መሪራስ አማን በላይ (፲፱፻፵፪-፳፻፱)

መሪራስ አማን በላይ

[፲፱፻፵፪-፳፻፱]

በፈንታሁን ጥሩነህ

.

አቶ አማን በላይን የማውቀው ከ20 ዓመት ገደማ ጀምሮ ነው። እስከዚያ ድረስ የጻፋቸውን መጻሕፍትን ሆነ እርሱን እራሱን በወሬ እንኳን አላውቅም ነበር።

ዶ/ር ወሰን እንቁባህሪ ረዘም ላለ ጊዜ “መጽሐፈ ሱባዔ” የተሰኘ መጽሐፍ አውቅ እንደሆነ ወይም በምሰራበት በኮንግሬስ መጻሕፍት ቤት (Library of Congress) ይገኝ እንደሆነ በደወለልኝ ቁጥር አዘውትሮ ይጠይቀኝ ነበር። እኔም በብራና መጻሕፍት ክምችትም ሆነ በታተሙ መጻሕፍት ዘንድ እንዲህ ዓይነት ርእስ ያለው መጽሐፍ ከስብስቡ እንደሌለ በተደጋጋሚ ስገልጽለት ቆየን።

ከዕለታት አንድ ቀን በኮንግሬስ ቤተ መጻሕፍት ሕንፃ ውስጥ ባለ አንድ ምግብ ቤት ምሳ ለመብላት በቀጠሮ ተገናኝተን አንድ የግልባጭ ግልባጭ የሆነ ጽሑፍ በማኅደር የታቀፈ ሰጠኝና ቤት ስገባ ብቻ እንዳነበው ነገረኝ። እንዳለውም ከሥራ መልስ ራት በልቸ ማኅደሩን ከፍቸ ማንበብ ስጀምር “የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ” በሚል ርዕስ ያላሰብኩት ከዚህ ቀደምም ሰምቸው የማላውቅ የጥንት የኢትዮጵያ ታሪክ ማንበብ ጀመርኩ።

ሥጋየ፣ አጥንቴ፣ ደሜ፣ ነፍሴ የሚመኘው ወይም የምናፍቀው የነበረ ታሪክ በዚያ ብጥቅጥቁ በወጣ መዝገብ ውስጥ ነበረ። በወረቀቱ ዳርና ዳር ያሉት ፊደሎች ከኩረጃ ብዛት የሉም፤ የሌሉትን በመላ እያሟላሁ ሳነብ መሽቶ ነጋ። እንዲህ የሳበኝና የማረከኝ መጽሐፍ አጋጥሞኝ አያውቅም – ለረጅም ጊዜ። ሁለመናየ ሳቀ፤ ተደሰትኩ። “ይህ ነው የጠፋብን ታሪካችን!” እያልኩ መገረም ጀመርኩ።

ስለኢትዮጵያውያን ሁልጊዜ የሚረብሸኝ አንድ ምናባዊ ሥዕል አብሮኝ ይኖር ነበር። እውነተኛ ታሪኩን ባለማወቁ እውነተኛ ማንነቱ ጠፍቶበት በየሄደበት ታሪኩን ለማግኘት የሚናውዝ፤ በአጥንቱ፣ በነፍሱ፣ በጊንሱ፣ የማንነቱ ገናናነት እየታወቀው ዓለም ሳያውቀው በመቅረቱ ሲያሳንሰው ሲደቁሰው የሚኖር፤ እንደግማሽ እብድ እንደ አውቆ-አበድ የሚያደርገውና ስለታሪኩ ገናናነት ሊገልጽ ሲሞክር በውስጡ ያለውን አውጥቶ መናገር መግለጽ ስለሚሳነው ዓይኖቹን በማፍጠጥ በቁጣ መንፈስ ከሰው ጋር የሚጋጭ፣ የሚደባደብ፣ እርስ በርሱም አንገት ላንገት የሚተናነቅ፤ የኢትዮጵያ ስም ሲነሳ በማያውቀው ሥነ ልቦና ውስጥ ተዘፍቆ እንደዛር የሚያንቀጠቅጠው፤ የቁጣ ማዕበል ልገንፍልብህ፣ ልፈንዳብህ እያለ የሚያቅበጠብጠው፤ የገዛ ወንድሙን ኢትዮጵያዊውን አገሬን እንደኔ አታውቃትም፣ አትወዳትም ብሎ የሚደነፋ •••

ግን ደግሞ በተቀበረው ማንነቱ በየሄደበት፣ በየተሰደደበት ስለእውነት የሚሞት፤ በትሕትናው ራሱን ዝቅ በማድረግ በአገልግሎቱ የሚያስከብር ሥራ በመሥራት፣ በሐቀኝነቱ የተከበረ፤ ፍቅረ-ንዋይ የማይደልለው፣  አድርባይነት የማይጠጋው •••

ጋሽ ጸጋዬ ገብረመድኅን ነፍሱን ይማረውና የዋሽንግተንን ከተማ በጎበኘበት ባንድ ወቅት ለእኔና ለጥቂት ሰዎች እንደገለጸልን፣

“በምዕራብ ከተሞች ሁለት እጁን በሁለት ኪሱ ከትቶ፣ ደረቱን ነፍቶ፣ በአስፋልቱ ላይ በሁለት እግሩ በእርግጠኝነት የሚራመድ፤ አሮጊት ነጮች በመስኮት ሰርቀው እያዩ ‘ይህ የማነው ጥቁር በኩራት በቀያችን የሚንጎራደደው’ ብለው የሚደነቁበት ያ የኛው አሎሎ ራስ ኢትዮጵያዊ ነው!”።

አማን በላይ ማለትም ከነርሱ አንዱ ነበር።

ግን አማን በላይ ደግሞ ከነዚህ ዓይነት ኢትዮጵያውያን ለየት የሚያደርገው ባህሪ አለው። የትምህርት ጥማት ስለነበረው በወጣትነቱ ከቤተሰቡ ተለይቶ ለረጅም ዓመታት ከደብር ደብር እየተዘዋወረ የቤተክርስቲያንን ትምህርት ልቅም አድርጎ ተምሯል። ቤተሰቦቹ ለዘመናት ስለጠፋባቸው ጫካ ለጫካ ሲሄድ አውሬ በልቶት ይሆናል ብለው እርግጠኛ በመሆን እርማቸውን በለቅሶ ካወጡ ከሰላሳ ዓመት በኋላ በሕይወት እንዳለ እንዲያውቁ አድርጓል።

ይህን ያህል ዘመን ለዕውቀት ከጠቅላይ ግዛት ወደጠቅላይ ግዛት በተዘዋወረበት ረጅም ዘመን ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ጋርም ተገናኝቷል። በቤተክርስቲያኗ የተለያዩ ቦታዎች ያሉትንም ብርቅ መጻሕፍት ለማወቅ ዕድል አግኝቷል። ከነዚህም ብርቅ መጻሕፍት አንዱ “መጽሐፈ ሱባዔ” የተሰኘው ይገኝበታል። ይህን መጽሐፍ በዓይኔ ባላየውም ከጥንታዊ መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ ተጠቅሶ ይገኛል።

በ1997 ዓ.ም ገደማ ከአማን በላይ መተዋወቅ እንደጀመርን በየጊዜው እየተደዋወልን ለረጅም ሰዓቶች በስልክ እናወራ ነበር። ለሀገሩ ሰው ያለውን ሁሉ ዕውቀት የማካፈል ምኞት ስለነበረው አብዛኛውን ጊዜ የሚናገረው እርሱ ነው። እጅግ ሰፊ ትንታኔና ሐተታ ማቅረብ ይችል ነበር።

በ1998 ዓ.ም ታትሞ የወጣውን “መጽሐፈ ሱባዔ ዘበአማን ካልዕ” እና የሱባ ቋንቋ መጽሐፍ ንድፉን ሲልክልኝ ወዲያውኑ ወደ የባለቤትነት መታወቂያ (Copyright) ክፍል ወስጀ በስሙ የባለቤትነት መታወቂያ ሰርቲፊኬት እንዲደርሰው አደረግሁ። ሰርቲፊኬቱ ሲደርሰው ደወለልኝና

“የደረሰኝ ሰርቲፊኬት ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀኝ።

“አንተ በየዋህነት የላክሃቸው የመጽሐፍ ንድፎች በቀላሉ ማንም ሰው ያንተን ስም ፍቆ የራሱን ስም ተክቶ የመጽሐፎቹ ደራሲ ነኝ ብሎ ማተምና መሸጥ ስለሚችል እኔንም ሆነ ማንንም ሰው እንዳታምን፣ በራስህ ስም የባለቤትነትህን ማረጋገጫ ሕጋዊ ሰነድ ሳትይዝ የጽሑፍህን ቅጂ ለማንም እንዳትልክ፣ እንዳታጋራ ለማስጠንቀቅ ያደረግሁት ነው” ብየ ገለጥኩለት። ከዚህም በኋላ እንደሚያከብረኝ ደጋግሞ ገልጾልኛል።

አከታትየም በጣም በረጃጅም ዓረፍተ ነገሮች የተነደፈውን ጽሑፉን በነጥብ ሥርዓት እያስተካከልኩ ለአንባቢ እንዳያሰለች ባጭር ባጭሩ እየከፋፈልኩ ሰርቸ መልሸ ላክሁለትና ደስ አለው።

“የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ” በተሰኘው የመጀመሪያ መጽሐፉ ላይ የደራሲው ስም “ኤ. ኤም. በላይ” ተብሎ ለምን እንደቀረበ ላነሳሁለት ጥያቄ ሲመልስ በጥንቱ የነገድ ታሪክ ላይ መጽሐፍ የሚጽፍ ሰው ዕድሜው አጭር ነው ተብሎ ስለተነገረው እንደሆነና ማንነቱ እንዳይታወቅ ምኅፃረ ቃል እንደተጠቀመ ገለጸልኝ። ማንነቱ እንዳይታወቅ ከፈራ አንድ ማኅበር አቋቁመን በዚያ ማኅበር ስም የሚጽፋቸውን መጻሕፍት ማሳተም እንደሚቻል ያቀረብኩለትን ሃሳብ ለጊዜው የተቀበለ መስሎ ችላ በማለት በስሙ መጠቀሙን ቀጠለ።

እውቅናችን እየጠበቀ ሲመጣም ባንድ ወቅት እርሱም እኔም ወደ ጎንደር የምንሄድበት አጋጣሚ ተፈጠረና እዚያው እንድንገናኝ ተቀጣጥረን ዓይን ለዓይን ለመገናኘት ችለናል። ቤተሰቦቹን አስተዋወቀኝ፤ እኔም ዘመዶቸን አስተዋወቅሁት። አንዱ ወንድሙ ጋር በተዋወቅንበት ወቅት የሀገር መድኃኒት አዋቂ ስለነበር የማከም ፈቃድ አውጥቶ እስከሐረር እየተጓዘ ያክም እንደነበር ነግሮኛል። የሀገር መድኃኒት ዝርዝር የያዘ የብራና መጽሐፍም አሳይቶኝ ነበር። ግን ብዙ ሳይቆይ ሳንባው ውሃ በመቋጠሩ በህክምና በመረዳት ላይ እንደነበረ አርፏል።

ከአማን በላይ ጋር ግንኙነታችን በስልክ በቀጠለበት ጊዜ እጅግ ከመቀራረባችን የተነሳ “ወንድሜ” ነበር የሚለኝ። ባንድ አጋጣሚ ጡረታ ስወጣ ጎንደር ከተማ አንድ ቤተ መጻሕፍት ከፍቸ አገልግሎት መስጠት እንደምመኝ ስላለኝ ሃሳብ ነግሬው “አንተ ይህን ያልከውን መጻሕፍት ቤት የምታቋቁም ከሆነ የምሰራበትን ዋናውን የብራና መጽሐፍ ላንተ ነው የምሰጥህ” ብሎኝ ነበር። በየጊዜው ስንደዋወልም ስለመጻሕፍት ቤቱ ጉዳይ ሳይጠይቅ አያልፍም ነበር።

አሁን ግን ይህ ሁሉ ነገር በተንጠልጠል ቀረ።

አማንም ድንገት ተለየን። የምወዳትን እህቴን አዲስ አበባ ቀብሬ እንደተመለስኩ የወዳጀን የአማን በላይን ሞት ስሰማ ታናሽ እህቴ ሞታብኝ ያለቀስኩትን ያክል ምርር ብየ አለቀስኩ።

ይህን መራር ዜና የሰማሁት ለእኔ ሊሰጠኝ አስቦት የነበረውን መጽሐፍ ብዙ ኢትዮጵያውያን ምሁራን እንዳሳሰቡት ለኮንግሬስ ቤተመጻሕፍት በስጦታ እንዲሰጥና የመጽሐፉን መኖር የተጠራጠሩ ሁሉ እንዲያዩትና እንዲገለገሉበት ለመምከር አስቤ ከሐዘኔ የማገግምበትን ጊዜ በመጠባበቅ ላይ እንዳለሁ ነበር።

እግዚአብሔር አምላክ የወንድሜን የአማንን ነፍስ ከርሱ ጎን ቦታ እንዲሰጣት ምኞቴ ነው። ቤተሰቦቹንና ወዳጆቹን በመላ እግዚአብሔር መጽናናትን ይስጣቸው።

ፈንታሁን ጥሩነህ

Washington, D.C.

.

(የሰምና ወርቅ መጽሔት አዘጋጆችም በመሪራስ አማን በላይ ከዚህ ዓለም ማለፍ ምክንያት ያዘኑትን ቤተሰቦቹን እግዚአብሔር ጽናቱን እንዲለግሳቸው መልካም ምኞታችንን እንገልጻለን።)


የመሪራስ አማን በላይ መጻሕፍት ዝርዝር

.

“የልቤ ወዳጅ የሰው ዘር ልጅ”

“ሕይወት እንደገና በሦስት ዓለሞች”

“መርሐ ጽድቅ ወአሚን ወመርሐ ግብር”

“መክስተ ምስጢር”

“መጽሐፈ ሠረገላ ታቦር”

“መጽሐፈ ሰይፈ ሃይማኖት ተዋሕዶ”

“መጽሐፈ ሱባኤ ዘበአማን ካልእ”

“መጽሐፈ ብሩክ (ብሩክ ዣንሽዋ)”

“መጽሐፈ አብርሂት”

“መጽሐፈ አድኅኖት”

“መጽሐፈ ኤልያስ ነቢየ እግዚአብሔር”

“መጽሐፈ ክቡር”

“መጽሐፈ ዕንቆ አእባን”

“መጽሐፈ ፈውስ”

“ምክር ከእኔ ስማ አንተ ወገኔ”

“ምዕራፈ ሕያዋን ቃለ ሕይወት ዘወንጌላውያን”

“የሱባ ቋንቋ መዝገበ-ቃላት”

“ብርሃነ ሕይወት ዘበአማን”

“በአንድ ሰውነት የሦስት አካላት ምስጢር”

“አፍሪ ካሁን”

“የእውነትን ሕይወት ውደዱ”

“ጥበብ ከሕይወት ትምህርት ከልጅነት”

“የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ”

“ጸሎተ አሚን ዘበአማን”

.

  

 

14 thoughts on “መሪራስ አማን በላይ (፲፱፻፵፪-፳፻፱)

 1. Where can I find his book ” የጥንትዋ ኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ” ? Anyone can give me a hint? I am not living in Ethiopia.

  Like

 2. Pingback: ስለ መሪ ራስ አማን በላይ | kassahunalemu

 3. Pingback: መሪራስ አማን በላይ (፲፱፻፵፪-፳፻፱) | Amsalutamirat

 4. በኑብያ ሃገር ከ ቤ/ክ ፍርስራሽ ስር፡አገኘሁት ያሉትን፡የብራና ጽሁፍ እስታሁን አየሁ ያለ ሰው አልተገኘም።
  ፕር ፍ.ቶሎሳም ነገሩኝ እያለ አንዳንድ ተረቶችን ለመጻፍ በቅቷል።
  መቸም እንዲህ አይነት ብርቅ ንብረት ያለው ሰው ኑዛዜ ሳይጽፍ አይሞትምና መቸስ በጅህ ይገባሉ ካሎነም ለማን እንደተላለፉ ተከታትለህ ታሰማናለህ። አንድ አይነት የምስጢር “ወንድማማቾች” ማህበር ያለ ይመስል ሰነዶቹ በምስጢር ተዛወሩ ወይ የገቡበት አልታወቀም ብትሉን ግን አረጉ ያክልን ሹፈት እቆጥረዋለሁ።

  Like

 5. ሰላም! I wanted to know where i can get ምዕራፈ ሕያዋን ቃለ ሕይወት ዘወንጌላውያን” book? i searched online but it was not available.
  I will be expecting your response!
  sincerely

  Like

  • ምንም እንኳ ቢዘገይ መልስ መስጠት ይገባልና ስለመዘግየታችን ይቅርታ እየጠየቅን ይህን የጠየቁትን መጽሐፍ ማግኘት ባለመቻላችን አሁንም በመፈለግ ላይ እንደሆንን ልናሳውቅ እንወዳለን። እንዳወቅን ወዲያውኑ እንገልጥልዎታለን። ስለትግስትዎ እናመሰግናለን።

   Like

 6. ኮንግረስ መጽሀፍት ቤት የት ይገኛል፣ በሰዉ ሀገር የምንኖር እንዴት ማግኘት እንችላለን?

  Like

   • ሰላም፤
    ኮንግሬስ ቤተመጻሕፍት በዋሺንግተን ከተማ ነው የሚገኘው። ያለሺበትን ስለማላውቅ የተሳሳተ መልስ ሰጥቸሽ ከሆነ ይቅርታ። አገር ውስጥ ካለሽ በየመጻሕፍት መደብር ብታጠያይቂ ለሽያጭ የቀረቡ አንዳንድ አይጠፋም ብየ አስባለሁ።

    Like

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.