንጦጦ ተራቢ፤ አንጀቴ ተቆርጦ ተሆዴ ተወጣ፤ እንግዲህ አኪሙ ምን ሊቀጥል መጣ ቢልም አፄ ምኒልክ ግን ሁሉንም በትህትና ተቀብለው በሚያስፈልጋቸው ቦታ አሰማርተው የኋላ የኋላ የባልቻን፣ የምኒልክንና ሌሎችን ሃኪም ቤቶች ለመመስረት እርሾ አርገው ተጠቀሙበት ።

እንግዲህ ቁም ነገሩ ዛሬ ስለአድዋ ድል ስናነሳ በአውሮጳውያን የተጠነሰሰውንና የተተገበረውን የከብት በሽታን፣ የክፉ ቀን ሰው ሰራሽ፣ ሰው አመጣሽ ረሃብና ቸነፈር መርሳት የለብንም። ያለቁብንን ሶስት ሚሊዮን እናትና አባቶች፣ ያጣናቸውን 20 ሚሊዮን የቀንድ ከብቶቻችንን አብረን ማስታወስ አለብን።

ይህ በሽታ እንዴት ገባ፤ ለምን ገባ ብለን ጠይቀን ምርምርና ጥናት እናድርግ። ይህ የኛ እልቂት ከ1905 የአርመኖች እልቂት እንዲሁም በ1940ቹ በአይሁዶች ላይ ከደረሰው እልቂት (Holocaust) ቢብስ እንጅ አይተናነስም። ይህን ጥያቄና ምርምር ማድረግ ያለብን ካሣ ለመጠየቅ አይደለም፤ ሆኖም ግን እውነቱ ታውቆ በታሪክ ማህደር ተመዝግቦ እንዲቀመጥና ተከታታዩ ትውልድ እንዲማርበት አስፈላጊ ስለሆነ ነው። አለበለዚያ ታሪክ ነገ ራሱን ይደግምና ያባቶቻችን ደም ቆሞ ይፋረደናል፤ አጥንታቸው እሾህ ሆኖ ይወጋናል፣ እሳት ሆኖ ያቃጥለናል።

የታሪክ ተመራርማሪዎቻችን ልዩ የጥናት ትኩረት ሰጥተውት በተለያየ መድረክ የዓለም ምሁራንን አሳትፈው እንዲመረምሩት፣ እንዲመክሩበት፣ ለጥያቄውም መልስና እልባት እንዲያገኙለት ምኞቴ ነው።

**** **** **** ****

ልዩ ምስጋና ምክር ለለገሱኝና ለመጣጥፉ ምንጮች ስለጠቆሙልኝ ለአቶ ፈንታሁን ጥሩነህ እና ለአቶ አክሊለ ገ/ ጊዮርጊስ፣ እንዲሁም ለውርስና ቅርስ ማኅበር ሊቀመንበር ለአቶ ለይኩን ካሣሁን ከፍ ያለ ምስጋና ይገባቸዋል።

ይህ ጽሑፍ የተዘጋጀው ጸሐፊው ከዚህ ቀደም ለውርስና ቅርስ ማኅበር በላኩት የቪዲዮ አቅርቦት በደራሲው ፈቃድና ተሳትፎ ተቀድቶ ነው።

የመጣጥፉ ጥናት ምንጮች፤

1- Richard Pankhurst; The Great Famine of Ethiopia 1888-1892። ገጽ 14

2- መንግሥቱ ለማ፤ መጽሐፈትዝታ ዘአለቃ ለማ፤ ገጽ 142።

3- እንደላይኛው፣ ገጽ 143።

4- The Great Famine of Ethiopia.ገጽ 45።

5- እንደላይኛው፤ገጽ 45።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.