ሰ ም ና : ወ ር ቅ: መጽሔት
ነፃና : ሁለ-ገብ : የጥናትና : የምርምር : መጽሔት
መሠረተ: ሐሳብ፤
ሰምና ወርቅ መጽሔትን መልሶ ማቋቋም ለምን አስፈለገ?
ሰምና ወርቅ መጽሔት በአማርኛ ቋንቋ እየታተመ የሚወጣ የምርምርና የጥናት መጽሔት ሆኖ በ1979 ዓ.ም. መታተም ጀመረ። በዚያን ወቅት ከኢትዮጵያ እየፈለሰ የሚወጣው ኢትዮጵያዊ እጅግ ብዙ ነበር። ነገር ግን እርስ በራስ ለመገናኘት፥ ሐሳብ ለሐሳብ ለመገበያየት የሚያስችል መድረክ ባለመኖሩ የስደቱ ኑሮ ለብዙኅኑ አሰልችና ተደጋጋሚ የሆነ ፈሊጥ ወደ መሆን ደርሶ ነበር። በዚህ መካከል አንዳንድ ምሁራን የአማርኛ ፊደልን በኮምፒውተር የመጠቀም ችሎታን ስለፈጠሩና እያሳደጉ በመምጣታቸው ለህብረተሰቡ አንድ አገናኝ የሆነ መጽሔት የማቋቋሙ አስፈላጊነት እጅግ ጎልቶ ይታይ ነበር። በፖለቲካ ምክንያት የወጣው ዜጋ የፖለቲካ ልምዱን በማካፈል ከሌሎችም ልምዳቸውን ማወቅ እና መማማር እንዲችል፤ በኢኮኖሚ ምክንያት ከሃገር የወጣው ዜጋም የውጭ ሃገርንም ሆነ ጥለን የመጣነውን ኢኮኖሚ አገናዝቦ የተሻለውን እንዲመርጥ ወይም አዲስ የኤኮኖሚ ብልሃት እንዲፈጥር ወይም አዲስ የኢኮኖሚ ዘዴ እንዲዘይድ ለማበረታታት፤ ከጠንካራ ባሕል የወጣው ኢትዮጵያዊ በስደት ዓለም በሚኖርበት ጊዜ አዲሱን ባህል በቅጡ እንዲረዳ፥ የተወለደበትንም ጥንታዊ ባሕል እንዳይረሳ ማስታወሻ ለመፍጠር፤ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ረገድ በስደት ኑሮ የቀሰምነውን ክህሎት ወደ አገራችን ለማስረጽ፤ እንዲሁም አበው ፈጥረውት የነበረውን መሠረታዊ ክህሎት አጥንተን፥ በምርምር ለማሳደግ እንድንችል አዲሱ ትውልድም ከነባሩ፥ ነባሩ ከአዲሱ እንዲማማሩ፤ በነዚህና በሌሎች ጠቃሚ ምክንያቶች ሰምና ወርቅ መጽሔትን አቋቁመን ለአራት ዓመታት ያህል ሰራን። አብረን በመሥራት ረገድም ያፈራነው ልምድም በቀላል የሚገመት አልነበረም። አዲስ ትውልድ እየጨመረ፥ የስደቱ ኑሮ ሲቀጥል መጽሔቱ በቆየበት አጭር ጊዜ ብቻ ሳይወሰን ከዚያም በኋላ መጽሔቱን የማንበብ እድል ላገኘ ሁሉ ጠቃሚነቱ ተወርቶለታል። ስለዚህም ብዙ ተቆርቋሪዎች በተለያየ ጊዜ መጽሔቱ እንደገና እንዲያንሠራራ ጠይቀው ነበር። ጊዜና ሁኔታ ባለመመቻቸቱ ምክንያት እነሆ እስከዛሬ ሳይቻል ቆየ። ነገር ግን አሁን ይህን ሐሳብ ዳር ለማድረስ ተነሥተናል። መጀመሪያ መጽሔቱ ሲቋቋም መጽሔቱ የምርምር ጥናቶችን እንዲያስተናግድ አዳዲስ ሐሳቦችም ተቀብሎ እንዲያትም ነበር። አሁንም ይህንኑ ሐሳብ በአዲስ መንፈስ፥ በላቀ ሥራና አስተሳሰብ አዳዲስ ዓላማዎችን ጨምረን ግብ ለማድረስ ቆርጠን ተነሥተናል።
ስለ: አዲሱ: ሰምና: ወርቅ: መጽሔት፤
አዲሱ ሰምና ወርቅ መጽሔት በቅድሚያ በድረ-ገጻችን እየወጣ ለአንባቢያን ይቀርባል። ከአንባቢዎችና ከደጋፊዎቻችን የምናገኘው ድጋፍ የመጽሔቱን እድሜና አቅርቦት ይወስነዋል።
አዲሱ መጽሔታችን ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን አላማዎችና ወደፊት ከደንበኞቻችን በምናገኘው ምክርና አስተያየት የሚያከናውን ይሆናል::
ከዚህ ቀጥሎ ሰምና ወርቅ መጽሔት ቀድሞ ይዟቸው ከተነሳው ዓላማዎች በተጨማሪ ለምን ማተም እንዳስፈለገ ያለንን ራዕይ እንመልከት፤
*በውጭ አገር የሚኖሩ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና በውጭ የተወለዱ ኢትዮጵያውያን እየተበራከቱ ከመሄዳቸው ሌላ የተበታተኑ የዕውቀት ዓይነቶች በየሙያቸው እያካበቱ ባለበት ሁኔታ መጽሔቱ እንደ ድልድይ በመሆን ዕውቀቱ ለአገር ግንባታ ጥቅም እንዲውል ይረዳል።
*በውጭ ሃገራት ከፍተኛ ተቋማት ውስጥ በማስተማርና በመሥራት ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን በየሙያቸው ያላቸውን የተለያየ ግንዛቤ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ መሰል ምሁራንና ሊቃውንት ባለሙያወች ጋር ትሥሥር እንዲኖራቸው መድረክ በመሆን ያገለግላል።
*በፖለቲካ ተሣትፎ ከሃገር የወጣው ወጣት ትውልድ በአሁኑ ጊዜ በእድሜ ገፍቶ የሰከነ የብዙ ልምድ፥ ጥበብና እውቀት ባለቤት በሆነ ሁኔታ ላይ ስለሚገኝ የግል ተሞክሮው ለሃገራዊ ጥቅም እንዲውል ለማስቻል፤
*በሃገር ውስጥ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የከፍተኛ ትምህርት መስጫ ተቋሞች በየቦታው በመከፈታቸው ጥልቀት ያለው የምርምር ጥናት ለማድረግ ሁኔታው ስለሚጠይቅና ስለሚፈቅድ ምሁራን የመጠቀ ምርምር እንዲያደርጉ ለመርዳት፤
*የኢትዮጵያ ሴቶች ንቃትና ተሣትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ ይበልጥ በተለያየ የምርምርና ተግባራዊ ሥራ ራሳቸውን ለማዋል፥ በወላዊ የሃገር ግንባታ ከወንዶች ጋር ለመሰለፍ የሚያስችላቸውን አቅም ለመጨመር፤ የሴቶች የመከራ ስንክሳር ቀርቶ በእናትነት የሰውን ልጅ ወደዚህ ዓለም ከማምጣት ጀምሮ በቤት ሥራ እንዲሁም በሙያ ተግባር የሚሰለፉ ፥ ቁልፍ የኅብረተሰብ አካል መሆናቸው እንዲያውቁ፥ እንዲያሳውቁ ለመርዳት፤
*የገበሬውና ኢንዱስትሪ ሠራተኛው የዕውቀት አቅም እድገቱ እንዲጨምር፥ ከተቀጣሪነት ወደሃብት ባለቤትነት የሚሸጋገርበትንና የሚያድግበትን ሁኔታ ለማመቻቸት፤
*ይሁዲው፥ ክርስቲያኑ፥ ሙስሊሙ ኢትዮጵያዊ በጋራ የሃገር ግንባታ ላይ በከፍተኛ ደረጃና ለዓለም ሕዝብ አርአያነት ባለው ሁኔታ ተጣምረው በፍቅር የሚሠሩበትን መንገድ ለማዳበር፤
*ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ በተለይ ስለ ጥንታዊት ኢትዮጵያ የውጭ ሃገራት ምሁራን እና ኢትዮጵያውያን የሚስማሙበትና የሚለያዩበት ስለሚኖር ይህን ጉዳይ መርምሮና አጥንቶ ለማጣራት፥ እስከዛሬ ተጽፎ የቆየውን ወይም በተለምዶ “የኢትዮጵያ ታሪክ” ተብሎ የታወቀውን በእውነተኛው የሕዝብ ታሪክ ለመተካትና፥ የኢትዮጵያ ሕዝብ የታሪኩ እውቀት ባለቤት እንዲሆን ለማስቻል፤
*የመንፈሳዊ ሕይወት የበላይነት፥ የምድራዊ ሕይወት ተፈላጊነት፥ የእግዚአብሔርና የፍጥረት ምስጢር ቀደም ሲል ከነበረው ግንዛቤ ከፍ ወዳለ እውቀትና ግንዛቤ እንዲሸጋገር ለመርዳትና የኢትዮጵያውያንን መንፈሳዊ ንብረት አዳምሮ ለማየት እንዲቻል፤
*በየዓለሙ ተዘርቶ ያለው ኢትዮጵያዊ ታሪክ እንዲዘገብ እንዲታወቅ፥ ለመርዳት፤
*እግዚአብሔርን ለማመስገንም ሆነ ለመዝናናት ኢትዮጵያውያን ተሰምቶ የማይጠገብ የሙዚቃ ሐብት አላቸው።ዘመናዊም ሆነ ጥንታዊ፥ ባህላዊ ዘፈኖች፥ እንጉርጉሮዎች፥ ሽለላዎች፥ ፉከራዎች፥ የየብሔረሰቡ ህዝብ ባህላዊ ጨዋታ፥ ውዝዋዜ እንዲሁም የተለያዩ መዝሙሮች የመሳሰሉት ሁሉ ተመዝግበው ለኢትዮጵያውያንም ሆነ ለዓለም እንዲታወቁ ለማስቻል፤
*በሃገር ቤት የመጻሕፍት፥ የጋዜጦችና መጽሔቶች እትመት እየበዛ በመምጣቱ ለገበያ የሚቀርቡት ጽሑፎች በዓይነትና በይዘት የጥራት ደረጃቸው እንዲጠበቅና ደረጃቸው ከፍ የሚልበትን ዘዴና ብልሃት ለመለዋወጥ፥ ለመወያየት መድረክ ለመሆን፤
ባጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ከተጋረጣቸው የእውቀት ተቀላችነት መንፈስ ወጥተው የእውቀታቸው ባለቤት እንዲሆኑ ለማስቻል፤ ይህ ሰምና ወርቅ የጥናትና የምርምር መጽሔት ይረዳል ብለን እናምናለን።
እቅዳችንና ዓላማችን መልካም ውጤት እንዲኖረው በምታደርጉልን ትብብር ሁሉ እናመሰግናለን:: በዚህ አጋጣሚ ከ25 ዓመታት በፊት መጽሔቱ ተቋቁሞ ሕትመቱ እስከቆመበት ጊዜ ድረስ (1979-1983ዓ.ም) በመጽሔቱ ሥራ በአባልነትና በተባባሪነት ያለአንዳች ክፍያ ለሃገር ፍቅር ሲሉ ጊዜና ገንዘባቸውን መስዋዕት ላደረጉ ሁሉ በደንበኞቻችን ስም የከበረ ምስጋና ይድረሳቸው።
በተለይም፦
ፕሮፌሰር አቢይ ፎርድ
ፕሮፌሰር ያዕቆብ ኃይለማርያም
አቶ ታምራት ገብረ መድህን
ፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ
ዶክተር ሐረጓ ጌጡ
ዶክተር ከፍ ያለው ገብረ ጊዮርጊስ
አቶ ሰይፉ በላይ
አቶ ሙሉጌታ ከበደ
ዶክተር ማይገነት ሺፈራው*
ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ተስፋዬ
አቶ አህመድ ኑር
ዶክተር ጌትነት በላይ
አቶ ኤንዮ ቦናኖ
ዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ
የሚመሰገኑ ናቸው