ያላዩት አገር ሲናፍቅ፥ የአዲስ መንግሥት ምኞት (ጌታቸው ኃይሌ)

መግቢያ

መቆየት መልካም ነው፤ የቆየ ሰው የማይሆን ነገር ሲሆን ያያል” ይባላል። ከማይሆኑ ነገሮች አንዱ ያላዩት አገር መናፈቅ ነው። ስለዚህ፥ “ያላዩት አገር አይናፍቅም” ይባላል። መቆየት መልካም ነው፥ እኔም ያላየሁት አገር እስኪናፍቀኝ ቆይቻለሁ። ግን የናፈቀኝ አዲስ ነገር ቢሆንም በኔ አልተጀመረም፤ መንፈሳውያን አባቶቻችንም ናፍቀውታል።

ናፍቆቴ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጻፈው ሕገ መንግሥት ተጠብቄና ሕጉን እኔም ጠብቄ፥ ረኀብ፥ በሽታ፥ ድንቁርና የሚወገዱበትን መንገድ እየፈለኩና እያደረኩ በነፃ መኖር ነው። ይህ ደግሞ፥ አንዲት ጻድቅት ሴት ስለ አንዱ ጻድቅ  ያየችው ራእይ ነው።

ወካዕበ፡ ነገረተኒ፡ አሐቲ፡ ብእሲት፡ ፈራሂተ፡ እግዚአብሔር፡ ዕበዮ፡ ለአቡነ፡ በርተሎሜዎስ፡ ወትቤ፡ ርኢኩ፡ ሀገረ፡ ዓባየ፡ እንተ፡ ትመስል፡ ፀሓየ። ወእቤ፡ ዘመኑ፡ ዝብሔር፡ ጥሉል። ወይቤሉኒ፡ ዘበርተሎሜዎስ፤ ወስማሰ፡ ለይእቲ፡ ሀገር፡ ወሰን፡ አልባቲ፤ ወዓባር፡ አልባቲ። እለ፡ አሥመርዎ፡ ለእግዚአብሔር፡ ይበውኡ፡ ባቲ። ዘንተ፡ ይቤ፡ አቡነ፡ ዮሐንስ፡ ዘኢሞተ፡ ከመ፡ ኢይበሉነ፡ ሰብእ፡ ነገሩ፡ ሐሰተ።

ደግሞ አንዲት እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ስለ አቡነ፡ በርተሎሜዎስ ታላቅነት እንዲህ ስትል ነገረችኝ፤ “አንዲት ፀሐይ የምትመስል ትልቅ አገር አየሁ። ይቺ ለምለም አገር የማን ነች? ብየ ጠየቅሁ። የበርተሎሜዎስ ነች አሉኝ። የሀገሪቱ ስም ወሰን የለሽ ነው። ድርቅም የለባትም። እግዚአብሔርን የሚያስደስቱ ይገቡባታል።” ሰዎች፥ “ነገሩ ውሸት ነው” እንዳይሉን፥ ይኸን የተናገረው አሁን በሕይወት ያለው አቡነ ዮሐንስ ነው።

አቡነ በርተሎሜዎስና አቡነ ዮሐንስ ወሎ ውስጥ ያለው የደብረ ዘመዶ የመጀመሪያዎቹ አበምኔቶች ናቸው። ለዛሬው  ጽሑፌ እግዚአብሔርን የሕገ መንግሥት ምሳሌ ብናደርግ፥ ክልልና ድርቅ በሌለባት ዲሞክራሳዊት ኢትዮጵያ ለመኖር እንችላለን። የሚናፍቀኝ ከአሁን በፊት ያላየሁት አገር ይህ ነው። ስለመንግሥተ ሰማያት ብዙ እንደምንሰማውና እንደምናነበው፥ ስለዲሞክራሲም ያንኑ ያህል እንሰማለን እናነባለንም። ሆኖም፥ ስሞት መንግሥተ ሰማያት እንድገባ እጸልያለሁ እንጂ፥ ኑሮው አይናፍቀኝም። የዲሞክራሲ ኑሮ ግን ስለሚናፍቀኝ፥ አገሬ ምድር ላይ ሰፍኖ ሳላየው እንዳልሞት እጸልያለሁ። “የሰማዩ ሰላማዊ ኑሮ በምድርም እንዲሆን ፈቃድህ ይሁን” እያልን የምንጸልየው፥ የዲሞክራሲ አስተዳደር የምንመኘውና የምንናፍቀው  እንዲፈጸምልን ነው።

ይህ ምኞትና ናፍቆት የታላላቅ ምዕራባውያንን ራስ ወደ ፍለጋ መስክ ልኳቸዋል። የሰር ቶማስ ሞር መጽሐፍ (Utopia (1516) by Sir Thomas More) የዚህ ውጤት ነው። ብዙ አገሮች ረኀብን፥ በሽታን፥ ድንቁርናን፥ መምዕላይን (= dictator = ፈላጭ ቈራጭን) አስወግደው በሰላም፥ በጤና፥ በጥጋብ፥ በነፃነት ሲኖሩ፥ ለምንድን ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በነዚህ ሁሉ ችግሮች የሚማቅቀው? መሬቷ ጠፍ ነው እንዳይባል፥ ለሙ መሬት ለአራሹ ከሚያስፈልገው ይበልጥ ተዘርግቷል። ድርቅ ነው እንዳይባል፥ ከወንዞቿ አብዛኞቹ ወራጅ ውሐ  አላቸው፤ እንዲያውም ድምበር ጥሰው እየሄዱ፥ ለጎረቤት አገርም ይተርፋሉ። ማዕድን የላትም እንዳይባል፥ የፋዙቅላ ወርቅ ከጥንት ዘመን ጀምሮ የታወቀ ነው። የሕዝቡ የማሰብ ችሎታ ዝቅተኛ ነው እንዳይባል፥ ተሰደው በተራመደው አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከሀገሬው ሕዝብ ጋራ በማናቸውም ረገድ ተወዳድረው፥ ሲሆን ሲበልጡ ካልሆነም ሲመጣጠኑ እናያቸዋለን። የችግራችን  ምንጩ መንግሥት ይሆን እንዴ?

የመንግሥት አስፈላጊነት

ለመሆኑ መንግሥት ምን ያደርግልናል? ለምን ያለመንግሥት መኖር አልታሰበበትም? መንግሥት የማቋቋም ሐሳብ ከየት መጣ? ማን አመጣውና በየሀገሩ ተዳረሰ? ወይስ እንደ ፍጥረት በየሀገሩ በቀለ? ፍጥረት በየሀገሩ የበቀለው የእግዚአብሔር የማይመረመር ሥራ ነው ተብለናል፤ መንግሥትም የእግዚአብሔር ሥራ ይሆን እንዴ? አዳምን ከፈጠረ በኋላ ረዳት ያስፈልገዋል ብሎ ሔዋንን ፈጠረለት። ከዚህ አምላካዊ ሥራ ሁለት ነገር እንረዳለን፤ አንደኛ፥ ሰው  ኑሮውን ብቻውን መኖር እንደማይችለው፥ ሁለተኛ ልትረዳው የተፈጠረችው ሔዋን ራሱ አዳም መሆኑን እንረዳለን። አዳምና ሔዋን አንድ ሰው እንደሆኑ ከነሱ የተገኘው ኅብረተሰብ፥ ማለትም ጠቅላላው የዓለም ሕዝብ፥ አንድ አዳም ነው። አንድ ብር እና መቶ ሳንቲም አንድ ናቸው።

እነዚህ ሰዎች (አዳሞች) ኑሯቸው በአደንና ከብት በማርባት ስለሆነ፥ ያሉበት ቦታ መጥበብ ግጭት አመጣባቸው። በሀገራችን ለዚህ በምሳሌነት የሚጠቀሰው የአብርሃምና ሎጥ ታሪክ ነው።

ከአብራም ጋር የሄደው ሎጥ ደግሞ የላምና የበግ መንጋ ድንኳንም ነበረው። በአንድነትም ይቀመጡ ዘንድ ምድር አልበቃቸውም። ንብረታቸው ብዙ ስለነበረ አብረው ሊቀመጡ አልቻሉም። የአብራምንና የሎጥን ከብቶች በሚጠብቁ እረኞች መካከል ጠብ ሆነ። . . . አብራም ሎጥን እንዲህ አለው፤ “አንተና እኔ ወንድማማቾች ነን፤ በእረኞቻችን መካከል ጠብ እንዳይኖር እለምንሃለሁ። ምድር ሁሉ በፊትህ አይደለችምን? እባክህ እንለያይ፤ አንተ ወደግራ ብትሄድ እኔ ወደቀኝ እሄዳለሁ፤ ቀኙን ብትመርጥ  እኔ ወደግራ እሄዳለሁ። . . .”  ሎጥም በዮርዳኖስ ዙሪያ ያለውን አገር ሁሉ መረጠ።. . . ተለያዩ።

መለያየት ሌላ ሕዝብ ያደርጋል፤ አንድን ሕዝብ ብዙ ሕዝቦች ያደርጋል። አንድ የነበረ ቋንቋቸውና አንድ የመሰለ መልካቸው አካባቢውን እየመሰሉ ከጥንታቸው እየራቁ ይሄዳሉ። እዚያው የቀሩትም ባሉበት ጠባይና ባህል ቆመው አይኖሩም፤ ቀስ በቀስ ይለወጣሉ። “ቋንቋቸው አካባቢውን ይመስላል” ማለት ባካባቢያቸው ላሉ ነገሮች ስም ያወጣሉ ማለት ነው። ለምሳሌ፥ አማርኛ ውስጥ “ካንጋሮ” የሚል ቃል የለም። ኤስኪሞዎች ጉሬዛን የሚጠሩበት ስም የላቸውም። አማሮች ካንጋሮ፥ ኤስኪሞዎች ጉሬዛ፥ የሚባል ፍጥረት አያውቁም። ለማይታወቅ ነገር ስም አይወጣም። እንግዴህ ሁሉም የአዳም ልጆች ሆነው ሳለ፥ የተለያዩ የሚያደርጓቸው አካባቢያቸውና ባህላቸው ናቸው።

አካባቢና ባህል ዘመድ ሲያራርቅ

ዘመዳሞች የሚጣሉትም የተለያዩ አካባቢ (ቀየ) ሰዎች በመሆናቸው፥ መሬት ያፈራውን ሊቦጠቡጡ ሄደው ሲገናኙ ነው። ወዲያ ማዶ ካለው መንደር ሰዎች ጋር  ለከብቶቻቸው ግጦሽ፥ ለቤታቸው የአደን ጫካ፥ የምንጭ ውሐ ሲሻሙ ይጣላሉ። ከዚያ ባህል ይመጣል። የባህል ግንዶች የሚባሉት ቋንቋና ሃይማኖት ናቸው። ሰዎች በዘር አንድ ሆነው ሳለ፥ በባህል ምክንያት፥ ማለትም፥ የተለያየ ቋንቋ በመናገራቸው፥ የተለያየ ሃይማኖት በመከተላቸው፥ ዝምድናቸውን፥ ያንድ አባት ያንድ እናት ልጆች መሆናቸውን ፈጽሞ ይረሱታል። በባህል ምክንያት ዘመዳሞች የተለያዩ ነገዶችና ጎሳዎች ይሆናሉ። በፖለቲካ ዓለም ነገዶችን እንደ ማቀራረብ የሚያስቸግር ነገር የለም። ከሰብአትካትነት (from primitive thinking) የወጡ ሳይቀሩ እንደሚፋጁ አየርላንዶች አሳይተውናል። አስተሳሰብን ለማስለወጥ በአስተማሪዎች ላይ እንዳንተማመን አንዳንድ ጊዜ እነሱ ይብሳሉ። ሆኖም ትግሉን ከመቀጠል ሌላ አማራጭ የለንም።

ማኅበረሰብና ግለሰብ፤

ፖለቲካ ማኅበረሰብን የማስተዳደር ስልት ነው። “ከዶሮና ከእንቁላል ማን ቀድሞ ተፈጠረ?” እንደማለት አይሁንብኝ እንጂ፥ ምርምሩ፥ “ማነው ማንን የሚያገለግለው፤ ግለሰብ ኅብረተሰብን? ወይስ ኅብረተሰብ ግለሰብን?” የሚል ነው።  እነ ቶማስ ሆብስ (Thomas Hobbes)፥ ጆን ሎክ (John Locke)፥ ጃንጃቅ ሩሶ (Jean-Jacques Rousseau)  በሰፊው እንደተቹት፥ የፖለቲካ መሠረቱ የዚህ መልስ መሆን አለበት። እንደ ኮሚንስቶቹ እንደነ ካርል ማርክስ (Karl Marx) ከሆነ፥ ኅብረተሰብ የበላይነት ስላለው የኅብረተሰቡ አባሎች የኅብረተሰቡ አገልጋዮች ናቸው። በካፒታሊስቶቹ ዘንድ ግን ኅብረተሰብ የተፈጠረው/የሚፈጠረው ግለሰብን ለማገልገል ነው። የግለሰብን የበላይነት ካፒታሊስቶች ስለደገፉት፥ መጥፎ ስም ሊወጣለት ቢችልም እውነቱ ግን ይህ ነው፤ ኅብረተሰብ የሚቋቋመው ግለሰብን ለመርዳት ነው። “ኑ የምንረዳዳበት እድር እናቋቁም” እንላለን እንጂ፥ “የምንረዳው እድር እናቋቁም” አንልም።  የሚሰበሰበው ገንዘብ የሚሰጠው ችግር ላጋጠመው ለአንዱ ሰው ነው።

ከፖለቲካ አንጻር ስናየው፥ ሀገርም፥ መንግሥትም፥ የፖለቲካ ፓርቲም የሚቋቋሙት የግለሰቡን ሕይወት የሚያደናቅፉ እክሎች እንዳይነሡ ዘብ ለመቆም ነው።መብት የግለሰብ ነው፥ አንድ ሰው አንድ ድምፅ” የሚባለው ስለዚህ ነው። ሰዎች በባህል (በቋንቋ፥ በሃይማኖት)፥ በቀየ፥ በርእዮተ ዓለም የመደራጀት መብት አላቸው። ራሱ ድርጅታቸው ግን ለራሱ የሚጠይቀው ሕገመንግሥታዊ መብት የለውም። መብቱ የአባሎቹ መብት ነው።

መንግሥት የሚቋቋመው የግለሰቡን ሕይወት የሚያደናቅፉ እክሎች እንዳይነሡ ዘብ ለመቆም መሆኑ ቀርቶ፥ ራሱ አደናቃፊ መሆን የጀመረው፥ ከታሪክ አንጻር ሲታይ በኋላ ዘመን ነው። የቀድሞውን ስንገምት፥ ብዙ መሆንና መንግሥት ማቋቋም የተጀመረው ከቤተ ሰብ ነው። የቤተ አስተዳዳሪ አባ ወራው የአዳም ወራሲ ነው። ይህ ሰው አባት ነው። ቤተሰቦች ሲበዙ ጎሳ፥ ነገድ ይሆናሉ። የነገዱ መሪ የነገዱ አባላት የሚያከብሩት ሽማግሌ ይሆናል።

የመንግሥት ፅንሰሐሳብ

የመንግሥት ፅንሰሐሳብን ለመተቸት፥ ከእኛ ጋር የባህልና የመንግሥት አመሠራት ግንኙነት ወዳላቸው ወደ እስራኤል ሄጄ ልምጣ። ሌሎች ኅብረተሰብ ዘንድ ሽማግሌው አስተዳዳሪ ወደ ንጉሥነት ሲለወጥና መምዕላይ (= ፈላጭ ቈራጭ) ሲሆን፥ እስራሌላውያን ነቢይ በሚሉት ሽማግሌ ሲተዳደሩ ብዙ ጊዜ ቈይተዋል። ነቢይ ሥልጣኑን የሚያገኘው ከእግዚአብሔር ነው ተብሎ ይታመናል። በሰው አእምሮ መሪና አምላክ ተገናኙ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ጥቅምም ጉዳትም አለው፤ ጥቅሙ፥ ነቢይ የርኅሩኁ አምላክ ወኪል ስለሆነ ለሕዝቡ ርኅራኄ ይኖረዋል። ጉዳቱ፥ በአንድ ሕዝብ ውስጥ ብዙ ሃይማኖቶች ሲኖሩ ግን፥ የአንዱ ሃይማኖት ነቢይ ሲመራ የሌሎቹ ሃይማኖቶች ተከታዮች ነቢዩ እንደማይወክላቸው ይሰማቸዋል።  ይኸንን ችግር ኢትዮጵያ እንዴት እንዳስተናገደችው እንነጋገርበታለን። አሁን አባቶቻችን በትርጓሜ ዳዊት አማካይነት የነገሩንን በእስራኤል የሆነውን እንይ፤

ነቢዩ ሳሙኤል እስራኤላውያንን ይመራቸው በነበረበት ጊዜ፥ ሕዝቡ ተሰብስቦ፥ “አንተ እንዳትመግበን (= እንዳታስተዳድረን) አረጀህ፤ ‘ወደቂቅከኒ ኢሖሩ በፍኖትከ’፤ ልጆችህም (ኢዩኤና አብያ) በአንተ መንገድ አልሄዱም። ‘ነሥኡ ሕልያነ ወገመፁ ፍት’፤ ጉቦ በሉ፥ ፍርድ አጐደሉ። (በዚያ ላይ ጠላት ተነሣብን። ያን ጠላት የሚያጠፋልን ንጉሥ አንግሥልን” አሉት።

ሳሙኤል ይኸን ሲሰማ አዘነ። ማዘኑም “መንግሥት  ለልጆቼ ሊቀርባቸው ነው” ብሎ አይደለም። “እግዚአብሔር በኔ አድሮ ይመግባቸው (= ያስተዳድራቸው) ነበረ። ያነገሥኩላቸው ንጉሥ የበደላቸው እንደሆነ፥ እግዚአብሔርን ይክዱታል፤ ጣኦት ከማምለክ ይደርሳሉ” ብሎ ነው እንጂ። ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክት፥ “ስምዖሙ ቃሎሙ ዘይቤሉከ”፥ “የነገሩህን ቃላቸውን ስማቸው”፤ “አኮ ዘመነኑ ኪያከ፥ አላ መነኑ ኪያየ ከመ ኢይንግሥ ቦሙ”፥ “(እንዲህ ያለ ጥያቄ ማንሣታቸው) አንተን ንቀው አይደለም፤ እንዳልነግሥባቸው እኔን ንቀው ነው እንጂ”። “ወባሕቱ አስምዖ አስምዖሙ”፤ “ነገር ግን (እስራኤልና ሴት ምክንያት ይወዳሉና ሳናውቅ ተደረገብን እንዳይሉ፥ የንጉሡን ወግ ሥርዓት ግልጥ አድርገህ ንገራቸው” አለው።

ሳሙኤልም (እንደታዘዘው እንዲህ ሲል ነገራቸው)፤ “ማንገሡን አነግሥላችኋለሁ። ሳነግሥላችሁም ከናንተ አንዱን ነው እንጂ ከሌላ አይደለም። ነገር ግን ወግ ሥርዓቱን ልንገራችሁ፤ ‘ይነሥእ ደቂቀክሙ ወአዋልደክሙ፥ ወይረስዮን መበስላተ ወመጽዕታተ’፥ ‘ወንዶች ልጆቻችሁን (መልከ መልካሞቹን) ይወስድና ምልምል፥ (መልከ ጥፉዎቹን) ቋሚ ለጓሚ፥ ሴቶች ልጆቻችሁን (መልከ መልካሞቹን) ገንቦ በጥባጭ፥ ሽቱ አጣፋጭ (መልከ ጥፉዎቹን) እንጀራ ጋጋሪ፥ ወጥ ሠሪ ያደርግባችኋል። ‘ወይነሥእ ዐጸደ ወፍርክሙ’፥ “ከመስካችሁ ያፄ መስክ፥ ከእርሻችሁ ያፄ ሁዳድ፥ ከአዝመራችሁ ያፄ ቆሎ፥ አህያችሁን ጎራዳ፥ በቅሏችሁን ወደል ጋዝ ፥ ከብታችሁን ተኵስ እያደረገ ይወስድባችኋል’” አላቸው። ይህም እስከ አፄ ፋሲል ደርሷል፤ ከክፋትዎ (= ከክፋታቸው) ሁሉ ይህን አስቀርተዋል። (ከትርጓሜ ዳዊት ተሻሽሎ የተቀዳ)  

ማስጠንቀቂያው ልክ በእስራኤል ታሪክ ብሉይ ኪዳን ውስጥ እንደተመዘገበው ሳይሆን፥ በጐንደር ዘመነ መንግሥት ይሆን እንደነበረው ነው። በኢትዮጵያ ንጉሣዊ አገዛዝ ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ታማኝ ሰነድ ነው። “ምልምል” የሚባለው በጎንደር ዘመነ መንግሥት ላላገቡ የቤተ መንግሥት ሴቶች ወዳጅ እንዲሆን ከወጣቶች ማህል የሚመለመል ጐረምሳ ነው። አፄ ፋሲልን በክፉነትና ከባድ ግብር በማስቀረት የሚያነሣ የቤተ ክርስቲያን ሰነድ ያጋጠመኝ ይህ ትርጓሜ ዳዊት ብቻ ነው። እርግጥ፥ ፈላስፋው ወርቄ/ዘርአ ያዕቆብ ስለ አፄ ፋሲለደስ ክፋት ብዙ ጽፎበታል፤ ግን እሱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሰው አልነበረም። ከባድ ግብር ለማስቀረት የሞከረ፥ በዚህም ሕይወቱን ያጣው አፄ ዘድንግል ነው።

በኢትዮጵያ የመንግሥት ሥርዓት

እንግዲህ፥ በኢትዮጵያ የመንግሥት ሥርዓት የንጉሥና የሕዝብ ግንኙነት የጌታና የባርያ ግንኙነት ነበር።መንግሥት አንድ ግለሰብ ሕይወቱን በሰላም እንዲኖራት እክል እንዳይገጥመው ዘብ ቋሚ (ማለት የግለሰብ አገልጋይ) መሆኑ ቀርቶ ተገልጋይ ሆነ። የሚገዛትን ሀገር እግዚአብሔር የሰጠው የግል ጒልቱ አደረጋት። ድጋፍ ለማግኘት ሎሌዎች እየሰበሰበ ከጥቅሙ አካፈላቸው። ካህናቱም ጥቅመኞች ስለሆኑ “እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጅህን አታንሣ” የሚለውን የሐዋርያውን ቃል ሰበኩ። ሕዝቡም ሃይማኖታዊና ኋላቀር ስለሆነ የንጉሥ አገልጋይ መሆን እግዚአብሔርን መታዘዝ መሆኑን ተቀበለው።

መንግሥት ንብረት ከሆነ ለልጅ ማውረስ ግድ ሆነ። ወራሹ “አልጋ ወራሽ” የሚል ቅጽል ወጣለት። ይህ ደግሞ ጉዳት ብቻ ሳይሆን ጥቅምም ነበረው።  ኃይለኞች ተነሥተው ለሥልጣ ሲሻኮቱ ተከታይ ማስጨረስን አስቀርቷል። ጨርሶ ግን አላስቀረውም፤ የንጉሥ ልጆች “እኔ እነግሥ፥ እኔ እነግሥ” በማለታቸው ብዙ ተከታይ አልቋል። መፍትሔው፥ አንዱን አንግሦ የቀሩትን ወደወህኒ መላክ ነበር። “ወህኒ” ልዑላኑ ይጋዙበት የነበረ ተራራ ስም ነው። ሌላው ደብረ አብርሃም ነው። ዛሬ እስር ቤት ሁሉ ልዑላኑ በሚታሰሩበት ተራራ ስም ወህኒ ይባላል።

ማን ንጉሥ እንደሚሆንና የንጉሡ ግዴታ ምን እንደሆነ ፍትሐ ነገሥቱ በግልጽ አስቀምጦታል፤

ወይኩን ንጉሥ ዘትሠይሞ እምአኃዊከ። ወኢይደሉ ከመ ትሢም ላዕሌከ ብእሴ ነኪረ ዘኢማእምን ከመ ኢያብዝኅ አፍራሰ ወኢአንስተ፥ ኢወርቀ ወኢብሩረ።

ወአመ ይነብር ዲበ መንበረ መንግሥቱ ይጽሐፉ መጽሐፈ አምላካዌ እምካህናት ከመ የሀሉ ኀቤሁ ያንብብ ኪያሁ በኑኀ መዋዕሊሁ ከመ ይትመሀር ፈሪሀ እግዚአብብሔር ፈጣሪሁ ወይዕቀብ ትእዛዛቲሁ ወይግበር ኪያሃ ከመ ኢይትዐበይ ልቡ ላዕለ አኃዊሁ ወኢይትገኃሥ እምሥርዓተ ሕግ ኢለየማን ወኢለጸጋም  ከመ ትኑኅ መዋዕሊሁ በውስተ ግንሡ ሎቱኒ ወለደቂቁ። ወይኩን አሚኖቱ ፍጹመ በእግዚአብሔር።

ከወንድሞችህ ማህል የምትሾመው (= የምትመርጠው) ንጉሥ ይሁን። ፈረስ (= ሠራዊት)፥ ሴት፥ ወርቅ፥ ብር  እንዳያበዛ፥ የማያምን እንግዳ ሰው በላይህ ላይ ልትሾም አይገባም።

ከመንግሥቱ ዙፋን ላይ ሲቀመጥ፥ አጠገቡ እንዲሆንና በዘመኑ ሁሉ እንዲያነበው፥ ፈጣሪውን እግዚአብሔርን መፍራት እንዲማር፥ ትእዛዞቹን እንዲጠብቅ፥ በወንድሞቹ ላይ  በልቡ እንዳይታበይባቸው፥ (ትእዛዞቹን) እንዲፈጽማቸው፥ ከሕግ ሥርዓትም ወደቀኝም ሆነ ወደ ግራ ውልፍት እንዳይል፥ የንግሡና የልጆቹ ዕድሜ  እንዲረዝም፥ በእግዚአብሔር እምነቱም ፍጹም እንዲሆን፥ ከካህናቱ ውስጥ (ዐዋቂዎች) አምላካዊ መጽሐፍ ይጻፉለት።

ይህን ሕግ የያዘው ፍትሐ ነገሥት ሦስት መቶ ዓመት ያህል አገልግሏል። ከዚያ በፊት የነበረው ሕግ መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፈ ሲኖዶስ ነበሩ። ሆኖም፥ በኢትዮጵያ መንግሥት የተቋቋመው ሕዝቡ እነዚህን መንፈሳዊ የሃይማኖት ሕጎች ከማወቁ በፊት ነው። ሕጉ የተፈጥሮ ሕግ የሚባለው ነበር። የተፈጥሮ ሕግ በራስ ማኅበር (ነገድ) ውስጥ በራስ ላይ ሲደረግ የሚጠላን አለማድረግ ነው። ክርስትና ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ ግን መንግሥቱ የክርስትና መንግሥት ሆነ። “ከወንድሞችህ ማህል የምትሾመው (= የምትመርጠው) ንጉሥ ይሁን፤ . . . አማኝ ይሁን” ማለት ክርስቲያን ይሁን ማለት ነው።

በዚህ ትእዛዝ መሠረት፥ ዓለማዊና መንፈሳዊ ወገኖች ሊቃውንት በጻፉት ሕግ የሚተዳደር መንግሥት  አቋቋሙ። ጳጳሱ ይቀባል፤ ንጉሡ ለቤተ ክርስቲያኗ ተአማኒነቱንና ሕዝብ ሳይበድል የሚገዛ  መሆኑን በመሐላ  ያረጋግጣል። ንጉሡና ጳጳሱ አንዱ ሌላውን እንዳይክድ ሁለቱም ማስፈራሪያ አላቸው፤ ንጉሡ የጦር ሠራዊት አለው፥ ጳጳሱ የመገዘት ሥልጣን አለው። ግን ንጉሡ የቤተ ክርስቲያንም አለቃ ሆኖም ይታያል። የሃይማኖት ውዝግብ ሲነሣ፥ ተከራካሪዎቹ ንጉሡን ፍርድ እንዲሰጥ ይጠይቁታል።

ከወንድሞችህ ማህል ሃይማኖት ያለውን አንግሥ” የሚለው፥ ማንገሥ የሕዝብ መብት መሆኑን ያመለክታል። ግን “የማያምን እንግዳ ሰው በላይህ ላይ ልትሾም አይገባም” ማለት፥ “ሌላ ሃይማኖት ያለው አይግዛህ” ማለት ነው። የተለያየ ሃይማኖት ያለው ሕዝብ የየትኛውን ሃይማኖት ተከታይ ያንግሥ?  ISIS የሚባሉት እስላሞች ችግርና አስቸጋሪነት ምንጩ ይሄ ነው። በዚህ ትእዛዝ መሠረት  የተለያየ ሃይማኖት ያለው ሕዝብ እንዳንድ ሕዝብ በአንድ መሪ ስር ሊኖር አይችልም። ሕጉ ተራ በተራ መንገሥን እንኳን አይፈቅድም። ምክንያቱም፥ ያንዱ ሃይማኖት ሰው በተራው ሲነግሥ፥ የሱ ዓይነት ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች አይቀበሉትም። ከተቀበሉት፥ “ሌላ ሃይማኖት ያለው አይግዛህ” የሚለውን አምላካዊ ሕግ መጣስ ሊሆንባቸው ነው።

መንግሥት ያለ ሃይማኖት ጣልቃገብነት

ከአፄ ዓምደ ጽዮንና ከአፄ ዘርአ ያዕቆብ ታሪክ እንዳየነው፥ የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ገዢዎች መፍትሔ እስላሞቹ በአንድ አካባቢ ስለሚኖሩ በራሳቸው ኢማም ወይም አሚር እንዲተዳደሩ፥ ክርስቲያኖች በሚኖሩበት አካባቢ የሚኖሩ እስላሞች ከክርስቲያን ሕግ ነፃ ሆነው እንዲኖሩ ማድረግ ነበረ። ግብር (ጂዝያ) እንኳን  እንዳይከፍሉ ተፈቅዶላቸው ነበር። ኢትዮጵያውያንን የሚያኮራ ፖለቲካ ነው።ግን ይኸም ሆኖ እስላሞቹ አልተደሰቱም። ነገሥታቱ የጋራ ሆነው ሳለ፥ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት ሲፎካከሩ፥ አንድ መስጊድ ሠራ የሚባል ንጉሥ አልተነሣም። ዛሬ የፖለቲካ ንግግራችን፥ “ተፈቃቅሮ በሰላም መኖር ታሪካችን ነው” እንላለን። የኢትዮጵያን የታሪክ ገጾች የሚያገላብጥ እውነታው ከዚህ የተለየ ሆኖ ያገኘዋል። በኢትዮጵያ ንጉሥ መሆን “ድንኳንቤቴ” ብሎ ዕድሜ ልክ የጦር አዝማች መሆን ነበር። የሃይማኖትና የጎሳ ጥርቃሞች ሆነን ሁሉን ያስደስታል የተባለው አስተዳደር ሁሉን ሳያስደስት ስለቀረ፥ ተጫረስን፤ ለጠላትም ተጋለጥን።

በአፄ ኃይለ ሥላሴ ተነገረ የተባለው አዲሱ ፍልስፍና “ሃይማኖት የግል አገር የጋራ” የሚል ነበረ፤ አልበቃም። የቤተ መንግሥትና የቤተ ክህነት ፍቺ ፍጹም ሊሆን አልቻለም። እንዲያውም፥ የኛ ዘመን ተማሪዎች ሁለቱን ተቋማት የአንድ ነገድ (የአማራ) ሀብት ሆነው አዩዋቸው። ያለ አንዳች ማስረጃና የሚያስከትለውን ጕዳት ሳያዩ፥ ሁለቱን ተቋማት ጥፋተኛ አድርገው፥ ጥፋታቸውን ሁሉ የአማሮች ሁሉ ጥፋት አደረጓቸው። የአማራው መንግሥት ለሀገር ግንባታ ያደረገው አስተዋፅኦ ተሰረዘ። በችጋር ያደ አማሮች ሁሉ ወንጀለኞች ተባሉ። ሁለቱ ተቋማት የአማሮች ከሆኑ፥ ሌሎቹ ነገዶችና ጎሳዎች፥ ሃይማኖቶችም በገዛ አገራቸው መንግሥትየለሽ ሕዝቦች ሆኑ። አሁን አሁን፥ ስሕተቱን ለማረም፥ “ጥፋቱ የገዢው መደብ እንጂ የአማራው ነገድ አይደለም” ማለት ተጀምሯል። ፍርዱ ከተሰጠና በሕዝቡ አእምሮ ከጸደቀ በኋላ፥ ይኸ ዓይነት እርማት ምንም የእምነት ለውጥ አያመጣም። ደግሞም እኮ፥ “የገዢው መደብ” ሲሉ፥ “ኦሮሞዎች፥ ጉራጌዎች፥ ወዘተ. የሌሉበት የአማሮች መደብ” ማለታቸው ነው። 

የዛሬው የፖለቲካ ችግራችን ይኼ የተማሪዎች ትንተና ነው። አፄ ምኒልክ በስንት ጥረት ወደቀድሞዋ ኢትዮጵያ የመለሷትን አገር ከመሠረቷ አናጓት። የተማሪዎቹ እንቅስቃሴ አንዱ ክፍል የሆነው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግምባር ሥልጣን ሲይዝ አንዱ ነገድ የበላይ ሌሎቹ ነገዶች የበታች የሚሆንበትን ሁኔታ ለማስወገድ መፍትሔው ነገዶች በሰፈሩበት ምድር ላይ ተከልለው ለየብቻቸው እንዲኖሩ ማድረግ ነው ብሎ በዓለም ታሪክ ያልተሰማ፥ በደቡብ አፍሪካ ተሞክሮ የከሸፈ ሥርዓት ዐወ። ኢትዮጵያ ሀገር መሆኗ ቀርቶ ሀገሮች ሆነች። ሥርዓቱ እንደማይሠራ አጥተውት ሳይሆን፥ በሥልጣን ላይ ለመኖር የሚያዋጣ ዘዴ መስሏቸው ነው። በጎ ሥርዓት አቋቋምንልህ ያሉት ሕዝብ በምርጫ 97 እነሱንም ሥርዓታቸውንም አሽቀንጥሮ ጣላቸው።

በዚህ ጊዜ የለበሱትን የበግ ቆዳ አውልቀው ተኵላነታቸውን አሳዩ። ለሕዝብ ሰጥተናል ያሉትን የመጻፍ የመናገር የመሰብሰብ ነፃነት መልሰው ወሰዱት። የአስቸኳይ ዐዋጅ ዐውጀው፥  ወታደራዊ አገዛዝ ዘረጉ፤ ዳግማዊ ደርግ ሆኑ።

ምን ይሻለናል?

ናፍቆታችን የኢትዮጵያ ሕዝብ በጻፈው ሕገ መንግሥት ተጠብቆና ሕጉን ጠብቆ፥ ረኀብ፥ በሽታ፥ ድንቁርና የሚወገዱበትን መንገድ እየፈለገና እያደረገ በነፃ የዲሞክራሲ ኑሮ መኖር ከሆነ፥ በቅደም ተከተል የሚፈጸሙ ጉዳዮች አሉ። ባለፉት አምሳ ዓመታት ውስጥ የተፈጸመው የፖለቲካ እንቅስቃሴ መንግሥት ማቋቋም የሕዝብ መብት መሆኑን አስተምሮናል። ብዙ ሰዎች የሚሉት፥ “የተማሪዎቹ እንቅስቃሴ ኮሚኒዝምን አመጣ” ነው። እውነት ነው፤ ግን ያመጣው ትልቁ ለውጥ የሥልጣን ምንጭ እግዚአብሔር መሆኑ ቀርቶ ሕዝብ መሆኑን ነው። አመፁ በእግዚአብሔርና በጡንቸኛ ላይ ነው። ከእንግዴህ ወዲህ፥ ኢትዮጵያን እንደ ቀድሞው፥ “እንድነግሥ እግዚአብሔር የመረጠው እኔን ነው”፥ ወይም፥ “ከማንም የበለጠ ጡንቻ ስላለኝ እኔ እገዛለሁ” የሚል ተንኮለኛ በሰላም አያስተዳድራትም። የሕዝቡ መንፈስ ነፃ ወጥቷል፤ ሥጋውንም በባርነት አያስገዛም። አሁን እንግዲህ ትችታችን “ሕዝብ እንዴት መንግሥት ያቋቁም” በሚለው ርእስ ላይ መሆን አለበት።

ከተያዘ ወምበር ላይ ለመቀመጥ የሚፈልግ ሰው፥ ወምበሩ በሕገወጥ መንገድ ተይዞ እንደሆነ፥ መጀመሪያ በወምበሩ ላይ የተቀመጠውን ሰው ማስነሣት የግድ ነው። ግን ከዚያ አስቀድሞ፥ ብዙ ሥራ መሠራት ይኖርበታል። መጀመሪያ  በወምበሩ ላይ የሚቀመጠውን ሰው መምረጥ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ያልተነጋገሩበት ትልቁ ችግር ይኸ ነው። ሁሉም፥ ወያኔን ጨምሮ፥ በዲሞክራሲ ያምናል። አንድ ጎሳ በነፃ ተነሥቶ፥ አሁን ያለውን ሥርዓት ቢወደው፥ ከዚያም አልፎ፥ እንደ ኤርትራ ተገንጥየ የራሴን አገር፥ የራሴን መንግሥት አቋቁማለሁ ቢል፥ ዲሞክራሲያዊው መልስ ምንድን ነው? አልተነጋገርንበትም፤ መቸም ዲሞክራሲን ሰብኮ ዲሞክራሲ ያመጣውን ኀይል መቃወም አይቻልም። የዲሞክራሲ አፍ አትገንጠል ይላል ወይስ አይልም።

ወያኔን ጥለው ሌላ መንግሥት ማቋቋም ያለባቸው በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምኑ ቡድኖች ብቻ ናቸው” እንላለን። በኢትዮጵያ አንድነት የማያምኑትን ቡድኖች በምን ዘዴ ነው የምናውቃቸው? ወያኔዎቹም “በኢትዮጵያ አንድነት እናምናለን” ይላሉ። የአሁኑን ክልል ወድደው፥ “በኢትዮጵያ አንድነት እናምናለን” የሚሉ ቡድኖችም አሉ። የኢትዮጵያ አንድነት ትልቁ ጠላት የክልል ፖለቲካ ሆኖ ሳለ፥ እንደዚህ ካሉ ቡድኖች ጋራ የኢትዮጵያን አንድነት መጠበቅ አይቻልም። የክልል ወሰን አንድን ኢትዮጵያዊ በፈለበት የኢትዮጵያ ምድር ላይ ሊኖር እንዳይችል ከአደረገ፥ ዓለምአቀፍ ወሰን (International boundary) እንጂ የውስጥ የወረዳ የአስተዳደር ድምበር አይደለም።

ስለዚህ፥ በኢትዮጵያ አንድነትና በዲሞክራሲ የሚያምኑ ቡድኖች የመጀመሪያ ሥራቸው የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት መጻፍ ነው። ስንዴው ከእንክርዳድ የሚለየው አዲሱሕገ መንግሥት በሚጻፍበት ጊዜ ነው። ሕገ መንግሥቱ ክልልን ይደመስሳል፤ አገሪቱን በራስገዝ ወይም በፌዴሬሽን ለማስተዳደር በሚመች መንገድ ይከፋፍላታል፤ የሕዝብን አንድነት ያጸድቃል። ኤርትራውያን ከኢትዮጵያ ጋር አንድ የሚሆኑበትን በር ክፍትና ማራኪ ያደርጋል። የቤተ ዘመዱ ጉዱ የሚታየው ያን ጊዜ ነው።

ከዚያ ቀጥሎ ዳግማዊ ደርግ ወምበሩን ሲለቅ ወደ ሕዝባዊ መንግሥት ለመሸጋገር የሚያስፈልጉት እርምጃዎች ይረቀቃሉ። መጀመሪያ መንግሥት ጠባቂ መንግሥት ማቋቋምና የተረቀቀውን ሕገ መንግሥት ሕዝብ እንዲያጸድቀው ማረግ ግዴታ ነው። ከኢትዮጵያ ለመገንጠ የሚፈልጉ ይኸንን ሕገ መንግሥት እንደማይቀበሉት የታወቀ ነው። ሆኖም፥ ሕገ መንግሥቱን ለማጽደቅ የሚቀርበው ፖለቲከኞች ሊገነጥሉት ለሚፈልጉ ሁሉ ጭምር መሆን አለበት።

የቤት ጠባቂው መንግሥት አባላት እነማን ይሁኑ? ግዴታና ኀላፊነቱ ምን ምን ይሆናሉ? ዘመኑስ ምን ያህል ይረዝማል? ጊዜያዊ ስለ ሆነ የነፃነቱን ትግል ሕገ መንግሥት ከመጻፍ ጀምሮ ያካሄዱት ቢመሩት ይመረጣል። የዚህ አመራር ዋናው ግዴታው ለውድድር ለሚቀርቡት ፓርቲዎች መንገዱን መጥረግ ነው።

ወያኔን ከወምበሩ ማስለቀቅ የሚጀምረው እነዚህ እርምጃዎች ተወስደው በአንድነት ስንቆም ነው። ይህ አንድነት በውጪ ሀገር የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያን እርዳታ ያስተባብራል። አንድ ድርጅት ለብቻው ታግሎ ሣልሳዊ ደርግ እንዳያቋቁም ያደርጋል።

ነገዶችና ጎሳዎች 

ከላይ ነካ አድርጌ ያለፍኩትን የነገዶችንና የጎሳዎችን ጉዳይ ኢትዮጵያንና እነሱን በመሆን መመልከት ያስፈልጋል። ወይንም  ከሁሉ አስቀድሞ፥ “ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝቦች” የሚሉት ስሞች የወጡት “Nations, Nationalities, peoples” የሚሉትን ለመተርጐም ከሆነ፥ መጀመሪያ በመተርጐም ምክንያት የተፈጸሙትን ሁለት ታላላቅ ስሕተቶች ማረም ያስፈልጋል። አንደኛ፥ አንድ የውጪ ቃል ወይም ስም የሚተረጐመው፥ አንድ እቃ ወይም አንድ ፅንሰሐሳብ ከነስሙ ከውጪ ሲመጣ ነው እንጂ፥ እኛ ዘንድ ላለ ነገር አይደለም። ለምሳሌ፥ “ወምበር” ከነስሙ እኛ ዘንድ ካለ፥ “chair” ለሚለው ስም መተርጐሚያ ቃል ፈልጉ አይባልም። “ነገዶችና ጎሳዎች” ከመባል ይልቅ “Nations and Nationalities” እንበላቸው ማለት ሳይቸግር ጤፍ ብድር ይሆናል።

ሁለተኛ፥ ነገዶችና ጎሳዎች በ“Nations and Nationalities” መተርጐም ሳይቸግር ጤፍ ብድር ብቻ ሳይሆን፥ “Nations and Nationalities” ላይ የሰፈረውን ጣጣ አብሮ ማምጣት ይሆናል። ያ ጣ እኮ ነው መፍትሔ ጠፍቶለት ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ በተወያየን ቍጥር ስናገላብጠው የምንኖረው። “Nations and Nationalities” እዚያው ሀገራቸው መንግሥት አላቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ነገዶች ከኢትዮጵያ ውጪ መንግሥት ያቋቋሙበት ዘመን አልነበረም። ኖሯቸው ከሆነ፥ በዘመነ መሳፍንት ሸዋ፥ ጐጃም፥ ትግሬ፥ ወሎ፥ አደል (አዳል) ውስጥ እንደተቋቋሙት አናሳ መንግሥታት ቢሆን ነው። ሁሉም ለኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የሚገብሩ የኢትዮጵያ ክፍል ነበሩ። ግራኝ ያመፀው እኮ “አልገብርም፥ በክርስቲያን ንጉሥ ስር የምትተዳደር አገር አናሳ መንግሥት ኢማም መሆን ያንሰኛል” ብሎ ነው እንጂ፥ ከቀይ ባሕር እስከ ህንድ ውቅያኖስ የተንሳፈፈው የአዳል ሀገር የኢትዮጵያ ግዛት አይደለም ብሎ አይደለም። ነገዶችና ጎሳዎች በ“Nations and Nationalities” ትርጐማ ጊዜ “ብሔር፥ ብሔረሰቦች” ስለተባሉ፥ እንደ “Nations and Nationalities” ተገንጥለን መንግሥት እናቋቁም ማለትን አምጥተው ታሪካዊቷን ኢትዮጵያ ውጥረት ላይ ጣሏት፤ መሠረቷን አናጉት። ታሪካዊት ያደረጓት የሁላችንም ወላጆች መሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ሲያቀርቡላቸው፥ “አታሳዩን” አሉ። “ሃይማኖታችሁን ለውጡ” የተባሉ መሰሉ።

የነገዶችና ጎሳዎች ፍላጎትና ሚና

ሚሲዮናውያን በደረሱበት ቦታ ሁሉ ያገኙትን ቋንቋ የጽሑፍ ቋንቋ ሲያደርጉት የኢትዮጵያ መንግሥት ሲያይ፥ የሀገሪቱን አንድነት የሚያሰጋና የመገናኛውን ቋንቋ (አማርኛን) ከመስፋፋት የሚገታ ስለመሰለው፥ ከአማርኛ በቀር ሌሎቹ በጽሑፍ እንዳይውሉ ከልክሎ ነበር። ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ ይሆናል እንጂ፥ መንግሥት ማድረግ  የነበረበት ሁለቱንም ቋንቋዎች እንዲያስተምሩ መጠየቅ ነበረ። አሁን እነዚህን ቋንቋዎች ከሚናገሩ አንዳንድ ፖለቲከኞች ዘንድ የሚሰማው ውሸት በቋንቋቸው እስከጭራሹም እንዳይናገሩበት ተከልክለው እንደነበረ ነው።

ማናቸውም የኢትዮጵያ ቋንቋ እንዳይሞት መጠበቅ፥ በጽሑፍም መዋል አለበት። መጻፊያውን ፊደል የሚመርጡት እነሱ ናቸው። ግን ብጠየቅ፥ አገር በቀሉን የኢትዮጵያ ፊደል እንዲመርጡ እመክራለሁ። በኢትዮጵያ ፊደል ላለመጻፍ የሚሰጠው ምክንያት ጥላቻን መሸፈኛ ነው።

ነገዶችና ጎሳዎች ምእመናንም በፖለቲካና በሀገሩ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚጫወቱት ትልቅ ሚና አላቸው። ግን ሚናቸው ማኅበራዊ ድርጅት (civic organization) ሆኖ ወገናቸውን ማገልገል እንጂ ብሔራዊ የፖለቲካ ፓርቲ አቋቁሞ አይደለም። የፓርቲዎች መሠረት አገርአቀፍነት ነው። የአማራ፥ የወላይታ፥ የሲዳማ፥ ወዘተ. ፓርቲ አገርአቀፍ ሊሆን አይችልም። ደግሞም እኮ፥ “የኔ ነገድ፥ የኔ ሃይማኖት ይግዛ” ማለት ሰብአትካትነት፥ ኋላ ቀርነት ከመሆኑ በላይ፥ የትኛውም ነገድ የሀገሪቱ አርባ በመቶ እንኳን ስለማይሆን፥ የነገድ ፓርቲ ምርጫ የማሸነፍ ዕድል የለውም። ግፋ ቢል የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ፓርቲ ቢያቋቁሙ ያሸንፉ ይሆናል። የሀገር ወዳዱ ምኞች መላ ኢትዮጵያውያንን የሚወክል ፓርቲ እንዲቋቋምና እንዲያሸንፍ መሆን አለበት።

በማኅበራዊ ድርጅት ግን ብዙ ሥራ ሊሠሩ ይችላሉ። ባህላቸውን (ቋንቋቸውንና ሃይማኖታቸውን) ያስፋፋሉ፤ የቀያቸውን ኢኮኖሚ ያዳብራሉ፤ መንግሥት ያላሟላውን የትምህርት፥ የጤና ጥበቃ፥ የመንገድ ሥራ ያሟላሉ። በምርጫ ጊዜ ድምፃቸውን ለሚፈልጉት ተወዳዳሪ ይሰጣሉ።

ናፍቆታችን የኢትዮጵያ ሕዝብ በጻፈው ሕገ መንግሥት ተጠብቆና ሕጉን እነሱም ጠብቀው፥ ረኀብ፥ በሽታ፥ ድንቁርና የሚወገዱበትን መንገድ እየፈለጉና እያደረጉ በነፃ መኖር የሚችሉት እነዚህን እርምጃዎች ሲወስዱ ነው።

በመጨረሻ፥ ኢሕአዴግ ያጸደቀውን ሕገ መንግሥት ጠጋ ብየ ሳጠናው የሚጠላ ሆኖ ሳላገኘሁ ቀረሁ። ሌላ ሕገ መንግሥት እንጻፍ ብሎ አዲስ ጭቅጭ ውስጥ ከማስነሣት፥ የሕዝቡ ሽብር መንፈስ እስኪረጋጋ ድረስ በጊዜው ባለው መንግሥት መተዳደሩ ይሻላል። ሕገ መንግሥቱ  አንደኛ፥ እመግቢያው ላይ ኢትዮጵያ  የብሔሮች፡ ብሔረሰቦች፡ ሕዝቦች አገር መሆኗን በይፋ ያውቃል፤ በእንግሊዝኛው nations, nationalities, and peoples ይላቸዋል። ጎሳዎቹንና ነገዶቹን ነው። የነሱ መኖር አይካድም፤ መኖራቸውን ማመኑም፥ “የሚታየው በዓይን ነው፥ የሚሰማው በጆሮ ነው” ብሎ እንደማመን ነው። ሁለተኛ፥ አገሪቱን በአንቀጽ 47 ከዘጠኝ የፌዴራል ክልል (States) ይከፍላታል ። አንቀጽ 39 የመገንጠል መብት የሚሰጠው ለእነዚህ በክልሎቹ ውስጥ (within the States) ለሰፈሩት ጎሳዎችና ነገዶች እንጂ፥ በጠቅላላው ለክልሎቹ አይደለም (not for the States)። ሕገ መንግሥቱን  ልጥቀስ፤

1. ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፡ ብሔረሰብ፡ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው። 4. የብሔር፡ ብሔረሰቦች፡ ሕዝቦች የራሱን ዕድል በራስ የመወሰን እስከመገንጠል  መብት ከሥራ ላይ የሚውለው (ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው።)

) የመገንጠል ጥያቄ በብሔር፡ በብሔረ ሰቡ ወይም በሕዝቡ የሕግ አውጪ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ የድምፅ ድጋፍ ተቀባይነት ማግኘቱ ሲረጋገጥ፡”

አንደኛ፥ እነዚህ ጎሳዎች ስንት እንደሆኑ አይታወቅም። ጎሳዎች የሌሉበት ክልል ስለሌለ፥ በየክልሉ ተፈልገው ቢቆጠሩ ወደ ሰማንያ ይደርሳሉ ይባላል። ሁለተኛ፥ ከሰማንያዎቹ ጎሳዎችና ነገዶች አንዳቸውም በሁለት ሦስተኛ ውሳኔ የሚያሳልፍ  “የሕግ አውጪ ምክር ቤት” ያለው የለም።

በመጨረሻ፥ አንቀጽ 41.1. እንዲህ ይላል፤

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት አለው። (እንግሊዝኛው የበለጠ ግልጽ ነው፤ “Every Ethiopian citizen has the right to engage freely in economic activity and to pursue a livelihood anywhere in the national territory.”)

በሕገ መንግሥቱና በሕዝብ መካከል አለ መግባባት የተፈጠረው የስያሜ ቃላት ባለመስተካከላቸው ነው። ዋናው መደንቅፍ “ክልል” የሚለው ስያሜ ነው። “ክልል” ሲባል  አንድ ክልል አጥር ሆኖ በውስጡ የሚኖሩ ዜጋዎች የግል ንብረት ያስመስላል። ልክ ማዘጋጃ ቤት የከተማ ቦታ ዳር ድምበር ከልሎ፥ ካርታ አውጥ  ለአንድ ሰው እንደሚያስከብር። ሐሳቡ ይኼ እንዳልሆነ ሁለት ነጥቦች ይመሰክራሉ፤ አንደኛ፥እንግሊዝኛው “States” ማለቱ፣ ሁለተኛ፥ በያንዳንዱ ክልል ውስጥ “ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች” መኖራቸውን ማወቁ። ስማቸውን መልአክ ሳወጣው ቀርቶ ነው እንጂ፥ ክልሎች ብሔራዊ የአስተዳደር ክፍሎች፥ ራስገዝ ግዛቶች ናቸው።  ሁኔታው ይህ ከሆነ፥ ጥያቄያችንን እናስተካልክ፤ “ወደጥንቱ ወደታሪካዊው አከፋፈል እንመለስ። ይኸም ካልሆነ፥  እስኪሆን ድረስ ያለው ሕገ መንግሥት ይከበር።”

  ጌታቸው ኃይሌ

ሰኔ 2010 ..

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.