“የኢትዮጵያ የጤና ሁኔታ ዳሰሳ” (ገብርኤል ዳንኤል)

የኢትዮጵያ ቀደምትና ጊዜያዊ የጤና ሁኔታ ዳሰሳ

ገብርኤል ዳንኤል

.

.

መግቢያ

ይህ ጤናን አስመልክቶ የቀረበ ጽሑፍ ለመንደርደሪያና አንዳንድ ሐሳቦችን ለመዳሰሻና ወደፊት ጥልቀት ባለው መልክ መንግሥት፣ የግሉ ዘርፍ፣ የአጋር ድርጅቶች፣ ባለድርሻዎች፣ የትምህርትና ጥናት መአከላት፣ ምሁራን ወዘተ… ትኩረት እንዲሰጡት እንጂ በአጠቃላይ የጤናን ሁኔታ የሚገልጥ ወይም የሚገመግም አይደለም። ጽሑፉ በአብላጫው የዳሰሰው ተስፋ ሰጪ የሆኑትን አዎንታዊና ጠቃሚ ናቸው የሚባሉትን ክንውኖች፥ እስካሁን የተገኙትን ውጤቶች ሊያስተጓጉሉ ይችሉ ይሆናሉ የሚባሉትን ደንቃራዎች፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን የጤና ሂደት ከታሪክ ማስታወሻ በአጭሩ በመጥቀስ ነው።

እንደ ዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ገለፃ፣ ጤና ማለት የተሟላ ሁለንተናዊ የሰውነት፣ የአእምሮና የኅብረተሰብአዊ ደኅንነት እንጂ በግንጥሉ የበሽታ ያለመኖር ክስተት ብቻ አይደለም ይላል። በአኃዝ የሚታዩ የጤና መለኪያ መስፈርቶችም በተናጠል የእድገት ማሳያ ሊሆኑ አይችሉም። የኑሮ ደረጃ ዝቅተኝነት፣ ፅዳት ጉድለት፣ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት፣ የሕይወት መሠረታዊ ፍላጎቶች እንደ ምግብ፣ ውሃና መኖሪያ ቤት በብቃት አለመሟላት ወዘተ… የኢትዮጵያን የጤና ሁኔታ በዝቅተኛ ደረጃ ከሚገኙ አገሮች ጎራ ውስጥ አስቀምጧታል።

የ2008 ዓ.ም የዓለም መንግሥታት የሰው ልማት ጠቋሚ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ብታሳይም፣ በጣም ድኀ ከሚባሉት 188 ሀገራት 174ኛ ዕርከን ላይ ትገኛለች። የድኃነት መጠን በአለፉት ጥቂት ዓመታት ቢቀንስም፣ እንደ 2005ዓ.ም. ምእተ ዓመት የልማት ግብ ዘገባ የኢትዮጵያ አንድ አራተኛው (ወደ 25 ሚሊዮን የሚጠጋው) ሕዝብ ከድኅነት የተነሣ መሠረታዊ ፍላጎቱን ለማሟላት የማይችል ነው።

ኢትዮጵያ አሁን የተያያዘችው ራሷን ከድኅነት ለማላቀቅና ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ራሷን ለማሰለፍ እንደዋንኛ አቅጣጫ የወሰደችው ኢንዱስትሪና ዘመናዊ ግብርናን ቀይሳ የተለያዩ ዕቅዶችን ነድፋ ተግባራዊ ማድረግ ነው። በዚህም ረገድ የጤና ፖሊሲና የጤና ዘርፍ መርኃ ግብር በመንደፍ የጤና መሠረተ ልማቶችን ለማስፋፋትና የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ለማጠናከር እየሠራች ትገኛለች። ኢትዮጵያ እነዚህን ዕቅዶች ለማሳካት ዓለም አቀፍ የጤና አጋርነትና ተመሳሳይ ስምምነቶችን በመፈረም የውጭ ለጋሽ አገሮች እርዳታዎች ከፍተኛ ተጠቃሚ ሆናለች። ለምሳሌ በ2005 ዓ.ም. ብቻ የተጣራ ኦፊሴል የእድገት እርዳታ ወደ 38 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር አግኝታለች።

የሀገር በቀል ሕክምና

ኢትዮጵያ ለዘመናት የምትጠቀምባቸው በርካታ ሀገር በቀል የባሕል መድኃኒትና ሕክምና ተመክሮዎች እንዳሉ የሀገርና የውጭ ሀገር ታሪክ አዋቂዎች ዘግበዋል።  የሀገር በቀሉ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጠው በዕፅዋት፣ በመንፈሳዊ፣ በእሽታ፣ በጠበል ወዘተ… ባተኮረ መንገድ ነው። በኢትዮጵያ ወደ 1,000 የሚጠጉ የመድኃኒት ዕፅዋት ዓይነቶችና ወደ ሰማንያ ሺህ የባህል ህክምና አዋቂዎች አሉ ይባላል። የኢትዮጵያ መልክአ ምድር አቀማመጥና የአየር ንብረት ተስማሚነት ለበርካታ ዕፅዋት መኖርና ልዩ ጠባይ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ።ብዙ ዘመናዊ መድኃኒቶች የሚገኙት ከዕፅዋት ስለሆነ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ የምታደርገው አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚታይ መሆን የለበትም። የዘመናዊ ሕክምና አቅርቦት በስፋት አለመኖር፣ የሕክምና ዋጋ ውድነት እና የሕዝቡ ግንዛቤ ዝቅተኝነት የባህሉ የሕክምና ዘዴ አሁንም ወደ 80% የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ አለኝታ እንዲሆን አድርጎታል። ለዚህም ነው መንግሥት ለዚህ ዘርፍም ትኩረት መስጠት ያለበት።እነዚህ በተገቢው መንገድ ተጠንተውና ድጋፍ ተደርጎላቸው፣ ከዘመናዊው ሕክምናና መድኃኒት ጎን ለጎን በመሆን ለሰፊው ሕዝብ አገልግሎት መስጠት እንዲቀጥሉ መደረግ ተገቢ ነው።

 የዘመናዊ ሕክምና በኢትዮጵያ ታሪካዊ ዳሰሳ

የባህሉ ሕክምና አስተዋጽኦና ጠቃሚነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የጥንት የኢትዮጵያ ነገሥታት ዘመናዊ ሕክምናን ለመጠቀምና ለማስፋፋት ባላቸው ፍላጎት የተለያዩ ሙከራዎችን ያደርጉ እንደነበር ታሪክ ያስታውሰዋል። ለአብነትም በንጉሥ ልብነ ድንግል ጊዜ በ1538 ዓ.ም. ነበር ጉልህ የውጭ ሕክምና ለመጀመርያ በኢትዮጵያ የታየው። ይህ መሰሉ ሕክምና የሚሰጠው በተለያዩ የሀገር ጎብኚዎች ሲሆን በዐፄ ቴዎድሮስና በዐፄ ዮሐንስ ጊዜም ታይቷል። እንዲህም ዐይነቱ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ለንጉሡ፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለባለሟሎቻቸው ነበር። በስፋትና ሕዝባዊ በሆነ መልኩ ዘመናዊ ሕክምና በኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው በዳግማዊ ምኒልክ ጊዜ በሩስያኖች የቀይ መስቀል ቡድን በ1888 ዓ.ም. በተመሠረተው የድንኳን ሆስፒታል ሲሆን፣ በዚሁ ስፍራ ነበር በ1901 ዓ.ም. ቋሚ የዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል ተሠርቶ እስከ ዛሬም በዚሁ ቦታና ስም አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው። በመቀጠልም ከተፈሪ መኮንን አልጋ ወራሽነት ተጀምሮ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተብለው ንጉሠ ነገሥት ከሆኑ በኋላ አንጋፋ የሚባሉት ሆስፒታሎች ተመሥርተው ይሄው ከስድሳ ዓመታት በላይ ከፍተኛ አግልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። ከነዚህም አንጋፋ ሆስፒታሎች ውስጥ እነ ራስ ተፈሪ መኮንን (ዶክተር ላምቤ በጉለሌ ፓስተር እንስቲትዩት በመባል የሚታወቀው ስፍራ ላይ የነበረው አሁን የሌለው)፤ ቤተ ሳይዳ (የበፊቱ ኃይለ ሥላሴ የአሁኑ የካቲት 12) ፤ የራስ ደስታ፤ የልዕልት ዘነበወርቅ ( አለርት የመላ አፍሪካ የስጋ ደዌ ጥናትና ማሰልጠኛ ተቋም የሚገኝበት)፤ የደጃዝማች ባልቻ፤ የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ የእናቶች ሆስፒታል፤ የጋንዲ ማዋለጃ ሆስፒታል፤ ብሎም የልዕልት ፀሐይ (የአሁኑ ጦር ኃይሎች) ሆስፒታል፤ የልዑል መኮንን (የአሁኑ ጥቁር አንበሳ) ሆስፒታል፤ የቅዱስ ጳውሎስ፤ የቅዱስ ጴጥሮስ የሳንባ ሆስፒታል፤ የፖሊስ፤ ቤላ የጦር ሠራዊት፤ የቅዱስ አማኑኤል የአእምሮ ህመምተኞች ወዘተ… ሆስፒታሎች ይገኙባቸዋል። በድሮዎቹ ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማዎች ውስጥም ነባር የሆኑ ሆስፒታሎች ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጡ እስካሁን ይገኛሉ። በአሁኑ ጊዜ በየክልሉ አዳዲስ ሆስፒታሎች እየተስፋፉ ሲገኙ፣ ጎልቶ የሚታየው ክስተት በርከት ያሉ የግል ሆስፒታሎች ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገሪቱ መስፋፋታቸው ነው።

የኢትዮጵያ ሕክምና ሙያተኞች ስልጠና

የሕክምና ባለሙያዎችን በሚመለከት ሁለት የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ሐኪሞችን ማስታወስ ይገባል። የመጀመሪያው በሕፃንነቱ በእንግሊዞች ከዐፄ ቴዎድሮስ ሞት በኋላ ተወስዶ የሕክምና ትምህርቱን በህንድና በእንግሊዝ አገሮች ተምሮ ዶክተር ወርቅነህ እሸቴ በ1890 ዓ.ም. በዐፄ ምኒልክ ጊዜ ኢትዮጵያ ተመለሰ። ወርቅነህ ባሳደጉትና ባስተማሩት ሁለት የእንግሊዝ ኮለኔሎች ስም ዶክተር ቻርለስ ማርቲን ተብሎ ይታወቅ ነበር። ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ የዐፄ ምኒልክ ሐኪም በመሆንና የአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ልዩ አማካሪ ሆኖ ከማገልገሉ በስተቀር በአስተዳደር ሥራ ተመድቦ አዛዥ ተብሎ የጨርጨር አውራጃ ገዥ ሆኖ ይሠራ ነበር።

ሁለተኛው ለትምህርት አሜሪካ ተልኮ በኦሃዮ ዩኒቨርሲቲና ሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ በሕክምና የተመረቀው ዶክተር መላኩ በያን ነበር። መላኩ የኃይለ ሥላሴ ሐኪምና  ልዩ አማካሪ ሆኖ ከመሥራቱ በስተቀር፣ ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ኃይለ ሥላሴን ተከትሎ ከሀገር በመሰደድ በሐኪምነት፣ በልዩ ጸሐፊነትና፣ በአስተርጓሚነት ከፍተኛ አገልግሎት ከመስጠቱም በላይ የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ቢሮችን በመክፈት፣ ጋዜጣን በማዘጋጀት፣ ኢትዮጵያን ከጣልያን ወረራ ለማውጣት የኢትዮጵያን የዓለም ፌዴሬሽን በማቋቋም ከታወቁት የጥቁር ሕዝቦች ታጋዮች እንደ ማረከስ ጋርቬይ ካሉ ታዋቂ ሰዎች ጋር ፀረ ወረራ የትግል አስተዋፅዖ አድርጓል። ወርቅነህ በ86፣ መላኩ በ40 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተሰናበቱ። እነዚህን ሁለት ፈር ቀዳጅ ባለሙያተኞች በመከተል በሙያቸው፣ በአስተማሪነታቸውና በአገልግሎታቸው አንቱ የተሰኙ የተወሰኑ ሐኪሞችን ቀጥሎ መጥቀስ ለትውስታ ያህል ነው። በተለያዩ ሀገራት [አብዛኛው በቤሩት] ሠልጥነው ኢትዮጵያ ተመልሰው ከሠሩት መካከል እነ ፕሮፌሰር/ዶክተር አሥራት ወልደየስ፣ አዱኛ መኮንን፣ ታዬ መኩሪያ፣ ጳውሎስ ቀንዓ፣ ማለደ ማሩ፣ ዊዳድ ኪዳነማርያም፣ ረዳ ተክለሃይማኖት፣ ተክለፅዮን ወልደማርያም፣ ጴጥሮስ ሃድጉ፣ ዕደማርያም ፀጋ፣ ደምሴ ሀብቴ፣ ነብያት ተፈሪ፣ ባዩ ተክሌ፣ ጀማል አብዱልቃድር፣ ፍቅረ ወ/ጊዮርጊስ፣ ፍቅሬ ወርቅነህ፣ ጀነራል ግዛው ፀሐይ፣ በቀለ አስፋው ወዘተ… ይገኛሉ።

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያና በተለያዩ የውጭ ሀገራት የታወቁ ሐኪሞች የሀገራቸውን ስም እያስጠሩና ሰፊ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ከላይ የተጠቀሱት አንጋፋ ሐኪሞች ውጤቶች ናቸው። የሕክምናና የጤና ስልጠና በኢትዮጵያ በ1927 ዓ.ም. በዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል የጤና ረዳቶችን፣ የፋርማሲና ላቦራቶሪ ቴክኒሺያኖችን በማሰልጠን መጀመሩ ይነገራል። በሽታን በመከላከልና ሕክምናን በመስጠት ጉልህ ሚና በኢትዮጵያ የተጫወተው ደግሞ በ1946 ዓ.ም. በአሜሪካ መንግሥት እርዳታ የተቋቋመው የጎንደሩ የጤና ጥበቃ ኮሌጅ ነበር። ይህም ሁለገብ የጤና መኮንኖችን፣ የገጠር የኅብረተሰብ ነርሶችንና ሳኒቴሪያኖችን በማሰልጠን በመላው የኢትዮጵያ ገጠሮች በጤና ጣቢያዎች ደረጃ በቡድን በማሰማራት ከፍተኛ ሚና ከመጫወቱም አልፎ ለሌሎች ታዳጊ ሀገራት ተምሳሌት ሆኗል።

የወታደራዊ ደርግ መንግሥት ይህ ኮሌጅ ወደ ሐኪሞች ማሰልጠኛ ተቀይሮ የጤና መኮንኖችን ማሰልጠን እንዲቋረጥ አድርጎ የነበረው አሁን ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እንደገና ተፈላጊነቱ ታምኖበት በመንግሥት ስልጠናው እንዲቀጥል ሆኗል። የመጀመሪያ የዶክተሮች ማሰልጠኛ ኮሌጅ በ1956 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሲመሠረት፣ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ምሩቆች የሕክምና ትምህርታቸውን በቤሩት አሜሪካን ዩኒቨርሲቲ አገባደው ለአንድ ዓመት በኢትዮጵያ በተመሠርተው ኮሌጅ ከሰለጠኑ በኋላ ተመርቀው ሥራ ጀመሩ። የመጀመሪያው የመድኃኒት ቅመማ ፋርማሲ ትምህርት ቤት የተከፈተው ደግሞ በ1954 ዓ.ም. ነበር። የአዲስ አበባውን ሕክምና ኮሌጅ ተከትለው የተቋቋሙት የጎንደሩና የጅማው ኮሌጆች ናቸው። በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ በአጠቃላይ 28 የመንግሥትና 8 የግል የሐኪሞች ማሰልጠኛ ኮሌጆች እንዳሉ ይታወቃል። በአንፃሩ የተወሰኑ ምሩቆች ወደ ሌላ ሀገራት መፍለስ፣ የመማሪያና የመገልገያ ግብአቶች አለመሟላት፣ የጥራት ጉዳይ የሚያሳስቡ የጤና ባለሙያተኞች ተግዳሮቶች ናቸው። ያለውን የምሩቃን ቁጥር በተለያዩ ዓመታት እንይ ቢባል፣ ከ1968 እስከ 1980 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 148 ሐኪሞችን ስያስመርቅ በ2003 ዓ.ም. ብቻ ከሃያ እጥፍ ገደማ በማሳደግ ወደ 2,500 አስመርቋል።  አስከ 1998 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ፣ ጎንደርና ጂማ ኮሌጆች ብቻ 3,728 ተመርቀዋል። ይህ እምርታ የሀገሪቱን ፍላጎት በሙሉ ባያሟላም መልካም የሚባል ዕድገት መሆኑ አያነጋግርም።

የኢትዮጵያ የጤና አወቃቀርና የስኬት መስፈርቶች 

የኢትዮጵያ የጤና አወቃቀር በሆስፒታል፣ በጤና ጣቢያና በጤና ኬላ ላይ የተመሠረተ ነው። በአሁኑ ጊዜ አቅርቦትን በማስፋት ደረጃ የተወሰደው እርምጃ በያንዳንዱ የሀገሪቱ ቀበሌዎች ሁለት ሁለት ሴት የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች አሰልጥኖ በማሰማራትና የሚሰሩበትንም የጤና ኬላዎች በህብረተሰቡ ዕርዳታ በመገንባት ነው። በአጠቃላይ በስምሪት ላይ ከ38,000 በላይ የጤና ኤክስቴንሽን ደሞዝተኛ ሠራተኞችና 16,000 የሚሆኑ የጤና ኬላዎች አሉ። እነዚህን የሚረዱና ህብረተሰቡን የሚያስተባብሩ ደግሞ 30,000 የሚሆኑ “የእድገት ወታደሮች” ተብለው የሚታወቁም አሉ። በዚህ መዋቅር መሠረት 17 የሚሆኑ የጤና አገልግሎት ፓኬጆች ሲኖሩ ትኩረታቸውም የእናቶች፣ የሕፃናት፣ የክትባት፣ የተላላፊ በሽታዎች ቁጥጥር፣ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና፣ የስነ ምግብ ወዘተ አገልግሎቶች ይገኙበታል። የዚህ ዓይነቱ ገጠር ተኮር አገልግሎት የተለያዩ የጤና ምእተ ዓመት የልማት ግቦችን ለማሳካት ኢትዮጵያ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ በርካታ ማስረጃዎች እንዳሉ ይታወቃል። ይህ ቁጥር ወደ 105 ሚሊዮን ሕዝብ ባላት ኢትዮጵያ በቂ ነው ሊባል አይችልም። ብዙ መሠራት እንዳለበትና የነዚህ መስፈርቶች ማደግ፣ ዘላቂነታቸውና ጥራታቸው ላይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

በተባበሩት መንግሥታት የምእተ ዓመቱ የልማት ግብ እርምጃዎች ግምገማ መሠረት፣ ኢትዮጵያ የሕፃናት ሞት፣ ኤችአይቪ ኤድስና የወባ በሽታዎችን አስመልክቶ ከምእተ ዓመቱ የልማት ግብ ለመድረስ በምትችልበት ሁኔታ ላይ ትገኛለች። የ2008ቱ የኢትዮጵያ ስነ ሕዝብ እና ጤና ጥናት እንደሚያሳየው በአራስነት የሚሞቱ ጨቅላዎች ቁጥር ከ97 ሞት (ከ1,000 ውስጥ) በ23 ዓመታት ወደ 48 ዝቅ ሲል፣ ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ሞት ከ166 ወደ 67፣ የእናቶች በእርግዝና እና በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ ከ871 ወደ 412 (ከ100,000 በህይወት ከሚወለዱ ሕፃናት ውስጥ) ዝቅ ብሎአል። እነዚህ የመቀነስ ሁኔታ ቢያሳዩም ከሌሎች ታዳጊ ሀገራት ሲወዳደር ብዙ እንደሚቀረውና የወሰደው ጊዜም ረጅም ከመሆኑ አንፃር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መፋጠን እንደሚገባው ግልፅ ነው። በሕፃናት ተናጠል ክትባትም ጥሩ መሻሻል ቢታይም፣ የሁሉም መሠረታዊ ክትባቶች ሽፋን ግን 39% ብቻ ነው የደረሰው። የሕፃናትና እናቶች ሞት መቀነሱ የተጠበቀ ሆኖ፣ በዓመት የሚሞቱት ቁጥር ከፍተኛነት አስደንጋጭና፣ አሳሳቢ ክስተት ነው። በተለያዩ በፖለቲካ ወይም በአደጋ ምክንያት ይህን ያህል ሰው ሞተ ቢባል ብዙ ግርግርና ቁጣ ያስነሳል። ነገር ግን በነዚህ የተነሳ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ በየዓመቱ የሚሞቱ ሕፃናትና እናቶች መኖራቸው እየታወቀ እንደ ተራ ቁጥር ሆኖ መወሰዱ ምን ያህል የትኩረት ማነስና አጣዳፊነቱ ላይ ቸልተኝነት ዝንባሌ እንዳለ ጠቋሚ ነው።

ጤናን የሚያጫጩ ክስተቶች

ጤናን ጎጂና እስካሁን የተገኙ አዎንታዊ እድገቶችን የሚያጫጩ ክስተቶች በአሳሳቢ ደረጃ እየተስፋፉ ይታያሉ። ለምሳሌ የጫት፣ የሺሻ ወይም ሁካ ፣የሲጃራ፣ የአልኮል፣ እንደ ሃሺሽና፣ እንደ ኮኬን ያሉ ጠንካራ የአደንዛዥ ዕፆች (ድረጎች) አጠቃቀም እያደገ የመጣና በጣም አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ ነው። እነዚህ ጎጂ ልማዶች ለነጋዴውና ለመንግሥት የገቢ ምንጭ ስለሆኑ፣የነዚህን ምርት፣ዝውውርና መጠቀም ለመቀነስ፣ ለመቆጣጠርም ሆነ ለማቆም የሚደረገው ጥረት እጅግ ደካማ ነው። መንግሥትም ሆነ ብዙው ተማረ የሚባለው ክፍል በነዚህ ተጠቃሚ ስለሆነ እምብዛም ተቆርቁሮና ጉዳቱን ተገንዝቦ አቋም ወስዶ ተገቢውን የችግር መፍትሔ አስተዋፅኦ ከማድረግ ይልቅ ዝምታን የመረጠ ይመስላል። ጫት በደርግ ዘመን የባለሥልጣናት ሚስቶች የንግድ ዘርፍ እንደነበር ሲነገር፣ አሁን ደግሞ በኢህአዴግ ዘመን ጫትን ከቡና አኳያ በማሰለፍ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ አስገኝ አድርጎ ይደግፈዋል። በኢትዮጵያ ጫት በባህላዊና በእምነቶች ዙሪያ ለበርካታ ዘመናት ጥቅም ላይ እንደሚውል ይታወቃል። እነዚህ አጠቃቀሞች እንደተጠበቁ ሆነው፣ በአሁኑ ጊዜ ግን በመጠንም በምክንያትም ሌላ ግንዛቤ በመውሰድ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እየሄደ እንዳለ መገንዘብ አያዳግትም። በጫት ውስጥ የሚገኙ ዋንኛ ንጥረ ነገሮች እንደ ካቲን፣ ካቲኖን ያሉ ንቃትን ይሰጣሉ ከሚባሉ ኢስቲሙላንት መድኃኒቶች ውስጥ ይፈረጃሉ። የጫት ጎጂ ገፅታዎች እንደ አጠቃቀሙ ብዛት መጠን የእንቅልፍ ማጣትን፣ የስነልቦና መታወክን፣ የወሲብ ስንፈትን፣ የምግብ ፍላጎት ማጣትን፣ የሰውነት መጫጫትን፣ የሆድ ዕቃ ቀውስን፣ የአፍ በሽታን፣ አንዳንዴም የአፍ ውስጥ ካንሰርን እንደሚያመጣ አንዳንድ ጥናቶች ሲያሳዩ፣ መጠነኛ ጥቅም አለውም የሚሉ ጥናቶች አልጠፉም። ጥቅምና ጉዳቱን በሚገባ ለመገንዘብና የጫት ልማድን ለመቀነስም ሆነ ለመቆጣጠር ሃላፊነት የተጎናፀፈና ሚዛናዊ ምርምርና ጥናት ግድ ይላል። የጫት ጎጂነት በዓለም የጤና ጥበቃ ድርጅት ተወስቷል። በቅርቡ በርካታ የአውሮጳ ሀገራት አሜሪካም ጭምር የጫትን ጎጅነት በመገንዘብና ሕዝባቸውን ለመታደግ የጫትን ማምርት፣ ማዘዋወርና መጠቀምን ሕገ ወጥ አድርገዋል። በአንፃሩ በኢትዮጵያ ብዙ የጫት ማብቀያ፣ መሽጫ መደብሮችና የመቃሚያ ቦታዎች (ትምህርት ቤቶች፣ የጤና መዋቅሮች፣ይባስም ብሎ ቤተ እምነት አካባቢም ጭምር) መስፋፋት ይታያል።

ሺሻን በሚመለከት፣ ሺሻ ከሲጃራ ማጨስ የተሻለ መሆኑንና ጉዳቱም አነስተኛ ተደርጎ ሲነገር ይሰማል። ሃቁ ይህ ሳይሆን፣ ሺሻ ከሲጃራ የባሰ ጎጅነት ሊኖረው እንደሚችል መገንዘብ ተገቢ ይሆናል። የሲጃራ ጭስ በርካታ ጎጂ ንጥረ ነገሮች አሉት። ከነዚህም ኒኮቲን፣ የተለያዩ ካንሰር የሚያመጡ ኬሚካሎች፣ ካርቦን ሞኖክሳይድ ወዘተ ይገኙበታል። የሺሻ አጫጫስ በአንዴ ረዘም ላለ ጊዜ ስለሚሆን የንጥረ ነገር ብዛትና አይነት ሲጃራ ከማጨስ ጋር ሲወዳደር ወደ ሰውነት ውስጥ የሚገባው የሺሻው ጭስ እንደሚበልጥ ጥናቶች ያሳያሉ። ሺሻ መሳቢያውንም አንድ ሰው ተጠቅሞ ሌላው ተቀብሎ ስለሚጠቀም በሽታን ለማስተላለፍ አመች መንገድ ይሆናል። ስለዚህም ሺሻ ከሲጃራ ጎጂነቱ ሊያይል ይችላል ማለት ነው። መንግሥት የሺሻ ቤቶችን ለመዝጋት ጥረት ቢያደርግም፣ ተገቢው ትምህርትና ግንዛቤ፣ ሕግና ተፈፃሚነቱ ካልተረጋገጠ ውጤቱ አጥጋቢ አይሆንም። በትግራይና ጋምቤላ ክልሎች ጫትን ለመቆጣጠር ተደርጎ የነበረውና የከሸፈው ሙከራ ለዚሁ ጥሩ ምሳሌ ነው።

ጤናን የሚያውኩ የእድገት ሂደቶች

ኢትዮጵያ አሁን የተያያዘችው ራሷን ከድኅነት በማላቀቅ ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ ስትቆርጥ ዋንኛው አቅጣጫ እንዱስትሪና ዘመናዊ ግብርና መሆኑ ተጠቅሷል። እነዚህ የእድገት እርምጃዎች፣ ግዙፍና መካከለኛ ማምረቻዎችን ማቋቋም፣ ግድቦችን መገንባት፣ መስኖን ማስፋፋት፣ ማዳበርያንና ፀረ ህዋስ ንጥረ ነገሮችን መጠቀም ወዘተ… ላይ ያተኮረ ነው። ከጤና አንፃር እነዚህን በመተግበር ጊዜ የሚወጡ አላስፈላጊ ውጤቶች አካባቢን ብሎም ህብረተሰቡን የመበከል ጎጂ ጎን ሊኖራቸው ይችላል። ከዚህ በፊት በተለያዩ ሀገራት ከነዚህ ዓይነት ክስተቶች የተነሣ የበሽታ መስፋፋት (እንደ ቢላርዚያ እና ወባ)፣ የአየር፣ የውሃ፣ የአፈር፣ የከርሰ ምድር ህይወት ጉዳት ታይተዋል። በኢትዮጵያ የአበባ እርሻ በተስፋፋበት ወቅት የተከሰተውና የቆዳ ፋብሪካ ፍሳሾች ያስከተሉት የአካባቢና የወንዞች ብክለት የቅርብ ጊዜ ትዝታዎቻችን ናቸው። መንግሥት ለእንደነዚህ ዓይነት ጉዳዮች ጥንቃቄ፣ጥናት፣ ሕግና፣ ቁጥጥር ላይ ትኩርት ካልሰጠ በጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉና እስካሁን የተገኙ ውጤቶችን የሚጎዳ መሆኑ አይቀርም።

ሌላው ጤና ላይ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ተፅእኖ የሚያሳይ ሁኔታ ቁጥጥር የጎደላቸው፣ ዕድሜያቸው ያበቃ፣ ጥራታቸው ያልተረጋገጠ፣ በሙስና የሀገር ድንበር ጥሰው የሚገቡ መድኃኒቶች፣ የጤና መገልገያዎች፣ ምግቦች፣ መጠጦች ወዘተ… መኖራቸው ነው። እነዚህ ጥቅም አልባ ከመሆናቸው በስተቀር፣መጠኑና ዓይነቱ የማይታወቅ የጤና መታወክ ያስከትላሉ። ጥራት የጎደላቸው ወይም የአገልግሎት ዕድሜያቸው ያበቃ መድኃኒት፣ ምግብ ወዘተ… ጠቃሚነታቸው አጠያያቂ፣ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ መርዛማነት የሚያሳዩ መሆን ይችላሉ። ከዚህም አልፎ ብቃታቸው ያልተረጋገጡት መድኃኒቶች ሲወሰዱ ጀርሞቹ መድኃኒቶቹን በመላመድ የፀረ ህዋስ አለመበገር (አንቲማይክሮብያል ሬዚስታንስ) ይፈጠራሉ። ይህ ደግሞ ብዙ ሚሊዮኖች ዶላር ወጥቶባቸው የተመረቱ መድኃኒቶች ጥቅም አልባ ይሆናሉ ማለት ነው። በኢትዮጵያ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ በምን ደረጃ ላይ እንዳለና ምን መፍትሔ እየተሰጠው እንዳለ በቂ ጥናት ያለ አይመስልም።

ሌላው ተግዳሮት ተብሎ የሚጠቀሰው ጥቅም ላይ የማይውሉትን ነገሮች የማስወገድ ወይም መልሶ ሥራ ላይ ማዋል (ሪሳይክል) የማድረግ ጉዳይ ነው። እነዚህን ጥቅም አልባ ነገሮች ሳይንሱ በሚፈቅደው መንገድ ለማስወገድ በኢትዮጵያ መመሪያው ቢኖርም ተግባራዊነቱ ደካማ ነው። በብዛት የሚታየው ክስተት ቁጥጥር በጎደለው መንገድ በተቆፈሩ ጉድጛዶች ማቃጠል፣ ያለአግባብ በየቦታው መጣል ወይም በየወንዙ መድፋት ነው። በተገቢው መንገድ ያልተወገዱ ጥቅም አልባ ነገሮች የአየር፣ የከርሰ ምድር ውሃና የአካባቢ ጤናን በመበከል ተጨማሪ ጉዳት ያስከትላሉ። በኢትዮጵያ እነዚህን በተገቢው መንገድ ማስወገድ አቅሙ በጣም የተወሰነ ነው። በተጨማሪም አሳሳቢነቱ ስለጉዳዩ ያለው ግንዛቤ በህብረተሰቡ ዘንድ ዝቅተኛ መሆኑ ነው። የተለያዩ ንጥር ነገሮች የተለያዩ የማስወገድ ዘይቤ ይጠይቃሉ። አንዳንዶቹ ንጥረ ነገሮች ልዩ የማስወገጃ ዘዴዎች ስለሚጠይቁ ወደ ሌላ አቅም ያላቸው ሀገራት ተልከው መወገድ ያለባቸውም ይገኛሉ። መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር በመሥራት በእነዚህ ሁኔታዎች ላይ የሚያደርገው ቁጥጥር፣ የማስወገድና መልሶ መጠቀም እርምጃ በከፍተኛ መጠን መጨመር ይኖርበታል። ለምሳሌም በአዲስ አበባና በክልሎች እንዲሁም ተጠቃሚ ድርጅቶች በርካታ ጥቅም የማይሰጡ ነገሮችን ማስወገድ እንደሚቻል ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት ተመክሮዎችን መመልከቱ ጥቅም አለው።

ኢትዮጵያ ከምታደርገው የከተሞች ዕድገት፣ የከተማ ኗሪዎች መብዛት የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እንዲሁም የተለያዩ የማምረቻ ተቋሞች አንፃር፣ የፍሳሽ፣ የፅዳት፣ የውሃ፣ የመብራት፣የቆሻሻ ማስወገድ አገልግሎቶች ማሟላት ተቀዳሚ ጉዳዮች ናቸው። ይህን ለማሟላት የተወሰደው ወይም እየተወሰደ ያለው እርምጃ ምን ያህል እንደሆነና ስኬቱስ ምን ያህል እንደሆነ ጥሩ ጥናት ይጠይቃል። በቅርብ የሚታዩትም ሆኑ የሚሰሙት ብሶቶች እንደሚያሳዩት ብዙ መሠራት እንዳለበት ነው።

በቅርቡ በአዲስ አበባ ረጲ አካባቢ በዘልማድ ቆሼ በሚባለው የቆሻሻ መጣያ ቦታ ላይ የደረሰው ያለመጠን የተከመረው ቆሻሻ መደርመስና መናድ ከስሩ ተጠግተው በሚኖሩ 114 ግለሰቦች ህይወት መጥፋቱን መንግሥት አስታውቋል። በዚህ ስፍራ በርካታ የቆሻሻው ተቋዳሽ የሆኑ ችግረኞች ቆሻሻ ውስጥ የሚያገኙትን ምግብና ሌላ የወደቁ ነገሮችን ለመጠቀም ሲሰበስቡ ማየት እጅግ የሚያሳዝንና የሀገሪቱን ሌላ ገፅታ የሚጠቁም ሁኔታ ነው። በዚህ ስፍራ ላይ የደረሰው የህይወትና የንብረት መጥፋት የአስተዳደር ጉድለትና በጊዜው ተገቢውን እርምጃ ያለመውሰድ ውጤት መሆኑ ይገመታል። በዚሁ ስፍራ ላይ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ቆሻሻን ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል የመቀየር ዕቅድ በቅርቡ ዕውን እንደሚሆን ይነገራል። ይህ ዕውን ሲሆን የከተማይቱን 80% ደረቅ ቆሻሻ በማስወገድ ወደ 50 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት የአዲስ አበባን 30% የቤተሰቦች የኤሌክትሪክ ፍላጎት እንደሚያሟላ ይነገራል።

በአዲስ አበባ የመንገድ ቆሻሻን በመጥረግ፣ ከየቤቱ በመሰብሰብና ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ በመውሰድ፣ አሮጌ ዕቃዎችን ከየሰፈሩ በመግዛትና በመሸጥ (ቁራሌ ወይም ቆርቆሮ ያለው! በመባል የሚታወቁ)፣ ምናለሽ ተራ መርካቶ የተለያዩ አሮጌ ዕቃዎችን በመሸጥ ኑሮአቸውን የሚገፉ በርካታ ናቸው።  ይህን ግን በሚያደርጉበት ወቅት ያለምንም የአደጋ መከላከያና ጥንቃቄ ስለሆነ ለተለያዩ በሽታዎችና አደጋዎች የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ እራሳቸው የበሽታ አስተላላፊዎችም ሊሆኑ ይችላሉ። ይህን በሚመለከት በተለያዩ ግንባታና ፣ ፋብሪካ የሚሠሩ ሁሉ ጤናቸውን ለመጠብቅ ይህ ዓይነቱ ጥንቃቄ ስለሚያስፈልጋቸው የተሟላ ግብአት ሊስተካከልላቸው ይገባል። ከዚህ በፊት እንደነዚህ ዓይነቶቹን ሠራተኞች ለመርዳት ተቋቁሞ የሚሠራ በጎ አድራጎት ድርጅት ዘርፈ ብዙ ጥሩ ውጤቶች እንዳሳየ ቢታወቅም ከዚህ የተገኘው ተመክሮ ምን ያህል በሀገሪቱ እንደተዛመተ የሚታወቅ ነገር የለም።

ከከተማዎች መስፋፋትና ኗሪዎች መብዛት ጋር በተያያዘ የሚሠሩ ቤቶች የውሃ፣ የመፀዳጃና የቆሻሻ ማስወገጃ አቅርቦት ችግር እንዳለ በሰፊው ይሰማል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ቀንደኛዋ የፅዳት ጉድለት የሚታይባት ሀገር ናት። ይህ የአፍሪካ አንድነትና የብዙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ ለሆነችው ኢትዮጵያ ጥሩ መገለጫ አይደለም። የምእተ ዓመቱን ልማት የውሃ አቅራቦት 57% ግብ አሟልታለች ቢባልም የተቀረው 50 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ አሁንም የንፁህ ውሃ ተጠቃሚ አይደለም። መፀዳጃን በሚመለከት 28% የሚሆነው ሕዝብ ብቻ ነው መሠረታዊ በሚባል ደረጃ መፀዳጃ የሚገለገለው። ሌላው ለጤና አደገኛ በሆነ መንገድ ይፀዳዳል ማለት ነው።ይህ ደግሞ ቀጥተኛ የሆኑ ውሃ አዘል የጤና ችግሮች (እንደ ኮሌራ ወይም አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ፥ አተት)፣ በዓለም ቀዳሚ የዐይን መታወር የሚያስከትለው ትራኮማ ወዘተ… ላሉ በሽታዎች ሕዝቡን ሰለባ ያደርጋሉ። ቤቶች ሲሠሩ ግንባታው ብቻ ሳይሆን ከላይ የተጠቀሱት ዓይነት አገልግሎቶች የግንባታ ፈቃድ ከመሰጠት ጋር የተቆራኙ ግዴታዎች መሆን ይገባቸዋል።

በቅርቡ የተጀመረው የደረቅ ቆሻሻን ለኃይል ማመንጫ መጠቀም ጥሩ ጅመራ ሲሆን፣ ይህን ተመክሮ በመላው ሀገሪቱ ማስፋፍት ለጤና ጎጂ የሆነን ቆሻሻ ከበካይነት አውጥቶ ወደ ጠቃሚ ኃይል መቀየር ወይም የገቢ ምንጭ ማድረግ እሰይ የሚያሰኝ ጅማሬ ነው። ሌላው መስፋፋት ያለበት ተመክሮ በአዲስ አበባ በያካባቢው የተጀመረው የህብረተሰቡ የቆሻሻ ማስወገድ ቀን መወሰኑ ነው። በርከት ያሉት ውሳኔዎችና ሙከራዎች በተፋጠነ ሁኔታና በስፋት በያካባቢው ካልተዛመተና በድርጊት ካልተደገፈ ከይስሙላነት አያልፍም። ከላይ የተጠቀሱት እንደተጠበቁ ሆነው፣ ከፍተኛ ጥረት መደረግ ያለበት የሕዝቡን ስነ ልቡና መቀየርና በትምህርት ማነፅ ነው። ሕዝቡ የቆሻሻን የጤና ጎጂነትና ፀረ ቆሻሻነትን ባህሉ ማድረግ ላይ ብዙ ካልተሠራ ጊዜያዊና ቁንፅል ድርጊቶች ብዙም አያስኬዱም።

ሌላው ከእድገት ጋር ተያይዞ የሚታየው ተግዳሮት፣ የተሽከርካሪዎች መብዛት ነው። በኢትዮጵያ የነፍስ ወከፍ ተሽከርካሪ ብዛት ባጠቃላይ እጅግ ዝቅተኛም ቢሆን ካሁኑ ተገቢው ቁጥጥርና ሕግ ካልታሰበበት ለወደፊት ብዛቱ ሲጨምር ችግሩ ቀላል አይሆንም። እንደ ቀልድ ተደርጎ የተነገረ ነገር አለ፤ የጂቡቲው ፕሬዜዳንት ጉሌድ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስን ሲጠይቁ፥ “እንዴት ነው ይሄ ሁሉ መኪና በየጊዜው በጂቡቲ ኢትዮጵያ የሚገባው? ሕዝቡ መኪና ነው የሚበላው?” ብለው ጠየቁ ይባላል።

ይህ ቁም ነገር አዘል ቀልድ የጉዳዩን ትኩረት ይጠቁማል። በሀገሪቱ 900,000 ገደማ ተሽከርካሪዎች ብቻ ሲኖሩ፣ በዓመት እስከ 8,000 መኪናዎች ሀገር ውስጥ እንደሚሠሩ፥ እንደሚገጣጠሙ ይሰማል። በብዛት ከውጭ የሚገቡት ደግሞ አዲስ ሳይሆኑ ጥቅም ላይ የነበሩ ናቸው። የተሽከርካሪ ታክስ አንዳንዴ ከመኪናው ዋጋ ጋር እኩል ስለሚሆን ሕዝቡ የረከሱትን መግዛት ይመርጣል።  በኢትዮጵያ እስከ ዐርባ ዓመታት ያስቆጠሩ ዕድሜ ጠገብ መኪናዎች አሁንም አገልግሎት የሚሰጡ አሉ። ባለፉት ዓመታት ደግሞ ባጃጅ የሚባሉ ባለሦስት ጎማ በህንድ የተሠሩ ተሽከርካሪዎች ሀገሪቱን አጥለቅልቀዋታል። በቅርቡ ወደ ሀገር በየወሩ የሚገቡት ባጃጆች ቁጥር እስከ 8,000 ነው ይባላል። ከነዚህ ተሽከርካሪዎች የሚወጡ ጭሶች አደገኛ ጋዞችና ጥቃቅን ብረታማ ነገሮች ከፍተኛ የአየር ብክለትና የጤና መታወክ ያስከትላሉ።  እንደ ብሮንካይተስና አስማ ያሉ በሽታዎች መንስኤና ማባባሻም ናቸው። የካንሰርም ምክንያት የመሆን አደጋ አላቸው። ከኤታኖል አልኮል ጋር የተደባለቀ ነዳጅ በሀገሪቱ ጥቅም ላይ መዋሉና ብክለትን ይቀንሳል ቢባልም ጥቅሙ ውሱን ከመሆኑ ሌላ የተሽከርካሪዎቹ ዕድሜና ዓይነትም ጥቅሙ ላይ ተፅዕኖ አላቸው። ብዙ ሰዎችን የሚጭኑ የከተማና ሀገር አቋራጭ፣ እንደ አውቶቢሶች፣ ባቡር ወዘተ ያሉ ማጓጓዣዎችን ማስፋፋትና መንገዶችን በሰፊው መገንባት እንዲሁም የአነዳድ ስነ ሥርዓትን ማስተማርና ማስከበር አዎንታዊ የጤና ውጤቶች ከሚያመጡ እርምጃዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ። በቅርቡ ሥራ ላይ የዋለው በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው “ላይት ሬል” የከተማ ባቡር ጥሩ ጅምር ሲሆን ከናሙናዊነቱ መዝለል ይጠበቅበታል።

በአሁኑ ጊዜ በርካታ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ። ጥቅም ላይ የማይውሉ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች በተገቢው መንገድ ማስወገድ ችሎታ በሀገሪቱ ያልዳበረ በመሆኑ በአልባሌ መንገድ ስለሚወገዱ ሊያስከትሉ የሚችሉት የጤና አደጋ በዓይነትና ውጤት ሊገመት አይችልም። በዚህ ላይ ጥናትና ቁጥጥር መደረግ ያለበት አስቸኳይ ጉዳይ ነው።

በድኃነት፣ በሥራ አጥነትና በቤት አቅራቦት ችግር ምክንያት በአንድ ቤት ውስጥ ተጣበውና ተፋፍነው የሚኖሩ በርካታ ሰዎች እንዳሉ የታወቀ ሲሆን፣ ከዚህ የተነሳ የተለያዩ የጤና ችግሮች ይከሰታሉ። ዋንኛ የበሽታ መተላለፊያ መንገድም ነው። በነዚህ ዙርያ ሰፊ ጥናት፣ የህብረተሰብ ግንዛቤና የመንግሥት ሚና ከፍ ሊል ይገባዋል።

ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበት ፈጣን የእድገት ሁኔታ በዓለም ካሉ ሀገራት ጭራነት መውጣት ሲሆን፣ የመንግሥት ትኩረት፣ የምሁራኑና የህብረተሰቡ ተሳትፎ ጤናን በመንከባከብ፣ በሽታን በመከላከል፣ ግለሰብን ያማከለ፣ ውጤት ተኮር፣ ጥራት የተሞላበት፣ ቀጣይነቱ የተረጋገጠ እርምጃ መሆን ጊዜ የማይጠብቅ ጉዳይ ነው። ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች በርካታና ሰፊ ከመሆናቸውም በስተቀር ብዙ ወጪ የሚጠይቁ ናቸው። የአንድ ሀገር ሃብቱ ሕዝቡ ስለሆነ ሁለንተናዊ ጤንነቱን ማረጋገጥ ደግሞ የመንግሥት ዋንኛ ግዴታው ነው።

.

ገብርኤል ዳንኤል

(መጋቢት 2010 ዓ.ም)

.

[አቶ ገብርኤል ዳንኤል ለአለፉት አራት አሰርት ዓመታት በፋርማሲ፣ በኤችአይቪ ኤድስ፣ በወባ፣ በኢቦላ፣ ትኩረት በተነፈጋቸው የቆላማ አገራት በሽታዎች፣ በስደተኛና በተፈናቀሉ ሰዎች እንክብካቤና የድህነት ቅነሳ ፕሮጀክቶች ላይ በተለያዩ የአፍሪካና እስያ አገራት ውጤታማ ተግባራት አከናውንዋል። ገብርኤል በሜሪላንድ እስቴት በአሜሪካ ነዋሪ ነው።]

.

.

ዋቢ ጽሑፎች

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.