መግቢያ
እንደሚታወቀው ከጥንት ጀምሮ ከልዩ ልዩ የዓለም ክፍሎች መነኮሳውያንና ሌሎች መንፈሳውያን ክርስትያኖች የቅዱስ ጴጥሮስንና የቅዱስ ጳውሎስን መቃብር ለመሳለም ወደ ሮም ይሄዱ ነበር። የሮም ርእሰ–ሊቃነ ጳጳሳት እነዚህን ነጋድያን (ፒልግርምስ) ፕሮፓጋንዳ ፊደ (Propaganda Fide) በተባለ በሮም ከተማ በሚገኝ እንግዳ–ቤት በጊዜያዊነት ያስቀምጧቸው ነበር። ከነዚህ የቅዱስ ጴጥሮስንና የቅዱስ ጳውሎስን መቃብር ለመሳለም በኢየሩሳሌም በኩል ወደ ሮም ከሄዱት ተሳላሚዎች መካከል ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል። በርእሰ–ሊቃነ ጳጳሳት ሲስቱስ ፬ኛ ዘመነ ጵጵስና (1471-1484) ኢትዮጵያውያንን ከሌሎች ለይተው በቫቲካን ውስጥ በቅዱስ ጴጥሮስ መቃብር አጠገብ (አሁን የቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል ያለበት ጎን) አንድ ቦታ ሰጧቸው። ይህ በሮም ሊቃነ–ጳጳሳት ለኢትዮጵያውያን የተሰጠው ቦታ በቅዱስ ኢስጢፋኖስ ገዳም (San Stefano degli Abyssini) ሆኖ ራሱን የቻለ እንግዳ–ቤት (መኖርያ ቤት) ያለው ነው። በነገራቸን ላይ የያኔ ቤተክርስቲያን እስካሁን ድረስ አለ። ኋላ ግን መኖርያ ቤት በነበረበት ቦታ ላይ ለኢትዮጵያውያን የሚሆን ኮሌጅ (Collegio Etiopico) ተሰርቶበታል።
ይህ ቦታ ለኢትዮጵያውያን ከተሰጠ በኋላ ወደ ሮም የሄዱ ኢትዮጵያውያን ነጋድያን (ተሳላሚዎች) ሁሉ የሚያርፉት በዚሁ ቦታ ነበር። ቦታው ሲበላሽ ራሳቸው እያሳደሱ ከዘመን ወደዘመን እንዳስተላለፉም ግልጽ ነው። ለምሳሌ “አባ ሃብተማርያም ዘደብረ–ጉባኤና አባ ተክለማርያም ዘደብረ–ዲማ ከመንበረ–ጴጥሮስ ተከታዮች ለኢትዮጵያውያን የተሰጠው ቤተ–ክርስቲያን አርጅቶና ተበላሽቶ ስላገኙት በገንዘባቸው እንደገና አድሰውታል” የሚል በቅዱስ ኢስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ውስጥ በእብነ–በረድ ላይ በግዕዝ ቋንቋ ተጽፎ ይገኛል።
ርእሰ–ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ ፲፭ኛ በ1919 ኢትዮጵያ ከድሮ ጀምራ በቫቲካን ውስጥ የነበራትን ቤት የመንገደኞች ማረፊያ ብቻ መሆኑ ቀርቶ ቋሚ የተማሪ–ቤት (ኮሌጅ) እንዲሆን አደረጉ። በርእሰ ሊቃነ ጳጳስት በነዲክቶስ ፲፩ኛ የሰሩት ኮሌጅ ስላረጀና የተሰራበት ቦታ እዛ ይኖሩ ለነበሩ ተማሪዎች ጤና የማይመች ስለነበር ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ ፲፩ኛ በቫቲካን አታክልት መሃል ከፍ ባለ ቦታ ላይ ሌላ አዲስ ኮሌጅ አሠሩ። ይህ ኮሌጅ ከተመሠረተ ዘንድሮ (2019) መቶኛ ዓመት ሆኖታል። ይህ ኮሌጅ እንዲመሠረት ምክንያት የሆኑት ከቀድሞ ዘመናት ጀምረው በእግር ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ከዛም ወደ ሮም በመጓዝ የቅዱስ ኢስጢፋኖስን ገዳም ያቆዩ መነኵሳት ስለነበሩ ነው፤ ስለነሱ እንመልከት።
ላይ እንደተጠቀሰው ኢትዮጵያውያን ተሳላሚዎች ከአስራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምረው የቅዱስ ጴጥሮስንና የቅዱስ ጳውሎስን መቃብር ለመሳለም ወደ ሮም ይሄዱ እንደነበረ በቫቲካን መዛግብትና በአንዳንድ የታሪክ ጸሓፊዎች ሰነዶች ተጽፎ ይገኛል። የሮም ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ለነዚህ ተሳላሚዎች በቫቲካን ውስጥ የሚገኝ ትልቁን ቅዱስ ኢስጢፋኖስ ገዳም የሚባለውን ጥንታዊ ቤተክርስቲያን ከነ እንግዳ ማኖርያ ቤት ሰጡዋቸው። ይህ ቤተክርስቲያን ለኢትዮጵያውያን ከተበረከተ በኋላ Santo Stefano Dei Mori “የቀይ ዳማዎች ቅዱስ እስጢፋኖስ” ተባለ። ከዛን ጊዜ ጀምሮ ይህ ቦታና ገዳም በኢየሩሳሌም በኩል ወደ ሮም ይሄዱ የነበሩ ኢትዮጵያውያን መነኮሳት የሚያርፉበት ንብረት ሆነ። መነኵሴዎቹ ከየትኞች የኢትዮጵያ ገዳሞች ይመጡ እንደነበረ ሁሉ በቫቲካን መዛግብት ተጽፎ ይገኛል። ደብረ–ዳሞ፣ ደብረ–ሊባኖስ፣ ደብረ–ቢዘን ወዘተ ለምሳሌ ሊጠቀሱ ይችላሉ። ኢትዮጵያ ከሌሎቸ ክርስተና ከተቀበሉ አገሮች ጋር ግንኙነት ማድረግ በማትችልበት ጊዜ ብዙ ጭንቅና ረሃብ ችለው ነበር እነዚህ መነኮሳትና ተሳላሚዎች በመንገድ ላይ ሊደርስባቸው የሚችለውን ችግርና አደጋ ተቋቁመው ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌምና ሮም ይጓዙ የነበሩት።
ከ1404 ዓም ቀደም ብሎ ከኢትዮጵያ ንጉሥ በአንድ ጣልያናዊ በኩል ለሮም ሊቃነ ጳጳሳት የተላከ ገጸ–በረከት መድረሱንና አለመድረሱን ለማረጋገጥ ሶስት ኢትዮጵያውያን በንጉሠ ነገሥታቸው ተልከው ወደ ሮም እንደሄዱና እንደደረሱ ተመዝግቦ ይገኛል። ከ1403 ዓ. ም. እስከ ፍሎረንስ ጉባኤ (1441) ድረስ ብዙ ኢትዮጵያውያን ወደ ሮም ተጉዘዋል፡፡ ከኢትዮጵያ የሚመጡ ነጋድያይ (ተሳላሚዎች) በሮም ሲኖሩ ከመኖርያ ቤት በተጨማሪ ለዕለት ምግባቸውና ለልብሳቸው ፓፓዎቹ ያስቡላቸው ነበር። ለነዚህ ተሳላሚዎች በጎ ተግባር ያደርጉ ከነበሩ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በስም የተጠቀሱም አሉ፦ ቦኒፋቾ ፬ኛ፣ ጎርጎሪዮስ ፲፪ኛ፣ ማርቲኖስ ፭ኛ፣ አውጎኒዮስ ፬ኛ፣ እስክንድር ፫ኛ፣ ሲክስቱስ ፬ኛ፣ ቀለምንጦስ ፯ኛ፣ ጳውሎስ ፫ኛ ወዘተ ። ኢትዮጵያውያን መነኵሳት ጉብኝታቸውን ጨርሰው ወደ አገራቸው በሚመለሱበት ጊዜ ጳጳሳቱ የጉብኝታቸውን ምስክር ሰጥተው በመንገድ ላይ እንዲረዱ ያደራ ደብዳቤ ይሰጡዋቸው እንደነበረም ተመዝግቧል። በ1441 ዓ. ም. የኢትዮጵያ መነኵሳት ኒቆዲሞስ በተባለ አበምኔት ተልከው ከኢየሩሳሌም በፍሎረንስ ጉባኤ ለመሳተፍ ሄደዋል፡፡ ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ከመመለሳቸው በፊት ሮምን ሊጎበኙ እንደሄዱና በሮም ቤተክርስቲያንና በመንግሥት ባለስልጣናት እንዲሁም በህዝብ ትልቅ አቀባበል እንደተደረገላቸው ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ መነኮሳት ወደ ሮም መሄድ ከጀመሩ እስከ 15ኛ ክፍለ–ዘመን መጨረሻ ድረስ በቅዱስ እስጢፋኖስ ቀዳሜ ሰማዕት ገዳም ይኖሩ የነበሩት የቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል ካህናት እንግዶች ሁነው ነበር፣ ከዛ በኋላ ግን የቅዱስ ኢስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ከነ መኖርያ ቤቱ የነሱ ንብረት ሆነ፣ የገዳሙ ባለቤቶችም ለመሆን በቁ።
በርእሰ–ሊቃነ ጳጳሳት ልዮን ፲ኛ ዘመነ ጵጵስና (1513-1521) በገዳሙ 30 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን መነኰሳት ይኖሩ እንደነበረና አንድ አባ ቶማስ የሚባል አንድ ዓይኑ የተጎዳ ኢትዮጵያዊ መነኵሴ የገዳሙ አበምኔት ሆኖ እንደተመረጠ ተመዝግቧል። አባ ቶማስ በጣም ሊቅ እንደነበረና ፓፓው በጣም ይወዱት ነበር ይባላል። አባ ቶማስ ከሁለት ዓመት በኋላ ታሞ እንደሞተና በቅዱስ ኢስጢፋኖስ ገዳም በክብር እንደተቀበረ ይነገራል። ከአባ ቶማስ ቀጥሎ አባ ዕንቊማርያም የተባሉ ተመረጡ፤ ከርሳቸው ቀጥሎም አባ ተክለማርያም ወይም ክፍለማርያም የሚባሉ ተመረጡ፤በዘመናቸው መነኵሳቱ የሚመሩበት ሕግ ወጣ። ቀጥለው አባ ዮሓንስ የሚባሉ ተሾሙ፡፡ በዘመናቸው ሁለተኛ የተሻሻለ የጎብኝዎች ሕግ አባ ተስፋጽዮን በሚባሉ የመነኵሳቱ አበ–ነፍስ በነበሩ መነኵሴ አማካይነት ተደነገገ። ሕጉ በግዕዝ ቋንቋ ተጽፎና ወደ ላቲን ተተርጐሞ የሁለቱም ቋንቋዎች ግልባጭ በገዳሙና በቫቲካን መዝገብ ቤት ተቀምጦ ነበር። አባ ዮሓንስ በሹመታቸው 32 ዓመት እንደቆዩና ክርሳቸው በኋላም ዮሓንስ መጥምቅ፣ጊዮርጊስ፣ ማርቆስ፣ ያዕቆብ፣ ሩፋኤል፣ ዮሓንስ አፈርዮ ወዘተ አበምኔቶች ሆነው እንደተሾሙ ተመልክቷል። ከዚህ ሁሉ የምንረዳው በ15ኛው ክፍለ–ዘመን የጀመረው የቅዱስ ኢስጢፋኖስ ገዳም በ16ኛው ክፍለ–ዘመን አንድ ትልቅ ገዳም ሆኖ እንደነበረ ነው።
በዘመኑ የሮም ፖፕ በነበሩ ሊዮን ፲ኛ እና በኢትዮጵያ ንጉሠ–ነገሥት መካክል በመልእክተኞች አማካይነትና በደብዳቤዎች ግንኙነት ይደረግ እንደነበረ ተመዝግቧል። ስለዚህም በተዋህዶ ቤተክርስቲያንና በካቶሊክ (ቫቲካን) መሃል ጥሩ የመተባበር መንፈስ ነበር፡፡ ይህ መልካም ግንኙነት በፖፕ ቀሌምንጦስ ፯ኛ ጊዜም ቀጥሏል። ስለዚህም የኢትዮጵያ ንጉሠ–ነገሥት ዳዊት ፪ኛ ወይም ልብነ ድንግል ለፖፑ አንድ ደብዳቤና አንድ የወርቅ መስቀል አልቫረዝ በተባለ ፖርቱጋላዊ መነኵሴ አማካይነት ልከውላቸው ነበር።
በ1550ዎች በቫቲካን ወደ 70 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን መንኮሳት እንግዶች ይኖሩ ነበር። ከነዚህ ብዙ ጊዜ ስማችው ተመልክቶ የሚገኝ አባ ጊዮርጊስ፣ አባ ዮሓንስ መጥምቅና አባ ተስፋጽዮን የሚባሉ ናቸው። አባ ዮሓንስ መጥምቅ በፖፕ ቤት የታወቀና የተወደደ እንደነበረ ተነግሮለታል። ከኢትዮጵያዊ አባትና ከግብጻዊት እናት በቆጵሮስ ደሴት ተወልዶ ያደገ ኢትዮጵያዊ እንደነበረ ፣ በቆጵሮስ በሚገኝ የኢትዮጵያ ገዳም ከመነኰሰ በኋላ ብዙ አገር ስለጎበኘ ብዙ ቋንቋ ያውቅ እንደነበረ ተነግሮለታል። የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ ወደ ፖፕ ፕዮስ ፬ኛ በዓረብኛ የጻፉትን ደብዳቤ ወደ ላቲን ቋንቋ ተርጉሟል፣ የኢትዮጵያ ንጉስ አጼ ዳዊት ፪ኛ ወደ ፖፕ ቀሌምንጦስ ፯ኛ የጻፉትን ደብዳቤ የተርጐመም እሱ ነበር። ፖፑ ከምስራቃውያን አብያተ ክርስቲያናት ጋር በነበራቸው ግንኙነት በእውቀቱ ይረዳቸውም ነበር። ስለዚህ ፖፑ በቆሮንጦስ ይገኝ የነበረው የኢትዮጵያ ገዳም ዋና ሆኖ እንዲቀመጥ ላኩት።
በየዘመኑ በቅዱስ ኢስጢፋኖስ ገዳም ይኖሩ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን መነኮሳት ብዙዎች ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ታሪክ፣ እንዲሁም ቋንቋን ለአውሮጳውያን በማሳወቅ ረገድ ብዙ አስተዋጾኦ አበርክቷል። ከነዚህ ሁሉም የላቀ አስተዋጽኦ ያደረጉ፣ በትምህርታቸው በጣም ይታወቁ የነበሩና በፈረንጆቸ “ጴጥሮስ ህንዳዊ” ተብለው ይጠሩ የነበሩ አባ ተስፋጽዮን ማልህዞ ናቸው። እርሳቸው በኢየሩሳሌም ጥቂት ዓመታት ከተቀመጡ በኋላ ከሁለት መነኮሳት ጓደኞቻቸው ጋር ወደ ሮም የሄዱት በ1538 ዓ ም ነበር። ሮም እንደደረሱ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን መነኵሳት ጋር በቅዱስ ኢስጢፋኖስ ገዳም ተቀምጠው ለሶስት ዓመት የላቲን ቋንቋ ተምረዋል። ሌሎቸ ብዙ ቋንቋዎችንም ያውቁ ነበር፣ እንዲሁም በቅዱሳን መጻሕፍት የበሰሉ ሰው ነበሩ፣ ስለዚህም ብዙ ሰው ያደንቃቸው እንደነበረ በተለይ በፈረንጆቸ ሊቃውንት ዘንድ እጅግ የተመሰገኑ እንደነበሩ ታሪካቸው ይገልጻል። አባ ተስፋጽዮን በ1548-49 በግዕዝ ቋንቋ የመጀመሪያ የሆነውን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት አሳትመዋል፤ የግዕዝ የቅዳሴ መጽሓፍ (የሓዋርያት አኰቴተ ቁርባን) እና እንዲሁም አንድ ሌላ ስለ ክርስትና በግዕዝ የተጻፈ መጽሓፍ ወደ ላቲን ተርጒመው አሳትመዋል። የኢትዮጵያን ቋንቋ ለማጥናት ብዙ ሊቃውንት ወደ እርሳቸው ይሄዱ ነበር። ከእርሳቸው ተምረው የተጠቀሙና ቁምነገር የሰሩ እነ ጳውሎስ ጀቦ፣ ፔትሮ ጓልትየሪ፣ ማርዮ ቪቶርዮን መጥቀስ ይቻላል። ከነዚህ ፔትሮ ጓልትየሪ ብዙ ቋንቋ ያውቅ እንደነበረና የፖፕ ጸሓፊ ሆኖ እንዳገለገለ ተመዝግቧል። እንዲሁም አባ ተስፋጽዮን መጻሕፍትን ከግዕዝ ወደ ላቲን ሲተረጒሙ እንደረዳቸው ተጠቅሷል።
ለኢትዮጵያውያን መነኮሳት ማረፊያ (ገስት ሃውስ) እንዲሆን በ1481 በፖፕ ሲክስቱስ ፬ኛ የተሰጠውን የቅዱስ ኢስጢፋኖስ ገዳም የኢትዮጵያውያን ንብረት እንዲሆን ፖፕ ጳውሎስ ፫ኛ በአባ ተስፋጽዮን አማካይነት በጽሑፍ አጸደቁ። በዛን ጊዜ በቤተክርስቲያኑ አጠገብ ለኢትዮጵያውያን መነኵሴዎች ሌላ ኣዲስ ቤት ተሰራ። ቲቮሊ በተባለ ሌላ አከባቢ ደግሞ የመነኵሴዎቹ የዕረፍት ጊዜ ማረፊያ የሚሆን ቦታ ሰጧቸው። ፖፕ ዩልዩስ ፫ኛም አባ ተስፋጽዮንን ስለኢትዮጵያ ጉዳይ አማካሪ አድርገው ነበር። የኢየሱሳውያን ማህበር ወደ ኢትዮጵያ እንዲላክ ምክር የሰጡም እርሳቸው ናቸው ይባላል። አባ ተስፋጽዮን በነሓሴ 28 ቀን 1550 ዓ ም በ42 ዓመት ዕድሜአቸው፣ ወደ ሮም በሄዱ በ12 ዓመት፣ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
የቅዱስ ኢስጢፋኖስ ገዳም
በቫቲካን የኢትዮጵያውን ገዳም አስተዋጽኦ
አባ ተስፋጽዮንና ሌሎች በቅዱስ ኢስጢፋኖስ ይኖሩ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን መነኵሴዎች ብዙዎቹ ከፍ ያለ እውቀት እንደነበራቸውና ኢትዮጵያና ቋንቋዋ በአውሮጳውያን ዘንድ እንዲታወቁ ብዙ አስተዋጽኦ አድርገዋል ፡፡ በዚያን ጊዜ ብዙ የአውሮጳ ሊቃውንት በራሳቸው ፍላጎት ሆነ በመንግስታቸው ተልከው ወደ ገዳማውያኑ እየሄዱ ስለ ኢትዮጵያ ሰፊ ጥናት ያደርጉ ነበር። በየጊዜው ርእሰ–ሊቃነ ጳጳሳትና ሌሎች ባለ–ስልጣናት መኖክሴዎቹን ወደ ቤቶቻቸው እየጠሩ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ሃይማኖትና ባህል ይጠይቋቸውና ከነሱ ብዙ እውቀት ይቀስሙ ነበር። ስለዚህ ስለ ኢትዮጵያ ጥናት በመላው አውሮጳ ሊዘረጋ የቻለው በዚሁ ገዳም በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መነኩሴዎች አማካይነት ነበር። ይሁን እንጂ እነሱ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በሰፊው መዘርዘር የዚህ አጭር ጽሑፍ ዓላማ ስላልሆነ አጫጭር ነጥቦችን ጠቀስ አድርጌ አልፈዋለሁ፡፡
የኢትዮጵያ ቋንቋ ጥናት በአውሮጳ በቅዱስ ኢስጢፋኖስ ገዳም እንደተጀመረ ከሁሉ በፊት የገለጸ ጆሓንስ ፖትከን የተባለ የጀርመን ምሁር ነበረ። እሱ የግዕዝ ቋንቋ የተማረው በሮም የፖፕ ጸሓፊ በነበረበት ጊዜ አባ ቶማስ ወልደ ሳሙኤል ከተባለ የኢየሩሳሌም ነዋሪና በሮም የፖፕ ለኦ ፲ኛ እንግዳ ከነበረ ኢትዮጵያዊ ነበር። ጆሓንስ ፖትከን በግዕዝ ቋንቋ ፊደልን ቀርጾ ለመጀመርያ ጊዜ በግዕዝ ቋንቋና ፊደል የዳዊት መጽሓፍ (መዝሙር ዘዳዊት) በሰኔ/ሓምሌ 1513 ዓ ም አሳተመ።
አባ ተስፋጽዮን ያስተማሩት ማርዮ ቪቶርዮ የተባለ ኢጣልያናዊ የኢትዮጵያን ነገሥታት ስም ዝርዝር የያዘ መጽሐፍና አንድ ትንሽ የግዕዝ ሰዋስው ለመጀመርያ ጊዜ አሳተመ።
በቅዱስ ኢስጢፋኖስ ገዳም ከተማሩት አንዱ ያዕቆብ ወመርስ የሚባል ዶመኒካዊ የግዕዝና የላቲን መዝገበ ቃላት ለመጀመርያ ጊዜ ጻፈ። ቴዶር ፒተር የሚባል የዴንማርክ ተወላጅም ብዙ የኢትዮጵያ መጻሕፍት እንዳሳተመ ይነገራል።
ኢዮብ ሉዶልፍ የሚባል የጀርመን ተወላጅ ወደ ቅዱስ ኢስጢፋኖስ ገዳም እየተመላለሰ አባ ጎርጎርዮስ ከሚባሉ ኢትዮጵያዊ መነኵሴ ተምሮ በብዛት የግዕዝ ሰነዶች የሚገኝበት በላቲን ቋንቋ የተጻፈ የኢትዮጵያ ታሪክ የሚል መጽሐፍ አሳተመ፡፡
የኢትዮጵያውያን ማረፊያ ወደ ኢትዮጵያውያን ኮሌጅ ተለወጠ
በአጼ ሱስኒዮስ ዘመነ–መንግሥት በኢየሱሳውያንና በኢትዮጵያውያን መካከል የተፈጠረው የሃይማኖት ክርክርና ጠብ በቅዱስ እስጢፋኖስ ገዳም ላይም ችግር ፈጠረ። በዚህ ምክንያት ወደ ሮም ይሄዱ የነበሩ ኢትዮጵያውያን መነኵሴዎቸ ቁጥር እየቀነሰ ሄደ፤ ቀስ በቀስም አቋረጠ። ይሁን እንጂ የሮም ርእሰ–ሊቃነ ጳጳሳት ለዚህ ገዳም ትልቅ ግምት ይሰጡ ስለነበረና ገዳሙ አንድ ቀን እንደገና በኢትዮጵያውያን መነኵሴዎች እንዲያዝ ተስፋ ስለነበራቸው ጠንቅቆ የሚይዘው ኃላፊ እየሾሙበት ቆይቷል። በዚህን ጊዜ በገዳሙ መነኵሴዎች እንዳልነበሩ ስላወቁ ከ1727 ዓ ም ጀምረው ግብጻውያን ይህን ገዳም ለመውረስ የተቻላቸውን ሁሉ አደረጉ። ለጊዜው ተሳካላቸው፥ ስለዚህ ለተወሰነ ጊዜ ገዳሙ በግብጻውያን እጅ ገብቶ ነበር። ግብጻውያን ብዙ መነኵሴዎች ካገራቸው በማስመጣትና በስፍራው ብዙ ሰው በማስፈር ገዳሙን ለሁልጊዜ ለመያዝ ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም። በ1815 ዓ ም የሃይማኖት አስፋፊ ማህበር (ፕርፓጋንዳ ፊደ) ካቶሊካዊት ሃይማኖት በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ ስላሰበ ከካፑቺን ማህበር ጋር በመነጋገር በነሱ አማካይነት አንድ በችሎታው የታወቀ ጊዮርጊስ ገለበዳ የተባለ ኢትዮጵያዊ ወጣት በ1816 ዓም ወደ ሮም እንዲመጣ ተደረገ። እነሱም ወጣቱ ሮም እንደደረሰ ቶሎ ብለው ኡርባን በተባለ የዘርአ–ክህነት ኮሌጅ እንዲገባ አደረጉት። እርሱም ክህነት እንደተቀበለ የቅዱስ ኢስጢፋኖስ ገዳም አስተዳዳሪነት እንዲሰጠው ጠይቆ ስለተሳካለት የገዳሙን ያስተዳዳር ስልጣን ያዘ። አባ ጊዮርጊስ ከአለቆቹ ጋር በመተባበር ገዳሙን አሳድሶ በ1820 ዓ ም ኢትዮጵያውያን ወደ ቅዱስ ኢስጢፋኖስ ገዳም እንዲመጡ ጥያቄ አቀረበ። ይሁን እንጂ እምበዛም አልተሳካለትም።
በ1855 ዓ ም ደብተራ ክፍለጊዮርጊስ የተባሉ ወደ ሮም ሂደው በቅዱስ ኢስጢፋኖስ ገዳም ለ10 ዓመት ተቀመጡ። ደብተራው በጣም ሊቅ ነበሩ ይባላል። እርሳቸው በሮም በተቀመጡበት ጊዜ እንደነ ኢግናዚኦ ጉኢዲ እና ሉደቪኮ ደቪቶና የመሳሰሉ ምሁራን የኢትዮጵያን ቋንቋ ለማጠናቀቅ ወደርሳቸው እየሄዱ ይማሩ ነበር። ደብተራ ክፍለጊዮርጊስ ሮምን ትተው ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱና እዛ 1908 ዓ ም ላይ ሞቱ። ከርሳቸው በኋላ የቅዱስ ኢስጢፋኖስ ገዳም እንደገና ያለ ኢትዮጵያውያን ቀረ። ስለዚህም የተለያዩ አቋማት ቦታውን ለመያዝ ተራወጡ። አባ ሉደቪኮ ደኮሳርዮ የተባለ መነኵሴ የቅዱስ ኢስጢፋኖስን ገዳም የዓይነ–ስዉራንና የዲዳዎች ት/ቤት ለማድረግ ፕዮስ ፱ኛን ጠይቆ ሳይሳካለት ቀረ። ከዚህ በኋላ በ1883 ዓ ም የቅድስት ሥላሴ ማህበር አለቃ የማህበራቸው ት/ቤት እንዲሆንላቸው ፈቃድ አግኝተው ገቡበት። በ1916 ዓ ም ገብረማርያም ዓምደሚካኤል የተባለ ወጣት ለትምህርት ወደ ሮም ሄደና በካፑችን መነኵሴዎች አማካይነት በቅዱስ ኢስጢፋኖስ ገዳም የነበሩት የቅድስት ሥላሴ ማሕበር መነኵሴዎች እንዲቀበሉት ተደረገ። ከዚያ በኋላ አንድ ለኢትዮጵያውያን የሚሆን ኮሌጅ በሮም እንዲሰራ ስለታሰበ የካፑችን መነኵሴዎች የቅዱስ ኢስጢፋኖስ ገዳም በብዙ ምክንያት ለኢትዮጵያውያን የተገባ ሆኖ ስለታያቸው አባ ካሚሎ በካሪ የተባሉ አንድ ኢየሱሳዊ ካህን ሓላፊነት ውስደው ወደ ፖፑ ጥያቄ እንዲያቀርቡ ተደረገ። አባ ካሚሎ ለምን ቦታው ለኢትዮጵያውያን እንደሚገባ ግልጽ አድርገው ለርእሰ–ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ ፲፭ኛ አቀረቡ። ፖፑ የቅድስት ሥላሴ ማህበር ቦታውን ለኢትዮጵያውያን ትተው እንዲወጡና በቦታው የኢትዮጵያውያን ኮሌጅ እንዲሰራ አስፈላጊው ዝግጅት እንዲደረግ ትእዛዝ ሰጡ። በዚህ መልክ በቫቲካን ከተማ ውስጥ የኢትዮጵያውያን ኮሌጅ ተሰርቶ “ጳጳሳዊ የኢትዮጵያውያ ኮሌጅ” ተባለ።
ስለዚህ ወደ ኮሌጁ ለመግባት በሰላሳ ነሓሴ 1919 ዓ. ም. ስምንት ኢትዮጵያውያን ከነፍስ–አባታቸው አባ ተክለማርያም ካሕሳይ ጋር ሮም ገቡ። እነዚህ የመጀመርያ ተማሪዎች ከፍተኛ ትምሀርት ለመቀጠል ወደ ቫቲካን የተላኩት ከዓሊተና (ኢሮብ) ልደታ–ለማርያም ትምህርት–ቤት እና ከከረን ነበር። የተማሪዎቹ መኖርያ ለጤና የማይመች ስለነበረ ከነዚህ የኮሌጁ የመጀመርያ ተማሪዎች አንዳንዶቹ እዛው ታመው ሞትዋል፤ ሌሎቹ ደግሞ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። ከነዚህ ተማሪዎች ሓጎስ ፍሱሕ አሞዓስ የተባሉ የኢሮብ ተወላጅ ብቻ ትምህርቱን እስከ ዶክቶራል ዲግሪ ቀጥለው ክህነት ተቀበሉ። ዶክቶር አባ ሓጎስ ትምህርታቸውን ከጨረሹ በኋላ ወደ አገራቸው ተመልሰው በደሴ ጥቂት ዓመቶቸ አገራቸውን በማገልገል ላይ እያሉ በለጋ ዕድሜአቸው በድንገት አረፉ። ከነዚህ ከዓሊተና ከተላኩት ተማሪዎች አንደኛው በ1950 ዓ ም የመላዋ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ የግዕዝ ስርዓት ካቶሊካዊ ጳጳስ ሆነው የተሾሙት አቡነ ኃይለማርያም ካሕሳይ ነበሩ። አቡነ ኃይለማርያም ካሕሳይ ከ1950 እስከ 1961 ዓ. ም. ድረስ የመላ ኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ሊቀ ጳጳስ ሆነው በአዲስ አበባ አገለገሉ። ከ1961 እስከ መጨረሻ ድረስ ደግሞ የዓዲግራት ሃገረ–ስብከት ጳጳስ ሆነው አገልግለዋል።
ከበነዲክቶስ ፲፭ኛ ቀጥለው የሮም ፖፕ የሆኑት ፕዮስ ፲፩ኛ የቀድሞ ኮሌጅ የተሰራበት ቦታ ለተማሪዎች ጤና የማይመች ስለነበር በ1928 ዓ ም ትንሽ ራቅ ባለ ቦታ በቫቲካን አትክልት መካከል አዲስ ትልቅ ኮሌጅ አሰሩ። ፖፕ ፕዮስ የአዲሱን የኢትዮጵያ ኮሌጅ መሰረት–ድንጋይ የጣሉት የልደታቸውን በዓል ምክንያት በማድረግ ነበር። ርእሰ–ሊቃነ ጳጳሱ በዚህ አጋጣሚ ባደረጉት ንግግር አሮጌው ቤት ከመጠን በላይ ተበላሽቶ እንደነበረና ለዓላማው የማይመች እንደነበረ ከገለጹ በኋል “መልካም መስሎ የሚታየን መልካም ሐሳባችንና ፍቅራችን እጅግ በጣም ክቡር ለሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ መግለጫ የሚሆን እኛ አጠገብ በቫቲካን መንግሥት ውስጥ አዲስ መኖርያ የኢትዮጵያ ኮሌጅ ማሰራት ነው … በሓዋርያዊ ስልጣናችን በቫቲካን ግቢ ውስጥ የኢትዮጵያ ዘርኣ ክህነት ኮሌጅ እናቆማለን” ብለዋል። በበዓሉ ሥነ ሥርዓት አከባበር አስራ አንድ ካርዲናሎችና ሌሎች የቤተክህነትና ዓለማውያን ባለስልጣኖች ተገኝተው ነበር።
በ11 የካቲት 1929 ዓ ም በቫቲካንና በጣልያን መንግስት መካከል “የላተራን ውል” የተባለ ስምምነት ተደረገ። በዚህ ውል መሰረት ቫቲካን ራሱን የቻለ ሉዓላዊ መንግሥት ሆነ። ይህ ስምምነት በተደረገበት ዓመት በቫቲካን ግቢ ውስጥ ይገኙ የነበሩት የዘርኣ–ክህነት ኮሌጆች እንዲሁም መነኵሳትና የመነኵሳት ማህበሮች ሳይቀር ቫቲካንን እንዲለቁ ተወሰነ። ይህ ሁሉ ሲተገበር የኢትዮጵያውያን ኮሌጅ ብቻ በቫቲካን ግቢ ውስጥ እንዲቀር ተደረገ። ይህንን አንዳንድ ካርድናሎች አልደገፉትም ነበር፣ በተለይ ደግሞ በሙሶሊኒ በሚመራ በጣልያን መንግስት በኩል ብርቱ ተቃውሞ ነበር፤ ይሁን እንጂ ፖፕ ፒዮስ ፲፩ኛ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን በጣም ይወዱ ስለነበር በላተራን ውል መሰረት ሌሎች ኮሌጆች በሙሉ ከቫቲካን ሲወጡ የላተራን ውል በሚያፈርስ መልክ የኢትዮጵያ ኮሌጅ ብቻ ቫቲካን ውስጥ እንዲቀር ወሰኑ።
ጣልያን ኢትዯጵያን በወረረበት ጊዜ በዚህ ኮሌጅ በነበሩ ተማሪዎች ላይ በፋሺስቶች ጉዳት እንዳይደርስ ፕዮስ ፲፩ኛ ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸው አድርገዋል። በነገራችንላይ ፕዮስ ፲፩ኛ የጣልያን ወታደሮች ኢትዮጵያን ለመውረር ሲሄዱ ባርከው ሸኙዋቸው ተብሎ የሚወራው የተሳሳተ ብሂል ነው። በአንዳንድ ስእሎች ላይ ለመባረክ እጁን ዘርግቶ የሚታየው የቄስ ልብስ የለበሰ ሰው እርሳቸው አይደሉም።
ይህ ከፍ ያለ ክብርና ታሪክ ያላት ብቸኛ አንዲት ኮሌጅ በቫቲካን ውስጥ መኖር ለኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ ክብር ነው። ስለዚህም የኢትዮጵያ ታላላቅ ሰዎችና ባለስልጣናት ወደ አውሮጳ ሲሄዱ ይህችን ኮሌጅ ሳይጎበኙ አያልፉም ነበር። ለምሳሌ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለት ጊዜ፣ አልጋውራሽ እያሉ በ1924 እና ንጉሠ–ነገሥት እያሉ በ1970 ዓ ም ፥ ልዕልት ተናኘ ወርቅና ልዑል አስፋ ወሰን በ1932 ዓ. ም. እንዲሁም በቅርቡ ዶክተር ዐቢይ አህመድ በ2019 ዓ. ም. ወዘተ. ይገኛሉ።
ይህ ኮሌጅ ለኢትዮጵያውያንና ለኢትዮጵያ ብዙ ደጋግ ነገሮች ያስገኘ ኮሌጅ ነው። ይህ ትምህርት ቤት የተሰራው የሃይማኖት መሪዎች ለማፍራት ነበር፣ ሆኖም በጣም ብዙ የሃይማኖት መሪዎች ከማፍራቱ በተጨማሪ እጅግ በጣም ብዙ ካህናት ያልሆኑ ኢትዮጵያን በልዩ ልዩ ሞያ ያገለገሉ ምሁራንንም አፍርቷል። ባለፉት መቶ ዓመታት ብዙ ከዚህ ኮሌጅ ተምረው የወጡ ምሁራን ለኢትዮጵያና ለኤርትራ በርካታ ጥቅም አበርክትዋል፤ ሆኖም በዚህ አጭር ጽሑፍ ውስጥ ስለነሱ ለመጻፍ አልሞክርም፤ ይሁን እንጂ እዛ ተምረው ትልቅ ደረጃ የደረሱና ትልቅ አስተዋጽኦ ካበረከቱና አሁን በህይወት ከሌሉ የሃይማኖት መሪዎች የተወሰኑትን ለምሳሌ ያህል ለመጥቀስ ፤ አቡነ ኃይለማርያም ካሕሣይ፣ ካርዲናል ጳውሎስ ፃድዋ፣ አቡነ ኣብርሃ ፍራንስዋ፣ አቡነ ስብሓትለኣብ ወርቁ፣ አቡነ ዮሓንስ ወልደጊዮርጊስ፣ አቡነ ኪዳነማርያም ተክለሃይማኖት፣ አቡነ ተስፋማርያም ብድሆ፣ ዶክቶር አባ ወልደማርያም ካሕሣይ፣ ዶክተር አባ ተወልደመድህን ዮሴፍ፣ አባ ገብረሚካኤል መኵንን፣ አባ ሥዩም ተድላ፣ አባ ኪዳነማርያም ገብራይ፣ አባ ገብረማርያም አመንቴ ወዘተ፡፡ እነዚህ ብዙ ቁምነገር ከሠሩ የሃይማኖት መሪዎቸ በጣም የተወሰኑት መሆናቸው ሊሠመርበት ይገባል።
ማስገንዘቢያ–
- በጣልያን ቋንቋ የ’ኮለጆ’ ትክክለኛ ትርጉም በከፍተኛ ትምህርት ቤት (ኮሌጅና ዩንቨርሲቲ) የሚማሩ ተማሪዎች መኖርያ ማለት ነው እንጂ የትምህርት ተቋሙ አይደለም። ስለዚህ በእንግሊዝ ቋንቋ ኮሌጅ ከሚባለው ጋር እኩል አይደለም። በ Collegio Etiopico የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ትምህርት የሚማሩት ወደ ተለያዩ በሮም ከተማ በሚገኙ ዩንቨርሲቲዎች እየሄዱ ነው።
- የዚህ ጽሑፍ ጸሓፊ የመጀመርያና የሁለትኛ ደረጃ ዲግሪዎች እስካጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ የተማረው በዚሁ ኮሌጅ እየኖረ ነበር። ስለዚህ ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ የተጠቀመው ከሁሉም በላይ ያኔ የኮሌጁን ታሪክ ለማወቅ በማንበብና በመጠየቅ ባገኘው መረጃ፣ እንዲሁም ያኔ በጻፋቸው የግል ማስታወሻዎች ነው። እንደ ተጨማሪ ምንጭ የተጠቀመው ደግሞ ኮሌጁ የተሰራበት 50ኛ ዓመት/ወርቃዊ ኢዮቤል በተከበረበት ጊዜ የኮሌጁ ምክትል አለቃ የነበሩ አባ ኣድሓኖም ስእሉ የተባሉ ካህን ካደረጉት ንግግር የወሰዳቸው ማስታወሻ ነጥቦችን ነው። በዚህ ጽሑፍ ስማቸው የተጠቀሱ ርእሰ-ሊቃነ ጳጳሳት (ፖፖች) የነበሩበትን ዘመን ለማረጋገጥ እንዲሁም ሌሎች ታዋቂ ግለ-ሰቦችን በሚመለከት የጉግል (Google) ፍለጋ ተጠቅሟል።
- በዚህ ጽሑፍ የተጠቀምነው የዘመን አቆጣጠር የአውሮጳውያንን አቊጣጠር ነው።
ተጨማሪ ምንባብ
Collegio Etiopico, Da Wikipedia, l’enciclopedia libera (From Wikipedia, the free encyclopedia)
St. Stephan Thomas of the Abyssinians: The churches of Ethiopia in Rome, Ethiopian Herald, Jan 2019.
Taste of Africa in the midst of the Vatican , Rome Reports.