እንደመቅድም የፖለቲካ ጽንሰ-ሃሳብ ትንታኔ፤
ደስታ ተክለወልድ በአማርኛ መዝገበ ቃላት መድብላቸው ፖለቲካን እንዲህ ይተረጉሙታል፤
“ቦለቲክ (ፖለቲክ) የነገር ዘዴ፤ ውስጠ ተንኮል፤ ፈሊጥ።
በግዕዝ፤ ጉሕሉት፥ ኂጣን ሚን ይባላል። (ላዩ ዳባ፤ ውስጡ ደባ)
ድለላ፥ ሽንገላ ማለት ነው፥” ይላሉ።
ቦለቲከኛ ለሚለው ቃል የሰጡት ትርጉም ደግሞ፥ “ዘዴኛ፥ ባለፈሊጥ፥ አዋቂ፥ በነገር ተራቃቂ፥” ብለው ተርጉመውታል።
የግዕዙን ቃል፥ “ጉሕሊ” የሚለውን ከነእርባታው ስንመለከት ሊቁ ደስታ ተክለ ወልድ ፖለቲካን የሚመለከቱት፥ “ጉሕሊት”
በሚለው ቃል አኳያ መሆኑን እንረዳለን።
“ጉሕሊ፦ ክፉ አድራጊ፤ ሌባ፥ ቀጣፊ፤
ጉሕሉት፦ ማታለል፥ ልብለባ፥ ክዳት፥ ተንኰል፥ ሰይጣናዊ ባሕል።1
ከዚህ ላይ የምንገነዘበው በሊቁ ደስታ ተክለወልድና በርሳቸው ትውልድ ዘመን ሊቃውንት ፖለቲካን እንደ ሰይጣናዊ ግብር አድርገው ይመለከቱት እንደነበር ነው።
ሌላ ማስረጃ ስፈልግ አባ ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር ያቀነባበሩትን መዝገበ ቃላት አገላብጨ የሚከተለውን ፍሬ ነገር አገኘሁ።
ፖለቲክ፦ በአዎንታዊ መልኩ ሲተረጉሙ፥ “…የማለፊያ ወይም የጥሩ አገዛዝ ችሎታ ዘዴ፤ የአስተዳደር ሥልጣኔ ሥራና ዕውቀት የሆነ ፈሊጥ ነው፥” ብለውታል።
በአሉታዊ መልኩ ሲተረጉሙ ደግሞ፥
“—በውስጡ ልግም እንደያዘ ቁስል ሆኖ በልብ የታባውን ሁሉ ሳይገልጽ ወይም እንዳይገልጽ በመሸፈኛ ፈሊጥ ለማሳመን፤…. የሰውን መንፈስ ለመማርክ የሚያስችል ዕውቀት፤… ዘወትር ሐሳቡን ሸሽጎ ሳይቆጣ፥ የግልፍተኝነት ባሕርይን ሳያሳይ… የጥቅምን ጉዳይ የማስፈጸሚያ ዕውቀት፤ ….ማደናገሪያ፤ ማሳሳቻ፥ ማታለያ፥ የብልጠት ዘዴ፤…
እውነት በሐሰት፤ ሐሰትን በውነት ለውጦ ዓለምን ለማሳመን የሚያስችል መሣሪያ፤… እስከ ጦርነት ማስነሳት የሚችል፤ … ከጥንት በባሕርያችን ያለ ነው። ኢትዮጵያውውያን በተለይ በባሕርያቸውና በጠባይ ሁሉ ፖለቲከኞች ናቸው፥” ብለው ይደመድማሉ።2
ግራውች ማርክስ የተባለ ታዋቂ አሜሪካዊ (በሬድዮ፥ በቴሌቭዥን ሥራው፥ በአስቂኝ ቧልቶች የሚታወቅ) ስለፖለቲካ ያቀረበው ቀልድ እንዲህ የሚል ነበር። “ፖለቲካ ችግሮችን የመፈለጊያ፥ ሁሉም ቦታ ችግሮች መኖራቸውን ማወቂያ፣ ችግሮችን አሳስቶ መገምገሚያና የተሣሣተ መፍትሔ ማቅረቢያ ዘዴ ነው::”
ላይ በተጠቀሱት ሰዎች አኳያ ፖለቲካ የተሰጠው ክብር ዝቅተኛ ነው። ሰው በሰው ላይ ብልጠትን በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቀምበት መሣሪያ ሆኖ ቀርቧል። ሰው የሚፋቀርበት ወይም ፍቅሩን የሚገልጽበት መድረክ ሳይሆን፥ ሰው ለሰው የሚጠላላበት፥ የሚነታረክበት ብሎም የሚጨራረስበት ዘዴ ሆኖ መታየቱ በነዚህ ላይ በተጠቀሱት ሊቃውንት ብቻ ሳይሆን አሁን ዘመን በየትም ሃገር የፖለቲካ ሚና እንደፀያፍ መታየቱ በየዕለቱ የምናየውና የምንሰማው ነው። መጀመሪያውኑ ፖለቲካ እንደ ከተማ አስተዳደር ስልት በግሪክ ሃገር ሲጠነሰስ አላማው በጎ ነበር። እያደር ግን የፖለቲካ አስተሳሰብ እየተራቀቀ ሲመጣ፥ በተለይም በከፍተኛ የትምህርት ተቋሞች ለትምህርት ሲውል እንደ ማኪያቤሊ አይነት ልሂቃንን እየወለደ መጣ። ሰዎችን ለመግዛት ከፋፍላቸው የሚለው መርህ በግብር ላይ ሲውል ታየ። ስለዚህም፥ “ላዩ ዳባ፥ ውስጡ ደባ” የሆነ የፖለቲካ ሥልት ቀስ በቀስ፥ “የመደብ ልዩነት” ጽንሰ-ሃሳቦችን እየፈጠረ ድሃና ሃብታምን ፈርጆ የሚያታግልና የሚያጫርስ እየሆነ ሄደ። በኢትዮጵያችን በኩል ሲታይ አምላክ በተለያየ ዝንጉርጉር ባህልና መልክ አስውቦ በሰጠን የነገድ/የብሔር ማንነት ጥያቄ ሳቢያ ብጥብጥና ፍጅት የሚጭር ፖለቲካ ሲሰለጥን ታይቷል።
ጥንት የቤተክርስቲያን ትምህርት የበላይነት ነበረው። የተለያዩ ፈላስፎች እየተነሡ የቤተክርስቲያንንና የአገልጋይ ካህናቱን የበላይነት የሚገለብጥ ሃሳብ መዘየድ ጀመሩ። ስለዚህ ፖለቲካ ሆነ ፍልስፍና ከነገረ መለኮት ጋር ተያይዘው እንደ ትምህርት የሚሠጡበት ዘመን አብቅቶ ራሳቸውን ችለው የሃሳብ ማፍለቂያ መሆን ጀመሩ። ዩኒቨርቲሲዎች ከቤተ እግዚአብሔር ጉያ ወጥተው ነጻነታቸውን አወጁ፤ አብዮት ተካሄደ። ሃሳብን ከነገረ መለኮት ውጪ በነጻ የማፍለቅና የመተግበር አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ። ይህ አዲስ ዘመን የልብን ከፍተኛ ዕውቀት ገልብጦ የአእምሮን ዕውቀት የበላይነት አስረገጠ። ከዚህ በኋላ በቴክኖሎጂ እድገት እየታጀበ የሚገሰግሰው የሰው ልጅ ነጻ አስተሳሰብ ውሎ አድሮ መልካም ፍሬ ያፈራል በሚል ተስፋ ቀጥሎ እስከ ዘመናችን የደረሰውን ማህበራዊ ኪሳራ፥ ሰብዓዊ መጨናነቅ እና የመንፈሳዊነት መንኰታኮትን አስከተለ።
የሰው ልጅ መንፈሳዊነት የጎደለው ህይወት የወደቁትንና የሞቱትን እኩይ መናፍስት መምሰል የጀመረው ከነገረ መለኰት ትምህርት ማዶ የፈጠረው አብዮታዊ/ሥር -ነቀል የትምህርት ሥርዓት ሥር በሰደደ ጊዜ ነው። የሰው ልጅ እራሱን ከእግዚአብሔር ትእዛዛት ተፅዕኖ ነጻ አውጥቻለሁ ባለበት ጊዜ በምትኩ የተዘረጋው የእኩይ መናፍስት (ሉሲፈራዊ) ዝባዝንኬ ትምህርት ነው። የሰው ልጅ እግዜር የሰጠው ነፃ ፈቃድ በሉሲፈራዊ መሠሪ ተግባር ተጠልፎ፥ “ላዩ ዳባ፥ ውስጡ ደባ” ብለው አበው በመሠጠሩት አኳያ እያየነው ያለውን ወደ ሞት በሚወስድ የውሸት “ነጻነት” ተተካ። ይህ ተግባር እንደ አዲስ ሥር- ነቀል እርምጃ ስለታየ “አብዮታዊ”፤ “ብርሃናዊ” እየተባለ በየመጽሐፉ ይለፈፍ ጀመር። መሥራቾችና የሃሳቡ አቀንቃኞች ታዋቂ ተብለው ስማቸው በወርቅ ቀለም ተጻፈ። የፖለቲካ ሊቃውንት ሃሳባቸውን ከሥነ መለኰት እየሠረቁ አዲስ ዓለማዊ ትርጉም በማጎናጸፍ ማራቀቃቸው እፁብ ድንቅ ተባለ። ተሸለሙ፤ ከበሩበት፥ ተከበሩበት። ይህ ሁሉ ድንቅ የሚመስለው የሰው ልጆች ተግባር መነሻው ሉሲፈር፤ መደምደሚያውም ሉሲፈር ነው። በእብሪቱ ከክብሩ የተወገደው ሉሲፈር የሰውን ልጅ ክብር እንደራሱ ወደአዘቅት ለማስገባት ሌት ተቀን መሥራት የጀመረው ገና ጥንት ነው።
በሥላሴ አምሳል የተፈጠረውን ፍቅር የሆነውን የሰው ፍጡር ለማዋረድና እንደራሱ ኪሣራ ውስጥ ለማስገባት ቅናቱን ቀና በማስመሰል እያታለለ የሰው ልጆችን የሚያጠምድባቸው ዘዴዎች ብዙ ናቸው። በዘፈን፥ በገንዘብ፥ በዝና፥ በንብረት፥ ከሚያደርገው ጥረት ሌላ የሰው ልጆች በሥነ መለኮት ተመሥርተው ያቋቋሟቸውን ተቋማት ሠርስሮ በመግባት የተቀደሰ ዓላማቸውን አስረስቶ በማዘናጋት ከትውልዶች በኋላ ቀልብሶ ሰይጣናዊ መሥመር ያስይዛቸዋል። ፖለቲካም የደረሰበት ኪሳራ ይኸው ነው። በዚህ መሠሪ ተግባሩ በሰው ልጆች ዘንድ፥ “ጉልሑት” የሆነውን ሰይጣናዊ ባህል አስፋፍቶ በየመዓልቱ እንደ “እውነት”እንዲሠራባቸው በዘረጋቸው ሉሲፈራዊ ተቋማት መረቦች ከዓለም ጫፍ እንደ ዓለም ዳርቻ እንዲሠራባቸው አድርጓል። የዚህ ውጤት አሁን ባለንበት ዘመን ክርስቶሳዊ የሚመስሉ አያሌ የተኮረጁ፥ መተክሎች ለሰው ልጅ መማሪያ ሆነው እናገኛቸዋለን። የኢሉሚናቲ ምሥጢራዊ ድርጅትና መሰል ድርጅቶቹን ማየት በቂ ነው። ወንድን ከወንድ፥ ሴትን ከሴት ማጋባት የዚህ ሉሲፈራዊ አሠራር ቁንጮው ነው። ይህ ደግሞ ተቃውሞ እንዳይነሳበት በየሃገራት ህግ እንዲፀድቅ ተደንግጓል።
የመንፈሳዊ ፖለቲካ ጽንሰ-ሃሳብ፤
መንፈሳዊ ፖለቲካ በዓለም ላይ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ሉሲፈራዊ የፖለቲካ ሥርዓት መዋቅሩን ሰባብሮ የሰው ልጅ ታስሮ ከተያዘበት የባርነት ሰንሰለት ነጥቆ ለማውጣት የሚጥር ጊዜያዊ መሸጋገሪያ ድልድይ ነው። ፖለቲካ ለሰው ልጆች መልካም አገልግሎት ተወጥኖ በሚያገለግልበት ጊዜ ተጠልፎ ለሉሲፈራዊ አገልግሎት እንዲውል ሉሲፈርና መንጋዎቹ ለዘመናቱ በሸረቡት ሤራ ክርስቶሳዊ ይዘቱን እንዲለቅ ስለተደረገ፥ መንፈሳዊ ፖለቲካ የሉሲፈርን እኩይ የፖለቲካ አሰራር በማፈራረስ የሰው ልጅ ክርስቶሳዊ ልጅነቱ እንዲመለስለት የሚጥር መሣሪያ ነው። በተጨማሪም በዘመን መጨረሻ ላይ የእግዚአብሔር መንግሥት በምድር ላይ እንዲመጣ መንፈሳዊ ፖለቲካ አስፈላጊውን መሰናዶ ለማድረግ ሁኔታውን ያመቻቻል። የእግዚአብሔር ክብር በመሬት ላይ ይገለጥ ዘንድ የእግዜር ፈቃድ በሰማይ እንደሰፈነ ሁሉ በምድራችንም ላይ እንዲሰፍን ተገቢውን መንፈሳዊ እርምጃ ለመውሰድ መንፈሳዊ ፖለቲካ ይፈጽማል፤ ያስፈጽማል። የሰው ፍጥረት ፍቅር ከሆነው አምላክ በአርአያውና በአምሳሉ የተፈጠረበት ፍቅርነቱ በሉሲፈርና በጭፍሮቹ ያላቋረጠ ጥረት እየደበዘዘና እየጠፋ ሂዶ ሰውና ሰይጣን አንድ ሆነ በሚያስብል ደረጃ በዝቅተኝነት በሚገኝበት ባሁኑ ጊዜ፣ ዋናውን ጠላት ከሰዎች ላይ በማስወገድ ወደቀደመውና አናስራዊ ፍቅርነታቸው እንዲመለሱ ለማስቻል መንፈሳዊ ትምህርት እንዲያንሰራራ፥ የክርስቶስ የማዳን መልካም ዜና በሰዎች ዘንድ ሥራውን ያለእንቅፋት እንዲሠራ፣ ወንጌል ከዓለም ዳር እስከ ዓለም ዳር እንዲሰበክ፣ ነቢያትና አገልጋዮች እንዲነሱና ቦታቸውን እንዲያዙ ያስችላል። ጦርነትና ሰላም ማጣት፥ መጋደልና መራከስ ካሁን በኋላ በሰዎች መካከል እንዳይሆን እግዚአብሔር ወደመደበላቸው መሠረታዊ ክብር እንዲገቡ በመንፈሳዊነት የሚመራ ፖለቲካ ነፃ ፈቃዳቸው እንዲከበር፣ ከሰው ሰራሽ የፖለቲካ እሳቤዎችና ንድፈ ሐሳቦች እንዲጠበቁ የእግዚአብሔርን ቃል ጋሻ በማድረግ ጥረት ያደርጋል።
ሰኔ ወር 2010 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ምድር የሚካሄደው የለውጥ ነፋስ አዲስና አስገራሚ ነው። በእግዚአብሔር ማመን ተስፋ አስቆርጧቸው የነበሩ ሁሉ ተገርመው የዶክተር አቢይ አህመድ አሊ በፖለቲካው መስክ መነሳት ላይ “የእግዚአብሔር እጅ አለበት” እስኪሉ ድረስ ሁኔታው ማራኪ ሆኖ ይገኛል። በምዕራቡና በምሥራቁ ዓለም የፖለቲካ ንድፈ-ሃሳቦችና ጽንሰ-ሃሳቦች የተራቀቁ ኢትዮጵያውያን ምሁራን በሁኔታው በመደመም የሚሉት አጥተው ዝምታን የመረጡበት ጊዜ ነው። አንዳንድ ዜጎች ደግሞ ይህ ክስተት ጊዜያዊ ቅዠት እንጂ እውን አይደለም በማለት ያላቸውን ግራሞት ይገልጻሉ። እኔ በበኩሌ በዶክተር አህመድ አሊ የሚመራው አዲሱ ፖለቲካ ሲጠበቅ የነበረው የእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት ያስከተለው መሆኑን አምናለሁ። ይህ እምነቴ ደግሞ ይህን መጣጥፍ እንድጽፍ ምክንያት ሆኖኛል።
የመንስፈሳዊ ፖለቲካን ጽንሰ-ሃሳብ በልቤ የመነጨው በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ ነበር። ይኽውም እኔ ከትግል ዓለም እርቄ በሩቅ ሃገር ሰላማዊ በሆነ አካባቢ መኖር ስጀምር ከኋላየ ጥየው የመጣሁት፤ የታገልኩለት ህዝብ ግን ከጦርነት ወደከፋ ጦርነት፤ ከሰላም ማጣት ወደባሰ ሰላም እጦት እየተሸጋገረ ኑሮውን እንዲገፋ የሆነበት ሁኔታ በመቀጠሉ ካለማመን ወደባህታዊነት ኑሮ ወደመናፈቅ ህሊናየ እየተወነጨፈ በሚያስቸግረኝ ጊዜ፤ ባገኘሁት አንፃራዊ ሰለምና መረጋጋት ተጠቅሜ ስለሃገሬ ሁኔታ ሃሳቦችን ሳሰላስል የመጣልኝ ሃሳብ ነበር። በማርክሳዊ የክህደት አስተሳሰብ የጎለበተው አእምሮየ የተወረወረውን ድንጋይ ኢላማውን ስላልመታ ድንጋዩ ከወደቀበት እርቀት አንስቸ ወደኢላማው እንድወረውረው የማላውቅበትን ግጥም ሁሉ መጻፍ ደረጃ ደርሸ ነበር። ጥሪዬ አብረን የጀመርነው ትግል ግቡን ስላልመታ፣ እባካችሁ የምዕራቡ ኑሮ ሳይፈታችሁ እንደገና ተነሡና ትግሉ ካቆመበት እንቀጥል የሚል ጥሪ ነበር። ምንም እንኳ በመድረክ ላይ ላወጣው ባልችል ለአንዳንድ ግለሰቦች ሃሳቤን ማካፈሌ አልቀረም። በ1985ቱ የድርቅና ጠኔ መከሰት ወቅት በተለይ የምናኔ ኑሮን የሚያስመኝ መንፈስ በህሊናየ ይቃጭል ነበር። ይህ ሁሉ መሆን ባለመቻሉ በምሰራባቸው በሃዋርድ ዩኒቨርሲቲና በኰንግረስ ቤተ መጻሕፍት በመታገዝ ያለኝን የማንበብ ኅይል ተጠቅሜ ብዙ ዓይነት መጻሕፍትን አገላበጥኩ። ሃሳቦችን ወሰድኩ፣ አጠራቀምኩ። አይዞህ የሚል ህሊናዊ ግፊት ገፋፋኝ። የሞቱት ወጣቶች አደራ በዓይነ ህሊናዬ እየመጣ እንዳልሰንፍ ወተወተኝ። በዚህ መሃል ከጓደኛየ ከዳዊት አብርሃ ጋር በመሆን ወደ New Age ቤተ አምልኮ መሄድ ጀመርኩ። ይህ ቦታ ዘመናዊ በሆነ መልክ አዲስ ሃይማኖት ነኝ የሚል ስለነበረ ከማውቀውና ከካድኩት ክርስቶሳዊ እምነት ልዋጭ ሆኖ ተሰማኝ። በዚህ መሃከል የዚሁ ኃይማኖት ካህናት የጥንቆላ ዓይነት ሥርዓት የሚጠቀሙ ሆኖ ስለተሰማኝ ነፍሴ አልተቀበለችውም። ወደሌላ ቡድን ገባሁ፤ ይህ ደግሞ የቅዱስ ጳውሎስን አስተምህሮ ብቻ ነበር የሚያጎላው። ኢየሱስ የሚነሳው በመጠኑ ነበር። ነፍሴ ተከፋፈለች፤ በጊዜም ተውኩት። ያገኘሁትን ፍልስፍና፣ ታሪክ፣ ከማንኛውም የዕውቀት መስክ አንፃር ማንበቤንና ሃሳቦችን ማስፈር ቀጠልኩ።
ከዕለታት አንድ ቀን በውስጤ የመጣልኝ ሃሳብ፤ “ከእኔ ውጭ የሆነ ኃይልና ፈጣሪ ኃይል የምፈልግ ከሆነ ለምን ወደቀደመው ሃይማኖቴ አልመለስም?” ብዬ አሰብኩኝና ወደ ክርስቶስ እምነቴ ተመለስኩ። አባ ተስፋማርያም ባራኪ የተባሉ የተባረኩ የካቶሊክ ካህን ጋር ተዋውቄ ስለነበር ያሳለፍኩትን ግላዊ ጉዞ ለሶስት ሰዓት ያህል ከዘረዘርኩላቸው በኋላ ቄስ ሆኘ በማገልገል እግዚአብሔርን መካስ እንደምፈልግ ሃሳብ አቀረብኩላቸው። እርሳቸውም ቤተክርስቲያንን ማገልገል እንድችል መጠነኛ የሥነ መለኰት ትምህርት እንድወስድ አመቻቹልኝ። ከስራየ በኋላ በሳምንት አንድ ቀን ለሶስት ሰዓት የምማርበት ትምህርት ቤት እይተመላለስኩ ለሶስት ዓመት ያህል በነፃ ተምሬ ጨረስኩ። ትምህርቱን ስጨርስ በኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን የነበሩ ወጣት ልጆችን ትምህርተ ክርስቶስ እንዳስተምር መደቡኝ።
ለማስተማር በገባሁበት ክፍል 13 የሚሆኑ ወጣቶች ነበሩ። ምን ብየ ትምህርት እንደምጀምርላቸው ግራ ገባኝ። ኃላፊነቱ ከበደኝ። ማን እንደነበርኩ የማያውቁ ጮርቃ ልጆች ከእኔ አንዳች ነገር በመጠበቅ ዓይን ዓይኔን ይመለከቱኝ ነበር። “ተነሡና በፀሎት እንጀምር” ብያቸው ተነሡ። “በስመ አብ፣ በስመ ወልድ፣ በስመ መንፈስ ቅዱስ” ብለን ካማተብን በኋላ በእንግሊዝኛ ፀሎት ቀጥለን አባታችን ሆይ፣ ሰላም ለኪ ማርያም ሆይን ጨርሰን ስናሳርግ እኔ ሌላ ፀሎት አሰማሁ፤ “ዛሬ የምንማረውን ትምህርት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እራሱ ይምራን፣ ይግለጥልን፥” ብዬ እንደጨረስኩ ጠመኔ ይዠ በደመነፍስ ወደ ጥቁሩ ሰሌዳ አመራሁ። ምንም ያልተዘጋጀሁበትን ሃሳብ በሰሌዳው ላይ አስቀመጥኩ፤ God=Love የሚል ጻፍኩ። ከዚህ ቀን ጀምሮ ለአራት ዓመታት ያህል ያስተማርኩት “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” የሚለውን አስተምህሮ የሚተነትን ነበር።
በዚህ አዲስ ህይወቴ መካከል የረሳሁትንና የካድኩትን አምላክ በጸጸትና በንስሃ ተመልሼ እንዳመልከው ፈቃዱ ሆነ። ቀድሞ ለሀገሬ የነበረኝ ዓላማ እልባት ባለማግኘቱ ስለእግዚአብሔር ፍቅርነት በማስተምርበት ጊዜ ይህ እግዚአብሔራዊ ፍቅር ለኢትዮጵያ ፖለቲካ መሠረታዊ ጥቅም ሊያበረክት እንደሚችል በውስጤ ተሰማኝ። በዚህ ጊዜ ለማውቃቸው በተደጋጋሚ የምናገረው ነገር ቢኖር፥ “ፖለቲካ መንፈሳዊነት ላይ ካልተመሠረተ በቀር ምድረበዳ ላይ እንደፈሰሰ ውሃ ነው፥” የሚል ነበር። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ “መንፈሳዊ ፖለቲካ” የሚለውን ሃሳብ በማሰብና በማሰላሰል ቆየሁ። በጣም የሚደንቀው ግን በዚያን ጊዜ አካባቢ አንድ የምወደው ምሁር ጓደኛዬ አንድ አርብ በዝናብ ቀን በአንድ ጃንጥላ ተጠልለን ዶፉን መክተን አዘውትረን ቡና ወደምንጠጣበት ካፌ ስናመራ ድንገት አንድ ጥያቄ ጠየቀኝ። “ፈንታሁን፣ አንተ ቤተ መጻህፍት ስትሰራ ብዙ ጊዜህ ነው። የምጠይቅህ አንድ መጽሐፍ እንድትጠቁመኝ ነው፥” አለኝ። ምን እንደነበር ስጠይቀው፤ ” የኢትዮጵያን ችግር የሚፈታ ፎርሙላ የያዘ መጽሐፍ ብትጠቁመኝ፣” አለኝ። እንደ ዛሬ ቢሆን በሙሉ ልቤ መፍትሔው ፍቅር ነው ብዬ በመለስኩለት ነበር።
መንፈሳዊ ፖለቲካ በአሁኗ ኢትዮጵያ፤
ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ነዋሪ በነቂስ ወጥቶ በግምት 4 ሚሊዮን ይደርሳል የተባለ የህዝብ ድጋፍ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ አሊ ድጋፍ ሰጠ። ታይቶ የማይታወቅ የህዝብ ድጋፍ ያስገኘው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከብዙ ዓመታት በኋላ በመንግሥት መሪ ደረጃ የአምላክን ስም አንስተው በማመስገናቸው ነበር። በመቀጠልም በተከታታይ የሚያደርጓቸው ንግግሮች በተለይ የፍቅርን የበላይነትና አስፈላጊነት አበክረው በመግለጽ አዲስ የፖለቲካ አመለካከት በማስተዋወቃቸው ነው። ህዝቡ ደግፎ ከወጣው የፖለቲካ አመለካከት አንፃር ሲታይ ቀደም ብለው ከነበሩት ሥርዓቶች ለየት ያለና የተራመደ፣ የብዙ መስዋዕቶች ድምር የሆነው አዲሱ የፖለቲካ አመለካክት የተዋቀረበት የኢትዮጵያውያን መንፈሳዊነት የወለደው በመሆኑ ነው። የኢትዮጵያውያን መንፈሳዊነት እጅግ ጽኑ ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሚመራው ይህ መንፈሳዊነት ከጥንት ጀምሮ ሲደመር፣ ሲዳብር የመጣ፣ የዜጎችን ጠባይ፣ ትህትና፣ መሰበር እና አፍቃሪነትን ወ.ዘ.ተ ቅርጽ የሰጠ አኩሪ ትውፊት በመሆኑ። ከዚያም በኋላ የተከተሉት እምነቶች ማለትም ካቶሊካውያን፣ ወንጌላውያን፣ ሞሃመዳውያን ሁሉ የዚህ የኦርቶዶክስ እምነት አሻራ ያለበት ሆኖ ይታያል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነትና ሥርዓት ቀደም ሲል በነቢያትና በሐዋርያት ሲሰበክ የነበረው የክርስቶስ ኢየሱስን ማንነት የማከለ ሥርዓት የወረሰ ስለሆነ፤ ከኢየሱስ መምጣት በኋላ የሐዲስ ሥርዓት ጋር የተቀናጀ ሥርዓተ አምልኮ አዳብሮ የያዘ ሃብታምና ብልፁግ ሃይማኖት ነው።
የካቶሊክ እምነት ከኦርቶዶክስ እምነት ጋር የተሳሰረ ብዙ ነገር አለው። በቅድሚያ መነሳት ያለበት የቅዳሴ ሥር ዓቱ ነው። ምንም እንኳ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እምነት ከሮማው ቫቲካን ጋር በፅኑ የተሳሰረ ቢሆንም የኢትዮጵያ ካቶሊኮችን ልዩ የሚያደርጋቸው ረጅም ዕድሜ ካለውና ከደለበው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት በመውረሱና በመተሳሰሩ ጭምር ነው።
የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ብየ የምጠራቸው በተለምዶ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ተብለው የሚታወቁት በጀርመን እና በአሜሪካ ካሉት ጋር ብዙ ልምድ የቀሰሙ ቢሆንም አሁንም እናት የሆነችው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ጋር በቤተሰብም የተሳሰሩ በመሆናቸው ብዙ ጥቅም አግኝተዋል፤ ከዓለም ወንጌላውያን የሚለያቸው ባህርይ አላቸው።
ቀድሞውኑ የበላይነት ሥፍራ የነበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት የኢትዮጵያውያንን ሥነ ምግባራዊነት፣ ፈሪሃ እግዚአብሔርን፣ ፍቅርን፣ መመሳሰልን፣ ርህሩህነትን ወዘተ… መሠረት በኢትዮጵያውያን ላይ በመቅረጹ ምክንያት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች መሠረታዊ ባህርያቸው ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር አንድ እንዲሆን አድርጎታል።
ዶክተር አቢይ አህመድ አሊ የሚያስተጋቡት የመደመር ሥነምግባር በነዚህ አቢይ እምነቶች ሥር የታቀፉትን ዜጎች አንድ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነትን አረጋዊነትና አንጋፋነት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያዊነትን መሠረት የጣለ (ያቋቋመ) መሆኑን መገንዘብ እና ተገቢውን ክብር መስጠት በጣም አስፈላጊ ነው። በዚህ ግንዛቤ ብዙ የተገነቡ አላስፈላጊ የሆኑ ገደብ የሚጥሉ ግንቦች/ ግድግዳዎች እና መዋቅሮች ይፈርሳሉ። ኢትዮጵያዊው ወደፈለገበት የእምነት ጎራ ነፃ ሆኖ መንቀሳቀስ፣ አባል መሆን፣ ፈጣሪን ማምለክ ይቻለዋል። ሌላውን እመነትና የእምነት አባል አጥቁሮ ከመመልከት ወይም በሌላነት ፈርጆ ከማራቅና ከመራራቅ እንዲሁም ከመጥላት ይወገዳል፣ ይቆጠባል። እግዚአብሔርን የህይወቱ ማእከል የማድረግ ፍላጎት ትክክለኛ ቦታውን ያገኛል። ይህ ደግሞ ዜጋውን በሞላ ለክርስቶስ ዳግም መምጣት ይበልጥ ያዘጋጀዋል።
ዶክተር አቢይ አህመድ እና የርሳቸው ቡድን እስካሁን በማሳየት ላይ ያሉ ትዕግሥት የሚደነቅ ነው። ከዚህ ቀደም እንደተለመደው በቃላት ማሳመር ብቻ እንዲህና እንዲያ እናደርጋለን በሚል ሳይወሰኑ በት ዕግሥትና ዘዴ በተመላበት ጥበብ ከማስተዋል ጋር፤ ከዚህም በላይ በፀሎትና በምህለላ ከእግዚአብሔር መምሪያ በመጠየቅ የሚወስዱት እርምጃ ሁሉ ውጤቱ ያማረ እንደሆነ ታይቷል። የኢትዮጵያ ዜጎች በእግዚአብሔር እየተመሩ ለዘመናት የተጋረጣቸውን ተግዳሮት ሁሉ እየተቋቋሙ እዚህ ደረጃ የደረሱ እንደመሆናቸው መጠን አቢይ ለሆኑ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ አገር-አቀፍ ጥያቄዎች ከእግዚአብሔር መፍትሔ ለመጠየቅ ህዝቡ በጸሎት፣ በምህለላ፣ በእግዚኦታ እንዲተባበር መጠየቅ የሚያስገኘው ውጤት ትክክለኛና አመርቂ እንደሚሆን እርግጠኛ መሆን ይቻላል። ይህንንም ማወቅ ከፍተኛ የአመራር ችሎታን የሚያመላክት ነው። እንደቀድሞው ዘመን ፖለቲካና እምነት ማዶ ለማዶ እንደሚቆሙ ተደርጐ መመልከቱ ማክተም አለበት። የሰው ልጅም በራሱ መመካቱን እንደጀግንነት ማየት መተው አለበት። በእግዚአብሔር መመካት ሞኝነት አይደለም፤ እንዲያውም ጥበበኛ ያሰኛል እንጅ።
ይህ በሚሆንበት ጊዜ እግዚአብሔር እኛን ለእኛ፣ ለሌላው፣ ለዓለምም መሣሪያው እንድንሆን ይመርጠናል። ስለዚህ ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያውያን ሆንን ሌሎች የምንመራበት ፖለቲካ ከመንፈሳዊነት ጋር የተሳሰረና የተቆራኘ መሆን ይኖርበታል። ይህንን አዲስ ክስተት መንፈሳዊ ፖለቲካ ብለን ልንሰይመው እንችላለን።
መንፈሳዊ ፖለቲካና ህግ/ ህገመንግሥት በኢትዮጵያ፤
የዶክተር አቢይ አህመድ አሊ ዋና ጥሪ ወደ አምላክ እንመለስ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት አዲሱ ትውልድ ከአባቶቹ የወረሰውን እምነት እንዳይጠቀምበት የተበረዙና የተከለሱ መንፈሳዊ መሰል ትምህርቶች ስለተጋረጡበት ነው። በዚህ ምክንያት ቁጥራቸው ብዙ የሆነ ኢትዮጵያውያን አግድመው በዘፈቀደ የመጓዝን፣ በደመነፍስ የመመራትን ባሕርይ እያሳደሩ ነው። በሉሲፈር አመፅና በዘረጋው የክፋት መረብ እየተያዙ በመሰነካከል ላይ ናቸው። መገዳደል ባህላችንና መታወቂያችን ሆኖ እየተቸከለ ነው። በኑሮ ለሚደርሰው ችግር ሁሉ ሰይጣን ፈጣን መልስ ይሰጣል እየተባለ ይታመንበት ዘንድ በአበጋዞቹ ጠንቋዮች፣ መተተኞች፣ ሟርተኞች፣ በተሳሳቱ ደብተራዎች ይነዛል። በውጭ ሃገር የሚጻፍ መጽሐፍ ሁሉ ያለማጣራት ወደሃገሪቱ በገፍ እየገባ እኩይ መልእክቶችን በግልጽና በስውር የሚያስተላልፉትን እንደመልካም ቁም ነገር በመቁጠር የመጠቀም ልምድ ተስፋፍቷል። ከውጭ ሃገር የሚመጣ ጨርቅም ሆነ ቆሳቁስ፣ መጻሕፍትም ሆነ ፊልም ብርቅ ሆኖ የመወሰዱ ጉዳይ ቀድሞ ከነበረው ባህል እጅግ ይለያል። ያገራችን ሊቃውንት የውጭውን ሲተረጉሙና ጥቅም ላይ ለማዋል ሲወስኑ ለህብረተሰቡ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ በማስተዋል፤ ከሁሉም በላይ ለእግዚአብሔር መንግሥት የሚያበቃ መሆኑን ገምግመው ነው። አሁን ግን ገንዘብን ሃብት መሰብሰብ የኢትዮጵያዊው ዜጋ ዋና ዓላማ ተደርጎ መታየት ጀመረ። ለእግዚአብሔር ክብር ብሎ ማደር ቀርቶ ለራስ ጥቅም የመስገብገብ ሰይጣናዊ ባህል ህዝቡን በተለይም አዲሱን ትውልድ በሚያስፈራና በሚያሳፍር ሁኔታ እየተጠናወተው መጣ።
ከውጭ የሚያደቡ እኩይ ኃይሎች ኢትዮጵያንና ዜጎቿን የሚያጠቁበትን ዘዴ ሌት ተቀን ያሰላስላሉ። ቀደም ሲል ቀጥተኛ በሆነ ቅኝ ግዛትነት በመያዝ ህዝቡን ማዋረድና እግዚአብሔር ከሰጣቸው ፀጋ ማደናቀፍ፣ ማሳነስ፣ ከዚያም ማንነታቸውን ማፍረስ እንዲሁም በግድያ መጨረስ አልሆንላቸው አለ። ቀጥለውም አመላቸውን ደብቀው፣ መልካም ያሰቡ መስለው በትምህርት የላቁትን ዜጎች ወደራሳቸው ሃገር በመውሰድ በራሳቸው ትምህርት እየሞሉ፤ አይዞህ አሁን ዘምነሃል፣ እኛን መስለሃል፣ የለውጥ ሃዋርያ ሆነሃል፣ አሁን ሃብታም የመሆን ዓላማህ ተቃርቧል፤ ሃገሬን እረዳለሁ ካልክም የኛ ወኪል ሆነህ መሥራት ትችላለህ… የሚል ተስፋ እየሰጡ ወጣቱ ትውልድ በራሱ ሃገራዊ ትምህርት እንዳይኮራ፣ ጨርሶም እንዲጠላው ይደክማሉ፤ ተሳክቶላቸዋልም። ከዚህ መሰል ወጥመድ ያመለጠው፣ ትምህርት ተመስሎ የተሰጠውን ማደንዘዣ መርዝ ያልተቀበለው፣ ዶክተር እሸቱ ጮሌ ለማስትሬቱ ወደአሜሪካ መጥቶ በዓመቱ ከተመለሰ በኋላ በቀ.ኃ.ሥ. ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ባንድ አዳራሽ ተሰብስበን ንግግሩን ስናዳምጥ ከህሊናዬ የሚይፋቅ ንግግር አደረገ፤ “We, Ethiopians have to unlearn whatever we have learned from the West so far.” [በግርድፉ ሲተረጎም፤ “እኛ እትዮጵያውያን እስካሁን የተማርነውን ምዕራባዊ ትምህርት ሁሉ እንዳልተማርን እንቁጠረው፥” የሚል ነው]
የትምህርት ሁሉ ዓላማው ከሁሉ በፊት ትምህርቱ የእግዚአብሔርን ክብር የሚገልጥ፤ ለፈጣሪ ክብር የሚውል መሆኑ መረጋገጥ አለበት ብየ አምናለሁ። ትምህርቱ ወደ እግዚአብሔር ዘለዓለማዊ መንግሥት የሚመራን ነው ወይ ተብሎ መጠየቅ አለበትም ብየ አምናለሁ። ፍቅርና ሰላምን የሚያነግሥ ነው ወይ ተብሎ መጠየቅ አለበት። ከዚህ ውጭ የምንማረው በዓለም ነገር ለመዘፈቅ፣ በዓለማዊ የጥቅም አረንቋ ገብተን እንድንዛግጥ፣ በዓለማዊ የኃጢአት አረም ተውጠን እንድንደናበርና የሰይጣን ሰለባ ወደመሆን አዘቅት የሚወስደን ነው የሚሆነው።
እስኪ ከዚህ በታች የቀረበውን ታሪካዊ ትውፊት እንመልከት፤
“ከንግሥተ አዜብ በፊትና ከሱዋም በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት—ነገሥታት መሮች [መሪዎች] የቤተክርስቲያን ካህናት ነበሩ። ነገሥታቱም አንደካህናቱ የእግዚአብሔርን ሕግ በግዕዝ ተምረው በሃይማኖት እግዚአብሔርን ሲያገለግሉ ይኖሩ ነበረ። የቤተክርስቲያኑም ትምህርት የእግዚአብሔርን ሕገ መንግሥት ይሰብክ ነበረ እንጂ ስለህዝቡ መተዳደሪያ የሚሆን የሥጋዊ ጥበብ ትምህርትን አይሰብክም ነበረ። ስለዚህ የቤተክርስቲያን ትምህርት የመንፈሳዊ ነገርን በመስበኩ ከኢትዪጵያ የስጋዊ ጥበብ ትምህርት በጣም ራቀ። የኢትዮጵያ መንበረ መንግሥት በሕገ መንግሥት ከአራት ሺህ ዘመናት የሚበልጥ ጠንቶ ሲኖር በመንበረ መንግሥቱ ላይ ባዕድ ዘር አልተቀመጠበትም። ሕገ መንግሥቱም የተለወጠበት ጊዜ የለም። ምክንያቱም በኢትዮጵያ መንበረ መንግሥት ላይ የሚነግሡ ነገሥታት የእግዚአብሔርን ሕገ መንግሥት ስለሚጠብቁ ነው። የእግዚአብሔርንም ሕግ የሚጠብቅ መንግሥት መንግሥቱ ሳይናወጥ ዘርዐ መንግሥቱ ሳይለውጥ(የመንግሥት ልጅ ሳይለወጥ) ፀሐይ እስከኖረበት ዘመን ድረስ ለዘወትር በመኖሩ ነው። ኢትዮጵያ ይኸነን ያህል ዘመን ሙሉ በነፃነት መኖርዋ መስቀል ከሰላጢን እንደሚባል በቀኝ እጇ መስቀል በግራ እጇ ዘገር (ጦር) ይዛ ካሉ ባላጋሮቿ ጋር እየተዋጋች ሃይማኖትዋን ሳትክድ አገርዋንም ሳታስወስድ …እስከአሁን ድረስ ኖረች።”3
በግርማዊ ጃንሆይ ዘመን ለኢትዮጵያ ህዝብ የተሰጠው ህገመንግሥት እንደታሪኩ ስንመለከተው መንፈሳዊነት ከተላበሰው ፍትሐ ነገሥት የራቀ ከጃፓን ንጉሣዊ አገዛዝ የተኰረጀ ህገመንግሥት ለኢትዮጵያውያን መመሪያ ሆኖ ተረቀቀ። በዚህ ህገመንግሥት መንግሥትና ሃይማኖት አብረው እንደማይሄዱ፣ አንዱ በለሌላው ተግባር ጣልቃ እንዳይገባ ሆኖ ተደነገገ። ሰማያዊውን መንግሥት እግዚአብሔር ይግዛ፣ ምድራዊውን ግን ነገሥታት ይግዙ የሚል ትርጉም ይሰጣል። የእስከ ዛሬው ምድራዊ መንግሥት ህግ በተጣሰ ቁጥር፣ ወንጀል ሲፈጸም በገሃድ የሚታየውን ሥጋ-ለባሽ ሰው ከመቅጣት የዘለለ አቋም አልነበረውም ስለዚህም ህገ መንግሥቱ በሚደነግገው፣ ፍርድ ቤት በሚፈርደው አንቀጽ ወንጀለኛው ሰው ይታሰራል፣ ይደየናል፣ ይደበደባል፣ ይገረፋል፣ ይገደላልም። ወንጀል ግን አልቆመም፤ እንዲያውም እየተራቀቀ መጣ እንጂ። የሰው ልጅ የሚቀጣበት መንገድ ብዙ ነው። ለጠበቃ፣ ለዳኝነት፣ ለመቀጮ ሲከፍል ኪሱን ያራቁታል። ህይወቱን ሁልጊዜ ሀ ብሎ መጀመር ይገደዳል። ፈጣሪውንም ያማርራል። በግድያ ጊዜ የሞተው አልበቃ ብሎ ገዳዩም ይሙት ተብሎ ይፈረድበታል። ቤተሰብ ካለም በመሃከል ልጆችና ቀሪው ወላጅ ፍዳ ሲቆጥሩ ይኖራሉ።
እንደሚታወቀው እግዚአብሔር ሲፈጥረን በረቀቀና ፍጹም በሆነ፣ በተቀደሰ አምሳሉና ምሣሌው ነው። ወንጀለኛነት በእኛ አፈጣጠር ውስጥ ፈጽሞ የለም። የወንጀል መሠረቱ ሉሲፈር ነው። የርሱ አጀቦች ሰይጣናትና አጋንንትም የዚህ የወንጀል ስራ ተባባሪና አስፈጻሚዎች ናቸው። እነዚህ መናፍስት የማይተኙ፣ የማይደክሙ በመሆናቸው ከአባታችን አዳምና ከእናታችን ሔዋን ጀምረው እኛን ለማሳሳት ሲማስኑ ኖረዋል። በሰዎች ላይ እያደሩም ወንጀል ያስፈጽሟቸዋል። ከእግዚአብሔር ከፈጣሪያቸው የሚያራርቅ ስራ ያስፈጽማቸዋል። ታዲያ ዘመናዊ ህገመንግሥት በሰይጣን ላይ የሚለው ነገር የለም። ይህ አልቦነትም ህግ አርቃቂዎቹን ከሰይጣን ተግባር ጋር የመተባበር ያህል ይቆጠራል። ስለዚህ ሰው በህግ የበላይነት እንዲገዛ/እንዲተዳደር ስናስተምር የሰው ልጅ ሰላምና ፍቅር የሚገኘው የተረቀቀውን ህግ በማክበር ብቻ ነው፤ አለበለዚያ ቅጣት አለብህ እየተባለ ነው። ይህ ግን መስመር የሳተ የአስተሳሰብ ዘይቤ ነው። እንዲያውም ሉሲፈርና ጭፍሮቹ የራሳቸውን እኩይ አስተሳሰብ የበላይነት ለማስፈን ያደረጉት ሴራ ውጤት ነው ብሎ መደምደም ይቻላል።
መንግሥትና ሃይማኖት መለያየት አለበት የሚለው መርህ በጀርባው ያዘለው መልዕክት እኛ መሪዎች በእግዚአብሔር ህግ አንገዛም የሚል ነው። በሌላ አነጋገር እንደቀድሞው ሁሉ ህዝቡ በእግዚአብሔር ህግ ሆነ እግዚአብሔር በመረጠልን መሪ ሳይሆን በራሳችን ምርጫ እንተዳደራለን ብለው የተስማሙ መሆናቸውን ይጠቁማል። በአንድ ህብረተሰብ የህግ የበላይነት ሰላምና ፍቅርን ያመጣል ብሎ ማስተማር ሰው ሰራሽ ህግ ከእግዚአብሔር ህግ ይበልጣል ብሎ መደምደም ማለት ነው። በመሠረቱ እግዚአብሔር ፍቅር ነው። ይህ አምላክ ደግሞ በራሱ ቅዱስ አምሳል ሰውን ሲፈጥረው ሰው ራሱ ፍቅር መሆኑን ያስገነዝባል። ሰይጣን የሰውን እውነተኛ ማንነት ማለትም ፍቅርነቱን ለማስጣል ራሱ ያወጣውን የተሳሳተ ህግ እንዲተዳደርበት ሲሸርብ የፍቅር የበላይነትን ተክቶ የህግ የበላይነት ቦታውን እንዲይዝ ያደረገው ጥረት ትሳክቶለታል። እዚህ ላይ መንፈሳዊ ፖለቲካ ልዩነት የሚያመጣው አናሥራዊ የሰው ልጅ ተሰጥኦዎች፣ ፀጋዎች፣ እሴቶች ሁሉ እንደገና ቦታቸውን መያዝ አለባቸው ብሎ ነው። የእግዚአብሔር ክቡርነት፣ የሰው ልጅ ተከባሪነት፣ የፍቅር አናሥርነት፣ የአንድ መንፈስ ወላዊነት፣ የመሳሰሉት መንፈሳዊ እሴቶች ከተቀበሩበት ወጥተው ተገቢ ቦታቸውን መያዝ ይኖርባቸዋል። በተለይ የጌታ ኢየሱስን መመለስ ስናስብ ከአጋንንትና ከአለቃቸው ከሉሲፈር ጋር የምናደርገው ግብግብ ትክክለኛውን አቅጣጫ ይዞ መሄድ አለበት።
መንፈሳዊ ፖለቲካና ትንቢት፤
በትንቢት መስክ ስለኢትዮጵያ የተጻፉና ያልተጻፉ እንዳሉ ይታወቃል። ወደትንቢቶች ከመግባታችን በፊት እስኪ “ኢትዮጵያ” ከሚለው ስያሜ ጋር ያሉ አንዳንድ ጉዳዮችን እንመልከት። በምዕራቡ ዓለም ፍጹም የሆኑ ህብረተሰቦችን ለመፍጠር ያላቸውን ምኞት “ኢትዮጵ” ከሚለው ስያሜ ጋር የሚመሳሰል ቃል ፈጥረው ነበር። ይኸም ቃል utopia የሚል ነው። ከተረቶቻችን መካከል “ላም አለኝ በሰማይ፣ ወተቷን የማላይ”ብለን ስናወራርድ የቆየነውን ምሣሌ ይመስላል። የምዕራባውያን “ዩቶፒያ”ቶማስ ሞር በተባለ እንግሊዛዊ ጸሐፊ በ1516 ዓ.ፈ. ገደማ የተፈጠረ ቃል ነው። ይህ ቃል በምድራችን ላይ እንዲኖር የተፈለገውን ፍጹም የሆነ ምድር፣ ደስታ የተመላበት ሃገር፣ ዜጎቿ በመልካም አስተዳደር የሚተዳደሩባት ዓለም ለመሳል የሚሞክር ነው። ምናልባትም አዳም እና ሔዋን የኖሩባትን ገነት የመናፈቅ ምልክት ሊሆን ይችላል። ግሪኮች ደግሞ “አውቶፒያ” የሚል መጠሪያ “የትም የማይገኝ” ማለትም የቅዠት ዓለም ለማለት ይህን ቃል ፈጥረዋል። በዚህ ምናባዊ ዓለም ዙሪያ ምዕራባውያን ጸሓፍት ለአምስት መቶ ዓመት ያህል ተነጋግረውበታል። የዚህ ቃል መነሻ “ኢትዮጵያ” ከሚባለው ከምዕራቡ ዓለም እሩቅ የሆነ፣ ያልታወቀ ምናልባትም ህዝቦቿ ፍጹም ደስተኛ ሆነው የሚኖሩባት ድብቅ ሃገር ለመምሰል ከመመኘት አኳያ የተፈጠረ ሊሆን ይችላል።
ኢትዮጵያ የሚለው ስያሜ “ኢትኤል” ከሚለው የኩሽ ዘመን ንጉሥ ስያሜ ጋር ይዛመዳል። እንደሊቁ አማን በላይ አባባል “ኢትኤል” ማለት “የእግዚአብሔር (ፈጣሪ) ሥጦታ”ማለት ነው።4 ስለዚህ ኢትዮጵያ የሚለው የሃገር መጠሪያ የ “ፈጣሪ ሥጦታ” ከሚለው ትርጉም ጋር ይዛመዳል። ኢትዮጵያ የሚለው መጠሪያ የእግዚአብሔርን/ የፈጣሪን የበላይነት ያዘለ፣ በዚህ ፈጣሪ አምላክ ለህዝቡ እንደሥጦታ የተበረከተ መሆኑንም ይጠቁማል። የምዕራባውያን፥ “ዩቶፕያ” ግን እግዚአብሔር/ፈጣሪ የሌለበት፥ ሰው የፈጠረው ፍፁም፣ እንከን-የለሽ እንቶ ፈንቶ ህብረተሰብ ወይም ሃገር እንዲኖር የሚያልም ሆኖ እናገኘዋለን።
ተክለ ኪዳን*የተባሉ ደራሲ ስለእግዚአብሔር መንግሥት ሲጽፉ እንዲህ ብለዋል፤
“ከአዳምና ሔዋን መፈጠር ጀምሮ የነበረ ቤተ ሕዝቡ፣ ቤተ ክህነቱ፣ ቤተ መንግሥቱ በአንድ ላይ ተውህደው. . በአንድ እግዚአብሔር በበላይነት ሲመሩና የእርሱ የእግዚአብሔር ፈቃድ ብቻ ሲፈጸም የሚታይ ህይወትና ሥርዓት ነው።”5
ይህ መንግሥት ምን እንደሚመስል ሲጽፉም፥ “ፈቃደኛ የሆነ ትውልድ በእግዚአብሔር መንግሥት ሥርዓት ውስጥ መመላለስና መኖር፥..” የሚችልበት፤ “አምላኩንና ፈጣሪውን የበላይ ንጉሥ አድርጐ እርሱ የሚሰራውን ሥራ በመስራት ቤተ ህዝቡ፣ ቤተ ክህነቱ፣ ቤተ አምልኰው በአንድ ላይ ተውህዶ ለእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲሰለፍ በምድርም በረከትን በሰማይም ህያው ሕይወቱን ይዞ መኖር፥…” የሚያስችል አድርገው አቅርበውታል። (ገፅ 128-9) ይህ አገላለጽ” በከፊል የምዕራባውያንን ምናባዊ “ዩቶፒያ” ሲመስል ፣ በሌላ በኩል ደግሞ “ኢትዮጵያ” የሚለውን ስያሜ ሙሉ በሙሉ የሚገልጽ ነው።
በተክለ ኪዳን ትንቢት አኳያ ስንመለከተው ኢትዮጵያ ጥንትም እንደ ስያሜዋ በአሁኑ ዘመን የስያሜዋ እውነተኛ ትርጉም የሚገለጥባት ሃገር ወደመሆን እየገሰገሰች ይመስላል። በተክለ ኪዳን ትንቢታዊ ቃል መሠረት ኢትዮጵያ ከወደቀችበት አዘቅት ወጥታ በቅርቡ የክርስቶስ ኢየሱስ መመለስ የሚበሰርባት፣ የእግዚአብሔር መንግሥት የሚከሰትባት ትሆናለች። ስሟና ግብሯ አንድ የሚሆኑበት ጊዜ ተቃርቧል ነው የሚሉን።
“በቅርቡ ከሚመጣው ጥፋትና ጠረጋ ቀጥሎ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ይመጣል። በቅርቦቹ ሆነ በሩቆቹ ወላጆቻችን ሲነገር የነበረው “ሳልሳዊ ቴዎድሮስ” ዘመን አሁን ባለነው ትውልዶች ጊዜ ውስጥ እጅግ በቅርቡ ይመጣል።” (ተክለ ኪዳን ፤ ገጽ 468)
ይህን ካሉ በኋላ ኢትዮጵያ እንዲያውም መጪውን ዓለም የምትመራ መሆንዋን ሲያበስሩ፥ “ኢትዮጵያ ለዓለም ብርሃን የምትሆንበት ዘመን፤… በዓለም ላይ የተዘረጋው የዲያብሎስ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ተደምስሶ የእግዚአብሔር መንግሥት የሚዘረጋበት ዘመን… በቅርቡ ይመጣል፥” ብለው አረጋግጠዋል። እርግጠኛ በመሆንም የእግዚአብሔር መንግሥት፥ “መሠረቱ በኢትዮጵያ ከዚያም በዓለም ላይ ይጣላል [ይቋቋማል]፥” ብለው ደምድመዋል።
እንግዲህ የምዕራባውያን እግዚአብሔር አልባ፣ የሰው ሰራሽ ሃገር ወይም መንግሥት መሠረተ-ቢስ በሆነ ምናባዊ ዓለም ለመፍጠር ተሞክሮ እንቶ-ፈንቶ ምኞት ከመሆን አልዘለለም። “ዩቶፕያ” የሚለው ተምኔታዊ ዓለም በምድር ላይ አልተገኘም። እውነተኛዋ የእግዚአብሔር ሃገር ኢትዮጵያ ግን በስሟ እውነተኛውን ትንቢታዊ ህይወት እውን የሚሆንበትን ጊዜ ትጠባበቃለች።
የተክለ ኪዳንን ትንቢታዊ ቃል የሚደግፉ ሌሎች ትንቢቶች ተነግረዋል።
በፍካሬ ኢየሱስ ተመዝግቦ የተላለፈልን ትንቢት አለ ሲባል ሰምተናል። ግን ይህ ትንቢት በይፋ ለህዝቡ የተነገረበት ጊዜ ያለ አይመስለኝም። በቅርቡ ግን ታትሞ እንደሚወጣ ተስፋ አለኝ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እየተነሱ ካሉት ነቢያት ዘንድ ስለ ኢትዮጵያ መነሳት፣ ወደ ብሩህ ዘመን መተላለፍ፣ ስለ ህዝቧ ከአጋንንት ፈጽሞ ነፃ መሆን፣ የእግዚአብሔር የኪዳን ሃገር ስለመሆንዋ፣ የድንግል ማርያም እርስት ስለመሆንዋ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ አውታሮች በይፋ እየተገለጸ ይገኛል።
የመካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ቄስ በሊና ሳርካ፥ “የከፍታ ዘመን ለኢትዮጵያ” በሚሰኘው መጽሐፋቸው ከጌታ ኢየሱስ ቃል በቃል ሰማሁ ያሉትን ትንቢት ገልጸዋል። ቄስ በሊና በኢትዮጵያ ውስጥ እግዚአብሔር ያስቀመጠውን የበረከት ዓይነት እያሰቡ ህዝቧ ግን የዚህ ፀጋና በረከት ተጠቃሚ አለመሆን እያሳዘናቸው ይህ ለምን ሆነ፤ ለምን ራዕይ ያላቸው የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች መነሳት አቃታቸው እያሉ በመጨነቅ ወደ ፈጣሪ በሱባዔና በፀሎት ይማፀኑ ነበር። በእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ለሥራ ጉብኝት ጀርመን ሃገር በነበሩበት ጊዜ ኢየሱስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በሚሄድ ግልጸት ብዙ ራዕዮችን ሰለወደፊቷ ኢትዮጵያ አሳያቸውና አፅናናቸው። በ1993 ዓ.ም. ላይ የሚጀምረው የኢትዮጵያ መነሳሳት በየአስር ዓመቱ አዎንታዊ እድገትን እያሳየ እንደሚቀጥል በዚህ ራዕይ እግዚአብሔር ለቄስ በሊና አሳያቸው። የመጀመሪያ አሥር ዓመት የችግር፣ የመከራ፣ እንዲሁም የሽግግር ዘመን እንደሚሆን፤ ከ2003 እስከ 2013 ዓ.ም. ከእንቅልፍ የመንቂያ ዓመት እንደሚሆንና በዚህ ጊዜ በሃገር ደረጃ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሃድሶ ይሆናል። ብዙ የልማት እንቅስቃሴዎች ይፋጠናሉ። ወንዞችና ጅረቶች በመስኖ ልማት ይጎለብታሉ፤ የህዝቡ ንቃት ከእንቅልፍ እንደነቃ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ህዝቡ ባለው እውቀት፣ ችሎታና ስጦታ ለመጠቀም የሚሯሯጥበት እንደሚሆን በራዕይ ተገለጠላቸው።
ሦስተኛው አሠርት ዓመት (2013-2023) ለኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን እንደሚሆን፣ የ500 ዓምታት ኋላቀርነት፣ ድህነትና መሃይምነት እንድሚወገድና የሃገራችን ህዝብ ከነዚህ ነፃ እንደሚወጣ፣ በዚህ አጭር ጊዜ የጃፓንን የኑሮ እድገት የሚተካከል ደረጃ እንደምትጎናጸፍ ገለጸላቸው። በመንፈሳዊ እንቅስቃሴ ደረጃ ኢትዮጵያዊያን አጋልጋዮች በየሄዱበት ሁሉ እንደ ጨው ይፈለጋሉ፤ ብርሃንነታቸውንም ይገልጣሉ።” እንደመድኅኒት የሚፈለጉ፣ በአገልግሎታቸው፣ በትጋታቸውና በንቃተ-ህሊናቸው የሚፈለጉ ህዝቦች ሆነው ለዓለም ይገለጣሉ። ተሰርተውም ይወጣሉ፤ ወጥተውም መድኃኒት ይሆናሉ። ዘመኑ እግዚአብሔር አህዛብን የሚጎበኝበት ዘመን ይሆናል።
“ሙስሊሞች በህልምና በራዕይ ያዩኛል፣ ከመካከላቸው አጋንንት የሚስቡትን አጠፋለሁ፤ በምድሪቱ ላይ ያሉ መተተኞችና ጠንቋዮች ያፍራሉ፤ ትብታባቸው ከንቱ ይሆናል፣ ሲል የሠራዊት ጌታ ለቄስ በሊና ነግሯቸዋል። 6(ገጽ 78)
መደምደሚያ ፤
ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ በቅርቡ በእንግሊዝኛ ባወጡት መጣጥፍ7 ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረውን በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የሚመራውን አዲስ የመንግሥት አስተዳደር በማድነቅ ጽፈዋል። በዚህ ጽሑፋቸው ታላቁ ኢትዮጵያዊ የሥነ ጽሑፍ ሊቅና የአስተዳደር ችሎታ የተቸራቸው አቶ ሃዲስ ዓለማየሁ፥ “ለኢትዮጵያ ምን ዓይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል፥” በሚለው መጽሓፋቸው ላይ ያነሱትን ጥያቄ መልስ የሚሰጥ በሚመስል አኳኋን ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በኢትዮጵያ ሙስሊሙንና ክርስቲያኖችን የሚያገናኘውና የሚመራው ኃይል ፍቅር ብቻ መሆኑን የተገነዘቡ መሪ ናቸው በማለት ያስቀምጣሉ። በማስከተልም የመሪዎች መንፈሳዊ ብቃት የግል ፍላጐትንም ሆነ የሥልጣን ጥምን አስወግዶ እውነተኛ መሪ ለመሆን ያበቃል። ፖለቲካም ፍቅር፣ መመሳሰል፣ እርቅ የመሳሰሉትን መንፈሳዊ እሴቶች በተግባር ላይ ለማዋል ያስችላል ሲሉ ገልጸዋል። የጋንዲንም ምሳሌ በማስታወስ ፖለቲካንና መንፈሳዊነትን ባንድነት ለማገልገል የቻለ መሪ መሆኑን አውስተዋል። ጋንዲ፥ “ከሁሉም የሰው ልጅ ጋር ለመገናኘት የሃይማኖት ህይወት ያስፈልገኛል። ይህን ለምድረግ ደግሞ ፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ አለብኝ፥” የሚል መርህ መጠቀሙን አስታውሰዋል።
ዶክተር አቢይ አህመድ አሊ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ስለመደመር፣ ስለፍቅር፣ ስለሰላም፣ ስለይቅር ባይነት እና ስለመሳሰሉት መንፈሳዊ እሴቶች በፖለቲካ መድረክ በተደጋጋሚ በማንሳት ተናግረዋል። የኢትዮጵያውያንን የልብ ትርታ ያወቁትን ያህል የህዝቡን መንፈሳዊነት መሠረት ያደረገ ትምህርት አዘል ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት የህዝቡ እርካታ እንዲህ ነው ተብሎ የሚነገር አይደለም። ከመቸውም ይልቅ ህዝቡ ልባዊ ደስታ ያገኘበትም ሆነ ልባዊ ደስታውን የገለጸበት ጊዜ ካሁን በፊት እንዳሁኑ አልታየም። የልቡን መሻት ያወቀለት መሪ በመነሳቱም ህዝቡ ፈጣሪውን አመስግኗል፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩንም ህይወት በስስትና በፀሎት ይጠብቃል።
ሽለቃ ዳዊት እንደጻፉት፥ “ኢትዮጵያ ባሁን ጊዜ መንፈሳዊነት ላይ የተመረኰዘ ፖለቲካ ያስፈልጋታል፥” ሲሉ በ1966 ዓ.ም. ላይ ክቡር ሃዲስ ዓለማየሁ የጠየቁትን ጥያቄ እልባት ሰጥተውታል። በሻለቃ ዳዊት አገላለጽ፥ “ኢትዮጵያ የሰው ልጆች አናሥር፣ የሥልጣኔ መነሻ፣ በዘመናችን ደግሞ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሊትና ተስፋ ናት።” እንዲሁም የመካከለኛውን ምሥራቅና የዓለምን ፖለቲካ መሠረት በመጣል ከጥንት ጀምሮ እናትነትዋን በማሳየትዋ፣ እንዲሁም ክርስትና፣ እስልምና፣ ይሁዲነት የየራሳቸውን ልዩነት ይዘው እንዲጠናከሩ በመርዳትዋ በዓለም ፊት ልዩ ሁና እንድትታይ አድርጓታል።
በተለያዩ ነቢያት እንደተነገረውም እግዚአብሔር በአሁን ዘመን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳይ ራሱ ጣልቃ እየገባ መሆኑ እና ከተለያየ ሉሲፈራዊ ጥቃት እየተከላከለላት መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ አሊ ወደ ፖለቲካው መድረክ ብቅ ያሉበት ምሥጢር መለኰታዊ ጣልቃ ገብነትን አመልካች ነው። ከእንግዲህ ኢትዮጵያ ለተዘጋጀላት ከፍተኛ ክብር በመዘጋጀት ላይ ናት ብሎ በልበ ሙሉነት መናገር ይቻላል። ጥንት የዓለም መሪ፥ የህዝቡ አናሥር የነበረችውን ያህል አሁን ደግሞ ዓለምን ለመምራት በእግዚአብሔር እየተመራች ነው። የዓለም ህዝብም የኢትዮጵያን ማንሰራራትና መምራት እየተጠባበቀ ነው። ኢትዮጵያውያን ለዚህ ዳግማዊ ትንሣኤ ዝግጁ መሆን አለባቸው።
ወስብሃት ለእግዚአብሔር!!!
የመጻሕፍትና የመጣጥፎች ዝርዝር፤
- ደስታ ተክለ ወልድ፤ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት፤
- ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር፤ መዝገበ ቃላት ትግርኛ–አምሐርኛ፤ አሥመራ 1948/49 ዓ.ም፣ ገጽ832-34።
- ተሰማ ኅብተሚካኤል፤ ከሣቴ ብርሃን ተሰማ የዐማርኛ መዝገበ ቃላት፤ ገጽ 13
- መሪራስ አማን በላይ፤ የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ፤ አዲስ አበባ፤ 1985, ገጽ 26
* ተክለ ኪዳን በመጽሐፋቸው የሚያነሷቸው ትንቢቶችና ነጥቦች የተከበሩ ንቡረ እድ ኤርምያስ ከበደ ወልደ ኢየሱስ ከሚጽፏቸው መጻሕፍት ጋር ተመሳሳይነት አላቸው።
- ተክለ ኪዳን፤ ታላቅ የብርሃን ተስፋ ፤ ገፅ 128
- በሊና ሳርካ፤ የከፍታ ዘመን ለኢትዮጵያ፤
- Dawit W.Giyorgis: “Ethiopia: Keep Your Eyes on the Stars, and Your Feet on the Ground.”
ABSTRACT
This article attempts to define and articulate the workings of the present Ethiopian political system. The concept of “spiritual politics” is coined in order to define the new political system in Ethiopia led by Prime Minister Abiy Ahmed Ali and his group.