“የአንድ ኢትዮጵያዊ ደራሲ ሕመም” (እንዳለጌታ ከበደ)

የአንድ ኢትዮጵያዊ ደራሲ ሕመም

(ከድሮ እስከ ዘንድሮ)

.

እንዳለጌታ ከበደ*

(አዲስ አበባ)

.

.

እንደ መግቢያ  

ድርሰት ሕይወትን የምንመረምርበት፣ ጉድፍና መብታችንን የምንለይበት፣ የሰው ልጅ የመርቀቅና የመጠበብ ችሎታውን የምንገመግምበት፣ ባህል ታሪካችንን ቀርፀን የምናስቀምጥበት፣ ሊወቀስና ሊከሰስ የሚገባውን የምንገስጽበት፣ የተንጋደደ አመላችንን የምናርቅበትና ብሔራዊ ጀግኖቻችንን አጉልተን የምናሳይበት መስታወት ነው። ድርሰት እንደአርአያ ሊቆጠሩ ከሚችሉ፣ ጨለማውን ከሚገፉና የኅብረተሰቡን ሰንኮፍ እንዴት መንቀል እንደሚቻል ከሚያሳዩ ልዩ ልዩ ነባርና መጤ ሃሳቦች ጋር የምንዛመድበት፣ የምንዝናናበትና የምንማርበት የጥበብ ቤተሰብም ነው።

ድርሰት በደራሲ ተከይኖ ሲቀርብ፣ ደራሲነት ደግሞ በተሰጥኦ የሚገኝ፣ በተምህሮና በተለምዶ የሚዳብር ሙያ መሆኑ ይታወቃል። ይህ፣ ጊዜ፣ ዕውቀት፣ ጉልበትና ገንዘብ የሚከፈልበት የደራሲው ሙያ ምሉእ የሚሆነው ደግሞ አጋዥ ሲኖረው ነው። አጋዦቹም አሳታሚዎች፣ አታሚዎች፣ አከፋፋዮችና አሰራጮች ናቸው። ያለ እነዚህ ደጋፊነት ደራሲው ቆሞ ሊራመድ ቀርቶ መዳህም የሚቸግረው ይሆናል። እነዚህ አጋዦች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሠናይ ልማድ እንዳይጣስና ስሙር ሥርዓት እንዳይጣረስ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክቱ ሁሉ፣ በተቃራኒው ደግሞ የተዛነፈ ታሪክ፣ ባህልና ርእዮት በኅብረተሰቡ ልቦና ውስጥ እንዲሰርፅ፣ ተደላድሎም እንዲቀመጥ ተጽዕኖ ያሳድራሉ።

ደራሲው፣ “ልጽፈው የሚገባ ሃሳብ አለ” ብሎ፣ እረፍት እንቅልፉን ሰውቶ፣ ሃሳቡን በወረቀት ላይ ለመዝራት በሚባትልበት ጊዜ፣ ምንም እንኳን ራሱን ከተዝናኖት ነጥሎ፣ ከፈጠራቸው ገፀ ባህርያት ጋር ወዳጅነት መስርቶ፣ ራሱ በፈጠረው ገዳም ውስጥ ሱባኤ ገብቶ ረቂቅ ድርሰቱን ቢያጠናቅቅም፣ በሌላው ዓለም ካሉ ደራስያን በተለየ መልኩ እንደገና ሌሎች ምጦች ይጠብቁታል።

ይህ ጽሑፍ፣ ትናንትም ሆነ ዛሬ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የንባብ ባሕል እንዲዳብር፣ በመጻሕፍት ሰበብ የሚለወጡና የሚለውጡ ዜጎች እንዲበዙ ሙያው ክቡር፣ ንዑድና ቅዱስ እንዲሆን የሚታገሉ ደራስያን ምን ዐይነት ሕማማት እያሳለፉ እንደሆነ በአጭሩ ይጠቁማል። ሕማማቱ በቅድመ ኅትመት፣ በኅትመትና በድኅረ ኅትመት ጊዜ የሚያጋጥሙ ፈተናዎች ናቸው፡፡ የአርታኢ፣ የአሳታሚ፣ የአከፋፋይ ችግርና የመንግሥት ድጋፍ አለመኖር በማለትም ልንመድባቸው እንችላለን፡፡

.

የአርታዒ ችግር

.

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለኅትመት የሚቀርቡና አንባብያን እጅ የሚገቡ መጻሕፍትን ስንዳስስ፣ ብዙ ወጣትና ጀማሪ ደራስያን ብቻ ሳይሆኑ፣ ነባሮችም በተደጋጋሚ የሚፈጽሟቸው ስህተቶች እንዳሉ ማስተዋል ይቻላል። በዚህ ዘመን ዐረፍተ ነገሩ ያላማረ፣ ሥርዓተ ነጥቡ ያልሰመረ፣ ሀሳቡ እርስ በእርስ ያልተያያዘ፣ አንቀፁ ያልተሰናሰለ እና የፊደል ግድፈቱ የበዛ መጽሐፍ ማንበብና ማስነበብ የተለመደ ሆኗል። አንዳንድ መጻሕፍት ደግሞ የይዘት ደረጃቸው ብቻ ሳይሆን የውስጥና የውጭ ገጽ ቅንብራቸውም እየደከመ መጥቷል። መጽሐፉ የታተመበት ዓመተ ምህረትና የኅትመት ቦታውን የማይገልጹ፣ ታሪክ ይሁኑ ልብ ወለድ፣ ወጎች ይሁኑ አጫጭር ልቦለዶች መሆናቸውን በመጀመርያ ገጾቻቸው የማያስተዋውቁ፣ ትርጉም ከሆነም የደራሲውን ስም፣ ወጥ ሥራው መጀመሪያ የታተመበት ዓ.ም እና የወጥ ሥራውን ቀዳሚ ሥያሜ የሚዘነጉ፣ ከዚህ ቀደም ገበያ ላይ በዋሉ መጻሕፍት ርዕስ መልሰው የሚያሳትሙ1፣ ታሪኩን ሊወክል የሚችል ምስል በፊት ሽፋን ላይ ከማስቀመጥ ይልቅ ልዩ ልዩ ምስሎችን ከየድረ ገጹ በመውሰድ ሥራውን ሊወክል በማይችል መልኩ መጽሐፋቸውን ‹ሲያሽሞነሙኑ› ይስተዋላሉ። በዚህም አንባቢው ሲከፋ፣ ሲገፋ፣ ሲገፈተርና ሙያውም አልሆነ ቦታ ሲወድቅ ይታያል፡፡

ይህ ሁሉ የአርታዒ አለመኖር የሚፈጥረው ክፍተት ነው፡፡ ንቁና ብቁ አርታዒ የጎበጠውን ያቃናል፤ የጎደለውን ይሞላል፤ የተትረፈረፈውን ይቀንሳል፡፡ ደራሲው ‹አውቆ በድፍረት ሳያውቅ በስሕተት የሠራው ኃጢአት› እንዳይኖር ረቂቅ ሥራውን ያክምለታል፡፡

ቀደም ሲል፣ በዚህ ዘመን ደራስያን ላይ የሚስተዋሉ ተብለው የተጠቀሱትን ችግሮች ለመፍታት፣ ደራሲው ባለ ልምድ እንዲሆን ወይም ክህሎቱን በትምህርትና ስልጠና እንዲያዳብር ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ አሳታሚ ድርጅቶችን መክፈትና ማብዛት እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡ አሳታሚ ሲኖር፣ ለሙያው ክብደት የሚሰጡ አርታዒያንን ቀጥሮ ያሠራልና አንባቢውም ደራሲውም ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ይተጋገዛሉ፡፡ በዚህ የተነሳ የሥነ ጽሑፍ ሙያ ጠዋት ተመርቶ ከሰዓት መርካቶ እንደሚገኝ ሸቀጥ በውክቢያ አንብቢ እጅ የሚገባ አይሆንም፡፡

.

የአሳታሚ ችግር

.

የአሳታሚ መኖር በረከቱ የተትረፈረፈ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ለደራሲው እንቅፋት ከሆኑበት ፈተናዎች መካከል ዋነኛው አሳታሚ ማግኘት ወይም ማሳተሚያ ገንዘብ ፈልጎ ማግኘት ነው። በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን አንድ ደራሲ ድርሰቱን የሚያስነብበው በራሱ ገንዘብ አሳትሞ፣ ራሱ አከፋፍሎ፣ የማከፋፈሉን ሥራ ሠርቶ ነበር፡፡ ደራስያኑ የቤት ካርታ ለማተሚያ ቤቱ አስይዘው፣ ወይም ደሞዝተኛ የሆነ ዋስ ጠርተው፣ ወይም ከቤተመንግሥት ሹማምንት ጋር ተወዳጅተው ወደ ማተሚያ ቤት ዘልቀው መጽሐፎቻቸውን ያስነብቡ እንደነበር አያልነህ ሙላቱ፣ ደራስያንን ለማፍራትና ለማበረታታት ምን መደረግ አለበት?” በሚል ርዕስ በ1985 ዓ.ም በሠሩት ጥናት ጠቁመዋል። አያልነህ ደራሲው በማሳተም ሥራ ተሳትፎ ጊዜውን ማባከን፣ ራሱን ማስጨነቅና ሥራውን ሊጎዳው እንደማይገባ ለመግለጽም እንዲህ ብለው ነበር፤

ደራሲው አሳታሚነት ሥራው ስላልሆነና የገንዘብ አቅም ስለሌለው የማሳተሙን ኃላፊነት ለባለሙያው መተው አለበት። ንግድ ሥራ ላይ መግባት የለበትም። ልገኝም ቢል አይችልም። ከስሮ ባዶ እጁን ይወጣል። ይህ ደግሞ ተረት ተረት ሳይሆን በአንዳንዳችን ላይ በተጨባጭ የታየ ክስተት ነው። ስለሆነም እያንዳንዳቸው ተደጋጋፊ ይሁኑ እንጂ ፈጽመው ተወራራሽ አይደሉም። በእርግጥ ሲቸግርና መፈናፈኛ ሲጠፋ አልፎ አልፎ ተደራርበው ይሠራሉ። 2

ይኸ አሳታሚ የማጣት ችግር የዘመናት የደራስያን ሕማም ነው። መንግሥቱ ለማ በ 1950 ዓ.ም የግጥም ጉባዔ” የተሰኘ መጽሐፋቸውን ሲያሳትሙ በትይብ ነበር ያሳተሙት።3 መንግሥቱ በዚህ መጽሐፍ መቅድም ላይ እንደገለጹት፣ አሳታሚ ማጣት ደራሲው የተጫነው በዚያ ዘመን የነበረ ችግር ነው። መንግሥቱ ለማ ይህንን ችግር እስከመቸውም ለመፍታት በማሰብ፣ በ1964 ዓ.ም በኢትዮጵያ ድርሰት ማኅበር ሥር፣ የደራስያን ዕቁብ እንዲመሰረት አደረጉ። ዕቁብ የወጣለት ግለሰብም ከደረሰው ገንዘብ ቀንሶም ሆነ ጨምሮ መጽሐፍ ያሳትም ያዘ።4 የኢየሩሳሌም በጎ አድራጎት ድርጅትም እንደ መንግሥቱ ለማ፣ ደጃዝማች ግርማቸው ተክለሐዋርያት ያሉ ዕውቅ ባለሙያዎች የተሳተፉበት አሳታሚ ድርጅት በ1960ዎቹ አጋማሽ አቋቋመ። አሳታሚ ድርጅቱ “ቆሜያለሁ፣ ተቋቁሜያለሁ” ባለ ማግስት አብዮት ፈነዳ። አንዳንድ የድርጅቱ መስራቾች የዘውዱ ሥርዓት ባለሥልጣን ነበሩና ታሰሩ፤ ተገደሉም። በዚህ የተነሳ ተስፋ የተጣለበት ድርጅት በነበር ቀረ። በኢትዮጵያ ድርሰት ማኅበር የተመሰረተው ዕቁብም ሥርዐቱ በፈጠረው አለመረጋጋት የተነሳ ፈረሰ።

የደርግ ሥርዓት ሲመጣ፣ በአቶ ተስፋዬ ዳባ አማካኝነት የተቋቋመው የኢትዮጵያ መጻሕፍት ድርጅት እና የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለምን ከማስተዋወቅ በተጨማሪ፣ የፈጠራ ሥራዎችን ያሳትም የነበረው ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ታሪክ ሊዘነጋው የማይገባ ውለታ ለኢትዮጵያ   ሥነ ጽሑፍ መዋል ጀመሩ። ነባር ደራስያን5 ተነሳሱ፤ አዳዲሶች 6 ብቅ ብቅ ማለት ቀጠሉ። ሆኖም፣ እነዚህ አሳታሚዎች ኢሕአዴግ ሲገባ ውሃ በላቸው። ቅርንጫፍ ቢሮዋቸውን ዘጉ። ተዘነጉ። የኢትዮጵያ መጻሕፍት ድርጅት ከገበያው ወጣ፡፡ ኩራዝ አሳታሚ ድርጅትም ወደሜጋ አሳታሚነት ተቀየረ። ሜጋ አሳታሚ ለጥቂት ዓመታት የነባርና የአዳዲስ ደራስያን ሥራዎችን ሲያሳትምና ሲያከፋፍል7 ቆይቶ በትምህርት መርጃ መጻሕፍት፣ በሕጻናት፣ በሙያዊ መጻሕፍትና በመሳሰሉት ላይ ብቻ ትኩረቱን አሳረፈ። በየቅርንጫፍ መሸጫ ሱቆቹ ለማከፋፈል የሚቀበላቸውን መጻሕፍት እየመረመረና ‹ሳንሱር› እያደረገ መለየት መለያየት ጀመረ።8

በዚህ ዘመን ደራስያንን በማበርታት በኩል ሻማ ቡክስ፣ ሀሳብ አሳታሚና ማንኩሳ አሳታሚ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ለማድረግ አልፎ አልፎ፤ እጅግ አልፎ አልፎ፣ ጥቂት የፈጠራ ሥራዎችን አስነብበዋል። የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበርም ከአርቲስቲክና ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ባገኘው ተዘዋዋሪ ሂሳብ አማካይነት ከደርዘን በላይ መጻሕፍትን መርጦና አርትዖት አድርጎ አሳትሟል።9

እርግጥ አሁን በዚህ ዘመን የአሳታሚነት ፈቃድ የሌላቸው ነጋዴዎች የሙያው ተሳታፊ ሆነዋል። እነዚህ ራሳቸውን እንደ “አሳታሚ” የሚቆጥሩ ግለሰቦች ቢሮ ከፍተው፣ ባለሞያ ቀጥረውና ሎጎ አስቀርፀው የሚንቀሳቀሱ አይደሉም። እነዚህ ነጋዴዎች አንዳንድ ነባርና አዳዲስ መጻሕፍት አንባብያን እጅ እንዲገቡ ጥረት ማድረጋቸው ቢያስመሰግናቸውም፣ በዕውቀት ጉድለት ወይም በዝንጋኤ ብዛት የሚፈጽሟቸው ስህተቶች መኖራቸው ደግሞ አይካድም። ድርጅቶቹ ብዙውን ጊዜ ታማኞች ሲሆኑ አይታዩም። አንድን ነባር ወይም አዲስ መጽሐፍ ሲያትሙ የሚመለከተውን አካል አያስፈቅዱም። የባለቤትነትን መብት አያከብሩም።

በቅርቡ በኤፍሬም ስዩም ተዋነይ መጽሐፍ ላይ የተፈጸመው ድርጊት እዚህ ላይ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ ተዋነይ መጀመሪያ ያሳተመው ሻማ ቡክስ ነበር። ቀጥሎ የኅትመት ጥራቱ ቀንሶ፣ ዋጋው ከመቶ ብር ወደሰባ ብር ወርዶ ገበያ ላይ ሲሸጥ፣ የመጽሐፉ ባለቤት ስውር ያለደራሲውና አሳታሚው ዕውቅና ሲሸጥ ገበያ ላይ አገኘው። ይህንን ዘረፋ አስመልክቶ የኛ ፕሬስ ጋዜጣ ደራሲውን ለቃለ መጠይቅ ጋበዘውና ኤፍሬም የሚከተለውን ሃሳብ በቁጭት ተናገረ፤

… አሁን እኔ ልጻፍ ብል የሚሰማኝ ስሜት ጥሩ አይደለም። በጣም ተጎድቻለሁ። እውነቱን   ልንገርህና እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ በጣም ተጎድቸ ነበር… አጽንኦት ሰጥቸ የምናገረው ነገር የተዘረፈው የኤፍሬም ሥራ ብቻ አይደለም፣ ነገ ከነገ ወዲያ የምናሳትማቸው መጽሐፎች ተመሳሳይ ዕድል እንደማይገጥማቸው ምንም ዋስትና   የለንም። በመፋጠጥ ልንኖር ነው ማለት ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ በጎዎቹም መልካሞቹም አሳታሚዎችና አከፋፋዮች ስማቸው ሊወቀስ ነው ማለት ነው።10

ነጋዴዎቹ፣ ከላይ የተጠቀሰውን ዓይነት የደራሲውን መብት ካለማክበራቸው በተጨማሪ፣ ደራሲው ወይም አዘጋጁ ያላለውን፣ እንዲባልበት የማይፈልገውን ከወጥ ሥራው ጋር ያልተዛመደ ሃሳብ ይደነጉራሉ። እዚህ ላይ የፈላስፋው ዘርዓያዕቆብን፣የወልደሕይወትን እንዲሁም የዘነብ ኢትዮጵያዊን መጽሐፍ በአንድ መድበል የታተመውን ሥራ ማንሳት ተገቢ ነው። አዘጋጁ እነዚህን ሥራዎች ለንባብ ሲያበቃ፣ ‹ቀለል ባለ መልኩና አንባቢው እንዲረዳው በሚል እሳቤ›፤ በቀዳሚ ሥራው ላይ የሌሉና የተዛቡ ሃሳቦችን አካትቶ በማሳተሙ በበርካታ ሊቃውንት ዘንድ ቁጣ አስነስቷል።

በሌላ በኩል የአሳታሚው ብቻ ሳይሆን የአታሚው ዐቢይ ጉድለትም ታማኝ ሆኖ አለመገኘት ነው። እነዚህ አታሚዎች ያለደራሲው ወይም ህጋዊ ባለቤት ፈቃድ ታትመው ያለቁትን አዳዲስ መጻሕፍት በጓሮ በር ወደገበያ እንዲወጡ ብርቱ ጥበቃ ወይም አመቺ መንገድ በመፍጠራቸው ነው። በካህሊል ጅብራን ተጽፎ፣ በርቱዓ አምላክ የተተረጎመው ነቢዩ የተሰኘው መጽሐፍ ለዚህ ጉዳይ ጥሩ ምሳሌ ሊሆነን ይችላል። ተርጓሚው ነቢዩ ን ከማተሚያ ቤት ለማስወጣት ጥቂት ቀናት በቀረው ሰሞን መጽሐፉን ገበያ ላይ ውሎ አገኘው። ምስክር አቁሞም አታሚውን ፍርድ ቤት ከሰሰው። ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያምም ባሻ ቅጣውን ባሳተሙ ጊዜ እንዲሁ ሆኗል። አለ አሳታሚው ፈቃድ መጽሐፉ ገበያ ላይ ሊውል ሲል እጅ ከፍንጅ ተደርሶበታል።13 ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው ማተሚያ ቤቶች ታማኝ ባለሙያ ባለመቅጠራቸውና የሚያደርጉት ቁጥጥር ደካማ በመሆኑ ነው።

ደራሲው በራሱ ገንዘብ ተበድሮ መጽሐፉን በሚያሳትምበት ጊዜም ሆነ በሌሎች አማካይነት ሥራውን ለኅትመት ሲያበቃ በአንዳንድ ማተሚያ ቤቶች የሚደርሱበት እንግልቶች በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም።

በተቆረጠ ቀን አለመስጠት ፤ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ አለማተም – ማለትም ጽሑፍ ሊኖርባቸው ሲገባ ጽሑፍ ያልሰፈረባቸው የተዘለሉ ገጾች መብዛት፣ የገጾች መዛባት፣ በኮላ እጥረት ምክንያት መገነጣጠል፣ ደራሲው አሰርቶ ያመጣውን የፊት ሽፋን ምስል በትክክል አለማተምና ሌሎችም – ከጉድለቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

አማረ ማሞ አሳታሚነትና የኅትመት ጥራት በተሰኘ ርዕስ፣ በ2000 ዓ.ም የሠሩትን ጥናት ስናነብ፣ እንዲህ ዓይነቱን ስህተት በመተግበር ኢትዮጵያ የረጅም ልምድ እንዳላት እንድንገነዘብ ያደርገናል።

ሀዲስ የተባለው የበዓሉ ግርማ መጽሐፍ የታተመው ሃያ ሺህ ቅጂ ሲመረመር 17 የተለያዩ የኅትመትና   የጥራት ጉድለቶች   ተገኝተውበታል። ከሁሉም የባሰው አክሳሪ ጉድለት የመጽሐፉ ሁለት ሺህ ቅጂ አዳባይ በተሰኘ መጽሐፍ ልባስ ተጠርዞ ለኩራዝ አሳታሚ ድርጅት መሰጠቱና ገበያ ላይ ውሎ በርካሽ ዋጋ መቸብቸቡ ነበረ።11

አንዳንድ ማተሚያ ቤቶች ብልሽት ያጋጠማቸውን መጻሕፍት ኃላፊነት ወስደው ምትኩን ይቀይራሉ። ግን ስንቱ አንባቢ ነው፣ የተበላሹ መጻሕፍት ወደ ገዛበት መደብር ሄዶ ያወጣሁት ብር ይመለስልኝ ወይም በምትኩ ገጹ ያልጎደለ፤ ሽፋኑ ያልተበላሸ፤ የኅትመት እንከን ያልጎበኘው ይሰጠኝ የሚለው?!

.

የአከፋፋይ ችግር

.

መጽሐፉ ከታተመ በኋላ አከፋፋዩና ቸርቻሪው እጅ ይገባል። ያለእነዚህ ተሳትፎ ኢንዱስትሪው ግቡን አይመታም። ደራሲው የታተመለትን መጽሐፍ ለአከፋፋዩ ሲሰጥ ተሸጦ የሚከፈል ደረሰኝ ይሰጠዋል። የመጽሐፉ የጀርባ ዋጋ 100 ብር ከሆነ 60 ወይም 65 ብር ሂሳብ ለአከፋፋዩ ይሰጠዋል፤ ከወራት በኋላ ደራሲው ወደ መጽሐፍ አከፋፋዩ ዘነድ ይመለሳል፤ መሸጥ አለመሸጡን ይጠይቀዋል፤ መቼ መጥቼ ልውሰድ ይላል። በተቆረጠለት ቀን ሲሄድ ገንዘቡ ሊሰጠውም ላይሰጠውም ይችላል። ሁኔታው አታካችና ክብረ ነክ ነው። ደጅ መጥናትን ይጠይቃል፡፡ ተስፋ ያስቆርጣል። ገንዘቡ እንደወጣ የመቅረቱ ዕጣ ፈንታው ሰፊ ይሆናል።

ቸርቻሪዎቹ አካባቢም አንጥፈውና አዙረው በሚሸጡት ላይም ሌላ ችግር አለ። ይኸውም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከመጽሐፉ ትክክለኛ ዋጋ በተጨማሪ ሌላ ዋጋ የመሥራት (ፎርጂድ) ሂደት ነው። ብዙዎቹ መጽሐፍ አዙረው የሚሸጡና በአዲስ አበባ ጎዳና የሚታዩ ወጣቶች በኪሳቸው ስባሪ ምላጭ አያጡም። በምላጩ ስባሪ የመጽሐፉ ዋጋ 30 ብር ከሆነ ፍቀው 80 ብር ያደርጉታል። እነዚህ ወጣቶች የመቶ ብሩን መጽሐፍ በ70 ወይም በ75 ብር ሂሳብ ከአከፋፋዩ ይቀበሉና አንባቢው እነሱ በተመኑት ዋጋ እንዲገዛ ያግባቡታል። እንዲህ ላለው ተግባር አሳታሚውም ይሁን ደራሲው ተባባሪ እየሆኑ መምጣት ደግሞ ይበልጥ አሳሳቢና አነጋጋሪ ሆኗል። ለምሳሌ የመጽሐፉ ጀርባ ላይ በጥቁር ቀለም በነጭ ሰሌዳ ላይ 71.20 ይጻፍበታል። ይህ ኮድ ነው – ደራሲው ወይም አሳታሚው መጽሐፍ አዙረው ከሚሸጡት ሰዎች ጋር የሚግባባበት መንገድ፡፡ 7 ቁጥርንና ነጥቧን በምላጭ ስባሪ በጥንቃቄ አጥፍታችሁ 120 ብር ሽጡት ማለት ነው። መጽሐፍ አዟሪዎቹ በዚህ መጽሐፍ የተለየና የተሻለ ጥቅም ስለሚያገኙ አዘውትረው የሚይዙት፣ ገዢውን እየጎተጎቱም ቢሆን የሚሸጡት ይሆናል፡፡ አዙዋሪዎች ‹ይህን ለማድረግ የተገደድነው፣አብዛኛው ገዢ ተከራካሪ ስለሆነ ከዋናው ዋጋ ቀንሰን የሸጥንለት መስሎ እንዲሰማው ብለን ነው› ይላሉ።

የሚገኘው ጥቅም ከፍ ስለሚል አዙዋሪዎች ለዚህ አሠራር ምቹ ያልሆነ መጽሐፍ አይዙም፡፡ አሠራራቸውን በገቢርም ሆነ በነቢብ በሚቃወም ደራስያን ላይም ቂም ይይዛሉ፡፡ ቂም የያዙበትን ሰው ሥራ አዙረው ባለመሸጥ ቁጣቸውንና ቅሬታቸውን ይገልጻሉ፡፡ አንዳንድ የመጽሐፍ አዘጋጅ ደግሞ የመጽሐፉን ዋጋ መቶ ሃምሳ ብር ብሎ በፊደል ይጻፍበትና ለአከፋፋዩ ሃምሳ ብር ሰጥቶ፣ አከፋፋዩ ደግሞ በስልሳ ብር ከዋናው አከፋፋይ ተቀብሎ፣ በአንባቢው ላይ ዘጠና ብር እንዲተረፍበት እያደረገ ገበያውን ለማሸነፍ ይሞክራል።

ባይለየኝ ጣሰው [ዶ/ር] የሥነጽሑፍን ዕድገት የገጠሙት ችግሮች በሚል ርዕስ ባደረጉት ጥናታቸው መጻሕፍት የዕውቀት ምንጭ ስለመሆናቸው ጠቅሰው እንዲህ ብለው ነበር፤

ዕውቀት የሰው ልጅ በረጅም የታሪክ ዘመናት ውስጥ ያካበተው ሁለንተናዊ ሃብት ነው…ማንኛውም ሰው ፊደሎችን እስከለየ ቋንቋውን እስከቻለ ድረስ በውስጡ ባለው እሴት አዕምሮውን መገንባት ሊጎዳው አይችልም። በፊደሎች ወይም በመጻሕፍት ላይ ጥላቻን መፍጠር ዕውቀትን መጥላት ነው። ዕውቀትን መጥላትም የመንፈስ መራቆትና የሞራል ውድቀት ነው የሚሆነው።13

እውነት ነው፣ እውቀትን የሚጠሉ፣ መጻሕፍትን የሚበድሉ ማጅራት መቺዎች በየሥፍራው አድብተው ቆመዋል።

.

መንግሥታዊ ድጋፍ አለመኖር

.

በዚህ ዘመን በኢትዮጵያ ደራስያን ላይ ያለው ችግር ከትናንትም፣ ከትናንት በስቲያም ከነበረው ችግር የሰፋ ነው። ትናንት በደርግ ዘመን አሳታምያን ስለነበሩ ደራሲው ይደርስበት የነበረ ጉስቁልና የተመጠነ ነበር። አንባብያኑ የተመረጡ ሥራዎችን እንዲያነቡ የአርታዒያኑ ትጋትና ድጋፍ ቀላል አልነበረም። ደራሲው ድርሰቱ ተመርጦ ከታተመለት በኋላ ተሸጠ አልተሸጠ፣ ተሰራጨ አልተሰራጨ የእርሱ ደንታ አልነበረም። የጦር ሠራዊቱ ሳይቀር መጻሕፍቱ ፊቱ ድረስ ይቀርብለት፣ ይገዛ፣ ይዋዋስ፣ ይወያይ፣ ይጻጽፍም ነበር። ሥርዓቱ ከወደቀ በኋላ ይህ ሁሉ የለም። መንግሥት ደራስያንን ለማገዝ፣ሙያው የሚጎለብትበትን መንገድ በመሻት፣ አንባብያን ለማብዛት ሲደክም አይታይም፡፡ ሀገሪቱ ውስጥ ካለው የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ቢሮ ይልቅ ንባብና አንባቢን በማገናኘት ረገድ የጀርመን ባህል ተቋም በየትምህርት ቤቱ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ምስጋና የሚቸረው ነው፡፡

በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን፣ በስማቸው የሚጠራ፣ አገር አቀፍ ሽልማት ነበረ። ከበደ ሚካኤል፣ ሀዲስ አለማየሁ፣ጸጋዬ ገብረ መድህን፣ መንግስቱ ለማና ሌሎችም የሽልማቱ ተቋዳሽ ነበሩ፡፡ የድርሰት ሙያም ‹የተመረጡ› ሰዎች የሚውሉበት፣ የከበሬታን ወንበር የሚያገኙበት ነበረ። ትምህርት ሚኒስቴርም ሠናይ ናቸው የሚላቸውን መጻሕፍት እየለየ፣ በየትምህርት ቤቱ እያሰራጨ፣ መማሪያ እንዲሆኑ እንዲነበቡም ያደርግ ነበረ። አሁን ይህ የለም፤ ዝጓል፣ ተዘግቷል። በደርግ ዘመን ደግሞ አሳታሚ ድርጅቶች ብቅ ብቅ አሉ፡፡ጦር ሰራዊቱ መጻሕፍት ይጎርፍለት ገባ፡፡

የዚህ ዘመን ትውልድ “ታድሏል” የሚባለው ሳንሱር “በተነሳበት” ጊዜ በመወለዱ ብቻ ነው ብዬ አምናለሁ። ልክ በ1966-67 ዓ.ም እንደነበረው ማንም ያመነበትን የፈጠራ ጽሑፍ ይጽፍ ያሳትም ነበረ። “ነበረ” ማለቴ በቅርቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኋላ የነበረው እንዳልነበረ ሲሆን በማየቴ ነው።

ከአዋጁ በኋላ አንዳንድ ኢሕአዴግን የሚተቹ መጻሕፍት በሻጮች እጅ እንዳይገኙ እየተደረገ ነው። በተወሰኑ መጻሕፍት ላይ ማዕቀቡ አይሏል። ይህን ዓይነት ቁጥጥር የዘውድም የደርግም መንግሥት አድርጎታል።ታሪክ ራሱን ደግሟል። “እንዳይደገም” የተባለው በኢሕአዴግ ዘመን ተደግሞ አይተነዋል። መንግሥትን የሚተቹ ከአዋጁ በፊትም ቢሆን የታተሙትን “ሸጣችኋል”፣ “አከፋፍላችኋል” ተብለው አንዳንድ መጻሕፍት አከፋፋዮች ለቀናት ታስረው ተፈትተዋል። በአዟሪዎችም ላይ ከፍተኛ መዋከብ ደርሷል። እየደረሰም ነው። ማተሚያ ቤቶች ከማተማችን በፊት እንመርምረው፣ እንመዝነው፣ ‹ሳንሱር እናድርገው› ማለት ጀምረዋል። ስጋት በሁለንተናቸው ላይ አርብቧል። ሳንሱር መልኩን ቀይሮ ደራስያኑን እያስደነበረ ነው።

.

ማጠቃለያ

.

በዚህ ዘመን ያለ አንድ ኢትዮጵያዊ ደራሲ በአብዛኛው ራሱ ጽፎ፣ ራሱ አርሞ፣ ራሱ አስተይቦ፣ ራሱ ፊደል ለቅሞ፣ ራሱ ማተሚያ ቤት ፈልጎ፣ ራሱ አሰራጭቶ፣ ራሱ ማስተዋወቂያ ሠርቶ፣ ራሱ አስመርቆ፣ ራሱ ለኅትመት ያወጣውን ገንዘብ ሰብስቦ፣ … ይኖራል። ብዙ ነው ድካሙ።

ይህ ሁሉ የአሳታሚ እንጂ የእሱ ሥራ መሆን አልነበረበረትም፡፡ የአሳታሚ መኖር ደራሲውን ያበረታዋል፤ ያነቃዋል፤ ያነቃቃዋል። አስታሚ ካለ አርታዒ አለ፤ አሰራጭ አለ፤ ሥራውን ለማስተዋወቅ ተግቶ የሚሠራ አካል አለ፡፡ አርታዒው ብዙውን ጊዜ የደራሲውን ረቂቅ ሥራ ዓይቶ፣ ምልአቱንና ጉድለቱን ለይቶ፣ ከደራሲው ጋር ተመካክሮ ረቂቁን ለኅትመት ዝግጁ ያደርግለታል። ይህ ፈር የያዘው መጽሐፍ ደግሞ በአሳታሚው ገንዘብ “ጥበቃ” ያደርግለታል። አሳትሞ ስለማሰራጨት ከመጨነቅ ይልቅ ስለአዲስ ሥራው እንዲያስብ መንገድ ይጠርግለታል፡፡

ከ50 ዓመት በፊት ዮሐንስ አድማሱ የልብወለድ ሥነጽሑፍ ጉዞ በሚል ርዕስ አንድ መጣጥፍ አስነብበውን ነበር። የመጣጥፉ ዳሰሳ ከ1933 እስከ 1960 ዓ.ም ድረስ ያለውን የሃያ ሰባቱን ዓመት ጉዞ የሚሸፍን ነው። የአጋጣሚ ነገር ሆኖ ይህም ዳሰሳ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የኢትዮጵያ ደራሲ የገጠመውን ችግር ለማሳየት ይሞክራል። ሆኖም፣ ዮሐንስ መጣጥፋቸውን ሲቋጩ የተመኙት ምኞት አሁንም ተፈጻሚ አልሆነም። ከዛሬ 50 ዓመት በኋላስ ደራሲዎቻችንን ምን ይፈትናቸው ይሆን? መጪው ትውልድ ችግራችንን እንዳይቸገረው ምኞቴ ነው።

ዮሐንስ መጣጥፋቸውን ሲቋጩት የተጠቀሙበትን ገለጻ ተጠቅሜ ጽሑፌን ልደምድም፤

“… የተጋድሎው ጎዳና ረጅም ሆኖ ጉድጓድ የበዛበት ቅርቅፍት ነው፣ ተስፋ መቁረጥ ግን አያስፈልግም። እንደጥንታውያኑ ለሃገራቸው ነፃነት ህይወታቸውን በየጎራው፣ በየሜዳው፣ በየአረሁ እንደሰውት ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን በአጭር ታጥቆ፣ የሥነጽሑፍ ዘገር ነቅንቆ፣ የሥነጽሑፍ ጋሻ መክቶ ለሥነጽሑፍ መጋደል የያንዳንዱ ደራሲ ፈንታ ነው። ኢትዮጵያውያን ደራስያን በዓለም የሥነ ጽሑፍ ሸንጎ ላይ ተሰልፈው የሚወዳደሩበትን ዕለት በናፍቆት እጠባበቃለሁ። ››14

.

የግርጌ ማስታወሻ

  1. ለምሳሌ፣ ‹አሻራ› በሚል ርዕስ ፈቃደ አዘዘ (ዶ/ር)፣ ዳዊት ፀጋዬ እና ተስፋዬ ብርሃኑ የግጥም መጽሐፍ አሳትመዋል።
  2. አቶ አያልነህ ሙላት ይህን ጥናት ያቀረቡት፣ ግንቦት 1985 ዓ.ም ተዘጋጅቶ በነበረው ለነፃ መጻሕፍት ገበያ ኮንፈረንስ ነበር።
  3. ይህ የአቶ መንግስቱ ለማ መጽሐፍ፣ በ1955 ዓ.ም አቶ ወርቁ ብሩ በተባሉ በጎ አድራጊ አማካይነት በማተሚያ ቤት ሊታተም ችሏል።
  4. ለምሳሌ ያህል ሁለት ሰዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አቶ መንግስቱ ለማ፣ ‹የተውኔት ድርሰት የአጻጻፉ ብልሃት› የተሰኘ መጽሐፋቸውንና ወይዘሮ አየለች በቀለ ‹አፍለኛው ውዴታ› በሚል ርዕስ በዕቁቡ ብር ለማሳተም በቅተዋል፡፡
  5. አቶ በዓሉ ግርማ ‹የቀይ ኮከብ ጥሪ›ን፣ ‹ደራሲው›ን፣ ‹ሀዲስ›ን፣ በኢትዮጵያ መጻሕፍት ድርጅት በኩል ሲያሳትሙ፤ ‹ኦሮማይ›ን በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት በኩል አስነብበውናል። የአቶ ብርሃኑ ዘርይሁን ፣‹ማዕበል› ‹የአብዮት መባቻ›፣ ‹የአብዮት ዋዜማ› እና ‹የአብዮት ማግስት› በኢትዮጵያ መጻሕፍት ድርጅት በኩል ሲታተሙ፣ ‹የታንጉት ምስጢር›ን በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት በኩል አስነብበውናል። አቶ ሀዲስ አለማየሁ ‹ወንጀለኛው ዳኛ›ን እና ‹የልምዣት›ን በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት አስነብበውናል።
  6. ሲሳይ ንጉሡ፣ ገበየሁ አየለ፣ ኃይለመለኮት መዋዕል፣ አበራ ለማ፣ የሺጥላ ኮከብ፣ አዳም ረታ፣ የዝና ወርቁ፣ ጀማል ሱለይማን፣ አንዳርጌ መስፍን እና ሌሎችም በዚህ ዘመን ብቅ ያሉ ደራስያን ናቸው።
  7. የሰርቅ ዳንኤል ‹ቆንጆዎቹ›ን፣ የዮሐንስ አድማሱ ‹እስኪ ተጠየቁ›ን፣ የደረጀ በቀለ ‹ህያው ፍቅር›ን፣ የስብሀት ገብረእግዚአብሔር ‹ትኩሣት›ን፣ የመስፍን ዓለማየሁ ‹ሽማግሌውና ባህሩ›ን፣ የሲሣይ ንጉሡ ‹የቅናት ዛር›ን፣ የሰዓዳ መሐመድ ‹እሾሃማ ወርቅ›ን መጥቀስ ይቻላል።
  8. ለምሳሌ እኔ ከጻፍኳቸው መጻሕፍት ‹ማዕቀብ› የሚለውንና ‹እምቢታ›ን ለማከፋፈል ፍቃደኛ አለመሆኑን ድርጅቱ ገልጾልኛል። የስንዱ አበበ እና አበረ አዳሙም መጻሕፍት ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሟቸዋል።
  9. ማኅበሩ የማሳተሙን ሥራ ብቻ ይሠራ ስለነበር ደራስያኑ መጽሐፎቻቸውን ለማስተዋወቅ፣ለማከፋፈልና ለማሰራጨት በመቸገራቸው፤ ብዙዎቹ ለኅትመት የወጣውን ወጪ ለማተሚያ ቤቱ ለመመለስ ተቸግረዋል። በዚህም የተነሣ በዚህ መልኩ የማሳተሙ ሥራ ላልተወሰነ የጊዜ ገደብ ተቋርጧል።
  10. ቃለ-መጠይቁ በ‹የኛ ፕሬስ ›ጋዜጣ ላይ “መጽሐፌ በድብቅ ታትሞ በመሰራጨቱ በጣም ከባድ ስብራት ነው የደረሰብኝ፤ ስድስትና ሰባት ዓመት የለፋሁበት መጽሐፍ ነው” በሚል ርእስ ገፅ 11 ላይ የተስተናገደ ነው-ነሐሴ 21 ቀን 2006 ዓ.ም፡፡
  11. አቶ አማረ ማሞ ይህን ጥናት ያቀረቡት የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር፣ “የምዕት ዓመቱ የኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ እድገትና የመጪው ክፍለ ዘመን አቅጣጫ” በሚል ርዕስ፣ ከግንቦት 24-28 ቀን 1999 ዓ.ም ባዘጋጀው ዓውደ ጥናት ላይ ነው።
  12. በግርግሩ የሰው ሕይወት መጥፋቱን እንዳለጌታ ከበደ ማዕቀብ በተሰኘው መጽሐፉ አብራርቶ ጽፎታል።
  13. በ2001 ዓ.ም፡፡
  14. መነን መጽሔት፣1960 ዓ.ም የታተመ፡፡

.

እንዳለጌታ ከበደ

.

* እንዳለጌታ ከበደ፣ ከአጫጭር ትረካዎችና ረጃጅም ልቦለዶች በተጨማሪ በጥናትና ምርምር የተደገፉ ኢልቦለድ ድርሰቶችን በማስነበብ የሚታወቅ ደራሲ ነው፡፡ እስካሁን አስራ አንድ መጻሕፍት ለንባብ ያበቃ ሲሆን፣ከነዚህ መካከል ከጥቁር ሰማይ ስር፣ የመኝታ ቤት ምስጢሮች፣ ዛጎል፣ ደርሶ መልስ፣እምቢታ፣ ማዕቀብ ፤ በአሉ ግርማ ሕይወቱና ሥራዎቹ የተሰኙ ስራዎቹ በተደጋጋሚ ከመታተማቸው በተጨማሪ ከመጀመርያ ዲግሪ ተማሪዎች እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ደረጃ ባሉ የሥነጽሑፍና ፎክሎር ተመራማሪዎች ዘንድ ትኩረት ስበዋል፡፡ እንዳለጌታ፣ በኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ከ1997-2005 በዋና ጸሐፊነት ያገለገለ፣ በ2005 ዓ.ም የአመቱ በጎ ሰው በሚል ዘርፍ ተሸላሚ የሆነ፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ውስጥ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል መስራችና ዳይሬክተር፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፎክሎር ትምህርት የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.